Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:45

‘ቮለንቲር ጠራጊ’

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ድሃ የመሆን ስጋት አይደለም ከሚወደው እንቅልፉ ጋር ያጣላቸው፡፡ ለድሃ አብዝቶ ማዘን ነው ማልዶ ከእንቅልፉ መንቃት ያስጀመረው፡፡ ካልረፈደ ከአልጋው የማይነሳ እንቅልፋም ሰው ነበር፡፡ አሁን ግን ማልዶ መንቃት ጀመረ፡፡በውድቅት ሌሊት ይነቃል፡፡ ከአልጋው ይወርድና የዶርም ጓደኞቹን እንዳይቀሰቅስ ተጠንቅቆ የዶርሙን በር በቀስታ ከፍቶ ወደ ኮሪደሩ ያማትራል፡፡ ዙሪያ ገባው ጭር ማለቱን አረጋግጦ ኮሪደሩ ላይ ተጋድመው ከሚያዛጉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶችን አንዱን ብድግ ያደርጋል፡፡ ኮሪደሩን ከሞላው ቆሻሻ እያፈሰ ቅርጫቱን ይሞላል፡፡ እርጥብ ደረቁን ሳይጠየፍ እየተጣደፈ ይለቃቅማል፡፡ በተቻለው አቅም ኮሪደሩን ከቆሻሻ ለማፅዳት ደፋ ቀና ይላል፡፡ ጊዜ ካገኘ ወደ መፀዳጃ እና መተጠቢያ ቤቶች ይገባና ያለመታከት ቆሻሻውን ያፀዳል፡፡ እየተጣደፈ ሌሊቱ ከመንጋቱ፣ ተማሪው ከመንቃቱ በፊት የቻለውን ያህለ ቆሻሻ ለቅሞ ወደ ዶርሙ ይመለሳል፡፡

እንዲህ ማድረግ የጀመረው በሕንፃው ነዋሪ ተማሪዎች ተስፋ ቆርጦ በከፍተኛ ብስጭት እንቅልፍ አጥቶ ያደረ እለት ነው፡፡

ከዚያ በፊት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተማሪዎች ቆሻሻን

በአግባቡ እነዲያስወግዱ ይመክርና ያግባባ ነበር፡፡ የሚሰማው አላገኘም፡፡ ኮሪደሩ ከነጋ ጠባ በቆሻሻ መሞላቱን አላቋረጠም፡፡ ይሄም ሆኖ ገን የሕንፃውን ንፅህና ለማስጠበቅ መጣሩን አልተወም፡፡ ቢመክሩት እንቢ ያለ ተማሪ ቢያስፈራሩት በጄ ይል ይሆናል ሲል አሰበ፡፡

አስቦ አልቀረም፡፡ ለማስፈራራት ሞከረ፡፡ ሙከራው ከንቱ ድካመ ሆነ፡፡ በሙከራው የሕንፃው ቆሻሻ የበለጠ ጨመረ፡፡

ከሕንፃው መግቢያ አለፍ ብሎ ወለሉ ላይ የወደቀውን ወረቀት ሲያይ በሕንፃው ተማሪዎች ተስፋ ቆረጠ፡፡

ተደብቆ የለጠፈውን ወረቀት ተደብቀው ገንጥለውታል፡፡ ቆሻሻውን ሊቀንስ ይችላል ያለው ማስጠንቀቂያ የተፃፈበት ወረቀት ከግድግዳው ተገንጥሎ ከወለሉ ወድቋል ከቆሻሻው ተደባልቋል፡፡

በከንቱ ሙከራው ተፀፀተ፡፡

በሁለት ብር ከሃምሳ ቆሻሻ እንደገዛ፡፡ ገንዘብ ከፍሎ በገዛ እጁ ቆሻሻውን እንዳበዛ ተሰማው፡፡ ወረቀቱ ላይ እንዳፈጠጠ ተስፋ ቆረጠ፡፡

“የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ

በሕንፃው ውስጥ ለምትኖሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በሙሉ፡፡ የዶርማችሁንና የሕንፃውን አጠቃላይ ንፅህና እንድትጠብቁ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጣችሁም ቆሻሻን ያለአግባብ ከማስወገድ ሕገ-ወጥ ተግባራችሁ አለመቆጠባችሁ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

በመሆኑም ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ከዚህ ተግባራችሁ ተቆጥባችሁ ለሕንፃው ንፅህና የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት ካልተወጣችሁ የዩኒቨርሲቲውን ሕግና ደንብ ለማክበር ፈቃደኛ እንዳልሆናችሁ በመቁጠር ቢሮው አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ያስጠነቅቃል፡፡

ከሰላምታ ጋር

የተማሪዎች አገልግሎት ቢሮ”

ይላል ወረቀቱ፡፡ ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ከፍሎ በኮምፒዩተር ያስፃፈውን ማስጠንቀቂየውን ገንጥለውታል፡፡ ጥለውታል፡፡ ደግሞ መገንጠሉ ሳይበቃቸው ማሾፍ መሳለቃቸው፡፡ በዚያው በወረቀት ላይ ፀያፍ ቃል መለቅለቃቸው!!

“የተማሪዎች አገልግሎት ቢሮ ሕጋዊ ማህተም መጠቀም በማቆሙ የተሰማንን ሃዘን እንገልፃለን” ይላል አንዱ ወልጋዳ የእጅ ፅሁፍ፡፡

“የሽንት ቤቱ ቧንቧ እስከሚሰራ በየዶርሙ ሁለት ሁለት ፖፖ እንዲከፋፈል እንጠይቃለን” በቀይ ብዕር ሌላው፡፡

“ሻወር ቤት ፓንት የረሳህ፡፡ ምልክቱን ተናግረህ መውሰድ ትችላለህ!” ሌላኛው ስድ ተማሪ፡፡

ሌላው ደግሞ “ከሰላምታ ጋር” ከሚለው ቀጥሎ…

“ከሰላምታ ጋር… ለሁላችሁም በነፍስ ወከፍ ስምንት ቅርጫቶች ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ስንገልፅ በደስታ ነው” የሚል ፅሁፍ አስፍሯል፡፡

እሱ ሁሉንም አንብቦ በሁሉም አዘነ፡፡ በሁሉም ተስፋ ቆረጠ፡፡ በውድቅት ሌሊት ነቅቶ ቆሻሻ መልቀሙን መረጠ፡፡

ይህን ሁሉ የሚያደርገው የአካባቢ ብክለት አሳስቦት አይደለም፡፡ ከሌሎች የተለየ ቆሻሻ ጥላቻ ኖሮበትም አይደለም፡፡ ቆሻሻ ወዶም አየደለም ቆሻሻ በእጁ ማፈስ የማይጠየፈው፡፡ እንዲህ ሲየደርግ ጥልቅ እርካታ ይጐናፀፋል፡፡ ያገዛት ይመስለዋል - ደፋ ቀናዋን የቀነሰላት፡፡

ብጥስጣሽ ወረቀቶች፣ የጫት ገረባ፣ የአቮካዶ ልጣጭ፣ ያለቁ ብዕሮች፣ ያረጀ የጥርስ ቡርሽ፣ ደርቆ የተጣጠፈ ካልሲ፣ የተደፈጠጡ የሲጋራ ቁራጮች፣ የተፋቁ የሞባይል ካርዶች፣ የጋዜጣ ቅዳጆች፣ የደረቁ ዳቦዎች፣ የበሶ መበጥበጫ ጐማዎች፣ ያረጀ የፂም መላጫ፣ አንድ እግር ነጠላ ጫማ፣ የሽሮፕ ብልቃጥ፣ የተጐለጐለ ካሴት፣ ክር የሌለው የሞባይል ቻርጀር፣ ያለቀ መወልወያ፣ የማንጐ ፍሬዎች፣ የሲጋራ ፓኮዎች፣ የታኘኩ ማስቲካዎች…

የመኝታ ክፍሎ ሌት ከቀን ቆሻሻ ይመረታል፡፡ በየኮሪደሩ ቀን ከሌት ቆሻሻ ይበተናል፡፡ ደረቅ ቆሻሻ… እርጥብ ቆሻሻ… ፈሳሽ ቆሻሻ… የአራቱም የህንፃው ወለሎች የሰርክ መለያ ሆኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት ወንድ ተማሪዎች የመኝታ ሀንፃ ቁጥር 302 ነጋ ጠባ ቆሻሻ አይለየውም፡፡ ሀንፃው የቆሻሻ ገንዳ መስሎ ውሎ ማደሩ ከማንም በላይ እሱን ነው የሚያሳስበው፡፡ ቆሻሻውን ለመቀነስ የቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ተማሪዎች ከየመኝታ ቤታቸው የሚያወጡትን ቆሻሻ በአግባቡ ቅርጫቱ ላይ እንዲያጠራቅሙ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምክሩን አስተላልፏል፡፡ ፈርተው ቢለወጡ ብሎ ማስጠንቀቂያ አስፅፎ ለጥፏል፡፡ ብዙ ደክሟል፡፡

በስተመጨረሻ የህንፃው ተማሪዎች የማይበዙበትን፣ ግርግሩ ጋብ የሚልበትን ጊዜ አየመረጠ ቆሻሻ መልቀምና መፀዳጃ ቤቱን ማፅዳት ጀመረ፡፡

ይሄን ሁሉ የሚያደርገው ስቃይዋን በመጠኑም ቢሆን የቀነሰላት መስሎት ነው፡፡ የህንፃውን ንፅህና የመጠበቅ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ሁለት የፅዳት ሠራተኞች አንዷ የሆነችውን ጠይም ወጣት ያገዘ መስሎት ነው፣ ጠይሟ ሴት ደጋግማ ስትማረር ሰምቷል፡፡“አዬ አምላኬ… አሁን ይሄም እንጀራ ነው!” ስትል ሰምቷታል ጥቁር ኩሬ የሰራውን የመታጠቢያ ቤት ሳህን እየጐረጐረች፡፡

“በሽታ እንጂ ምን አተረፍኩ…” እያለች እየበረታባት የመጣውን የኩላሊት ህመም በተመለከተ ለስራ ባለደረባዋ ስታወራ ሰምቷል፡፡ ሰምቷት ግን ዝም አላለም፡፡ ስቃይዋን ሊያቃልል፤ ሸክሟን ሊጋራ ተነሳ፡፡

ቀድሟት መጥረጊያውን ይመዛል፣ ከእሷ በፊት መወልወያውን ይይዛለ፡፡ ቆሻሻውን ቀንሶ ይጠብቃታል፡፡ ወለሉ ፀዳ ብሎ ሲጠብቃት የሚፈጠርባትን ደስታ ተደብቆ ተመልክቷል፡፡ ከመታጠቢያ ቤቱ የወለቀ የበር እጀታ ቀዳዳ አጮልቆ “ዛሬስ ተመስገን ነው! ልብ ገዙ መሰለኝ” እያለች ስትደሰት አይቷታል፡፡

ይህን ማየት ፈፅሞ ደስታ ይሰጠዋል፡፡ ለወራት ተደብቆ ህንፃውን እያፀዳ፣ ተደብቆ የእሷን ደስታ በመመልከት ተደሰተ፡፡

ሳይነጋ ከእንቅልፉ ነቅቶ ኮሪደሩን ከቆሻሻ ያፀዳል፡፡ ደፋ ቀና እያለ ቆሻሻውን ይጠርጋል፡፡ በጠረገው መንገድ እሷ ትመጣበታለች፡፡ መማረሯን ትታ “ዛሬስ ተመስገን ነው! እያለች ፈገግታዋን ይዛ ትመላለስበታለች - የቀሩ ረጋፊ ቆሻሻዎችን ልታፀዳ፡፡

እንደወትሮው እስከ እኩለ ቀን ደፋ ቀና አትልም ሳይረፍድ የእለቱን ስራዋን ታጠናቅቃለች፡፡ እሷ የተመደበችባቸውን የህንፃው ሁለት ወለሎች በጊዜ አፅድታ አጠናቅቃ የስራ ባልደረባዋን ቀሪ ሁለት ወለሎች በማፅዳት ትተባበራለች፡፡እንዲህ ዘና ብላ ሲያያት ደስ ይለዋል፡፡ ስራ ሳይበዛባት ድብቅ ውበቷ ከፊቷ ላይ ደምቆ ይታያል፡፡ ደፋ ቀናው ሲቀንስላት የበለጠ ታምራለች፡፡ለወራት ዘና እያደረገ፣ ደፋ ቀናዋን እየቀነሰ፣ የበለጠ ስታምር አይቶ ተደሰተ፡፡ ተደብቆ ቆሻሻ ማፅዳት፣ ተደብቆ ‘እፎይ’ ስትል ማየት የእለት ከእለት ተግባሩ ሆነ፡፡

እጆቹ ቆሻሻውን፣ አይኖቹ እሷን መናፈቅ ያዙ፡፡ ሰሞኑን ግን የፅዳት ሰራተኛዋ ከአይኖቹ ተሰውራለች፡፡ ለሳምንታት ወደ ህንፃው ዝር ሳትል ቆየች፡፡ እንደ ወትሮው ቆሻሻውን ቀንሶ ቢጠብቃትም እሷ ግን ደብዛዋ ጠፋ፡፡ በእሷ ምትክ ሌላኛዋ የስራ ባልደረባዋን አራቱንም የህንፃው ወለሎች ማፅዳት ጀመረች፡፡

እሱ ግራ ተጋባ፡፡ ምናልባት የኩላሊት ህመሟ ጠንቶባት አልጋ ላይ ውላ ይሆን’ ሲል አሰበ፡፡ ናፈቀችው፡፡

“ስራ እንዴት ነው’” አላት መወልወያ እያጠበች የምትጨምቀውን አዲሷን የፅዳት ሰራተኛ፡፡

“እኔ እምልሽ… ያቺ የድሮዋ የፅዳት ሰራተኛ ሰሞኑን የት ጠፍታ ነው?” ፈራ ተባ እያለ መልሶ ጠየቃት፡፡

እሷም እንደዋዛ ነገረችው፡፡የዩኒቨርሲቲው የሰራተኞች አስተዳደር ኃላፊ የተማሪዎችን የመኝታ ህንፃዎች አጠቃላይ ሁኔታ ገምግመዋል፡፡

በግምገማቸውም ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ በተለይ በህንፃ ቁጥር 302 የሚኖሩ ተማሪዎች ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ መሻሻል ማሳየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ህንፃው የድሮ መልኩን ቀይሮ ሌት ተቀን ፀዳ ብሎ መታየቱን ቀጥሏል፡፡ ብዙም ቆሻሻ ለሌለበት ሕንፃ ቁጥር 302 ሁለት የፅዳት ሠራተኞችን መቅጠር ደግሞ አላግባብ ወጪ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ያቺኛዋንም ከስራ ቀንሰው ሙሉ ህንፃውን የማፅዳት ኃላፊነቱን ለዚችኛዋ ሰጡ፡፡/በቅርቡ በተካሄደ አገራዊ የሥነ ፅሁፍ ውድድር በአጭር ልብ ወለድ ዘርፍ በአንደኝነት ካሸነፈው የደራሲ አንተነህ ይግዛው “መልሶ አዳኝ” መድብል የተወሰደ/

 

 

Read 3388 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 11:39