Saturday, 22 October 2011 11:54

ቺኑዋ አቼቤ - ሰውዬው

Written by  ቀዳማዊ ሰሎሞን
Rate this item
(0 votes)

በአፍሪቃ የሥነ - ጽሑፍ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የሀገረኛ ዘይቤ አጠቃቀም ሊቅ በመባል የሚታወቅ ስመጥሩው ናይጀሪያዊ ብዕረኛ ቺኑዋ አቼቤ በምስራቃዊው የናይጀሪያ ክፍል ልዩ ስሙ ኦጊዶ በተባለ ሥፍራ ከአንድ የክርስቲያን ቤተሰብ ተወለዱ - ጊዜው 1930 ዓ.ም ነበር፡፡ 
ከኢባዳን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1953 ዓ.ም ከተመረቁ በኋላ በናይጀሪያ የሬዲዮ ስርጭት ፕሮግራም ውስጥ ተቀጥረው አገልግለዋል፡፡ ዛሬ በአርባ አምስት የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ የዓለማችንን ኪናዊ ጥማት በማርካት ላይ የሚገኘውንና “ቲንግስ ፎል አፓርት” በሚል ርዕስ የሰየሙትን የበኩር ሥራቸውን በ1958 ዓ.ም ለንባብ አበቁ፡፡

“ቲንግስ ፎል አፓርት” በተሰኘው ቀዳማዊ ፈጠራቸው የብዕራቸውን ትባት ያለጥርጥር ያስመሰከሩት አቼቤ፤ ከ1958 -1966 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት ውስጥ ሌሎች ሥሎስ ልቦለዶቻቸውን በተከታታይ አሳትመዋል፡፡ ቀጣይ ሥራቸውን ለማየት ግን የኪነ - ጥበቡ ዓለም ለድፍን ሃያ አንድ ዓመታት ያህል መቆየት ነበረበት፡፡  
በ1981 ዓ.ም “አንትሒልስ ኦፍ ዚ ሳቫና” ብለው የሰየሙት ልቦለድ መጽሐፋቸው በእንግሊዝ ምድር ታትሞ ከወጣ በኋላ፣ ራሳቸው አቼቤ ለሁለት ወሰነ - ትምህርት በክብር መምህርነት ተጋብዘው አምኸረስት ውስጥ በሚገኘው በማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ በነበሩበት ወቅት በአሜሪካ ሀገር በድጋሚ ለመታተም በቃ፡፡ ይህ ድርሳን ጠሊቅ ሙያዊ ክለሳ የተካሄደበት ከመሆኑም በላይ ጥቁሩን የፈጠራ ሰው የዓለማችን ሕብረተሰብ ደምና ሥጋ ሆነው እንዲዋሀዱም አስችሏቸዋል፡፡
ታላቁ አፍሪቃዊ ጠቢብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ምድር ያቀኑት በ1963 ዓ.ም ሲሆን፤ አሜሪካ በዚያን ወቅት በቀውጢ ትዕይንት የተሳከረችበት ዘመን ነበር - አንድ መቶኛው ዓመት የነፃነት ክብረ - በዓል የሚደለቅበት…በማርቲን ሉተር ኪንግ ፊታውራሪነት በዋሽንግተን ከተማ ውስጥ መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ አመጽ የተካሄደበት . . . ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በጥይት አረር የወደቁበት፡፡ ዘመኑ የአሜሪካ አየር በነውጥ የታወከበት ዓመት ከመሆኑም በላይ በሰው ልጆች መሀል ይፈፀም የነበረውን የዘር መድልኦ በመቃወም “ቀጣዩ ወላፈን” በተሰኘ ርዕስ፣ ደራሲ ጄምስ ባልድዊን መራር ተቃውሞአቸውን ገሀድ ያወጡበት ወቅት ነበር፡
በ1980 ዓ.ም አቼቤ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አሜሪካ ምድር በመሻገራቸው ሳቢያ ፍሎሪዳ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪቃ ሥነ - ጽሑፍ ማህበር ስብሰባ ላይ ከባልድዊን ጋር ተገናኝተው ወዳጅነት ለመመስረት በቁ፡፡ እንደገናም በ1981 ዓ.ም ለመገናኘት ሁለቱ ፀሐፍት ቀጠሮ ይዘው ሳለ፣ ታዋቂው ደራሲ ጄምስ ባልድዊን በታህሳስ ወር 1987 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የተነሳ ውጥናቸው መከነ፡፡
በ1977 ዓ.ም በሥነ - ጽሑፍ የዶክትሬት ማዕረግ ለሰጣቸው ለማሳቹሴት ዩኒቨርሲቲ ቤተኛ የሆኑት አቼቤ፤ ከ1970 -1975 ዓ.ም በዚያ ላደረጉት ጉብኝት ፍላጐቱን የጫሩባቸውም ሆኑ ማንኛውንም ወጪያቸውን የሸፈኑላቸው ከአሜሪካ ዝነኛ ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት ሟቹ የብዕር ሰው ሀርቬይ ስዋዶስ ነበሩ፡፡ ወቅቱ የቢያፍራ ጦርነት የተጋጋመበት ዘመን ነበር፡፡
በልሂቅ የፈጠራ ሥራዎቻቸው ውስጥ የጥቁሩን ዓለም ሕይወት አበራይተው የናኙት አቼቤ፤ በአሜሪካ ቆይታቸው ወቅት ደብልዩ ኢ.ቢ.ዲ ቦይስ ውስጥ በሚገኘው የአምኸረስቱ የአፍሮ - አሜሪካ ጥናት ማዕከል አስተምረዋል፡፡ በዚያን ወቅት ነበር ከሰፊው የዕውቀታቸው ውቅያኖስ እየጨለፉ ጥበብ ለተጠሙ ደቀመዝሙሮቻቸው የእውቀትን ብርሃን የፈነጠቁት፡፡ ያኔ በትምህርት ክፍሎቻቸው ውስጥ ከገናና የአፍሪካ ፀሐፍት መካከል የኬኒያዊውን የጀምስ ንጉጊን፣ የካሜሮኑን የፈርዲናንድ ኦዮኖን፣ የናይጀሪያውን ተወላጅ የአሞጽ ቱቶላን፣ የሴኔጋሉን የዑስማን ሳምቤኒን እና የሼክ ሀሚዱ ኬኒን፣ የጊኒውን የካማራ ሌይን፣ እንዲሁም የደቡብ አፍሪቃዎቹን የአሌክስ ላ ጉማን፣ የሎዊስ ንኮሲንና የደቡብ አፍሪቃዊቷን ደራሲ የናዲን ጐርዲመርን ኪነ -ጥበባዊ ሥራዎች እየፈተሹ መተንተን ያዘወትሩ ነበር፡፡ እንደደቡብ አፍሪቃዊው ደራሲና ሃያሲ እንደ ሕዝቅኤ መፋለሌ አባባል፤ እነዚህ ጠቢባን “የሽግግር ወቅት ተምሳሌቶች - ከንቡር ማህበራዊ እነርሱነታቸው ውስጥ የቀዱትን ኪነ-ጥበባዊ ጠበል በምጡቅ ምናባዊ ድጋም ባርከው የወደፊቱን ሕይወት የሚያረሰርሱ ጠቢባን ናቸው፡፡”
የጥቁር ዓለም ፈርጥ ስለሆኑት ስለቺኑዋ አቼቤ የአፍሮ - አሜሪካው ጥናት ማዕከል ዳሬክተር የሆኑት ጁለስ ቻምተስኪ ሲናገሩ፤ “የአቼቤ በትምህርት ክፍሎች ውስጥ መገኘት እንደ ኤሌክትሪክ ንዝረት የሚቆጠር ነው፡፡ ማራኪው ግልጽነታቸው፣ ጥዑም አንደበታቸው፣ ጠሊቅ አስተውሎታቸውና የማይጠገበው ለዛቸው…ድምር ውጤት ሰውዬውን ፍፁም አድርጓቸዋል፡፡” በማለት የንሴብሖ ጠበል እንደረጩአቸው ይታወሳል፡፡
በ1988 ዓ.ም መባቻ ግድም በዋሽንግተን ከተማ መሀል በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ለተገጠገጠው ወፈ - ሰማይ ሕዝብ “አንትሒልስ ኦፍ ዚ ሳቫና” ከተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ጥቂቱ ክፍል በፈጣሪው አንደበት ተነበበ፡፡ በአቼቤ ልሣን የተነበበው ክፍል ድርቅ በመታውና ካንጋን በተባለው አንድ አፍሪቃዊ ልብወለድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የአባዞን መንደር አረጋዊ ያደረጉትን ንግግር ነበር፡፡ አቼቤ ንግግራቸውን ሲያሰሙ በጥቁር ሙሉ ልብስ ከመጌጣቸውም በላይ በትልቁ የዓይን መነጽራቸው መስኮት በኩል የብሩህ አስተውሎታቸውን ጮራ እየፈነጠቁ ነበር፡፡ በታሪኩ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ፣ አዛውንቱ ገጠሬ የሕዝብ ተወካዮችን እየመሩ ወደዋናው ከተማ ገሰገሱ - “ብርንዶውም ሆነ ካራው በእጃቸው ከሆነው፣ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ከፈሰሰው ቅንጥዎቹ ከተሜዎች ዘንድ ደረሱ” - ለፕሬዚዳንትነት በተደረገው ውድድር ላይ የአባዞን ሰዎች ድጋፋቸውን ባለመስጠታቸው የተነሳ በአካባቢው ምስለኔ ትዕዛዝ የተዘጉባቸው የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶቻቸው እንደገና እንዲከፈቱላቸው “አቤት” ለማለት ነበር ወደ ከተማው ያቀኑት፡፡
አረጋዊው መልዕክተኛ ታሪክ አዋቂነትንና ተራኪነትን አፍሶ የሰጣቸው የዕድሜ ሀብታም ነበሩ፡፡ የአባዞን ሰዎችን ብሶት ለአቤቱታ ሰሚዎቹ ሲያቀርቡ - “ታሪክ ነው ዋቢያችን - የታሪክ ነቃሽነት ከሌለን የወደፊት ጉዞአችን የተዳፈነብን ልበ - ሥውራን ነን” የሚለውን ቃል ደጋግመው ተናገሩ፡፡ ስለነብርና ስለአዞ ጠብ የተነገረውን አፈ - ታሪክም አበክረው አወሱ፣ “የእኛ ድካምና ጥረት ምናልባት ወደፊት ልጆቻችን፤ አባቶቻችን በእርግጥም ለጊዜው ተሸንፈዋል፣ ቢሆንም የአቅማቸውን ሞክረዋል” እያሉ በኩራት እንዲያስቡን ብቻ ነው፡፡” ሲሉ ጨመሩ፡፡ ይኸው አባባላቸው እንደድፍረት ተቆጥሮባቸውም ዘብጥያ ተወረወሩ፡፡
ለአዛውንቱ እንግልት በመቆርቆር የሀገሪቱ “ብሔራዊ ጋዜጣ” ዋና አዘጋጅ ሆኖ የተሾመው ኢኬም ኦሲዲ ተቃውሞውን ቆሰቆሰው፡፡ ኢኬም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ስብሰባ ከጠራ በኋላ በዕድሜ ፀጋ የሸበቱት አዛውንት ወህኒ ሊገቡ የበቁበትን ምክንያት ሲገልጥ “ታሪክ አዋቂዎች እንደጦር ይፈራሉ፡፡ የዜጐችን መሰረታዊ መብቶች በኃይል ነጥቀው፣ ሰብአዊ ክብረ - ህሊናን ደፍቀው፣ ታላቁን የሰው ልጅ አዕምሮ አንኳሰው የሚረግጡን ገዢዎቻችንና የታሪክ ማህደር የሆኑ አረጋውያን ዓይንና ናጫ ናቸው፡፡” ሲል ተንደረደረና በሽማግሌው ላይ የተዋለውን ግፍ ዘከዘከው፡፡
እነዚህ ከልቦለዱ ሁለት ማዕዘናት የተሰነዘሩ ገለጻዎች፣ ማህበረሰባዊው ይትባህል ያለውን ረቤታና ይህንኑ ዘይቤ በአንባብያን አዕምሮ ውስጥ ለማስፈር ደራሲው የታደሉትን የላቀ ክህሎት ያረጋግጣል፡፡
የናይጀሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደባቸው ማለትም ከ1967 -1970 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት ውስጥ አቼቤ የቢያፍራ ተገንጣዮችን ወግነው ነበርና የጠቢቡ መኖሪያ ቤት ለውድመት ተዳረገ፡፡ በዚህም የተነሳ ልቦለድ መጻሕፍትን ከመፃፍ ይልቅ ብዕራቸውን ወደ ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ዘውጐች ለማዞር ተገደዱ፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት ነበር በሥነ ግጥም ዘርፍ “የገና በዓል በቢያፍራ” እና ሌሎች የስንኝ ቋጠሮቻቸውን፣ “ልጃገረዶች በጦርነት ነበልባል ውስጥ” የተሰኘውን የአጫጭር ልቦለዶች መድብላቸውን፣ “ነብር እንዴት ጥፍራም ሆነ” የተባለውን የሕፃናት መጽሐፋቸውንና “የፍጥረት ቀን ማለዳ” የተሰኘውን መጣጥፍ ለመፃፍ የበቁት፡፡
ቺኑዋ አቼቤ የፈጠራ ሥነ - ጽሑፍ ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ የቀለም ቀንድ የተሰኙ መምህርም ጭምር በመሆናቸው አያሌ ደቀመዛሙርት ያፈሩ የቀለም አባት ናቸው፡፡ ኢኑጉ ውስጥ በሚገኘው የአናምብራ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጥብቅ ቻንስለር ሆነው የሠሩበትም ወቅት ነበር፡፡ የወገኖችን ክብረ - ሕሊና ላለማስደፈርና የጥቁር አፍሪቃውያንን መብት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን የሚተጉ ብዕረኛ እንደመሆናቸው “ለማንነቱ ሊሟገት የሚሻና ለሰው ልጆች በጐነት የሚያልም ማንኛውም ልባም አፍሪቃዊ ደራሲ ለእግዚአብሔር ብቻ ጥብቅና መቆም የለበትም - ለሰይጣንም ጭምር እንጂ፡፡” በማለት ለአህጉራቸው ያላቸውን ቀናኢነት በምፀት ተናግረዋል፡፡ የአፍሪቃውያን የብዕር ቀስት ወዴት መወንጨፍ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አቼቤ በአንድ ወቅት ወደ አሜሪካ አቅንተው በነበረበት ጊዜ፣ ነጮች ለአፍሪቃ ኪነ - ጥበብ የነበራቸው ዝንባሌ ከምንጊዜውም በላይ ጐልብቶና ጐምርቶ በመመልከታቸው መንፈሳቸው ጠገበ፡፡ በወቅቱ አቼቤ የዕውቀታቸውን ማዕድ ካቋደሷቸው ተማሪዎቻቸው አንዱ ስለመሲሁ ተሰጥኦ ያለውን አድናቆት ሲናገር፣ “በ - ቲንግስ ፎል አፓርት ውስጥ የተሳለው ኦኮንክዎ የተባለው ገፀ ባህርይ ቁርጥ ወላጅ አባቴን ይመስለኛል” በማለት የአቼቤ የፈጠራ ሥራዎች እንደ ልቦለድ የሚነበቡ ጽሑፎች ብቻ ሳይሆኑ በአካል ታይተው እንደሚዳሰሱ የገሀዱ ዓለም ፍጡራን እንደሚስተዋሉም ጭምር ገልጧል፡፡
አቼቤ በአሜሪካ ምድር ስላስተዋሉት ሁናቴ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “በእንዲህ ዓይነቱ ሰፊ ሀገር ውስጥ ጐባጣውም ሆነ ቀናው በአንድ ላይ ተዘንቆ ይገኛል፡፡ የቀለምና የዘር መድሎኦው አንጀት ያበግናል - ሕሊና ያቀነጭራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በምሁራኑ ዘንድ መጠነኛ የእርካታ መንፈስ ሰፍኖ ይታያል” በማለት ነበር ምድሪቱ የተቃርኖ ሕይወት መስተዋት መሆኗን ያስረገጡት፡፡ በበጐ መልኩ ሲስተዋል፤ የሕዝቡን በአደባባይ ነፃ አስተያየት የመግለጽ ባህል ያደንቃሉ፡፡ በተጨማሪም በአሜሪካንና በአፍሪቃ መካከል ያለውን ቀና ግንኙነት ሲያወሱ “ግንኙነቱ በእውነተኛ ሰብዓዊ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተና ከጌታ ሎሌነት መንፈስ ፍፁም የፀዳ መሆን ይገባዋል፡፡” ሲሉ ምሁራዊ ትዝብታቸውን አስፍረዋል፡፡
ዛሬ የ81 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ቺኑዋ አቼቤ እና በአንድ ወቅት ማሳቹሴትስ ውስጥ መምህርት የነበሩት ባለቤታቸው እመት ክሪሲቲ ያላቸውን የጋራ መርህ ሲገልጡ፣ “ከጥንት እኛነታችን ጋር ሳንፋታ፣ ከበቀልንበት ሕዝብ ጋር በጽኑ ባህላዊ ሰንሰለት የተቆራኘን መሆናችንን ዘወትር ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡” በማለት የትዳር ጓደኛሞቹ በጥምረት ተናግረዋል፡፡ አቼቤና ውሃ አጣጪያቸው ዘመናት ባስቆጠረው የፍቅር ህይወታቸው ትዳራቸው አራት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፤ ከእነዚሁ የአብራካቸው ክፋዮች መሀል ገሚሶቹ የቀለም ትምህርታቸውን የቀሰሙት እዚያው አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡
ዛሬም አቼቤና ክሪሲቲ የእርጅና ዘመናቸውንና ትዳራቸውን በደስታ ይመራሉ፡፡
ቺኑዋ አቼቤ - ሥራቸው
ቀጥሎ ከአቼቤ ልሂቅ ጥበባዊ ድርሳኖች መሀከል በሦስቱ ላይ መጠነኛ ቅኝት እናድርግ፡፡ እግረ - መንገዳችንንም የጠቢቡን የዘይቤ አጠቃቀም ሊቅነት፣ ንጥር አፍሪቃዊነትና ኪነ ጥበባዊ ኪሂሎት እንመዝን ዘንድ በቅንጭብ እንመልከት፡፡
ከ - አንትሒልስ ኦፍ ዚ ሳቫና
“… በመኸር ወቅት ሰማይና ምድር ከጣብቂያቸው ሳይላቀቁ፣ ጥዑም የሆነው የማለዳ እንቅልፍ ጫና ሲደብት፣ እንደመርግ በከበደው ሌሊት፣ የንጋት ወፍ ስትጮህ ገበሬውን ለማንቃት - በዚያ ቁርና ዳፍንት፡፡ ለመሆኑ ገበሬው እንቅልፍ እንደተጫነው ብትት ብሎ ነቅቶ ወደማሳው ይገሰግሳል ወይንስ በንጋት ወፋዋ ላይ መልሶ ይጮህባታል፣ “አፍሽን ዝጊ እባክሽ… መንጋቱን ማን አባሽ ነው የነገረሽ? አንቺ ራስሽ አንድ ፍሬ በቆሎ ዘርተሽ፣ አረሙንስ አርመሽ ለመሆኑ ታውቂያለሽ - ምን አዝምረሻል በሕይወትሽ?” ብሎ ያበሻቅጣት ይሆን? ፈጽሞ! በእርግጥም አፈር መስሎ በመሥራት፣ ጉንጩን ሞልቶ ለመብላት የሚጥር ታታሪ ገበሬ፤ ከሌሊት ወፍዋ ጋር እንካ ሰላንቲያ አይገጥምም፡፡ ጩኸቷን መና አያስረቀውም፡፡ ይነቃል - ይነሳል - ትዕዛዟንም ይፈጽማል፡፡
“ለመሆኑ በእስከዛሬው ሕይወታችሁ ይህን ጉዳይ አስባችሁበት ታውቃላችሁ? እኔ ግን እውነቱን ልንገራችሁ፣ ምንተስኖት የሆነው አምላክ ዓለማችንን በዚህ መልክ ነው ከፋፍሎ የፈጠራት፡፡ ሁሉም የየራሱንና የግሉን፤ የንጋት ወፍዋም ጩኸቷን፣ ገበሬውም እርሻውን፡፡
“ሰማያዊው ጌታ ለአንዳንዶቹ፣ የመንቂያው ሰዓት የመድረሱን ትንቢት የመናገር ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ለሌሎቹ ደግሞ የጥሪውን ደወል ሰምተው የመንቃቱን ብርታት፣ በሚንተገተግ የደም ዑደት የመነሳት፣ ባጋተ ወኔ ወደ ትግሉ አውድማ የመዝመት፣ ከጠላት ጋር ጉርቦ ለጉርቦ ተናንቆ የመሟሟት…ተልእኮ ያድላቸዋል፡፡ ከእነዚህ የተለዩ ደግሞ አሉ - አንገታቸውን ደፍተው፣ ጦርነቱ እስኪያልቅ ድረስ አድብተው፣ ብዕር ከወረቀት አዋደው፣ ታሪክ ቀርፀው ለማስቀረት የታደሉ፡፡
“የውጊያውን መጀመር የሚያበስረው የእምቢልታ ድምጽ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው፤ የመተረኩም ጉዳይ እንደዚያው …ሁሉም በየፈርጁ የየራሱ ረቤታ አለው፡፡ ከእነዚህ በቅደም ተከተል ከተንሰላሰሉ ድርጊቶች መሀል አንዱን ብናጣ ታሪካችን ሰንካላ ይሆናል፡፡ ነገር ግን “ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ የትኛው ሚዛን ይደፋል?” ብላችሁ ብትጠይቁኝ መልሴን በልበ ሙሉነት እሰጣችኋለሁ፡፡ ታሪክ ነው ከምንም ነገር በላይ የሚልቀው - ታሪክ ነው የሚያኮራው - ይሄው ነው፡፡ በአፍላ የወጣትነት ዘመኔ ይህን መሳዩን ጥያቄ አንስታችሁልኝ ቢሆን ኖሮ፣ ውጊያውን ለመምረጥ ቅንጣት አላቅማማም ነበር፡፡ ዳሩ ግን ዕድሜ ደጉ በቀኝ እጁ አንዳች አዲስ ባህርይ ሲለግሰን …በግራ እጁ ደግሞ ንቡር ማንነታችንን ሲነጥቀን እነሆ እስከዛሬ አለነው፡፡
በኮበሌነት ዘመን እንደሚሆነው ሳይሆን አረጋውያን ደመ - በራድ ናቸው፡፡ እናም ተስፋው ነጥፎ፣ ወኔው ተገፎ፣ ድኩም ጉልበቱን አቅፎ፣ ቀሪ የዕድሜ ዘመኑን ለመግፋት ይገደዳል - አዛውንቱ፡፡ ታድያ አቅሙ ቢከዳውም በእግረ - ሕሊናው ይኳትናል፤ በዓይነ - ልቦናው ይጓዛል፣ አስተውሎቱ ይመጥቃል፣ የዕይታው አድማስ ይሰፋል፣ ከጽንፍ - ጽንፍ ያማትራል…
“…የእኛ ሰዎች ለሴት ልጆቻቸው ስም ሲያወጡ “ኒኮሊኮ” ብለው መሰየማቸው ይህን በማወቃቸው ይመስላል - “ማስተዋል ደጉ” እንደማለት፡፡ ለምን - ? ምክንያቱም ከትግሉም ሆነ ከታጋዩ ዕድሜ አንጻር ሲሰላ የታሪክ እድሜ የትየለሌ ነው፡፡ ልጆቻችን ተጨፍነው በየሰው ደጅ ለምጽዋት እየዞሩ “በእንተስማለማርያም” የሚሉ የእኔ ብጤዎች ከመሆን የሚያድናቸው እኛ አባቶቻቸው የምናቆይላቸው አኩሪ ታሪክ ነው - ታሪክ ብቻ ነው የሚታደጋቸው፡፡ ታሪክ ነው ዋቢያቸው …አዳኛቸው…ጠባቂያቸው፡፡ ታሪክ የሌለው ዜጋ ዓይነ - ሥውር ነው - ልበ ሥውርም ጭምር፡፡ ልበ - ሥውራን የታሪክን ክቡርነት የት ያውቁታል? እኛስ ብንሆን ታሪክን መች ጨበጥነው፡፡ ይሁን እንጂ ታሪክ ነው የሚመራን፣ ማንነታችንን የሚያሳየን፣ ሰብዕናችንን የሚቀርፀን፡፡ ይኸው ቀዳማዊ ማንነታችን ነው ከእንስሳት የሚለየን፡፡
ከ-“ቲንግስ ፎል አፓርት”
“የንጉሥን አፍ የሚያስተውል ሰው” አሉ አንድ አረጋዊ “የእናቱን ጡት የጠባ አይመስለውም፡፡” አዛውንቱ ይህን ያሉት ትፈሳ ዶሮ ሳይኖረው ከትቢያ ተነስቶ በሀብት ስለናጠጠውና በወገኖቹ አናት ላይ ቂብ ስላለው ስለአኮንክዎ ለመናገር ፈልገው ነው፡፡ ሰውዬው የአኮንክዎን ክፉ የሚመኙ ሰው ሆነው አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥሮ ግሮ ሕይወቱን ለማሻሻል ባደረገው ትጋትና በጨበጠው ስኬት የሚያከብሩት ሰው ናቸው፡፡ ሆኖም በኑሮ ከእሱ ለሚያንሱ ሰዎች በሚያሳየው ንቀት ይንቁታል ይበሽቁበታል፡፡
“ከአንድ ሣምንት በፊት በተካሄደ የቤተ ዘመድ ስብሰባ ላይ ሲወያዩ ነበር ከአንዱ ተሰብሳቢ ጋር አኮንክዎ የተጋጨው፡፡ አጅሬ አኮንክዎ ሆዬ፣ የሰውዬውን ፊት እንኳን በቅጡ ሳያየው ይህ ስብሰባ የተፈቀደው ለወንዶች ነው፡፡” በሚል የንቀት ቃል ነበር በአግቦ የተናገረው፡፡ ይሄኔ ሰውዬው የሚናገረው ጠፋው፡፡ በኦኮንክዎ ቤት አጠይሞ ሰውዬውን እንደሴት በመቁጠር በነገር መውጋቱ ነበር፡፡ መቼም የሰው ልጆችን መንፈስ እያኮሰመኑ የመግደልን ጥበብ አኮንክዎ ተክኖታል፡፡
“በቤተ ዘመድ ስብሰባው ላይ የነበሩት ተሰብሳቢዎች ሁሉ በአንድነት “ሴት” ተብሎ የተሰደበውን ሰው ወገኑ፡፡ ከዕድሜው ዝቅ አድርጐ የሰጣቸው አዛውንት ግን፣ በጐ አሳቢ ወገኖች ሁሉ በተለመደው ግዙፍ ትዕግስታቸው እንዲፀኑ ገዘቱ፡፡ በመጨረሻም አኮንክዎ በፀያፍ አንደበቱ ለፈፀመው በደል ይቅርታ ጠየቀና የስብሰባው ሥነ - ስርዓት ቀጠለ፡፡ “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የእጁን ጭብጥ ዘርግቶ ለአኮንክዎ በፀጋ ያስረከበው ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ራሱ ኦኮንክዎ ነው ድርሻውን አስረግፎ የወሰደው፡፡ የድህነትን ሰንሰለት በእልህ አስጨራሽ ጥረታቸው በጣጥሰው በአሸናፊነት የተወጡ ሰዎች በዕድል ድህነትን አመለጡ ሊባሉ አይገባም፡፡ በአጋጣሚ መክበር አይቻልም፡፡ የድካሙን ፍሬ ጐንጩን ሞልቶ ለመብላት የበቃ ሰው ቢኖር ኦኮንክዎ ነው - ድህነትን ድል ያደረገ ብርቱ ሰው፡፡
“ልጅ ሳለ ከጫፉ የሚደርስ ተፎካካሪ የሌለው የነፃ ትግል አሸናፊ ነበር፡፡ ያ በዕድል አልነበረም፡፡ ከራማው ወይም ፈጣሪው እየደገፈው ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በኢቦ ጐሣ ተወላጆች ዘንድ “አንድ ብርቱ ሰው ለሽንፈት አልበገርም የሚል ቆፍጣና መንፈስ ካለው፣ ከራማው አይበገሬነቱን ያፀድቅለታል” የሚል የዘልማድ አባባል ነው፡፡ አክንክዎ በፍርጥምታ ሽንፈትን “እምቢኝ” አለ፤ ከራማውም ይህንኑ ጽናቱን አጸደቀለት፡፡ ከዚያ በኋላማ ከራማው ብቻ ሳይሆን ሀገሬውም ጭምር የሰው ልጅ ከጣረ የድካሙን ፍሬ እንደሚበላ አመነ፡፡ አመርቂ ውጤት የሥራ ፍሬ መሆኑም የሕዝቡ እምነት ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ አንዲት የኢቦ ሴት በሰው እጅ በመገደሏ ሳቢያ የገዳዩ ወገኖች አንድ ኮበሌና አንዲት ኮረዳ ጉማ እንዲከፍሉ አለበለዚያ ግን ምድሪቱ በጦርነት እሳት እንደምትጋይ በዘጠኝ መንደር ነዋሪዎች የጸደቀው፡፡ የክተት አዋጁን ጦማር እንዲያደርስ ደግሞ ጀግናው አኮንክዎ ነበር የተመጠረው፡፡”
ከ-ሞርኒንግ የትኦን ክሪኤሽን ዴይ
“በተዋበ ቋንቋ የሚቀርብና በጣፋጭ የአተራረክ ዘይቤ የሚንኳለል ተረት ማድመጥ የልጅነት ቀልቤን ያማልለው ነበር፡፡ በልጅነቴ የትውልድ መንደሬ አረጋውያን በኩል በኢግቦ ቋንቋ ያቀርቡልኝ የነበረውን የተረት ጅረት እየሰማሁ አድጌአለሁ፣ ኋላም ስምንት ዓመት ከሞላኝ በኋላ በእንግሊዞች ቋንቋ የሰማሁት ተረት እስከዘላለሙ ይታወሰኛል፡፡ ሆኖም ምክንያቱን በውል አይቼ ባላውቀውም ከእንግሊዘኛው ይልቅ አያሌ የኢግቦ ቃላትን በሰለጠነ አንደበት መናገር እችላለሁ - በጽሑፍ ከሆነ ግን እንግሊዘኛው እንደሚቀናኝ አውቃለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ለመሆኑ በቃሁ፡፡ ብዙ ሰዎች በኢግቦ ቋንቋ የመፃፍ ችሎታዬም የተዋጣ እንደሆነ ሀሳባቸውን ለግሰውኛል፡፡ አንዳንዴም ወደ ግል ሕይወቴ በመግባት በየትኛው ቋንቋ ሕልም እንደማልም ጭምር ይጠይቁኛል፡፡ በሁለቱም ቋንቋዎች እኩል እንደማልም ስነግራቸው ግን አያምኑኝም - በፍፁም፡፡”
ስለ ቺኑዋ አቼቤ ስራዎች ጥቂት ብለን ጽሁፋችንን ብንቋጭ ወደድን፡፡
ምንም እንኳን በርዕሱ ላይ ጭጋጋማ ድባብ ቢያጠላም “ኢንትሂልስ ኦፍ ዚ ሳቫና” የኢግቦዎችን ብሂል ይዘክራል - በበረሃማው የሳር ምድር ላይ የተዛመተው ሰደድ እሳት አልፎ አልፎ የሚታዩትን ጉብታዎት መጧቸው አልፏል - ይኸም የሰደዱን አጎዳ ያስታውሳል - በእግረ ትዝታ ያስኳትናል - ያለፈውን እያስቃኘ መጪውን ያመላክታል...
“አንትሂልስ ኦፍ ዚ ሳቫና” ጠሊቅ ሂሳዊ ንባብ የሚሻ ኪነ-ጥበባዊ ውጤት ነው፡፡ አንድ ምዕራብ አፍሪቃዊ የመጽሐፍ ቅኝት አድራጊ፤ ስለመድበሉ ሲገልጡ “. . . የታለመለትን ግብ በሚያመረቃ ደረጃ የመታ የኪነጥበብ እሴት” በማለት በውዳሴ ጠበል አራጥበውታል፡፡ ይኸው መጽሐፍ ሦስት ተራኪዎች ሲኖሩት ብዕረኛው የተጠቀሙበት ቋንቋ ደግሞ፤ ከከፍተኛው መደብ የእንግሊዞች ልሣን አንስቶ፣ ጉራማይሌ ተናጋሪዎችን አካቶ፣ አቼቤ በልጅነት የዕድሜ ዘመናቸው እስከቀሰሟቸው የቤተክህነት ጥቅሶች ድረስ ያሉትን የአነጋገር ፊሊጦች ያካተተ ነው፡፡ በማህበራዊውና በፖለቲካው መስክ የተደረጉት ፍተሻዎችም ቢሆኑ እንደፈርጥ በሚንተገተጉና በምፀታዊ ሕብር በቀለሙ ውብ ቃላት ተከሽነዋል፡፡
“ቲንግስ ፎል አፓርት” የተሰኘው የአቼቤ የበኩር ሥራ ጭብጥ በደራሲው ምንዥላቶች ሕይወት ዙሪያ የተጠነጠነ ሲሆን በ18ኛው ምዕተ-ዓመት መካተቻ ግድም በግፉአን ጥቁር የሀገሬው ተወላጆች ላይ ሚስዮናዊያንና ቅኝ ገዢዎች የጫኑባቸዉን አሰቃቂ የግፍ ቀንበር በጥልቀት ይዳስሳል፤ ተገቢውን የክብር ሸማ ለወንዝ ልጆች ያላብሳል፡፡ እንደራሳቸዉ እንደፈጣሪው አባባል ከሆነ ይህ ሥራቸዉ “ያለፈውን እኔነት አንጥሮ የሚያወጣ፣ ማጋጣውን ወጣት በሥርዓት አርቆ ወደ ጤናማው ማህበረሰባዊ ሕይወት የሚያመጣ ልብወለድ ነው”
መቼቱ በነፃነት ዋዜማ ግድም ሌጐስ ከተማ ውስጥ ከተዋቀረውና “ኖ ሎንገር አት ኢዝ” ከተባለው መጽሐፋቸው ቀጥሎ በ1920 ዓ.ም ወደነበረው የኢግቦ መንደር እንደገና በመመለስ የማህበረሰባቸዉን መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ድቀት የቃኙበትን “የእግዜር ቀስት” የተባለውን ድረሳናቸውን አበረከቱ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ በንቅዘት ተበሻቅጦ በወታደራዊ መኮንኖች አመጽ ስለተፈነገለው መንግስት ያወሱበትን መድበላቸውን ከብሩህ አዕምሮአቸው አንቅተው የፈጠሩት፡፡ ይህንኑ ከቅድመ አርነት አፍሪቃ ጋር መልሶ በማቆራኘት ሰምና ፈትል ያደረጋቸውን የብዕራቸውን ውጤት “ኤ ማን ኦፍ ዚ ፒፕል” ብለው በመሰየም ለተደራሲያን አቀረቡት፡፡ ስለዚሁ መጽሐፍ ከተሰነዘሩት አስተያየቶች መሀል አንድ ሁለቱን እንመልከት፤
“አንዳንድ ሸፍጥን ሥራዬ ብለው የተነሱ ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም የሚፈጽሙት ገደብ የለሽ ደባ በተዋጣለት ሽሙጥና ሽንቆጣ ይፋ ወጥቶ ተዝረጥርጧል፡፡ . . . ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገሀዳዊው ዓለም ሕይወት እጅግም ሳያፈነግጡ የተሳሉ አስቂኝ ገፀ-ባህሪይ ናቸው፡፡ አጭበርባሪ፣ ወስላታ፣ ምላሰኛ፣ ፌዘኛ የሆኑ ሰው፡፡ ከእርሳቸው በተቃርኖ የቆመውና በአንደኛ መደብ ትረካ ራሱን የሚያስተዋውቀው ወጣቱ ኦዲሊ ደግሞ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው ቢሆንም ቁርጠኛ፣ ሀቀኛና ብርቱ ተፋላሚያቸው ሆኖ ተስሏል፡፡ የኦዲሊ ቅን ልቦና፣ የቁርጥ ቀን ልጅነት፣ ልበ-ሙሉነትና ሳንካአልባነት ለጥበባዊው ሥራ ምጡቅነት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ሆኖም ራሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመሆን ምኞቱ በታሪኩ አመሻሽ ላይ መክኖበታል፡፡”
(አንገስ ዊልሰን - በ”ኦብዘርቨር” ላይ ከሰነዘሩት አስተያየት የተቀዳ፡፡)
“ይህ የአቼቤ ልቦለድ በአፍሪቃ ውስጥ የሚገኝ አንድ የመንግስት ሹመኛ ይፈጽመው የነበረው ቅሌትና ክፋት በምሬት የተኮነነበት የፈጠራ ሥራ ነው . . . ያለፈውን ማህበረሰባዊ ወግና ልማድ ከሚያወድሱት ቀደምት ድርሳኖቻቸው እኩል የዜጐችን ሁለንተናዊ ሕይወት እንደመስተዋት በሚያሳይ ጥዑም ገለጻ የተከሸነ ሸንቋጭ ልቦለድ ነው፡፡”
(ዲ.ኤን.ኤን ጆንስ በኒው ስቴትስማን ላይ ካሰፈሩት ግምገማ የተቀነጨበ፡፡)
(የዘመን አቆጣጠሮቹ በሙሉ እ.ኤ.አ ነው)

 

Read 2240 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 12:02