Saturday, 26 May 2012 12:02

የቁጥሮች ጨዋታ!

Written by  ቃልኪዳን ይበልጣል
Rate this item
(0 votes)

በባለ አስራ አራት ኢንቹ ቴሌቭዥን ውስጥ ቆሞ የሚታየው በሙሉ ልብስ የዘነጠ ሰውዬ፣ ተመልካቹን ለማሳመን ከአለቃው ጋር ተዋውሎ ቀብድ የተቀበለ ይመስላል፡፡ ከውትወታም ከተማጽኖም ሊመደብ በሚችል ሁኔታ ስለሚመነደጉ በጐነቶች እና ስለሚያሽቆለቁሉ መጥፎነቶች ያወራል፡፡ ቀስቶችና ቁጥሮች ከጐኑ በተዘረጋ ሰሌዳ ላይ እየተቀያየሩ ያግዙታል፡፡ ያልተለመደ ፍላጐት አትኩሮቴን ገራውና ለአፍታ ቀልቤን ሰብስቤ አስተዋልኩት፡፡ እየተወናጨፈ ያቀረበልንን ዝክረ ስኬት የበለጠ ተዐማኒ ለማድረግ፣ ሰዋዊ ለዛም ለማላበስ ይመስላል፡፡ አንድ ሁለት የትሩፋቱ ተቋዳሾችን ጋበዘልን፡፡ እነርሱም አላሳፈሩትም፣ የኑሮዋቸውን በአያሌው መለወጥ ደስ እያላቸው መሰከሩ፡፡ በህይወት ያሉ ማስረጃዎች መሆናቸው ነው፡፡ ወዲያውኑ ራሴን በድንገተኛ የጥያቄ ወጀብ ሲላጋ ያዝኩት፡፡ በነጋ ጠባ የቁጥሮች ጉልበት እየበረታ የመምጣቱ እውነት ተሰማኝ፡፡

ማንም ስለምንም ጉዳይ ለመናገር ምላሱን ሲስል፣ የሃሳቡን ቅቡልነት ለማስረገጥ የሚተኩሳቸው ጥይቶች ሆነዋል፡፡ በመቶኛ፣ በአስርዮሽ፣ በንፃሬ የማይደገፍ፤ የማይበለጽግ ሀተታ የለም፡፡ ነገር ግን ከእወጃዎቹ ሁሉ ልባስ ስር የተሸጎጠችው እውነት፤ የተባለላትን ትመስል ይሆን? በየጐዳናው ስንንገላወድ ከምንባጀው ተራ ተርታ ብዙኃን እውነታዎች ጋር የሚሰምሩ ቁጥሮችስ ከወዴት አሉ?ከሰሞኑ አንብቤ ያጠናቀቅሁት በቼክ - ፈረንሳዊው ሚላን ኩንዴራ የተፃፈ Immortality የተሰኘ መጽሐፍ፤ ስሜቱ ሙሉ በሙሉ አልለቀቀኝ ኖሮ፣ ጥያቄዎቼ ወደ ታሪኩ መለሱኝና አንዲት ሽራፊ ትዕይንት መዘዙ፡፡

አውራው ባለታሪክ ቼክ ሪፖብሊክ ውስጥ ሞራቪያ በምትባል ሚጢጢ የገጠር መንደር የሚኖሩ፤ አያቱን ህይወት በቅናት የሚያወሳባት ትዕይንት ናት፡፡ የአያቱ እውቀት በጠቅላላ የተገኘው በግል ተሞክሮ ብቻ መሆኑ ማርኮታል፡፡ ዳቦ እንዴት እንደሚጋገር፣ ጐጆ የሚቀለሰው ምኑ ከምን ተጋጥሞ እንደሆነ፣ አሳማ በምን አኳኋን እንደሚታረድ ወዘተ--- የተረዱት ሞክረውት ነው፡፡ የት/ቤቱ መምህር ዓለምን የሚያይበትን አግባብ፣ የቄሱን አመለካከት ሁሉ ያውቁታል፡፡ በስሚ ስሚ፣ በቱርጅማን ሳይሆን በቀጥታ ተጋፍጠውት፡፡ ከመንደሯ ጥበት የተነሳ ነዋሪዎቹ በየቀኑ በአካል ይገናኛሉ፡፡ ይጨዋወታሉ፡፡ ውሎ አዳራቸውን ይገመግማሉ፡፡ የህልውናቸው ሀቅ ያን ያህልም ከአይናቸው የተሸሸገ አይደለም፡፡

የመጽሐፍት ማጎሪያ ካርቶኖቼን አተረማምሼ፣ ልባድ አልባውን ክታብ አወጣሁትና አልጋ ላይ ተሰይሞ የተማሪዎቹን የፈተና ወረቀት ማረም፣ መከርከም ወደተያያዘው አስተማሪው ደባል ወዳጄ ተጠጋሁ፡፡ የኩንዴራን ገፀ ባህርይ አስተሳሰብ ከራሴው ትንታኔ ጋር አደባልቄ ካወጋሁት በሁዋላ ከመጽሐፉ የሚከተለውን አንቀጽ ቆነፀልኩለት:-

“She (አያቲቱ) had, so to speak, personal control over reality, and nobody could fool her by maintaining that Moravian agriculture was thriving when people at home had nothing to eat”

ቀጠልኩናም ከረጅም ጊዜ በፊት ያለምንም ግልጽ መነሻና አላማ የሞነጫጨርኳትን ደካማ ባለሁለት መስመር ግጥም፣ ለወጌ ማድመቂያነት በምርቃት መልክ በቃሌ ተወጣሁለት፡፡ እንዲህ:-

“ምንኛ ደስ ባለኝ ቁጥሮችን ባምናቸው

ታሪኬን ለመግለጽ አቅም እንዳላቸው”

ጓደኛዬ በአርምሞ ጥቂት ቆየ፡፡ የአንደበቱ በር ሲከፈት፣ ከፊት ለፊቱ የተዘረጋው ሌላኛው አልጋ ላይ ተመቻቸሁ፡፡ የጆሮዎቼን መጋረጃዎች ከዳር ዳር ገላልጬ፡፡

“ይገርማል - ግማሹን ቀኔን ያቃጠልኩበትን አታካች ስብሰባ ነው ዳግመኛ ያስታወስከኝ፡፡ መቼስ በስራ ሂደት ውስጥ የቁጥሮችን አምልኮ መታዘቤ አልቀረም፡፡ ያው አንተም እንደማታጣው የማስተምርበት ት/ቤት የግል ነውና የበረታ ፉክክር አለበት፡፡ ዘርፉ የራሱ መልክና ጠባይ ይኑረው እንጂ የንግድነት ካባውን ከቶ አይጥልም፡፡ ከምንነቱ አይካካድም፤ በንግድ ዓለም ደግሞ ነጥሮ መውጣት፣ ተሽሎ መገኘት፤ልቆ ደምቆ መታየት ያስፈልጋል፡፡ አሊያ ትበለጣለህ፡፡ ከኋላ ትቀራለህ፡፡ ስለዚህ ተማሪ ደንበኞቻችን ይበረክቱ ዘንድ በማስታወቂያ እሩምታታ ጃሎ ለማለት ቁጥሮች ሚናቸው አይነተኛ ነው፡፡ ስማችን በሀገር መንደሩ ተነዝቶ ከገበያው የዳጐሰ ድርሻ ለማፈስ በሚገባ እንገለገልባቸዋለን፡፡ እሱ ብቻም አይደለም - ቁጥሮችን መቆጣጠርንም ተክነንበታል፡፡ ምን መሰለህ? በአስደማሚ ክዋኔ ወደቀጣዩ ክፍል ወይም የህይወት ገጽ የሚያልፉ ተማሪዎችህን መጠን ታበዛለህ፡፡ ውጤታቸውን ታስመነድጋለህ፡፡ ከቻልክና ብርቱ ሰው ከሆንክ በላብህና በጥረትህ፤ ካቃተህ ደግሞ በላጲስ እና በብዕርህ፡፡ የተቀመጠውን ግብ እንዳትዘነጋ አለቆችህ አሰልቺ ስብሰባዎችን ይደግሱልህና በገደምደሜ ያስታውሱሃል፡፡ ከዚያ ለአደባባይ ትርዒት ወገብህን ታጠብቃለህ፡፡ ብዙ ታወራለህ፡፡ ብዙ ትንጣጣለህ፡፡ አውራጐዳናውን በማስታወቂያ ውርጅብኝ ታወናብደዋለህ፡፡ ወደ መቶ በሚጠጋጉ ፐርሰንታይሎች አጃቢነት የስኬትህን ገድል ታስነግራለህ፡፡ “እንዴት?” ሲል በጥያቄያዊ ምልከታ የሚያፈጥብህ ብዙም የለም፡፡ እንደገባኝ በዒላማህ መረብ ልትጠልፋቸው ያነጣጠርክባቸው በርካቶቹ በኑሮ ውጣ ውረድ ተሰንገዋል፡፡ የምትሰጣቸውን መረጃ አድቅቀው ፈጭተው፤ ፍሬና ገለባውን ለመነጠል ወይ ተነሳሽነቱን ወይ ፍላጐቱን ወይ ጊዜውን አጥተዋል፡፡ የሚታደሙህ ከጨረፍታ በማይዘል ግልብ የአልፎ ሂያጅ ትኩረት ነው፡፡ ቅጥፈትህን፣ ግነትህን፣ መሬት የማይነካ ባዶ ተስፋና ማጎምተህን አይነቅሱም፡፡ መንገድህን አይጠይቁም፡፡ አያይዘህ የምትተርክላቸው ሶስትና አራት እጅግ የመጠቁ አካዳሚያዊ ድል አድራጊነቶች ጠቅላላውን እንደማይወክሉ፣ ይልቁንም ልትዘረዝራቸው የማትፈቅዳቸው አያሌ ግብዓቶች ድምሮች መሆናቸውን አይገነዘቡም፡፡ ከስር የሚዋልለውን ቀጭን መረቅ ትደብቅና ስጋውን ከላይ አንሳፈህ ታቀርበዋለህ፡፡

“ቆይቼ ሳጤነው ለካ አገር በሞላ የያዘው ፈሊጥ ይህ ኖሯልና፡፡ በሪፖርት ልክፍት ክፉኛ አቅሉን ያልሳተ ተቋም እምብዛም አይገኝም፡፡ በሩቅ የምዛመደውን አንድ ሰው በማሳያነት ብጠቅስልህ ተገቢ ነው፡፡ ስሟን ካርታ ላይ ለማግኘት እንኳ የሚቸግር ገጠር ቀመስ ከተማ ውስጥ በግብርና ባለሞያነት ያገለግል ነበር፡፡ በኋላ ከኃላፊዎቹ ጋር መስማማት ተሳነውና ስራውን ትቶ ንግድ ጀመረ፡፡ የአለመግባባቱ አስኳል ምክንያት ቁጥር ነበር፡፡ አለቆቹ ለበላዮቻቸው የሚላከው የአፈፃፀም ሪፖርት በጀብደኛ ስኬት እንዲያሸበርቅ ይሻሉ፡፡ እውነታው ደግሞ ከዚያ በተፃፃሪ ቆሟል፡፡ ዘመዴ ሆዬ፤ የመጣው ይምጣ ብሎ ከሀቁ ጐን ተሰለፈ፡፡ እና ምን ተከሰተ? ቁርሾና ፍልሚያ፡፡

“አባዜው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከላይ እስከታች፣ በየትኛውም አቅጣጫ ተንሰራፍቶ ይታይሃል፡፡ ክፋቱ ደግሞ ለማረጋገጥ ማዳገቱ፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት የቦሎቄ ምርት በ14 በመቶ ጨምሯል ትባላለህ፡፡ አይገባህም፡፡ አትረዳውም፡፡ የአሃዙን ከፍታና ዝቅታ ብቻ ታስተውልና “ይሄማ ብዙ ነው” አሊያም “ውይ ምነው?” ነገር ታስባለህ፡፡ ተገላልጦ ከልብህ አይደርስም፡፡ ወይም “ሁለት ቢሊዮን ኪሎ ቦሎቄ ተመረተ” ዓይነት ዜና ትሰማለህ፡፡ የዜናውን ሃቀኝነት በምን አጣርተህ ትደርስበታለህ? ቆርጠህ ተነስተህ ቦሎቄ ስታሳድድ አትከርም? ስለዚህ ዝም ትላለህ፡፡ እንዲያው ዝም፡፡ የተባለውን አልተቀበልክም፡፡ አላጣጣልክምም፡፡ አትደግፍም፡፡ አትቃወምምም፡፡ ብቻ ዝም፡፡ “በአብዛኛው ትኩረት የሚሰጠው ተግባርን በአግባቡ መከወን አይደለም፡፡ መከወኑን ማወጅ ነው፡፡ ለእወጃ የተመቻቸ የታይታ ድል ከጨበጥክ አጨብጫቢ ድል ያለ ሙገሳ ያሽርሃል፡፡ በዚህም የቁልቁል ጉዞህ ሽቅብ ይመስልሃል፡፡ ይመስልልሃል፡፡ እዳው የሚወራረደው ግን ቆይቶ ነው፡፡”

አስደማሚው ዲስኩሩ ሳይደመደም ከትውስታዬ ማህደር አንድ ህንፃ ገንኖ ታየኝ፡፡ በየማለዳው አልፌው የምራመደው፣ ከቤታችን ባሻጋር የተገተረ፣ የወረዳው አስተዳዳሪ ያስገነባው ቤተ መጽሐፍት ነው፡፡ ከስምንት ዘጠኝ ወር በፊት የነበረው የምርቃት ስነ ስርዓት ትዝ አለኝ፡፡ ንግግሩ” ሽልማቱ” ቃል መግባቱ ወዘተ--- እስከዛሬም ድረስ ግን ለአንባቢያን ደጁን አልከፈተም፡፡ ይሄንን ያህል አብያተ መጽሐፍትን ገንብተናል የሚሉ ዘገባዎችና ዜናዎች ታሰቡኝ፡፡ በቃ ይሄው ነው --- የቁጥሮች ፋይዳ? ከሃሳቤ ስባንን የጓደኛዬ ማጠቃለያ ተቀበለኝ፡፡

“ስታትስቲክስ እንደማንኛውም የሰው ልጅ እንደፈጠራቸው እቃዎቹ ነው፡፡ አንዳንዱ ሀቅን ይገነዘብበታል፡፡ ሌላው እብለትን ይነዛበታል፡፡ መጥኔ ለእኛ ከንቱ ሽለላ ለተጣባን!”

 

 

Read 3747 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:10