Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 November 2012 14:46

የባራክ ኦባማ እና የሚት ሮምኒ ፉክክር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዲሞክራት እና ሪፐብሊካን በፊኒክስ፤አሪዞና   ያለፈው ማክሰኞ ለአሜካ ወሳኝ ቀን ነበረች፡፡ እንደሌሎቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሁሉ በፊኒክስ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ነበር የተከፈቱት፡፡ ቀድመው በሚመሹ ግዛቶች ምርጫው ተጠናቆ የምርጫ ውጤት መገለጽ ሲጀምር የየፓርቲው ደጋፊዎች  በከተማዋ መሀል እንብርት ላይ ወደተዘጋጁት የውጤት መከታተያ ድግሶች ላይ ለመገኘት ዝንጥ እያሉ መጓዝ ጀመሩ፡፡አሪዞና ለረጅም ዘመናት በሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊነቷ ትታወቃለች፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን በርካታ ወጣቶች አስቀድመው  ድጋፋቸውን ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በመስጠታቸው ምርጫውን አጓጊ እንዳደረገው የአሜሪካን ምርጫ የመዘገብ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች ነግረውኛል፡፡የዴሞክራቲክ ፓርቲ የአሪዞና ጽ/ቤት የምርጫ ውጤት መከታተያ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው በሬነሳንስ ሆቴል ሲሆን ሪፐብሊካኑ ደግሞ ከዚሁ ሆቴል ጎን ባለው በሃያት ሆቴል ነበር ያዘጋጀው፡፡

ፕሮግራሙን በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ ሳተላይት የተገጠመላቸው መኪኖች ሆቴሎቹ በር ላይ ተደርድረው ነበር፡፡ የዲሞክራቶቹ ዝግጅትሆቴሉ ከመግቢያው ጀምሮ በሰዎች ተሞልቷል፡፡የሪፐብሊካኑ ደጋፊዎች ያሉበት አገር ነው በሚባለው አሪዞና፤ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው የኦባማ ደጋፊዎችን ማየት የሚገርም ነው፡፡ በሆቴሉ ምድር ላይ ባለው ሰፊ ባር ዙሪያ የተገጠሙ የቴሌቭዥን ስክሪኖችን ከበው፣ እየበሉና እየጠጡ ውጤቱን የሚከታተሉ ሰዎች የየግዛቶቹ ውጤት በተነገረ ቁጥር ጩኸታቸውን ያሰማሉ፡፡ በሁለተኛው ፎቅ ላይ ወዳለው ዋናው የዝግጅቱ አዳራሽ ለመግባት በርካታ ሰዎች ሰልፍ ይዘዋል፡፡ተራ የደረሳቸው ከሥር ከሥር እየገቡ ነው፡፡ ያልደረሳቸው ደግሞ ምድርቤት ወዳለው ቲቪ ዓይናቸውን ጣል እያደረጉ ይቁነጠነጣሉ፡፡ለኦባማ ደጋፊዎች የተዘጋጀው አዳራሽ ዙሪያውን አሸብርቋል፡፡ስክሪኑ ከተሰቀለበት ማዕዘን ውጭ ያሉት ሦስት መዓዘኖች እና የአዳራሹ መሐለኛው ክፍል ለጋዜጠኞች ተብለው ከፍ ብለው በተሠሩ መድረኮች ተሞልቷል፡፡የጋዜጠኛው ቁጥር ከተመልካቹ ሊበልጥ ምንም አልቀረውም፡፡ከፊት ያለው ተመልካች በሙሉ መሬት ላይ ቁጭ ብሏል፡፡እየበሉ፣እየጠጡና እየጮሁ ውጤቱን ይከታተላሉ፡፡ ምርጫ ሳይሆን ኳስ ጨዋታ የሚያዩ ይመስላሉ፡፡ በመጨረሻ የሰው ቁጥር እየጨመረ መጥቶ አዳራሹ በሰው ተጨናነቀ፡፡በሚነገረው ውጤት መሰረት ሁለቱ ተፎካካሪዎች አንገት ለአንገት ተናንቀዋል፡፡ ውጤታቸው በጣም ተቀራራቢ ነበር፡፡ ውድድሩን አሸንፎ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያበቃቸውን የኤሌክቶራል ቮት 270 ድምጽ ማግኘት የግድ ነበር፡፡ ቴሌቭዥን ከሚመለከተው ሌላ አንገቱን ደፍቶ ስልኩ ላይ ያደፈጠው ሰው ቁጥርም ቀላል አልነበረም፡፡የግዛቶቹ ውጤት ሲነገር ቆይቶ በድንገት ሰበር ዜና ተሰማ፡፡  ኦባማ 303 ድምፆችን በማግኘት ማሸነፋቸው ተነገረ። አዳራሹ በጩኸት ተጋና፡፡ ሰው እርስ በእርስ መተቃቀፍ መሳሳም ጀመረ፡፡ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ ውጭ ያለው ወደ ውስጥ ገባ፡፡የቴሌቭዥን ጣቢያዎቹ አዳራሹ ውስጥ ያለውን ደስታ ለተመልካቾቻቸው ለማስተላለፍ ካሜራቸውን ደቀኑ፡፡ የሪፐብሊካን ዝግጅትበሃያት ሆቴል የተዘጋጀው የሪፐብሊካን ፓርቲ የመጀመሪያ ዝግጅት በጣም የደመቀ ነበር፡፡አዳራሹ በሚት ሩምኒ እና በሌሎች ተወዳዳሪዎች ፖስተር አሸብርቋል፡፡አዳራሹ መግቢያ ላይ የሚት ሩምኒ ፎቶ ያለበት ቲሸርቶት በብዛት ተሸጠዋል፡፡ ሩምኒ ያሸነፉበት ግዛት ሲታይ ስማቸው የታተመበትን መፈክር የያዙ በርካታ ሰዎች መፈክራቸውን ወደ ላይ ከፍ እያደረጉ ጩኸት ያሰሙ ነበር፡፡አንድ ዓይነት ልብስ የለበሱ በርካታ አስተባባሪዎች ወዲያ ወዲህ እያሉ ለአዳራሹ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ ከሩምኒ ሽንፈት በኋላ ወደ አዳራሹ ተመልሼ ስገባ ሁሉ ነገር ተለውጧል፡፡ ፀጥታ ነግሷል፡፡ የሩምኒ ፖስተር በየሰው እግር ሥር ወዳቋል፡፡ አንዳንዶች እየጠጡ ያስካካሉ፡፡ እነዚህኞቹ የሩምኒን መሸነፍ አምነው የተቀበሉት ናቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ ሐረር እና ድሬደዋ ከተማ ነበርኩ፡፡ ይህንኑ ምርጫ ተከትሎ በተነሳ አለመግባባት ምርጫው ይደገም በተባለባቸው ሆሳዕና እና አካባቢዋ እንዲሁም ወሊሶ ተገኝቼአለሁ፡፡ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ደግሞ በትግራይ ክልል ተንቤን ምርጫውን ዘግቤያለሁ፡፡ እነዚህን ጊዜያቶች በምናቤ ወደኋላ እየመላለስኩ ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡ ልዩነታቸው የትየለሌ ነው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤  ሚት ሮምኒ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ላደረጉት ጠንካራ ፉክክር ሲያመሰግኗቸው፤ ሚት ሮምኒ በበኩላቸው በቦስተን ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ ለፕሬዚዳንት ኦባማ  የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።ሁለቱም ለአገራቸው በአንድነት እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል፡፡  ከሁለቱ ሆቴሎች የሚወጡት የሁለቱ ፓርቲዎች ደፊጋዎች ደስታቸውን እየተለዋወጡ ነበር፡፡ አንዷ ሞቅ ያላት የሩምኒ ደጋፊ፣ እኔ የኦባማ ደጋፊ መስያት ‹‹እመኚኝ መጪውን አራት ዓመት አብረን ነን›› አለችኝ፡፡ ከተማዋ በመኪና ጡሩንባ ደምቃ ነበር፡፡ ኦባማ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ያሸንፉ እንጂ ልዩነታቸው ትንሽ ቢሆንም በአሪዞና ግዛት አሸናፊ የሆኑት ሮምኒ ናቸው፡፡ ባራክ ኦባማ ከድላቸው በኋላ በቺካጎ-ኢሊኖይ ፣ ሚት ሩምኒም በቦስተን  ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገው የዘንድሮ ምርጫ በዚሁ ተቋጨ፡፡  ምርጫው እና ሂደቱፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ የሚመዘገቡ አሜሪካውያን ድምጽ የሚሰጡት በሁለት መንገድ  ነው፡፡ ከምርጫው በፊት በሚደረግ የቅድመ ድምጽ አሠጣጥ ስነሥርዓት እና የዕለቱ ዕለት በሚሰጥ ሥነስርዓት፡፡ በፊኒክስ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ምን እንደሚመስሉ ለማየት በለሊት ነበር የሄድኩት፡፡ምርጫ ጣቢያው ተራቸውን ጠብቀው በሥነ ሥርዓት በሚስተናገዱ መራጮች ተሞልተዋል፡፡መርጠው ከወጡት ውስጥ አንዳንዶቹን ለማነጋገር ሞከርኩ፡፡ በጣት ከሚቆጠሩት ውጭ ሁሉም ለመናገር ፍቃደኛ ነበሩ፡፡ ኦባማን በሚከተሉት የጤና ፖሊሲ ምክንያት ያለምንምን ማወላወል እንደመረጧቸው በድፍረት ይገልጻሉ፡፡ የምርጫ ጣቢያዎቹ እጅግ ዘመናዊ ከመሆናቸውም ባሻገር የምርጫ ሥነሥርዓቱ የትየለሌ ነው፡፡ አሜሪካ ዲሞክራሲዋን ለመላው ዓለም የምታሳየው በዚህ ምርጫ ነው፡፡ መራጮች አንዳንድ ቅሬታዎች ቢኖራቸውም በመጨረሻ ግን ‹‹በዲሞክራሲያችን እንኮራለን” ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡

Read 4339 times