Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Monday, 05 November 2012 08:00

...ቅድመ ማረጥ ... Pre Menopause››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእድሜያቸው ከ40 አመት በሁዋላ በሆኑ ሴቶች የሽንት ፊኛ ሕመም እና የወር አበባ መቋረጥ (Pre Menopause& Menopause) ግንኘነት አላቸውን? ለሚለው ጥያቄ አዎን ... በትክክል ግንኙነት አላቸው ...ይላል Perimenopause symptoms.org የተባለው መረጃ መልስ ሲሰጥ፡፡ ምክንያቱም ይላል መረጃው...የወር አበባ ሊቋረጥ ሲልና ከተቋረጠ በሁዋላ በሴቷ ሰውነት ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን ወይንም ቅመም መመረቱን ያቆማል፡፡ ኢስትሮጂን በሽንት ፊኛ አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን የማጠንከር ድርሻ ያለው ሲሆን መመረቱ በሚያቆምበት ጊዜ ግን ዙሪያውን ማለትም በአካባቢው ያሉ ጡንቻዎች መላሸቅ ይጀምራሉ፡፡ መረጃው ከተለያዩ ሰነዶች እና ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ የሰጡን ነው፡፡

ዶ/ር የወንድወሰን በዚህም እትም ከቅድመ ማረጥ ጋር በተያያዘ የሽንት ፊኛን ፣የወገብን እንዲሁም ማረጥ ከውፍረት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን በካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
ሴቶች በሚያርጡ ወይንም የወር አበባቸው በሚቋረጥበት ጊዜ ከሚፈጠረው የኢስትሮጂን እጥረት ጋር ተያይዞ የሽንት ፊኛ ጉዳት ላይ መውደቁን የሚያረጋግጡ አንዳንድ ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
1/ ሽንትን ለመሽናት ምንም ፋታ የማይሰጥ ወይንም ሽንትን ይዞ ለመቆየት አለመቻልና ሽንት መጣሁ ባለ ጊዜም ቶሎ እንዲሸና ማስገደድ፣
2/ ሽንት የሚመጣው በድግግሞሽ ማለትም በአጭር የጊዜ እርቀት ነው፡፡ ይህ ድግግሞሽ ምናልባትም በ24 ሰአት ጊዜ ውስጥ ከስምንት ጊዜ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም የሽንት ድግግሞሹ የእንቅልፍ ሰአትን በጣም ይረብሻል፡፡
3/ ሽንትን ለመቆጣጠር አለመቻል ወይንም አሁንም አሁንም ሽንት መጣሁ የማለትን ስሜት ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ ከመታጠቢያ ቤት ለአፍታ እንኩዋን ዘወር ማለትን ላያስችል ይችላል፡፡
ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪም ቅድመ ማረጥ ወይንም ማረጥ በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ምቹ ያልሆኑ ስሜቶችን ሊፈጥር እንደሚችል ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጸምበት ወቅት የመድረቅና የህመም ስሜት የሚኖር ከሆነ በተያያዘ መልኩ የሽንት ፊኛ ችግርም እንደሚከሰት መገመት ደግ ነው፡፡ የሴት ብልት ግድግዳ መሳሳትና መድረቅ በሌላው ጎኑ የሽንት ፊኛን መስመር መጎዳትንም የሚያሳይ ነው፡፡
ሴቶች በቅድመ ማረጥ ጊዜ የኢስትሮጂን እጥረት ሲደርስባቸው ሌላው የሚከሰተው ችግር የጀርባ አጥንት በተለይም ፐልቪክ ቦን የሚባለው ክፍል መዳከም ነው፡፡ ይህ ፐልቪክ የተባለው የወገብ አጥንት ክፍል አካባቢ ያሉ ጡንቻዎች የሽንት ፊኛን ለማጠናከር የሚያግዙ ሲሆኑ ከተዳከሙ ግን ስራቸውን መስራት አይችሉም፡፡ በእርግጥ የተጠቀሱት የህመም ስሜቶች የሚከሰቱ ከሆነ ዝም ብሎ በራስ ግምት የሽንት ፊኛ ነው አይደለም ...ከወር አበባ መቋረጥ ጋር በተያያዘ ከሚከሰተው የኢስትሮጂን አለመመረት ጋር ይገናኛል ...አይገናኝም ከማለት ይልቅ ሕመሙን ለመለየት ወደ ሕክምና በመሄድ የጤና ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ዶ/ር ወንድወሰን ፡፡
በወር አበባ መቋረጥ ወቅት የሚኖረውን የሽንት ፊኛ ሕመም ለማስታገስ የህክምና ባለሙያዎች የተለያዩ ምክሮችን ለታማሚዎች የሚለግሱ ሲሆን የመጀመሪያው ከምግብ ጋር የተገናኘ ነው የሚለን Perimenopause symptoms.org የተባለው ድህረ ገጽ ነው ፡፡ በተለምዶ ከምንወስዳቸው ምግቦች መካከል፣
• ቡና እና ሻይ፣
• እንደ ብርቱካን ያሉ ፍራፍሬዎች፣
• ቃሪያ እና ቅመማቅመሞች፣
• ቸኮሌት...አልኮሆል...ቲማቲም፣
• ኮምጣጤ እና ተያያዥነት ያላቸው የሰላጣ ማጣፈጫዎች፣
• ስኩዋር እና ማር...ወዘተ፣
ከላይ የተጠቀሱትና መሰል ምግቦች የሽንት ፊኛን ሊያስቆጡ ስለሚችሉ ባይወሰዱ ጥሩ ነው ይላል የህክምናው መረጃ፡፡
• ለጤንነት የሚረዳውን በቀላሉ በተፈጥሮ የምናገኘውን ውሀን በቀን ውስጥ ስምንት ብርጭቆ ያህል መጠጣት በጣም ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
• የላም ወተት ወይም የአኩሪ አተር ወተትን እና የመሳሰሉትን መጠጣት እና ፊኛውን የማያስቆጡ ምግቦችን መመገብ ጠቃሚ ነው፡፡
ዶ/ር ወንድወሰን እንደሚገልጹት የወር አበባቸው የተቋረጠና እድሜያቸው ከፍ ያሉ ሴቶች ከወገብ አጥንታቸው ጋር የተያያዙ ጡንቻዎቻቸው የሽንት ፊኛን የሽንት መያዝ ችሎታ በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው ፡፡ እነዚህ ጡንቻዎች በኢስትሮጂን መመረት መጉዋደል ምክንያት መዳከም ስለሚደርስባቸው ከሰውነታችን የሚወገደውን ሽንት የተሰኘውን ፈሳሽ ለመቋጠር ወይንም ሴትየዋ በፈለገችው ሰአት እንድትሸና ለመቆጣጠር እንዳትችል እንደሚያደርጋት የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመከላከል ከምግብ ባሽገር ጡንቻዎችን የማጠናከር ስራ መስራት ተገቢ ነው፡፡
አንዲት ሴት በሽንት መሽኛ እና በወገብ የመጨረሻው ክፍል እየተባለ በሚጠራው አካል ጡንቻዎችን ለማጠንከር በማኮማተርና በመዘርጋት ወይንም የተለያዩ የወገብ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ምንም እንኩዋን ይህንን አካላዊ እንቅስቃሴ በግል ማድረግ ቢቻልም ይበልጡኑ በሐኪም ምክር በመታገዝ ማካሄድ ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም የሽንት ፊኛውን እራሱን በሚመለከት የሚደረግ የማለማመድ ስራም መስራት ያስፈልጋል፡፡
• ሽንት እሁንም አሁንም መጣሁ ሲል ያዝ አድርጎ ለመቆየት መሞከር...እራስን ማሳመን፣
• ሽንትን መጣሁ ባለ ሰአት ላለመሽናት ጥረት በማድረግ ወደመታጠቢያ ቤት የሚኖረውን ፈጣን ምልልስ በመቀነስ ረዘም ላሉ ሰአታት መቆየትን መለማመድ ፡፡
ይህ የሽንት ፊኛን ጥንካሬን የማለማመድ ዘዴ ቢያንስ ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንት ጊዜ ሊፈጅ ስለሚችል በትእግስት መስራት ይጠበቃል፡፡
ወደሕክምናው እርዳት ፊታችንን ስናዞር...ከወር አበባ መቋረጥ ጋር በተያያዘ በሚኖረው የጡንቻ መላላት የሚከሰተው የሽንት መቆጣጠርን ችግር ኢስትሮጂን ..ራፒ በሚባለው የህክምና ዘዴ ሁኔታውን ማሻሻል ይቻላል፡፡ በወር አበባ መቋረጥ ወቅት የሚፈጠረውን የሆርሞን መዛባት ለመቆጣጠር በሴት ብልት አካባቢ በክሬም መልክ የተዘጋጁና የሚወሰዱ ወይንም በሌሎች ዘዴዎች በሕክምናው አለም የሚሰጡ መድሀኒቶችን መውሰድ ችግሩን ለማቃለል ይረዳል፡፡ በእርግጥ ይህ የህክምና ዘዴ በቀጥታ በሀገራችን የማይሰጥና መድሀኒቶቹም የማይገኙ ሲሆን በተመሳሳይ ግን በሀገራችንም አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡
ቅድመ ማረጥ ወይንም ማረጥ ክብደትን እንደሚያስከትል በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያረጋግጣሉ፡፡ የክብደት መጨመሩ ሊከሰት የሚችለው ብዙዎቹ ሴቶች ቀደም ባለው ጊዜ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበርና በሁዋላ ግን በተለያየ ምክንያት ማለትም እንደመጨነቅ ወይንም መደበር በመሳሰሉት ሁኔታዎች እና በእድሜ ምክንያት እረፍት ማድረግ ስለሚበዛ ክብደቱም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ክብደት በወገብ አጥንት እና በሽንት ፊኛ አካባቢ ባሉ ጡንቻዎች ላይ ጫና ሰለሚያሳድር ችግር ያስከትላል፡፡ ነገር ግን አካላዊ እንቅስቃሴዋን እየቀጠለች የምትሄድ ከሆነ ክብደቱም የመጨመር ሁኔታው የሚገታ ሲሆን በተያያዘም የሚመጡ በሽታዎች አይኖሩም፡፡ እንደ ደም ግፊት የልብ ሕመም የመሳሰሉትን ሁሉ ማስወገድ ይቻላል፡፡ አንዲት ሴት በቅድመ ማረጥ ወይንም ማረጥ የእድሜ ክልል ውስጥ ስትገባ እንደ አረጀች እና በዚያ እድሜ ምንም መስራት እንደማትችል ከማሰብ ይልቅ በተለያዩ መንገዶች ለጤና በሚረዳ ሁኔታ በመደበኛው የአኑዋኑዋር ዘዴ እንቅስቃሴን መጨመር እንዲሁም አመጋገብን ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ የሽንት ፊኛ ሕመም የደረሰባቸው ብዙ ወፍራም ሴቶች ክብደታቸውን በመቀነሳቸው ሕመሙ እንደታገሰላቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በተለይም በህክምና ዘዴዎች የጤናውን ሁኔታ በተገቢው መንከባከብ እንደሚቻል ዶ/ር ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡
ሴቶች የወር አበባ መቋረጥ እድሜ ላይ ሲደርሱ ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን መመረቱን ስለሚያቆም ተያያዥ የሆኑ የጤና እክሎች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ አስቀድሞውኑ በመገመት
• ክብደትን መቆጣጠር፣
• አመጋገብን ማስተካከል፣
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ፣
• እራስን ከጭንቀት መከላከል፣
በማኝኛውም የጤና መጉዋደል ወቅት ሐኪምን ማማከር የመሳሰሉትን እርምጃዎች ሊወስዱ እንደሚገባ ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ ይመክራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየእለቱ የሚኖረውን የጤና ሁኔታ ...የምግብ...የመጠጥ...ሌሎችም የተያያዙ ነገሮችን ለመረዳት እንዲቻል የራስን ማስታወሻ መመዝገብና ለሐኪም ማሳየት አንዱ የምርመራ አካል ሊሆን እንደሚችልም የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ ገልጸዋል፡፡

 

Read 9663 times Last modified on Monday, 05 November 2012 08:06

Latest from