Saturday, 10 November 2012 14:23

የሊስትሮ ሳጥን ጀርመን ቤተ-መንግሥት ገባ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

የጀርመን ፕሬዚዳንትና ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጫማ ሊጠራረጉ ነበርሊስትሮ ምን ማለት ነው?  ብትባሉ፣ ያለአንዳች ማመንታት “ጫማ ጠራጊ ወይም ጫማ አሳማሪ ነዋ!” እንደምትሉ መገመት አያቅትም፡፡ ልክ ናችሁ፡፡ ቃሉ ከየት መጣ? ወይም የቃሉ ሥረ - መሠረት (ሥርወ - ቃል) ኢትዮጵያዊ ወይስ የውጭ? ብትባሉ ግን ግር ሊላችሁና - ትንሽ ያዝ ሳያደርጋችሁ እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ብዙዎቻችን ቃሉን ከመጠቀም በስተቀር፣ “ከየት መጣ? አገራችን መቼ ነው ቃሉን መጠቀም የጀመረችው?” የሚለው አሳስቦንና አስጨንቆን የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም “መሠረቱ የውጭ ቃል ነው” ካላችሁ ትክክል ናችሁ፡፡ በስፋት እየተጠቀምንበት የሚገኘው ሊስትሮ የሚለው ቃል ሥረ - መሠረቱ “ሊስትሯ” የሚለው የላቲን ቃል ነው፡፡ ቃሉ በአገራችን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ነው፡፡ ወራሪዎቹ ጫማ የሚጠርግላቸው (የሚያሳምርላቸው) ሰው ሲፈልጉ “ሊስቱራ፣ ሊስቱራ” እያሉ ይጣሩ ነበር፡፡

ሕዝቡም እነሱን ተከትሎ “ሊስትሮ” በማለት መጥራት ጀመረ ያሉን፣ በበርሊን - ጀርመን የሊስትሮስ ፕሮጀክት መሥራችና ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ዳዊት ሻንቆ ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ሊስትሮ የሚለው ቃል ይዘት ሰፍቶ ዝቅ ብለው የሰው ጫማ ፏ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆን መንገድ ዳር ቆሎ፣ መፋቂያ፣ ሶፍት፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ … የሚሸጡ፣  መኪና በማጠብና በመጠበቅ (ፓርኪንግ) ሕይወታቸውን ለማስተካከልና የተሻለ ነገር ለመፍጠር የሚጥሩ ወጣቶችና ሰዎች ማዕከላዊ መጠሪያ እንደሆነ ኢንጅነሩ ተናግረዋል፡፡ የሊስትሮ ፕሮጀክት በበርሊን የተመሠረተው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነው፡፡ ሙያው በጀርመን ሕዝብ ዘንድ ክብርና እውቅና እንዲያገኝ በተለያዩ ዘዴዎች ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት ሰፊ ተቀባይነት እንዳገኘ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አርት፣ ኤግዚቢሽን፣ ውይይት … በማዘጋጀት ያደረጉት ጥረት ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከተመዘገቡት ስኬቶች አንዱና ዋነኛው ከዛሬው የጀርመን ፕሬዚዳንት በፊት የአገሪቷ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሆርስት ኰለር ከአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጋር ጫማ እንዲጠራረጉ ያስማሙበት ጥረት ነው፡፡ ይህም፤ የሊስትሮስ ፕሮጀክት ከሕዝቡ አልፎ በፖለቲካው መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ያመለክታል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ያለመታደል ሆነና ፕሬዚዳንቱና ኃይሌ ጫማቸውን ሳይጠራረጉ ቀሩ፡፡ ከ2006 ጀምሮ የሊስትሮስ ፕሮጀክት ደጋፊ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኰለር፤ በዓለም ባንክ ያገለገሉ ሰው ስለነበሩ አፍሪካን በስፋት ያውቃሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ሲይዙ፣ “አሁን ያለውን ዓለምአቀፋዊ ችግር መፍታት የምንፈልግ ከሆነ፣ የዛሬው ትውልድ፣ አፍሪካን እንደ ተረጂ ሳይሆን እንደ ማዕከላዊ ጉዳዩ ማየት አለበት ብዬ አምናለሁ …” ብለው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ በ2010 “እባክዎን ይምጡና ጫማ በመጥረግ ያግዙን” በማለት የሊስትሮስ ፕሮጀክት ጋበዛቸው፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ፊት-ለፊት ሳይሆን ከአማካሪያቸው ጋር ብዙ ውይይት ከተደረገ በኋላ ተስማሙ፡፡ የተፈለገው እሳቸው ጫማ እንዲጠርጉ ሳይሆን ጫማ ሲጠርጉ የሚነሱት ፎቶግራፍ የጀርመንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ አገለግላለሁ ካሉት በላይ የሚናገር የፖለቲካ መልዕክት ስላለው ነበር፡፡ የማንን ጫማ ይጥረጉ? የሚለውም ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ከብዙ ውይይትና ክርክር በኋላ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በጀርመን ማራቶን ብዙ ጊዜ ስላሸነፈ፣ ተወዳጅነት ስላለውና የኢትዮጵያንም ገጽታ የለወጠ ስለሆነ እሱ እንዲሆን ተወሰነና ከእሱም ጋር ውይይት ተካሄደና “እኔ ነኝ በቅድሚያ የእሳቸውን ጫማ መጥረግ ያለብኝ፡፡ እሳቸው ከፈለጉ ከዚያ በኋላ የእኔን ይጥረጉ” በማለት ተስማማ፡፡ ከ2010 የጀርመን ማራቶን ውድድር በኋላ የጫማ ጠረጋው እንዲካሄድ ቀጠሮ ተያዘ፡፡ በመጨረሻ ግን ኃይሌ በኒውዮርክ ማራቶን መወዳደር ስለመረጠ፣ “በጀርመን ማራቶን ከተወዳደርኩ ለኒውዮርኩ የማገገሚያ ጊዜ አይኖረኝም” በማለት የጀርመኑን ማራቶን ሰረዘው፡፡ “በዚህ ጊዜ ይህም ትልቅ ሥራ ስለሆነ ወጪህን በሙሉ እንችልሃለንና እባክህን ለሁለት ቀን ናልን” በማለት ኃይሌን ለመንነው፡፡ እሱ ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ ፕሬዚዳንቱም ከሥልጣን ወረዱ፡፡ ዕቅዳችንም ኃይሌ እንቢ በማለቱ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ዝቅ ብሎ መሥራት የሚያስከብር እንጂ የሚያሳፍርና የሚያሳንስ አይደለም፡፡ ኃይሌ ትልቅ ሥራና አስተዋጽኦ ያለው ሰው ቢሆንም፣ ያቺን ነገር ቢያደርግ ኖሮ ለአገሩ ልጆች ብዙ ሳይደክም የሚሰጠው ነገር ከፍተኛ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ላደረግንለት ተደጋጋሚ ጥያቄ እሺ! ወይም እንቢ! የሚል ምላሽ ባለመስጠቱ በጣም አዝናለሁ በማለት ኢ/ር ዳዊት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌላው አቢይ ነጥብ የሊስትሮችን ሁኔታ አመለካከትና ሐሳብ እንዴት ነው ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ማቅረብና ማሳየት የሚቻለው? የሚል ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ “ደብዳቤ ለዓለም” የሚል ፕሮጀክት አዘጋጅተው 3,500 ጫማ ጠራጊዎችን በተለያየ ጊዜያት አሰባስበው የሚመስላቸውንና ዓለም ማወቅ አለበት ብለው የማያስቡትን ነገር እንዲጽፉ በማድረግ ምላሽ መገኘቱን ኢ/ር ዳዊት ገልጸዋል፡፡  የሊስትሮስ ፕሮጀክት፣ “ያ የሚረገጠው ቆሻሻና አመዳም የሊስትሮ ሳጥን ራሱ ይናገር በማለት ደብዳቤውን ብቻ ሳይሆን 3,500 የሊትስሮ ሳጥኖችን የልጆቹ (አምባሳደሮች) አድርገው ወደ በርሊን በመውሰድና የተወሰኑ ደብዳቤዎችን በመተርጐም ከተለያዩ አርቲስቶች ሥራ ጋር በማድረግ የ14 ቀን ኤግዚቢሽን አዘጋጀተው ሕዝብ እንዲመለከተው አደረገ፡፡ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የጀርመን ፕሬዚዳንት ነበሩ - ሆርስት ኰለር ሳይሆኑ ከእሳቸው በኋላ ሥልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ክርስትያን ቩልፍ ናቸው፡፡ ያንን ኤግዚቢሽን 560ሺህ ሕዝብ እንደጐበኘው ኢ/ር ዳዊት ገልጸዋል፡፡ ደብዳቤዎቹና ጽሑፎቹ ሕዝቡን ከማሳቅና ከማዝናናታቸውም በላይ በተለየ ሁኔታ እንዲያያቸውና እንዲያውቋቸው ተደርጓል ያሉት የፕሮጀክቱ ፕሬዚዳንት፤ “በመሠረቱ የሥራን ምንነትና ክቡርነት ለጀርመን ሕዝብ መንገርና ማውራት ባያስፈልግም “ኢትዮጵያም ውስጥ ድህነትና ችግር ብቻ ሳይሆን ለሥራ የሚጥሩና የሚሯሯጡ ባለራዕይ ኢንተርፕረነሮች እንዳሉ ያሳየንበት ነበር” ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ክርስትያን ቩልፍ ኤግዚቢሽኑኑ ሲከፍቱ፤ “እኔም ራሴ ሊስትሮ ነኝ፡፡ የስምንት ዓመት ልጅ ሆኜ እናቴ ታናሽ እህቴን ወልዳ ሐኪም ቤት በነበረችበት ወቅት በአቅራቢያችን ወደነበረ አንድ የነዳጅ ማደያ ሄጄ የመኪና መስተዋት በመወልወል በአምስት ቀን ከአምስት ዶችማርክ በላይ አግኝቻለሁ፡፡ በዚያ ዕድሜ የሚያጋጥምህ ነገር አይረሳህም፡፡ አንድ ፊያት 500 ያሽከረክር የነበረ ሰው አንድ ዶችማርክ ሰጠኝ፡፡ ትላልቅ መኪኖችን የሚያሽከረክሩ ሰዎች ደግሞ ዝርዝር ስለማይኖራቸው ለሰጠኋቸው አገልግሎት ብዙ ጊዜ ሳይከፍሉኝ ነበር የሚሄዱት፡፡ በራስህ ተነሳሽነት በፈጠርከው ሥራ የምታገኘው የመጀመሪያ ገቢህ በወደፊት ሕይወትህ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሥራ ምን እንደሆነና አንድ ነገር ካበረከትክ ጠቃሚ ነገር እንደምታገኝበት የተማርኩት በዚያን አጋጣሚ ነበር” በማለት የሥራን ክቡርነት ገልጸዋል፡፡ የሊስትሮዎች አምባሳደር ሆኖ ጀርመን በቤተ መንግሥት የሚቀመጥ አንድ የሊስትሮ ሳጥን ለፕሬዚዳንቱ ተሰጥቷል፡፡ የዚያ ፕሮጀክት ሌላው ስኬት ኤግዚቢሽኑን ካቀረቡ በኋላ ከ2,600 ተማሪዎች በላይ የሊስትሮ ሳጥን ወስደው ጫማ እንዲጠርጉ በማድረግ፣ ዝቅ ብሎ መሥራት የበታችነት እንዳልሆነ ለዚያ አገር ያበረከትነው አስተዋጽኦ ነው ያሉት ኢ/ር ዳዊት፤ ይህ በዚያ አገር ጠንክሮ መሥራትንና ችግርን ተረድቶ መፍትሔ ፈላጊነትን ያስተማረው ተግባር እዚህም መታየት፣ መታወቅና መለመድ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ከተለያዩ ት/ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች በዚህ ፕሮጀክት እንዲሠሩ ተደርጓል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በበርሊን-ጀርመን በርካታ አንፀባራቂና ስኬታማ ተግባር የፈፀመው የሊስትሮስ ፕሮጀክት በአገር ውስጥስ ምን ሠርቶ ይሆን? ሳትሉ እንደማትቀሩ እገምታለሁ፡፡ ይህ ፕሮጀክት በሊስትሮ፣ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታና በሕጋዊነት ጥያቄ ዙሪያ እየሠራ ነው፡፡ የሊስትሮ ማኅበር የእርዳታ ድርጅት አይደለም ያሉት ኢ/ር ዳዊት፤ የሐሳብ ማፍለቂያ፣ የውይይትና የግንዛቤ መፍጠሪያ ማዕከል በመሆን መንግሥት፣ መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ … በአጠቃላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የባህርይና የአመለካከት ለውጥ በማድረግ ሊስትሮች፤ ነገ ትልቅ ቦታ እንደርሳለን የሚል ዓላማ ይዘው ሥራ ሳይንቁ ዝቅ ብለው በመሥራት፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፉ ባለ ራዕይ ኢንተርፕረነሮች መሆናቸውን ተረድቶ ለእነሱ ፍቅር፣ ለሥራቸው ክብር በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው፣ … አስተባባሪ አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የሊስትሮችን ችግር በማጥናት፣ ፀሐይና ዝናም የሚፈራረቅባቸው መሆኑን ተረድቶ፣ መጠለያ ወይም የሊስትሮ ጎጆ እንዲሠራላቸው ለመዲናዋ አስተዳደር ሐሳብና ዲዛይን ሠርቶ አቅርቧል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ሐሳቡን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉ ያስመሰግነዋል ያሉት ኢ/ር ዳዊት፤ እነሱን አስወጥቶ ፕሮጀክቱን ለፔፕሲ መስጠቱ ግን አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፔፕሲ ኩባንያ እኛ ያቀረብነውን ዲዛይን ትንሽ ለወጥ በማድረግ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞች ጎንደር፣ ባህርዳርና ሀዋሳ እንዳሠራ ማየታቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የሊስትሮ ጎጆ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ “እነዚያን ጎጆዎች ዛሬ ሊስትሮ እየሠራባቸው አይደለም፡፡ ዛሬ ኪዮስክ፣ መጻሕፍትና የተለያዩ ነገሮች መሸጫ ሆነዋል፡፡ ያኔ ሊስትሮ የነበረ ሰው ዛሬ አድጐ አነስተኛ ንግድ ጀምሮ፣ ቤተሰብ መሥርቶ፣ ከጐኑ ላስቲክ ወጥሮ የከተማዋን ገጽታና ውበት በሚያበላሽ መልኩ እየተጠቀመበት ነው፡፡ እኛ ቀደም ሲል ያቀረብነው ዲዛይን የነበረበትን ችግር በማጥናት የከተማዋን ውበት በጠበቀ መልኩ ዲዛይኑን አሻሽለን ለታለመለት ዓላማ በማዋል ሊስትሮዎች ብቻ የሚጠቀሙበት መጠለያ እንድንሠራ መንግሥት ፈቃድ እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው፡፡ መጠለያዎቹን የሚሠሩ ድርጅቶችም እያፈላለግን ነው፡፡ ለምሳሌ ልደታ አካባቢ እንዲሠራ ሀበሻ ከተባለ ድርጅት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ከሚሌኒየሙ አንስቶ እየተሠራበት ያለው “ሊስትሮስ ቮይስ“ ፕሮጀክት የተባለው ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ በመንግሥትና በፓርላማ ፀድቆ “የሊስትሮ ቀን” ከዓመታዊ የበዓላት ቀናት አንዱ ሆኖ በግልጽ እንዲመዘገብና እንዲታወጅ ነው፡፡ ሊስትሮች የተለያዩ በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ ቀን ቀን እየሠሩ ማታ የሚማሩ ልጆች አሉ፡፡ በአገሪቷ ትምህርት ደግሞ 8ኛ ክፍል የወደቀ ሰው በፍፁም ደግሞ የመማር ዕድል የለውም፡፡ ለምሳሌ በአንጋፋው ዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ከሚማሩና የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት ያለፉት ተማሪዎች ከፍተኛ ቁጥር ከመቶ 64 እንደነበር ኢ/ር ዳዊት ገልጿል፡፡ “ይህ ማለት በየዓመቱ ከመቶ ተማሪዎች 36ቱ ይወድቃሉ፡፡ እነዚህ ወዳቂ ተማሪዎች እነማን ናቸው? ተብለው ሲፈተሹ ከ90 በመቶ በላይ እየሠሩ ማታ የሚማሩ ሊስትሮች ልጆች ናቸው” ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በምኒሊክ ት/ቤት ከ5ኛ-8ኛ ክፍል ቆሎ፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ፣ … እየነገዱ ጫማ በመጥረግ የሚማሩ ተማሪዎች ስንት ይሆናሉ? የሚል መጠነኛ ጥናት አድርገው ከመቶ ተማሪዎች 61ዱ የተለያዩ ነገሮች እየሠሩ የሚማሩ መሆናቸውን እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡ ዩኒፎርም መልበስ ግዴታ ስለሆነ፣ አንድ ጫማ ጠራጊ ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ ዩኒፎርም ብቻ ለመግዛት ስንት ቀን መሥራት አለበት? ሲሉ አጥንተው፣ በቀን 15 ጫማ ይጠርጋል በሚል ግምት፣ ዩኒፎርም ለመግዛት 31 ቀን መሥራት አለበት፡፡ እነዚህ ተማሪዎች 31ዱን ቀን በሥራ ሳይሆን በትምህርት እንዲያሳልፉ ከ5ኛ-8ኛ ክፍል እየሠሩ ለሚማሩ ተማሪዎች በዕርዳታ መልክ ሳይሆን ያለባቸውን ችግር ለማወቅ ዩኒፎርም አቅርበው “እኛ ዩኒፎርም እንሰጥሃለን፤ አንተ ደግሞ መረጃ ስጠን” በማለት አምስት ጥያቄዎች አቀረቡላቸው፡፡ ጥያቄዎቹም ት/ቤት ጥሩ ውጤት እንዳታመጣ የሚያደርግህ ችግር አለብህ ወይ? በት/ቤትህ የሚታዩ ችግሮች ምንድናቸው? በትምህርትህ ስንተኛ ክፍል እደርሳለሁ ብለህ ታስባለህ? አንተስ ትልቅ ስትሆን ለዚህ ት/ቤት ምን ድጋፍ ታደርጋለህ? የሚሉ ነበሩ፡፡ ከደረሷቸው ደብዳቤዎች ሁሉም መላሾች መቶ ፐርሰንት ዋነኛ ችግሮቻችን መምህራኖች ናቸው፡፡ ምከሩልን ወይም ሌላ አምጡልን፣ ወይም በጥናት አግዙን፣ ሁለተኛ ሽንት ቤታችንን ዝጉት ወይም አድሱልን፣ ማየት የተሳናቸው ደግሞ የት/ቤቱ መንገዶች አስቸጋሪ ናቸው አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሰፈራችን መጫወቻ ሜዳ የለም፤ እዚህ ያለውም አባጣ ጐርባጣ ስለሆነ እባካችሁ ይደልደልልን…” የሚሉ ጥቆማዎች እንደደረሷቸው ተናግረዋል፡፡ “በዚህ መሠረት ለማስተማሪያ እንዲሆን ዘንድሮ የሴትና ወንድ ሽንት ቤት ለመለየት ግንባታ እንጀምራለን፡፡ እዚህ መመላለስ ከጀመርኩ በኋላ 12 የኮንዶሚኒየም ግቢዎች አይቻለሁ፡፡ ሁሉም የልጆች መጫወቻ የላቸውም፡፡ ልጆች የሚማሩት በጨዋታ ነው፡፡ ስለዚህ እሁድ እሁድ መኪና ቀለል ስለሚል አስፋልት ላይ ነው የሚጫወቱት፡፡ ስለዚህ በት/ቤት እንኳ ጥሩ መጫወቻ እንዲኖራቸው ዘንድሮ የምኒሊክን ት/ቤት ሜዳ እናሠራለን፡፡ ልጆቹ የምሳ መመገቢያ ቦታ የላቸውም፡፡ አንድ ልጅ ክፍል ውስጥ ምሳውን ቢበላ ቀጥሎ የሚገባው መምህር “ማነው እዚህ ምሳ የበላው?” በማለት ከክፍል ያባርረዋል፡፡ ስለዚህ ምሳ መብያ እንሠራላቸዋለን፤ የት/ቤቱንም ግቢ መንገዶች እናስተካክላለን፡፡ “የእውቀት ጠብታ” በምንለው ዘዴ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በየወሩ አውሮፕላን አብራሪም ሆነ ሐኪም፣ አንድ አንድ ባለሙያ እየጋበዝን …ስለሙያው፣ ስለደረሰበት ችግርና ስኬት ለተማሪዎቹ እንዲያወራ እናደርጋለን፡፡  የመምህራን ጥራት ችግርን ለመቅረፍ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመቅጠር (የኪስ ገንዘብ በመክፈል) ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሂሳብ፣ ቋንቋ፣ … በሳምንት አንድ ቀን እያስተማሩ እንዲረዷቸው እናደርጋለን፡፡ ይህን የምናደርገው ሠራን ለማለት ሳይሆን ተማሪው አሉብኝ ብሎ የተናገረውን ችግር መረዳታችንን ለመግለጽ፣ እነዚህ ችግሮች በምኒሊክ ት/ቤት ብቻ ሳይሆን በተቀሩት ት/ቤቶችም የተንሰራፉ ስለሆነ፣ ኅብረተሰቡ እነዚህን ችግሮች ተገንዝቦ በተቻለው አቅም ምላሽ እንዲሰጥ አርአያ ለመሆን ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡ ሊስትሮዎች ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ከመቶ ልጆች 40ዎቹ እየሠሩ በሚማሩባቸው 10 የመንግሥት አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ርዕሰ መምህራንና አስተዳደር ጋር ባደረግነው ውይይት 10ሩም ት/ቤቶች ከ1ኛ-8ኛ ክፍል ያሉ 50 ተማሪዎች ተቀብለው በነፃ ሊያስተምሩ ተስማምተዋል፡፡ ምዝገባም የጀመሩ አሉ፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችና ባለሀብቶች፣ ከፍለው መማር የማይችሉ ልጆችን እንዲያስተምሩልን ብንጠይቅ ብዙዎቹ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን፡፡ ለምሳሌ ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 10 ልጆችን ተቀብሎ ዩኒቨርሲቲ እስኪገቡ ድረስ ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ሸፍኖ ለማስተማር ተስማምቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈቃደኝነት ከብዙ ድርጅቶችና ባለሀብቶች እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን፡፡ እስካሁን ያልጠየቅነው “ጥያቄያችሁን ተቀብለናል፤ ይህን ያህል ልጅ ስጡን” ቢሉን ማንን ነው የምንሰጠው? ስለዚህ በቅድሚያ የተለያዩ ነገሮች በመሸጥ የሚተዳደሩ ሊስትሮችን ማደራጀት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ማደራጀቱን በተመለከተ ባደረግነው የአንድ ቀን ኮንፈረንስ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ፖሊሶች፣ ቁጠባ ማኅበራት … ተገኝተው ነበር፡፡ ይኼ በጣም የሚመሰገን ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት፣ ሊስትሮዎቹ፣ እኛ ሕጋዊ አይደለንም፡፡ በዚህ የተነሳ ከፖሊስ ጋር ከፍተኛ ግጭት አለ፤ ማኅበረሰቡ ከደቡብ የመጣነውን እንደሌባ ነው የሚያየን፣ እኛ የአገሪቷ ዜጐች ነን፡፡ በየትኛውም የአገሪቷ ክልል ተዘዋውረን የመኖርና የመሥራት ሕገ - መንግሥታዊ መብት አለን፡፡ ስለዚህ ሕጋዊ ፈቃድ ይሰጠን፣ መተዳደሪያችን ሥራችን ነውና መደበኛ መሥሪያ ቦታ ይሰጠን፤ … የሚሉ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በፖሊስ ወይም በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚመለሱ ስላልሆኑ፣ በፌዴራል ደረጃ ውሳኔ የሚሹ ናቸው፡፡ ሊስትሮዎቹ እንድናደራጃቸው እየተወተወቱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሊስትሮዎች የመጡት ከደቡብ ክልል ስለሆነ በመኖሪያ ሳይሆን በሥራ አካባቢ ልጆቹን ለማደራጀት ከደቡብ ልማት ማኅበር ጋር እየሠራን ነው፡፡ “ፍሮም ሹሻይን ቱ ሹሜከር” የሚባል ፕሮጀክት አለን፡፡ ሉም ጫማ ጠራጊ ለራሱ ብቻ አይደለም የሚኖረው ቤተሰብ የሚመሩና የሚያስተዳድሩ አሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ልጆቹን ሙያ ማስተማር ነው፡፡ የጫማ አሠራር፣ የጫማ ስፌት፣ …ሙያ ለማስተማር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየተዋዋልን ነው፡፡ በተለያዩ የስፌት ሥራዎች ሙያ የሚቀስሙበትን መንገድም እያሰብን ነው በማለት ኢ/ር ዳዊት ሻንቆ ሊስትሮስ  ፕሮጀክት እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት አስረድተዋል፡፡

Read 3457 times