Saturday, 31 December 2011 11:29

“ለልጅ ፍቅርን ሰጥቶ ማሳደግ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የአለም የጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ባወጡት መረጃ እንደተጠቆመው በአለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናት ሞት ፡-

እ.አ.አ. በ1999 ዓ/ም 12 ሚሊየን ይጠጋ ነበር፡፡

እ.አ.አ. በ2010 ዓ/ም ወደ 7.6 ሚሊዮን ዝቅ ብሎአል፡፡

ንጽህናን በመጠበቅ በአለም አቀፍ ደረጃ  በአመት ውስጥ የአንድ ሚሊዮን ሕጻናትን ሞት መቀነስ ይቻላል፡፡ (WWW.Child mortality.org)

በኢትዮጵያ በ2005 የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናት ሞት በአመት፡-

በሕይወት ከተወለዱ እስከ አንድ አመት ባለው እድሜ ከ1000/አንድ ሺህ ሕጻናት 96.8 ያህሉ ለሞት ይጋለጣሉ፡፡

በሕይወት ከተወለዱ ከአምስት አመት በታች ካሉ ሕጻናት ከ1000/አንድ ሺህ ወደ 123/ ያህሉ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

ሕጻናት በአጠቃላይ ለሞት የሚዳረጉባቸው እድሜዎች የተለያዩ ናቸው፡፡

Neonatal mortality: በተወለዱ በመጀመሪያው ወር፣

Post –neonatal mortality: በተወለዱ ከአንድ ወር በሁዋላ፣

Infant mortality: ከተወለዱ ከአንድ አመት በታች፣

Child mortality: ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት፣

Under-5 mortality: ባጠቃላይ ከተወለዱ እስከ አምስት፣

ሕጻናት የአምስት አመት እድሜያቸውን ሳያከብሩ ለምን ይሞታሉ ?በሚል ምክንያቱንና በአገር አቀፍ ደረጃ በመደረግ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በሚመለከት ዶ/ር ንግስት ተስፋዬ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የከተማ ጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለዚህ እትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡  ዶ/ር ንግስት በተጨማሪም የወጣቶች ሕጻናትና የእናቶች ጤና አስተባባሪ ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ንግስት ማብራሪያ የሳምባ ምች፣ ተቅማጥ እንዲሁም የምግብ እጥረት የመሳሰሉት ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናትን ለሞት ያጋልጣሉ፡፡ እንዲሁም በመጀመሪያው 28 ቀን አስፈላጊውን ክብደት ይዞ አለመወለድና ከአተነፋፈስ ጋር በተያየዘ የተለያየ የጤና መጉዋደል ሊከሰት እና ሕጻናቱን ለሞት ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡ ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናትን የሞት ምክንያቶች በእድሜያቸው ለይቶ ማየት ይቻላል፡፡

በመጀመሪያው ማለትም እስከ 28 ቀን  የጨቅላ ሕጻናት ደህንነት ክትትሉ መጀመር ያለበት ገና እናትየው ለማርገዝ በምታስብበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ እናትየው ሰውነቷ ለእርግዝና ምን ያህል ዝግጁ ነው እንዲሁም አስቀድሞውኑ በተለያዩ ሕመሞች የተያዘች ወይንም ያልተያዘች መሆን ያለመሆኑዋን አስቀድማ እንድታውቅ ይመከራል፡፡ ይህ ከማርገዝ በፊት ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሲሆን በእርግዝና ወቅት ደግሞ ተገቢው የህክምና ክትትል እንዲደረግ ይመከራል፡፡ አንዲት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ቢያንስ ቢያንስ አራት ጊዜ ሐኪም ማየት ይኖርባታል፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት የህክምና ክትትል እንድታደርግ የሚያስፈልገው ለእራስዋ ብቻም ሳይሆን ለልጇም ጤንነት ሲባል ነው፡፡ እናትየው ባጠቃላይ ምን ያስፈልጋታል ? ምግብ ፣እረፍት፣ ሕክምና ፣የምክር አገልግሎት ፣በእርግዝናው ወቅት ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ፣የደም ማነስ የመሳሰሉት እንዳይኖሩ አስቀድመው ከተከሰቱም አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ማድረግ የሚወለደውን ሕጻን ጤንነት ለመጠበቅ ያስችላል፡፡ ሕጻናቱ በባለሙያ በታገዘ መንገድ የሚወለዱ ከሆነ ክብደታቸው ባይሟላ መተንፈስ ባይችሉ እና ሌሎች ተያየዥ ችግሮችን በቀላሉ ለማስተካከል ይረዳል፡፡ ሕጻኑ ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ የመጀመሪያውን የጡት ወተት እንገር ማግኘትና እስከ ስድስት ወር ድረስም ከጡት ወተት በስተቀር ምንም ተጨማሪ ምግብ ሊሰጥ አይገባም፡፡ ሕጻናቱ ሲወለዱ አቅም በፈቀደ መንገድ በተሟላ ሁኔታ ለእድገታቸው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ከተቀበልናቸው የህጻናቱን ሞት በእጅጉ መቀነስ ይቻላል የሚል እምነት አለ እንደ ዶ/ር ንግስት፡፡ከአምስት አመት በታች ላሉ ሕጻናት ሞት ምክንያት ከሚባሉት መካከል የአናቶች የትምህርት እጦትም እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የክትባት ፕሮግራሞችን በተገቢው ሁኔታ ቀናትን አንብበው ለማስፈጸም እንዲሁም ተጨማሪ ምግብ መውሰድ በሚገባቸው ጊዜ የተለያዩ ለሕጻናቱ የሚሆኑ አመጋገቦችን ለመከታተል እንዲችሉ ጽሁፎችን አንብቦ መረዳት የመሳሰሉት ከእናቶች ትምህርት ማጣት ጋር ስለሚገናኝ ይህም እንዲስተካከል ተገቢውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮያ ካልተማሩ እናቶች በአመት በሕይወት ከሚወለዱ ከ1000/ ሕጻናት 139/አንድ መቶ ሰላሳ ዘጠኙ ያህሉ ለህልፈት እንደሚዳረጉ እና ቢያንስ እናቶቻቸው የአንደኛ ደረጃን ትምህርት ያጠናቀቁት  ልጆች ግን ከዚህ ባነሰ ቁጥር እንደሚሞቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ሞት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አራርቆ አለመውለድና አንዲት እናት ብዙ ቁጥር ያላቸውን ልጆች መውለድ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ (DHS)  Ethioopian Demographic and Health Survey 2011 /በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ እንደሚያመለክተው  በአገር አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን የመጠቀም ሁኔታ ወደ 29 ደርሶአል፡፡ ይኼውም የተለያዩ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያዎችን ሴቶች ስለሚጠቀሙና እንዲሁም የወንዶች ኮንዶምን ተጠቃሚነትን ጭምር ያሳያል፡፡ ዶ/ር ንግስት ተስፋዬ አክለው እንደገለጹትም ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናትን ሞት ለመከላከል ክትባት በትክክለኛው ጊዜ እንዲወስዱ ማስቻል ከወላጆች ይጠበቃል፡፡ ለምሳሌ እንደፖሊዮ ፣የሳምባ ምች፣ ኩፍኝ የመሳሰሉት በክትባት ልንከላከላቸው የሚገቡ ነገር ግን ክትባቱ ካልተወሰደ ውጤቱ እጅግ አስከፊ ስለሆነ ሕጻናቱ ከአካል ጉድለት በተጨማሪም ሞት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ሕጻናቱን በጤንነት ለማሳደግ እንዲቻል እንደሀገር ባጠቃላይ ለጤና ባለሙያዎቹም ሆነ  ለህብረተሰቡ የእውቀት ማዳበሪያ ስልጠና ይሰጣል፡፡ ወደህብረተሰቡ ስንመለከት አሉ ዶ/ር ንግስት በጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች አማካኝነት በከተማም ሆነ በገጠሩ በተለያዩ ማለትም  አስራ ስድስት በሚሆኑ ፕሮግራሞች ይሰለጥናሉ፡፡ ስለምግብ ፣ስለአካባቢ ንጽህና፣ ስለ ልጅ አያያዝ ፣ስለ ጡት ማጥባት አስፈላጊነት፣ ስለ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፣ ስለ ንጽህና ፣ስለምግብ አዘገጃጀት ፣ስለ ስርአተ ምግብ የመሳሰሉት ሁሉ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማዳበሪያ እንዲሆን ስልጠና ይሰጣል ፡፡በኢትዮያ ከአምስት አመት በታች ያሉ ሕጻናትን ደህንነት በተመለከተ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ክትባትን፣ ማዋለድን የመሳሰሉትን አገልግሎት ሁሉ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕጻናቱ አስቸኩዋይ በሆነና ወደሌላ ተቋም ከመሄዳቸው በፊት የህክምና እርዳታ በሚያስፈልግ ጊዜም የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞቹ ይረዳሉ፡፡ ከዚያም ከእነሱ ወደሚቀጥለው የህክምና ተቋም እንዲሁም ከፍ ወደአለ ሆስፒታል ወደመሳሰሉት የታመሙት ሕጻናት እንዲሸጋገሩ ያደርጋሉ፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ንግስት እንደገለጹት ለህጻናት ጤና መሰረታዊ ናቸው ከሚባሉት መካከል በሽታን አስቀድሞ በመከላከል ብዙ ነገሮችን ማስተካከል ይቻላል፡፡ አንድ ቤተሰብ ወይንም እናት ለልጁዋ የሚያስፈልገውን ምግብ ፣እንክብንቤ የመሳሰለውን እንዴት መሟላት እንደሚችል ልጁ ከመረገዙ በፊት አስቀድሞ ልታስብ ይገባታል፡፡ ቤተሰብን በእቅድ ለመምራት የሚያስችለውን ፕሮግራም በመተግበር አቅም የሚፈቅደ ው ያህል ልጅ የሚወለድ ከሆነ ሕጻኑ ምንም የህመምና ሞት ችግር ሳይገጥመው ሊያድግ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እናት ለልጁዋ ጡት በትክክል የምታጠባ ከሆነና ለልጁዋ ፍቅርን የምትሰጥ ከሆነ የተወለደው ልጅ በተሟላ ሁኔታ እንደሚያድግ ጥርጥር የለውም ፡፡ ለልጅ ፍቅርን ሰጥቶ ማሳደግ እንደ አንድ የጤና መሰረት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ልጅ ጡት እየጠባ ካደገ ከእናቱ ፍቅርን ስለሚያገኝ በደስተኝነት ሊያድግ ይችላል፡፡   ዶ/ር ንግስት ተስፋዬ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የከተማ ጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የወጣቶች የህጻናትና የእናቶች ጤና አስተባባሪ እንደገለጹት ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን በሚመለከት በቅርብ የወጣው መረጃ  (DHS)  Ethioopian Demographic and Health Survey 2011 / የሞት መጠን እንደቀነሰ ያሳያል፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራው ስራ በተጠናከረ መንገድ ከቀጠለ የምእተ አመቱን ግብ ለማሳካት ይቻላል ፡፡

 

 

Read 3346 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:37