Saturday, 10 November 2012 16:43

ኦቴሎ

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ስሙ ጥሩውና ታላቁ እንግሊዛዊ ጸሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒር “ቪነስና አዶኒስ” እንዲሁም “ሬፕ ኦፍ ሉክረስ” የተባሉትን ቅኔዎቹን እ.ኤ.አ ከ1593 እስከ 1594 ዓ.ም ባለው ጊዜ ሲያሳትም ገና የ28 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ “ሶኔትስ” የተሰኙት ቅኔዎቹ ሲታተሙለት ደግሞ ሼክስፒርን ደራሲ፣ ባለቅኔ እና ፈላስፋ አሰኝተውታል፡፡ ከቅኔዎቹ መታተም በኋላ ሮሜዎና ዡልየትን፣ ሪቻርድ ዳግማዊን፣ ሚድ ሰመር ናይትስ ድሪምን፣ ኪንግ ጆንን፣ የቬነሱ ነጋዴን እና ሔንሪ አራተኛን በተከታታይ ጽፏል፡፡ ከነዚህ ሥራዎች በኋላ ነው የሼክስፒር የበሰሉ ቴአትሮች የሆኑት ሐምሌት እና ኦቴሎ ወደ መድረክ ብቅ ያሉት፡፡ ሼክስፒር ኦቴሎን የደረሰው በ1604 ዓ.ም እንደነበረ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ 

ኦቴሎ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎመ የዊሊያም ሼክስፒር ሥራ ሲሆን ተርጓሚውም ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ነበር፡፡ ጋሼ ጸጋዬ ኦቴሎን ከመተርጎሙ በፊት በቴአትር ደራሲነት እየታወቀ የመጣ ወጣት ደራሲ ሲሆን በዚህ ጊዜ እድሜው እንደ ሼክስፒር ገና 28 ዓመት ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ሥራዎቹም (አምስት ባለ ሙሉ ክፍል ቴአትሮች) የደም አዝመራ፣የእሾህ አክሊል፣ በልግ፣ የመጨረሻው ከንቱነት፣ የእማማ ዘጠኝ መልክ፣ ሲሆኑ (አምስት ባለ አንድ ክፍል ድራማዎች) እኝ ብዬ መጣሁ፣ ጆሮ ገድፍ፣ ሰማህ ማሞ፣ አስቀያሚ ልጃገረድ፣ ኮሾ ሲጋራ እና በተጨማሪ ደግሞ (ሁለት ትርጉሞች) ከሞሊየር የፌዝ ዶክተር እና ከታርቲዩፍ ደግሞ አወናባጅ ደብተራ ነበሩ፡፡ ጋሼ ጸጋዬ ከዛሬ 49 ዓመት በፊት ኦቴሎን ተርጎሞ ቴአትሩን ለሕዝብ ካቀረበ በኋላ እንደጊዜው ልማድ ቴአትሩ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጥቶ ነበር፡፡ የዚህን መጽሐፍ መቅድም የጻፉት ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ አስተያየታቸውን ሲያመለክቱ፤ “ንባብ የሚያፈቅሩ ኢትዮጵያውያን የዚህን ሰው (የሼክስፒርን) ጽሑፎች በአማርኛ ለሚተረጉምላቸው ሰው የልብ ምሥጋና ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ እንዲያውም ጽሑፎቹ እንደተጻፉ ዕውቀት የደረሰው ዓለም ሲያነባቸው፤ እኛ የሱን ጽሁፎች ከማንበብ 350 ዘመን ወደ ኋላ ቀርተናል፡፡ አሁንም እንደ አቶ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ያሉ ተርጓሚዎችና ደራሲያን ባይኖሩን ዘመኑ ከዚህ የበለጠ ሊውልብን፤ ሊያድርብን ኖሯል” ብለው ነበር፡፡ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ አስተያየታቸውን በመቅድሙ ሲያጠቃልሉ፤ “አቶ ጸጋዬ የሼክስፒርን ድርሰቶች ሲተረጉም በምን ምክንያት ኦቴሎን ከቀዳሚዎቹ አንዱ እንዳደረገው አልነገረኝም” ካሉ በኋላ ግምታቸውን ሲሰነዝሩ “የወገናችን የቤተሰብ ኑሮ በሆነው ባልሆነው ስለሚፈታ ምክሩን በሼክስፒር ስም ሊያበረክት የፈለገ ይመስለኛል” በማለት ደምድመዋል፡፡ ከመቅድሙ ቀጥሎ በተከተለው ገጽ መግቢያውን የጻፈው ጋሼ የድርሰቱን ጭብጥ ሲያትት፤ “የአንድ ሰው ጽናት፤ ታማኝነትና ብርታት እንዴት ተወናብዶ ሊወድቅ እንደቻለ ለማሳየት፤ ጀግናውንና ልበ ቅኑን ጥቁሩን ኦቴሎ፤ የቬኒስያ መንግሥት የጦር መሪ ሳለ፤ በኢያጎ ሣጥናኤላዊ ልክፍት በሚስቱ አለመታመን እንዲያምን አእምሮውና ቅን ልቦናው ተገዶ፤ የተሳሳተ እምነቱም የሚወዳትን ወጣት ሚስቱን ሕይወት ለመቅጠፍ እንዳበቃው፤ በስህተት ታውሮ ላጠፋውም ህይወት መበቀያ ራሱን በተጨማሪ እንዳጠፋ ይነግራል” በማለት ዘርዝሮ ነበር፡፡ ኦቴሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከዛሬ 52 ዓመት በፊት ሐምሌ 24 ቀን 1953 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (አሁን ብሔራዊ ቴአትር) ሲሆን ለሕዝብ የቀረበውም የቴአትሩ አንዱ ክፍል ብቻ ነበር፡፡ በዕለቱም የጋሼ ጸጋዬ ሥራዎች የሆኑት “እኝ ብዬ መጣሁ” እና “የፌዝ ዶክተር” ከኦቴሎ በኋላ በተከታታይ ቀርበው ነበር፡፡ኦቴሎ ለሕዝብ ሲቀርብ ተከታትሎ የዘገበው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር፤ “በቀ.ኃ.ሥ ቴአትር ልዩ ልዩ ጨዋታዎች አየን” በሚል ርዕስ ሐምሌ 24 ቀን 1953 ዓ.ም አንድ መጣጥፍ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ሪፖርተሩ በዘገባው በውጪ ቋንቋ የተጻፈ ጨዋታ ወደ ራስ ቋንቋ ሲመለስ ከሚገጥሙ ችግሮች መካከል ተመሳሳይ ቃላት የመፈለግና የማግኘት እንዲሁም የእነዚህ ቃላት አሰካክ እንደ ዋናው ጨዋታ ተመሳሳይ ስሜት እንዲፈጥር ማድረግ መሆናቸውን ገልጾ “አቶ ጸጋዬ ገብረ መድኅን በዚሁ ዓይነት ጨዋታውን ለአማርኛ ቋንቋና ለአማርኛ ባህል እንዲስማማ አድርገው መተርጎማቸውን ለማወቅ ጨዋታውን መመልከት ይበቃል፡፡ ለዚህ ሥራቸውም ተርጓሚው ሊመሰገኑ ይገባል” ብሎ ነበር፡፡ ዘጋቢው በዚሁ ጽሁፉ የኦቴሎ ቴአትር ተዋናዮችን አስመልክቶ በሰጠው ሂስ “ኦቴሎን ሆኖ የተጫወተው ተዋናይ በአነጋገሩም ሆነ በሰውነቱ ሁናቴ የኦቴሎን በቂ ተመሳሳይነት ሊያገኝ አልቻለም፤ ብዙዎች ከዚህ በፊት የኦቴሎን ጨዋታ ያነበቡና በሲኒማ የተመለከቱ ይህንን ተጫዋች ቀዝቃዛ ሆኖ አግኝተውታል” ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ጸሐፊው በበጎ ጎኑ የተመለከተውን ትዕይንት ሳይዘግብ አላለፈም፤ ይኸውም “የኦቴሎ ታማኝ አሽከር ኢያጎን ሆኖ የተዋነየው በተሻለ ሁኔታ ተጫውቷል፡፡ እንዲያውም እርሱ እንዲህ ባለ አኳሀን ባይጫወት ኖሮ ጨዋታው ዝቅተኛ ግምት የሚጣልበት ከመሆኑም በላይ ፍጹም ለዛውን ያጣ ነበር” ሲል አትቷል፡፡ ጋሼ ጸጋዬ የተሟላውን የኦቴሎ ትርጉም ያቀረበው ሶስት ዓመት ያህል ቆይቶ በ1956 ዓ.ም ነበር፡፡ ኦቴሎ እንደገና የቀረበው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት ሲሆን ጊዜውም ግንቦት 7 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚሁ ዕለት ዐጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ልዑል አልጋ ወራሽን፣ ልዕልታትና ልዑላንን፣ ንጉሣዊ ቤተሠብን፣ መሣፍንትና መኳንንትን፣ ሚኒስትሮችን፣ የጦር አለቆችን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸውን ሹማምንትን አስከትለው ከምሽቱ ሶስት ሠዓት ሲሆን ቴአትር ቤቱ ሲደርሱ አቶ ሥዩም ሐረጎት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሚኒስትር እና አቶ ከበደ አስፋው በረዳት ሚኒስትር ማዕረግ የቴአትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቀባበል አደረጉላቸው፡፡ ከአቀባበሉ ሥነ ሥርዓት በኋላ ጋሼ ጸጋዬ ወደ ቴአትር መድረኩ ወጥቶ ስለ ኦቴሎ ታሪክ እንዲሁም የሼክስፒርን 400ኛ ዓመት መታሠቢያ በመዘርዘር አጭር ንግግር ካደረገ በኋላ መጋረጃው ተከፍቶ ቴአትሩ ተጀመረ፡፡ በሰኔ ወር 1956 ዓ.ም የታተመው የመነን መጽሔት የኦቴሎ ቴአትር በንጉሠ ነገሥቱ መታየቱን በዘረዘረበት ጽሑፉ “የኦቴሎ ታሪክ ከዚህ ቀደም በሲኒማ ተዘጋጅቶ የታየ ቢሆንም፤ በሀገር ቋንቋ በሀገር አርቲስቶች በሙሉ ስሜት ጣፍጦ በመታየቱ ለተመልካች እውነት የኦቴሎን ዘመን ወቅት መስሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ቴአትሩ አራት ሠዓት ተኩል ጊዜ የወሰደ ረጅም ትርኢት እንደመሆኑ የአራት ደቂቃዎችን ያህል ሳይጠገብ የፍጻሜው መጋረጃ ተዘጋ፡፡ አክተሮቹ ወደ ግርማዊነታቸው ቀርበው እጅ በነሱበት ጊዜ “የሰራችሁት በጣም ጥሩ ነው” ሲሉ በማመስገንና በመሸለም አበረታተዋቸዋል፡፡” በማለት አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር፡፡ እንደዘገባው ቴአትሩ የፈጀው ጊዜ አራት ሠዓት ተኩል ከሆነ ንጉሠ ነገሥቱና ተከታዮቻቸው ቴአትሩ እስኪፈጸም ድረስ ስለቆዩ የወጡት ከሌሊቱ በሰባት ሠዓት ተኩል ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በቴአትሩ ላይ የተጫወቱት ተዋንያን - አውላቸው ደጀኔ እንደ ኦቴሎ፣ ተስፋዬ ሣህሉ እንደ ኢያጎ፣ አስናቀች ወርቁ እንደ ዴዝዲሞና፣ መኮንን አበበ እንደ ብራቫንሽዮ፣ ጀምበሬ በላይ እንደ ቃስዮ፣ ነጋሽ ዘለቀ እንደ መስፍኑ፣ ጌታቸው ደባልቄ እንደ ሮድሪጎ፣ አስካለ አመነሸዋ እንደ ኤሚልያ ሲሆኑ ጠቅላላ ቁጥራቸውም 28 ነበር፡፡ ጋሼ ጸጋዬ ንጉሠ ነገሥቱ የኦቴሎ ቴአትርን ከተከታዮቻቸው ጋር በተመለከቱበት ጊዜ የነበረውን የማይረሳ ትውስታ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ለጦቢያ መጽሔት ሲናገር፤ “በ1956 ዓ.ም ጃንሆይ “ኦቴሎ” የተባለውን የሼክስፒር ትርጉም ቴአትር ተመልከተው ሲወጡ አስጠሩኝና ቀረብኩ፡፡ “ለምንድን ነው ሌሎች ቴአትሮችህን እንድናይልህ እስካሁን ያልጋበዝከን? እስከዚህ ድረስ ርቀንህ ነው? አሉኝ፡፡ እጅ ነሳሁና “አዎን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት! ግርማዊነትዎ ለእኔ ብጤ ሩቅ ነዎት፤ ያም ቢሆን ግርማዊነትዎ እንዲመጡልኝ ለአለቃዬ (ለረዳት ሚኒስትር ከበደ አስፋው)፣ አለቃዬ ደግሞ ለአለቃቸው (ለማስታወቂያ ሚኒስትሩ ለክቡር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት) አቅርበው “ቴአትር የሚመለከቱበት ፕሮግራም የላቸውም ተብለሀል” ተብዬ ነው” ስላቸው ፈገግ ብሎ የነበረ ገጻቸው በዝምታ ከሰመ” “መኳንንቱ፣ ሚኒስትሮቹና አጃቢ ክቡር ዘበኞቹ በረገጉ፡፡ ክቡር ደጃዝማች ቀረቡ፡፡ ተርበተበቱ፡፡ አቶ ከበደ አስፋው ከክቡር ዘበኞቹ ጀርባ እንደመሸሸግ ብለው ተሸማቀቁ፡፡ የነሱን መደንገጥ ሳይ እኔም ፈራሁ፡፡ ክቡር ደጃዝማች ለአለቃቸው ለክቡር ጸሐፌ ትእዛዝ ተፈራ ወርቅ በአንድ ወቅት መንገራቸውን እየተደናገጡ ተናገሩ፡፡ ጸሐፌ ትእዛዝ ወደ ጃንሆይ ቀረብ ብለው በለሆሳስ ድምጽ የሆነ ነገር ሹክ አሏቸው፡፡ ጸሐፌ ትእዛዝ ትንሽ ወደኔ ራመድ ብለው “ነገ ጧት በሁለት ሠዓት ታላቁ ግቢ ና እና እጅ ንሳ! ሲሉኝ ተደናግሬ እጅ ስነሳ ጃንሆይ እንደተቆጡ እጥፍ ብለው ወጡ፡፡ ከዚያ በኋላ አለቆቼ አፈጠጡብኝ” ብሎ ነበር፡፡ ግንቦት 8 ቀን 1956 ዓ.ም ጋሼ ጸጋዬ መላውን የኦቴሎ ተዋንያንና የመድረክ ሞያተኞች ይዞ በአገር አስተዳደር የጸጥታው የበላይ ሹም በነበሩት በደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ አማካይነት ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀረበ፡፡ ለተዋናዮቹ እና ለመድረክ ሙያተኞች ዳረጎት ከተሠጣቸው በኋላ “ኦቴሎ ቴአትር በነጻ እንዲታተምልህ ታዞልሀል” ተብሎ በንጉሠ ነገሥቱ ተነገረው፡፡ ጋሼ ጸጋዬም እጅ ነስቶ የሥራ ባልደረቦቹን ይዞ ከቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፡፡ ጋሼ ጸጋዬ የኦቴሎ ትዝታውን ሲያጠቃልል፤ “ጃንሆይ ከዚያ በኋላ ኦቴሎን ሁለት ጊዜ አዩት፡፡ በመጀመሪያ ግን ሙሉ ለሙሉ ታግዶ ነበር፡፡ ከታገደ ከስምንት ወር በኋላ ነው “በንጉሡ ነገሥቱ መልካም ፈቃድና ትዕዛዝ ኦቴሎ ቴአትርን ታዝዘሀል” ተብዬ ያቀረብኩት” ሲል አክሏል፡፡ ኦቴሎ ከዚህ ጊዜ በኋላ እየተደጋገመ ለሃያ ዓመት ያህል ለሕዝብ ቀርቧል፡፡ የመልካም ድምጽ ጸጋን የታደለ ድምጻዊ ያለ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች እና አቀናባሪዎች የተሟላ ዜማ ለማዜም እንደማይቻለው ሁሉ የቴአትር ደራሲ ወይም ተርጓሚም ብቁ አዘጋጅ እስካላገኘ ድረስ ድርሰቱ ህያው ሊሆንለት እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በመሆኑም የኦቴሎ ቴአትር እየተደጋገመ ለሕዝብ ሲታይ በተለያየ ጊዜ ቴአትሩን ያዘጋጁ ባለሙያዎችም የምስጋና ድርሻቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡ በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥቱ ጥበብን አክብረው ከመላው ቤተሰባቸው፣ ከሚኒስትሮቻቸውና ከጦር አለቆቻቸው ጋር ቴአትርን ለማየት ከምሽት እስከ ሌሊት መቆየታቸውን እንዲሁም ለተዋንያኑና ለመድረክ ሞያተኞች ማበረታቻ ድርጎ መስጠታቸዉን፣ በተጨማሪ ቴአትሩ በነጻ እንዲተተም መፈቀዱን ስንመረምር ዘውዳዊው መንግሥት ከነችግሮቹ የኢትዮጵያ ጥበብ ወዳጅና ባለውለታ እንደነበረ ለመረዳት አያዳግተንም፡፡ ይህን ጽሁፍ የማጠቃልለውም አገሬን “ለምን ቴአትር ሳትጋብዙኝ ቀራችሁ? ለናንተ ይሄን ያህል ሩቅ ሆኜ ነው?” የሚል መሪ ይስጥሽ እያልኩ እየተመኘሁላት ነው፡፡

Read 6656 times