Saturday, 10 November 2012 14:33

በመላው ዓለም ከ346 ሚ. በላይ የስኳር ህሙማን አሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

መራራው የስኳር ህመምአገራችንን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በ150 አገራት እ.ኤ.አ November 14 የዓለም ስኳር ህሙማን ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡ ቀኑ በዚህ ዕለት ታስቦ እንዲውል በአለም አቀፍ ደረጃ የተመረጠበት ምክንያት ሰር ፍሪድሪክ ባንቲንግ የተባለው የካናዳ ተወላጅ ሀኪምና ተመራማሪ ከምርመራ ባልደረቦቹ ጋር ኢንሱሊንን በ1922 ዓ.ም በማግኘቱና ይህ ታላቅ ተመራማሪ ሀኪም የተወለደው November 14 ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ተመራማሪው ኢንሱሊንን ለስኳር ህመም ሕክምና እንዲውል ማድረግ በመቻሉ እ.ኤ.አ በ1934 ዓ.ም ከሌሎች ሁለት ተመራማሪዎች ጋር የኖቤል ሽልማትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ዘንድሮ ለሃያ ሁለተኛ ጊዜ በአገራችን የሚከበረው የስኳር ህመም ቀን መሪ ቃል “የወደፊቱን ትውልድ በጋራ ጠብቁልን” የሚል ነው፡፡ በ1974 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር የኢንተርናሽናል ዲያቤትስ ፌዴሬሽን አባል ነው፡፡

ማህበሩ የስኳር በሽታ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ በማድረጉ፣ ህመምተኞቹና ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል እያከናወነ ያለው ተግባር የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ማህበሩ ህብረተሰቡ በስኳር ህመም ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር እና ራሱን ከበሽታው ለመከላከል የሚችልባቸውን መንገዶች እንዲያውቅ ለማድረግ የስኳር ህመም ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብር ቆይቷል፡፡ ዘንድሮም በዓሉ ህዳር 2 ቀን ከምኒሊክ አደባባይ አንስቶ ኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ ድረስ በሚካሄድ የእግር ጉዞና ህዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ በሚከናወን የምክክር መድረክ ይከበራል፡፡ በስኳር ህመም ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማዳበሩ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ያሉትንና በበሽታው ዙሪያ ከተለያዩ ፅሁፎችና ድረገፆች አሰባስበው ያገኙትን መረጃዎች እንድንጠቀምበት የሰጡን ዶ/ር አብርሃም አዳምን በአንባቢያን ስም እያመሰገንን የስኳር በሽታ መንስኤዎችንና መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆነውን ምግብ ለመፍጨት የሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮች (enzyms) በማመንጨት የሚታወቀው ቆሽት በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠንም ለመቆጣጠር የሚችሉ ኢንሱሊንና ጉሉካጉን የተባሉ ሁለት ንጥረ ቅመሞችን (Hormones) ወደ ደማችን ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ቅመሞችም በደማችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የማስተካከል ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ለምሣሌ ምግብ በምንመገብበት ወቅት በደማችን ውስጥ የሚኖረው የስኳር መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡ በዚህ ወቅትም ቆሽታችን ኢንሱሊን የተባለውን ቅመም በብዛት ያመርታል፡፡ ይህም ኢንሱሊን የተባለው ቅመም ስኳሩን ከደም ወደ ተለያዩ ህዋሣት እንዲገቡ በማድረግ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ያስተካክላል፡፡ ጉሉካጉን የተባለው ቅመም ከኢንሱሊን ተቃራኒ የሆነ ተግባር የሚያከናውን ሲሆን ቆሽት በደም ውስጥ ያለው የጉሉኮስ መጠን ሲቀንስ የሚያመነጨው ንጥረ ቅመም ነው፡፡ ይህ ለህይወታችን እጅግ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውኑ ቅመሞችን የሚያመነጨውና ለምግብ መፍጨት ሂደት ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ቆሽት በአንዳንድ ችግሮች ሊታወክና ተግባሩን በተገቢው መንገድ ማከናወን ሊሣነው ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜም የምግብ መፈጨት ሂደቱ ሊስተጓጐልና ከፍተኛ የጤና ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከል ዋነኛውም የስኳር በሽታ እያልን የምንጠራው ነው፡፡  የስኳር ህመም መገለጫው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ ቢሆንም፣ የበሽታው መንስኤ ግን ከበሽተኛ በሽተኛ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የስኳር በሽታ መንስኤን መሠረት በማድረግ፣ በሽታውን በአራት ዋና ዋና መደቦች መክፈል ይቻላል፡ እነዚህም፡-የመጀመሪያው አይነት የስኳር ህመም ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት  የስኳር ህመም እና በሌሎች በሽታዎች ወይም በመድሃኒቶች ሣቢያ የሚከሰት የስኳር ህመም በመባል ይታወቃሉ የመጀመሪያው አይነት የስኳር ህመም ቆሽታችን ኢንሱሊንን በበቂ መጠን ማምረት ሲያዳግተው ወይንም ጭርሱኑ ማመንጨት ሳይችል ሲቀር የሚከሰት ህመም ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ህመሙ ያለበት ሰው ከተመገበው ምግብ የሚያገኘውን ስኳር በጥቅም ላይ ማዋል ስለማይችል በደሙ ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ይህ አይነቱ የስኳር ህመም አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን አልፎ አልፎ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይም ይከሰታል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ባሉት የህክምና መረጃዎች፣ ይህንን ዓይነቱን የስኳር ህመም ለመከላከል አይቻልም፡፡ ይህ አይነት የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ኢንሱሊን ዕድሜ ልካቸውን በመርፌ ወይም በሌላ መንገድ ከውጭ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም ይህ የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ሰውነታቸው በበቂ ሁኔታ ኢንሱሊኒን አያመርትም ወይም የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም አይችልም፡፡ እነዚህ ህሙማን እንደ የመጀመሪያው አይነት የስኳር ህመምተኞች ኢንሱሊን ከሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ህሙማን ግልፅና የማያሻማ ምልክት አያሳዩም፡፡ ስለዚህም ብዙውን ጊዜ ህሙማኑ ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱት በሽታው ስር ከሰደደና ሰውነታቸው በጣም ከተጐዳ በኋላ ነው፡፡ ከ85%-90%  የሚደርሱት የስኳር ህሙማን የሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም ተጠቂዎች ናቸው፡፡ እንደ አሜሪካ የስኳር ህመም ማህበር ማሳሰቢያ፤ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆነ፣ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው፣ የቅርብ ዘመዳቸው (እናት፣ አባት፣ ወንድም ወይም እህት) በሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ተጠቂ የሆኑባቸው፣ በደማቸው ውስጥ ያለው የቅባት መጠን ከፍ ያለባቸው ሰዎች በየጊዜው የደማቸውን የስኳር መጠን እየተመረመሩ የስኳር በሽተኛ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በሽታው ሥር ሰዶ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ተገቢውን ህክምና ለማስጀመር ይጠቅማል፡፡ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት የስኳር ህመም ይህ በሽታ  ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ነፍሰጡሮች፣ ከዚህ ቀደም ክብደቱ 4 ኪ.ግ እና ከዚያ በላይ የሆነ ልጅ የወለዱ፣ የቅርብ የሥጋ ዘመዳቸው በበሽታው የተያዙ፣ ክብደታቸው 90 ኪሎና ከዛ በላይ የሆኑና ቀደም ሲል ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የስኳር ህመም የነበረባቸው እናቶች ከሌሎች ሴቶች ጋር ሲነፃፀሩ ለዚህ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ማንኛውም አይነት የስኳር ህመም ከነፍሰጡሮች በተጨማሪ በጽንሱ ላይ እስከሞት የሚያደርስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ እርጉዝ ሴቶች በሽታው የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ህክምና ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በሌሎች በሽታዎች ወይም በመድሃኒቶች ሳቢያ የሚከሰት የስኳር ህመም ይህ በሽታ የሚከሰተው አልፎ አልፎ ነው፡፡ መነሻው ከሌሎች በሽታዎችና መድሃኒቶች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሽታው በአብዛኛውን ጊዜ በስፋት የማይታይ በመሆኑ አንዳንድ መረጃዎች የስኳር በሽታን በሶስት ደረጃ ይከፍሉታል፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የስኳር ህመምን በመቀነስ የስኳር ህመም በሁለት እንደሚከፈል ይገልፃሉ፡፡ የስኳር ህመም የተለያዩ አይነት ምልክቶች ቢኖሩትም በአብዛኛው የተለመዱት በበርካታ ህሙማን ላይ የተስተዋሉት ወቅቱን ያልጠበቀ ተደጋጋሚ የረሃብ ስሜት፣ የእጅና እግር መዳፍ መደንዘዝ፣ የእይታ ብዥ ብዥ ማለት፣ የደረት ውጋት፣ ራስን መሳት፣ ውሃ ጥማት፣ ድካምና ቶሎ ቶሎ ሽንት መሽናት ናቸው፡፡ በሽታው በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በአደገኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የሚገኝ ሲሆን የአለም ጤና ድርጅት በ2012 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ346 ሚሊዮን በላይ የስኳር ህሙማን ይገኛሉ፡፡ ይህ ቁጥር በ2030 እ.ኤ.አ ከእጥፍ በላይ ሊያሻቅብ ይችላል፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑት የበሽታው ተጠቂዎች ደግሞ ነዋሪነታቸው መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ውስጥ ነው፡፡ ለቁጥሩ ማሻቀብ ዋንኛ ምክንያት ተብለው የተጠቀሱት፡- የአኗኗር ሁኔታ መለወጥ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ የሲጋራና የአልኮል ሱሰኛ መሆን፣ ቅባትና ጣፋጭ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ ናቸው፡፡ የስኳር በሽታ በህክምና ክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል ይችላል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ጤናማ አመጋገብን መከተል ያስፈልጋል፡፡ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በድንገት አደገኛ በሆነ ሁኔታ ወደ ታች ካሽቆለቆለ ለሞት ይዳርጋል፡፡ ለዚህ ሁኔታ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እንደታዩ በአፋጣኝ ስኳር ወይም ከረሜላ መውሰድ ይገባል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በድንገት ስለሚከሰት ህሙማኑ የስኳር በሽተኞች መሆናቸውን የሚገልጽ መረጃ (መታወቂያ) ሁልጊዜም መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአለም ሣይንቲስቶች የስኳር ህመምን በማያዳግም መልኩ ለማዳን የሚያስችሉ መድሃኒቶችንና ህክምናዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ተሌት እየታተሩ ሲሆን ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም እየታዩ ነው፡፡ ምርምሩ ውጤት አግኝቶ ለበሽታው የማያዳግም መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ ተገቢውን ጥንቃቄ በመውሰድ በሽታው እንዳይከሰት ለማድረግ መሞከር፣ ከተከሰተ ደግሞ ከበሽታው ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት ማድረግ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡

Read 6799 times