Print this page
Saturday, 07 April 2012 07:57

ድሐዊ /ሕዝባዊ/ አድሃሪ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

SIDE: A አሉላ

ጐዳናው ድሮ ሃያ ሁለት ማዞሪያ ተብሎ ይጠራ የነበረው ስፍራ ነው፡፡ አንድ የአርባ አመት ሰው፣ ታክሲ እየጠበቀ ቆሟል፡፡ የሶስት አመት ሴት ልጁ ሱሪውን ጐተት አድርጋው ከራሱ አለም አነቃችው፡፡ ወደ እሷ፣ ወደ ታች ተመለከተ፡፡ ሁለት እጆቿን ወደሱ ሰቅላለች፡፡ እቀፈኝ ማለቷ ነው፡፡ ብድግ አድርጐ አቀፋት፡፡ በፀጉር የተሸፈነውን ትንሽ ጭንቅላቷን አንገቱ ስር ወሸቀች፡፡ የትኩሳቷ መጠን ምን ያህል እንደጨመረ ታወቀው፡፡ መኪና ማግኘት አለበት፡፡ መኪናዎቹ ገና መውጣት አልጀመሩም፡፡ ለመውጣትም ለነገሩ አይቸኩሉም፡፡ ማንም ባለመኪና በህግ ስለተገደደ እንጂ፣ በራሱ ፍላጐት የነፃ አገልግሎት መስጠት አይፈልግም፡፡ ጠዋት ከአስራ አንድ ሰአት እስከ ሶስት፤ እንደዚሁም ማታ ከአስራ አንድ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰአት… ባለ መኪና ሁሉ የከተማውን ህዝብ ማገልገል አለበት፡፡ ህጉ ይኼንን ያስገድዳል፡፡ ህጉ ከወጣ አራት አመት ሊሆነው ነው፡፡ በነፃ የቀዳውን ቤንዚን ለራሱ አገልግሎት ቢጠቀም መኪናው ይወረስበታል፡፡ በመንግስት ሳይሆን በህዝብ፡፡ ዘመኑ የህዝብ ሆኗል፡፡ አባትየው እና ልጁ የህዝቡ አካል ናቸው፡፡ እጃቸው ላይ ያደረጉት ባንዲራ ይኼንን ገላጭ ምልክት ነው፡፡

በስቃዩ አመታት ሀገራቸው ላይ የቆዩ፣ ሀገራቸውን ያልሸጡ፣ ለግል ጥቅማቸው የጋራውን ያልበሉት ሳይሆን የህዝብ ጉዳይ አይመለከተኝም ያሉት…የህዝብ ጠላት ተብለው ተፈረጁ፡፡ የስቃዩ አመታት አከተመ፡፡ ከመጠን በላይ የጠገቡት በአገልግሎት ለተበላው ሁሉ እንዲመልሱ ተወሰነ፡፡ አባትየው መንገዱ ጥግ ቆሞ የመኪና አገልግሎቱን እየጠበቀ ነው፡፡ የለበሰው ካኪ ኮት እና ሱሪ አድፏል፡፡ አርጅቷል፡፡ ተጥፏል፡፡

በመንገድ ላይ የሚያልፉት መኪኖች የቤት መኪና ታርጋ ቢለጥፉም…እንደ ቤት መኪና በእንክብካቤ አልተያዙም፡፡ ተላልጠዋል፣ ተገጫጭተዋል፡፡ ብዙ ሚሊዮን ብር ወጥቶ የተገዛ ቤት መኪና መንገድ ላይ የቆመ አይነ ስውር ለማኝ ከእነ ልጆቿ ተሳፍራበት ወደ መረጠችው የልመና ስፍራ መጓዝ ትችላለች፡፡ ክፍለሀገር መሄድም ከፈለገች… መብቷ ነው፡፡ ባንዲራዋን በክንዷ ዙሪያ ሸብ እስካደረገች ድረስ፡፡ መአከላዊ ስለላ ዋና ስራው ህዝብ የሆኑትን እና ያልሆኑትን መለየት ነው፡፡ ህዝብን ከብሔር ውስጥ ለይቶ አንጥሮ ማውጣት፡፡ ነጥረው ለወጡት እውቅና መስጠት፡፡ እውቅናው መታወቂያ ባንዲራ ነው፡፡ ባንዲራው ከቀስተደመና በቀጭኑ እየተቆረጠ እንደሚሰጥ አይነት…ሊባዛም፣ ተመሳስሎ ሊሰራም አይችልም፡፡ የህዝብ ልጅ መሆን እንዲሁ በቀላል አይቻልም፡፡ የህዝብ ልጅ ለመሆን:- ከህዝብ አብራክ ብቻ መውጣት አይሰራም፡፡ አብራክ ውስጥ መቆየት መቻል ግዴታ ሆነ፡፡ “መብት የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ነው”

የይቅርታ ዘመን ነው፡፡ የተጐዳው እና ጐጂው አብረው በዝምታ የሚኖሩበት፡፡ ዝምታው የላሽ እና የተላሽ ዝምታም ነው፡፡ አቁሳይ፤ ያቆሰለውን እየላሰ፣ ቁስሉ እስኪጠግግ የሚለማመጥበት የአገልግሎት ዝምታ፡፡ ቁስሉ እየደረቀ፣ እየተሻለው የመጣው ተበዳይ፤ በዝምታው ውስጥ ቅኔ ንዴት ተቋጥሮ የሚጮህ ይመስላል፡፡ “ቁስሉ ቢድን እንኳን ጠባሳው እንደሚቀር አይገባውም” የሚል የቁጣ ቅኔ ቋጥሮ፡፡

አባትየው አንድ መኪና ከሩቅ እየከነፈ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ መኪናው ቀረብ ሲል አድሐሪያን ልዩ ነን ሲሉ ገዝተው የሚቀዳጁት፤ ደረጃን ማሳያ ተብሎ የሚገመት “መዶሻ” የተባለው መኪና እንደሆነ አወቀ፡፡ የመኪናውን ትክክለኛ የባህር ማዶ ስም መጥራት በፍፁም አልከጀለም፡፡ ከባህር ማዶ የመጡ የባህል ወራሪዎች ህዝብን ለማጥፋት ዋነኛዎቹ መሳሪያዎች እንደነበሩ እንደ ሁሉም የህዝብ ልጅ ያስታውሳል፡፡ እንደ ሁሉም ጭቁን ጨቋኙን ለመዋጋት የበቃው “ውጭ እንቢ” በማለት ነው፡፡

እጁን ያለብዙ ችኮላ በማውለብለብ መኪናውን እንዲቆም አደረገው፡፡ መኪናው እንደ ግመል እሱ እቆመበት መጥቶ ተንበረከከ፡፡ የተከበረው “መዶሻ” መምቻ ሳይሆን የሚመታ ሚስማር ሆኖ… ለአባትየው እና የታመመችው ሴት ልጁ ፍጥነቱን አብርዶ ቆመ፡፡

መኪናው በጥቁር መስታወት የተሸፈነ ስለነበር፤ ሾፌሩን ማየት አልቻለም ነበር አባትየው፡፡ የመኪናው ትልቅ በር ወለል ብሎ ሲከፈት፣ ልጁን እንደታቀፈ በንቀት እርምጃ ወደ ተከፈተው በር ተጠጋ፡፡ ከንቀቱ የተነሳ ነጂውን ለመመልከት እንኳን አልሞከረም፡፡

“በድህነቱ የሚመካ ህዝብ ሀብትን ወይንም ሀብት አግበስባሶቹን ቀና ብሎ አያይም” የሚለው ህዝባዊ መዝሙር… ከዜማ በላይ እውነት ሆኖ በህዝብ ልጆች ህሊና ከፍ ብሎ አድሯል፡፡ አድሮም ተሰናብቶ አልሄደም፡፡ በአደረበት መኖር ቀጥሏል፡፡

“የድህነት ጮራ” አለ አባትየው ለሹፌሩ፡፡ መሄድ የፈለገበትን በቁጣ ተናገረ፡፡

“የድህነት ጮራ…ይቅርታ ጓድ…ቀበሌውን…አድራሻውን ትነግረኛለህ?” አለች በሚንቀጠቀጥ የሴት ፍርሐት ቅላፄ፡፡ አዳዲሶቹን የከተማ እና የቦታ ስያሜዎች እንደማታውቅ…እና ባለማወቋም ችግር ይደርስብኛል ብላ የምትፈራ መሆኗ ገብቶታል፤ አባትየውን፡፡

“እናንተ ከርሰ ፈረንጆች እስከ መቼ ነው… የህዝብን ሀገር የማታውቁት?! ይሄኔ የአሜሪካን ከተማ እና ዘፈን ቢሆን… ሳትጠየቂ ነው የምትመልሽው፡፡ እቺ የህዝብ ልጅ (ወደ ሴት ልጁ እያመለከተ) ህመሟ አንድ እክል ቢፈጥር… ካንቺ እራስ አልወርድም፡፡ ለአገልግሎት የማትበቃ አድሐሪ በሚል ክስ መስርቼ የሞት ፍርድ ይጠብቅሻል፡፡”

አለ አባትየው፡፡ በተለመደ የህዝብ ልጅ ብስጩነት፡፡ ባሪያን በአለፈ ባገደመ ቁጥር በአለንጋው ሸንቆጥ እንደሚያደርገው ባሪያ አሳዳሪ፤ የባሪያውን ንቁነት መቆጣጠሪያ ዘዴው እንጂ… የመጉዳት ፍላጐት ኖሮት አይደለም፡፡

“የድህነት ጮራ…የድህነት ጮራ…ሆስፒታል ነው” እናትየዋ ጠየቀችው፡፡

“ማሚ…” አለች ከኋላ ወንበር ተቀምጣ እንደነበር እስካሁን ልብ ያላሏት የመኪናይቷ ባለቤት ሴት ልጅ፡፡ “ማሚ…የድህነት ጮራ የነፊያት ዳዲ የሚሰራበት መስሪያ ቤት ነው፡፡ ቬሪታስ ተብሎ የሚጠራው እኮ ነው፡፡ አንድ ቀን ለልደቴ አይስክሬም ገዝተሽልኝ… ጥርሴን ካስነቀልሽኝ በኋላ… ትዝ አይልሽም ማሚ?”

አባትየው አድሐሪን የመመልከት ፍላጐት ባይኖረውም…የህፃኗ ድምጽ ውበት ከመቅጽበት እንዲዞር አደረገው፡፡ ህፃኗ ኋላ ወንበር ተቀምጣ በሚገጣጠሙ የፕላስቲክ ምስሎች ትጫወታለች፡፡ እናቷ የጠፋትን አቅጣጫ የጠቆመቻት ከጨዋታዋ ላይ ቀና ሳትል ነው፡፡ በቁጣ የሚገላምጣትን ሰውዬም አልተመለከተችውም፡፡ “ማንንም ሰው ቀና ብለሽ እንዳታይ” እያለች እናቷ በየቀኑ ታስጠነቅቃታለች፡፡ ማስጠንቀቂያውን የተቀበለችው እናቷን ስለምትወዳት ነው እንጂ…እንደ እናቷ ፈርታ በጭራሽ አልነበረም፡፡

አምስት አመቷ ነው፡፡ ምንም ነገር ለመፍራት አቅም የላትም፡፡ አቅሟ በሙሉ አለምን በማወቅ ላይ መዋሉን እንኳን ለማወቅ… ገና የዋህ ነች፡፡

“ሳትጠየቂ መናገር ብልግና መሆኑን አላስተማረችሽም እናትሽ…ተመዝልገሽ አላደግሽም…” የአባትየው አፍ የተለምዶ ቁጣውን እያስተላለፈ ልቡ ግን በድንገት ክው ብሎ ቀርቶበታል፡፡ የውስጣዊ ልቡ፡፡

ኋላ ወንበር ተቀምጣ የምትጫወተውን ልጅ ሲመለከት የሆነ የተቆለፈ የልጅነት ትዝታ እንደ ጋለ ሹካ በተዘጋው ውስጠ ማንነቱ ገብቶ እየፈተፈተ ነበር፡፡ የልጅቷን መልክ ያውቀዋል፡፡ የሚያውቀው ደግሞ ድሮ ነው፡፡ መልኳን እና ፀጉሯን ብቻ ሳይሆን…ደሟንም ያውቀዋል፡፡ ደም አይዋሽም፡፡

…እስካሁን ለማየት የተጠየፋትን ከጐኑ የተቀመጠችውን ሴት ሹፌር የግንባሩን መቆጣጠር ሳያፍታታ የጐድን ፊቱን አዙሮ ተመለከታት፡፡ ታናሽ እህቱን ሀርመኒን፡፡…በልጅነቷ ትምህርት ቤት እጇን ይዞ ተረት እያወራ፣ ስታለቅስ እያባበለ …ያሳደጋትን ሀርመኒን…፡፡ አድጋ እንደ ዘመኑ ወጣት ውጭ ሀገራዊ መሆንን ስትፈልግ እየራቀችው የመጣችው ሀርመኒ፡፡ በወሲብ ሱስ በመለከፏ ሴተኛ አዳሪ ሆነች ተብሎ ሲነገረው የጉሮሮው ሳግ ያነቀው ቀን ሊደውል የሞከረላት ሀርመኒ፡፡ የአሜሪካ ወታደር አግብታ… አሜሪካ የቀረችው ሀርመኒ፡፡ እናት እና አባቱ የሚኮሩባት ሀርመኒ፡፡ ብር የምትልከዋ ሀርመኒ፡፡ ከውጭ ሀገር እና ከዶላር ጋር አብሮ የጠላት ሀርመኒ፡፡ መሞት እና መኖራቸው እንዳይገደው ጠልቶ ከራቀው ቤተሰቦቹ ጋር አብሮ አርቆ የቀበራት ሀርመኒ፡፡ ሀርመኒ እና ሴት ልጇ መኪና ውስጥ ነው ያለው፡፡ አሉላ ሀርመኒን ዞሮ ቢመለከታትም…እሷ ግን አላወቀችውም፡፡ እሱም እሷን እህቱን ያወቃት በልጅነታቸው ምክንያት ነው፡፡ አዋቂነት ላይ የደረሰው ማንነታቸው በሁሉም ነገር ተረሳስቷል፡፡ ተራርቋል፡፡ ተለያይቷል፡፡

የእሷ ፊት የድሮ ሀብታምነት… የሱ ፊት የድሮ ባርነት፤ ባሪያው ባሪያ ነጂ ሆኗል፡፡ ልጆቻቸው ግን የድሮው ቦታ ነው ያሉት፡፡

አንገቱ ስር የተወሸቀችው ሴት ልጅ በአንገቱ አሾልካ ኋላ ወንበር ላይ ምላሷን በጨዋታ ተመስጦ በአፏ ጐን ያሾለከችውን እኩያዋን እየተመለከተች ነው፡፡

እሷም ምላሷን አውጥታ ስትመሰጥ አባቷ ለምን ተይ እንደሚላት አይገባትም፡፡

ከአንቱ ስር ወጥታ ወደ ኋላ ወንበር ለመሄድ ተንጠራራች፡፡ አሉላ ጐትቶ አስቀመጣት፡፡ አሉላ ከአብዮቱ ጋር ስሙን መቀየሩን ማንም አያውቅም፡፡ የድሮ ስሙን የሚያውቁት የድሮው ዘመን ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከድሮው ዘመን ሰዎች እና ከድሮ ጋር አዲሱ ዘመን ተጣልቷል፡፡ የአባትየው አዲስ ስም ጽሐዊ ነው፡፡ በስሙ ግን ብዙም አይጠቀምበትም፡፡ የግለሰብ ስም ጥቅም የሌለው ዘመን ነው፡፡ ግለሰብ እና ግለኝነትን ህዝባዊነት ገድሎታል፡፡

*   *   *

አሁንም ቢሆን፤ በህዝባዊ ሀገር ውስጥ እየኖሩ የምዕራባዊ ህይወት ልምዳቸውን ሙሉ ለሙሉ ያልተው ባሮች መኖራቸው ለድሮው አሉላ ለአሁኑ ጽሐዊ ተገለፀለት፡፡ ምንም ነገር ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀየር ተገለጠለት፡፡ ሀርመኒ ከማይቀየሩት መሀል ነች፡፡ ገንዘብ እና ከገንዘብ ጋር የሚመጡ ምቾቶችን ድሮም እንደምትወደው አሁንም ቢሆን አልተቀየረችም፡፡

“ግን በማን በኩል” ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ መጠየቅ ግን አያስፈልገውም፡፡ ያውቀዋል፡፡ ህዝባዊነት ብቻውን የለም፡፡ አበሻዊነት አብሮ ተዳብሎታል፡፡ አበሻዊነት በሁለት ቢላዋ መመገብ የሚወድ ነው፡፡ አበሻዊነት ንፁህ ሀብታም አልያም ንፁህ ደሀ በሙሉ መንፈሱ መሆን አይችልም፡፡ በባንዲራው ላይ ያለው እምነት በሌላ ባንዲራ ላይ የተዳበለ ነው፡፡ በድህነት ባንዲራው ላይ ምኞቱ ተጥፎበታል፡፡ ጥፈቱ… ዋናውን ጨርቅ ከልሎታል፡፡

አንድ ህዝባዊ ነኝ የሚል ሰው ሀርመኒን ፈረንጃዊነት አፍቅሮ አስጠግቷታል፡፡ አስጠግቷታል፤ ግን እሷም ሙሉ ለሙሉ እጇን ሰጥታ አትጠጋም፡፡ አሜሪካዊውን ወታደር አግብታ ልቧ የነበረው የሀገሯ ወንዶች ዘንድ ነበር፡፡ በሀገሯ ሰው ላይ ደግሞ ስትሆን የባህር ማዶ ውትድርና እንደ እርጉዝ ሴት ያምራታል፡፡

“ወዴት እየሄድሽ ነው?” በቁጣ ጠየቃት፡፡ ድሮ ከትምህርት ቤት ይዟት ሲመለስ

“የምሳ እቃሽን የት ጣልሽው?” ብሎ እንደሚጠይቃት፣ ንግግሩ ርህራሄ የለበትም፡፡ ርህራሄ ማንንም እንዳልጠቀመ ያሳለፈው ህይወት አስተምሮታል፡፡ በሞት መገላገል የነበረበትን ህይወት ማቆያ የከንፈር አመጣጠጥ አይነት ነው፡፡ ስቃይን ያብሳል ቂምን ለግዜው ይደብቃል፡፡ በኪሳራ ጊዜ መግፊያ ዘዴ ነው፡፡ አይቶታል፡፡

“ወደ ስራ”

“የህዝብ ሴት ቤቷን በስነሥርአት ማስተዳደር፣ ባሏን ማገልገል ነው የተጣለባት ህዝባዊ አደራ…ሴት በመስክ መሰማራቷ… በአለፈው ቀውሰኛ ስርዓት ያመጣውን መዘዝ ታውቂያለሽ፡፡ በስራ ስም የሀገርን ስም ማጉደፍ…ሴተኛ ርካሽነቶችን ከሀገር አልፎ በአለም ማስፋፋት ነበር… የተገኘው ጠንቀኛ የታሪክ አሻራ፡፡ ሀገር እና ህዝብን ያሳፈረ ታሪክ የተሰራው በሴቶች የዋህነት ላይ ተመርኩዞ ነበር፡፡….ለመሆኑ ባለቤትሽ እንደሚጠየቅበት አያውቅም፡፡?”

“ባለቤቴ አርፏል”

“ባለቤትሽ ካረፈ ያንቺ አገልግሎት ቤት እና ንብረትሽን ጨምሮ የህዝብ መሆኑን ታውቂያለሽ፡፡ ሴት ልጅሽም ህዝባዊ አደራን ለመወጣት የጐልማሶች ማሰልጠኛ መግባት ይኖርባታል፡፡ በደሀ ሀገር ላይ እንደ ሀብታም ለመኖር ማን ፈቀደልሽ?...የቁጥጥር ኮሚቴውስ እንዴት ሳይደርስብሽ ቀረ?...”

“የጓድ ተፈሪ አብዲሳ እጮኛ ነኝ” እጇን እያሳየች፡፡ “ቀለበት አስረናል፡፡ በቅርቡ ጋብቻ እንፈጽማለን…ደግሞ ጓድ እኔ ለህዝብ አደራ የቆምኩ ነኝ፡፡ ለህዝብ እስከሆነ ድረስ ቤት እና ንብረቴን አሳልፌ ለመስጠት አብዮታዊ ተነሳሽነቴ አያጠያይቅም፡፡ በቀበሌ ነዋሪነቴ ታሪካዊ አደራን ለማሳካት ያደረኩት ተጋድሎ ወጥቶ ሊመረመር ይችላል”

ጓድ ተፈሪ የህዝብ ልጅ ነው፡፡ ከነ ሙሉ ማዕረጉ “የመአከላዊ ድህነት ኮሚቴ” ተለዋጭ አባልም ነው፡፡ አሉላ ሊወነጅለው የማይችል አይነት ሰው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከእህቱ ይበልጥ የሚቀርበው ይህ ሰው ነው፡፡ ሀርመኒን ምንም ሊያደርጋት አይችልም፡፡

“ጫማሽ ደስ ይላል” አለች፤ የታመመችው ልጁ በእቅፉ ውስጥ ሆና የማታውቃት አክስቷን በፍቅር እያየች፡፡ እሷ ከተወለደች ጀምሮ የላስቲክ ጫማ ነው የምታደርገው፤ እንደማንኛውም ታዳጊ የህዝብ ልጅ፡፡ ከቅንጦት ውግዘት በኋላ፣ የፕላስቲክ ጫማ የሁሉም ሴቶች እግርን መሸፈኛ ሆነ፡፡ “መዋብ ድህነትን ያስረሳል” የሚል መፈክር እየተዘመረ፡፡ የፕላስቲኩን ጫማ “የደሀ ኩራት” ብለው ሰየሙት፡፡ ቀይ ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለም አለው፡፡ እውነተኛ ህዝባዊ ልጆች ብቻ ይጫሙታል፡፡ ድሮ ውድ ተብለው ከሚገዙ ጫማዎች የበለጠ በህዝብ ዘንድ ይከበራል፡፡

ባትታመም ኖሮ፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በተቀባው “የአባት ቁንጥጫ” አለንጋ… ጥሩ ተደርጋ ትገረፍ ነበር፡፡ በቀሚስ ባልተሸፈነው ባቷ ላይ በቀስታ አባትየው መዘለጋት፡፡ አላሳመማትም፡፡ አሉላ፤ በአፉ እንደሚናገረው ነው በእጁ የሚሰራው፡፡ ንግግሩም ሆነ ቁንጥጫው በውስጣቸው ባዶ ናቸው፡፡ ሁሉ ነገሩ ሽፋን ነው፡፡ ወደ ሆስፒታሉ በር አስጠግታ ካቆመችው በኋላም ቶሎ ለመውረድ አልፈለገም፡፡ አመነታ፡፡ ጥንካሬው እንዳልነበረ ሆኖ እየተጋለጠ መሆኑ ሲገባው በግድ ግንባሩን ሰብስቦ ቋጠረ፡፡ ስለ እናት እና አባቱ ሊጠይቃት ፈልጓል… ግን ህዝባዊ ያልሆነ ልፍስፍስ ጥያቄ ስለሚመስልበት ሌላ ጊዜ ለማድረግ ወሰነ፡፡

“በነገው እለት፤ ዛሬ የተገናኘንበት ቦታ ተመሳሳይ አገልግሎት ስለሚያሻኝ ከእነ አድሐሪ ልጅሽ እንድትመጪ…ጓድ ተፈሪን ስለ አንቺ የጀርባ አጀንዳ እንዲያስረዳኝ በግንባር ቀርቤ እጠይቀዋለሁ…ኃይል የህዝብ ነው” ብሎ ጮሆ ከመኪናው ወረደ፡፡ መፈክሩን ሀርመኒ እና ልጇ እጃቸውን ጨብጠው ደገሙ፡፡ ሂዱ የሚል ፈቃድ እስኪያገኙ በትእግስት ጠበቁ፡፡ በአገጩ ምልክቱን ሰጣቸው፡፡ መዶሻው ተንቀሳቀሰ፡፡

*   *   *

አሉላ የታመመችውን ሴት ልጁን አሳክሞ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ህመሟ በቀላል አንቲባዮቲክ የሚድን ነበር፡፡ በድሮው የካፒታሊዝም ዘመን ቢሆን መድሀኒቱን ከየትኛውም የግል ፋርማሲ ገዝቶ ያስውጣት ነበር፡፡ ከደሀ አብዮት በኋላ… ንግድ እና ነጋዴ በህዝባዊ ሀይል ተገርስሶ ወደቀ፡፡ …የቅንጦት በሽታ ለገንዘብ ማጋበሻ እየፈጠሩ መድሐኒቱን ውድ አድርገው ከሚሸጡት ምእራባዊያን ጋር የመድሀኒት ቤት ንግድ ከሰመ፡፡ የመድሀኒት ሱሰኞች ወደ ባህላዊ የቅጠላ ቅጠል ህክምና ተመለሱ፡፡ ህዝባዊ የሆኑ የባህል ሀኪሞች… ለንግድ ሳይሆን በሀገራዊ አላማ… ነፃ ህክምና ለበሽተኛው መስጠት ጀመሩ፡፡ በባህላዊ ህክምና ሊፈወስ ያልቻለ ህመም ብቻ… ወደ ህዝባዊ ሆስፒታል ሄዶ መፈወስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ህክምናም ሆነ ትምህርት በጥቅሉ አይበረታታም፡፡ እንቅርት እንደ ጥንቱ በየሴቶቹ አንገት ላይ መብቀል ጀመረ፡፡ ውበት ተብሎም ተወሰደ፡፡

አሉላ፤ ልጅ ይዞ ወደ ደሳሳ ህዝባዊ ቤቱ ሲመለስ፤ ጭንቅላቱ ውስጥ ለብዙ ዘመን ተፈጥሮ የማያውቁ የሀሳብ ሰንሰለቶች እየተቀጣጠሉበት ነበር፡፡ አድሐሪይቱን ሴት (እህቱን) ከተለያየበት ሰአት ጀምሮ የገደለው አእምሮው ከሞት ተነስቶ እንደ አዲስ ይነተርከው ጀመር፡፡ አእምሮን ከማሰብ የሚያስቆም ባህላዊ መዳኒት አለመኖሩ ድንገት አበሳጨው፡፡

አእምሮው መስራት የጀመረው በትዝታ መልክ ነው፡፡

አባቱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ…ያደገበት ቤት…ልጅነቱ በይኑ ላይ እየመጣ ግጥም ማለት ጀመረ፡፡ የማያስታውሳቸው ቅጽበቶች… ሳይጠራቸው መጥተው… ላስታውስ ሳይል ታወሱት፡፡

ታወሰው፤ ድህነት ውስጥ እድሜ ልኩን ይኖር የነበረው ህዝብ፡፡ ድህነቱን ወዶ የወደደውን የመለወጥ ምንም ፍላጐት ሳያድርበት፤…አንድ አይነት ኑሮ ይኖር የነበረው ህዝብ፡፡ ከነ በሽታው፣ ከነተመጣጠነ እህል እጦቱ፣ ብር ምን እንደሚሰራ ያልተገነዘበው ህዝብ…በመተጋገዙ ብቻ አብሮ በህልውና መቆየት የቻለው ህዝብ…የህዝብ እንጂ የግለሰብ ማንነቱን ገና ያላወቀ ህዝብ፡፡

በድንገት አዲስ ሃሳብ ያነገበ መንግስት…ድህነት ውስጥ ነህ ያለኸው ብሎ ለዚህ ያለበትን የተቀበለ…የሌለበትን የሀብት አለም ለማያውቅ ህዝብ ነገረው፡፡…በባዶ እግሩ እየተጓዘ… መሬቱን ከእግሩ ነጥሎ የማያውቅ… እንደ መሬቱ እንደ አፈሩ እግሩ የሚሰነጣጠቅ… በመሬት ላይ የሚኖሩ ተባዮችን በሰውነቱ ውስጥ አስገብቶ የሚያኖር ህዝብ…

እህቱ፤ ሀርመኒ ብላ ስሟን የለወጠችው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ አሉላ ትዝ ይለዋል፡፡ አሁን ትዝታው አገረሸ፡፡ የድሮ ስሟ ደብረወርቅ ነበር፡፡ ሀርመኒ ራሷን ለአንድ ፈረንጅ ሀገር ለሚኖር ሱዳናዊ ሸጠች፡፡ ከሀገሯ አውጥቶ ወደ ሀገሩ በጭነት ዋጋ ወሰዳት፡፡ ሱዳናዊው እየተገለገለባት ሳለ አንድ ልጅ ወለደችበት፡፡ የወለደችለት ቢሆን ውልዱ በህይወት ይኖር ነበር፡፡ የወለደችበት ልጅ፤ ሞተ፡፡ ሱዳናዊው  ሌላ ሚስቶችም አሉት፡፡ ተጨማሪም ማግባት ይችላል፡፡ ብር አለው፡፡ መልክ ያለው ደሀ ወጣት መግዛት ይችላል፡፡ ድሀ ራሱን በጠላ መጠን በቀላሉ ይገዛል፡፡ ይሸጣል፡፡

ሀርመኒ፤ የሀገር ውስጥ ስሟ ነበር፡፡ ለፈረንጅ እና ፈረንጅ መሰል ንኪኪዎች ራሷን ለመሸጥ የሚመች ስም ስለሆነ ነበር ያወጣችው፡፡ የስሟን ድምፅ እንጂ ትርጉሙን ቆይታ ነው የተረዳችው፡፡ ከሱዳኑ ቤት ሳትወጣ ሌላ መሻገሪያ ድልድይ አገኘች፡፡ የአሜሪካኑን ወታደር፡፡ ወታደሩ ያገባት ቀን ደስተኛ እንደሆነችው በህይወቷ ደስተኛ ሆና አታውቅም፡፡ የሰማይ ቤት ዜግነት አግኝቶ ደስ የማይለው የመሬት ሰው የለም፡፡

አሉላ፤ በዚህ ወቅት ነበር ለእህቱ ለመገዛት ድርድር የጀመረው፡፡ ራሱን ለመሸጥ ቢሞክርም የሚገዛው አላገኘም፡፡ ሽያጭ እና ግዢን የሚያስቆመው ፍቅር ነበር፡፡ እሱ ነገር በሰዎች መሀል ጠፍቷል፡፡

ጉልበቱም ሆነ እውቀቱ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም፡፡ ለእህቱ ድህነቱን ቀስ በቀስ ለመሸጥ ድርድር ጀመረ፡፡ ትንሽ ትንሽ ብር እንድትልክለት… ድህነቱን ቀስ በቀስ እየቀረፈች እንድታነሳለት ጠየቀ፡፡ ግን የጠየቀው እሱ ብቻ አልነበረም፡፡ አባቱም እናቱም ሌሎች ወንድም እና እህቶቹም ጥያቄ አቅራቢ ሆኑ፡፡ ሀርመኒ የምትፈልገውን ደሀ ገዝታ… የማትፈልገውን ደግሞ ተወች፡፡ እሱ ከተተውት መሀል ነበር፡፡ … ከሰዎች ጋር መስማማት አቃተው፡፡ አንድ የነበሩ ህብረቶች በሙሉ መፈረካከስ እና ተቃርኖ እየፈጠሩ መጋጨት፣ መጐዳዳት የመረጡበት ወቅት ነበር፡፡

አሉላም ከቤተሰቡ ጋር መስማማት አልቻለም፡፡ ሁሉም ደሀ … ሁሉም ገንዘብ ፈላጊ… ሁሉም ለመሸጥ የቋመጡ ቢሆንም፤ የተሻለ ገንዘብ ያለው ይከበራል፡፡ ያነሰ ያለው ይጠላል፡፡ እሱ የማርያም ጠላት ሆነ፡፡ ማርያም ሀርመኒ ሆነች፡፡ የእለት ተእለት ፀሎት … ምስጋና፣ ክብር እና ጠባቂነት ለሷ ተተወ፡፡

አሉላ ከቤተሰቡ፣ ከውድ ጓደኞቹ … በስተመጨረሻ ከመንግስትም ጋር ተጣለ፡፡ የመንግስት ባህሪ ራሱ ቤተሰቡ ውስጥ ከሚታየው የተለየ አልነበረም፡፡ … በዚህ ሁኔታ ትንሽ ሲከርም ጭንቀቱም ፍርሐቱም ተስፋ መቁረጡም ተደራርበው … የአእምሮ ቀውስ ውስጥ ከተቱት፡፡ መጀመርያ ቤተሰቡ ተንከባክበው … የእእምሮ ህክምና ቦታ ወሰዱት፡፡  … ሲቆይ ችላ አሉት፡፡ እሱም ከቤት እብደት ወደ ጐዳና እብደት ራሱን አሳደገ፡፡

ከእዛ ጊዜ እስካሁን እሱም ስለ ቤተሰቦቹ፣ ቤተሰቦቹም ስለ አሉላ ሰምተው አያውቁም፡፡ እሱ በጐዳና ላይ ወጥቶ በይፋ አበደ እንጂ… በወቅቱ ሁሉም እብደት ላይ ነበረ፡፡ ዝም ብሎ ይሮጣል እንጂ ለማስተዋል ብቃት አልነበረውም፡

*   *   *

አሉላ በአእምሮ ቀውስ ውስጥ ስንት ጊዜ እንደቆየ አያስታውስም፡፡ ማስታወስ ሲጀምር እንደገና በአንድ ገዳም ውስጥ ሆኖ ራሱን አገኘው፡፡ ገዳሙ ውስጥ መሬት ላይ መኖርን ለመደ፡፡ ረስቶ የቆየውን ነገር፡፡ ገዳሙ ውስጥ ድህነትን ኖረበት፡፡ ገዳሙ ውስጥ የህዝብ አብዮት መቀስቀሻ ነጥቦች የሆኑት አንኳር ሀሳቦች ተወለዱ፡፡ እሱም ከውልደት በኋላ በተካሄዱት ህዝብን ወደ ድሮው ማንነቱ የመመለሻ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ ሆነ፡፡ … ከብዙ ትግል በኋላ የድህነት አብዮት ፈነዳ፡፡

*   *   *

“አሁን እቺን ሴት ምን ላድርጋት?” ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ እህቱን ዘመድም ሆነ ጠላት ለማድረግ አቅም አጣ፡፡ ትዝታዎቹ በአእምሮው ውስጥ እየተሽከረከሩ ሰላሙን አጠፉት፡፡

“የሀገሬ ህዝብ እና ድህነት ብቻ ናቸው እስከ ዘለቄታው የማይከዱ ቤተሰቦቼ” ብሎ በሀያል የመፈክር ድምፅ ጮኸ፡፡ አላማ በልብ ሳይሆን በአፍም ነው፡፡ ድህነት የዋህነትም ነው፡፡ ሾካካ እና ሾላካ የሚያደርገው… ሀብት እና የሀብት ፍላጐት መሆኑ አያጠራጥረውም፡፡ ሰው ከሀብት ጋር እና ያለ ሀብት ምን እንደሚመስል ያውቃል፡፡

ድንገት ለተፈጠረበት ጥያቄ እና ሀሳብ መዝጊያ የሆነው የፍቺ መልስ ተከሰተለት፡፡ ሲከሰትለት ዶሮ ሦስት ጊዜ ሲጮህ ስማ፡፡ … የፍቺውን መልስ ስንት ጊዜ በአልቀበል ባይነት ሊክደው ሞከረ፡፡ የፍቺው መልስ የማይካድ እውነት ሆነበት፡፡ ያላወለቀውን ልብሱን አስተካክሎ ከመኝታ እንደተነሣ ሰው ፊቱን ወደ ገበቴው ተጐንብሶ ታጠበ፡፡ ልጁን ከአልጋዋ ቀስቅሶ አስነሳት፡፡ የእሱ እና የሀርመኒ የቀጠሮ ሰአት እየተቃረበ ነው፡፡ “ድህነት ጮራ” የቀጠሮ ሰአታቸው ደርሷል፡፡

እመንገዱ ጥግ እንደ ትናንቱ፤ ሴት ልጁን በግራ እጁ ይዞ የእህቱ መኪና እስክትከሰት መጠበቅ ጀመረ፡፡ ወደ ሆስፒታሉ የሚሄድበት ምክንያት የለውም፡፡ ሴት ልጁ ትላንት በተሰጣት ህክምና ከትኩሳቷ ማገገም የጀመረችው ገና የመጀመሪያዎቹን ሁለት ክኒኖች እንደዋጠች ነበር፡፡ “የድህነት ጮራ” የሚሄድበት ምክንያት በዛሬው ለት የለውም፡፡ … መሄዱን ነው እንጂ የሚፈልገው መድረሱን አይደለም፡፡ እውነተኛ ጉዳዩ … እውነተኛ ህመሙ የሚታከመው በሆስፒታሉ ሳይሆን በእህቱ አማካኝነት ነው፡፡ የምታስለውን ሴት ልጁን ለመፈክር በሚያነሳው የግራ እጁ ጨብጦ መጠበቁን ቀጠለ፡፡

መኪናው ከሩቅ ሲመጣ አየው፡፡ መዶሻው በትክክለኛ ሰአቱ ትክክለኛው ቦታ ላይ ተጠግቶ ቆመ፡፡ አጠገቡ፡፡ እንደቆመ የጋቢና በሩ ተከፈተለት፡፡ በአብዮታዊ እርምጃ ወደ በሩ ተራመደ፡፡ ባዶ እግሩን፡፡ ሀቀኛ “ድሀዊያን” በእግራቸው ላይ ጫማ አይጫሙም፡፡ የውስጥ ሱሪ፣ ካኔቴራ፣ እስፕሪንግ አልጋ፣ የጥርስ ብሩሽ፣ ሶፋ፣ መስታወት … ወዘተ የሰለጠነውን አለም መገልገያዎች አይጠቀሙም፡፡ እሱ ደግሞ ሀቀኛ ተራማጅ ነው፡፡ ድሀዊያን ከፍተኛ እርካታን የሚያገኙት ከስቃይ ነው፡፡ ስቃይን ለመሸፋፈን አልያም ለመቀነስ መሞከር አድሐሪነት ነው፡፡ እግሩ እንደ ኮትቻ አፈር ተሰነጣጥቋል፡፡

መኪና ውስጥ ገብተው ወዲያው ጉዞ ጀመሩ፡፡ የድህነት ጮራን አቅጣጫ ሀርመኒ አሁን በደንብ አውቃዋለች፡፡ በተቻላት መጠን ድሀ ለመምሰል በአለባበሱዋ ሞክራለች፡፡ በእጅ ከተሰራ ቆዳ ጫማ የመኪናውን የቤንዚን መስጫ እየረገጠች በጐንዮሽ ወንድሟን ታየዋለች፡፡ እሷ ድህነትን ለመምሰል እየሞከረች እንደሆነችው እሱ ደግሞ ከሀብት ጋር የሚመጡ ምቾቶች እንደ ክፉ ሰይጣን ከትዝታው ማህደር ድንገት ብቅ እያሉ እየበጠበጡት ነበር፡፡

የሲጋራ መለኮሻ በመኪናው ዳሽ ቦርድ ላይ ተቀምጦ ሲያይ የሲጋራ ማጨስ ፍላጐት ድንገት ውል አለው፡፡ ሲጋራን እና አብዝቶ ስጋን መመገብ የድህነትን መንፈስ እንድንረሳ ያደርገናል፤ እያለ የሚሰብከው እሱ ነበር፡፡ ቄሱ በሰይጣን መንፈስ ከተለከፈ ማን ልክፍቱን ያባርርለታል… ቄሶቹ በሙሉ ደግሞ በግልፅም ይሁን በድብቅ የሠይጣን ቲፎዞዎች ናቸው፡፡ … ለነገሩ የሰይጣንን መኖር ከማንም በበለጠ የሚፈልጉት ቄሶቹ ናቸው፡፡ ሴጣን ከሌለ ሀይማኖትም ሆነ አብዮት ሊኖር አይችልምና፡፡ … ሌሎቹ ህዝባዊ ባለስልጣናት ይሄንን ፅንሰ ሀሳብ አስቀድመው ያውቁታል፡፡

በፊለፊት ምዕራባዊነትን እያወገዙ በድብቅ ግን የሀብት ተከራካሪ ናቸው፡፡ እነሱ ዘንድ ያለው ብልጠት እሱም ነብስ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ ድሮ በመኪና ሊፍት እንዲሰጡት አድሀሪያኑን የሚጠይቀው እነሱን ለማስከፈል ስለሚፈልግ እንጂ… በእግሩ መሄድን ጠልቶ አልነበረም፡፡ ጫማ የማያደርገው ከጫማ ጋር የተያያዘውን የቅንጦት ፅንሰ ሀሳብ ስለማይደግፍ እንጂ… በእግሩ እየሄደ እንቅፋት ሲመታው… ደም ሲፈሰው ደስ ስለሚለው አይደለም፡፡ ግን ለምንድነው ደስ የማይለው? … ደስ ሊለው ይገባ ነበር፡፡ የታገሉለት የድህነት ስርአት… ያለ ስቃይ እና የስቃይ ፍቅር ግቡን ሊመታ የሚችል አይደለም፡፡ እምነቱ በድንገት ለምን እንደተሸረሸረ ግራ ገባው፡፡

“አንቺ የአብዮቱ ጠላት መሆንሽ ጥቆማ ደርሶኝ ክትትል ሳደርግብሽ ቆይቻለሁ… የምእራባዊያን የህሊና ዝቅጠት በህዝባዊ ትግል ከተወገደ በኋላ … በውስጥ አርበኝነት የተወገደውን ስርዓት ለመመለስ በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱት መሀል ቁንጮ መሆንሽን ደርሰንበታል፡፡ በመሆኑም፤ በህዝባዊ ፍርድ ቤት ፊት ቆመሽ ከተዳኘሽ በኋላ… ወንጀለኛነትሽ ከተረጋገጠ … ለህዝብ አገልግሎት አንቺ … ልጅሽ እና በአጠቃላይ በህዝቡ ደም ያፈራሽው ንብረት … እንዲመለስ ይደረጋል” አላት፡፡

ሀርመኒ ንግግሩን ከጀመረበት ቅፅበት በኋላ ምንም ነገር አትሰማም ደንዛዛለች፡፡ ሴት ልጇም እንደሷው፡፡ መኪናው ውስጥ ፀጥታ ነገሰ፡፡ መዶሻው ወደፊት መወርወሩን ቀጥሏል፡፡

*   *   *

SIDE: B ሀርመኒ

ሁሉም ታሪክ ሁለት ጐን አለው፡፡ ብዙውን ጊዜ፤ አንዱ ጐን የእውነታ ሲሆን፤ ተቃራኒው ጐን ደግም የቅዠት ይሆናል፡፡ ሁለቱም ጐኖች ለራሳቸው እውነት ናቸው፡፡ እርስ በርስ ሲተያዩ ግን ተቃራኒ ይሆናሉ፡፡

ድሀዊ የሚያውቀውን አለም፣ ሀርመኒ አታውቀውም፡፡ ለሀርመኒ ወንድሟ እብድ ነው፡፡ ጠዋት ጠዋት ጐዳና ጥግ ቆሞ የሚለፈልፍ እብድ ነው፡፡ እሱ የሚያውቀው የድሀ አብዮት … ማንም አያውቀውም፡፡ አብዮቱ የፈነዳው በእሱ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ … የታመመችውን ልጁን እንጂ መታደግ የምትችለው… ያበደውን ወንድሟን ማዳን ከእንግዲህ አትችልም፡፡ ያላት አንድ አማራጭ ብቻ ነው፡፡ እሱን ወደ አማኑኤል የእብዶች ሀኪም ቤት ማስገባት እና ሴት ልጁን ወስዳ ከራሷ ልጅ ጋር ማሳደግ፡፡

ሀርመኒ፤ ሀመር መኪናዋን እየነዳች ወንድሟንና ልጁን የጐንዮሽ አየቻቸው፡፡ ልጅቱ በአባቷ የድህነት የሀሳብ ሀገር ውስጥ በመኖር በጣም ተጐሳቁላለች፡፡ በእብዱ አባቷ ትከሻ አሻግራ ኋላ ወንበር በናፍቆት እየተመለከተች ነው፡፡ እንደ ሀብታም ልጅ መሆን ትፈልጋለች፡፡ ጣፋጭ ምግብ ያምራታል፡፡ መጫወት ትፈልጋለች፡፡ ልደቷ በየቀኑ እንዲከበርላት ትመኛለች፡፡

እናቷን ትናፍቃለች፡፡ ሀርመኒ እናቷ ብትሆንላት በጣም ደስ ይላታል፡፡ አክስቷ እንደሆነች ነግራታለች፡፡ አባቷ ሳይሰማ፡፡ አቧቷ ማንንም አይሰማም ከራሱ በስተቀር፡፡

ሀርመኒ ታላቅ ወንድሟን ትወደዋለች፡፡ እንዲኖር ትፈልጋለች፡፡ ግን ለእሱ የሚሻለውን እማያውቅበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ፤ እሱ በህፃንነቷ እሷን እየተንከባከበ እንዳሳደጋት እሱን ደግሞ እሷ መንከባከብ ነበረባት፡፡ … ውጭ በነበረችበት ጊዜ ችላ ብላው እንዴት እንደታመመ ታውቃለች፡፡

“ወደ መአከላዊ የድህነት ቢሮ በፍጥነት ውሰጂን” ብሎ ድሀዊ ቆራጥ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

“እሺ ወንድም አለም” አለችው መኪናውዋን ወደ አማኑኤል ሆስፒታል አቅጣጫ ነዳችው፡፡

መኪናውን ስታቆም በሱ በኩል በሩን ቆለፈች፡፡ ረዳቶቹ መጥተው እጁን እስኪያስሩት ድረስ ስለ ድህነት እየዘመረ ነበር፡፡

እጁን ሲያስሩት፤ ተባበረ፡፡ ምክንያቱም ልቡ ወደ ምዕባራዊያኑ ምቾት እያደላ ስለነበረ፤ በቁጥጥር ኮሚቴው ተደርሶበት እንደታሰረ አልተጠራጠረም፡፡ አድሐሪ እህቱን ሳያጋልጥ በጉያው ደብቋት በመቀመጡ ቅጣቱ እንደደረሰበት አልተጠራጠረም፡፡

“ልጄን አደራ … ልጄን አደራ፡፡” አለ ለአማኑኤል ሆስፒታሉ አንድ ሀኪም መሳይ ሰውዬ፡፡ አንድ አብዮተኛ ለሌላው አደራ እንደሚሰጠው ቆፍጠን ብሎ፡፡ “ጓድ! ልጄን አደራ … ደሀ ናት፡፡ ከእናት ሀገሯ ውጭ እናት የሌላት፡፡ ከድህነት ውጭ ዘመድ የሌላት … ከአፈሯ ውጭ ሀብት የሌላት … አደራ ልጄን” አለ በሀይል፡፡ አደራ የተባለችዋ ልጅ በአድሐሪዋ እህቱ መኪና ውስጥ ቀርታለች፡፡

አባቷን ይዘውት ሲሄዱ ህፃኗ ሴት ልጁ እየጮኸች ማልቀስ ጀመረች፡፡ ሀርመኒ ድሀዊ ለእሷ የሚላትን ሁሉ እያስታወሰች ነበር፡፡ አደራ አለባት፤ አደራ ተጥሎባታል፡፡ እንደ እናት ሀገሩዋ አድርጋ ልጅቷን ታሳድጋታለች፡፡ በደረቷ ላይ እንዳቀፈቻት መኪናውን አስነሳችው፡፡ መዶሻው ወደፊት ተንቀሳቀሰ፡፡

 

 

Read 3691 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:08