Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 November 2012 07:57

ሳንዲ ማን ናት?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዎች ሰሞኑን በሀይለኛ ዝናብ እና ውሽንፍር ተመተዋል፡፡ ሀሪኬ ሳንዲ የሚል ስያሜ የተሰጣት ውሽንፍር እና ከባድ ዝናብ በማሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያለመብራት አገልግሎት አስቀርታለች፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ከተዘጉ ውለው አድረዋል፡፡ በኒውዮርክ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች የተቋረጡ ሲሆን ከ1888 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውዮርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ ለቀናት ተዘግቷል፡፡ ሀሪኬን ሳንዲ በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደውን የአሜሪካ ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻዎች አስተጓጉላለች፡፡ የአሜሪካን የፌደራል የድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ባለስልጣን ሀላፊ ሚስተር ክሬይ እንደሚሉት፤ ሀሪኬይን ሳንዲ በሚቀጥለው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ጫና አሳድራለች ይላሉ፡፡

በሀሪኬኗ ቀጥታ ተጠቂ የሚሆኑት አስራ አንዱ የአሜሪካን ግዛቶች ምርጫውን በተያዘለት መርሃግብር መሠረት መከወን ሊከብዳቸው እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን የመብራት መቋረጡ እና ሌሎች ሁኔታዎች የመራጮች ቁጥር ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ 
ሳንዲ በአሜሪካ ግዛቶች ላይ የምትፈጥረውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎችን ለመናገር መጨረሻዋን ማየት የግድ ቢሆንም አስከፊ አደጋዎችን አድርሳለች፡፡
ለመሆኑ ሳንዲ ማን ናት? የሀሪኬንን ስም የሚያወጣው የአለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት ነው፡፡ በኪው፣ ዩ፣ ኤክስ ዋይ እና በዜድ ከሚጀምሩ ስሞች ውጪ ሌሎች 21 ስሞች በስድስት ዝርዝር በፊደል ቅደም ተከተል ተዘርዝረው ይቀመጣሉ፡፡
እንደየቅደም ተከተላቸውም አንድ የወንድ፣ አንድ የሴት እያለ በጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ሳንዲ ለዚህ አመት ተዘርዝረው ከተቀመጡ የሀሪኬን መሰየሚያ ስሞች አንዷ ናት፡፡
የካሪቢያን ደሴት ነዋሪዎች ሀሪኬንን በዕለቱ በዋለው የሮማ ካቶሊክ ቅዱስ ስም ይሰይሙ ነበር፡፡ በተለያየ አመት ነገር ግን በተመሳሳይ ቀን ሃሪኬን ካጋጠመ የመጀመሪያው፣ የሁለተኛው በማለት ይለዩታል፡፡
በአሜሪካን አገርም ለሀሪኬኖች ስያሜ መስጠት የተለመደ ሲሆን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የነበሩ ሜትርዎሎጂስቶች ውሽንፍሮችን በሴት ስም ይሰይሙ ነበር፡፡
ከዚህም በመነሳት በ1953 በብሔራዊ የሀሪኬን ማዕከል ስያሜ መስጠት ተቀባይነት አግኝቶ በስራ ላይ መዋል ጀመረ፡፡ የወንዶችን ስም ለሀሪኬን መጠሪያነት መጠቀም የተጀመረው በ1979 ነው፡፡
በአሜሪካን አገር ይፋ ባልሆነ መንገድ የተሰየመው የመጀመሪያው የሀሪኬን ስያሜ ጆርጅ ሲሆን በ1949 የተከሰተው ሃሪኬን በወቅቱ የአሜሪካን ቀዳማዊት እመቤት ቤስ ቱርማን ስም ተሰይሟል - ሀሪኬይን ቤስ በሚል፡፡
የስያሜው ጉዳይ የሪፐብሊካን ፓርቲ የዳላስቴክሳስ ተወካይ በነበሩት ሼይላ ጃክሰን ሊ ልዩ ትኩረትን አግኝቶ አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ የነበረ ሲሆን የሀሪኬን ስያሜዎች ሁሉንም ወገኖች የሚወክሉ የአፍሪካ አሜሪካውያንን ስም ሊያካትት ይገባል ብለው ነበር፡፡
በ2006 ዓ.ም ይህ ነው የሚባል ሀሪኬን ባለመመዝገቡ ዘንድሮ ጥቅም ላይ የዋለው ሀሪኬን ስም ዝርዝር የ2006ቱ ሲሆን አለምአቀፉ የሜትሪዎሎጂ ድርጅት የ2013 ስያሜዎችን ዝርዝር አውጥቷል፡፡
በየአመቱ የሚወጡ የስም ዝርዝሮች ከስድስት አመት በኋላ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የሚታወቁ ከሆነ ከስያሜ ይሠረዛሉ፡፡ ከ1954 ወዲህ 40 ስሞች በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርጓል፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዷ የ1ሺ ሰው ህይወትን የቀጠፈችው ሀሪኬይን ካትሪና ነች፡፡
ሳንዲም አያያዟ ወደዛው ነው፡፡ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚደረግበት ምክንያት መጥፎ ትዝታ ይቀሰቅሳሉ በሚል ነው፡፡
ለአመቱ ከተመደበው 21 ስም የበለጠ ሃሪኬን ሲያጋጥም በግሪክ ሆሄያት (አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ፣ ዴልታ፣ ኤፓሴሎን እና ዜታ) ተብሎ ይሰየማል፡፡ በ2005 ዓ.ም ከ21 በላይ ሀሪኬን በማጋጠሙ የግሪክ ሆሄያት ጥቅም ላይ ውለው ነበር፡፡
በዚህ አመት ከተመዘገቡ ሀሪኬኖች ሳንዲ አስራ ስምንተኛዋ ስትሆን፣ አስራ ዘጠነኛውና ሃሪኬይን ቶኒ በቀላሉ ምንም ጉዳት ሳያደርስ አልፏል፡፡ ሀሪኬን ቫለሪ እና ዊሊያም ወደፊት ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፈጣሪ ይሰውራቸው!!

 

Read 3121 times Last modified on Monday, 05 November 2012 08:00