Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 January 2012 11:04

ኖር በይው ልብሱን፤ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ኖር በዪ የኹጅር የጋኽምን ምስ) - የጉራጊኛ ተረትና ምሣሌ

(Old wine in a new bottle) - የእንግሊዞች ተረትና ምሣሌ

ሩሲያውያን አንድ ተረት አላቸው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ በዋናው ከተማ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ የጣት ቀለበቱ ይጠፋበታል፡፡ ወዲያው በጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ “የጣት ቀለበቴን አግኝቶ ላመጣልኝ ሰው ወሮታውን እከፍላለሁ” የሚል ነው ማስታወቂያው፡፡ አንድ ተራ ወታደር ዕድለኛ ሆነና ቀለበቱን አገኘ፡፡ “ምን ባደርግ ይሻላል” ሲል አሰበ፡፡ “ወደ ዋናው ጦር ክፍሌ ሄጄ ሪፖርት ባደርግ ጉዳዩ ወደ በላይ ይመራል፡፡ እያንዳንዱ የበላይ የራሱ የበላይ አለው፡፡ ስለዚህ ወደ በላይ ይመራዋል፡፡

ሃምሣ አለቃው ለመቶ አለቃው፤ መቶ አለቃው ለሻምበሉ፤ ሻምበሉ ለሻለቃው፣ ሻለቃው ለኮሎኔሉ፣ ኮሎኔሉ ለብርጋዲየር ጄኔራሉ እያለ ማለቂያ በሌለው የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ ሲቀባበሉት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ወደ ንጉሱ ሄጄ ቀለበቱን ባስረክባቸው ይሻላል” ብሎ ይወስናል፡፡

ወደ ቤተ - መንግሥቱ ይመጣል፡፡

የጥበቃ መኰንኑ፤ “እዚህ ምን ልታደርግ መጣህ?” ይለዋል፡፡

“የንጉሱን የጣት ቀለበት አግኝቼ ለማስረከብ ነው የመጣሁት” ይለዋል ተራ ወታደሩ፡፡

“በጣም ጥሩ ነው ወዳጄ፡፡ ለንጉሱ እነግርልሃለሁ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይኸውም ንጉሱ ቀለበቱን ስላገኘህላቸው ከሚሸልሙህ ነገር ግማሹን ለእኔ የምትሰጠኝ ከሆነ ነው፡፡ ተራ ወታደሩም በሆዱ፤

“ወቸ ጉድ! በዕድሜዬ ዛሬ አንድ መልካም ዕድል ቢገጥመኝ፤ እሷኑ የሚቀራመተኝ አዘዘብኝ፡፡ ግን ይሁን ግዴለም፡፡ ይካፈለኝ” ይልና ወደ ጥበቃ መኮንኑ ዞሮ፤ “ይሁን ከሽልማቱ ግማሹን ላካፍልህ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቅድመ - ሁኔታ ነው” ይለዋል፡፡

“ምንድነው ቅድመ ሁኔታው?” ሲል ይጠይቃል የጥበቃ መኮንኑ፡፡

“ከማገኘው ሽልማት ግማሹን አንተ፤ ግማሹን እኔ እንደምወስድ የሚገልጽ ማስታወሻ ፃፍልኝ” ሲል ይጠይቃል፡፡

የጥበቃ መኮንኑ ማስታሻውን ጽፎ ይሰጠዋል፡፡ ከዚያም ሄዶ ለንጉሱ ቀለበቱን ያገኘ ሰው መምጣቱን ይናገራል፡፡ ንጉሱም ቀለበታቸውን ስለማግኘቱ ያን ተራ ወታደር እጅግ አድርገው ያመሰግኑትና፤

“በጣም አመሰግናለሁ ጀግና ወታደር! ሁለት ሺህ ብር በሽልማት መልክ ሰጥቼሃለሁ” ይሉታል፡፡

“የለም ንጉሥ ሆይ ለወታደር የሚገባው ሽልማት ሁለት ሺ ብር ሳይሆን ሁለት ሺ ጅራፍ ነው፡፡” ይላል፡፡

ንጉሡም፤ እየሳቁ

“ምን ያለው ጅል ነው?” ብለው “እሺ ጅራፉ ይምጣ” አሉና አዘዙ፡፡

ተራ ወታደሩ ልብሱን ማወላለቅ ሲጀምር በድንገት አንዲት ወረቀት ዱብ ትላለች፡፡

“የምን ወረቀት ነው እሱ?” ሲሉ ይጠይቃሉ ንጉሱ፡፡

“ንጉሥ ሆይ፤ ይህ ማስታወሻ የሽልማቴን ግማሹን የጥበቃ መኮንንዎ እንዲወስድ የተስማማንበትን ውል የሚጠቁም ነው”

ንጉሱ ሳቁና የጥበቃ መኮንኑን አስጠሩት፡፡ ከዚያም “እንግዲህ መቶው ጅራፍ ያንተ ነው ማለት ነው” አሉት፡፡

ቀጥሎም የጥበቃ መኮንኑን በጅራፍ ገራፊው ይገርፈው ጀመር፡፡ የመጨረሻው አሥር ጅራፍ እንደቀረ ያ ተራ ወታደር ወደ ንጉሱ ጆሮ ጠጋ ብሎ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እኔ እንደሱ ስስታም ሰው አይደለሁም፤ የቀረውን ግማሹን ሽልማቴንም ሰጥቼዋለሁ!” ይላቸዋል፡፡

“እንዴት ያለህ ደግ ሰው ነህ ጃል” አሉና ንጉሡ፤ የጥበቃ መኮንኑ ሌላውን የጅራፍ ሽልማት እንዲወስድ አዘዙ፡፡ ያ የጥበቃ መኮንን በእምብርክኩ እስኪሄድ ድረስ ተለጠለጠ፡፡

ከዚያም ንጉሱ ተራ ወታደሩን ጠሩና፤ “በል ከዛሬ ጀምሮ ከሥራ መደብህ በክብር ተባረሃል፡፡ ለመቋቋሚያ ይሆንህ ዘንድ ሶስት ሺ ብር ተሸልመሃል?” አሉና አሰናበቱት፡፡

***

ከበላይ ወደበላይ ሲመራ ከሚውል ጉዳይ ይሰውረን፡፡ በየደረጃው ሽልማትህን አካፍለኝ ከሚሉም ያውጣን! ለበቀል ብለን የመዘዝነው ጅራፍ በራሳችን ላይ እንደሚዞር ማስተዋያ ልቦና አያሳጣን፡፡ ባሳበቅንበት ሊሳበቅብን፣ ባስቀጣነው ልንቀጣ፣ ባጨበጨብንበት ሊጨበጨብብን እንደሚችል፤ በጭራሽ አንዘንጋ፡፡

“አፈር ወስዶ ብለን፣ ያማረርነው አባይ

የሚያጨበጭብ ሰው፣ ይዞ ነጐደ ወይ?”

አለ አሉ ገጣሚ፤ ሆይ ሆይ ሲል ውሃ የወሰደውን ሰው አይቶ፡፡ እንሸለም ብለን ሌላውን መጉዳት ውሎ አድሮ የከፋ ጉዳት ወደማስተናገድ ሊያመራ እንደሚችል ዐይናችንን ገልጠን እንይ፡፡ ተማርን የምንል፣ ሥልጣን ላይ ያለን፣ በሞቅ ሞቅ ሙስናችንን ለመሸፈን የምንፍጨረጨር፣ የባለቤቱ ልጅ ነን የምንል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፊታችን ያለው እየወደቀ እያየን እኔን አይመለከትም እያልን የምንስቅ “አቤቱ ወደፈተናም አታግባን” ብንል ይሻላል፡፡

አንድ አዛውንት “በዚህ ዘመን ዘርዛራ ወንፊት፣ ቀጥሎ ጠቅጣቃ ወንፊት መኖሩን አዳሜ አያውቅም ከዘርዛራው ወንፊት ያመለጠው፣ በጠቅጣቃው ወንፊት የተያዘውን እየሰደበና እያዋረደ ብዙ የሚቆይ ይመስለዋል” ሲሉ ስለስብሰባዎች ተናግረዋል፡

አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀምበር ጥልቅ አለ ነው ነገሩ፡፡

በሰው ገንዘብ፣ በሰው ንብረት ላይ መፍረድ ቀላል ነው፡፡ እርዳታ ላያደርጉ ይሄ ይሁን ይሄ አይሁን ማለትም እጅግ ቀላል ነው፡፡ የማያግዝ “ቤቱን አስፍታችሁ ሥሩ” ይላል፤ እንደተባለው ነው፡፡

ሳናወያይና ሳናጠና መመሪያ አናውጣ፡፡ ሳናስብ አንናገር፡፡ ከተናገርን አንፈር፡፡ ካፈርኩ አይመልሰን ብለንም በግትርነት አንደንፋ፡፡ ላወቅነውና ላለምነው ጉዞ በልባምነት እንገስግስ፡፡

አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ የተባሉ ደራሲ “የጐጃም ትውልድ በሙሉ፤ ከአባይ እስከ አባይ” በተባለ መጽሐፋቸው፤ “የማኖ የላስታ ሰው ነው፡፡ ጀግና ፈረሰኛ ነበር፡፡ ሥነፀሐይን ሲያጭ “ምን ገንዘብ አለህ” ቢሉት፤ “ልብና ፈረስ አለኝ” አለ፤ አሉ፡፡ ዓላማ ያለው፣ ለሀገርና ለህዝብ አሳቢ የሆነ ሰው ልብና ፈረስ ያስፈልገዋል፡፡ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ አርቆ አስተዋይ ሊሆን ይገባል፡፡ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነግ ተነግወዲያውን ሊያሰላ፣ ሊያሰላስል ያሻል፡፡ ዕድገትና ብልጽግና የዚህ መርህ የልጅ ልጆች ናቸው፡፡ መልካም አስተዳደር ይኑር፡፡

ፍትሕ አይጓደል፤ የግለሰብም ሆነ የቡድን ወገናዊነት ይውደም፤ ሙስና ይወገድ፣ የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ እየተባለ ነጋ ጠባ የሚወተወተው ለአንድ ሀገራችን ዕድገት እንጂ ጥቂቶች የሚያወለውሉባትና ብዙሃን በአጥንታቸው የሚሄዱባት አገር ትሆን ዘንድ አደለም፡፡ ያውም ለሀብታሞቹ እንኳ ባልተመቸው በአሁኑ ዓለም!!

ፕሮፌሰር ሳች የተባሉ ምሁር “በዛሬ ጊዜ፤ ሀብታሞቹ የአናሳ ፍትሕና የተትረፈረፈ አለመረጋጋት ሰለባ ይሆናሉ (A Less Just and more unstable world) የሚሉትን አባባል በጥሞና ማውጣት ማውረድም ይኖርብናል፡፡ ፍርሃትንና የደህንነት ምቾት ማጣትን የምንቋቋምበት ሥርዓት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ “የተገደበውን የፖለቲካ መንቀሳቀሻ ሥፍራ የሚተካ/የሚያካክስ መላወሻ ሜዳ መፈጠር አለበት” እንደሚለን ማለት ነው ፒተር ጊልስ፡፡ ዛሬ እንደዋዛ የዘጋነው በር ነገ ከናካቴው ተከርችሞ፤ ቆላፊውም ተቆላፊውም መንገድ እንዳያጡ ስጋቱን መግለፁ ነው፡፡

በጥቃቅን እርምጃዎቻችን ከባባድ ለውጥ ያመጣን አስመስለን ከማጋነን መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ ችግሮቻችን ዝሆን አከል ናቸው፡፡ የዝሆንን ግዙፍ አካል እለካለሁ ብላ እንደተነሳችው ጉንዳን እንዳንሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሥር - ነቀልና ሥር የያዘ ለውጥ እያመጣን መሆኑን እያስረገጥን መጓዝ አለብን፡፡ በዚያው በትላንቱ ልባችንና አካሄዳችን እያለምን፤ ዛሬን አዲስ ነው ብለን ለማሳየት መሞከር፤ “ኖሮ በይው ልብሱን፣ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው” እንደሚባለው የጉራጊኛ ተረት ይሆናል፡፡ Old wine in a new bottle እንደሚሉት መሆኑ ነው ፈረንጆቹ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Read 5165 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 11:11