Print this page
Saturday, 07 July 2012 10:03

የህልሜ ጓደኛ

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(3 votes)

ህልም - ወለድ ታሪክ ሊልሌ

ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥሬ ስለምውል ስለብቸኝነቴ ለማሰብ ፋታ የለኝም፡፡ ብቸኝነቴ ትዝ የሚለኝ ሲጨልም ነው - ፀሃይ ስትጠልቅ፡፡ ጨለማው ከች ሲል የብቸኝነትን ብርድ ልብስ ያከናንበኛል፡፡ በተለይ ወደ ተከራየኋት አንዲት ክፍል ቤት ሳመራ ብቻዬን ሆኜ አላውቅም፡፡ ከጐኔ ብቸኝነት አለ - የባጥ የቆጡን እያወራ፡፡ ብቸኝነትን ለማባረር የዘየድኩት መላ ምሽቱን በድራፍት ቤት ማሳለፍ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ድራፍት ቤት ውስጥ ዝንተ ዓለም መቀመጥ አይቻልም፡፡ በዚያ ላይ አከራዮቼ የውጭውን በር ይከረችሙታል፡፡ ከርፊው ከምሽቱ 4 ሰዓት ተኩል ላይ ነው፡፡ ስለዚህ በጊዜ ሦስት ወይም አራት ጃምቦዬን ተከናንቤ ወደ ማደሪያዬ ማዝገም አለብኝ፡፡

ከድራፍት ቤቱ እንደወጣሁ ሞቅታው ባጐናፀፈኝ መነቃቃት ታጅቤ የምሽቱን ነፋሻማ አየር እየማግሁ እጓዛለሁ - ወደ ብቸኝነቴ፡፡ በተለይ ሰፈሬ ስደርስ ድብርት ይጫጫነኛል፡፡ የገዛ ቤቴ ያስፈራራኛል፡፡ ይሄኔ ትንሽ መራር ፀሎት ወደ ሰማዩ ጌታ እልካለሁ፡፡ “አምላኬ ስጠኝ በልኬ!” እለዋለሁ - ሁልጊዜ ማታ ማታ ከድራፍት በኋላ፡፡ አንዳንዴ ግን እራሴን እጠይቃለሁ - “ፈጣሪ የሞቅታ ፀሎት ይሰማ ይሆን?” እያልኩ፡፡ ትንሽ ጥርጣሬ ይገባኝና ወዲያው ደግሞ “እሱ እንደሰው አይደለም፤ የልብ ያውቃል” እልና እፅናናለሁ፡፡ ነገም፤ ከነገ ወዲያም፤ ከዛ ወዲያም ያው ነው፡፡ ሆዴን በድራፍት ፀበል አጥብና “ኧረ ዓምላኬ ስጠኝ በልኬ!” እያልኩ ውትውት አደርገዋለሁ - “ዝምታ ወርቅ ነው” ያለ የሚመስለውን ፈጣሪዬን፡፡ ከዛ እተኛለሁ - ብቻዬን፡፡

ሌሊት ላይ ድንገት ከእንቅልፌ ስባንን ግን ብቻዬን አይደለሁም፡፡ ከጐኔ ብቸኝነት ተጋድሟል፡፡ በእርግጫ ብዬ ከአልጋዬ ላይ ብወረውረው ደስታዬ ነው፡፡ ግን አቅመ ከየት ይምጣ! እሱ እንደሆነ አንዳች ነው የሚያህለው፡፡ አንድ ሌሊት ግን እልህ ያዘኝ፡፡ ተነሳሁና ጐትቼ መሬት ፈጠፈጥኩት፡፡ ሊታገለኝ አልሞከረም፡፡ “ምናባህ ትፈልጋለህ?” ብዬ አምባረቅሁበት፡፡ እሱ እቴ! ጋግርታም ነው፡፡ ትቢቱ የበለጠ አሳረረኝ፡፡ እየጐተትኩ ከቤቴ አስወጥቼ ደጅ ብርድ ላይ ወረወርኩት - በቀትር ሌሊት፡፡ ደግነቱ ካልገባሁ ብሎ አልታገለኝም፡፡ በሬን ቀረቀርኩና ትልቅ ሳፋ አስደግፌ ተመልሼ ተኛሁ - ገና ከሌሊቱ 9 ሰዓት ነበር፡፡ ለካስ መኝታው ሲጐረብጠኝ የነበረው ይሄ ጋግርታም ያለ ሃሳብ እላዬ ላይ እየተጋደመ ነበር፡፡ አሁን ዘና ብዬ በምቾት ለጥ አልኩኝ፡፡

በሚቀጥለው ክፍል እናቴ እንጀራ ትጋግራለች፡፡ እኔ አልጋዬ ላይ ተቀምጬ መፅሃፍ አነባለሁ፡፡ ትልቋ እህቴ በሬ ላይ ቆማ ስትጠራኝ ቀና ብዬ አየኋት - አቤትም እመትም ሳልላት፡፡ “ስጥልኝ ብላኝ ነው” አለችና በእጇ የያዘችውን ሦስት ነጫጭ ሻማዎች አሳየችኝ፡፡ “ማነው ያለሽ?” አልኳት ተገርሜ፡፡ ሻማ ያዋስኩት ሰው እንደሌለ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ አንዲት ረዘም ያለች የምታምር ቀይ ወጣት ድንገት ብቅ አለች፡፡ ተያየን፡፡ ከፈገግታ ውጭ አንዲት ቃል አልተነፈሰችም፡፡ የሻማዎቹ ባለቤት እኔ ነኝ ማለቷ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ሻማዎቹን ለምን እንዳመጣችልኝ እኔም አልጠየኳትም፤ እሷም አልነገረችኝም፡፡

ከእንቅልፌ ስነቃ የአዕምሮዬ የመጀመሪያ ሥራ ስለ ህልሙ ማሰላሰል ነበር፡፡ ልጅቷን በዓይን አውቃታለሁ - አልፎ አልፎ መ/ቤታችን ብቅ ትላለች፡፡ ከሰላምታ ያለፈ ትውውቅ ግን የለንም፡፡ በህልም ሻማ መስጠትና መቀበል ምን ይሆን እያልኩኝ ወደ ሥራዬ ለመሄድ ተነሳሁ፡፡

በጣም የገረመኝ ግን ከዚያን ሌሊት ወዲህ ብቸኝነትን አይቼው አላውቅም፡፡ ማታ ማታ ድራፍቴን ተከናንቤ ወደ ቤቴ ሳዘግም ብቸኝነት አጠገቤ የለም - ሁሌም ብቻዬን ነኝ፡፡ ፀሎቴን ግን ዘንግቼ አላውቅም - “አምላኬ ስጠኝ በልኬ”  እለዋለሁ - በየምሽቱ ወደ ላይ አንጋጥጬ፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ ለሥራ ጉዳይ ወደ መተሃራ የሚሄድ አውቶብስ ላይ ተሳፍሬያለሁ፡፡ በጠዋቱ ዝናቡ እየረገጠው ስለነበር ብስብስ ብያለሁ፡፡ ከኋላ ወንበር ላይ ነበር የተቀመጠኩት፡፡ አውቶብሱ ሊነቃነቅ ሲል አንድ የሥራ ባልደረባዬና በህልሜ ሦስት ሻማዎች የሰጠችኝ ረዥሟ ቀይ ልጅ አውቶብሱ ውስጥ ገቡ፡፡ ክው አልኩኝ፡፡ መጀመርያ ያየችኝ ባልደረባዬ ነበረች - ፈገግታ ለገሰችኝና ተያይዘው ወደ እኔ መጡ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥንና ከእኔ ፊት ያለው ወንበር ላይ ተቀመጡ፡፡ ለስሙ ነው እንጂ ከጐኔ የተቀመጡ ያህል ነበር፡፡ ባወራሁ ቁጥር ፊታቸውን ወደኔ እያዞሩ ነው የሚያዳምጡኝ - ወግ በዓይን ይገባል እንዲሉ፡፡ መቼም የዛን ዕለት “ቀልዶች” ከየት እንደመጣልኝ እግዜር ይወቀው! አንዳንዶቹን እኔም ራሴ አላውቃቸውም፡፡ በቃ እኔ አወራለሁ፡፡ እነሱ ይስቃሉ፡፡ በተለይ በህልሜ ሻማ የሰጠችኝ ልጅ ከልቧ ነው የምትስቀው፡፡ ጥርሷ ብቻ ሳይሆን ዓይኗም ይስቃል፡፡

በዝናቡ በስብሶ የነበረው ኮቴ በምን ተዓምር እንደደረቀ ግራ ገብቶኝ ልጅቷን ጠየቅኋት፡፡ ያደላት ናት - እሷ! ሥራዋ መሳቅ ብቻ ነው!

“ሳቅሽ ይሆናል ያደረቀው!” - አልኳት ሳላስበው፡፡ የባሰ ለቀቀችው - ሷቋን፡፡ ብዙ ዓይኖች ወደ እኛ ተወረወሩ፡፡ አጠገቧ የተቀመጠችው የሥራ ባልደረባዬ “ኧረ ቀስ በሉ!” አለች - በተወረወሩት ዓይኖች ተሸማቃ፡፡ እኛ ግን ዓይነ ጥላችን ተገለጠልን መሰለኝ ባሰብን፡፡ ከዚያ በኋላማ ማን ይቻለን! የማናወራው ወሬ፤ የማንስቀው ሳቅ የለም፡፡

መተሃራ ጉዳያችንን ጨርሰን ስንመለስም በአንድ አውቶብስ ላይ ነበርን - እዚያው መቀመጫችን ላይ፡፡ አሁንም ከጣራ በላይ እየሳቅንና እያወጋን አዲስ አበባ ገባን፡፡ የሥራ ባልደረባዬ ግን እኛን ትታ መፅሃፍዋን መርጣ ነበር፡፡ ወሬያችንና ሳቃችን ፋታ ስላልሰጠኝ ልጅቷን በህልሜ እንዳየኋት የነገርኳት ከወረድን በኋላ ነው፡፡ በህልሜ አየሁሽ አልኳት እንጂ ዝርዝሩን ግን አልነገርኳትም፡፡ እንኳንም አልነገርኳት ሳልል አልቀረሁም፡፡ የሞባይል ቁጥሯን ለመቀበል ሁነኛ ምክንያት አገኘሁ፡፡ “ስልክሽን ስጪኝና ማታ ደውዬ ህልሙን እነግርሻለሁ” አልኳት፡፡ እሷ እንደሆነ ፈጣሪ እጁን ታጥባ የፈጠራት ናት - ቅንጣት ጥርጣሬ ሳይታይባት በተለመደው ሳቋ አጅባ ቁጥሯን ነገረችኝ፡፡ ማታ ደወልኩላት፡፡ ሳቋ ናፍቆኝ እንጂ ህልሙን ልነግራት አልነበረም፡፡ የማይቋረጠውን ንፁህ ሳቋን ሰማሁና ለውለታዋ ሁለት ግጥሞችን በጆሮዋ አንቆረቆርኩላት - የጥበብ ስሜቷን ለመፈተሽ፡፡ አላወቅሁም እንጂ ልጅቷ ሁለመናዋ ከጥበብ የተሰራ ነው፡፡ ሳቅ ራሱ ጥበብ አይደለም እንዴ!

በየቀኑ መደወል ጀመርኩ - በህልሜ ያየኋት ልጅ ጋ፡፡ ህልሙን ግን አልነገርኳትም - ልቧን ለማንጠልጠል ሳይሆን ለመገናኘት ምክንያት እንዲሆነን ብዬ ነው፡፡

በዚያው ሰሞን ህልሙን ልንገርሽ ብዬ ምሳ አብረን ለመብላት ተቀጣጠርን፡፡ ፍልውሃ ሬስቶራንት ምሳ በልተን ማኪያቶ እየጠጣን ህልሜን ከሀ እስከ ፐ ነገርኳት፡፡

በጆሮዋ ብቻ አይደለም የሰማችኝ - በሁለመናዋ ነው፡፡ ሁሉ ነገሯ ከእኔ ጋር እንደነበር ታስታውቃለች፡፡

የተለመደው ሳቋ ጆሮዬ ውስጥ ይፈሳል - እንደ ጣፋጭ ዜማ፡፡

ያየሁትን ህልም ለእናቷ አስፈትታ እንድትመጣ ተስማማን፡፡ የህልሙ ነገር በዚህ ቢቋጭም ሳናውቀው ሌላ ነገር ጀምረን ነበር፡፡ መነካካት፤ ትክ ብሎ መተያየት … እና የተለመደው የሳቅ ጅረት! … ጅረቱ እንደ ጉድ ጆሮዬ ውስጥ ይፈሳል … ይፈሳል … ይፈሳል፡፡

ተቀራርበን ስናወራ ሁለተኛ ቀናችን ነው፡፡ በህልሜ ያየኋት ቀን ከተቆጠረ ምናልባት ሦስተኛ ቀናችን ሊባል ይችላል፡፡ ለታዘበን ግን ከዓመት በላይ እንደሚተዋወቅ ሆነን ነበር፡፡ መነካካቱና መደባበሱ አቅሌን አሳጣው መሰለኝ ሳላስበው ጠጋ አልኳትና የግራ ጆሮዋ ላይ ከንፈሬን አሳረፍኩባት፡፡ እኔ ደነገጥኩ፤ እሷ ግን ሳቀች፡፡

ሳቅዋ ድንጋጤዬን አባረረውና ዓይኔን በጨው አጥቤ የግራ ዓይንዋ ላይ ደገምኳት፡፡ አሁን አልሳቀችም፤ ትክ ብላ አየችኝ፡፡ እቺ የሳቅ ዥረት የፍቅር ዥረትም ሳትሆን እንደማትቀር ልቤ ጠረጠረ፡፡ ከዚህ በኋላ ማን ይቻለን! የፍቅር አክተሮች ሆነን ቁጭ አልን፡፡ ወሬያችን፣ ሳቃችን፣ ፍቅራችን ሞቀ፤ ደመቀ፡፡

ሌላ ቀን (ምናልባት ከዓመት ገደማ በኋላ) ሳቂታዋ የህልሜ ጓደኛ እንዲህ ስትል ጠየቀችኝ “ለምን ወደድኩህ?” ደንግጬ አየኋትና “ምን አልሽ?” አልኳት፡፡ “ለምን  ወደድኩህ?” ደገመችው - ዓይኗን ዓይኔ ላይ እያንከባለለች

“ፈጣሪዬን ጨቅጭቄው ነበር” አልኳት - ለጥያቄዋ መልስ እንደማይሆን እያወቅሁኝ፡፡

“ምን ብለህ?” አለችኝ - እየሳቀች

“አምላኬ ስጠኝ በልኬ ብዬ” - አልኳት፡፡

የበለጠ ሳቀች፡፡ በጣም ሳቀች፡፡ ብዙ ሳቀች፡፡ ሳቋን እንዳገባደደች በተራዬ ድንገተኛ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ “ፍቅሬ፤ ህልሙ እኮ አልተፈታም” አልኳት

“ኧረ ባክህ … ከዚህ በላይ እንዴት ይፈታ!” አለችኝ - ገፋ ብሎ ወደሚታየው ሆዷ በእጇ እያመለከተችኝ፡፡

በህልሜ ያበረከተችልኝ ሻማ ፍቺው ገባኝ፡፡ በህልም ሻማ ማለት ሳቅ … ደስታ … ፍቅር… ደግነት… ህይወት… ልጅ… ነው ለካ!! ፈጣሪዬ በልኬ የተሰፋ ፍቅር ስለሰጠኝ አመሰገንኩት፡፡

 

 

Read 5825 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:28