Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 20 August 2011 10:43

የቃላት ማረሚያ ያለው የአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌር!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ስራችንን የሚያቀላጥፍልን የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ
ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አገራት ከቴክኖሎጂው ጋር አብረው በመራመድ በራሳቸው ፊደል ለመጻፍ የሚችሉበትን የኮምፒዩተር ሶፍትዌር ማበጀት ከጀመሩ ቆየት ብለዋል፡፡ በአገራችንም እንደ ..ፓወር ግዕዝ.. እና ቪዥዋል ግዕዝ.. ያሉ የአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌሮች ተሰርተው በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን የአገርኛ ቁጥሮች መጻፊያ እና የቃላት ወይም የፊደላት መጠን ማስተካከያዎችም አሉ፡፡ በቃላት አጻጻፍ ዙሪያ የሚታዩ የፊደላት ግድፈቶችን ለማስተካከል የሚያግዘን የቃላት ማረሚያ ግን ይጐድለናል፡፡

የእንግሊዝኛ መጻፊያ ሶፍትዌሮች የስፔሊንግ ወይም የቃላት አጻጻፍ ማረሚያ አላቸው፡፡ ለምሳሌ “Technology”  የሚለውን ቃል ስፔሊንግ አሳስተን “Technology” ብለን ብንጽፍ የሶፍትዌር ፕሮግራሙ ወዲያውኑ ቃሉ ላይ ያሰምርበታል፡፡ ይህ ቃል በትክክል አልተጻፈምና ተመልሰህ አርመው እንደማለት፡፡
እኛ ብንዘነጋው እንኳ ራሱ በቀይ እያሰመረ በድምጽ አልባው የማባተቻ ደወል ጥሪ በማድረግ ተመልሰን እንድናርመው ያደርገናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የቃሉን ትክክለኛ አጻጻፍ ባናውቀው እንኳ ሌላ አማራጭ ስለሚያቀርብልን በ..ማውሱ.. ቀኝ በኩል ያለውን ቁልፍ በመጫን ትክክለኛውን አጻጻፍ ማየትና ማስተካከል ይቻላል፡፡
በአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌሮች ይህ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የቃላት ማረሚያ ወይም የፊደላት ግድፈቶች ማስተካከያ ያለው የአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌር መስራት ከባድ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው የቃላት ማረሚያ ያለው የአማርኛ መጻፊያ ተሰርቶ ለገበያ ያልቀረበው? የ..ፓወር ግዕዝ.. (Power Gees) ፕሮግራምን የሰሩት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያ አቶ መሳይ ዘገየ ስለሁኔታው ሲገል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ሰው የሚገዛው ..ኦሪጅናል.. ያልሆኑትን ስራዎች ስለሆነ ብዙ ጊዜ ወስደንና ደክመን ይህንን የቃላት ማረሚያ (ስፔል ቼከር) ያለውን የአማርኛ መጻፊያ ሰርተን ብናቀርብ (ከልፋቱ አንጻር) ብዙም ትርፋማ ባለመሆኑ አልሰራንም ይላሉ፡፡
የ..ቪዥዋል ግዕዝን.. (Visual Geez) የሠሩት የ “Cuftor” ድርጅት ባለቤት የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያው አቶ ገብረሥላሴ አናንያ በበኩላቸው፤ የቃላት ማረሚያ ሶፍትዌር መሥራት እየተቻለ እስካሁን ያልተሰራበት ምክንያት ለጉዳዩ ብዙም ትኩረት ባለመስጠታቸው እንደሆነ ጠቅሰው አሁን ግን ሰርተው ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑና ከስድስት ወራት በኋላም ለገበያ ሊቀርብ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ ይህንን ሶፍትዌር ለመስራት ብዙ የሚያስቸግር ነገር የለውም፡፡ የቃላት ማረሚያ ያለው የአማርኛ መጻፊያ ለመስራት በዋነኛነት የሚያስፈልገው ደረጃውን የጠበቀ (ስታንዳርድ) መዝገበ ቃላት ነው፡፡
በቃላት አጻጻፍ ላይ ግድፈት ሲፈጠር ፕሮግራሙ ቃሉ ላይ እያሳመረ ስህተቱን እንድናርም የሚያደርገውም ከዚሁ ከተጫነለት መዝገበ ቃላት በመነሳት (ከዚያ ጋር እያናበበ) ሲሆን ለዚህ ደግሞ ቃላቶችን የሚያብላላ (Word Analyzer) መኖር እንዳለበት አቶ ገ/ሥላሴ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም እየሰሩት ያለው ሶፍትዌርም ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸውን (እንደ ..ሀ.. ..ሐ....ኅ..፣ ..ሰ.. ..ሠ.. ወዘተ ያሉ) ፊደላትን መቀበል የሚችል በመሆኑ ለምሳሌ ..ኃይል.. የሚለውን ቃል በሃሌታው ..ሀ.. ም ሆነ በኃይሉ ..ኅ.. መጻፍ እንችላለን፡፡
ስለዚህ ..ሃይል.. ብለን ብንጽፍም ትክክል ነው፡፡ የኦምኒኬት ስራ አስኪያጅና ..ሼርሆልደር.. የሆኑት የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያው አቶ ድረስ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የፊደላት ግድፈቶች ማረሚያ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም (ልክ እንደ እንግሊዝኛው ..ቴሳውረስ..) አማራጭ  ቃላቶችንም ሁሉ ሊያቀርብልን የሚችል ሶፍትዌር መስራት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ..ኃይል.. በሚለው ቃል ፋንታ ..አቅም.. ወይም ..ጉልበት.. የመሰሉትን ቃላቶች ሁሉ የያዘ ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በተለያዩ የጽሑፍ ስራዎች ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ የቃላት በትክክለኛው መንገድ አለመጻፍ ወይም የፊደላት መገደፍ ነው፡፡
ይህ ችግር በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ ሆነ በተለያዩ የማስታወቂያ ጽሑፎች ላይ በብዛት የሚታይ ብቻ ሳይሆን ከእንግሊዝኛ ጽሑፍ ጋር ሲነፃፀር በአማርኛው ላይ የሚታዩት ስህተቶች (ግድፈቶች) እጅግ የበዙ ናቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ አንደኛው ምክንያት የምንገለገልባቸው የአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌሮች የቃላት ማረሚያ ስለሌላቸው ነው፡፡ ስለሆነም የቃላት ማረሚያ ያለው የአማርኛ መጻፊያ ሶፍትዌር ቢሰራ ለጽሑፍ ስራዎቻችን ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

Read 4712 times

Latest from