Monday, 05 November 2012 08:06

የአጆራ ፏፏቴዎች

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(3 votes)

“ስንት ነው የከፈላችሁት?...” ጠየቀ፡፡ ገና ትኬት አልቆረጥንም ነበር፡፡ “ከ9 ብር ከሃያ ሳንቲም በላይ አትክፈሉ” ብሎ ወረደ፡፡ ጉዞ ቀጠልን፡፡ ምቾት ያልጎደለው አይነት ጉዞ ነው፡፡ የመኪናችን ጎማዎች መንገዱ እንደተመቻቸው ያስታውቃሉ፡፡ በዝምታ፣ ያለምን ገርገጭ ተሸክመውን ይፈሳሉ ለላም ቀንዷ አይከብዳትም በሚል አይነት፡፡ ጫወታ ለመጀመር፣ “ባህር ዛፍ ነው የሚበዛው” አልኩት ጎኔ የተቀመጠውን አብሮ አደጌን፣ በመስኮት ወደ ውጪ እያየሁ፡፡
አዲስ አመትን ከወላጅ ቤተሰቦቼ ጋር ላሳልፍ ነው የመጣሁት፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ በአጭር ጊዜ እያሳየች ያለችው ለውጥ ከገረሙኝ ነገሮች ዋናው ነው፡፡ በተለይም በከተማው ውስጥ ያሉ የአስፓልት (አራት አምስት የሚሆኑ በቁመት የተዘረጉና እንዲሁ በወርዷ የሚዘልቋት ሌሎች) እና ኮብል ስቶን መንገዶች፣ እንቅስቃሴን፣ ፍጥነትን የሚሰብኩ … ግስጋሴን የሚጋብዙ የለውጥ ደቀመዛሙርት አይነት ናቸው፡፡ በየቦታው የሚታዩ ህንጻዎችም ለከተማዋ ሞገስ እየሰጡዋት ነው፡፡

እንደውም አንዱ ጓደኛዬ እንዲህ አለኝ … የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወላይታን ለማየት በአውሮፕላን እየመጡ አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲያንዣብብ … “ይሄማ አዋሳ እኮ ነው” አሉ አሉኝ፡፡ 
ሃሳቡ ቢገባኝም፣ ብጋራውም … “ይህች የማን ፈስ ትመስልሃለች?” አልኩት፡፡ ፈስ እና ወሬ አይመሳሰሉም? … ጊዜ ሁሉን እንደሚለውጥ አየሁ፡፡ የእኛ ሰፈር እንኳን ያደኩበት ሰፈር አልመስልህ አለኝ፡፡ ግርግሩ እጅግ ጨምሮአል፡፡ እንደበፊቱ ወጭ ወራጁን አውቃለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ በፊት እንደልባችን ኳን የምንጠልዝበት፣ ውለን የምናመሽባት፣ ህጻናት “አድባርዋ” የነበርናት፣ የአፈር መንገድ ኮብል እስቶን ተነጥፎበት፣ “ህጻናት ከማይደርሱበት” የተለጠፈበት የምትመስል የስራ ሰፈር እየሆነች ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ስንት አዲስ አመት አለፈ?
ከከተማ ወጣ ብለው ያሉ አካባቢዎች የአዲስ አመት ምስክርነታቸው እንደሚጎላ ከአዲስ አበባ፣ ቡታጀራ፣ በሆሳና አድርጌ ስመጣ ዋቢ ሆኛለሁ፡፡ ገጠር ያለው አዲስ አመት ደብዛዛ አይደለም፤ ጉልህ ነው፡፡ ከተማ የሚለወጥ በየቀኑ ነው … ገጠር ደግሞ በወቅት፡፡ ከተማ ያሉ የግዜ ምስክሮች ሰው ሰራሽ ናቸው፣ በገጠር ደግሞ ተፈጥሮአዊ፡፡
ከተማ “ገባ” ሲባል የሰማሁትን አዲስ አመት፤ በሚሮጥ መኪና መስኮት ያየሁትን ቀረብ ብዬ በእጄ ልዳብስ፣ በቅርበት በአይኖቼ ላየው፣ በጆሮዎቼ ላደምጠው ፈለግሁ፡፡
በዚህም አዲሱ አመት አዲስነቱ እንዲጎላልኝ አሰብኩ፡፡ እንዴት የሚለው ግን አልገባኝም ነበር፡፡
ድንገት አብሮ አደግ ጓደኛዬ “ወደ አጆራ ፏፏቴዎች ጠዋት የሚሄዱ ልጆች የምሄድ ከሆነ ጠይቀውኛል” እስኪለኝ፡፡ ድንቅ አለኝ፡፡ ከአሁኑ ከአዲስ አመት ጋ እጅና ጓንት የሆንን መሰለኝ፡፡ ወዳጅነቱን እሱም (አዲሱ አመትም) የፈለገው እስኪመስለኝ ደስ አለኝ፡፡
በነጋታው ከጠዋቱ ሁለት ሰአት አካባቢ ሶዶ መናሃሪያ ከጓደኞዬ ጋር ገባን፡፡ ልጆቹ ቀድመውን ደርሰዋል፡፡
ከሁሉም ጋር ተዋወቅን፡፡ ስድስት ናቸው፤ አንድ ላይ ስምንት መሆናችን ነው፡፡ ደስ የሚል አይነት አየር ነው፡፡ ሙቀትም ቅዝቃዜም የሌለበት ነፋሻ አየር - ሰሞኑን በብዛት እንዲሁ ነው (በቀትርም)
የገባንበት መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ብዙም ሳይቆይ ተንቀሳቀሰ፡፡ ከከተማዋ ሳንወጣ መኪናችን ቆመችና ትራፊክ ፖሊስ ገባ፡፡ የተሳፋሪውን ብዛት በአይኖቹ ገረፍ አድርጎ …
“ስንት ነው የከፈላችሁት?...” ጠየቀ፡፡ ገና ትኬት አልቆረጥንም ነበር፡፡ “ከ9 ብር ከሃያ ሳንቲም በላይ አትክፈሉ” ብሎ ወረደ፡፡ ጉዞ ቀጠልን፡፡ ምቾት ያልጎደለው አይነት ጉዞ ነው፡፡ የመኪናችን ጎማዎች መንገዱ እንደተመቻቸው ያስታውቃሉ፡፡ በዝምታ፣ ያለምን ገርገጭ ተሸክመውን ይፈሳሉ ለላም ቀንዷ አይከብዳትም በሚል አይነት፡፡ ጫወታ ለመጀመር፣ “ባህር ዛፍ ነው የሚበዛው” አልኩት ጎኔ የተቀመጠውን አብሮ አደጌን፣ በመስኮት ወደ ውጪ እያየሁ፡፡ ከመንገዱ ግራና ቀኝ አረንጓዴ ገጽታ የተላበሱ፣ ዛፎቻቸው የተመናመኑ ሜዳማ ቦታዎች ይታያሉ፡፡ የቆርቆሮ ቤቶች በእንሰት እና የቡና ተክሎች የታጀቡ ናቸው፡፡
አንዳንድ ቦታ ባህር ዛፎቹ በመንገዱ ግራና ቀኝ የተሰቀሉ አረንጓዴ መጋረጃዎች ይመስላሉ፡፡ ተመሳሳይ ገጽታ ከፊታችን ይቀድማል፤ ከሁዋላችን ይከተለናል፡፡ መኪናችንም ይሮጣል፡፡
“ባህር ዛፍ እሚገርም ተክል ነው፡፡ በክረምት እንዲህ እንደምታየው ወዛም ነው፡፡ በበጋ ሌሎች ዛፎች ውሃ ለመቆጠብ ቅጠሎቻቸውን ይቀንሳሉ … እሱ ግን ወይ ፍንክች! ሌሎች ዛፎች አጠገባቸው ሌሎች ተክሎችን ብትተክል አይጋፉም፡፡ ባህር ዛፍ ከሆነ ግን ያደርቃቸዋል፡፡
አንዴ እንደውም ምን ሆነ መሰለህ… አንድ አካባቢ ወንዙ እየደረቀ አስቸገረ፤ ነገሩ የገባው ሰው ባህር ዛፎቹ እንዲቆረጡ አደረገ፡፡ የሚገርመው የወንዙ ውሃ ብዙም ሳይቆይ ተስተካከለ” ጫወታችንን አቋርጬ የመንገዱን ጎንና ጎን እየተቀባበሉ ከፊት ለፊታችን የሚቀድሙትን ባህር ዛፎች አየሁ፡፡
በአንጻራዊነት አካባቢውን ተቆጣጥረውታል፡፡ አልፎ አልፎ ሌሎች ተክሎች ይታያሉ፡፡ ምናልባት በዚህ ራስ ወዳድነት በመሰለኝ ባህሪው ባይሆን ኖሮ በአካባቢው ገዢ ዛፍ ባልሆነ ነበር ብዬ አሰብኩ (ለምን እንደዛ አሰብኩ? ግን ራሱ ወዳድነት ገዥ ያደርጋል እንዴ…? የመግዛት አንዱ መንገድ ነው እንበል?) ከአዲስ አበባ ጀምሮ ባሉ መንገዶች ሁሉ እንደሚበዛ አይቼያለሁ፡፡ምንም ያህል ሳይታወቅን ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ አረካ (ቦሎሶ ሶሬ) ከተማ ገባን፡፡ በወላይታ ዞን አንድ ወረዳ ነች፡፡ መናኸሪያው ሰፊ ሜዳ ነው፡፡ ግቢው ውስጥ አንድ ነገር ገረመኝ፡፡
እጅግ ረዣዥም፣ ዋርካ የመሰሉ ግዙፍ ዛፎች ራቅ ባለ ከፍታ ላይ እንደዣንጥላ የተዘረጉ ቅርንጫፎቻቸውን ገጥመው ሰማዩን ጋርደውታል፡፡ ይህንንም መሰረት አድርጎ አወራኝ፡፡ ስለ ብራዚል (?) ጥቅጥቅ ደኖች፡፡ የአለም ሳንባ እንደሆኑ፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እነሱን ለመንከባከብ ድጋፍ እንደሚደረግ፡፡
ጉዞ የምንቀጥልበት መኪና እስኪነሳ ከመናኸሪያው ወጣ ብለን አንድ ቤት ማኪያቶ አዘን ቁጭ አልን፡፡
በንጣቱ ብቻ ሳይሆን በይዘቱም ወተት ወተት የሚል (ውሃ ያልበዛበት) ማኪያቶ ጠጣን፡፡ ሆኖም ማቅረቢያው የሻይ ሲኒ ሆኖ ጽዳቱ ምሳሌነቱን ያጓድለዋል፡፡ አዲስ አበባ ማኪያቶ ለመጠጣት በተሻለ አስፓልት ተጉዘህ፣ የተሻለ ቤት ገብተህ፣ በበለጠ ዋጋ፣ በተሻለ ማቅረቢያ … ወተት መሳይ ነገር ሊቀርብ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ወተቱ እንደውም የላም ሳይሆን ከማሽኑ ከራሱ ሚቀዳ ይመስለኛል፤ ያ ደረቅ ማሽን ከዚህ በላይ ከየት ያምጣ፡፡ አንድ ትርፍ አልኩኝ፡፡ ወደ ተፈጥሮ በመጠጋት የሚገኝ ትርፍ፡፡ ሏማ ብትጠየቅ “የራሴ” የምትለው ወተት መጠጣት!
“ቦምቤ/ቦምቤ/ …” ወደሚል መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተመልሰን ገባን፡፡ የመጨረሻው ረድፍ ጎማው ላይ ቦታ አግኝተን ተቀመጥን፡፡ መቀመጫዎች ሞልተዋል፣ መቆሚያዎችም /መተላለፊያዎች/ እንዲሁ … መኪናው ሌላ ተሳፋሪ ይጠብቃል … ከሶዶ ስንወጣ ትራፊክ ነበር … ትርፍ የጫነ መኪና አልነበረም … እዚህ ትርፍ ተጭኗል … ትራፊክ የለም፡፡ ሰው እንደእቃ፡፡
የከተማ ገጠር አንድ እንቆቅልሽ፡፡የቅድሙ ትርፍ ሊጣፋ ነው፡፡ ላሟ የምታውቀው ወተት ከላይ፣ ትራፊክ በሌለበት እንደ እቃ መሆኑ ከታች፡፡ ወደ ተፈጥሮ የመቅረብ እዳ፡፡ ትላንትናችንን ለማየት ወደነሱ እንመጣለን፡፡ ነጋቸውን ለማየት ወደኛ ይመጣሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን የነሱን ነገ ይዘናል፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው የኛን ትላንት ይዘዋል፡፡
እነሱ ወደኛ እንደሚመጡ በሰፋፊ መንገዶቻቸው ሙሉ መልእክተኛ ልከዋል፡፡ እኛ ወዴት እንሂድ? … ያልታወቀው የኛ ነገ ነው፣ የታወቀው የኛ ትላንት እና የነሱ ነገ … ወተት ከሻይ ማሽን የታለበ ወይም ከላሟ? … ትራፊክ ፖሊስ ያለበት ወይም የሌለበት? (ለነገሩ የአዲስ አበባ ባሶችስ …) … የት ነበር ያየሁት … “በተወለደበት ማንነት ለተወለደበት ማንነት ማብቃት” የሚል፡፡ ከነ እንቆቅልሹ ጥሩ አባባል ነው፡፡
በዚህ መልኩ ጭኖን መኪናው ከአረካ መናኸሪያ ጥቂት እንደተጓዘ፣ በሆሳዕና ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ ትቶ፣ ወደ ግራ ታጥፎ ፒስታ መንገድ ያዘ፡፡ ያኔ ነበር በምን ተዓምር እንደሆነ ሳላውቅ መንገዱ ገበቴ፣ መኪናዋም ከነተሳፋሪው የገበቴ ውሃ የመሰለኝ (እድሜ ለሾፌሩ እንዲሁም ለሌሎች ትራፊኮች)፡፡ ትንፋሽ በሚሰርቅ ልዩነት ከአንድ ጠርዝ ወደ ሌላ ጠርዝ፣ ቁልቁልና ሽቅብ መፍሰስ፡፡ (ስንመለስ ፒስታ ከመሆኑ ውጭ መንገዱ ለጥ ያለ መሆኑን አይቼያለሁ፡፡ ታዲያ እንዴት አድርጎ የገበቴ ውሃ የሆንኩ አስመሰለኝ … ለማንኛውም ልዩ ትርኢት ነበር ማለት ይቻላል) ወይስ እኔ እንዴት አስቤው ነው? …ደግነቱ በቦምቤ መንገድ ብዙም ሳንጓዝ ሂምቤቹ የምትባል ቦታ ወርዳችሁ በእግራችሁ ሂዱ ተባልን - በአካባቢው ተሳፋሪዎች፡፡
ቦምቤ ከተማ ብንደርስም ከዚህ የማይተናነስ የእግር መንገድ ወደ ፏፏቴዎች እንደሚጠብቀን ተነገረን፡፡ ወረድን፡፡ የወረድንበት ቦታ ኋላ ላይ አምሽተን ስንመለስ ገበያ ቆሞበት ነበር፡፡
የእግር መንገዳችን ገጽታ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለጥ ያለ፣ እርጥብ ሆኖ ጫማ የማይዝ የአፈር መንገድ (ማታ ዘንቦ ነበር)፡፡ በግምት አምስት ስድስት ሜትር ስፋት ካለው መንገድ ጎኑና ጎኑ ገባ ብለው ያሉ ቤቶች አሉ፡፡ ቤቶቹም ተመሳሳይ ናቸው፤ መለስተኛ የቆርቆሮ ቤቶች፡፡ ምናልባት የተለሰኑ ያልተለሰኑ፣ ቀለም የተቀቡ ያልተቀቡ የሚል ልዩነት ነው ማየት የቻልኩት፡፡
ሰብሰብ ብለው የሚጫወቱ ህጻናት አልፎ አልፎ መንገዱ ላይ እና ከቤቶቹ ፊት ለፊት ባሉት ሳርማ ሜዳዎች ላይ ይታያሉ፡፡ የገጠር መንገዶች ባህሪ የመሰለኝ ነገር መንገዱ ብዙ ሰው አያስተናግድም፡፡ ሰዎች ሲተላለፉ “ሎኦ” (ደህና ነህ) ይባባላሉ፡፡ አልፎ አልፎ ሽማግሌዎች በፈረስ ሲጓዙ ይታያሉ፡፡ የመቃብር ሃውልቶችም አልፎ አልፎ አይቼያለሁ፡፡ ቦታዎቹ ግን ለመቃብር ተብለው የተለዩ አይደሉም፡፡ ከመኖሪያ ቤቶቹ በቅርብ ርቀት ያሉ ናቸው፡፡
ካየሁዋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ አስገረመኝ፣ አንዱ አሳቀኝ፡፡ ያስገረመኝ ይህ ነው፡፡ ሰፊ እንደገበቴ ሆኖ የተቆፈረ አፈራማ ጉድጓድ አየሁ፤ ዙሪያውን ተቆፍሮ በወጣው በቀይ አፈር የተከበበ ነው፡፡ ምናልባት ሶስት ሜትር በአምስት ይሆናል፡፡ ጥልቀቱ ቢበዛ አንድ ሜትር ይሆናል፡፡ የተገረምኩት ጓደኛዬ “ገንዳ ነው” ሲለኝ ነው፤ ውሃ እየቀዱ ሲወስዱ አይቼያለሁ፡፡ ያሳቀኝ ደግሞ የመቃብር ሃውልት ላይ አንድ ከለበሱት በጥቁር ቀለም ከተቀባ ካፖርት በቀር ምናቸውም የማይለይ ሰው ፊት ስር “እኝህ ነበሩ” ተብሎ ስማቸው ተጽፎአል፡፡ አጠገቡ ያለ ሌላ መቃብር ላይ ደግሞ “ሩጫዬን ጨርሼአለሁ” የሚል አለ፡፡ የትኛውን ሩጫ? … አስር ሺ? አምስት ሺ? ወይስ … ምንም የለም፡፡ ህይወት ሙሉዋን ሩጫ ናት ማለታቸው ነው? … “…ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ” የሚለውን ፈርተውት ይሆን? … ለፈጣሪ ትተው፡፡
በዚህ መልኩ ለአንድ ሰአት ከሃያ ያህል ከተጓዝን በኋላ (የሚፈልግ ሞተር ሳይክል ወይም ተመሳሳይ ትራንስፖርት ሊያገኝ ይችላል) ከመጣንበት መንገድ ወደ ቀኝ የሚገነጠል በመጠኑ ድንጋይ የተነጠፈበት ቅያስ አየን፡፡ በሱ ትንሽ እንደተጓዝንም … “ዌል ካም ቱ አጆራ ፏፏቴ …” “…ሃሹ ስሩዋን ይዴታ…” “ወደ አጆራ ፏፏቴዎች እንኳን ደህና መጣችሁ” በሶስት ቋንቋዎች በእንግሊዝኛ፣ ወላይትኛ እና አማርኛ በላሜራ ላይ የተጻፈ ጽሁፍ ተቀበለን፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ በእጁ ማጭድ የያዘ አስራ ሶስት አመት የሚሆነው ልጅ፣ ጥድ እጅብ ካለበት አንድ ጎን ወጥቶ ወደ እኛ መጣ፡፡
“ውስጥ ሰው አለ?” ጠየቅነው፤ ወደ ግቢው እየተጠጋን፡፡
“እኔ ነኝ ያለሁት፡፡ አባቴ ነው ሚጠብቀው፤ አሁን ይመጣል፡፡ እዚህ ቁጭ በሉ” ብሎን ሄደ፡፡ ለእንግዳ መቀበያነት የተዘጋጀ ወደ መሰለን ጎጆ ገባን፡፡ ምናልባት በሶስት ሜትር ሬዲየስ የወለል ስፋት እና ሰባት እና ስምንት ሜትር በሚሆን ምሰሶ የቆመ ጎጆ ነው፡፡ ወለሉ ሲሚንቶ፡፡ ጎጆው ያለበት አካባቢ አምረው በተከረከሙ ጽዶች እጅብ ያለ ነው፡፡ ከጎጆው ወጣን፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚትጎለጎል ነጭ ጢስ እስከ ሰማይ ወገብ ይወጣል፡፡
ጢሱ ከሚወጣበት አካባቢ ድው-ድው-ድው የሚል ድምጽ ይሰማል፡፡ ቦርጫም ውሃ ከመሬት ሲላተም የሚያሰማው ድምጽ ከርቀት ሲሰማ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ተነቃቃሁ፡፡ በሰማየሁት፣ ባየሁት ነገር ደስ ደስ አለኝ፡፡ ከፊቴ ሆኖ የሚጠብቀኝ ስበቱ እንደማግኔት ተሰማኝ፡፡
በህጻኑ መሪነት ቁልቁል እየወረድን ሄድን፡፡ ሁለት ሶስት የሚሆኑ አጫጭር እጥፋቶችን እየወሰድን አሁንም ወረድን፡፡
በዚህ መሃል ድምጹም ጢሱም እየቀረበን እንደውም በእንኳን ደህና መጣችሁ የተነኑ ውሃዎች በቅዝቃዜ በተለይ ፊታችንን አበሱት - አቅፈው ሳሙን፤ ወደ ውስጥ ይዘውን ዘለቁ፡፡ አሁን በአራቱም አቅጣጫ በከፍታዎች ተከበናል፡፡ በአንደኛው ከፍታ እምብርት ላይ ነን፡፡ ከኛ አጠገብ ሰዎች የሚቀዱት ጸበል አለ፡፡ መንታ ፏፏቴዎች ከፊት ለፊታችን ትርኢታቸውን ያሳያሉ፡፡ ከላይ ከመነሻቸው ብዙም አይን የማይገቡ የሚመስሉት ውሃዎች ከአፎታቸው እየተመዘዙ፣ እየተዘረጉ፣ እየተወረወሩ፣ ቁልቁል ሲቀሰሩ ምትሃታዊ ውበት አላቸው፡፡ ለተመልካች በስተቀኝ በኩል ያለው ፏፏቴ ሰፊ እና ድፍርስ ነው፡፡
እየወረደ ሲሄድ ይጠራል፡፡ በስተግራ ያለው እንደ ነጠላ ስስ፣ ንጹህ እና አርበ ጠባብ ነው፡፡ የፏፏቴዎች ውሃ የዝቅታው መጨረሻ ሲደርስ እየነጠረ እንገደና ይነሳል፤ ሽቅብ ይወጣል፡፡ ወርዶ ሲፈጠፈጥ ከስር ጥጥ የሚመስለው ውሃ በትነት ከፍ ባለ መጠን እየሳሳ፣ የእጣን ጢስ እየመሰለ፣ የተነሳበትን ከፍታ አልፎ ድምጽ ብቻ እስኪቀር የፏፏቴዎቹን ትርኢት በነጭ እንፋሎት ይደርሰዋል፡፡ ዋናው የፏፏቴዎች ትርኢት ይቀጥላል፡፡ ይበልጥ ወደታች መውረድ ይገለጣል፤ ተመልካች ቀዝቃዛ እንፋሎት ይደርሰዋል፡፡ ዋናው የፏፏቴዎቹ ትርኢት ይቀጥላል፡፡
ይበልጥ ወደታች መውረድ ፈለግሁ፡፡ ቆንጆ ልጅ አይቶ እንደመመለስ ሆነብኝ፣ ቢበዛ አውርቶ፡፡ ወደታች መቅረብ ፈለግሁ፡፡ ግን ያልነገርኳችሁ ነገር አለ፡፡ የቆምንበት ቦታ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከፊት ለፊታችን ያለው ገደል እንደመሆኑ ያስፈራል፡፡ ህጻኑ አስጎብኚያችን “ከዚህ በላይ አትውረዱ” ስላለን እዛው ሆነን ትርኢቱን ደጋግመን አየን፡፡
እኝህ ፏፏቴዎች ያሉበት አካባቢም የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተወልደው ያደጉበት አካባቢ መሆኑንም ሰማሁ፡፡ ስለነዚህ ፏፏቴዎች በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው መንታ ፏፏቴዎች ናቸው ሲባልም ሰምቼአለሁ፡፡ ሁለቱ ፏፏቴዎች ሲወርዱ በየመልክ፣ በየስፋታቸው የሚያሳዩት ትርኢት፤ ቁልቁል የሚቀሰረው ውሃ ከመሬት ተላትሞ ሲመለስ የሚዘረጋው ነጭ የእንፋሎት መጋረጃ፤ ነፋስ አንዴ ከእንፋሎቱ ቅዝቃዜ ወስዶ የሰው ፊት ሲያለብስ፣ ደግሞ እንደ ትርኢቱ አጋፋሪ መጋረጃውን ገልጦ ትርኢቱን ሲያስቀጥል ማየት … ደስ ያሰኛል፡፡ የቆምንበት ቦታ ገደላማነቱ የሚፈጥረውን ፍርሃት መቀነስ እና የበለጠ ወርዶ ማየት ቢቻል ደስታችን ሙሉ ደስታ ይሆን ነበር፡፡


Read 4347 times