Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 10:35

በውዴታ ከተወሰደብኝ ወርቄ፤ በግዴታ የተወሰደብኝ ጨርቄ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ የኤሌክትሪክ መስመር በአውሮፓ ተዘርግቶ ጥቂት እንደቆየ ሁለት ገበሬዎች ስለህይወታቸው ሊጨዋወቱ ተቃጥረዋል፡፡ ሁለቱም እርሻቸውን አርሰው፣ ዘራቸውን ዘርተው፤ ሰብል ይጠብቃሉ፡፡ ሁለቱም ከብቶች ነበሩዋቸውና ወደ ሆራ ነድተው፣ ውሃ አጠጥተው፣ ለግጦች መስኩ ላይ አሰማርተዋቸዋል፡፡ የከብቶቹ ባህሪ ግን ለየቅል ነው፡፡ የአንደኛው ከብቶች ይግጡ ይግጡና መስኩ ግማሽ ከሄዱ በኋላ ወደ ኋላ ተመልሰው መጋጥ ይጀምራሉ፡፡ የሁለተኛው  ገበሬ ከብቶች ግን የመስኩን ግማሽም አልፈው ሄደው እንደልብ ይግጣሉ፡፡ ይሄንን ያስተዋለው ሁለተኛው ገበሬ ወደ አንደኛው ገበሬ ይዞርና፤

“አያ እገሌ” ይለዋል፡፡

አንደኛው ገበሬ “አቤት” ይላል

ሁለተኛው ገበሬ “የከብቶቻችን ዓመል አይገርምህም?”

አንደኛው ገበሬ “ከብት ከብት ነው ምን ይገርማል? ትነዳዋለህ ትነዳዋለህ”

ሁለተኛው ገበሬ “መንዳት ብቻ ሳይሆን ዓመላቸውንም አጢን እንጂ”

አንደኛው ገበሬ “ዓመል ስትል እንዴት ነው?”

ሁለተኛው ገበሬ   “አታያቸውም ያንተ ላሞች ከግጦሹ መስክ ከግማሹ ዘልቀው አይሄዱም፡፡ የኔዎቹ

ደግሞ እስከ ድንበሩም፣ ከዚያም አልፈው ድንበር ዘልቀው እንደልብ  ይንቀሳቀሳሉ”

አንደኛው  ገበሬ   “ዕውነትክን ነው፡፡ እኔ የፈለኩት ድረስ ብቻ እንዲግጡ ገርቼ አሠልጥኜ ለያዝኳቸው

ነው፡፡”

ሁለተኛው ገበሬ “እንዴት አድርገህ አሠለጠንኻቸው ጃል?”

አንደኛው ገበሬ “አየህ የእኔም ላሞች እንዳንተው ግጦሽ ሜዳውን እያቋረጡ እየሄዱ ያስቸግሩኝዥ

ነበር”

ሁለተኛው ገበሬ “በጄ፡፡ ኋላ ምን መላ ፈጠርክላቸው?”

አንደኛው ገበሬ “ልነግርህ አይደል? አንድ ቀን፤ ዕድሜ ለኤሌክትሪክ ዘመን፣ የኤሌክትሪክ ሽቦ

ታውቅ የለም?”

ሁለተኛው ገበሬ “አሳምሬ”

አንደኛው ገበሬ “በኤሌክትሪክ ሽቦው ሜዳዉን ማህል ለማህል አጠርኩና ኤሌክትሪኩን ለኮስኩት፡፡”

ሁለተኛው ገበሬ “በጄ?”

አንደኛው ገበሬ “ከዛ ላሞቹን አሰማራኋቸው፡፡ ለቀኳቸው፣ የግጦሽ ሜዳው ላይ፡፡ እንደልማዳቸው

እየጋጡ ሽቦው ጋ ሲደርሱ ያ የኤሌክትሪክ ሽቦ አንድ ሁለቱን ሲጠብሳቸው

ወዲያው ተመለሱ!”

ሁለተኛው ገበሬ “ከዛስ? አሁን የታለ ሽቦው?”

አንደኛው ገበሬ “ቆይ መች ጨረስኩልህ?”

ሁለተኛው ገበሬ “በጄ?”

አንደኛው ገበሬ “በነጋታው ያንን የኤሌክትሪክ ሽቦ አነሳሁት፡፡ ከዚያ ላሞቹን ሜዳው ላይ ለቀቅኳቸው፡፡ ይግጡ፣ ይግጡ፣ ይግጡና ልክ የኤሌክትሪክ ሽቦው የነበረበት ቦታ

ሲደርሱ ምልስ ይላሉ! ይሄውልህ የላሞቼ ዓመልና ሥልጠና ሚስጥር ይሄ ነው፡፡”

*   *   *

ከኤሌክትሪክ አጥር ይሰውረን፡፡ ከላምነትም ያድነን፡፡ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ዓለም፤ ረዥም ዘመን የቆው የኤሌክትሪክ አጥር (electric fence) የሚዲያ ህግ ነው ይባላል፡፡ ጋዜጠኞቹም በዜና ማምረቱ ተግባር ወቅት “የኤሌክትሪክ አጥሩን እንዳትነካ ወይም አትጠጋ” በሚል የሚጠሩት ህግ አላቸው - እንደ ኒክ ዴቪስ አባባል፡፡ (Avoid the electric fence – Rule Three) ያገራችን ባለቅኔ እሱ በገባው መልኩ (ያገሩን ሠርዶ ባገሩ በሬ ነውና) እንዲህ ሲል ይገልጠዋል፡-

“አሻግራቸውና ከብቶቹ ሣር ይብሉ

ያ - ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ” ይለዋል፡፡

ፀሀፌ - ተውኔትና ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህንም፤ “ስደተኛው ዘላን በሄደበት ሁሉ አንድም ሣር፣ አንድም አሣር ይጠብቀዋል” ይለናል፡፡ ሣሩን እያየን አሣሩን ከማግኘት ይሰውረን፡፡ በእንግሊዝ አገር፣ መንግሥት ሚሥጥር ያለውን ነገር የፃፈ ጋዜጠኛ እሥራት እንደሚጠብቀው ያስፈራራል ይላል ፀሀፊው (The official Secrets Actን በማጣቀስ) ቀጥሎም የስም ማጥፋት ወንጀልማ ከዚያም በላይ ማስፈራሪያ ነው፡፡ በእንግሊዝና በሳውዲ ዓረቢያ ያሉ ንጉሣውያን ቤተሰቦች የስም-ማጥፋት ወንጀልን በመንተራስ በሌላው ዓለም የትም ቦታ የሚገኙ መፃህፍትን እንዳይታተሙ አስቁመዋል፤ ይለናል ኒክ ዴቪስ፡፡ ዛሬ ዛሬ የኤሌክትሪክ አጥሩ ሽቦ የሚዘረጋው በአዲሶቹ የጀግንነት ዓለም ቡድኖች የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች ሆኗል፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ፤ በዓለም ላይ እጅግ ኃይለኛው የኤሌክትሪክ አጥር እሥራኤልን ከጋዜጠኞች አፍ ለመጠበቅ የተዘረጋው ሽቦ ነው ይሉናል፡፡ የ”ኢንዲፔንደንት” ጋዜጠኛ ሮበርት ፊስክ ሳይቸግረው ስለ እሥራኤል ፅፎ እንዲህ ብለው አስፈራሩት አሉ፡- “እናትህ የአዶልፍ አይችማን ልጅ ናት፡፡ የሰማይ ቤትህ ከኦሳማ ቢን ላደን ጋር ገሀነም ውስጥ ነው፡፡ የጥላቻ አራማጅ ነህ፡፡ ቀንደኛ ፀረ ሴማይት፣ የፋሽስት አቀንቃኝ፣ እስላማዊ ፕሮፓጋንዲስት” የሚል ውርጅብኝ ወርዶበታል፡፡ እንደነ CAMERA (Committee for Accuracy in Middle East Reporting in America) ያሉ ደግሞ ጎዳና ሠልፎችን በመጠቀም፣ የማስታወቂያ  ድርጅቶች ላይ ጫና በመፍጠር፣ መደበኛ አቤቱታዎችንና የኢሜል-ጋጋታዎችን በመልቀቅ የኤሌክትሪክ አጥሩን ያጠብቃሉ፡፡ በአጥሩ ምክንያት ቃላት ሳይቀሩ አደገኛ ይሆናሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ “ስለተያዙ ግዛቶች” መፃፍ አደገኛ ነው፡፡፣ የፓሊስታይንን ቦምብ አፈንጂዎች “አሸባሪዎች” ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል መጠቀም አለመቻሉ፤ ወዘተ. የራሱ ተፅዕኖ አለው በጋዜጠኞች ላይ፡፡ የትላልቅ ምዕራባውያን አገሮችን ጋዜጠኞች ችግር ስናስተውል፤ የሚጢጢ አገሮችማ “አበስኩ ገበርኩ!” ሳያሰኝ አይቀርም፡፡ ከሁሉም ዓይነት አጥር ይሰውረን ማለት ያባት ነው፡፡ የሁሉም አዛዦች ጌቶቹ ናቸውና፡፡

ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት የአንድ አገር የዲሞክራሲዋ ምሰሶ ነው፡፡ ሰውና ሰው፣  መንግስትና ሰው ያቀራርባል፣ ያግባባል፣ ያቻችላል፣ አስፈላጊ ሲሆን በአግባቡና በሠለጠነ መንገድ ያለያያል፡፡ ይህንን መብት ያለገደብ የለቀቅን ዕለት አገርም፣ ህዝብም፣ መንግሥትም ይጠቀማል - ላሜ ወለደች ማለት ይሄኔ ነው! ለሌሎች ነፃነት ስንሰጥ  ለራሳችንም ሰጠን፤ ይሉናል ፀሀፍት! ነፃነቱን፣ መብቱን ፍትሑን የሚጠይቅ ህዝብ አያሳጣን!! “በውዴታ ከተወሰደብኝ ወርቄ፣ በግዴታ የተወሰደብኝ ጨርቄ” የሚለው ተረት የሚከሰተው ለጠየቀው ምላሽ ሲያጣና ምላሹን የመቀበልም ሆነ ያለመቀበል መብቱን ሳናከብርለት የቀረን እንደሆነ ነው፡፡

የገና በዓል በኑሮም፣ በፖለቲካም፣ የመልካም ልደት ይሁንልን!

 

 

Read 4959 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:53