Saturday, 25 February 2012 14:00

ከስብሐት - ለስብሐት - የሳቅ አበባ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

እንግዲህ በሣቅ እንፈነዳለን፡፡ እንደፊኛ ሳይሆን እንደ አበባ በአመት አንዴም የመፈንዳት ዕድል ለማይገጥማቸው ጭፍግግ አበቦች እየፀለይን፡፡ በአመት አንዴ ካልፈነዱ ምኑን አበባ ሆኑት በማለት እያሽሟጠጥናቸው በሳቅ መፈንዳት ምርጫችን ብቻ አለመሆኑ ይታወቅልን፡፡ ዕጣ - ፈንታችንም እንጂ፡፡ ዕጣ - ፈንታ ደግሞ ቦታና ጊዜ አይመርጥም “ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ” ምናልባት ሥርዓተ ቀብር ላይም ሊሆን ይችላል - የሳቅ ሰለባነት ከች ይላል፡፡ የስብሐት ሥርዓተ ቀብር በራሱ፣ ከራሱ - ከባለቤቱ አንፃር ሲታይ አስቂኝ ሊሆንብን ይችላል፡፡ ቀና ብሎ ቢያየው ብለን የምንገምተው በሌሎች ቀብር ላይ ከሚሰጠው አስተያየት በመነሳት ነው፡፡

“ይኸው፣ የሐበሻ ድራማ!” ይላል ከልብ ያልሆነውን የማስመሰል ለቅሶ፡፡ “ልብ ካላማጠው ለቅሶ ከሹፈት ጋር ድሪያ የያዘ ሳቅ ይበልጥበታል፡፡

ስብሐት በህይወቱ (እኔ ሳውቅ) አንዴ ብቻ መሪር ለቅሶ ውስጥ ተዘፍቆ አይቼዋለሁ፡፡ ልጁ ዜና የሞተች ዕለት፡፡ ነፍሷ ከሥጋዋ ሲለይ፡፡ የሚጥል ህመሙ ሲነሳ እንደሚያደርገው ሁለመናው በላብ ተዘፈቀ፡፡ ከትከሻው እየተናጠ ተንሰቀሰቀ፡፡ አስር ደቂቃ ያህል፡፡ አበቃ! ከዚያ በኋላ ዜና የታጀበችው በሌሎች “የሐበሻ ድራማ” ነው፡፡ ስብሐት ዝም እንዳለ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፀመ፡፡ ማታ:-

“ቴሌቭዥን ክፈቱ” አለ

“ኧረ - አቦይ - ዛሬ…”

“ተውት፣ እሱ የሐበሻ ድራማ ነው፡፡ ይልቅ ክፈቱ” ተከፈተ፡፡ ለስብሐት ከዜና የቀረበ አልነበረም፡፡ ለእሷ እንጂ ለህዝብ ይሉኝታ አላለቀሰም፡፡ እኛም እንደሱ ከዚህ የይሉኝታ ዕዳ መቼ ነፃ እንወጣ ይሆን? ለማንኛውም ስብሐት እንደወጉ ዜናን እቀድማለሁ እንጂ በዜና እቀደማለሁ ብሎ አያስብም ነበር፡፡ የዛሬ አስራ አንድ አመት በፊት በፀና ታምሞ ሳለ ዜና ይሄን ደብዳቤ ጽፋለት ነበር፡፡

“አባ! አባዬ አባይዬ የኔ ቆንጆ ኑርልኝ፡፡ እወድሀለሁ፡፡ እስከምሞት ድረስ ለኔ ለዜና ይቺ አለም አንድ ታላቅ ስጦታ ብቻ አላት፡፡ ባቢዬን ብቻ ነው የሰጠችኝ (እኔም ሌላ ምን እንዳላት አላውቅም) ባቢ ብዙ ብዙ ብዙ ብዙ …ነው ለኔ፡፡ ስለዚህ ምንም ያልጐደላት ልዕልት ነኝ፡፡

ከብዙ ባሪያና አሽከር ጋር - ሁሉንም ባቢዬ ነው የሰጠኝ፡፡ እምናውቀው እውነት ነው፡፡ በዚች ምድር ላይ ያለው አንድ “ፍቅር” ነው፡፡ እና አፍቃሪ እሱ የኔ ባቢ ብቻ ነው፡፡ አልተጋነነም፡፡ ሺህ ምስክር እጠራ! - ዘመድ አዝማድ፣ እህት ወንድም፣ አልፈልግም ለምን ቢሉ… የግቢዬ ሙሉው ባቢዬ ብቻ ነው፡፡ ለሌላ ቦታም የለው፡፡ ነዋ! አባ እንዴት ነው?…”

እንዳጋጣሚ ደብዳቤው ያሳደረበት ትኩስ ስሜት ሳይበርድ አግኝቼዋለሁ፡፡ ዜና እራስዋም አለች፡፡ በሞት እንደሚቀድማት ተማምኖ እንዲህ አላት፡፡

“እኔ የምሞተው በሚወዱኝ ሰዎች ልብ ውስጥ መረሳት ስጀምር ነው፡፡ ሥጋዬ ሞተ ብለሽ አትዘኚ፡፡ በልብሽ እረስተሺኝ በአፀደ ሥጋ ከምንከላወስ ሞቼ ብታስታውሺኝ ለእኔ ምርጫዬ ነው”

የስብሐት ሞት ይሄ ነው፡፡ ከሚወዱት ሰዎች ልብ ላይ መፋቅ፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም ያኔ ተፈፀመ፡፡ ፍትሐተ ሞት የሌለበት፣ “የሐበሻ ድራማ” የማያስፈልገው ሞት፡፡ ዜና ከስብሐት ልብ ውስጥ አልተፋቀችም፤ እስከመጨረሻው፡፡ በአፉ ባያወጣትም በልቡ እንደሚያጉላላት እሙን ነው፡፡ (የእኛ ነገር፣ እንዳሰብነው ሥርዓተ ቀብሩን በሳቅ ማጀብ አቅቶን ወደ ሀዘኑ አደላን አይደል? ቀጥታ በሳቅ ወደመፈንዳታችን! የሳቅ አበቦች ሆይ!)

===================

ስብሐት የቀልድ ወዳድ ነፍስ አለችው፡፡ ይሁን እንጂ ለእኔ ከሚነግረኝ ቀልድ በላይ አንዳንድ የሚያደርጋቸው ነገሮች ያስቁኛል፡፡ “ኔሽን” ጋዜጣ እያለን ነው፡፡ ስብሐት አምድ ይዞ ይጽፍ ነበር፡፡ በሆነ ስህተት አንድ የስብሐት ወዳጅ ቅር ተሰኝታብን ኖሮ ለጋዜጣው ደብዳቤ ፃፈች፡፡ “ልከስ ስለሆነ መልሳችሁን አዘጋጁ፤ ጠበቃዬን አዘጋጅቻለሁ” የሚል፡፡ የጋዜጣው ምክትል አዘጋጅ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ እጅግ አድርጐ ተበሳጨ፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል በፃፈችው ጽሑፍ ላይ መልስ ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቋት እሷም ተስማምታ ጽሑፏ ጋዜጣው ላይ ስለታተመ ነበር፡፡ መልስ መጥቶ ሲወጣ ተቆጣች፡፡ ስለዚህ ምክትል አዘጋጁ እዚህ እንዳትገባ ሲል ለጥበቃው ነገረ፡፡

ጥበቃው መመሪያቸውን ተቀብለው እየጠበቁ ነው፡፡ ከውፍረታቸው የተነሳ የግቢውን የመኪና መግቢያ በር ሊሞሉት ትንሽ የሚቀራቸው ጥበቃ፡፡ በአንድ አሳቻ ሰዓት ያቺ የስብሐት ወዳጅ ስብሐትን ይዛው ወደ ኔሽን ቢሮ መጣች፡፡ ጥበቃው ገና ሲያይዋት አፍጥጠው “አንቺ አትገቢም” አሉ፡፡

“ለምን” ጠያቂው ስብሐት ነበር፡፡

“እንዳትገባ ተብሏል” የመኪና መግቢያውን በር በሰውነታቸው ሸፍነው፣ እግራቸውን አንፈራጥጠው፣ ለፀብ ተዘጋጅተው ቆሙ፡፡

“ከፈለግን ገርስሰንህ እንገባለን” የስብሐት መልስ ነበር፡፡ ይሄን የሰማሁ ቀን ግማሽ ቀን ሳቅሁ፡፡

*   *   *

እዚያው “ኔሽን” ጋዜጣ እያለሁ ነው፡፡ “ጠርጢዎስ - ከቫቲካን” የሚል ብዕር ስም የሚጠቀም ፀሐፊ ስብሐትን የሚወርፍ መጣጥፍ አቀረበልን፡፡ የፀሐፊውን ማንነት ባናውቅም በተደጋጋሚ የሚሳተፍ በመሆኑ መጣጥፉን ገረፍ ገረፍ አድርገን አወጣነው፡፡ ለካ ጽሑፉ መካከል ላይ አንዳች ሳት ያለው ስድብ ነክ ገለጣ ኖሮታል፡፡ ከስብሐት በላይ ያቺ ወዳጁ ቱግ አለች፡፡ ተቆጣች፡፡ ይገባት ነበርና ቱግታዋንና ቁጣዋን ተቀብለን ዝም አልን፡፡ ብዙም ሳይቆይ ስብሐት ደውሎልኝ፡፡ “ለዚያ ፀሐፊ መልስ አዘጋጅተናል” አለኝ፡፡ ደስ ብሎኝ ወዳለበት ቦታ ሄድኩ፡፡ የመልስ ፅሁፉን ሰጠኝ፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ መልስ የተባለው ሁለት መስመር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

“እንግዲህ ጠርጢዎስን ስንተነትነው፣ በትግርኛ ጠርጢ ማለት ፈስ ሲሆን ጠርጢዎስ ደግሞ ፈሶ ማለት ይመስለኛል”

“በቃ?” አልኩት

“በቃ!” አለኝ፡፡

ስብሐት በህይወቱ ሦስት ተከታታይ “ጠላቶች” አሉት፡፡ የሚበሽቅባቸው፡፡ አንዱን “ሸይጣኔ” እያለ ይጠራዋል፡፡ “ሸይጣኑ” የሆነበትን ምክንያት ቆይቶ ነው የተረዳሁት፡፡ ስብሀት “የተበደለውን” አይናገርም፡፡ የትም ይሁን የትም በደሉን ሲያስታውስ አጠገቡ ያለውን ሰው “የዚያ የሸይጣኔ ስልክ ቁጥር አለህ?” ይላል፡፡ አለኝ ከተባለ “ደውልልኝ” ከተደወለለት ቀጥታ ወደ ስድብ ይገባል፡፡ “አንተ ሸይጣኔ፣ …” ብዙ ስድብ፡፡

አንድ ቀን ደረስኩበት፡፡ “ሸይጣኑ” ከኛ ጋር ነው፡፡ “ቆይ ጋሽ ስብሐትን ወግሜያቸው (አበሳጭቼአቸው) ልምጣ” ብሎ ሲወጣ ተከተልኩት፡፡  ስብሐት በወቅቱ አንድ ኪዎስክ ውስጥ ቁጭ ብሎ ከኪዎስኩ ኃላፊ ጋር እየተጨዋወተ ደስ የሚል መንፈስ ሰፍኖበት ነበር፡፡ “ሸይጣኑ” ደርሶ ስብሐትን ሳይሆን እሷን መናገር ጀመረ፡፡

“ይሄ የስራ ቦታ ነው፡፡ ሌላ ነገር ካሰኘሽ ሌላ ቦታ፡፡ እዚህ …” ብዙ ከተናገረ በኋላ ወደ ስብሃት መለስ ብሎ “ደህና ዋሉ ጋሽ ስብሃት” አለው፡፡

ስብሃት ኩምሽሽ!

ሌላ ቀን ጠየኩት፣ ጐተጐትኩት፡፡ በኋላ እንዲህ አለኝ፡፡ “እየተጫወትክ ደስ ብሎህ መንፈስህ ተሟሙቆ ሳለ ያመጣና በረዶውን ይቸልስብሃል፡፡ ስልኩ አለህ?”

“አለኝ”

“እስኪ ደውልልኝ”

*   *   *

ከሦስቱ “ጠላቶቹ” ሁለተኛው በእድሜ እኩያው ነው፡፡ ይሁንና አንቱ ይለዋል፡፡ እርግጥ ሰውየው ከውትድርና ጡረታ ቢወጣም ገና የአርባ አመት ጎልማሣ ይመለሳል፡፡ እራሱን በምግብም፣ በአለባበስም የሚጠብቅ የአንድ ምግብ ቤት ኃላፊ ነው፡፡ ስብሐት ከሰዎች ጋር ለመመገብ ወደዚያ ሲሄድ “ጠላቱ” ከንፈሩን በሐዘኔታ በመምጠጥ ይጀምረዋል፡፡

“እምጵፅ! ለምን እዚህ ድረስ ታለፉዋቸዋላችሁ፡፡ ላይበሉ ነገር እዚህ ድረስ ማምጣት አልነበረባችሁም፡፡ እሳቸውን ሞግዚት ቀጥሮ እዚያው ቤት ቀስ እያለች በኩክ ማውጫ ብታበላቸው …”

“ይሄ ብሽቅ ምንድነው የሚለው?” ይላል ስብሐት ቱግ ብሎ፡፡ “ብሽቁ” ሁሌም ይሄው ነው፡፡ ስብሐት የ”ብሽቁ” ማብሸቅ ሆዱ ገብቷል፡፡ መንገድ ላይ እሱን የሚመስል ሲመለከት “ያንን ብሽቅ አይመስልም?” ይላል፡፡

*   *   *

አንድ ጊዜ ስብሐት ከአንዲት ልጅ ጋር በታክሲ (ሚኒባስ) እየሄደ ነው፡፡ ታክሲው ሞልቶ ስለነበር አንድ ጐረምሣ መጥቶ በሦስተኝነት ተዳበላቸው፡፡ መሀል መንገድ ላይ ልጅቷ መንጨቅጨቅ አለች፡፡ ለካ ልጅ እጁን ሰደድ አድርጐ ነካካቷይ ኖሯል፡፡ ስብሐት እንዳልገባው ለመምሰል ሞከረ፡፡ ልጁ መነካካቱን ልጅቷም መመነጫጨቋን ቀጥለዋል፡፡ በመካከል ስብሐት፡-

“ሰማህ ወይ” አለው፡፡ “ብትፈልግህ ኖሮ እኮ ዝም ትልልህ ነበር፡፡ አልፈለገችህም፡፡

ለምን አትተውም?”

“እ-ሺ ፋዘር” ግን አልተወም፡፡

ስብሐት እንደተበሳጨ መድረሻቸው እስኪደርስ ጠበቀ፡፡ ደረሰ፡፡ ስብሐት ልጅቷ ከወረደች በኋላ እንደመውረድ ቃጥቶ ጐረምሣውን በጥፊ አጮለው፡፡ “እንዴ?” ብሎ ጐረምሣው ሲነሣ ታክሲው ሙሉ ሰው ጮኸበት፡፡ በተለይ ረዳቱ “ጋሽ ስብሃትን ልትመታ ነው?” አነቀው፡፡

ቆየት ብዬ ስብሐትን ጠየኩት፡፡ “እችለዋለሁ ብለህ ነው የመታኸው?”

“አይ ሰዎቹን አይቼ ነው፡፡ መቼም እነሱ እያሉ አይመታኝ” አለ፡፡ ስልታዊ ማጥቃት እንበለው?

የስብሐትን ድርጊትና ንግግር ከቀልድ አንፃር አይቶ አይዘለቅም፡፡

እንዲህ አለፍ-አለፍ እያልን የቀልድ ዝክር እናደርጋለን፡፡ ነፍሱን በቀኙ ያኑርልን - አሜን!!!

 

 

 

 

Read 2180 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:25