Saturday, 22 September 2012 12:27

ተሬ ሞተሬ እና ከቤ

Written by  -ነ.መ-
Rate this item
(0 votes)

እውነተኛ ልብ ወለድ

ያ እሥር ቤት እንደላሊበላ ውቅር ቤተ - ክርስቲያን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የተሠራ ይመስላል፡፡ መሀከሉ ላይ ቦይ አለ፡፡ ግቢው ሲፀዳ የውሃ መውረጃ ነው፡፡ ግራና ቀኙ ላይ፤ አንድ-አለፍ አንድ-አለፍ ትይዩ በሮች አሉ - ከዚያው አለት የተቦረቦሩ የሚመስሉ፡፡ ከአየር ሆነው ቢያዩት፤ አንድ ትልቅ አፉን የከፈተ መቃብር ኖሮ ግራና ቀኝ ኪስ - መቃብር የተሠራለት ይመስላል፡፡ እሥረኞቹ ምግብ የሚበሉት በቀን አንዴ ነው - ዕድሜ ለተሬ! ተሬ በኩምቢ ቮልስቫገን ሞልቶ ጠዋት ጠዋት ሁሌ ዳቦ ይዞ ከተፍ ይላል፡፡ ከመንግሥት የሚሰጥ ራሸን - ቁርስ፡፡

“ተሬ ሞተሬ መጥቷል! ተሬ ሞተሬ መጥቷል!” ይላል እዚያ የድንጋይ አሸንዳ አፍ ላይ የተገጠመው የብረት በር አጠገብ፣ የደፍ - ሀዲዱ ላይ የቆመው ካቦ፡፡ ካቦ ማለት የአስተዳደሩን ደግ እይታ ያገኘ የእሥረኞች አለቃ ነው፡፡ ግን ያው እሱም እሥረኛ ነው፡፡ አንፃራዊ ነፃነት ያለው እሥረኛ፤ ማለትም፡- ፀሐይ እንደልቡ ለመሞቅ የሚችል፣ ነፋስ እንደልቡ መናፈስና መተንፈስ የሚችል እሥረኛ፡፡ አንዳንዴ እሥረኛ መሆኑን እስኪረሳ ድረስ ይኮራና - “ሁልህም ግባ በየክፍልህ! አለዛ ዋ አስቆነድድሃለሁ!” ይላል፡፡ ጠቁሞ ማስገረፍን እንደሥልጣን ቆጥሮት መሆኑ ነው፡፡ ማታ ማታ እሥረኛው ሁሉ ወደየድንጋይ ጉሮኖው ሲገባ እሱ ሲጃራ እያጨሰ እስከ አራት ሰዓት የመቆየት ነፃነት አለው - የታደለ እሥረኛ ነው፡፡

ሁሌ ጠዋት ጠዋት ተሬ ሞተሬ ዳቦ ይዞ ሲመጣ፤ ካቦው “ቤቶች ዳቦ ውሰዱ!” ይላል፡፡ (ራሱ ያመጣው ነው የሚመስለው፤ ትዕዛዙን ጮክ ሲያረገው!) ተሬ ሞተሬ ዋና ስሙ ተረዳ ነው፡፡ እስረኛው፤ ተረዳ የዳቦው ጌታ፣ የጉሮሮው አባት በመሆኑ “ተሬ” እያለ ያቆላምጠዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ እንደሞተር የሚሠራ ታታሪ ሰው በመሆኑ ሞተሬ የሚል ማዕረግ ጨመረለት - እሥረኛው፡፡

ተሬን የማይወድ እሥረኛ የለም፡፡ ተሬ ደንዳና፣ ጡንቻማ፣ አጭርና አስቀያሚ ሰው ነው፡፡ ያቺ ኩምቢ ቮልስቫገን ከልደት እስከሞት የተሰጠችው ነው የሚያስመስለው፡፡ ሲያሾራት እንደጉድ ነው፡፡ እሷም ታውቀው ይመስል ትታዘዘዋለች፡፡ ሙሉዋን ዳቦ በጆንያ ተሞልታ፣ በዳቦ ሽታ ታፍና ነው የምትመጣው፡፡

ግራና ቀኝ ስለምትንገዳገድና ሲጥሲጥ ስለምትል የምታቃስት ትመስላለች፡፡ ያም ሆኖ ተወዳዳሪ በሌለበት እየተዝለፈለፈ የሚሮጥ ሰው ብቻውን ያሸነፈ የሚመስለውን ያህል፤ ቮልሷም ሯጭ የሆነች ሳይመስላት አይቀርም፡፡

ተሬን ከሚወዱት እሥረኞች መካከል ከቤ ደምቡ አንዱ ነው፡፡ ተሬም ከቤን ይወደዋል! ተሬ ገና ከኩምቢው ዱብ ሲል ማንንም ፊትለፊት ያገኘውን እሥረኛ፤

“ከቤ ደህና ነው?” ይልና ይጠይቃል፡፡

“ደህና ነው፡፡ አለ ቆይ ልጥራልህ” ይልና ከቤን ያስጠራዋል የተጠየቀው እሥረኛ፡፡ ከቤ ሲመጣ “ታዲያስ የዳቦ አባታችን” ይለዋል ተሬን፡፡ “የዳቦ አባታችን” የምትለውን ቅጽል ከቤ ብቻ ነው የሚጠቀምባት፡፡ ከልቡ ነው የሚላት፡፡

ከቤ የረዥም ጊዜ እሥረኛ ነው፡፡ ከግርፍ ብዛት ግራ እግሩ ያነክሳል፡፡ ከቤ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ብሎ እንደሌሎቹ እሥረኞች ሃሳቡን ለአሣሪዎቹ ጥሎ ለጥ እንዳይል፤ ሁሌ አዲስ የፖለቲካ እሥረኛ በመጣ ቁጥር “ከቤን ሊያውቀው ይችላል፤ ወይም ከከቤ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል” በሚል ይጠራል፡፡ “አውቀዋለሁ” ካላለ ይገረፋል፡፡ “በአለንጋ እንዳውቅ ልታደርጉኝ አትችሉም!” ይላቸዋል ገራፊዎቹን፡፡

እንደደንቡ አንድ እሥረኛ ሲገረፍ ወይም ወፌ ሲገለበጥ (በእሥር ቤቱ ቋንቋ)፤ እግርና እጁ ታሥሮ፣ ዐይኑን በጨርቅ ተሸፍኖና የበሰበሰ በደም የራሰ የጨርቅ ኳስ ወይም ካልሲ በአፉ ተጐስጉሶ ነው፡፡ ከቤ እነዚህን ሁሉ ደረጃዎች ስላለፈ እግር - እጁን ከመታሠሩ በስተቀር ዐይኑን አይሸፈንም፡፡ አየ አላየ የሚያመጣው ለውጥ የለማ - መርማሪዎቹንና ገራፊዎቹን ሁሉ እንደ ውስጥ እግሩ ያውቃቸዋል - ማንን እንዳያይ ይሸፍኑታል? ምንም ቢገረፍ ስለማይጮህ ከቀን በኋላ ጨርቅ ባፉ መጐስጐሱንም ትተውታል፡፡ የተለመደውን አርገውለት ሲያበቁ፤ “አንተ ምን ድንጋይ ነህ ምንም አይሰማህም እንዴ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ “እንዴ አሥራ አንድ ዓመቴኮ ነው ለቶርች እንግዳ አይደለሁም -ለዶክትሬቴ እየሠራሁኮ ነው!” እያለ ደም በደም የሆነ እግሩን እየጐተተ በምፀት እየሳቀባቸው ይወጣል፡፡ አንዳንዶቹ እርር ድብን ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ በሆዳቸው ያዝናሉ፡፡ ራሳቸውን በከቤ ቦታ እያዩ ውስጣቸውን ሀዘን ሳይቆጠቁጣቸው አይቀርም፡፡ አያውጡት እንጂ ፊታቸውን በማየት ከቤ ይረዳላቸዋል - “እንጀራችሁ ነው ምን ታደርጉ?!” ይላቸዋል፡፡ አንድ ቀን ለአንደኛው ገራፊ፤

“ስትገርፍ ምን ይሰማሃል? ጀግንነት፣ ጉልበት፣ ጥላቻ ወይስ ሥራዬ ነው የሚል ስሜት?” ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡

ገራፊውም፤ “ከዓመታት በፊት ገራፊ ነበርኩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በመጣው መንግሥትም ገራፊ ሆንኩ፡፡ በዚህኛው መንግሥትም እንደምታየው ገራፊ ነኝ፡፡ ነገ እናንተ አሸንፋችሁ ብትመጡም ገራፊ ነው የምሆነው!” ብሎ ኮስተር ብሎ መልሶለታል፡፡

ከቤም እየሳቀ፤ “የሥራ ልምድ የመሰለን ነገር የለም!” ብሎታል በምፀት፡፡

ሌላ ቀን፡፡

ከቤ፤ “የዳቦ አባታችን” አለው ዛሬም ተሬን፡፡

ተሬ - “ምን ሆነሽ ታነክሻለሽ፤ ከቤ?” ሲል ጠየቀው በሩህሩህ ልሣን፡፡

ከቤ - “ትላንት ተገርፌ ነው - እንደተለመደው”

ተሬ - “አይዞሽ ቀን እስኪያልፍ ነው - ሁሉም የእጁን ያገኛታል!”

ከቤ - “ዕውነት ነው! ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል!”

ተሬ - “አይዞሽ!” ይልና የከቤን ፀጉር ያሻሽና “እዚህ ቢሮ አካባቢ ደረስ ብዬ ልምጣ! ለአለቆቼ ፊቴን ላስመታ - ዳቦውን ቶሎ ቶሎ አጋቡልኝ በያቸው” ብሎ ይሄዳል፡፡ የት እንደሚሄድ ማንም አያውቅም፡፡ የአለቆቹ ቢሮዎች ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው - ግራ ያጋባሉ፡፡ ግራ እንዲያጋቡ ተደርገው በዕውቅ መሀንዲስ የተሠሩ ይመስላሉ፡፡

ከየጉሮኖው የሚወጡት እሥረኞች ማዳበሪያ ማዳበሪያቸውን ይዘው ወደተሬ ኩምቢ ቮልስቫገን ይመጣሉ፡፡

ካቦው በብጫቂ ወረቀት የቤት ቁጥርና የእሥረኛ ብዛት ጽፎ ያነባል - ለዳቦ ማከፋፈሉ ሥርዓት፡፡

“አንድ ቁጥር - 55 ዳቦ” ይላል፡፡ እሥረኞቹ 55 ናቸው ማለት ነው፡፡

“አሥራ አንድ ቁጥር - 44፡፡ እንዴ ትላንት 39 አልነበራችሁም እንዴ?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ለመንግሥት መቆርቆሩ ነው፡፡

“ትላንት ከመጡት አዲስ እሥረኞች አምስቱን እኛ ላይ አይደለም የጨመርከው?” ይላል የክፍሉ ተወካይ፡፡

“እሺ ውሰድ፡፡ ሁለት ቁጥር - 50 ዳቦ፡፡ እናንተ ትላንት 52 አልነበራችሁም? ሁለቱ የት  ሄዱ?”

“ትላንትና ማታ ለምርመራ ተብሎ ተጠርተው ወጥተው በዛው አልቀሩም? ራስህ አደለም እንዴ የጠራሃቸው?”

“መንግሥት ወፍጮ ነው ሰው ይበላል? ምን ይሆናሉ ብለህ ነው በዛው ቀሩ የምትለው?” ይላል፤ ምን እንደተደረጉ እየታወቀ መንግሥትን ደግ ለማድረግ በመፈለግ ቃና፡፡

“በል ፖለቲካውን ትተህ ዳቦህን ይዘህ ሂድ! ፖለቲካ ዳቦ አይሆንም!”

ልጁ ይዞ ይሄዳል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ ለ12ቱም ክፍሎች ዳቦ ይታደላል፡፡ በሻይ ያንን በልተው ይውላሉ፡፡ ህይወት እንዲሁ ይቀጥላል፡፡

አንዳንዶቹ “ዕድሜ ለፀሐዩ መንግሥት!” ይላሉ በምፀት፡፡

ሌሎቹ - “የእሥር ዘመናችን ሳያልቅ እንዳንሞትበት ብሎ ነው፡፡ ለእኛ አስቦ መሰላችሁ?” ይላሉ፡፡

ደሞ ሌሎቹ፤ “የውጪ መንግሥታትን ፈርቶ ነው!” ይላሉ፡፡

“የውጪ መንግሥታት ደሞ በእኛ ሆድ ምን አገባቸው?” ይላሉ መላሾች፡፡

“ኧረ አርፈን እንታሰርበት” አሉ ከሁሉም ሸምገል የሚሉት እሥረኛ፡፡

በእንደዚህ ካሉት የአዘቦት የእሥር ቀናት በአንደኛው ዕለት፤ ተሬ እንደተለመደው “ቶሎ ቶሎ ብላችሁ አጋቡልኝ” ብሎ ከሄደ ቆይቷል፡፡

ከቤም እንደተለመደው ወደ ምርመራ ተጠርቶ የሄደው በጠዋት ነው፡፡

መርማሪዎቹ፤ ታውቀዋለህ የተባለውን አዲስ እሥረኛ አምጥተው

ከቤን፤ “የት ነው የምታውቀው?” ብለው ይጠይቁታል፡

“በፍፁም አላውቀውም!” ይላል ከቤ፡፡

“ብታውቀውና ነግረኸን ብትገላገል ይሻልሃል”

“የማውቀው ነገር የለም!”

“እንድታውቀው እናደርግሃለን!”

“ሌላ ምን አቅም አላችሁ መግረፍ ነው ዕውቀታችሁ!”

እያዳፉ ወደመግረፊያው ክፍል ይወስዱና አንጠልጥለው መግረፍ ይጀምራሉ፡፡ ከቤ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ!

በመካከል አንድ እንግዳ ድምጽ ወደ መግረፊያው ክፍል ይገባል -

“ጐበዝ የደከመው አለ ልተባበር?”

“ና አግዘኝ! ይሄ ደነዝ አላምን ብሏል!”

“እንዴት አባቱ አያምንም - እኔ አሳየዋለሁ!” ይላል ያው ድምጽ፡፡

ከቤ ይሄን ድምጽ ያውቀዋል፡፡ በደምብ ጆሮውን አስልቶ ሲያዳምጥ ይሄ ድምጽ የማን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ታወቀው - የተሬ ሞተሬ ድምጽ ነው፡፡ የዳቦ አባታችን!

ለካ ዳቦውን አጋቡልኝ እያለ ወደ ቢሮ የሚሄደው ወደ መግረፊያ ክፍል ነው!

እዚያ ጨለማ ክፍል ተሬ የሚችለውን ያህል ገርፎ ሐራራውን ከቤ ላይ ተወጥቶ ሄደ፡፡

ቆይተው፤ ከቤ ፍንክች ባለማለቱ ገራፊዎች ከመስቀያው አውርደው ገፈታትረው አስወጡት፡፡

ከቤ መሬቱ ላይ በደሙ እያተመ እየተወላከፈ ሲመጣ፤ ተሬ ኩምቢው ጋ ቆሞ አየው፡፡ ተያዩ፡፡

ከቤ ትክ ብሎ አይቶት

“ተሬ - ጉማሬ!” ብሎት አለፈ፡፡ ተሬ በቆመበት በድን ሆኖ ቀረ!

ከዚያን ቀን ወዲህ ተሬ ሞተሬን አገር የሚያቀው በ”ተሬ - ጉማሬ” ነው!! ተሬ-ጉማሬም እንግዲህ፤ ሀቀኛ ያገሩ ልጅ ነው!!

 

 

 

Read 2115 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 12:41