Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 11:04

“የእኛ ሰዎች በየመን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የመን-የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ገሐነም!
አሁን የያዝነው ዘመን የአለማችን ግንባር ቀደም ባለፀጋ ሀገራት ለሚባሉት አውሮፓና አሜሪካ እንኳን የተመቸ አይደለም፡፡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የአለማችን ህዝቦች የስደትና የመልካም ህይወት ህልም የነበረው ባለፀግነታቸው እክል ገጥሞታል፡፡ እንደ አሜሪካና አውሮፓ አይሁን እንጂ ሌሎች ባለፀጋ የእስያ ሀገራትም የኢኮኖሚ እክሉ ውሽንፍር በሸካራ ምላሱ ልሷቸዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊው ችግር በነዋሪዎቹ ወይም በዜጐቹ ላይ የጣለው የፈተና ቀንበር አንድ እጅ ቢሆን በስደተኞች ላይ ግን ሸክሙ በአስር እጥፍ የከበደ ነው፡፡ እናም ይህ የያዝነው ዘመን ለአለም ስደተኞች ከምንጊዜውም ይልቅ እጅግ የከፋና ከእሬት ይልቅ የመረረ ነው፡፡

የችግሩ ቀንበር የፈለገውን ያህል የከፋና የመረረ ቢሆንም ግን የስደተኞች መንገድ እንደ ወንዝ ውሀ ነው፡፡ እግሩን ያነሳለትን ሁሉ እየያዘ በየአቅጣጫው ያነጉደዋል፡፡ 
እንደ ሌሎቹ ሀገራት ሁሉ መቼም የማይታክተው ይህ የስደት ወንዝ፤ ዘርና ቀለም፣ ጾታና ሀይማኖት ሳይለይ የቀረበለትን እያጨቀ ወደ መካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር የመን የባህር ዳርቻ ይደፋል፡፡ ከባህሩ ዳርቻ ላይ ቆሞ እነኝህን መጤ ስደተኞች “እንዲያው ለመሆኑ ከወዴት አገር መጣችሁ?” ብሎ ለጠየቀ በዋናነት የሚያገኘው መልስ “ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ የሚል ነው፡፡
“እስቲ በየወገናችሁ ቁሙ” በሚል ቢጠየቁ ደግሞ የእኛዎቹ ሠዎች ቁጥራቸው እጅግ ይበረክታል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት የስደቱ ወንዝ ወደ የመን እየወሰደ ከሚዘረግፋቸው ስደተኞች በቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ሶማሊያውያን ሲሆኑ ከነሱ ለጥቀው ደግሞ ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ዛሬ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡
የእኛዎቹ ስደተኞች የሶማሊያውያንን የቀዳሚነት ቦታ ወስደውባቸዋል፡፡ ባለፉት ስድስት አመታት ብቻ ሁለት መቶ ሠላሳ ሺ የሚሆኑ የእኛ ሰዎች በስደተኝነት ወደ የመን መግባታቸውን እንደመዘገበ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
ከቀናት በፊት የወጡ የተለያዩ ሪፖርቶችና የዜና ሀተታዎች፣ በያዝነው የፈረንጆቹ 2012 ዓ.ም ብቻ ሃምሳ አንድ ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ወደ የመን መግባታቸውን መስክረዋል፡፡
ዘመኑ ለስተደኞች የተመቸ ዘመን ቢሆን ኖሮ የስደተኞቻችንን ቁጥር መብዛትና ማነስ ይህንን ያህል ነገሬ ባላልነው ነበር፡፡ አሁን ግን ዘመኑ ለስደተኞች በእጅጉ አስፈሪ ነው፡፡ በተለይ በየመን ለሚገኙ ስደተኞች ሁኔታው ከሌሎች ስደተኞች በአስርና ሀያ እጥፍ የከፋ ነው፡፡ ስደተኞችን በተመለከተ ከየመን የሚነፍሰው ዜናም የሰሚውን ልብ በድንጋጤና በሀዘን የሚያርድና ጉልበትን የሚያብረከርክ ነው፡፡ ስደተኞችን በተመለከተ ከእልቂትና ከምድር ላይ ፍዳ የተለየ ሠላማዊ ዜና ከየመን መስማት አሁን ጨርሶ አይቻልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የመን ለስደተኞች የሚሆን ሰላማዊ ነገር ጨርሶ አጥታለች፡፡ እንደ ጅረት የመን በየቀኑ በባህር ዳርቻዋ ላይ ለሚዘረገፉት ስደተኖች ያዘጋጀላቸው ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ ከዘለቀው የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና ታሪኳ ይልቅ ሞትንና ተነግሮ የማያልቅ የምድር ላይ ፍዳና መከራን ብቻ ነው፡፡ ለስደተኞች የዛሬዋን የመን በአንድ ቃል ግለፁ ቢባል “ገሀነም” ከሚለው ሌላ የተሻለ ገላጭ ቃል ፈልጐ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ስደተኞችን በተመለከተ በየእለቱ ከየመን የሚወጡት ዜናዎች የያዙት መርዶ ብቻ ነው፡፡
የሚያስረዱትም የገሀነሙ እሳት የፈጃቸውንና እንዳይሞቱም እንዳይድኑም አድርጐ እየለበለባቸው ስላለው የእኛዎቹ ስደተኞች ታሪክ ነው፡፡
“ከወረኢሉ ወሎ ተነስቼ በጂቡቲና በሶማሌላንድ አቆራርጬ በጀልባ የመን የገባሁት በ2003 ዓ.ም ነሀሴ ወር ላይ ነበር፡፡ የመን ለመግባት ያየሁትን ስቃይና የተቀበልኩትን መከራ ዘርዝሬ መናገር አልችልም፡፡
የባህሩ አሳ ሲሳይ ከመሆን በአላህ እርዳታ ተርፌ የመን ገባሁ ስል ድንበሩ ላይ ያሉት የየመን ቤዶይኖች የያዝኩትን ገንዘብና የለበስኩትን ልብስ መዝረፋቸው አልበቃ ብሏቸው ክፉኛ የደበደቡኝ፡፡ በሁዋላ በያዙት የየመን ጩቤ ከአንገቴ እስከ እምብርቴ ድረስ አርደው ሞቷል ብለው ጥለውኝ ሄዱ፡፡ የበረሀው ዝንብ ወሮኝ ደሜን እየጠጣው ሳለ ሩሄን ሳትኩ፡፡ ራሴን ሳውቅ በአንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ባለ ሠፊ ድንኳን አጐዛ ላይ ተኝቼ ነበር፡፡ ድንኳኑ ውስጥ ያስተኙኝ የመናዊ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ እየደጋገሙ ወደ ሀኪም ቤት ወስጄ አሳክምሃለሁ ይሉኝ ነበር፡፡ አንድ ሶስት ቀን በሽርጥ ቅዳጅ ያሰሩልኝን ቁስል እያጠቡ የግመል ወተት ሲያጠጡኝ ከቆዩ በኋላ፣ ወደ ሀኪም ቤት ልውሰድህ ብለው በፒክአፕ ጭነው ራቅ ወዳለ የየመን ቤዶይኖች መንደር ወሰዱኝ፡፡
አንድ ክፍል ውስጥ ካስገቡኝ በኋላ ረጅም ጠረጴዛ ላይ አስተኙኝ፡፡ ጠረጴዛው ቀለሙ የተላላጠና በደረቀ ደም የተጨማለቀ ነበር፡፡ ክፍሉ ጨርሶ ሀኪም ቤት አይመስልም ነበር፡፡ ልቤ በአፌ ውስጥ የወጣች እስኪመስለኝ ድረስ ብደነግጥና ፍርሀት ፍርሀት ቢለኝም ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡
በደረሠብኝ ከፍተኛ ድብደባና በጩቤ በታረደው ቁስሌ የተነሳ ራሴን ችዬ መንቀሳቀስ ጨርሶ አልችልም ነበር፡፡ አላህን ከሞት እንዲያተርፈኝና ከዚህ መአት እንዲያወጣኝ አጥብቄ ብማፀነውም የሰማኝ አልመሠለኝም፡፡ ያመጡኝ ሽማግሌ የመናዊ ሀኪሞች ናቸው የተባሉ ሁለት ልጅ እግር ሰዎችን አሳዩኝ፡፡ እነሱም ቁስሌን ፈተው ጠቅላላ ሁኔታዬን ካዩ በኋላ፣ በፖስታ የታሸገ ጥቅል ለሽማግሌው ሰጧቸው፡፡
ሽማግሌውም ሰዎቹን እየደጋገሙ “ሽኩረን፣ ሽኩረን!” እያሉ ካመሠገኗቸው በኋላ ከክፍሉ እየተጣደፉ ወጡ፡፡ ወዲያውም ፒካፑ መኪና ተነስቶ ሲሄድ ድምፁን ሰማሁት ይህን ጊዜ የእኔ ነገር ያለቀለት ጉዳይ እንደሆነ ገባኝ፤ ግን እንዳልኩህ ምንም ማድረግ በፍፁም አልችልም ነበር፡፡
“ከሁለቱ ሰዎች አንዱ የግራ እጄን ጥብቅ አድርጎ ከያዘኝ በሁዋላ፣ መርፌ ወጋኝ፤ ከዚያ በኋላ የሆነውን አላውቅም ሰዎቹ ጎድኔን ቀደው አንዱን ኩላሊቴን ወሰዱብኝ፤ ጥለውኝ ከሄዱት ከሃናዳህ እዚህ ሰንዓ ድረስ ማን እንዳመጣኝና እዚህ አስፋልት ጥግ እንደጣለኝ አላውቅም፡፡
የጎኔ ቁስል በደንብ ስላልተሰፋ አመርቅዟል፡፡ ከደረቴ እስከ ሆዴ ድረስ የታረድኩት ቁስልም መጠጥ ያለ ቢሆንም አልፎ አልፎ መግል እየያዘ ያሰቃየኛል፡፡
የረሃቡን ነገር ጨርሶ አታንሳ፤ በቀንም በሁለት ቀንም አንድ ጊዜ ለነፍሴ ያሉና አላህን የሚፈሩ ሲገኙ ቁራሽ ቂጣና ትርፍራፊ ሩዝ ይጥሉልኛል፡፡ እንኳን ሰርቼ ለምኜ እንኳ እንዳልበላ እንደምታየኝ መራመድ ቀርቶ በአራት እግሬ መንፏቀቅ እንኳ አልችልም፡፡ እንደ እኔማ ሀሳብ ቢሆን ተወልጄ ያደኩበትን ቀዬ ትቼ ሊያውም የአባቴን የእርሻ በሬዎች ተካልቤ በማይሆን ዋጋ ሸጬ ወደዚህ የተሠደድኩት አረብ አገር ትልቅ ሲሳይ አለ ሲሉኝ ጊዜ፣ እኔም አላህ የሚሠጠኝን የፍርቱናዬን እርዚቅ አፍሳለሁ፤ እናትና አባቴንም አሳልፌላቸው በምርቃት እደቃለሁ ብዬ ነበር፡፡ ግን ሁሉም ነገር መና ሆኖ በኖ ቀረ አንተው! የእኔ ነገር እንግዲህ ተፈጥሟል፡፡ ዋ! እናትና አባቴን እንጂ! አላህ ግን ጨከነብኝ አንተው! ጣሬን አበዛው! ከዚህ ሁሉ ስቃይ አንድ ሞት አጥቶልኝ ነው በል አቦ?”
የዚህ ታሪክ ባለቤት የሀያ ሠባት አመቱ ያሲን አሊ (እውነተኛ ስሙ ለዚህ ጽሁፍ የተቀየረ) ነው፡፡ ያሲን አሊ ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ በስደተኝነት ወደ የመን ከገቡት “የእኛ ሰዎች” መካከል አንዱ ነው፡፡
እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በያዝነው አመት ብቻ የስደቱ ጅረት የመን የባህር ዳርቻ ድረስ ወስዶ የዘረገፋቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ የእኛ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እናም ከየመን ወደ አገር ቤት በየእለቱ የሚመጡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እንደ ያሲን አሊ አይነት አንጀት አንሰፍስፍ የመከራ ታሪኮች አሉ፡፡
በየመን የሚገኙት ስደተኛ “የእኛ ሰዎች” አሳዛኝ መጨረሻ የሚፈጥረው ሰቀቀን ባለሁለት ስለት ሰይፍ ነው፡፡ ተጐጂውንም ትቶት የሄደውን ቤተሠቡንም እኩል ይቀረድዳል፡፡
ወደ የመን ከሚሠደዱት የእኛ ሠዎች ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚገባ አንድ ሰው እንኳ ማግኘት ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደ ማሾለክ ይቆጠራል፡፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሁሉም የሚገቡት በህገወጥ መንገድ ነው፡፡
እነዚህ ስደተኛ የእኛ ሠዎች ሀይማኖታቸው የተለያየ፣ የተውጣጡትም ከመላው የሀገራችን አካባቢዎች ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ወር ባወጣው ይፋ መረጃ መሠረት፤ በያዝነው የ2012 ዓ.ም ብቻ በስደተኝነት ወደ የመን ከገቡት አምሳ አንድ ሺ አራት መቶ አርባ አንድ ስደተኛ የእኛ ሰዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከኦሮሚያ (4704) ከትግራይ (1997) እና ከአማራ (1707) የተወጣጡት ናቸው፡፡
ከእነዚህ ስደተኛ የእኛ ሰዎች ውስጥ ልክ እንደ ያሲን አሊ የመንን እንደ መጨረሻ የስደት መዳረሻቸው በማድረግ የሚገቡት ቁጥራቸው በንጽጽር አነስተኛ ነው፡፡
በቁጥር የሚበዙት የመንን እንደ ጊዜያዊ መሸጋገሪያ በመጠቀም ወደ ሌሎች ሀገራት በተለይም ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሄድ የሚሞክሩት ናቸው፡፡ ተሳክቶላቸው ወደ ሳኡዲ አረቢያም ሆነ ወደ ሌሎች ሀገራት መግባት የሚችሉት ግን በአንድ እጅ ጣት ልክ እንኳ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ የተቀሩት ቀልጠው የሚቀሩት በየመን ገሀነም እሳት ውስጥ ነው፡፡
የመን የሳኡዲ አረቢያ ጐረቤት ሀገርና በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ እንደ ሌሎች ጐረቤቶቿ በነዳጅ ዘይት ሀብት የተንበሸበሸች ባለጠጋ ሀገር አድርገው የሚቆጥሯትና ከምድሪቱ ሲሳይ ለማፈስ የሚመኙ በርካታ የእኛ ሠዎች ለመሙላታቸው አሌ አይባልም፡፡ ይህ ግን የመንን በሚገባ ካለማወቅ የሚመጣ አስተሳሰብና እምነት ነው፡፡ ወቅታዊው የየመን ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ወደ ሀያ ሦስት ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያላት የመን በዓለም የሀገራት የእድገትና ብልጽግና ዝርዝር ውስጥ ምድቧ እጅግ ኋላቀርና ደሀ ከተባሉት የአለማችን ሀገራት ተርታ ውስጥ ነው፡፡
የመን ሶስት አራተኛው የሚሆነው ህዝቧ በገጠር የሚኖርባት፣ ከአርባ እስከ ሀምሳ በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ከድህነት ወለል በታች ሆኖ የእለት ኑሮውን በችጋር የሚገፋና አስራ ሠባት በመቶ የሚሆነውም በቀን ከአስራ ስምንት ብር በታች (አንድ የአሜሪካ ዶላር) ገቢ ያለው ነው፡፡
የመን በጠቅላላው ካሏት ህፃናት ልጆቿ መካከል አርባ ሶስት በመቶ የሚሆኑት በምግብ እጥረት የሚሠቃዩ ሲሆኑ ከጠቅላላው ህዝቧ መካከልም አርባ ሠባት በመቶ የሚሆኑት በመሀይምነት ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡
ስለ ጫትና ጫት ቃሚዎች ጉዳይ ማንሳት ለኢትዮጵያውያን ከቶውንም እንግዳ ነገር ሊሆንባቸው አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የፈለጉትን ያህል የጫት አይነት ቢኖራቸውና የፈለጉትን ያህል መቃም ቢችሉ የመናውያንን ሊወዳደሯቸው ከቶውንም አይችሉም፡፡
የመን ከጠቅላላው ህዝቧ ዘጠና በመቶ የሚሆነው በየቀኑ በአማካይ ከሶስት እስከ አራት ሰአት ጫት በመቃም የሚያሳልፍ ሲሆን ከየመን ሴቶች ሀምሳ በመቶ የሚሆኑት የዚህ የለየለት ጫት ቃሚ ቡድን አባላት ናቸው፡፡
ልክ እንደኛው ሀገር ጫት በየመን ኢኮኖሚ ያለው ሚናም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከየመን አመታዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ስድስት በመቶ ያህሉን በመሸፈን አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይይዛል፡፡
ከየመን ጠቅላላ የሰራተኛ ቁጥር ውስጥ አስራ ስድስት በመቶ ያህሉ የተሰማራው በጫት ምርት ነው፡፡
የየመን ጫት ቃሚዎች ከገበያቸው በአማካይ ሀምሳ በመቶ የሚያህለውን ገንዘብ ለጫት በማዋል በየቀኑ ሁለት ሺ ቶን ወይም ሀያ ሺ ኩንታል ወይም ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ግራም ጫት ይቅማሉ፡፡ እንግዲህ በእንዲህ ያለ እጅግ ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያለችው የመን፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተረጋጋ ሰላምም የላትም፡፡ ለሰላሳ አመት ሰጥ ለጥ አድርገው በገዟት በፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ እግር የተተኩት የቀድሞው ምክትላቸው አቡድራቡህ መንሱር ሀዲ አሁን ዋነኛው ትግላቸው መንግስታቸውን በስልጣን ማቆየት ብቻ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱና የስራ አጥነት ችግር ግን መላ የመናውያንን ሰቅዞ ይዞ አላላውስ ብሏቸዋል፡፡ እናም በዚህ ፋታ የማይሰጥ ችግራቸው ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሲደፉባቸው “እንኳን ከእኔ ልትበላ ያንተንም ብታበላኝ አልጠላ” ነበር ያሉት፡፡ በዚህ የተነሳም ከየመናውያን ስራ አጦች ተርፎ ስደተኞችን ድል ያለ ሲሳይ ሊያሳፍስ የሚችል የስራ እድል የላቸውም፡፡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች የተወችላቸው እንደ መርፌ ቀዳዳ የጠበበ የስራ እድል ቢኖር በጫት እርሻ ውስጥና በግንባታ ቦታዎች የቀን ስራ መስራት፣ ቆሻሻ መጥረግና መሰብሰብ፣ መኪና ማጠብና የቤት ሠራተኝነት ብቻ ነው፡፡ እናም በመቶ ሺ የሚቆጠሩት በየመን የሚገኙ የእኛ ሰዎች ያለሙትና የተመኙትን አዱኛ ማግኘት ቀርቶ ህይወታቸውን ለማቆየት ያህል የሚረዳቸውን የእለት እንጀራ ለማግኘት የሚማስኑት በጫት እርሻና በግንባታ ቦታዎች የቀን ስራ በመስራት፣ በየከተማው ቆሻሻ በመሠብሠብና በመጥረግ፣ መኪና በማጠብ፣ የግለሰብ ቤት፣ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል የመሳሠሉትን በማጽዳት ነው፡፡
አብዛኞቹ ሴቶቻችን በቤት ሠራተኝነትና እነዚህን አይነት መናኛ ስራዎች በመስራት የሚያገኙት ክፍያ አንድ የመናዊ ለተመሳሳይ ስራ ከሚከፈለው በግማሽ ያንሳል፡፡ ቢሆንም ግን የእኛ ሰዎች ሳያጉረመርሙ አንዳንዴም በደስታ ይሠሩታል፡፡
ምክንያቱም ይህንንም ስራ የሚያገኙት ጥቂት እድለኞች ብቻ ናቸው፡፡ የዚህ እድል ተቋዳሽ አዲስ መጪዎቹ ሳይሆኑ ከአመታት በፊት ወደ የመን የገቡት የእኛ ሠዎች ብቻ ናቸው፡፡
ለአዲስ መጪዎቹ ስደተኛ የእኛ ሠዎች ዋናው ትንቅንቅ በየመን ስራ ማግኘት ወይም ወደ ሌላ ሀገር መሻገር ሳይሆን በህይወት የመን የባህር ዳርቻ ላይ መድረስ ነው፡፡
ሰፊውን የባህር ዳርቻ በራቸውን በወጉ መጠበቅ ያልቻሉት የመኖች፤ በየቀኑ የሚጐርፈውን ስደተኛ ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ማድረግ አልቻሉም፡፡
ለዚህ ችግርና ድክመታቸው እንደ መፍትሄ የተጠቀሙበት ዘዴ ግን ሀገራቸውን ለመጤ ስደተኞች ገሀነም ማድረግና ስደተኞቹን እንደ አትራፊ ሸቀጥ በመቁጠር ጥቅም ማግኘት ነው፡፡
የእኛ ሰዎች መከራ የሚጀምረው ገና እግራቸው የሀገራቸውን መሬት እንደለቀቀ ነው፡፡ ከመከራም መከራ አለው ከተባለ ያዩት ስደተኞቹ የእኛ ሰዎች ናቸው፡፡
ይህን አበሳ ይህን የምድር ላይ መከራ፣ መከረኞቹ ራሳቸው ይነግራችኋል፡፡

 

Read 3585 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:14