Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 09:55

ነገር የገባት ሰጐን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ነገር የገባት ሰጐን

(ቁጥር ሁለት)

ነቢይ መኮንን

የዓለም ሩጫ ገጥሞን፣

እኔ፣ በምጥ ብዛት

አንቺ፣ በጐን ውጋት፣

ሁለታችን ታመን፡፡

አንቺ መለኛ ነሽ፣ መላውን ታውቂያለሽ፣

ብልሂቱ ሰጐን፣ ነገር የገባሽ ነሽ፣

“አገሬን!” “አገሬን!” “አገሬን!” ብለሽ ሻርሽ!

ህመምሽን እረስተሽ፣ አገርሽን አዳንሽ፡፡

እኔ መቼም አልዳንኩ

ባንቺ እግር እየሮጥኩ

በዓለም ስቄ ስቄ፣ ይኸው በደስታ ሞትኩ፡፡

ጥሩዬ በእኔ ሞት፣

ይሄን ያንቺን መላ፣ ይሄን ያንቺን አስማት

ምናለ በምስጢር፣ ላገርሽ ብትነግሪያት

እንዳንቺ አካላቷን፣ በገዛ እጇ አብሳ

መከራዋን አልፋ፣ ሰቀቀኗን ዳሳ

አቅሟን አጠራቅማ፣ እንዳንቺ ታግሳ!!

ህመሟን ፈውሳ፣

ተስፋዋን ጠንስሳ፣

ምነው ስትሮጥ ባየን የእልህ ጥርሷን ነክሳ!!

ምነው አልነገርሽው፣ ለድፍን አበሻ

ከድህነት ጫካ፣ ከስንፍና ጢሻ

እንዲወጣ ተግቶ፣

ከኋላ ተነስቶ….. ህመሙን እረስቶ

ወደፊት ሮጦ - ነገ ፊት ተገኝቶ

ጋሬጣውን ማለፍ… ትምህርት አደል ጥሩ?

በአንቺ ለሚኮራው፣ ለህዝቡ ለአገሩ፣

ጥሩዬ ልንገርሽ፣ ዛሬ በሰዓቱ

ይለወጥ ተረቱ

አበው ያወጉቱ፡-

“ልጅ ለእናቷ ምጥን፣ አታስተምር” ሲሉ

አንቺ አሳየሻቸው፣ ከነግልግሉ!!

ጥሩ አሳየሻቸው፣ ከነግልግሉ!!

ነሐሴ 22 1999

(ለጥሩነሽ ዲባባ እና ለጀግኖች አትሌቶቻችን

እንዲሁም በልቡ ላልተለያቸው ያገሬ ሰው)

 

 

 

 

 

Read 3261 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 10:08