Saturday, 11 August 2012 10:12

ነገር - የገባት ሠጐን፣ ነገር የገባት ወለደች (ነገር የገባት ሠጐን ቁጥር 3)

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

(ነገር የገባት ሠጐን ቁጥር 3)

ነገር - የገባት ሠጐን፣ ደሞ ዛሬ ጉድ አመጣች

“አንድ - አይነድ -አይፈርድ” ብላ፤

ነገር - የገባት ወለደች!

አዲሷ ሠጐን ክንፍ አብቅላ፣ ባዲስ መላ በአዲስ ማላ

እሾህ ወግቷት እሾህ ነቅላ

መንገድ መቷት መንገድ ጠርጋ

እንደፈንጂ - አምካኝ ፊት ቀድማ-፣ ተራምዳ በራሷ ፈርዳ

ክንፏን ትንፋሿን ሰዋች፤ ለእናቷ መሮጫ ሜዳ!

ልጅ ከግንባር ተጋድላ፣ ባላንጣዋን አደንዝዛ

እናት በፈገግታ አድፍጣ፣ በፈገግታ ጦሯን መዛ

ዛሬም እንደትላንትና፣ ባገር የመጣ ነው ብላ

ድሏን እንደነብር ግልገል፣ በጥርሷ ጫፍ አንጠልጥላ

ካደፈጠችበት ጢሻ፣ እንደወንጭፍ ተስፈንጥራ

አንዳቀባበሉት ቃታ፣ እንደክብሪት ተግ ብላ

የድል ጉልላት ላይ ወጣች፣ ወርቅ ይዛ ባንዲራ ሰቅላ!

አንዷ ሠጐን የልብ አውቃ

አንዷ ሠጐን የልብ አድርስ

አንዷ አማላይ አንዷ ገዳይ፣ ሁለት ሠጐን አንች - አርስ!

ነገር የገባት ሠጐን ነገር የገባት ልጅ ወልዳ

በግራቸው ጣምራ ጦር ሰብቀው፣ ዓለምን አሳዩት ፍዳ፡፡

በዓይን እየተነጋገሩ

በእግር ኬላ እየሰበሩ

ከልብ ልብ እንደሚለይ፣ ከእግር እግር መለየቱን

ይኸው በኦሎምፒክ ሜዳ፣ አሳዩ ሰብረው አጥሩን!!

ፊትና ኋላ ተማክረው

አሳዩን ጉዱን ለይተው፤

መንታ ሠጐኖች አድመው

ወርቅ መስፈሪያ እግር ሠርተው!!

ዓይኔ መስክሯል ዛሬ፣ ይህን የተጋድሎ ምስል

በሩጫው ዓይነት ህይወትን፣ ማሸነፍ እንደምንችል፡፡

እነዚህ ሯጭ ሰጐኖች

ማህል አግተው ሌሎችን፣ እንዳሳንድዊች ከላይ ታች

በረዥም ፅናት እንደ እንሰት፣ ባንድ አፍታ ጥቃት እንደምች

አስጨንቆ ሯጩን ሁሉ

መተጋገዝ እስከድሉ

ምንኛ መታደል ነው በሉ፣ ነገር ለገባው ሁሉ?

እንደሰጐኗ ቀድሞ፣ መንገድ የመጥረግ መከራ

እንደ ሠጐኗ አድፍጦ፣ ጊዜ አውቆ ለድል በረራ

ምነው ሁላችን በገባን፣ የወል - መላ ደቦ - ሥራ

የቁርጥ ቀን ልጅ ሆነናት፣ አገሬ ብታንሠራራ

የቁርጥ ቀን ልጅ ሆነናት ኢትዮጵያ ብታንሠራራ!

(ለጥሩዬ፣ ለወርቅነሽ እና ለአትሌቲክ ጀግኖቻችን እንዲሁም

ለሚወዳቸው ነገር -የገባው ህዝብ)

ነሐሴ 2004 ዓ.ም

 

 

 

 

Read 47528 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 15:12