Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 10:32

የቅ/ላሊበላ ደብር ካህናትና ምእመናን የመንግሥት ያለህ እያሉ ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

. ቤተክህነቱ በደብሩ አለቃ የሚፈጸመውን ሙስናና የአስተዳደር በደል መቆጣጠር ተስኖታል
. የውቅር አብያተ መቅደሱ የቱሪስት ገቢ ተቆጣጣሪ የለውም፤ የቅርሶቹ ጉዳት ተባብሷል
. በደብሩ ገንዘብ የተሠሩት የቤተ አብርሃም እና ይምርሐነ ሆቴሎች ባለቤት አይታወቅም
በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የቅዱስ ላሊበላ ደብር የሚያገለግሉ ካህናት እና ምእመናን÷ በደብሩ አስተዳዳር በሚፈጸመው ሙስናና የአስተዳደር በደል መማረራቸውንና አቤቱታቸው ሰሚ አለማግኘቱን ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የቱሪዝም ገቢ የግል ሀብትን ለማደለብ እየዋለ መኾኑን የጠቆሙት ካህናቱ÷ በቅርሶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መባባሱን፣ሙሰኝነትንና የአሠራር ብልሹነትን የሚቃወሙና የሚያጋልጡ ካህናትና ሠራተኞች ለመባረርና ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት ስምንት ዓመታት “ካህናት - ነገሥታት” ተብለው በአገራችን ከሚታወቁት አራቱ የዛጉዌ ዘመን ስመ ጥር መሪዎች ዋነኛው በነበረው ቅዱስ ላሊበላ የተሠሩትና አገራችን በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች ግንባር ቀደም በኾኑት ዐሥራ አንድ አብያተ መቅደስ በአስተዳዳሪነት የቆዩት መምህር አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን÷የደብሩን ካህናት ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ሸፍኖ በዓመት ከቱሪዝም ብቻ በአነስተኛ ግምት የሚገኘው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለምን እንዳዋሉት አይታወቅም ይላሉ - አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡
ደብሩ ሦስት ታላላቅ ሆቴሎች፣አንድ የእንግዳ ማረፊያ፣ ለሁለገብ አገልግሎት የተከራየ ባለሦስት ፎቅ ሕንጻ፣መኪኖች፣ወፍጮዎችና ሙዳዬ ምጽዋትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ቢኖሩትም የተቋማቱ አስተዳደር በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ በሌላቸው፣ እንዲሁም በጥቅም በተሳሰሩ ደጋፊዎቻቸውና ዘመድ አዝማዶቻቸው እንዲመራ በማድረግ፣ የሕዝብና የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እያባከኑ ነው ብለዋል፡፡የአቤቱታው አቅራቢዎች አስተዳዳሪው የደብሩን ገንዘብ ወጪ የሚያደርጉባቸውን ስልቶች ሲያስረዱም÷ ‹‹የደብሩን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በበላይነት ለመምራት በካህናትና ምእመናን ጉባኤ የተሠየመው ሰበካ ጉባኤ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንዲያደርግ ካስወሰኑ በኋላ ውሳኔው የሰፈረበት ቃለ ጉባኤ ተቀዶ እንዲጣል ያደርጋሉ፡፡ የግዥም ሆነ የግንባታ ሥራዎች ያለጨረታ በራሳቸው ፈቃድ እንዲከናወን ያደርጋሉ፡፡ በአብዛኛው አዲስ አበባ የሚገዙ ዕቃዎችን ያለፕሮፎርማ ራሳቸው ገዝተው ሲያበቁ ዕቃ ግዥ ሓላፊውን ወደ አዲስ አበባ ልከው እንደገዛ አስመስለው ይልኩታል፤››ይላሉ፡፡አስተዳዳሪው ቤተ አብርሃም የተሰኘውን ሆቴል አሠርተዋል በሚል “የልማት አርበኛ” ቢባሉም አሠሩት የሚባለው ሆቴል ከፍተኛ ሙስና የተፈጸመበትና ሪፖርት የተደረገው ገንዘብ በሥራ ላይ ከዋለው ገንዘብ በዕጥፍ እንደሚበልጥ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም ሆቴሉ በሚገነባበት ጊዜ በሕዝቡና በካህናቱ በታማኝነቱ የተመረጠው ገንዘብ ያዥ÷ ያለምንም ምክንያት ከጅምሩ ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደርጎ÷ በሌላ ሰው መተካቱንና እስከ አሁን ድረስ ግን ደሞዝ እንደሚከፈለው የሚያስረዱት ምንጮቹ፣ ቤተ አብርሃም እና ይምርሐ የተባሉት ሁለት ታላላቅ የደብሩ ሆቴሎች ባለቤትነታቸው በውል እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡ የሆቴሎቹ ፈቃድ በግለሰቦች ስም የተያዘ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ባለመብትና ባለይዞታ ነች ብሎ በሕግ መከራከር እንደማይቻል ምንጮቹ ጠቁመው÷ የደብሩ ሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ሲካሄድ ያለሰበካ ጉባኤው ዕውቅና መሆኑን÷ ገቢ የሚደረገውም በገንዘብ ያዥ ብቻ በመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥቆማ÷ ደብሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት ብር የሚያንቀሳቅስ ቢሆንም የሥራና የበጀት ዕቅድ የለውም፡፡ ገቢና ወጪው መደበኛ የሒሳብ አሠራር ተከትሎ ለሰበካ ጉባኤውም ኾነ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አይቀርብም፡፡የሒሳብ ቁጥጥር ካለመደረጉም በተጨማሪ የሒሳብ ሪፖርቱ ከተሠራው ሥራ ጋር ተገናዝቦ ስለማይቀርብ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና ምዝበራ እየተፈጸመ መሆኑ ያሳስበናል ብለዋል፡፡የቦታው ነባር መንፈሳዊ ቅርሶችና ተቋማት እየፈረሱና እየተዳከሙ የጥገና ያለህ በሚሉበት፣የካህናቱ ኑሮ ባልተለወጠበት፣በደብሩ ከፍተኛ አቅም መታቀፍና መደገፍ የሚገባቸው አብነት ት/ቤቶች ወንበሮቻቸው እየታጠፉ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው በተበተኑበት፣ ገዳማቱ ወደ መፈታት በደረሱበት ኹኔታ አስተዳዳሪውና ዘመድ አዝማዶቻቸው ያለከልካይ ይፈጽሙታል የሚባለውን ምዝበራና ሙስና እንዲገታ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ቀድሞው ፓትርያሪክ ድረስ በተደጋጋሚ የቀረበው አቤቱታ ሰሚ እንዳላገኘ ካህናቱ ይስረዳሉ፡፡ አስተዳዳሪው ማንንም ሳያስፈቅዱ ለሁለት ወራት በአሜሪካ በቆዩበት ወቅት ለቦታው በሚመጥን ሌላ ሰው እንዲተኩ በፓትርያርኩ ተሰጥቶ ነበር የተባለው ውሳኔም ባላወቁት ምክንያት ተፈጻሚ እንዳልኾነ ነው ካህናቱ የሚናገሩት፡፡በምትኩ በየጊዜው ተቃውሞ የሚያቀርቡ ካህናትና የሀገረ ስብከት ሠራተኞች ሳይቀር እንደሚታሰሩ፣ ያለምንም ምክንያት ደመወዛቸው እንደሚቆረጥ፣ ከሥራቸው እንደሚባረሩ፣ በዕድሜ የገፉ ሊቃውንትና መምህራን ለመንፈሳዊ ሥልጣናቸውና ክብራቸው ተቃራኒ በኾነ መልኩ በየሰበቡ እንደሚዋረዱና በተመልካቾች ፊት እንዲንበረከኩ ከመደረጋቸውም በላይ በተቃውሞ የተገኙ ካህናት ከአገልግሎት እንደሚባረሩ በግዴታ የፈረሙበት ሕግ በአስተዳዳሪው መውጣቱን አቤቱታ አቅራቢዎቹ በምሬት ይገልጻሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዐዋዲ ደንብ መሠረት የአስተዳዳሪውን አካሄድ ለመቆጣጠር ሥልጣን ያለው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ለይስሙላ የተቀመጠና አባላቱም በየጊዜው በአስተዳዳሪው ከሓላፊነታቸው እየተነሡ በሥነ ምግባር ጉድለታቸው በሕዝቡና በካህናቱ የታወቁ ግለሰቦችን እንደሚተኩበት ይናገራሉ፡፡ አስተዳዳሪው ችግሩን የሚያውቁትንና እንዲታረምም ማሳሰቢያና ምክር የሚሰጡትን የመንግሥት ባለሥልጣናት በአንድ በኩል ‹‹በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብኝ›› እያሉ እያናናቁ በሌላ በኩል ደግሞ የዞንና የክልል ባለሥልጣናት ‹በእጃቸው እንደኾኑ›ና የከተማው አስተዳደር ሓላፊዎች ከእርሳቸው ጋራ ካልተስማሙ ሥልጣናቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ እንደሚያስፈራሯቸው በአቤቱታው ላይ ተመልክቷል፡፡ አክለውም የጥንታዊው ቅዱስ ላሊበላ ደብር ጥገናና ክብካቤ ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከተው የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ጋራ ተስማምተው መሥራት እንዳልቻሉ፣ ለሌሎችም የመንግሥት ሓላፊዎች ሳይቀር ማስቸገራቸውን ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡ በአስረጅነትም የከተማውን የቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ሳያማክሩ በራሳቸው ፈቃድ የቱሪስት መግቢያ ክፍያን ከኻያ ዶላር ወደ ኀምሳ አምስት ዶላር እንዲጨምር መወሰናቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
ይህም አስተዳዳሪው ቀድሞም የባለድርሻ አካላቱን (አስጎብኚዎች፣ የጉዞና የጉብኝት ወኪሎች) በመዝለፍና በማዋረድ የሻከረው የሥራ ግንኙነታቸው የከፋ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስበትና ከዘርፉ ቤተ ክርስቲያኒቱና አገሪቱ ማግኘት በሚገባቸው ጥቅም ላይ ዕንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ስለ መኾናቸው በበቂ ስለሚያስረዳ በመንግሥትና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለደብሩ ተገቢውን መምህር በመመደብ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የዝግጅት ክፍሉ ስለጉዳዩ የጠየቃቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች አስተዳዳሪው የሚፈጥሩት ችግር ከቀድሞም ጀምሮ የሚታወቅ በመኾኑ መንበረ ፓትርያሪኩ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋራ በመነጋገር በአጭር ጊዜ እልባት እንደሚሰጠው ያላቸውን አስተያየት ገልጸዋል፡፡

 

ሃም የተሰኘውን ሆቴል አሠርተዋል በሚል “የልማት አርበኛ” ቢባሉም አሠሩት የሚባለው ሆቴል ከፍተኛ ሙስና የተፈጸመበትና ሪፖርት የተደረገው ገንዘብ በሥራ ላይ ከዋለው ገንዘብ በዕጥፍ እንደሚበልጥ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም ሆቴሉ በሚገነባበት ጊዜ በሕዝቡና በካህናቱ በታማኝነቱ የተመረጠው ገንዘብ ያዥ÷ ያለምንም ምክንያት ከጅምሩ ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደርጎ÷ በሌላ ሰው መተካቱንና እስከ አሁን ድረስ ግን ደሞዝ እንደሚከፈለው የሚያስረዱት ምንጮቹ፣ ቤተ አብርሃም እና ይምርሐ የተባሉት ሁለት ታላላቅ የደብሩ ሆቴሎች ባለቤትነታቸው በውል እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡ የሆቴሎቹ ፈቃድ በግለሰቦች ስም የተያዘ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ባለመብትና ባለይዞታ ነች ብሎ በሕግ መከራከር እንደማይቻል ምንጮቹ ጠቁመው÷ የደብሩ ሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ሲካሄድ ያለሰበካ ጉባኤው ዕውቅና መሆኑን÷ ገቢ የሚደረገውም በገንዘብ ያዥ ብቻ በመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡

Read 3547 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 10:40