Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:38

የፌጦ ፍትፍትና እንቁጣጣሽ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የፌጦ ህክምና ሳይንሳዊ ፋይዳ የለውም

የክረምቱ ወራት ተጠናቆ ወርሃ መስከረም ሊከት እነሆ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ የአዲስ ዘመን፣ የአዲስ ተስፋ፣ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ የሆነውን ወር ሁሉም እንደአቅሙና እንደ ባህሉ ሊቀበለው ጉድ ጉዱን ተያይዞታል፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ ገላን፣ ህሊናን፣ ልብስን፣ ንፁህ አድርጐ መቀበል ከጥንት የመጣ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በተለይም በገጠራማው አካባቢ የጳጉሜ ወር የመታጠቢያና የመጠመቂያ ወር ነው፡፡ በጳጉሜ ወር ወደ ወንዝ ወርዶ ገላ መታጠብ ከሀጢአት ሁሉ እንደመንፃት፣ ሀጢአትን አጥቦ እንደ ማስወገድ ይቆጠራል፡፡ በወረሃ ጳጉሜ በ3ኛው ቀን በዝናብ መታጠብ እንደ ፀበል መጠመቅ፣ እንደ መንፈሳዊ ፈውስም ይታያል፡፡

ይህ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላዊ ትውፊት ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ይኸው ባህል ዛሬም ድረስ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከአሮጌው አመት እድፍና ቆሻሻ ጋር አዲሱን አመት መቀበል የማይወደው ኢትዮጵያዊ፤ በአሮጌውና በአዲሱ አመት መካከል ባለችው የመሸጋገሪያ ድልድይ (የጳጉሜ ወር) ሰውነቱን ከቆሻሻ በማንፃት ንፅህናውን መጠበቁ ሳይንሱም የሚደግፈው ጉዳይ ነው፡፡

በወርሃ መስከረም የመጀመሪያ ዕለት በአገራችን በብዙ አካባቢዎች በስፋት የተለመዱ የነበሩና ዛሬ ዛሬ እየተረሱ ከመጡ ባህላዊ ሥርዓቶች መካከል የእንሶስላ መሞቅና የፌጦ ፍትፍት ሥርዓቶች ይገኙበታል፡፡ በምስማር እየተሸነቆረ በተሰራው የኪዊ ቀለም ቆርቆሮ ተፈቅፍቆ የተዘጋጀው እንሶስላ በዋዜማው የሎሚ ጭማቂ ተደርጐበት በከሰል እሳት እየተሞቀ እናቶች፣ ሳዱላዎችና ሕፃናት ሴቶች ሳይቀሩ እጃቸውንና እግራቸውን እንዲያሹበት ይደረጋል፡፡ በእንቁጣጣሽ ዕለት ደምቃ ለመታየት የምትሻ ኰረዳ፤ እንሶስላው በእጇ ላይ በደንብ እንዲይዝና ቶሎ እንዳይለቅባት ለማድረግ ረዘም ላለ ሰዓት እንሶስላውን ትሞቃለች፡፡ በእንቁጣጣሽ በዓል እንሶስላ ሳትሞቅ የወጣች ኰረዳ ቀደም ባሉት ዘመናት እንደ ስልጡን አትታይም ነበር፡፡ እናቶች እንሶስላው ከቁርጥማትና መሰል በሽታዎች ፈውስ ይሰጣል ብለው ያምኑ ስለነበር፣ በእንቁጣጣሽ ዋዜማ እንሶስላ መሞቅ የማይዘነጋ ሥራቸው ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ይኼ ባህል እየቀረ የሄደ ይመስላል፡፡ በተለይም ከተሞች አካባቢ ከአንዳንድ ሰዎች በስተቀር በአብዛኛው ባህሉ ተዘንግቷል፡፡

በእንቁጣጣሽ በዓል ዕለት በንፅህና ተለቅሞና ተደቁሶ የተሰናዳ የፌጦ ዱቄት፣ በደቃቁ የተከተፈ ቃሪያና ነጭ ሽርኩርት ተጨምሮበት በእንጀራ ከተፈተፈተ በኋላ የሚቀርበው ምግብም በቀደመው ዘመን እጅግ ይዘወተር የነበረ ሲሆን ዛሬ ዛሬ እየተረሳ የመጣ ባህላዊ ሥርዓት ሆኗል፡፡ የፌጦውን ፍትፍት የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ምግብ ከመመገባቸው በፊት በባዶ ሆዳቸው እንዲመገቡ ይደረጋል፡፡

ቤተሰቡ የፌጦ ፍትፍቱን ከተመገበ በኋላ ለጥቂት ሰዓታት ከሌላ ከማንኛውም ምግብ ታቅቦ ይቆያል፡፡ ይህም የሚሆነው ፌጦ ተመጋቢው በአሮጌው አመት በአንጀቱና በጨጓራው ውስጥ ተጠራቅሞ የቆየ ቆሻሻና አላስፈላጊ ነገሮች እንዲወገዱ ለማድረግ ነው፡፡

ከሰዓታት ቆይታ በኋላም በዕለቱ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብ ይመገባል፡፡ ይህ ባህላዊ ሥርዓት ከሳይንሳዊው የህክምና ሥርዓት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌላ በአደልት ሄልዝ ነርሲንግ ማስተርሳቸውን የሰሩትና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ገብሬ ይታይህ ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ገብሬ ገለፃ፤ በባዶ ሆድ የሚበላው የፌጦ ፍትፍት እንደውም በአንጀትና በጨጓራ ላይ የመቆጣትና የማቃጠል ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ፌጦ ተመጋቢው አንጀቱ ወይም ጨጓራው በሚቆጣበት ወቅት ሊያስመልሰው ስለሚችል የምግብ ፍላጐቱም ይጠፋል፡፡ ቃሪያ፣ ሽንኩርትና መሰል አትክልቶችና ቅጠላ ቅጠሎችን አብዝቶ መመገቡ የምግብ ስልቀጣ ሥርዓቱ የተስተካከለና የተፋጠነ እንዲሆን የሚረዳ ከመሆኑም በላይ የሆድ ድርቀትንም በማስወገድ የምግብ ፍላጐትን የተሻለ ለማድረግ ይረዳል፡፡

ለክፉም ለደጉም ፌጦ መድሃኒት ነው እየተባለ ለዘመናት ሲወሰድ የኖረው የፌጦ ሕክምና እምብዛም ሳይንሳዊ ፋይዳ እንደሌለው ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አመት በባተ ቁጥር በባዶ አንጀት የምንመገበው ፌጦ-ጠቀሜታ ከሌለውና መውሰዳችን ጤናችንን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከሆነ ባህላዊ ስርዓቱ ሊፈተሽና በደንብ ሊታሰብበት ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ መልካም አዲስ አመት! የጤና ዘመን ይሁንልን፡፡

 

 

Read 5021 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:41