Saturday, 26 November 2011 09:17

ሰቅራጥስን ዝከሩ - ተዘከሩ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሳምንት “የፍልስፍና ቀን” መከበርን ምክንያት በማድረግ፤ አንድ ነገር ለማለት ባስብም ሣይሆንልኝ ቀረ፡፡ ሆኖም ቀኑን ለመዘከር ዛሬም የረፈደ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ ጎዳና የያዘ የአዕምሮ ምርመራ ወይም ፍልስፍና የሚያጎናፅፈውን የመንፈስ ልዕልና ከማሳየቱ በተጨማሪ የምዕራባዊው ፍልስፍና የመሰረት ድንጋይ የሆነውን፤ አመፅን በህግ አክባሪነት፤ ክፋትን በቅንነት፤ ለማሸነፍ የቻለውን፤ ስለ እውነት ክብር ሄምሎክ ጠጥቶ የሞተውን ሰቅራጥስን አንስቶ ዕለቱን መዘከር ጥሩ ምርጫ ስለመሰለኝ ሰቅራጥስን መዘከር መረጥሁ፡፡

ሰቅራጥስ አስቂኝ ባርኔጣ በአናቱ ደፍቶ፤ ከአትሮኑስ ፊት ሆኖ በእጁ ላባ እንደ ያዘ የሚታይበትና በ13ኛው ክፍለ ዘመን የተሳለ አንድ አስገራሚ ስዕል በእንግሊዝ ይገኛል፡፡ በዚሁ ስዕል፤ ከሰቅራጥስ ጀርባ የሚታይ አንድ ሰው አለ፡፡ እርሱም አፍላጦን ነው፡፡ አጭር እና ቁጡ ጌታ የሚመሰለው አፍላጦን፤ መምህሩ የሆነውን ሰቅራጥስን በጣቱ ጎነጥ ሊያደርገው የከጀለ መስሎ በስዕሉ ይታያል፡፡ በሥዕሉ የሚታዩት ሰዎች “ሰቅራጥስ” እና “አፍላጦን” መሆናቸውን የምናውቀው ከመጠቆሚያ ቀስት ጋር “ሰቅራጥ” እና “አፍላጦን” የሚል ፅሁፍ በመኖሩ ነው፡፡ ታዲያ መጠቆሚያው ባይኖር ሥዕሉ እንቆቅልሽ እንደሆነ ይቀር ነበር፡፡ 
በሀገረ እንግሊዝ ኦክስፎርድ በሚገኝ “ቦድሊያን ላይብረሪ” በሚል የሚጠራን ቤተ-መፃህፍት በ1978 ዓ.ም ሊጎበኝ የሄደው የ20ኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ ዣኮዝ ዴሪዳ ያን ሥዕል አየው፡፡ ዴሪዳ በአንድ መፅሀፉ ስለዚሁ ስዕል ነገር ሲናገር፤ “ወደ ቤተ መፃህፍቱ ስገባ ሥዕሉን ድንገት አየሁት፡፡ እናም ግራ ተጋብቼ ድርቅ ብዬ ቆምኩ” ይላል፡፡ በዚያ ጊዜም ቅዠትና ራዕይ የተቀላቀለበት ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ድርቅ ብሎ እንደ ቆመ ያትታል፡፡ ስዕሉን ስንመለከት፤ አፍላጦን፤ አስቂኝ ባርኔጣ ያደረገውን እና ሽቁጥቁጥ ህፃን መስሎ የሚታየውን፤ መምህሩ የሆነውን ሰቅራጥስን የሚያዝ-የሚያናዝዝ መስሎ ይሰማናል፡፡ በዚሁ ስዕል የተበሳጨው ዣኮዝ ዴሪዳም በተቀሰረው የአፍላጦን ጣትና በሌላው የስዕሉ ይዘት ላይ እርግማን አውርዶበታል፡፡ ስዕሉ፤ ሲግመንድ ፍሮይድ የሚጠቅሰው “አባትን የመግደል” የሥነ-ልቡና አመፅ የተጋለጠበት መሆኑን ለማስረዳት ይችላሉ ብሎ ያሰባቸውን ጉዳዮች እየጠቀሰ ሀተታ አቅርቧል፡፡
ይህን የዴሪዳ ታሪክ የጠቀሰው ማርቲን ኮኸን የተባለ ሰው፤ “ሆኖም ስዕሉን ስንመለከት ሰቅራጥስን ከመርዳት በቀር የማዋረድ ሁኔታን የሚያመለክት ነገር አናገኝም፡፡ ይልቅስ በስዕሉ የምንመለከተው ሰቅራጥስን ገሸሽ የማድረግ የምዕራቡን የፍልስፍና ታሪክ አባዜ ነው፡፡ እውቁን የፈረንሳይ ፈላስፋ ዴሪዳን ያስደነገጠውም ይኸው ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም፤ የምዕራቡን የፍልስፍና ታሪክ ስታነቡ፤ በእርግጠኝነት ሰቅራጥስ የማይረባ ሰው መስሎ ይታያችኋል፡፡ ስለ ሰቅራጥስ የሚታወቀው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሰቅራጥስ በ469 ዓ.ዓ በአቴና ከተማ ስለመወለዱ አባቱ ቀራጺ፣ እናቱ አዋላጅ ስለ መሆናቸው ከመግለፅ ያለፈ ስለ እርሱ ብዙ አይነገርም” ይላል፡፡
ሰቅራጥስ ስለሚባለው ሰው ማንነት መጠነኛ ፍንጭ የሚሰጡ መረጃዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች መካከል አንዱ፤ ፕሮፌሰር ዩ ትሬዴኒክ በተባሉ አንድ የታሪክ ፀሀፊ የቀረበው ታሪክ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ትሬዴኒክ ስለ ሰቅራጥስ ሲያወሱ፤
“የሥዕል እና የፁሁፍ መግለጫዎች ሰቅራጥስ መልከ ጥፉ እና ደባደቦ ፊት፤ ደፍጣጣ አፍንጫ ጥቅጥቅ ካለ ቅንድብ ሥር ያሉ ጎላ ጎላ ያሉ ዓይኖች ያሉት፤ አፈ - ሰፊ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ፂሙ የተዠረገገ እና ራሰ ብራ ነው፡፡ ጥቅጥቅ ያለ ሰውነቱና አጭር ቁመናውም መከራ ቻይነቱን ያሳያሉ፡፡ ሲራመድ፤ ገተር - ገተር እያለ ነው፡፡ ሁሌም በባዶ እግሩ የሚሄድ ነው፡፡ እንደ ቆመ ለበርካታ ሰዓታት ተመስጦ ውስጥ ገብቶ ይጠፋል፡፡ . “አዕምሮው፤ ምናባዊነት ባይኖረውም፤ ወደር የለሽ አጥርቶና አጥልቆ ማሰብን የታደለ ጉጉ አዕምሮ ነው፡፡ የሰቅራጥስ አዕምሮ ግብዝነትን ፍፁም የሚጠየፍ ሲሆን፤ እምነቱ እንደ ፈቃደ ኃይሉ (will) ፅኑ የሆነ፤ ባህርይውም እንደ አስተሳሰቡ በሎጂክ የሚመራ ነው፡፡ በዚያ ጥርጣሬ በነገሰበት ዘመን ለሰው ልጅ፤ ወሣኙ ጉዳይ ሞራላዊ ብቃት እንደ ሆነ በጽኑ ያምን ነበር፡፡ ሞራላዊ ብቃትንና ዕውቀትን ነጣጥሎ አያይም፡፡ ሰቅራጥስ ያለው ቀጥተኛ ስብዕናም ትክክለኛውን ነገር ማየት የሚቻለው በተግባር ብቻ መሆኑን እንዲያምን አድርጎታል” ብለዋል፡፡ ይሄ ጥሩ ምስክርነት ነው፡፡ እዚህ የተገለፀው ነገር ሁሉ፤ ከዚያ የ13ኛው ክፍለ ዘመን ሥዕል ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ሰቅራጥስን በተመለከተ ከሚነገሩት ነገሮች ሁሉንም የሚያስማማው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም ሰቅራጥስ ከሁሉም ፈላስፎች የላቀ ተፅዕኖ ያሳረፈ ሰው ነው የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ያለ እምነት የተያዘው፤ ሰቅራጠስ ምን እንዳሰበ ሳይሆን ምን እንደ ተናገረ እንኳን በእርግጠኝት መናገር ባልተቻለበት ሁኔታ ነው፡፡ ሰቅራጥስ “ይህን አለ” የሚል እርግጠኝነት ለመያዝ የሚረዱ ጥቂት ነገሮች ቢኖሩም ጥርጣሬ ያላጠላበት እውነተኛው ሰቅራጥስ አሁንም የውሃ ሽታ እንደሆነ ቀርቷል፡፡
በእርግጥ የሰቅራጥስ ን አሻራ የሚያሳዩ ነገሮች በየቦታው አሉ፡፡ ነገር ግን ትክክለኛው ሰቅራጥስ “ማካቪቲ “ እንደሚሏት የአፈ-ታሪክ ድመት አድራሻው በውል አልታወቀም፡፡ ወጣት እና ገራገሩ አፍላጦን የወጣትነት አባዜ ያመጣበትን የግጥም መግጠም አመል እርግፍ አድርጎ እንዲጥል ስለመከረው ወግ አጥባቂው ሰቅራጥስ፤ ከአንድ ቦታ ተተክሎ ቆሞ ከሀሳብ ጋር ሲታገል ቀንና ሌሊት ስለሚያሳልፈው ሞገደኛው ሰቅራጥስ፤ በዚህ ዓመሉ የተገረሙ ሰዎችም የሰቅራጥስን መጨረሻ ለማየትና ምን ያህል ጊዜ እንደ ቆመ ይቆያል ብለው ለመወራረድ ፍራሽ አውጥተው በደጅ ስለሚያድሩ ሰዎች፤ እንዲሁም ከመልዓከ ሞት ፊት ቆሞ፤ ሄምሎኩን ፉት ከማለቱ በፊት ስለተናገረውና “ፊዶ “ በተሰኘው የአፍላጦን መፅሃፍ በውብ ቋንቋ ስለ ተገለፀው ሁኔታ ሚያወሱ ታሪኮች አሉ፡፡
“ወዳጆቼ፤ እኔ ልንገራችሁ፤ ሞትን መፍራት፤ አላዋቂ ሳለ አዋቂ ነኝ ብሎ ከማሰብ የማይለይ ጉዳይ ነው፡፡ የማያውቁትን ነገር አውቃለሁ ብሎ ከማሰብ የሚቆጠር ነው “ ሲል መናገሩን የሚጠቅሱ ታሪኮች አሉ፡፡
የታሪክ ፀሐፊዎች ስለ ሰቅራጥስ የታመነ ብቸኛ የመረጃ ምንጭ የሚሉት ዲዮጋነስ ላይሪተስን (Diogenes Laertius) ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ታሪክ ፀሐፊዎቹ ሃሳብ፤ ከላይሪተስ በስተቀር፤ እንደ ጉም የማይጨበጥ ስለ ሆነው ሰቅራጥስ የሚያትቱት ሰነዶች ሁሉ፤ ከእርሱ ይልቅ የሚናገሩት የፀሐፊዎቹን ፍላጎት ነው፡፡
ዜኖፎን፤ የተግባር ሰው መሆኑን የሚያመለክት ፈዛዛ ምስል ያለው ሰቅራጥስን ያሳየናል፡፡ ሄግል በዓለም ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው እና አንዱ - መጪውን፤ ሌላኛው -ያለፈውን ዘመን የሚያይ እና ጃኑስ እንደ ተባለው አማልክት ሁለት ፊት ያለው ሰው አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ፍሬድሪክ ኒቼ ደግሞ፤ “አላጋጭ እና በፍቅር የተገለፀ ጭራቅ “ እንዲሁም ፍልስፍናን የሚያዜም “በጭቃ የተደፈነ የአቴና ዋሽንት “ በማለት ይገልፀዋል፡፡
ሆኖም ከሁሉም ጎልቶ የወጣው አፍላጦናዊው ሰቅራጥስ ነው፡፡ ሁላችንም የምናውቀውን የሰቅራጥስን ምስል የፈጠረው እርሱ ነው፡፡ ሀሳባዊው አፍላጦን፤ ሰቅራጥስን የፍልስፍና ንጉስ እና ጣኦት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ በአፍላጦን ዓይን ሰቅራጥስ ቅዱስ እና የፀሐይ አምላክ ነቢይ ነው፡፡ እንዲሁም በሚያስተምረው ትምህርት የተነሳ መናፍቅ ተደርጎ የተወገዘ መምህር ነው፡፡ በጣም ውብ በሆነ ቋንቋ የሰቅራጥስን ታሪክ የነገረን እርሱ ነው፡፡ ለምሳሌ አፍላጦን ሲምፖዚየም ብሎ በሰየመው መፅፉ ውስጥ ስለ ሰቅራጥስ የሚከተለውን ይላል፤
“ገና ጎህ ሲቀድ አንድ ሃሳብ ከልቡ ከገባ፤ ያን ሲያብሰለስል በአንድ ቦታ ተተክሎ እንደ ቆመ ይውላል፡፡ ሃሳብ ጠኖ ሲያስቸግረው፤ የራሱ ጉዳይ ብሎ በመተው ፈንታ፤ ከቆመበት ሳይነቃነቅ እንቆቅልሽ የሆነበትን ነገር ለመረዳት ይጣጣራል፡፡ እንዲያ እንደ ቆመ እኩለ ቀን ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ እርሱን የሚመለከቱ ሰዎች ሰቅራጥስ ገና ጎህ ሲቀድ ጀምሮ በዚያ ቆሞ ሃሳብ ሲያወጣ ሲያወርድ ይኸው እስከ አሁን አለ በማለት በአድናቆት እርስ በእርስ ይነጋገራሉ፡፡ ወቅቱ በጋ በሆነ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ራታቸውን በልተው ምንጣፍና ፍራሽ ይዘው በቀዝቃዛው አየር በደጅ ለማደር ይወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ ሰቅራጥስ እንዲያ እንደ ቆመ ሌሊቱን ያሳልፍ እንደሆነ ለማየት ዓይናቸውን አፍጠው ያድራሉ፡፡ እርሱ አሁንም እንደ ቆመ ነው፡፡ ጎህ ሲቀድ እና ጀንበር ብቅ ስትል ለፀሐይ አምላክ ፀሎት አድርሶ ከዚያ አካባቢ ይሄዳል፡፡ “ በማለት ይገልፀዋል፡፡
እኔ ከሁሉ በላይ የሀገሬ ሰው፤ ሠረቀ ብርሃን ገ/እግዚእ -በ1947 ዓ.ም?፤ ክሪቶን ሲሉ ለሰየሙት መፅሃፋቸው በጻፉት መግቢያ ስለ ሰቅራጥስ ያወሱት ነገር ይበልጥ ደስ ይለኛል፡፡ ፀሐፊው የሀገራችንን ትውፊት፤ የግሪኩን ታሪክ እና ቋንቋ የሚያውቁ በመሆናቸው ትረካቸውን ለልብ ለአዕምሮ የተመቸ አድርጎታል፡፡ አሁን ቦታውን ለአቶ ሠረቀ ብርሃን ገ/እግዚእ እለቃለሁ፡፡ እንዲህ ይላሉ
ሰቅራጥስ የደሀ ወገን ነበር፡፡ አባቱ ሃውልት የሚያንፅ፤ እናቱም አዋላጅ ነበሩ፡፡ እንደ አፈ - ታሪኩ ከአይኑ በቀር ሌላው መልኩ ጅል የሚመስል የነበረው ሰቅራጥስ የት - ተማረ ሳይባል አልባሌ መስሎ፤ የአቴናን አደባባይ ሲመለከተው ቆይቶ፤ ጊዜው ሲደርስ ወይም የደረሰ መስሎ በተሰማው ጊዜ ተጠጋውና እሱም በፈንታው የተራ ሰው መሰል ጥያቄዎችን በመካከሉ እየጣለ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያም እንደ ነበረው በሚመስል “በተጠየቅ ስርአተ ነገር “ ቀጥ ባለና በማያላውስ፤ የመጨረሻውን እውነት እንጂ አስተያየትን በማይቀበል ስርዓተ - ሃሳብ እውቀት፣ ህላዌ፣ ህላዌ ስጋ፣ ህላዌ ነፍስ፣ ሰናይ፣ ርትዕ፣ ፅድቅ፣ እኩይ፣ መንግስት፣ ህግ፣ አስተዳደር፣ ሥርዓት፣ ምግባር፣ ዳኝነት፣ ፍርድ፣ መብት፣ ግዳጅና ግዴታ፣ ፍቅር፣ መውደድና ወዳጅነት፣ ሃሴት፣ ሃዘን፣ ተድላ፣ ችሎታ፣ ሃኬት፣ ሙያ፣ እንከን፣ ጥበብ፣ ብልሃት ወዘተኝ እነሱንም ስለሚመስሉ ኹሉ ምንድን ናቸው?፣ ምንስ ይመስሏችኋል እያለ እየጠየቀ፤ በሚያገኘው ምላሽ ላይ የነዚህን ሁሉ ተቃራኒና መልሶም የሚዛመደውን፤ ተመሳሳዩን፤ ተወራራሽ የሚመስለውን ወይም በፍፁም ጋፈኛ የሚሆነውን ሃሳብ እያስከተለ በጠቅላላ የሰውን ሥጋና መንፈሳዊ ህላዌን በሚመለከት መመራመርና መከራከር ሲጀምር “ራስህን ዕወቅ “ ሲል ተነሳ፡፡
ሰቅራጥስ ምድርን፣ ሰማይን፣ ክዋክብትን፣ ቀላያትን፣ አየርን፣ እፅዋትንና ሌላውን ፍጥረት ኹሉ ተመልክቶ ያደንቃል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ኹሉ በላይ፤ ሰውን እጅግ አብልጦ ስለሚያስብ “ራስህን ዕወቅ “ በማለት የተከተለው የፍልስፍና አካኼድ “ነገረ ሰብዕ “ ተብሎ ለሚጠቀሰው ለፍልስፍና ክፍል ዋና ተጠሪና የመሰረት ድንጋይ ያህል አሰኘው፡፡ ስለዚህም የሮማው ሊቅ ቆርቆሮስ (ciceron) “ሰቅራጥስ ፍልስፍናን ከሰማይ ወደ ምድር አወረደ “ ሲል ተናግሮለታል፡፡ ሰቅራጥስ “ራስህን ዕወቅ “ ከማለቱ ጋር “ማወቄ ምንም የማላውቅ መሆኔን መገንዘቤ ነው “ ሲል ሁለት መሰረታዊ ሃሳቦችን መነሻ አድርጎ በአደባባይ በኪነጥበባትና በተግባረ - ዕድ ቤቶች፤ በግልም ከወዳጅና ከተማሪዎቹ ዘንድ፤ እንዲሁም በተገኘበት ሥፍራ ሁሉ ራሱ ለመማር የሚሻ እየመሰለ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሃሳቦች ሁሉ ተፈላሰፈ፡፡
የፍልስፍናው አካኼድ ከመሰረቱ ካለፉት ፈላስፎች ሁሉ የተለየ ሲመስል፤ ከሶፊስቶች ስርዓተ - ሃሳብ ጋር ዝምድና አያጣም፡፡ ይኽውም ለፍልስፍናው አውደ - ዙሪያ ባደረገው ሃሳብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሶፊስቶች ከአስተያየት በቀር ፍፁም እውነትን የማይቀበሉ ሲሆኑ፤ እሱ የተጣራም ባይሆን በሰው አዕምሮና ኅሊና ዘንድ ፍፁም በሚሆን ጠቅላላ እውነት መኖር ያምናል፡፡ ይህ እውነት ግልጥ እንዲሆን፤ የሰውን ኹሉ ሃሳብ፤ በትምህርትና በአዕምሮ ምርመራ ማከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባል፡፡ የእውቀት መነሻና መድረሻ ርትዕና ፅድቅ፤ ሠናይ ምግባር ናቸው፤ መሆንም አለባቸው ሲል በስውር ሳይሆን በግልጥ በአደባባይ አስተምሯል፡፡
የአዕምሮ ስሜቱ ወደ አንድ አምላክ ያመራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስንኳ በንግግር ላይ “አማልክት” ሲል ቢሰማ ወይም “የአማልክት ፈቃድ፣ የአማልክት ሥልጣን “ ብሎ ሲናገር የተሰማበት ጊዜ ቢኖርም፤ ምንም ቢረቁ ያደጉበትና የአካባቢ አንደበት ልምድ የማይለቅ በመኾኑ የተባለ ይሆናል እንጂ፤ ስለ አንድ አምላክ የነበረው እምነት ጽኑ እንደ ነበረ ስለእርሱ ከተፃፈው ሁሉ ተገልጧል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ አንድ ፈጣሪ አምላክን ለመስበክ ወደ አቴና ሄዶ፤ በከተማው የሚገኙትን መካናተ - ፀሎት ሁሉ ዞሮ ተመልክቶ “ላልታወቀው አምላክ “ የሚል መሰዊያ - መስገጃ አየሁ ሲል የሚጠቅሰው፤ ሰቅራጥስ ያቆመው ነበር የሚል አፈ ታሪክ እስካለንበት ዘመን ይነገራል፡፡ ስለአስተዳደር የነበረው ሃሳብ በግልጥ ወደ ኦሊጋርኺያ ይስባል፡፡ ኦሊጋርኺያ፤ -የጥቂቶች አገዛዝ፤ በጥቂቶች ስልጣን መተዳደር? ስለተባለ ግን፤ ከፍተኛ መንፈስ፣ አዕምሮና ችሎታን የታደሉትን፤ በስልጣን ላይ ሆኖ አስተዳደርና ህዝብን ለማካሄድ የሚችሉትን የአስተዳዳሪዎችን ክበብ ይጠቅሳል እንጂ፤ በዘመናችን በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው፤ ከቶታሊተር አስተዳደር ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡ በህዝብ መብት ስም ይሆን የነበረው ዲሞክራቲያዊ ውካታ፣ ጋጋታና ትርምስ ሁሉ እጅግ ያሳዝነው ነበር፡፡ ህዝብን ለማስተዳደር ልዩ መዘጋጆ አስፈላጊ ከመሆኑ በላይ፤ መሪዎች፣ መሠረቱ መልካም ምግባር በሆነ ዕውቀት፣ ሙያና ችሎታ የተለዩ እና ከፍተኞች መኾን አለባቸው ሲል አስተምሯል፡፡ የዳኝነት እና የአስተዳደር ሥርዓት አዋቂዎች ከሚኾኑ ጥቂቶችና፤ ዕውቀታቸው ፅድቅና ርትዕን፤ ሠናይ ምግባርን ከለየ ሲመሩ እንጂ፤ የላይ የላዩን ብቻ የሚመለከት ይኼን ሁሉ ዘርዝሮ አውቆ ለመገንዘብ የማይችለው ተርታው - ህዝብ -ድምር - ህዝብ? መብት ካገኘሁ ዘንድ የወደድኩት - የመሰለኝን ብሎ በሚመርጣቸው ሹማምንት ብዛት የማይከናወኑ የማይጠበቁ መሆናቸውን ክርክር ባጋጠመው ሁሉ ሲናገር፤ በፍጥረታዊ መብት የዜጎች ትክክልነት (equality) በመሪነትና በአገልግሎት ደረጃ እኩል እንዲሆኑ አያስገድድም በማለት በግልጥ ይናገር ነበር፡፡ ሰቅራጥስ ይህን ባጭር - ባጭር ለመግለጥ የሞከርኩትን ሃሳብ ሲያሰማ ብዙ ተከታዮች ነበሩት፡፡ ይሁን እንጂ የሃሳቡ ተቃዋሚዎች የነበሩትም ጥቂቶችና ደካሞች አልነበሩም፡፡ ለዕድሉ፤ በእስፓርቲና በአቴና መንግስት መካከል የሆነው በታሪክ የፔሎፖኒሶስ ወይም የ30 ዓመት ጦርነት ከሚባለው ከእርስ በእርስ ግጭት ፍጻሜ በኋላ፤ በአቴና ከተማ -መንግስት፤ በእርሱ -ሶቅራጥስ፤ ሰላማዊ አካሄድና -ማስረዳት፤ ስልጣንን ለመጨበጥ ተከራካሪ በነበሩት ተማሮቹ ሲመራ የነበረው የኦሊጋርኺያ አስተዳደር ወገን ትግል፤ በዲሞክራቲያ ወገን ሲቸነፍ በሽማግሌው ፍላስፋ ላይ እንዲከሰስ ተመከረበት፡፡
ዋናው ከሳሹ አኒቶስ የሚባል በአቴና ከተማ ከፍ ያለ የቆዳ ማልፋት ሥራ የነበረው፤ ጥቅሙን ከዲሞክራቲያ አስተዳደር ጋር አዛምዶ የነበረ፤ አንድ ጊዜም በጦር አዝማችነት ታዞ የተላከበትን ግዳጅና ግዴታ በሚገባ ሳያከናውን ቀርቶ በክስ ከፍርድ ቤት ቀርቦ በገንዘብ እርዳታ ከቅጣት የዳነ ሰው ነበር፡፡ በዚሁም ኹነታው ምክንያት ሰቅራጥስ ስለ አስተዳደር ዘዴና ስለአስተዳዳሪዎች የሚያሰማው የነበረ ድምፅና ሃተታ በቀጥታ የሚመለከተው፤ የሚነካው ስለነበረ በተለይም የወለደው ልጁ የሰቅራጥስ ትምህርት ተከታይ በመሆኑ ያዝን ነበርና የፍላስፋው ዋና ከሳሽ ሆኖ ከእርሱ ጋር ከፍርድ ቤት ለመቋቋም በመቻሉ እጅግ ደስ አለው፡፡
እንዲህም ሆኖ -በ369 ዓ.ዓ ከክርስትናው በፊት፤ እንደ እርሱ ከተከፉ ሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በሰቅራጥስ ላይ የሚከተለውን ክስ አቀረበ፤ “ሰቅራጥስ ሃገሩ በሚያምንባቸው አማልክት ባለማመኑና እንግዳ መናፍስትን በመስበኩ ያምፃል -አመፀኛ ነው፤ የወጣቶቹንም ጠባይ የሚያጠፋ -የሚያበላሽ፤ በመኾኑ ያምፃል -ስለዚህም፤ ሞት ይገባዋል፡፡
በአጭር ፅህፈት፤ ለዘመኑ ባህልና መንፈስ ከባድ የመሰለ ክስ ቀረበበት፡፡ በእውነትም ነገሩ በቋፍ ያህል ነበረና የፈላፋው መከሰስ ካስቸጋሪ ሰው የሚገላግል ዘዴ ሆኖ ታየ፡፡ እንደ ፖሊክራቲስ ያለ አስመስሎ ለመናገርና ለመፃፍ ችሎታ የነበረው ተሟጋች በፍርዱ ዕለተ - ቀጠሮ የሚሰማውን የክስ መዘርዘሪያንና ማስረጃን ቃል ለአኒቶስ አሰናድቶለታል፡፡ እገሌ ቀረ ሊባልበት ባልተቻለ፤ የአቴና ህዝብ በሙሉ በተሰበሰበበት ከሳሽና ተከሳሽ ከአቴና ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
አስቀድሞ እንደ ተጠቀሰ አኒቶስና ጓደኖቹ -ሊኮንና ሜሊቶስ፤ ከሰቅራጥ ጋር በመቋቋማቸው ደስታ የተሰማቸው ቢመስሉም የሽማግሌውን ፈላስፋ ተራ መሰል አንደበት ጥልቅና ብርቱ ኃይልን የሚስቱ አልነበሩምና ድንጋጤያቸውን በብልጠት ፈገግታ ለመሸፈን ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ ትክ ብለው የሚመለከቱ የሰቅራጥስ ንቅ ዓይኖቹ ሁሉንም ያስደነግጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ልቡ ስለሰዎች ክፋት ያዝናል፡፡ ህሊናውም ወዳልታወቀው አምላክ ይመለከታል፡፡
ለባለስልጣኖች ብቻ ቀርቦ የነበረው ክስ በአደባባይ ተገልጦ ታወቀ፡፡ የክሱ ማስረጃ መመዘኛ ንግግር ከተሰማ በኋላ ተከሳሽም እንዲከላከል ተፈቀደለት፡፡ ነገር ግን ከፍ ያለ መንፈስ የሚሰማውና በዚሁም የሚመራ ስለነበረ፤ ከተራ ዝርዝር ሳይገባ በጠቅላላው በደለኛ አለመሆኑን በመግለጥ ከተናገረ በኋላ ለመከላከል የተፈቀደለትን ጊዜ ለመገሰጥ የተጠቀመበት መስሎት ሥጋዊ - ህላዌውን ለማቆየት ሳያስብ በነብይ የመንፈስ አለንጋ ተጋረፈበት፡፡ ቁጥራቸው 501 ከነበሩት አቴናውያን ዳኞች 220ው ነፃ ሲያወጡት 281 እንደ ጥፋተኛ ቆጥረውት በ61 የድምፅ ብልጫ “ይሙት በቃ “ ተፈረደበት፡፡
ፍላስፋው ግን የተጣለበትን ፍርድ በእርጋታ ሰምቶ ብዙ እጅግ ኃይለኛና ጥልቅ ሃሳብን የተመላ ቃል አሰምቶ “ እንግዲህ እኔ እንድሞት እናንተም ለመኖር መለያየታችን ነው፡፡ ነገር ግን ከሁለቱ የሚሻለውን የሚያውቅ አምላክ ነው “ ብሎ ከተናገረ በኋላ የችሎት መልስ ሆኖ ወደ እስር ቤት ሲያመራ፤ የፍርድ ቤቱ በመጥበቡ ውጭ ቆይተው የነበሩ ወዳጆቹ ተስፋ ቆርጠው ቢያለቅሱ “ገና ስወለድ እንድሞት ከፍጥረት የተወሰነ እንደ ነበር አታውቁም ኖሯልን? ለምን ታለቅሳላችሁ? “ ሲል ያዘኑትን ልብ ሲያፅናና ታይቷል፡፡
ይህንንም ሲያደርግ፤ መሰረተ ሃሳቦቹን በእምነት ጠብቆ ለመዝለቅ ሲል ነው እንጂ ኑሮን በመሰልቸት ወይም በፈላስፋ ትዕቢት ተመርቶ እና ከሌሎች ሰዎች ተለይቶ ለመታወቅ ሲል አልነበረም፡፡ እንዲህ ሆኖ ሰቅራጥስ በ70 ዓመት ዕድሜው በፅርዕ ጸቋንቋፀ ኮንዮን የተባለውን እንስላል የተባለውን የችኩታ ቅጠል ጭማቂ ፅዋ፤ የመተከዝና የድንጋጤ ሁኔታ ሳይታይበት ጨልጦ ጠጥቶ በአዕምሮ ምርመራ እምነት ወደ ተመለከተው መንፈሳዊ ነዋሪ ዓለም አለፈ፡፡
ዓለም እንደ ሰቅራጥስ ለዕውነት የሚሞት ፈላስፋ ዳግም ታገኝ ይሆን?

 

Read 2804 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:20