Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Monday, 05 November 2012 09:07

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በምድብ 3 ከዛምቢያ፤ ከናይጄርያና ከቡርኪናፋሶ ጋር የተደለደለው ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ትኩረት አገኘ፡፡ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መብቃቷን በርካታ ዘገባዎች በአድናቆት አውስተዋል በምድብ 3 የሚገኙ ተፋላሚዎች ለዋልያዎቹ ከባድ ግምት እንደሰጡም ከድልድሉ በኋላ በተገለፁ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ናይጄርያ እና ዛምቢያ ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያደርጉትን ዝግጅት ሰሞኑን በዝርዝር ሲያስታውቁ ኢትዮጵያ እና ቡርኪናፋሶ ምን አይነት የዝግጅት መርሃ ግብር እንደያዙ እስከ ትናንት አልታወቀም፡፡ በወጣው የጨዋታ ፕሮግራም መሰረት ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሁለቱን ጨዋታዎች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አምስተኛ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር 2013 በገባ በ21ኛው ቀን እንዲሁም በ14ኛው ጨዋታ ደግሞ 2013 በገባ በ25ኛው ቀን ከቡርኪናፋሶ ጋር በኔልስፑሪት በሚገኘው የሞምቤላ ስታድዬም ታደርጋለች፡፡ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ 2013 በገባ በ29ኛው ቀን ከናይጄርያ ጋር በሩስተንበርግ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም ታካሂዳለች፡፡


ደቡብ አፍሪካ 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት 52.12 ሚሊዮን ዶላር በበጀት አንቀሳቅሳለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጆች በውድድሩ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚኖርና በዓለም ዋንጫው የስታድዬሞች ድምቀት የነበረው ቩቩዜላ መጠቀም እንደሚቻል ከሰሞኑ ገልፀዋል፡፡ በ2012 የመጨረሻ ሳምንታት የውድድሩን 400ሺ ትኬቶች ሊሸጥ መዘጋጀቱን የገለፀው አንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ከምድብ ድልድሉ በፊት 20ሺ ትኬቶች ተሸጠው እንደነበረ ጠቅሶ ከድልድሉ በኋላ ኢትዮጵያ 15ሺ እንዲሁም ዛምቢያ 10ሺ ትኬቶችን ለመግዛት በፌደሬሽናቸው በኩል መጠየቃቸውን ዘግቧል፡፡
አርኤስኤስኤፍ የተባለ የእግር ኳስ ውጤቶች እና አሃዛዊ መረጃዎች አሰባሳቢ ድረገፅ በሰራው ስሌት ኢትዮጵያ ከ10ኛው በፊት በ9 የአፍሪካ ዋንጫ በነበሯት ተሳትፎዎቿ በአፍሪካ ዋንጫ አጠቃላይ ውጤታማነቷ 33.33 በመቶ ይለካል፡፡ በምድብ 3 የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች ላይ የኢትዮጵያ የማሸነፍ እድል ሲሰላ ደግሞ በዛምቢያ ላይ 35.71 በመቶ ፤በናይጄርያ ላይ 16.67 በመቶ እንዲሁም በቡርኪናፋሶ ላይ 50 በመቶ ስኬት እንዳላት አመልክቷል፡፡
ምድብ 3 ከድልድሉ በኋላ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ሰውነት ከምድብ ድልድሉ በኋላ በሰጡት አስተያየት በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏን አገራችን እና የሴካፋ ዞን የማያፍሩበትን ውጤት እናስመዝግባለን ብለዋል፡፡ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው እስከ ሩብ ፍፃሜ የመድረስ አቅም እንዳላቸው የሚናገሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ተጨዋቾቻቸው በአፍሪካ ዋንጫው ከኮትዲቯር ጋር ለመገናኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡ ብዙዎች ከምድቡ ናይጄርያ እና ዛምቢያ ማለፋቸውን ቢገምቱም ኢትዮጵያና ቡርኪናፋሶ ስለመሆናቸው ማን ያውቃል ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት በምድቡ የመክፈቻ ጨዋታ ዛምቢያን በማሸነፍ በምንፈጥረው ተስፋ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖረን እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡
ሲዲዋ ለተባለ ለቡርኪናፋሶ ትልቅ ጋዜጣ የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ቤልጅማዊው ፖል ፑት በሰጡት አስተያየት ከናይጄርያ እና ከዛምቢያ ይልቅ የምሳስበን ኢትዮጵያ ናት ብለዋል፡፡‹ ዛምቢያ እና ናይጄርያ እናውቃቸዋለን፡፡ ዋናው ስጋታችን ምንም የማናውቃት ታላቋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ተገቢውን ጥናት በማድረግ ለሁሉም ቡድን የተሟላ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ቢያንስ ምድብ ማጣርያውን ለማሸነፍ እንፈልጋለን› በማለትም ፖል ፑት ተናግረዋል፡፡ የቡርኪናፋሶ የስፖርት ሚኒስትር በበኩላቸው‹ናይጄርያ የመብረቅ ጦርነት አይደለችም፤ ኢትዮጵያ እየተነሳች ነው፤ ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ የምትገባው ዛምቢያ ማጣርያውን ተቸግራ ያለፈች ናት፡፡ በቀላሉ የምድብ ማጣርያውን በማለፍ ጥሎ ማለፍ እንገባለን› ብለዋል፡፡ የቡርኪናፋሶ አሰልጣኝ የሆኑት የ55 ዓመቱ ቤልጅማዊው ፖል ፑት ከፈረሰኞቹ በፊት የጋምቢያን ብሄራዊ ቡድንና ከዚያም በፊት የቤልጅዬም ክለቦችን በማሰልጠን ልምድ ያላቸው ሲሆኑ የፈረሙት ለሶስት ዓመት የኮንትራት ቅጥር ነው፡፡
አረንጓዴዎቹ ንስሮች በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቅ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ሲሆን በ2002፣ በ2004፣ በ2006 እና በ2010 እኤአ ሶስተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ኢኳቶርያል ጊኒ እና ጋቦን ባዘጋጁት የ2012ቱ 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ አልተሳተፈም ነበር፡፡ ዋና አሰልጣኙ የቀድሞ ተጨዋች ስቴፈን ኬሺ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ ዳንኤል አሞካቺ ነው፡፡
ናይጄርያ ከዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በ2010 አንጎላ ባዘጋጀችው 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሩብ ፍፃሜ ተገናኝታ በመለያ ምቶች አሸንፋ ግማሽ ፍፃሜ ገብታለች፡፡ ከቡርኪናፋሶ ጋር የተገናኘችው ደግሞ አገሪቱ አፐር ቮልታ ተብላ እየተጠራች በጋና 1978 እኤአ ላይ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን 4ለ2 አሸንፋለች፡፡ በ1982 እኤአ ላይ ደግሞ ሊቢያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ናይጄርያ በምድብ ማጣርያ ኢትዮጵያን 3ለ0 ረትታለች፡፡ የናይጄርያ አምበል የሆነውና ለቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ የሚጫወተው የ32 ዓመቱ ጆሴፍ ዮቦ ለኤምቲኤን ፉትቦል ሲናገር ተመጣጣኝ ግን መጥፎ ያልሆነ የምድብ ድልድል ደርሶናል ብሎ በአፍሪካ ትንሽ ተብሎ የሚናቅ ቡድን እንደሌለ ማወቅ ያስፈልጋል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ክሪስትያን ቹኩ እና ፓትሪክ ፓስካል የተባሉት የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ደግሞ ምድብ ሦስትን ቀላልና አመች ብለውታል፡፡ ከሶስቱ ቡድኖች የሚቀለው ሻምፒዮኑ ዛምቢያ እንደሆነ የገለፀው ቹኩ የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሲሆን ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያን ያህል የሚቸግር አይሆንም ብሏል፡፡ ፓትሪክ ፓስካል በበኩሉ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሰልጣኙ ከበርካታ ምርጥ ተጨዋቾች ምርጦቹን በመያዝ መሳተፋቸው ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
የመዳብ ጥይቶች ወይም ቺፖሎፖሎ ተብሎ የሚጠራው የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሻምፒዮናነቱን ሊያስጠብቅ የሚሳተፈው በአሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ እና በአምበሉ ክሪስቶፈር ኮቶንጎ በመመራት ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካን ኮሳፋ ካፕ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በ2007 እኤአ ላይ በኔልስፕሩዊት ድል ማድረጉን በማስታወስ የተናገረው በ1998 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው እና የአገሪቱን የእግር ኳስ ፌደሬሽን የሚመራው ካሉሻ ቡዋሊያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሴካፋ ውክልና የኒኮላስ
ሙንሶኜ ምክር
የሴካፋ ምክርቤት ዋናፀሃፊ የሆኑት ኒኮላስ ሙንሶኜ የምስራቅ አፍሪካ ወኪሏ የምትገኝበትን ምድብ 3 የሞት ምድብ ብለውታል፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በውድድሩ ብዙ የማይታወቁ ጥቁር ፈረሶች ቢሆኑም ትልቅ የፉክክር አቅም እንደሚኖራቸው እና አስደንጋጭ ድሎችን እንደሚያስመዘግቡ እጠብቃለሁ ያሉት ኒኮላስ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ቡድን ጥንካሬ አለው ኢትዮጵያም የዚህ ብቃት ምሳሌ ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን የወከለ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን ስለያዘች የዞኑ አገራት ድጋፋችንን እንሰጣታለን ያሉት ዋና ፀሃፊው ኒኮላስ ሙንሶኜ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫው ጥብቅ ትኩረት በማድረግ፤ ቅድመ ዝግጅቱን በቶሎ በመጀመርና በቂ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ በማዘጋጀት መስራት እንዳለበት መክረዋል፡፡ ከጎል ድረገፅ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የሴካፋ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችው የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን በአመራር ለውጥ የወሰዳቸው መልካም እርምጃዎች አስተዋፅኦ በማድረጋቸው ነው ብለው የዞኑ እግር ኳስና ተጨዋቾቹ በአህጉራዊ ደረጃ ያላቸው ተፎካካሪነት እያደገ መሄዱን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የኬንያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን እና የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሃላፊዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፏ መደሰታቸውን ሲገልፁ ጎረቤታቸው በውድድሩ ላይ በሚኖራት ተሳትፎ ሁላችንንም የሚያኮራ ውጤት ታስመዘግብ ዘንድ ተመኝተዋል፡፡
የዛምቢያ እና የናይጄርያ ዝግጅት
የምድብ 3 ትንቅንቅ የሚከፈተው ኔልስፑሪት በሚገኘው የሞምቤላ ስታድዬም ኢትዮጵያ ከሻምፒዮናዋ ዛምቢያ ጋር በሚገናኙበት ጨዋታ ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በ2010 እኤአ ላይ በሴካፋ ካፕ ተገናኝተው ኢትዮጵያ 2ለ1 ያሸነፈችበት ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙበት ነው፡፡
የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታን ከኢትዮጵያ ጋር ከማድረጉ በፊት ከኖርዌይ ጋር የመጨረሻውን የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ማቀዱን ፌደሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ዛምቢያ ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት የምታደርገውን ዝግጅት በህንድ ጎአ በሚገኝ ካምፕ ለማከናወን የወሰነች ሲሆን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት በተመሳሳይ ካምፕ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ለመጀመርያ ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቷ ለውሳኔው ምክንያት ነበር፡፡ በዚሁ ካምፕ ብሄራዊ ቡድኑ ከጎአ ምርጥ እና ከህንድ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችን የማድረግ እቅድ ይዟል፡፡ ለ10 ቀን የካምፕ ዝግጅቱ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ከህንድ ሁለት ኩባንያዎች የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ አግኝቷል፡፡
በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ከዝግጅት እስከ ዋንጫው ድል ባደረገው እንቅስቃሴ በተለያዩ ወጭዎች፤ የአበልና የቦነስ ክፍያዎች እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንዳንቀሳቀሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡በቅርቡ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ኬኬ 11 በሚል በስማቸው የተሰየመላቸው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ የአገራቸው ልጆች ሻምፒዮናነታቸውን ለማስጠበቅ እንደሚችሉ አምናለሁ የሚል ማበረታቻቸውን ለሉሳካው ታይምስ ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡
የዛምቢያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ካሉሻ ቡዋልያ በበኩሉ ለብሄራዊ ቡድኑ ስኬታማነት በምድብ 3 የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያን አሸንፎ በመጀመር ይወሰናል ብሏል፡፡ ዛምቢያ ለአፍሪካ ዋንጫው በምታደርገው ዝግጅት የመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታዋን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ማንዴላ ቻሌንጅ ካፕ በሚል ስያሜ በጆሃንስበርግ በሚገኘው ሶከር ሲቲ ስታድዬም ለማድረግ ፕሮግራም ይዛለች፡፡
የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫው በጥንቃቄ የበሰለ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት በአገሪቱ እግር ኳስ ባለሙያዎች እየመከሩ ናቸው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ኮሚቴ በምድብ ሶስት ያሉ ቡድኖችን በማጥናት እና በማወቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሟላ ስንቅ ይዞ መጓዝ እንዳለበት የሚያሳስቡ አስተያየቶች እየተሰሙ ናቸው፡፡ አረንጓዴዎቹ ንስሮች ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያደርጉትን የመጨረሻ ዝግጅት ከ5 ሳምንታት በኋላ በዚምባቡዌ ካምፕ በመክተም ለማካሄድ አቅደው ነበር፡፡ ይሁንና በዚምባቡዌ ለናይጄርያ ቡድን የሚመጥን በቂ መሰረተልማት አለመኖሩ ከታወቀ በኋላ ሰሞኑን ፌደሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያደርገውን የመጨረሻ ዝግጅት በፖርቱጋሏ ከተማ ፋሮ ለማድረግ እንደወሰነ ተገልጿል፡፡ አረንጓዴዎቹ ንስሮች በዝግጅታቸው የመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታቸውን ከቬንዝዋላ ጋር ለማድረግ ፕሮግራም ይዘዋል፡፡ ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ከ13 ቀናት በኋላ በአሜሪካ ሚያሚ ውስጥ የሚደረግ ሲሆን የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በአውሮፓ ያሉ ፕሮፌሽናሎችን በቡድናቸው ለመቀላቀል ከሰሞኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑ አፍሪካ ዋንጫውን ማለፍ አለበት በሚል ዓለማ ተነስቷል፡፡ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በሚያሚ ከቬንዝዋላ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ 24 ተጨዋቾችን ከአገር ውስጥ በማሰባሰብ ቡድናቸውን ሰርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካምፕ የፈለገችው ጋና
የአፍሪካ ዋንጫን ካሸነፈች 30 ዓመታት ያስቆጠረችው የአራት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ጋና በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በታሪኳ ለአምስተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን ከፍተኛ እድል አላት እየተባለ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ጥቋቁር ክዋክብት የሚሰኘው የጋና ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ካምፕ በመመስራት የመስራት እቅድ አለው፡፡ እነ ዴዴ አየው፤ አሳሞሃ ጊያን እና ሌሎች የጥቋቁር ክዋክብቱ ምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ለአፍሪካ ዋንጫ ድል ብቁ እነደሆኑ የመሰከረው የቀድሞው ተጨዋች ሳሚ ኩፎር ነው፡፡ ጋና በምድብ 2 ከማሊ፤ ኒጀርና ዲ ሪፖብሊክ ጋር መደልደሏ ሲታወቅ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ በፖርት ኤልዛቤት ተቀማጭ ትሆናለች፡፡
ሞምቤላ እና ሮያል ባፎኬንግ ስታድዬሞች
የምድብ ሶስት ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫው በሰሜን ምስራቋ የደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ በኔልስፑሪት ከተማ ተቀማጭ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ በኔልስፑሪት የሚገኘው ሞምቤላ እና በሩስተንበርግ ያለው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬሞች የምድብ 3 ትንቅንቆችን ያስተናግዳሉ፡፡
ሞምቤላ ስታድዬም ለ19ኛው የዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ አዲስ ያስገነባችውና ባለ ሙሉ መቀመጫ ሆኖ 41ሺ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፡፡ ዬሙምፑማላኛ በተባለው የደቡብ አፍሪካ ግዛት ዋና ከተማ ከሆነችው የኔልስፕሪት ከተማ በምእራብ በኩል በ6 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ስታድዬሙ ከእግር ኳስ ባሻገር የአትሌቲክስ፤ የክሪኬት እና የሌሎች ስፖርቶች ሁለገብ ግልጋሎት መስጠት ይችላል፡፡ ደቡብ አፍሪካ 19ኛው ዓለም ዋንጫን ባስተናገደችበት ወቅት የሞምቤላ ስታድዬም አራት የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናገደ ሲሆን ቺሊ ሆንዱራስን 1ለ0፤ አውስትራሊያ ሰርቢያን 2ለ1፤ ኮትዲቯር ደቡብ ኮርያን 3ለ0 ያሸነፉባቸውንና ጣሊያን ከኒውዝላንድ ጋር አንድ እኩል የተለያዩበት ግጥሚያዎች ናቸው፡፡
የሮያል ባፎኬንግ በሩስተንበርግ ከተማ አቅራቢየ የሚገኝ የእግር ኳስ፤የራግቢ እና የአትሌቲክስ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችልና እስከ ሺ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው ስታድዬም ነው፡፡
ለ19ኛው ዓለም ዋንጫ በአዲስ መልክ ታድሶ የተሰራው ስታድዬሙ በ2009 አራት የኮንፌደሬሽን ካፕ ግጥሚያዎችንም አስተናግዷል፡፡ በዓለም ዋንጫው ወቅት ደግሞ የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም 6 ግጥሚያዎች ሲደረጉበት 5 የምድብ አንዱ የጥሎማለፍ ፍልሚያዎች ነበሩ፡፡
ግጥሚያዎቹ እንግሊዝ ከአሜሪካ፤ ኒውዝላንድ ከስሎቫኪያ፤ ጋና ከአውስትራሊያ 1 እኩል በሆነ ተመሳሳይ ውጤት አቻ የተለያዩባቸው፤ ኡራጋይ ሜክሲኮን 1ለ0፤ ጃፓን ዴንማርክን 3ለ1 እንዲሁም በጥሎ ማለፍ ጋና አሜሪካን 2ለ1 ያሸነፉባቸው ነበሩ፡፡


 

Read 4889 times Last modified on Monday, 05 November 2012 09:09

Latest from