Saturday, 03 December 2011 08:27

ግራ እና ቀኝ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

ታሪኩ ከቁም ሳጥኑ መስታወት ፊት ለፊት ቆሟል፡፡ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በመስታወቱ ይታየዋል፡፡ መስታወቱን ያያያዘው ማጠፊያ በመገንጠሉ በሚስማር መልሶ ሊጠግን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በመስታወቱ ራሱን መመልከት ለምን እንዳስፈለገው አልገባውም፡፡ ሰሞኑን የተጠናወተው አንዳች ውስጣዊ ሃይል ገፋፍቶታል፡፡ የገዛ ሰውነቱን ማዘዝ ተስኖታል፡፡ ወፎች ሳይነቁ ከእንቅልፉ የተነሳው መላ ሰውነቱ እንደ ሸክላ ፈራርሶ ዶግ አመድ የሚሆንበት ህልሙ አቃዥቶት ነበር፡፡ በቅርብ ቀን ያለወትሮው በግራ እጁ ለመፃፍ ሞክሯል፡፡ አንዴ ደግሞ ቁጭ ባለበት ፀጉሩን ለማከክ የሞከረው በእግሩ ነበር፡፡ የጤና እንዳልሆነ አውቆታል፡፡

በቁም ሳጥኑ መስታወት ግራ በተጋባ ስሜት ራሱን እያጠና ነው፡፡ ሁለመናውን ይጠራጠር ጀምሯል፡፡ የራስ ፀጉሩ ተንጨብርሯል፡፡ ፂሙ አድጎ ተንዠርግጓል፡፡ ግንባሩ እንደወረቀት ተጨማድዷል፡፡ ዓይኖቹም ደም መስለዋል። በቁም ሳጥኑ መስታወት ፊት ማየት የፈለገው ታሪኩን ነበር፡፡ ሆኖም ተቃራኒው ምስል እንጅ እሱ አልነበረም፡፡ የሚያውቀው ተክለሰውነቱ ተጎሳቅሏል፡፡ በመስታወት የሚያየው ግራው ቀኝ፤ ቀኙ ደግሞ ግራ ሆኖበት ነው፡፡ የተቃረነ ስሜት ፈጠረበት፡፡ በመስታወቱ ውስጥ ተክለሰውነቱ ግራና ቀኙ ቢዟዟርም ራሱ ታሪኩ ነው፡፡ በዚያች ቅፅበት ቀልቡ የፈቀደውን ለማድረግ ፈለገ፡፡ በመስታወቱ ራሱን እየተመለከተ ከራሱ ሊወያይ አሰበ፡፡ ሁለት ጆሮ በግራና ቀኝ፤ ሁለት ዓይን በቀኝና በግራ፣ሁለት ግራና ቀኝ ቀዳዳዎች ያሉት አፍንጫ፤ አንድ ጭንቅላት ያለው ገፅታውን በደንብ አስተዋለ፡፡ ከራስ ፀጉሩ የጀመረውን እይታ እስከ እግር ጥፍሩ በመቀጠል መላ ተክለሰውነቱን በትዝብት ቃኘ፡፡ በመስታወቱ ውስጥ የሚታየው ታሪኩ የሚያደርገውን ሁሉ እኩል እያደረገ ነው፡፡ ልዩነቱ ታሪኩ ወደ ቀኝ ሲያይ መስታወቱ ውስጥ ያለው ምስሉ ግን ግራውን፤ ታሪኩ ቀኝ እጁን ሲያነሳ ምስሉ ግራውን እያነሳ አጓጉል መቃረኑ ብቻ ነበር፡፡ በእርግጥ የጎደለ ሰውነት በመስታወቱ ላይ አይታይም፤ የተዛባው ግራና ቀኙ ነው፡፡
በቁም ሳጥኑ ላይ መስታወቱን አስደግፎ ለማንጠለጥል ሚስማርና መዶሻውን አዘጋጅቷል፡፡ በግራ እጁ አውራና ጠቋሚ ጣቶቹ ሚስማሩን ጨብጦ ይዟል ፡፡ በቀኝ እጁ ደግሞ መዶሻውን ጨብጦታል፡፡ ባለ በሌለ ሀይሉ መዶሻውን ወደ ሚስማሩ ሰነዘረ፡፡
አሰነዛዘሩ ልክ አልነበረም፡፡ ሚስማሩን ሳተውና የግራ እጁን አውራ ጣት ድብን አድርጎ ቀጠቀጠው፡፡ ጥፍሩ ተገሸለጠ፤ ደሙ በየአቅጣጫው ፊን ፊን ይል ጀመር፡፡
“ምነው?” በህመም ሲቃ እየጮኸ ሲናገር የሰማው በግራ እጁ ላይ ያለ አውራ ጣቱ ነበር፡፡
“ምኑን?” አላዋቂ መስሎ መዶሻውን አንከርፎ የያዘው ቀኝ እጅ መለሰ፡፡
“በመዶሻ ልትገለኝ “የግራ እጁ ነበር፡፡ ታሪኩ በገጠመው አደጋ አቅሉን ስቷል፡፡ ህመሙን ዋጥ ለማድረግ እየሞከረ ባለበት ግዜ ደግሞ ቀኝ እጁና የግራ እጁ አውራጣት አፍ አውጥተው እየተወዛገቡ ነው፡፡ በእውኑ ይሁን በህልሙ መለየት አቃተው፡፡
ቀኝ እጁ ሆን ብሎ ያደረገው አለመሆኑን ለማሳመን ጥረቱን ቀጥሏል፡፡ የግራ እጁ ግን የተጎዳ አውራ ጣቱን አንከርፎ እንደያዘ በንዴት ግንፍል ብሏል፡፡
ታሪኩ ቅዠቱን ተቋቁሞ ለመንቀሳቀስ ግራና ቀኝ እግሮቹን ለማንሳት ሲሞክር ሁሉ ነገር ጨላለመበት፡፡ ሊያንጠለጥለው የነበረውን የቁም ሳጥኑ መስታወት እንደተገነጠለ ቀርቷል፡፡ ሚስማሩም እንደሳተው ወደ መሬት ተምዘግዝጎ ወድቋል፡፡ መዶሻው ግን በቀኝ እጁ ላይ እንደሙጫ ተጣብቋል፡፡
ዓይኖቹ በድንጋጤ ፈዝዘው ከቆዩ በኋላ እንደመስለምለም አሉና ተጨፈኑ፡፡ ወዲያውኑ ታሪኩ በቆመበት ዘፍ ብሎ መሬቱ ላይ ተዘረጋ - ራሱን፡፡ በወለሉ ላይ የተዘረጋው ሰውነቱ በድን ሆኗል፡፡ ሁለቱም ዓይኖች ሲጨፈኑ የቀኝና የግራ እጅ ውዝግብ ግን ቀጥሏል፡፡ አይኖቹ መጨፈናቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ በግራም ሆነ ቀኝ እያዩ አደጋው ተፈጥሯል፡፡ እነሱ ያላዩትን ዒላማ ማን ሊመለከተው ኖሯል፡፡ በቀኝ እጁ በያዘው መዶሻ ሚስማሩን ስቶ የግራ እጁን አውራጣት ሲመታ ዓይኖቹ ታውረው ካልሆነ በቀር አደጋው እንዴት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለደረሰው አደጋ የመጀመርያ ተጠያቂዎች አይኖቹ ናቸው ብሎ ማንም ይመሰክራል፡፡ ጭፍንፍን ያሉት ይህንኑ ተጠያቂነት ሽሽት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጆሮዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ ግን ይከብዳል፡፡ ሁለቱም የሰሙት ቢኖር ከአደጋው በኋላ እሪ ብሎ የጮኸውን ምላስ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና በቀኝ እና ግራ እጆቹ ከአደጋው በኋላ ድንገት የፈነዳውን አተካራ እየሰሙ እንዳልሰሙ መሆንም አልቻሉም፡፡ ሁኔታውን በቀጥታ ስርጭት ለታሪኩ ሰውነት ማሰራጨት ነበረባቸው፡፡ እጆቹ አንደበት አውጥተው መናገራቸው ዱብእዳ ሆኖባቸዋል፡፡ የአይን እንጂ የጆሮ እማኝነት ምስክር ሊሆን አይችልም፡፡ አሁን ለማን ሊወግኑ ነው? ግራ ለግራው ቀኝ ለቀኙ፡፡
በቀኝ እጅ በተሰነዘረ መዶሻ የግራ እጅ አውራ ጣት ክፉኛ መቁሰሉ ግራዎችን አበሳጭቷቸዋል፡፡ ቀኞች በአምባገነንነት መቀጠላቸው መብቃት አለበት በሚልም እንዲያምፁ ምክንያት ሆነላቸው፡፡ ቀኞችም የበላይነት በተሞላ መንፈስ የግራዎችን ቁጣ ከማፈን ውደ ኋላ አላሉም፡፡
በክፍፍሉ ለግራውም ለቀኙም መወገን ያልቻሉት የታሪኩ የሰውነት ክፍሎች ሁኔታው አላማራቸውም፡፡ ገለልተኞቹ እነ ግንባር፤ ልብና እንብርት በግራና ቀኝ ተከፋፍሎ የከረረው ውዝግብ ቢያሳስባቸውም ታሪኩ አቅሉን ቢስትም እንዳልሞተ እርግጠኞች ነበሩ፡፡ ግን በወደቀበት ደም እንደጉድ እየፈሰሰው ነው፡፡ ውዝግቡ ለእሱ ትኩረት ነፍጎ እንደተካረረ ቀጥሏል፡፡
ግራ እጅ ከቀኝ እጅ፤ግራ አይን ከቀኝ አይን፤ ግራ ጆሮ ከቀኝ ጆሮ፤ ግራ ክንድ ከቀኝ ክንድ፤ ግራ ጉልበት ከቀኝ ጉልበት፤ ግራ እግር ከቀኝ እግር በማይታረቅ ልዩነት ይጨቃጨቃሉ፡፡ በተለይ ቀኙ ወገን በጉልበት ለመቆጣጠር ሲሞክር ግራው ወገን እኩልነት ወይም ሞት የሚል መፈክር ያስተጋባል፡፡ ግጭቱ ከውጪያዊው የታሪኩ የሰውነት ክፍሎች ወደ ውስጥም ተዛመተ፡፡ ቀኝ አንጎል ከግራ አንጎል፤ ቀኝ ጎድን ከግራ ጎድን፤ ቀኝ ሳንባ ከግራ ሳንባ፤ ቀኝ ኩላሊት ከግራ ኩላሊት፤ ሁሉም ያለበትን አቅጣጫ ወግኖ የርስ በርስ ጦርነት ወይም አብዮት የፈነዳ መሰለ፡፡
ታሪኩ አለመሞቱን በምቱ ያረጋገጠው ልብ ብቻ ነው፡፡ በግራና ቀኙ ክፍፍል ግን ሁለት ልብ ሆኗል፡፡ ውዝግቡን በእርጋታ ለማብረድ ቀልባቸውን ሊገዛ ልብ አሰበ፡፡ በልቦናው ያሰበውን ለመላው ሰውነት በሚያሰራጨው ደም ለማድረስ እንደሚችል አውቆታል፡፡ ታሪኩ በድን ሆኖ ሲቀር ግን ልብ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሆነ፡፡ በወደቀበት ብዙ ደም ፈሶት እንዳይሞትም ሰግቷል፡፡
የታሪኩን የሰውነት ክፍሎች ቀልብ ሰብሰብ አድርጎ ስለተፈጠረው ሁኔታ ግራ ቀኙን ሊያመዛዝን ሞከረ ፡፡
የቀኝ ወገን ትክከለኛ፣ ጠንካራ፣ ተገቢ ተብሎ ሲታወቅ ግራው አሳሳች፤ ስንኩልና አማራጭ ሆኖ መታየቱ የእኩልነት መርኽን ጥሷል፡፡ ቀኝ ታማኝ ግራ ከሃዲ ያለው ማነው? ለታሪኩ ሰውነት ቀኝ እጅ አድራጊ ፈጣሪ፣ ግራው ደግሞ ድጋፍ ሰጪ ሆነው ኖረዋል፡፡ታሪኩ ቀኝ እጁን ለመሰረታዊ ጠቀሜታ ስለሚያውል ግራ እጅ ስራፈት ሆኖ ኖሯል፡፡ ትንሽም ልዩ ክብር ያገኘው የታሪኩን የጋብቻ ቀለበት በማሰሩ ብቻ ነበር፡፡ በዚያ የምፅአት ቀን ግን የጋብቻ ቀለበቱ በግራ እጅ ላይ ባለው የቀለበት ጣት አልነበረም፡፡ ብቸኛ ልዩ ክብሩን ያጣው ግራ እጅ ታድያ ብሶተኛ ቢሆን ለምን ይደንቃል፡፡
ሰው በአፈጣጠሩም ቢሆን ግራውና ቀኙ ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ሙሉ ሰውነት በ100 ሚሊዮን ሴሎች የተገነባ ቢሆን ምን ያህሉ በቀኝ ምን ያህሉ በግራ እንደሚገኙ ለመገመት ግን ያዳግታል፡፡
በሰው አፈጣጠር ላይ ልብ ያለበት ስፍራ ወደ ግራ ያመዝናል፡፡ ግራው የልብ ክፍል በመላው ሰውነት ደም ያሰራጫል፤ ቀኙ ደግሞ ከሳምባ ጋር እስትንፋስን ይሰጣል፡፡ ደምም አየርም ለሰውነት እኩል የሚሰጠውን ልብ ግራና ቀኝ ብሎ መክፈል ያዳግታል፡፡ የታሪኩ ልብ ተጨነቀ፡፡ አሁን የግድ ካንዱ መወገን ቢኖርበት ከየትኛው ሊወግን ነው? ከቀኝ ወይስ ከግራ? ልብ በሃሳብ መቆዘሙን ቀጠለ፡፡
ግራ ተሻጋሪ ቀኝ አሻጋሪ፤ ግራ ፍትህ ፈላጊ፤ ቀኝ ምህረት አድራጊ፤ ግራ ጠማማ ቀኝ ቀጥተኛ፤ ግራ ተቀባይ ቀኝ ሰጭ፤ ሆነው ይገለፃሉ፡፡ ልብ ማሰቡን ቀጥሏል፡፡
ግራና ቀኝ ለፖለቲካ አቋም ቢመቹም ለሳይንስና ለሂሳብ ግን ሳይመች የኖረ አወጋገን እንደሆነ ዓለም ያውቀዋል፡፡
ይሄው የግራና ቀኝ ጎን ዝብርቅርቅ ሁኔታ በሰውነት ክፍሎቻችንም ላይ ይታያል፡፡ በእርግጥ ጨጓራና ሐሞት በግራ፣ ጣፊያና ጉበት በቀኝ የሰውነት ክፍል ይገኛሉ፡፡ ከሁለቱ ሳንባዎች በቀኝ ያለው ከግራው ይገዝፋል፡፡ በማንም የሰው ፍጡር ላይ በግራና ቀኝ ያሉ አይኖችና ጆሮዎች አይመሳሰሉም፡፡ ቀኝ እግር ከግራው ይረዝማል፡፡
የሰውነት ክፍሎቻችን በተናጠል አይሰሩም፡፡ በጋራ ግን ተዓምር የሆኑ ተግባራትን በማከናወን ህልውናችን ናቸው፡፡ ሁለቱም ሳንባችን በጋራ ሲሰሩ በቀን እስከ 2 ሚሊዮን ሊትር አየር ወደ አካላችን ያስገባሉ፡፡ ቀኙና ግራው ምን ያህል አየር እንደሚስብ ግን አይታወቅም፡፡ በውስጣችን ያሉት የደም ቧንቧዎች፤ ስሮችና ጅማቶች ቢቀጣጠሉ ርዝማኔያቸው 60ሺ ማይል ይሆናል፡፡ ስንት ማይል በቀኝ ስንቱ በግራ እንደሆነ የለካ የለም፡፡ ዓይኖቻችን ሚሊዮን አይነት ቀለማትን ይለያሉ፡፡ጆሮዎቻችን በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ድምፆችን ይሰማሉ፡፡ የትኛው የበለጠ እንደሚያዳምጥ ግን አይታወቅም፡፡ ባለሁለት ቀዳዳው አፍንጫችን 50ሺ ጠረኖችን ያሸታል፡፡ የሁላችን አንደበት የሆነው ምላሳችን 9ሺ አይነት ጣዕሞችን ያጠጥማል፡፡
ከሰውነት ክፍሎች 21 ያህሉ በቀዶ ጥገና ሊተኩ ይችላሉ፡፡ ያለ ጨጓራ፤ ያለ ልብ ለመኖር ግን አንችልም፡፡ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ግን በከፊልም ባይኖሩም ህይወት ይቀጥላል፡፡ የጉበት 75 በመቶ፤ የአንጀት 80 በመቶ፤ ከኩላሊት አንዱ፤ ከሳንባም አንዱ የጎደለው ሰውነት ይኖራል፡፡ ካልሆነም ደግሞ በቀዶ ጥገና ሊተካ ይችላል፡፡
መላው አካላችን በሚያደርገው ርብርብ በየሰከንዱ 15 ሚሊዮን የደም ሴሎች እያወደመ፣ በየቀኑ 100 ቢሊዮን የቀይ ደም ሴሎችን ያመርታል፡፡ ይህን ለህልውናችን ወሳኝ የሆነውን ግልጋሎት ሌት ተቀን ሳይታክት የሚሰራው ልብ፤ በቀኝም በግራውም ያሉትን አካላቶች ያስተባብራል፡፡
አንጎል በቀኝና ግራ ክፍሎች የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ሳይንስ አረጋግጧል፡፡ አንብቦ መረዳት፤ መፃፍ፤ የሂሳብ ስሌት፤ ማመዛዘን፤ ቋንቋ መናገርና ሳይንስን መገንዘብ የቀኝ አንጎል ሃላፊነት ነው፡፡ አርቆ የሚያስበው፤ ጥበብ የሚዘልቀውና በላቀ አስተሳሰብ የሚሰራው ግራ አንጎል ነበር፡፡ ቀኝ አንጎል የግራ እጅን እንቅስቃሴና ልብን ሲቆጣጠር ግራው ደግሞ የቀኝ እጅን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ያዛል፡፡ ልብ ይህን ሲያስብ በታሪኩ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ግራ አንጎል ቀኝ እጅን አዞ መፈፀሙ ገባውና በማን እንደሚፈርድ ግራ ገባው፡፡
የታሪኩ ልብ በገጠመው ድንገተኛ አደጋ መብሰክሰኩን ቀጥሏል፡፡ ማንም ሰው በገዛ ቀኝ እጁ በመዶሻ አውራ ጣቱን ቢመታ እንዲህ አይነት የክፍፍል ጐራ ሊያጋጥም ይችላል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ጉዳቱ ሲያጋጥም ሁሉም የሰውነት ክፍል ይደነግጣል፡፡ ቀኝ እጅ የያዘውን መዶሻ ጥሎ በስህተት የመታውን የግራ አውራ ጣት አፈፍ አድርጎ ህመሙን ሊያስታግስ ይሞክራል፡፡ ሁለቱም እግሮች ቢሆኑ ጉዳቱ እንደደረሰ ህክምና ለማግኘት ተባብረው ይሯሯጣሉ፡፡ በአላስፈላጊ ንትርክ ግራው እየደማ ሌላው ቀኝ የሰውነት ክፍል አያገባኝም ብሎ ሞትን እንዳማይፈልግ ግልፅ ነው፤ ልዩነትን ከማጥበብ ይባስ ማስፋት ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ራሳችንን በመልካም ጤንነትና እንክብካቤ ከጠበቅን የሰውነት ክፍሎቻችን ለረጅም ጊዜ በማገልገል የሁላችንም እድሜ ይጨምራሉ፡፡
ልብ ይህን ሁሉ ሲያብሰለስል ታሪኩ ከገባበት ሰመመን ሙሉ ለሙሉ አልነቃም፡፡ በመላው ሰውነቱ የተቀጣጠለው እሰጥ አገባም አልተቋጨም ነበር፡፡ ልቦና ሲያስብና ሲረዳ የቆየውን ሁሉ የትኛውም የሰውነት ክፍል ሊገነዘብ አልቻለም፡፡ ግራና ቀኝ የሰውነት ክፍሎች ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው አጥፊው የሚቀጣበት የፍርድ ውሳኔ ያስፈልጋል ብሎ በቁጣ ጫጫታውን ዝም ያሰኘው የግራ አንጎል ክፍል ነበር፡፡ እንዲህ ያለው እሱ ያሰበውን ቀኝ እጅ መፈፀሙ ከታወቀ ጥፋተኛ እንዳይባል ሰግቶ ቢሆንም ይህን ድብቅ ሴራ ያላወቁ ሁሉም የግራ ሰውነት ክፍሎች በሙሉ ድምፅ ደገፉት፡፡ ወዲያውኑ የፍርድ ሂደቱን ማን መዳኘት እንዳለበት ምክር ተያዘ፡፡ የሁላችንም ህልውና የሆነው ማመዛዘኛ ያሉትን ልብን በዳኝነት ሾሙት፡፡
የፍርድ ሂደቱ እጅግ የሚያወዛግብና የሚያከራክር ነበር፡፡ መላው የሰውነት ክፍልም በፍርድ ጉዳዩና በተያያዘ ጉዳዮች ላይ አተካራዎችን ፈጥሮ ለሁለት እንደተከፈለ በመቆየቱ ልብ ለውሳኔ በጣሙን ተቸገረ፡፡ በመጨረሻ ከውሳኔ ላይ ሊደረስ የተቻለው በድምፅ ብልጫ ችሎቱ እንዲበይን ከስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡ በግራ እጅ አውራ ጣት ላይ የመግደል ሙከራ ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰው ቀኝ እጅ፤ ወንጀለኛ መሆኑን ችሎቱ ሲያረጋግጥ ግራ አንጎል ያሰበውን ቀኝ እጅ እንደፈፀመ የሚያውቀው ልብ፤ ገለልተኛ ከተባሉት የችሎቱ አባላት ወሳኟን ድምፅ እንዲሰጥ ተወሰነ፡፡ የፍርድ ውሳኔውን አንቀፅ ጠቅሶ ለመላው ሰውነት የሚያሳውቅበት ጊዜም ደረሰ፡፡ የታሪኩ ቀኝ እጅ በግድያ ሙከራ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ችሎቱ የግራና ቀኝ ክርክሩን ከመዘነ በኋላ ከሰውነት ላይ ተቆርጦ እንዲጣል በሚል የቅጣት ፍርዱን በየነ፡፡ በፍርድ ውሳኔው የረኩት በግራ በኩል የሚገኙ ሁሉም የሰውነት ክፍሎች ደስታቸውን በሆታ ገለፁ፡፡ ቀኞች አዘኑ፡፡ ከመቅፅበትም የፍርድ ውሳኔውን ለመተግበር የታሪኩ ግራ እጅ ጤናማ ጣቶች ተንጠራርተው በአቅራቢያው የሚገኘው ኮመዲኖ ላይ ያለውን ቢላ ለማንሳት ተሽቀዳደሙ፡፡ ይሄኔ ራሱን ስቶ ወለሉ ላይ የተዘረጋው ታሪኩ፤ ከሰመመን ወጥቶ አይኖቹ ቁልጭ ቁልጭ ይሉ ጀመር፡፡

 

Read 3972 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:30