Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 10:28

ይወልደዋል ከተባለ ይመስለዋል ማለት አይገድም

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንድ የህንዶች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
የዱር እንስሳት ተሰብስበው የወቅቱን ችግራቸውን ለመፍታት የወያያሉ አሉ፡፡
በመጀመሪያ ሰስ ተነስታ፤
“ቅጠለ - በል (Herbivore) እንስሳት እኔ ከምመገበው ዛፍ እየበሉ አስቸግረውኛልና አንድ መላ ይበጅልኝ” ስትል አመለከተች፡፡
ለመልሷም፤ ተሟጋቾቿ፤
“ዱር የበቀለ ዛፍ የማንኛችንም ሀብት ነውና የብቻዬ ብላ ልትጠይቅ አይገባም” ተባለች፡፡
ቀጥሎ ጅብ ያነሳው አቤቱታ፤
“እኔ በጭለማ ደፋ ቀና ብዬ ያገኘሁትን አህያ፣ ሌሎች ቀን መንቀሳቀስ የሚችሉ እንስሳት ይቀራመቱኛልና ማዕቀብ ይጣልልኝ” ሲል ጠየቀ፡፡
ሌሎቹ እንስሳትም፤

“አህያውኮ የሰው ነው፡፡ ሊጠይቅ የሚገባው የአህያው ባለቤት እንጂ አያ ጅቦ አይደለም” ሲሉ ተከራክረው ረቱት፡፡ 
ቀጥሎ የቀረበው የዕለቱ ትልቁ አጀንዳ የተባለው የገመሬ ዝንጀሮ ጉዳይ ነው፡፡ ገመሬ ዝግጀሮ የወቅቱ የዱር እንስሳት ኃላፊ በመሆን፤ አንበሳ በመታመሙ ምክንያት፤ እሱን አክሎ እሱን መስሎ እንዲሠራ በመላው እንስሳት የተመረጠ አለቃ ነወ፡፡ እሱ ያቀረበው ችግርም፤
“ወዳጆቼ!”
አንበሳን ተክቼ ሥራዬን ለመሥራት እንቅፋት የሆኑብኝ ነገሮች አሉ፡፡ እነሱም፤
አንደኛ - በአያ አንበሶ ጊዜ እንደልብ ያዙ፣ ይፈርዱ፤ የነበሩ አለቆች ዛሬም እንደልብ እንፈንጭ ሲሉ በጣልኩባቸው ማዕቀብ፤ እኔን መቀየማቸውና ለአሠራሬ እንቅፋት መሆናቸው፤
ሁለተኛ፤ በቂ ችሎታ የለህም እያሉ የሚያስወሩብኝ አዋቂ - ነን ባይ ምሁራን
እንስሶች፤
ሦስተኛ፤ አያ አንበሶ አንዳንዴ ስለሚደክማቸው፤ ያሰቧቸውን ነገሮች ሁሉ በግልጽ ስላልነገሩኝ፣ አንዳንዶቹም ሚስጥር ስለሚሆኑብኝ፣ በትክክል ውሳኔ ለመስጠት የማዳገቱ፤
የመጨረሻውና አራተኛው ነጥቤ፤ የግልገል ዝንጀሮዎች ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ሥራዬን ለማቀላጠፍና ጫካውን በትክክል ተቆጣጥሬ ለማስተዳደር ቆፍጠን ቆፍጠን ያሉ ግልገል ዝንጀሮዎች እንዲያግዙኝ ለማድረግ፣ ሥራ ስመድባቸው፤ እነ ነብር፣ እነ ጎሽ፣ እነ ግሥላ፣ እነ ጉሬዛ፣ ሌላው ቀርቶ፣ ይኑር ይለቅ የማይታወቀው ቀይ ቀበሮ ሳይቀር፤ “በዘመድ ነው የሚሠራው” እያሉ እሪ ብለውብኛል!! ከላይ ስለጠቀስኳቸው ጉዳዮች ውሳኔ እንድትሰጡኝ እፈልጋለሁ” አለና ጨረሰ፡፡
እንስሳቱም በሰፊው ከተወያዩ በኋላ፤ በአያ አንበሶ ጊዜ እንደልብ ይቧችሩ የነበሩትና አሁን ያስቸገሩህ ተለይተው ይውጡና ፍርድ ይሰጥባቸዋል፡፡ “የአዋቂ ነን ባይ ምሁራን እንስሶች” ጉዳይ ብዙ አያሳስብህ፤ ልማዳቸው ነው፡፡ ትዝ ይልህ እንደሆን ዱሮም፤ “ወርቅ ሲያቀርቡላቸው ኩበት የሚፈልጉ ናቸው!” የተባሉ ናቸው፡፡ የአያ አንበሶ ሚስጥር ስላልከው፤ ይሄ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልማድ ስለሆነ ቀስ በቀስ የሚበቃህን ያህል እያወቅህ እንድትጓዝ ይደረጋል፡፡
የመጨረሻው የግልገል ዝንጀሮዎች ጉዳይ ግን ከአቅም አቅም የላቸው፣ ከዕውቀት ዕውቀት የላቸው፣ ከልምድ ልምድ የላቸው፤ እንደው ዝንጀሮ ስለሆኑና ግልገል ስለሆኑ ብቻ ሥራ ላይ ማስቀመጡ አሳሳቢ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርዱን ለአያ አንበሶ ብንተወው ይሻላል፤ ብለው ደመደሙ፡፡
***
የአገራችን ሀብት የሁላችንም ሀብት መሆኑን አንርሳ፤ ሌሎችን ማጋራት ግድ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ገንዘብ ዘርፈን ንብረቱን መብት እንጠይቅበት ማለት ዐይን - አውጣነት ነው፡፡ በትላንትና ዝና፣ በትላንትና ወንበርተኛነትም፤ ልዘዝ፣ ዛሬም ልፍለጥ ልቁረጥ፣ ዛሬም እጅ ላስነሳ ማለት፤ የሞተ ፈረስ መጋለብ የሚባለውን ዓይነት እንደሚሆን ልብ እንበል፡፡ ደሞም ሌላውን አላዋቂ በማድረግ አዋቂ መሆን አይቻልም፡፡ ዝቅ ሲል ከስም ማጥፋት፣ ከፍ ሲል ከተራ ጥቆማ የማያልፍ፤ ህዝብ የማያሳውቅ፣ አገር የማያሳድግ ዘለፋ ነው፡፡ ካወቅን፣ ያወቅነውን ሥራ ላይ አውለን ማንነታችንን እናሳይ፡፡ የሚጮህ ውሻ አይናከስም ይሏልና፡፡
ጐበዝ! ዛሬም የሙስና አባዜ አልለቀቀንም፡፡ መጤም ይሁን ነባር፣ ፀጉረ - ልውጥም ይሁን አብሮ - አደግ፣ ቤተኛም ይሁን የባለቤቱ ልጅ፤ ሌብነት ያው ሌብነት ነው፡፡ ዳኝነት ደግሞ ለሁሉም እኩል መሆን አለበት፡፡ የበኩር ልጅ ሆነ የመጨረሻ ልጅ ህግ በእኩል ደረጃ መሥራት አለበት!! በአሁኑ ሰዓት ትልቁ ሌባ “ሌባ ሲጠግብ ቀን ይሠርቃል” እንደሚባለው ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ወጣም ወረደ፤ “ፍርዱን ለአያ አንበሶ እንተው” ማለት ብዙ አያዋጣም፡፡
በዘዴኛነታቸው የሚታወቁት የአፄ ሚኒልክ የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ አባ መቻል ሀብቴ ባስቻሉበት አንድ አደባባይ፤ ሁለት ባላጋራዎች ሲሟገቱ ቆይተው፤ የተፈረደበት ሰውዬ በንዴትና በብስጭት እየተነጫነጨ፤ “ድህነቴን እኮ የሚነሳኝ የለም…” በማለት ደጋግሞ በምሬት ቢናገር፤ አባ መላ በታወቀው ንዴትን የማብረድና ቁጣን የማለዘብ ልዩ ተሰጥዎአቸው፤ ተረቺውን ሲመክሩት፤ “ተው እንዲህ አትሁን፤ ድህነቱንምኮ እኛ ስንፈቅድልህ ነው የምታገኘው” አሉት ይባላል፡፡ ያኔ እንደዛ ነበረ፤ አሁን ግን ከተሰጠን የቆየ ድህነት አናታችን ላይ እያናጠረ ነውና ታግሎ ከመገላገል የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ እንደ ትዝታ ስናስብ፤ በዱሮው ጊዜ “በአሥር ወር ሰላሳ ሺ ቤት እንሠራለን” ላሉ መሀንዲሶች፤ “ቤት ነው ድንኳን?” አሉ ይባላል ባለሥልጣኑ ሲመልሱ፡፡ ምክንያታዊና ዕሙናዊ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚና የስታቲስቲክስ አሀዞች ምንም ዓይነት ዕድገት አሳዩ “አይዞህ ፈጣሪ ይሰጥሃል” የተባለውና፤ “የምሰማው አገኘሁ፤ የምበላውስ?” እንዳለው የኔ - ብጤ፤ ከዕውነታው መፋጠጥ አይቀሬ ነው፡፡ “እኔ የራበኝ ዛሬ፣ ሠርግ የሚደገሰው በጥር ወር” የተባለው ዓይነት ሁኔታን ልብ ማለት አግባብነት አለው፡፡ ዋናው በልቶ ማደር ነውና፡፡ ሌላው እዳው ገብስ ነው፤ (ገብሱም ካለ)፡፡ ዋናው ጉዳይ ላይ ከተግባቡ አሀዙና አባሪው ላይ መደራደር አያቅትም፡፡
አበው፤ “ይወልደዋል ከተባለ ይመስለዋል ማለት አይገድም” የሚሉት ይሄንኑ ሊያፀኸዩ ነው!

Read 4449 times