Print this page
Saturday, 11 August 2012 11:30

የፆም ከንፈር…!

Written by  ዋሲሁን በላይ(አዋበ)
Rate this item
(26 votes)

ግርም ይለኛል፡፡

ድንቅ፡፡

ነገ…ዛሬን… አለመምሰሉ፡፡

ዛሬ ደግሞ … ትናንትናን አይደለም፡፡

***

እንደ እኔ አይነት ብርታት ያላት ሴት ካለች … ፀሐይ ቅናቷ አይጣል ነው፡፡ በቁመቴ ልክ ያሰራሁት መስተዋት ቄንጠኛው … ስወለድ እንዲህ ሆኜ እንደመጣሁ … ሲያሳብቅ በለውጡ ተገረምኩ፡፡

ልቅም ያልኩ ቆንጆ ነኝ፡፡

ሁለመናዬን ውድድድድ አደርገዋለሁ፡፡

ሴትነቴን በአግባቡ እየተጠቀምኩ እንደሆነ ይሰማኛል … ፊት ለፊቴ ተገትሮ በእርቃኔ የሚማልለው መስተዋት “እኔን” በግርምት ያስቃኘኛል፡፡

ጡቶቼ ያ.ም.ራሉ፡፡ ብስል የዘይቱን ፍሬዎች፡፡ ወገቤም ከልቡ ወገብ ነው፡፡

ጀብድ ባይሆንብኝ … እስከዛሬ የተኙኝ ወንዶች በሙሉ አንዳቸውም ጡቴን ነክተውኝ አያውቁም፡፡ ልክ ከባድ በረድ እንደደበደበው የደረሰ የጥጥ ማሳ ሙሽሽ የሚሉብኝ ይመስለኛል፡፡ እንኳን የወንድ ልጅ እጅ ቀርቶ፣ ጡት ማስያዣ የሚሉት የሴቶች የጡት አንቀልባ እንኳን ነክቶት አያውቅም! (ምን ሲሞከር …  የወንድ እጅ ሊያርፍባቸው) እንኳንስ ሌላ ተጋሪ ቀርቶ እኔንም ስፍስፍ ያደርጉኛል፡፡ ግን … ግን … መስተዋት ፊት ቆሞ የራስ ገላን እንደመመልከት ምን የሚያሳሳ ነገር አለ?

***

ፊቴን ሳየው ታዘብኩት፡፡ አይኔ ላይ የተኳልኩት ኩል … ማስካራ … ሻዶ … ሰባት ፉንጋ ሴት፣ ለሶስት ቀን ትዋብበታለች፡፡ ከንፈሬን የተቀባሁት ኤልሳቤት ሊፕስቲክ “እኔ ነኝ” ያለ ጀግና ስሞ አያስለቅቀውም፡፡

የሆነ ያላወቅሁት ስሜት ገላዬን በላባ እጁ ዳብሶ … የብርሃን ሻማ ሲያጐናፅፈኝ … ታወቀኝ፡፡ ሁሌም በራሴ እኮራለሁ፡፡ ወደፊት እንጂ … እንዳልቆምኩ ይገባኛል! ግን … በአንድ ነገሬ አፍራለሁ… /ወንድ በመውደዴ/ ግን ይሔ ሽቶው ከሩቅ የሚጠራ፣ ፀጉሩን በጄልና በፐርም አሳብዶ፣ የሀብታም ውሻ ይመስል የተብለጨለጨውን፣ … በስኪኒ ጅንስ የተወጠረውን … በባዶ … ተቆንኖ ቦርጩን የሚያስኮመኩመውን ሳይሆን … አለ አይደል … “ላይክ” … ፀጉር ክርድድ ብሎ … ወጋ! ወጋ! የሚያደርግ …፣ ጠረኑ ሠንፈጥፈጥ የሚያደርግ … ሲጨብጥ ሻከር፣ ጨምደድ … ሲያቅፍ ትንፋሽ የሚያሳጣውን፣ ወንድ የሆነውን ወንድ ሳየው አውቀዋለሁ … ያኔ … ውስጤ ያዘኛል፤ እኔ ካዘዘችኝ አያመልጠኝም፡፡

***

ህፃን ሆኜ፤ .. አምስተኛ ክፍል እያለሁ … ከቤታችን ሰርቪሶች አንዱን ተከራይቶ … ማተሚያ ቤት ይሰራ የነበረው … ባህሩ… ዛሬዬን… እንዳንጐራጉር በትላንትና ቃኝቶኛል፤ ከነ ጥቁረቱ … ከነ ጠረኑ … አሁን ድረስ … ይከተለኛል፡፡ መላጣ፡፡ ወንድ የሆነ ወንድ፡፡ “ዶቃ” … እያለ በገባ በወጣ ቁጥር ብብትና ብብቴን ሰቅስቆ ከፍ ካደረገኝ በኋላ … ግራና ቀኙን ቃኝቶ … ከንፈሬን በስሱ ስሞኝ … ወደ ክፍሉ ይገባል፡፡ ሳላስበው ሱስ ሆነብኝ … ለሰባት አመት የእኛን ቤት ተከራይቷል፡፡ ሰባት አመት ሙሉ ስንገናኝ ስሞኛል … ከውጭ ሲገባ በረንዳ ላይ ሰው ቢኖር እንኳ … ክፍሉ ተከትዬው እገባለሁ … “ሆጵ” ያደርገኝና ሳም አድርጐ ሱሴን ያጐርሠኛል፡፡  ሶስት በጣም ዘናጭ እህቶች አሉኝ፡፡ አንገታቸውን ደፍተው ከቤት ይወጣሉ፣ አንገታቸውን ደፍተው ይመለሳሉ፤ … ሲበዛ ኩሩዎች ናቸው … እወዳቸዋለሁ … በጣም ይመስጡኛል፡፡ ግን አንድም ቀን ውጭ ሊገጥመኝ ስለሚችለው የወንዶች ትንኮሳ አውርተውኝ … አያውቁም፡፡ /ምናልባት ወንድ ስለማያውቁ ይሆን … እላለሁ/

***

ይሔ … ጥቁር … መላጣ … ሲስም ከንፈር ላይ ረዥም ልብ ወለድ የሚተርክ፣ ባህሩ … አንዳንዴ የህትመት ቀለም እጁን እንዳበላሸው … አሻራውን … አሻራዬ ላይ ያትማቸዋል፡፡ ፍቅር ልቤ ላይ ይፅፋል፡፡ ከንፈሬ ላይ ይተርክልኛል፡፡ ሁሉም ልቤ ውስጥ አሉ፡፡ ችግኝ ናቸው ትዝታዎቼ፣ ከተከልኳቸው ይበቅላሉ፡፡ ብቻ … ወንድ … የራሱ ጠረን ከሌለው አልወድም፡፡ ይሔኛው ድክመቴ ያበሳጨኛል … ሰፊ ቀዳዳ ይመስለኛል፤ … እስቲ አስቡት … አንዲት የተማረች ጥሩ ገቢ ያላት ሴት፣ እንዴትና በምን ሒሳብ … እንዲህ ሆና ትኖራለች? ይሔን ድክመቴን ለማረም ከምለፋ ይልቅ … መንታ ወልጄ በእነርሱ ብቀጣ ይቀለኛል፡፡ /ደግሞ አባት የሌለው ልጅ ጥሩ አይደለም፡፡/

***

በበሩ ቀዳዳ የሚገባው ነፋስ … ቂጤን ሲዳብስ ይሰማኛል … አንዲት የገነት አበባ የመሠለች ውብ ሴት … ብቻዋን … ራቁቷን … ቤቷ … መስተዋት ፊት ለፊት ቆማ በራሷ ገላ ተማርካ … ፈዛ .. ወይ ጉድ፤

***

ከርቀት የሚሠማው የፀጋዬ እሸቱ “እንክት ይበል ድቅቅ ጐኔን አይመቸው መቼም ያለወዳጅ አይደላም ያለሰው” … የሚለው ጣዕም ያለው ዘፈን … ልብን በትዝታ የሚያሸፍት ውብ ዜማ … የተዘጋውን በሬን ሳያንኳኳ … ሰንጥቆ ከነፋሱ ጋር ገብቷል … ማን ጀግና ነው ትዝታን አትድረስብኝ የሚለው!

***

ባህሩ … ቤታችንን በለቀቀ በሳምንቱ … ቀጥሮኝ … ራቴን አሣ ጥብስ ጋበዘኝ … በሆነ አስማት አብረን አደርን …!

አደገኛው ጊዜ … ተጀመረ፡፡

ሌሊቱን ማሳው መኝታችን ላይ ቀይ አበባ ዘራን … ያኔ … ለየት ያለ … ስሜት ልቤ መሀሉ ላይ ለእሱ ብቻ ሐውልት ቀረፅኩለት፡፡

ሐሙስ ማታ ሶስተኛው ቀን፡፡ ቀጠረኝ … /የኔ ሰበብ አገኘሁ/ ፒያሳ ፒዜሪያ አሩስቶ ጋበዘኝና .. እዛው ዝቅ … ብለን … አብርሃ ሆቴል ይመስለኛል … በስተቀኝ ታጥፈን አልጋ ይዘን አደርን፡፡ ያቺን ዘቢብ የመሠለች ምሽትም … ልቤ ውስጥ በትልቁ ቆፍሬ ከተከልኩት ሀውልት ስር የከበረ ማዕድን አስቀመጠ፡፡ ከዛ በኋላ ትዝታውን እንጂ … በአካል አግኝቼው አላውቅም፡፡

***

/እኔ ለመባለግ … ባልጌ … ማነው ተጠያቂው…? ልጅነቴ … ወይስ … በመገረዜ ምክንያት … የተፈጥሮን እርካታ በማጣቴ …?/  እንግዲህ እንዲህ ነው … የተጀመረው … የኔ ህይወት፡፡

ባህሩዬን እያሰብኩ ነው ልቤ ደጅ የሚያድረው፡፡ በትምህርቴ ጐበዝ አይገልፀኝም፡፡ ከሶስተኛ በታች ወጥቼ አላውቅም፡፡ ማትሪክ “Straight A” አምጥቼ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፣ … በሁለቱም ነገር ባሠብኝ … በትምህርቴም … የአዳም ችግኝ በመንቀሉም፡፡ የትምህርቴን ጉብዝና ሙሉ ጊቢው ያውቀዋል … በተለይ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ተማሪውም መምህሩም፡፡ ወንድ አዳኝ መሆኔን ግን … ከታደኑት ወንዶች ሌላ … ማንም አያውቅም፡፡ “ኮርማው” የሚሉት ጠውላጋ ጊቢ ያወጡለት ሥም ነው፡፡ ሴት አይቶ ማለፍ አንጀቱ አይችልም አሉ /እሱም እንደእኔ ቤታቸው ሴት ተከራይ አባልጋው  ይሆን?/… እሱ ስሜን ለማጥፋት ሞክሮ ነበር … መጀመሪያ ጠየቀኝ “ካልሲህን አፅዳ” ብዬ ካለው ክሳት ላይ ቀነስኩበት፡፡

ወንድ ሲጠይቀኝ ያመኛል … ይደብረኛል! ዳግም ለአይን እንኳ ለማየት እጠየፈዋለሁ፡፡ /ጊቢ ውስጥ ከወንድ ጋር ምኔ ሞኝ! ታይቼም አላውቅ/

***

አራት አመት ብዙ ተአምር ታየ … “አላዩንም እንጂ ያላየነው የለም” አይደል፡፡ የእያንዳንዷ አመት ግሬዴ አስገራሚ ነበር … የረሳሁት /ያልጠየቀኝ መምህር የለም/ “ጢቅ” ብዬባቸዋለሁ፡፡

በአመቱ መጨረሻ ላይ ዋንጫና ወርቅ ተሸላሚ ሆኜ ተጨበጨበልኝ … ለራሴም … አጨበጨብኩላት፡፡ “ሴታታ” አልኳት እኔን፡፡ ወንዳታ እንደሚባለው፡፡

እዛ ሰተቴ አዳራሽ ውስጥ … ከሎው ዲፓርትመንት ዋንጫና ወርቁን የተቀበለው .. ናሆም አክሊሉ … በእንኳን ደስ ያለህ ሰበብ እዛው አበሠልኩት፡፡ 11፡45 ቤቱ ተገኘሁ፡፡ ነፋስ አልቀደመኝም፡፡ ጠዋት ተመራቂ የነበረችው … የገነት አበባ … አበባ ይዛ ናሆም ቤት ትገኛለች፡፡ መሸ፡፡ … ሁሉም ወደ የመሔጃው ሔደ፡፡ ናሆምና እኔ … ላብ ላብ እሚለው ሳሎን ውሰጥ ቀረን … “አትሔጂም እንዴ?”

“የት?” አልኩት… ፈገግታው ያምራል … እስክስታ የሚመታ ባህር ይመስላል፡፡

“አይ መሽቷል ብዬ ነው”

“ተወው ይነጋል” ፈጣጣ የሆንኩ መሠለኝ፡፡ ገባው፡፡ ደረቱ ላይ በምቾት .. የተንፈላሰሰውን ከረባት ጭርሱን እየፈታ ወደ እኔ ቀረበ … እጄን እያሻሸ ወደ መኝታ ቤት ገባን፡፡ በሩን ዘጋው፡፡

***

“ልገላበጥ እንጂ ጐኔን ላመቻቸው

ማን ለማን ይተኛል ሁሉም ለራሱ ነው”፡፡

ናሆም ደጋግሞ ላግኝሽ አለኝ … ዝናዬን ያውቅ ነበር የትምህርቴን፡፡ ላግባሽ አለኝ…ብን እስኪል…ሠከረ፤ የለሰለሰ የወንዝ ድንጋይ መሠለኝ…አልጌ፡፡ የሆነ ተሽሞንሟኝ…አፈር አይንካኝ ቢጤ ስለሆነ ከልቤ አፍ ተፋሁት፡፡ (ባህሪዬን አልሆነማ)

***

አሁን ትንሽም ቢሆን ልቤን ሞላ ያደረገው የተለየ ወንድ የሆነ ወንድ ከልቤ ሠፈር እንግዳ ሆኖ መጥቷል…ግባም…ሒድም ለማለት ተቸግሬአለሁ፡፡ አራት ልጆች አሉት፡፡

አመሏ ከሀር በላይ የለሠለሠ…ማማሯ የቤተመቅደስ ምንጣፍ የመሰለች ሚስት አለችው…ፈገግታዋ ትኩስ የቡላ ገንፎ የመሰለ!

አየር ማረፍያ ግራውንድ ቴክኒሻን ነው፡፡ ደረቱ ላይ ያለማጋነን…አራት ሴቶች የፍቅር እስክስታ ማስነካት ይችላሉ፡፡

አሁን ልቤ ሰው ማሰብ ሰው መውደድ ጀምሯል መሠለኝ…ቁልፉን ያገኘው ይሔ ወስላታ መሠለኝ … ትንሽም ቢሆን የሥጋ እርካታ አገኛለሁ…! መሣም ያውቅበታል….

ቀይ የወይን ዘለላ የመሰለው ከንፈሩ…ለማውራትም ለመሳምም አይጣደፍም፡፡ መጀመሪያ ቀን…ራት ጋበዝኩትና ዐይን ዐይኑን ሳየው … የት እንደር ልለው…በመኪናው ቤቴ ድረስ…ሸኘኝ…

“አትገባም?” ድፍረቴ ገርሞኛል

“አንቺ ግቢ ቆንጆ ቢራቢሮ”

“የሴት ቤት ነው ብለህ ነው?”

“የሴት ቤት እኮ ዘው ተብሎ አይገባም…ብዙ ማንኳኳት ይፈልጋል”

“ምናልበት ለዛሬ ፈቅጄልሃለሁ” ቢገባ ብዬ ተመኝቼ ነበር…ወንዝ ዳር የበቀለ ቄጤማ…

“ሌላ ቀን አስፈቅጄ እገባለሁ” እጄን ስሞ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ…ጠረኑን አቅፌው አደርኩ፡፡ እጄን ጡቶቼ ላይ አድርጌ፡፡

እሱ ባለትዳር፡፡

እኔ ባለጌ፡፡ ባህል የገፈፈኝን ስሜት ሳድን…የከሳሁ…!!

የሱ ከንፈር የፆም፡፡ እየሳሳሁ ነው የምስመው…(የዛች ቆንጆም ያለ እየመሰለኝ)

የኔ የፍስክ ከንፈር … ተቆጭ..! ገልማጭ! ቆንጣጭ! የሌለበት…

ለእንደኔ አይነቷ ሞኝ…ሰርቆ ፍቅር እንደመስራት የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ (እንደኔዋ ነውሯ ኩራቷ ለሆነባት ነፍስ ምን አይነት ይቅርታ አለ!)

***

ነፋሱ …ሥጋ ለብሶ…የነፋስ…ነፍስ አበጅቶ ከኋላዬ ቆሞ በብርሃን እጁ እየዳበሰኝ ተመስጦ ይታየኛል….

“ውብ…ሴት…የዋህ…የገዛ…ጐዶሎዋን አጉድላ…የሌላን ሰው ስሜት ለመሙላት እምትታትር “እፉዬ ገላ” የሆነች እያለ በልቡ ሲያልጐመጉም ሰማሁት…እሱ ለኔ አዝኖ አሳዘነኝ…በስስት አይኑ አገላብጦ ከፊትም ከኋላም አየኝ…እንዳይበርደኝ ከነፋስ የተፈተለ ነፋስ ሸማ…ባዶው ገላዬ ላይ አለበሰኝ…(አሳዘነኝ የሱም ገላ ተራቁቷል…የሱም ስሜት ተጐድቷል) ቀስ አድርጐ…አንገቴ ስር ሳመኝ…አይኖቼን ስለጨፈንኩ ቀስ ብሎ ድምጽ ሳያሰማ በመጣበት ወጣ፡፡ በልቤ ግን አየሁት…ሲራመድ ያምራል፡፡

***

ከአንድ ክር የተሠራውን የውስጥ ሱሪዬን ታጠቅሁ፡፡

***

ያልሰፋም፣ ያልጠበበም…ውቧ አረንጓዴ ቲሸርት…ለላይኛው ገላዬ አጠለቅሁለት፣ (ነፋሱ ከስር ያለበሰኝ እንዳለ)

***

“እስቲ ዛሬ ቀሚስ ልልበስ…” ለራሴ ነገርኳት…እንደ ህፃን ልጅ…ብስኩት እንደተገዛለት…ፈገግ አልኩ፡፡

***

ከቴክኒሻኔ ጋር ተገናኝተናል፡፡ መረቅ የሆነ አዳር ለማደር ተዘገጃጅቻለሁ፡፡

በጣም ዝቅተኛ ሆቴል ነው ያለነው፡፡ ፊት ለፊት ተቀምጠናል…ዐይኑ…

ዐይኔ ውስጥ የሆነ ነገር ይበረብራል…(ምንም እንደሌለኝ አላወቀም፡፡)

“ልጆችህ ደህና ናቸው?”

“በጣም” ምንም ውስልትና እንደሚሠራ ሰው አይቅበዘበዝም…

“ባለቤትህስ?”

“ሠላም ናት”

“አታሳዝንህም?” ለምን እንዳልኩት አልገባኝም፡፡

“ታሳዝነኛለች…አንቺም ታሳዝኚኛለሽ”፡፡ አለኝ ትንፋሹን ወደ ከንፈሬ እየገፈተረ…ይዞልኝ የሚመጣቸው ውስኪዎች ልቤን ሳያንኳኩ…ያስከፍቱኛል…የገቢ ምንጭም ናቸው፡፡

“ታሳዝነኛለች አንቺም ታሳዝኒኛለሽ?...

“ለምንድነው የምታሳዝንህ?”

“የልጅነት ፍቅረኛዬ ናት…ሲበዛ ታምነኛለች…ከእሷ ሌላ ሴት የጐበኘሁት አንቺን ነው፡፡”

“እኔስ ለምን አሳዝንሀለሁ?”

“እንደማላዛልቅሽ አውቃለሁ!”

“ለምን?”

“ሚስቴን በጣም እወዳታለሁ”

“ከወደድካት ለምን በላይዋ ላይ…” አላስጨረሰኝም፣ የቁጭት ፈገግታ ፈግጐ… “አራት ልጅ የወለድነው…ያለምንም እረፍት በተከታታይ ነው…እኔ ያ..እንዲሆን ፍላጐቱ የለኝም ነበር…እሷ ግን…አሁን ዘግይታ የነገረችኝ ነገር ያሳስባት ስለነበር…በልጅ አስራኝ በፍቅሯ ቀይዳ ማቆየት ፈለገች፡፡

“ምን ብላህ ነው…?” ለመንገር አልፈለገም ነበር…ከእኔ ጋር የወጣቸው ቀኖች አመውታል፡፡ “አየሽ…ሚስቴ ተወልዳ ያደገችው ገጠር ነው፣…የአስራ ሰባት አመት ልጅ ሆና ነው እዚህ የመጣችው…ልጅ ሆና …ተገርዛ ስለነበር…” መብረቅ የመታኝ መሠለኝ…! ትክል ድንጋይ ይመስል ድርቅ!

“ህመሙም…ፍርሃቱም ልቧ ውስጥ እማይድን ቁስል ነበር…ከመጋባታችን በፊት ነክቻት አላውቅም…ተጋባን…”…የሚያቃጥል ትንፋሽ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ፊቴ ላይ የነበረውን የመደንገጥ ፍም እፍ ብሎ አቀጣጠለው፡፡

“ከተጋባን በኋላ ደስታን ፈልጌ አጣኋት…ምንም ስሜት አልነበራትም…የእሷን ስሜት ስፈልግ የኔን ስሜት እየጣልኩት…አራት ልጅ ወለድን…አልጋ ላይ ስሜት ባይኖራትም እወዳታለሁ…ታሳዝነኛለች…ገላዋ…የእኔን ገላ ያምናል…እየታመምኩም ቢሆን ከአሁን በኋላ ህመሟን አክማለሁ…ለዛ ነው…ያሳዘነችኝ…ቀድማ ብትነግረኝ ኖሮ…ያጣሁት የመሠለኝን ጊዜያዊ ደስታ እሷው ውስጥ አገኘው ነበር…”

እኔ እንዳታለልኩት አውቃለሁ…ግን …የሚስቱን ህመም ሳያድን…የእኔን ስሜት…ማከም ችሏል…የዛች ምስኪን እድለኛ ሚስቱ ቁስል…የእኔም ህመም ነበር…ለአመታት ጠፍቶብኝ የነበረውን የሥጋ ስሜት አግኝቶልኝ ነበር…እውነቱን ነው…አያዛልቀኝም…ቀምቶ መብላት አያጠግብም፡፡ የማይጠጣ ውሃ ነው …እማያድን ጠበል፡፡ ያዘዝነው ምግብ ሳይመጣ ተነሳሁ…ስሜቴ ገብቶታል መሠለኝ ቀስ ብሎ “ምነው?” ብቻን ተነፈሰ…”አሳዘንከኝ” አልኩት፡፡ “አሳዘነችኝ” ነበር ማለት የነበረብኝ…ከመቀመጫው ሳይነሳ በሩን አልፌ ወጣሁ…ልቤ ግን…”አቤት ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም…” ትል ነበር፡፡

***

ከወንድ የተረፈኝን ጊዜ…ህመምተኞችን እና አቅመደካሞችን እጐበኛለሁ፡፡

አቅም በፈቀደ፡፡ ለወንድ ያዘመመ መንፈሴን ይሄ ይሆን ቀና ብዬ እንድሄድ የረዳኝ፡፡

***

ለዛችኛዋ ሴት እያዘንኩ ራሴን በፀፀት ሳማ እየለበለብኩ እገኛለሁ፡፡

ንስሃ ቢሆነኝ፡፡

***

ፈጣሪስ ሰሎሞንን ታግሶት የለ…ስንትና ስንት እቁባቶች የነበረውን፣ ጐልያድን ጉልበተኛ አድርጐ፣ በትንሹ ዳዊት ሲረታው…እኔን አዕምሮዬን የሥጋ እውቀት ሞላውና ነፍሴን ከሲታ አደረጋት፡፡

***

የልጅነት ትዝታ ልቤ ውስጥ መቅደሱን ሠርቶ እያመለኩት ነበር….ያልተማረ ማህበረሰብ…ይዞት እሹሩሩ ሲለው የነበረው አጉል ባህል ዋርካውን ካልገረሠስነው…እሚያስከፍለን ዋጋ…ውድ ነው፡፡

የተፈጥሮ እርካታዬን ተነፍጌ…ከሥጋ ሥጋ እየዘለልኩ…ሥጋት ላይ ነኝ…

ብዙ ነገር እያለኝ…ግን…ምንም የለኝም፡፡

ለሌሎች እየኖርኩ…ለራሴ ግን የለሁም፡፡ በሰፊው ነው የማፈሰው!

ትላንትና ዛሬ አይደለም…!....ዛሬም ነገን አይሆንም…!

“መላእክቱ ሁሉ ይሰግዱለታል…አቤቱ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፡፡

የይሁዳ ሴት ልጆች ደስ አላቸው፡፡”

***

የወደቀን ማንሳት ከተቻለ…፣ የተናደን ከገነቡት፣ የፈሰሰን አፍሰው ለቅመው ንፅህናውን ከጠበቁለት…ምነው ታዲያ እኔን ረሳኝ…?

***

መስተዋት ፊት ቆሜ አላውቅም፡፡ እኔን ጠልቻት ወይ ደግሞ ፈርቼ አይደለም፡፡ ገላዬ አይደለም ልቤም አይደለም፡፡ ከንፈሬም አይደለም፡፡ ነፍሴ ፆመኛ ናት፡፡

 

አንድ የሆነ ደስ የሚል …ስሜት…በልጅነቴ ፍልሰታን አስቀድስ በነበረበት ጊዜ የሚሰማኝን አይነት ጥሩ ስሜት…እንደ ነፋሱ የተላከ…ተይ! ተይ! ይለኛል…”ትቼስ” እለዋለሁ …

(እግዚአብሔር ያውቃል፡፡)

***

አብቅቷል

 

 

 

 

Read 76732 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 11:49