Saturday, 04 August 2012 10:32

“አመመኝ ደከመኝ የማላውቅ ብርቱ ሠራተኛ ነበርኩ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

“አመመኝ ደከመኝ የማላውቅ ብርቱ ሠራተኛ ነበርኩ፡፡ ዛሬ ሰርቼ ተለውጬ ነገ የተሻለ ነገር ለማግኘትና ልጆቼን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግና ለማስተማር እጥር ነበር፡ከአገሬ ውጪ ሪያድ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ሰርቻለሁ፡ወደ አገሬ ከመጣሁም በኋላ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኝነት ስለነበረኝ በየድግሱና በየሠርጉ ቤት እየተጠራሁ እሠራ ነበር፡፡ በምሠራበት ጊዜ ሁሉ ሰዎች ራሳቸው የሥራዬን ዋጋ ይከፍሉኛል እንጂ ይህን ያህል ክፈሉኝ ብዬ እንኳን አልጠይቅም ነበር፡ በዚህ መሃል ታመምኩ፡፡ ህመሜ በቀላሉ የማይድንና ረዘም ያለ ህክምናን የሚፈልግ ነበር፡ የስኳርና የደም ብዛት በሽተኛ ሆንኩ፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ የጡት ካንሰር በሽታ ያዘኝ፡፡ በዚህ ምክንያትም የቀኝ ጡቴ ተቆረጠ፡፡ ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ነበር፡፡

ለአምስት አመታት ያለማቋረጥ የሚወሰድ መድሃኒት ታዞልኛል፡፡ መድሃኒቱ ደግሞ በወር ከአራት መቶ ብር በላይ ነው፡፡ እኔ በቀን ሥራ እየሠራሁ ለራሴና ለልጆቼ የማላንስ የነበረ ቢሆንም ከህመሜ በኋላ ሁሉም ነገር ቀርቷል፡፡ ሁለት ህፃናት ልጆቼንም የማስተዳድራቸው እኔው ነበርኩ፡፡ ትምህርት ቤት፣ ምግብ፣ የቤት ኪራይ ሁሉም ነገር ያለገንዘብ አይሆንም፡፡ አሁን ደግሞ በየቀኑ መድሀኒት መውሰድ አለብኝ፡፡ ሃኪሞቼ መድሃኒቱን ካቋረጥኩ እንደምሞት ነግረውኛል፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ የመኪና መንገድ እንኳን ማቋረጥ የማይችሉ ሁለት ህፃናት ልጆቼን ለማን ትቻቸው እንደምሞት ማሰቡ ጨነቀኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለሁ ሰዎች መሰረት በጐ አድራጐት ድርጅት ብትሄጂ ይረዱሻል አሉኝና ወደዚህ መጣሁ፡፡ ችግሬን እያለቀስኩ ስናገር ሥራ አስኪያጇ በጣም አዘነችልኝ፡፡ ከዛም ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ በነበረው ፕሮግራም ላይ ይዛኝ ሄዳ ስለ ችግሬ እዛ ለነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ነገረችልኝ፡፡

በሁኔታዬ እጅግ ያዘኑት የህክምና ባለሙያዎች መድሃኒቱን ማቋረጥ እንደሌለብኝ ገልፀውልኝ መድሃኒቱን እየገዙ ሊሰጡኝ ቃል ገቡልኝ፡፡ ይህ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ ልትረዱኝ አትችሉም፡፡ እኔ ከእንግዲህ ቢርበኝም ራበኝ አልልም - ልጆቼ ትንሽ ነፍስ እስኪያውቁና ራሳቸውን ችለው መራመድ እስኪችሉ እንኳን መቆየት መቻሌ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሌላውን ደግሞ አላህ ያውቃል፡፡ ዛሬ እዚህ የመጣሁት ዶክተሮቹ የህክምና ምርመራ ስለሚያደርጉ ለመታየት ነው፡፡”

ይህንን ታሪክ ያጫወቱኝ ባለፈው ቅዳሜ በ “ምርጦች 7ሺ የወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን” ይሰጥ የነበረውን የነፃ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት መጥተው ያገኘናቸው ወ/ሮ ሶፊያ መሐመድ ናቸው፡፡

ከፍለው ለመታከም ለማይችሉ እጅግ ለተቸገሩ እናቶችና ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት የህክምና እርዳታ በነፃ ለመስጠት ከጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የተሰባሰቡ የህክምና ባለሙያዎች እንደ ወ/ሮ ሶፊያ መሐመድ ያሉ ችግረኞችን መርዳትና ነፃ አገልግሎት መስጠት ዋንኛው ተግባራቸው ነው፡፡ ከ20 በላይ ዶክተሮችን፣ 20 ነርሶችን፣ ሰባት ፋርማሲስቶችንና አራት ላብራቶሪ ቴክኒሺያኖችን ያቀፈው ቡድኑ፤ ሐምሌ 21/2004 ዓ.ም ቅዳሜ ማለዳ በቤተክርስቲያኑ አዳራሽ የተሰባሰበው 311 ለሚሆኑ ችግረኞች የጤና ምርመራ ለማድረግና መድሃኒት ለመስጠት ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ በመሠረት በጐ አድራጐት ድርጅት ውስጥ ለታቀፉ 311 ችግረኞች እናቶችና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ሙሉቀን የጤና ምርመራ፣ የላብራቶሪ አገልግሎትና የመድሃኒት አቅርቦት ሲሰጡ ውለዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎቹ አስተባባሪ፣ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሃኪምና የአራተኛ ዓመት የሰርጀሪ ስፔሻላይዜሽን ተማሪው ዶ/ር ያሬድ አግደው፤ ቡድኑ በበጐ ፈቃደኝነት የህክምና አገልግሎት በነፃ ለመስጠት ታስቦ ከአንድ አመት በፊት መቋቋሙን ነግረውናል፡፡

በየሶስት ወራቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍለው መታከም ለማይችሉ አቅመ ደካሞች የነፃ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በአዲስ ዓለም ማረሚያ ቤት ተገኝቶ ለታራሚዎቹ የነፃ ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ የጐዳና ተዳዳሪዎችና እናትና አባታቸውን ያጡ ችግረኛ ህፃናትም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ሐምሌ 21/2004 ዓ.ም በሥፍራው ከተሰባሰቡት የህክምና ባለሙያዎች መካከል የህፃናት ሐኪሞች፣ የዓይን ሀኪሞች፣ ጠቅላላ ሃኪሞች፣ በቀዶ ጥገና፣ በውስጥ ደዌና በማህፀን ህክምና ስፔሻላይዜሽን ትምህርት ላይ የሚገኙ ዶክተሮች ይገኙበታል፡እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች በዕለቱ የሰጡት የጠቅላላ ህክምና አገልግሎት ሲሆን (Top 10 disease) የተባሉትን በሽታዎች የመመርመርና የማከም አገልግሎትም ተሰጥቷል፡፡ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የታይፎይድ ታይፈስ፣ የህፃናት፣ የሠገራና የሽንት ምርመራና ውስብስብ ያልሆኑ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችም በበጐ ፈቃድ የህክምና ባለሙያዎቹ ሲሰጥ ውሏል የህክምና ባለሙያዎቹ ውድ ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገውና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን ሁሉ ትተው በበጐ ፈቃደኝነት ከፍለው ለመታከም አቅም የሌላቸውን ወገኖቻቸውን ለመርዳት መሰባሰባቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ያሬድ፤ ይህንን ተግባርም  ወደፊት አጠናክረው ይቀጥሉበታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ ከህክምና ቡድኑ አባላት መካከል ያነጋገርናቸው ዶ/ር መኳንንት፤ በቀላል የህክምና እርዳታ ሊድኑ በሚችሉና በቀላሉም ልንከላከላቸው በምንችላቸው የጤና ችግሮች በርካታ ሕፃናት ያለአግባብ እየሞቱብን ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥና ከፍለው መታከም የማይችሉ ወገኖችን ለመርዳት እዚህ ተገኝተናል ብለዋል፡፡ በቡድኑ ውስጥ የተሰባሰቡት የህክምና ባለሙያዎች በበጐ ፍቃደኝነትና በፍላጐት ወገኖቻቸውን ለመርዳት የተሰባሰቡ መሆናቸውንም ዶ/ር መኳንንት አረጋግጠውልናል፡፡

የህክምና እርዳታውን ለማግኘት በሥፍራው የተገኙት ህፃናትና አቅመ ደካሞች በመሰረት በጐ አድራጐት ድርጅት ውስጥ የታቀፉ ናቸው፡፡

ድርጅቱ በለጋ ዕድሜያቸው ተደፍረው ወይም ተታለው ያረገዙና የወለዱ እናቶችንና ልጆቻቸውን፣ የካንሰር ህሙማንን፣ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያሉ ህፃናትንና ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን አሰባስቦ የተለያዩ እርዳታዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በዕለቱም ከ “ምርጦች 7ሺ የወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን” ጋር በመተባበር እነዚሁ ችግረኞች የህክምና ምርመራና የመድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት በበጐ ፈቃደኛ ሃኪሞች እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ የማህበሩ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰረት አዛገ በዕለቱ ሲሰጥ የነበረውን የነፃ ህክምና አገልግሎት አስመልክተው ሲናገሩ፤ እነዚህን ችግረኛ እናቶችና ሕፃናት በህክምና ለመርዳት በጐ ፈቃደኛ ሆነው የተሰባሰቡትን የህክምና ቡድን አባላት አመስግነው፣ ይህንን መሰሉን ወገን ለወገን የመረዳዳትና የመተባበር ተግባር ሁላችንም አጠንክረን ልንቀጥልበት የሚገባን ታላቅ ተግባር ነው ብለዋል፡ ከአራት ወራት በፊት ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት የጤና መኮንንነት ተማሪዎች የበጐ አድራጐት ክበብ ሊመሰርቱ በእንግድነት በተጠሩበት ወቅት፣ በድርጅታቸው ስለታቀፉት ችግረኛ እናቶችና ህፃናት በመናገራቸውና በፕሮግራሙም ላይ የተወሰኑትን ይዘው ሄደው በማሳየታቸው በዕለቱ ተሰባስበው የነበሩት የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች በሁኔታው እጅግ አዝነው፣ ለችግረኞቹ የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ፍላጐታቸውን አሣይተው ከቤ/ክርስቲያኒቱ ጋር በመተባበር ለ311 ደጋፊና ረዳት ለሌላቸው ችግረኞች፣ የህክምና አገልግሎት በነፃ ሊሰጡ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በዕለቱ ከሰጡት ነፃ የህክምና አገልግሎት ሌላ በድርጅቱ የታቀፉ ችግረኞች በሚያጋጥማቸው የጤና ችግርና የህክምና እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ በሙሉ ፍቃደኝነትና ፍላጐት እየረዷቸው እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከሃያ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ መሰረት፤ ይህም ሰዎችን የመርዳት ፍላጐታቸውን እንዲዳብር እንዳገዛቸው ገልፀዋል፡፡ “ለራሳቸው የሚበሉትና ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት አጥተው የተቸገሩ እናቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ለማሳደግ ሲረከቡ ሣይ በጣም ይገርመኛል፡፡ ድሃ ለድሃ እኮ በጣም ይረዳዳል፡፡ ሰዎች ምንም ሣይኖራቸውም ሌሎችን መርዳት እንደሚችሉ እነዚህ እናቶች ጥሩ ማሣያ ናቸው፡፡ እኚህ የዛሬዎቹ የህክምና ባለሙያዎችም ለብዙዎቻችን አርአያ ሊሆን የሚችል ተግባር በመፈፀማቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል” ሲሉም ወ/ሮ መሰረት አክለዋል፡፡

ከሃምሣ በላይ አባላትን ያቀፈው የህክምና ቡድኑ፤ የጤና ምርመራ ላደረገላቸው ህፃናትና እናቶች የመድሃኒት አቅርቦትና የምክር አገልግሎትም ሰጥቷል፡፡ ይህ  በህክምና ባለሙያዎቹ የተከናወነው የበጐ ፍቃድ ተግባር በሌሎችም ሊለመድና ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡

 

 

 

Read 4814 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:44