Saturday, 03 November 2012 13:27

ራዕይ የሌለው መሪ አልመርጥም! (እናንተስ?)

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(9 votes)

“የቁርጠኝነት ችግር የለብንም፤ የትኩረት እንጂ”
በአሁኑ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የሚሉ የመንግስት ባለስልጣናትና ካድሬዎች እንዲሁም የኢህአዴግ አባላት እንደ ፋሽን የያዙትን አነጋገር ሳታውቁት እንደማትቀሩ እገምታለሁ፡፡ ሁሉም ምን ይላል መሰላችሁ? “የመለስን ራዕይ ለማሳካት …” ብሎ ይጀምርና ይሄንኑ አባባሉን በየመሃሉ እየሸነቆረ ትክት አድርጐን ይሄዳል፡፡ ሰሞኑን አንዷ የመንግስት ሠራተኛ “ጠዋት ቀደም ብዬ ሥራ እገባለሁ፤ ማታ እስከ 11 እና 12 ሰዓት ቆይቼ እሰራለሁ” ስትል ተናገረች (“አበጀሁ” ያለችው ማን ነበረች?) ጉዱ የሚመጣው “ለምን ትሰራለች?” የሚል ጥያቄ ስትጠይቁ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ የምትሰራው እኮ “የመለስን ራዕይ ለማሳካት” ነው፡፡

ግን እኮ እሳቸው ከ8 ሰዓት በላይ የማሰራት ራዕይ የነበራቸው አይመስለኝም፡፡ (ያለ ክፍያ ከሆነ እኮ የጉልበት ብዝበዛ ነው) ቆይ ግን “አዳሜ” የራሱ ራዕይ የለውም እንዴ? የመንግስት መሪዎችም ቢሆኑ እኮ “የመለስ ራዕይ” ላይ የራሳቸውን ጨምረው ካላጐለበቱት ብዙም የሚያዛልቅ አይደለም፡፡ “ድህነት ጠላታችን ነው” ብሎ መዋጋት የመለስ ራዕይ ነው ቢባል ተገቢ ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡንም የመለስ ራዕይ ነው ብሎ ለስኬቱ መታተር ስህተት የለውም፡፡ በሰበብ አስባቡ “የታላቁን መሪ” ስም መጥራት ግን ተገቢ አይደለም (አረፍ ይበሉበት እንጂ!) እንዴ አንዳንዴ እኮ ራስን ችሎ መቆምም ያስፈልጋል፡፡ እንደውም የኢህአዴግ መሪዎች ከመለስ ራዕይ ውጭ የራሳችሁ ራዕይ ምንድነው ቢባሉ የሚመልሱትን ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ “የራሳችን ራዕይ የለንም” ካሉ ግን በ2007 ምርጫ ያገናኘን ብዬ አልፋቸዋለሁ፡፡ በድምፄ ጉድ እሰራቸዋለሁ (ዛቻ እኮ አይደለም!) ራዕይ የሌለው መሪ አልመርጥማ! (እናንተስ?)
እኔ የምለው … መዲናችን ልደቷን እያከበረች ነው የሚባል ነገር ሰማሁ ልበል (የትኛውን ልደት?) አምና 125ኛ ዓመቷን አከበረች አልተባለ እንዴ? አንዱ ወዳጄን ስጠይቀው ምን አለኝ መሰላችሁ … “እያረፈች ማክበር አትችልም?” ወቸ ጉድ … ደሞ ልደት ለማክበር የምን ማረፍ ነው! እሺ ማክበሩንስ ታክብር … ግን ስንተኛ ዓመቷን ነው የምታከብረው? ቆይ አዲስ አበባም ዕድሜዋን መደበቅ ጀመረች እንዴ? (“የወንድ ደሞዝና የሴት ዕድሜ አይጠየቅም” አሉ) ግን እኮ አምና 125ኛ ዓመቷ ከሆነ ዘንድሮ 126ኛ ዓመቷን መሆን አለበት! (ቀላል የማቲማቲክስ ስሌት ነው!)
ወዳጆቼ … የመዲናዋን የልደት ጉዳይ ያነሳሁት ከተማዋ የጋራችን ናት የሚለውን “ታሳቢ አድርጌ” እንጂ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ለነገሩ በዚህ የኑሮ ውድነት ከተማዋ ሁለቴ ልደት ለማክበር ሽር ጉድ ማለቷ ቅሬታ ሊፈጥር እንደሚችል መጠርጠር ብልህነት ነው! ነዋሪዎቿ ከወር ወር አልሞላ ብሏቸው መከራ ሲበሉ እሷ አንድ ልደት ሁለቴ ማክበሯ “ፌር” አይመስለኝም፡፡
ምናልባት ለልደቷ የተመደበው በጀት ገና አልተነካ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ሌላ መፍትሄ አለው፡፡ መዲናዋ ለልደቷ የተመደበላትን በጀት ለህዳሴ ግድብ በማርከት ለሌሎች ከተሞችም በጐ አርአያነቷን ማሳየት ትችላለች፡፡
(ቴዲ አፍሮ ከሰርግ ወጪው ቀንሶ 150ሺ ብር ለአካል ጉዳተኞች ሰጥቷል እኮ!)
ያ ነገረኛ ወዳጄ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “ብቻ… በከተማዋ አሳበው የራሳቸውን ልደት እያከበሩ እንዳይሆን!” (ማንን ማለቱ ነው?) እኔም ግን ዝም አላልኩትም “ይሄማ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!” አልኩት ፍርጥም ብዬ፡፡ ይሄኔ ትከሻውን ነቅንቆ እቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡ አቤት ይህቺን ቃል ሲጠላት! “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚባል ቃል ከሰማ በቃ ብርርር … ያደርገዋል (ግን’ኮ ኪራይ ሰብሳቢ አይደለም!)
በነገራችሁ ላይ ለመዲናዋ ልደት የወጣው ጠቅላላ ወጪ በሁነኛ የሂሳብ ባለሙያ ተሰልቶ ቢነገረን ጥሩ ነው (የግልፅነትና ተጠያቂነትን ባህል ለማዳበር እኮ ነው!) እንዲህ ስል ደግሞ መነሻዬ ጥርጣሬ እንዳይመስላችሁ (ማንን ነው የምጠረጥረው?) ምናልባት ከተማዋ ለ125ኛ ዓመት ልደቷ ያለ አቅሟ ገንዘብ ተበድራ (እንደ ፍንዳታዎች) ዕዳ ውስጥ ተዘፍቃ ከሆነ አዋጥተን እንድንከፍልላት ብዬ ነው (አይቀርልንማ!) በዚያ ላይ እንኳን የመዲናዋ የልደት ወጪ ቀርቶ፣ የቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሃብትም ይፋ እየተደረገ አይደል! (ስለከተማችን የልደት ወጪ ማወቅ መብታችን መሰለኝ)
እኔ የምላችሁ … ሰሞኑን የሩዋንዳ መዲና የሆነችውን ኪጋሊን በኢቴቪ አያችሁልኝ! አቤት ፅዳት! አቤት ውበት! አቤት አረንጓዴነት! የምታስቀና ከተማ ናት! (የሚቀና ካለ!) እኔማ ጋሽ አበራ ሞላ እዚያም ሄደ እንዴ ብዬ ነበር፡፡
በኋላ ሳጣራ ግን ሩዋንዳውያን በሙሉ “ጋሽ አበራ ሞላ” መሆናቸውን ሰማሁ፡፡ እኔ የምለው ግን … የእኛዋ አዲስ አበባ እንደ ኪጋሊ የምትፀዳውና የምትዋበው በስንተኛ ዓመት ልደቷ ነው? የአዲስ አበባ መስተዳድር ቀኑን ቁርጥ አድርጐ ቢነግረን አሪፍ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? የመስተዳድሩ ሃላፊዎች ኪጋሊን ጐብኝተው መጥተው የለ! የጐበኙትን መቼ እንደሚተገብሩት ለማወቅ ጓጉቼ ነው (በትኩስ ካልሆነ እኮ ይረሱታል!) በነገራችሁ ላይ ከጐብኚ በድኑ ጋ ኪጋሌ የተጓዘው የኢቴቪ ጋዜጠኛ፣ የጉብኝቱ ተሳታፊ ለነበሩት ለኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ ያቀረበው ጥያቄና የእሳቸውም መልስ ተመችቶኛል፡፡
“አዲስ አበባ እንደ ኪጋሊ ያልፀዳችውና አረንጓዴ ያለበሰችው የኢህአዴግ መንግስት የሩዋንዳ መንግስትን ያህል ቁርጠኝነት ስለሌለው ይሆን?” (ልብ አድርጉ! ቃል በቃል ሳይሆን ሃሳቡን ነው ያስቀመጥኩት) ክቡር ሚኒስትሩም ሲመልሱ “የቁርጠኝነት ችግር የለብንም፤ ትኩረት ሰጥተን አለመስራታችን ነው ችግራችን … ከሩዋንዳው መንግስት የሚተናነስ ቁርጠኝነት አይደለም ያለን” (ቁርጠኛ መልስ ማለት ይሄ ነው!) ምን ትዝ አለህ አትሉኝም “የፖሊሲ ችግር የለብንም የአፈፃፀም እንጂ!” የሚለው የኢህአዴግ መልስ (“አልሸሹም ዞር አሉ” እኮ ነው!)
ግን እኮ ክቡር ሚ/ሩ ነገርዬውን የ“ቁርጠኝነት” ውድድር አስመሰሉት፡፡ በነገራችሁ ላይ ሚኒስትሩ እጅ ላለመስጠት ያደረጉትን “ቁርጠኝነት” አድንቄላቸዋለሁ፡፡
በእርግጥም ውድድሩ የ“ቁርጠኝነት” ቢሆን ኖሮ መንግስታቸው (መንግስታችን ማለቴ ነው!) ከሩዋንዳ መንግስት ቢልቅ እንጂ ፈፅሞ አያንስም ነበር፡፡ ውድድሩ ግን የሁለት ከተሞች ፅዳትና አረንጓዴነት በመሆኑ “ለዛሬ አልተሳካልዎትም” መባላቸው አይቀርም (እንደ አይዶል ውድድር!) እንዴ … ኪጋሊንም አዲስ አበባንም ጐን ለጐን አየናቸው እኮ! (ዕድሜ ለኢቴቪ!)
ከቡድኑ ጋ ኪጋሊ ደርሶ የተመለሰ አንድ የመስተዳድሩ ሃላፊ “ቁጭት የሚፈጥር ነው!” ሲል የሁለቱ ከተሞች ልዩነት የፈጠረበትን ስሜት ገልጿል (እውነት ተናግሯል!) ይሄን አስተያየት ስሰማ ምን እንዳሰብኩ ታውቃላችሁ? ስፖንሰር አፈላልጌ የመስተዳደሩን ሃላፊዎች በሙሉ ኪጋሊ ለመውሰድ! ለሽርሽር እንዳይመስላችሁ! በእያንዳንዱ ሃላፊ ልብ ውስጥ የሃላፊው ዓይነት የቁጭት ስሜት ለመፍጠር ነው (ቁጭት የወለደው የአዲስ አበባ መስተዳድር … እንዲሉ!)
እኔ የምለው ግን … መስተዳድሩ የፈለገ አቅም ቢያንሰው፣ የቱንም ያህል ኪራይ ሰብሳቢዎች ቢያስቸግሩት፣ የአንድ ግለሰብ ያህል እንኳን መጣጣር ያቅተዋል እንዴ? (ጋሽ አበራ ሞላ ትዝ ብሎኝ እኮ ነው!) ግዴለም ባለፈ ነገር መወቃቀስ ይቅርብን፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መስተዳድሩ ከኪጋሊ ከተማ መልካም ተመክሮ ወስዶ መዲናችን ላይ የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል (እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ “አብስትራክት” ውጤት አንፈልግም!) ተጨባጭ ውጤት ካልመጣማ… የኪጋሊው ጉብኝት ሽርሽር ሆኖ ሊቀር ነው (ያውም በህዝብ ገንዘብ!)
በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባን 125ኛ ዓመት ልደት ሁለት ጊዜ ከማክበር እኮ በገንዘቡ ከተማዋን ማፅዳትና አረንጓዴ ማልበስ ይሻላል፡፡ (ከተማዋም ትመርቀናለች!) ዝምተኛዋ መዲናችን “ሸገር” አልተናገረችም እንጂ ይሄኔ በልቧ “ቆሽሼና ተራቁቼ ምኑን ልደት አከበርኩት!” ብላ ይሆናል፡፡ (ደሞም አይፈረድባትም!)
አደራ ታዲያ … የአዲስ አበባ የፅዳትና የአረንጓዴነት ፕሮጀክት ዘመቻ እንዳይሆን - ቦግ ብሎ ጥፍት፤ ዛሬ ፀድቶ ነገ ቁሽሽ የሚል! በኢቴቪ የቀረበው የኪጋሊ ከተማ የመንግስት ሃላፊ፤ ስለ መዲናዋ ፅዳትና አረንጓዴነት ሲጠየቅ ምን አለ መሰላችሁ? “It’s about culture!” አዎ እኛ ጋም ጊዜያዊ ዘመቻ ሳይሆን ባህል ሊሆን ይገባል … ዘላቂ የፅዱና አረንጓዴነት ባህል! እዚህ ጋ ትንሽ ያሳሰበኝን ብተነፍስ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ይሄን የፅዳት ፕሮጀክት የሚመሩ የመስተዳድሩ ሃላፊዎች በኢቴቪ ቀርበው “የመለስን ራዕይ እውን ለማድረግ…” ምናምን ብለው እንዳይዘባርቁ፡፡
እኔ የምለው … ኪጋሊ ሄዶ የንፁህና አረንጓዴ ከተማ ተመክሮ መውሰድ የእሳቸው ሃሳብ ነበር እንዴ? (ይሄ ራዕይ አይባልማ!) በመጨረሻ ለመንግስት ባለስልጣናት አንድ ቀላል ፈተና እነሆ፡፡
እያንዳንዱ ባለስልጣን ራዕዩን በአንዲት መስመር ይፃፍ (በሁለት ቀን ውስጥ!) ራዕይ የሌለው ግን ከአሁኑ ሥልጣንን ይሰናበታት፡፡ ራዕይ የሌለው መሪ እንኳን ለአገር ለራሱም አይበጅም፡፡ (“የመለስ ራዕይ”ን መኮረጅ አይፈቀድም!!)

 

Read 26330 times Last modified on Saturday, 03 November 2012 13:43