Saturday, 07 April 2012 08:01

በዓመት ሞት መቀነስ ይቻላል!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ቫይረስና ባክቴሪያ የሚገድል ሳሙና ቀርቧል

አላቂ ዕቃዎች በተለያዩ አገራት በማምረትና በማከፋፈል የሚታወቀው ዩኒሊቨር ኩባንያና  አል ፋራጅ ትሬዲንግ፤ ቫይረስና ባክቴሪያ የሚባል አዲስ ዓይነት “ላይፍ ቦይ” ሳሙና  አቀረቡ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቋ ብሪታኒያ በ1894 ዓ.ም ለገበያ የቀረበው ላይፍ ቦይ ሳሙና ተወዳጅ ስምና ዝናውን ጠብቆ ከ100 ዓመት በላይ የዘለቀ ሲሆን፤ አዲሱ ሳሙና የጤና አገልግሎቱን በማሻሻል የቫይረስና ባክቴሪያ ገዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አዲሱ ላይፍ ቦይ በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች ምግብ ከመብላታቸው በፊት እንዲታጠቡበት መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ምግብ ከመብላት፣ ከማዘጋጀት በፊት እንዲሁም ከተፀዳዱ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ በተቅማጥ የመያዝ ስጋትን 45 በመቶ እንደሚቀንስ መረጃዎች በቋሚነት እያሳዩ መሆኑን የዩኒሊቨር መረጃ አመልክቷል፡፡

ተቅማጥ እጅግ አደገኛ ገዳይ በሽታ ነው - በተለይ ሕፃናትን፡፡ አደገኛነቱ በአኅዝ ሲገለጽ፣ አምስት ዓመት ያልሞላቸው አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ያህል ሕፃናት በየዓመቱ ወይም 3ሺህ ያህል ሕፃናት በየቀኑ የዚህ ገዳይ በሽታ ሰለባ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ተቅማጥ በመላው ዓለም ሁለተኛው የሕፃናት እጅግ ገዳይ በሽታ መሆኑን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ የእጅ መታጠብ ባህርይን አስመልክቶ አንድ ቅኝት በ11 አገሮች ተካሂዶ ነበር፡፡ ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ ከመቶ እናቶች እጃቸውን በሳሙና የሚታጠቡት 17 ብቻ ነበር፡፡ ከመቶ እናቶች 45 ያለ ሳሙና በውሃ ብቻ ታጥበዋል፡፡ ብዙ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ከት/ቤት የሚቀሩት በታወቀው አደገኛ የልጆች በሽታ ነው - በተቅማጥ፡፡ በቻይና፣ በኮሎምቢያና በግብፅ ያሉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ጥሩ የእጅ መታጠብ ልማድ ስላዳበሩ፣ ታመው ከት/ቤት ይቀሩ የነበሩ ልጆች ቁጥር ከ20 እስከ 50 በመቶ ቀንሷል፡፡ እጅን መታጠብ ለተቅማጥ ብቻ ሳይሆን በንፅህና ጉድለት ለሚከሰቱ በርካታ በሽታዎችም ይጠቅማል፡፡ በመላው አገር የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ወረርሽኝ ሲከሰት እጅን መታጠብ ዋነኛ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ኋለኛ የመተንፈሻ አካል ወረርሽኝን ሲከሰት እጅን በሳሙና መታጠብ፤ ችግሩን ከመቶ 23 እጅ ይቀንሳል፡፡ እጅን በውሃ ብቻ መታጠብ በቂ አይደለም፡፡ አንድ ሰው እጅን በሳሙና ሲታጠብ፣ የማንኛውም ዓይነ - ምድር ባክቴሪያ እጅ ላይ እንዳይኖር ከ44-48 በመቶ ይቀንሳል፡፡ በውሃ ብቻ እጅን መታጠብ ግን 23 በመቶ ብቻ እንደሚቀንስ መረጃው ገልጿል፡፡

የሳሙና ያለመኖር እጅን በሳሙና ላለመታጠብ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ በ11ዱ አገራት በተደረገው ቅኝት ወይም ዳሰሳ ጥናት፤ ድሃ ከሆኑት መቶ ቤተሰቦች መካከል 95ቱ ሳሙና እንዳላቸው ቢያሳይም ለእጅ መታጠብ የሚጠቀሙት አልፎ አልፎ ነው፡፡ ሳሙናን ከእጅ ይልቅ ለልብስና ለገላ እንዲሁም ለድስትና ሳህን ማጠቢያነት በቅድሚያ እንደሚያውሉት ታውቋል፡፡ ላይፍ ቦይ፤ በ2015 በመላው ዓለም ያሉ አንድ ቢሊየን ሰዎች በሳሙና እንዲታጠቡ ለማድረግ ያወጣውን ዕቅድ፤ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ለመደገፍ በዚህ ዓመት በተደረገው “ግሎባል ሃንድ ዎሽ ዴይ” ቃል መግባታቸውን ዩኒሊቨር አስታውቋል፡፡ ላይፍ ቦይ በሚሸጥበት ቦታ ሁሉ ገበያውን እንደሚመራ ኩባንያው ጠቅሶ፣ ለቤተሰባቸው ጤና በላይፍ ቦይ ስለሚተማመኑ በኤስያና በአፍሪካ ያሉ 73 እናቶች በየሰኮንዱ ሳሙናውን ይገዛሉ ብሏል፡፡ በኩባንያው መረጃ መሠረት፡-

በተቅማጥ ምክንያት በመላው ዓለም በእያንዳንዱ ዓመት 272 ሚሊዮን የትምህርት ቀናት ይባክናሉ፡፡

በመላው ዓለም በየ15 ሰከንዱ አንድ ልጅ በተቅማጥ ይሞታል፡፡

በመላው ዓለም አብዛኞቹ በሽታዎች የሚከሰቱት ከዓይነ ምድር ጋር በተገናኘ ነው፡፡

የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር ሰባት ቢሊዮን የደረሰው ባለፈው ጥቅምት ወር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሰው ዓይነ-ምድር (ሰገራ) ውስጥ እጅግ በርካታ ቫይረስና ባክቴሪያዎች ይገኛሉ - አንድ ትሪሊዮን (1,000,000,000,000) ,ቫይረሶችና አስር ቢሊዮን (10,000,000) ባክቴሪያዎች፡፡

እጆቻችን ጀርሞችን በመንካት ዋነኞቹ የበሽታ አስተላለፊ ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ እጆቻችንን በሳሙና በመታጠብ፣ በዓመት አንድ ሚሊዮን ሞት መቀነስ ይቻላል፡፡

 

 

Read 4142 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:08