የቴክኖሎጂና አቅሙን በማሳደግ ለደንበኞቹ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ማይሲክ ከተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ (ኮር ባንኪንግ) እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፣ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ደንበኞች በርካታ ዘመናዊና በአገሪቱ ያልተለመዱ ልዩ አገልግሎቶችን ያገኛሉ ብሏል፡፡
አዋሽ ኢንተርናሽናል ከንብ ኢንተርናሽናልና ከሕብረት ጋር በመተባበር ያቋቋሙት ፕሪምየም ስዊች ሶሉሽንስ የመጨረሻ ዝግጅት እየተጠናቀቀ በመሆኑ “አዋሽ ካርድ” ማዘጋጀቱን ጠቅሶ፣ ካርዱን የያዘ ደንበኛ በቅርቡ ወዳገኘው የሦስቱ ባንክ ቅርንጫፍ ጐራ ብሎ ኤቲኤም መሳሪያ በመጠቀም አገልገሎት ማግኘት እንደሚችል ገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ካርዱን የያዙ ደንበኞች “የአዋሽ ካርድ እንቀበላለን” የሚል ምልክት በተሰቀለባቸው የንግድ ድርጅቶች፣ ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ ስጋት ተላቀው በካርዱ መገበያየት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡