Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 August 2011 13:20

የዕኩሊሌሊትወግ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አራት ሰዎች ነን፡፡ በአንድ ጓደኛችን ቤት ውስጥ ተቀምጠናል””ጫት እየቃምን፡፡የመሸግነው አውቶቡስ ተራ ሲሆን ጊዜው የረመዳን ጾም ወቅት ስለሆነ ገንዘብ ካለ ሃያ አራት ሰአት ጫት መግዛት የሚቻልበት ሰፈር ነው፡፡ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰአት ላይ ሶስተኛውን ዙር ጫት አንዱ ጓደኛችን ይዞ መጣ፡፡
እንደአጋጣሚ ሆኖ የሚወራው ወሬ ስለሞት ነበር፡፡ ሚስቱን ገሎ እራሱን ስለገደለው ሰው ከተወራ በኋላ ነበር የጨዋታው መንፈስ የተቀየረው፡፡ እሱን ተከትሎ ሌላው ጓደኛችን መጠጥ ቤት በተፈጠረ አምባጓሮ ሲደባደብ በጠርሙስ አናቱን ተበርቅሶ ስለሞተው ኮበሌ አወጋን፡፡ ቢታገስና ባይደባደብ ኖሮ አይሞትም ነበር፤ ብዬ ስከራከር ቢታገስም ባይደባደብም መሞቱ አይቀርም ነበር የሚሉት ሁለቱ ጓደኞቼ እሰጥ አገባ ጀመሩ፡፡ ለግማሽ ሰዓት ያህል ተከራከርን፡፡ ባጭሩ የክርክሩ መንፈስ ሰው እራሱን ለአደጋና ለበሽታ ሳያጋልጥ ከኖረ ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል በሚልና የፈለገውን ጥንቃቄ ቢያደርግ ከተጻፈለት ቀን አያመልጥም በሚል ሐሳብ መካከል የተደረገ የሐሳብ ፍጭት ነው፡፡

አንደኛው ጓደኛችን ብቻ ዝም ብሎ ያዳምጥ ነበር፡፡ ይስሐቅ ይባላል፡፡ ወፍራምና ረጅም ነው፡፡ የሽያጭ ሠራተኛ ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍት አንብቧል፡፡ ለብዙ ዘመናት አውሮፓ ውስጥ ኖሯል፡፡ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው እንግሊዝ አገር ውስጥ ነው፡፡ ሲጋራውን እያጤሰ ዝም ብሎ ይመለከተን ነበር፡፡
..እሺ አንተስ ምን ትላለህ.. ስል ጠየቅሁት፡፡ በዕድሜ በዕውቀትና በሕይወት ልምድ ስለሚበልጠን እሱ ያለው እንደሚያስማማን ሁላችንም በውስጣችን አምነናል፡፡ ..ከዚያ በፊት አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ ከዚያ ፍርዱን እራሳችሁ ትፈርዳላችሁ.. አለ፡፡ ሁላችንም የሚለውን ለመስማት ድምጻችንን አጠፋን፡፡ ክፍሉ ጥ እረጭ አለ፡፡ ጊዜው ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከአስር ነበር፡፡
..ደቡብ ለንደን ውስጥ የሚኖር አጐቴ ነበር.. ሲል ጀመረ፡፡ ..ልክ እንደኔው ወፍራም ነበር፡፡ ውፍረት መቸም የዘራችን ነው፡፡ ሲበዛ ተግባቢና ከሰው ጋር ተስማምቶ በሰላም የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ዕድሜው ወደ ስድሳ ይጠጋል፡፡ በጣም የተማረ ከልክ ያለፈ የዊስኪና የሲጋራ ሱሰኛ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ቁጭ ብሎ የሚጠጣው አንሶት መንገድ ላይ ካስፈለገው የሚጠጣበት ከአሉሚንየም የተሠራ የቆርቆሮ የዊስኪ መያዣ ዕቃ ነበረው፡፡ ዊስኪውን በዚያ ቆርቆሮ ላይ ይገለብጥና ቀኑን ሙሉ ሲጠጣ ይውላል፡፡ ይታያችሁ፡፡ በረዶና ሶዳ እንኳን አይጠቀምም፡፡ ደረቅ ዊስኪ ነው እንደ ውሃ የሚጐነጨው፡፡ ታዲያ የመረመረው ዶክተር ባጭር ጊዜ መጠጥና ሲጋራ ካላቆምክ ህይወትህ አደጋ ላይ ነው ይለዋል፡፡ ከመጠን ያለፈ እንቅስቃሴም አታድርግ፡፡ ከባድ የልብ ድካም በሽታ አለብህ ብሎታል፡፡ ታዲያ እንደዚህ አጐቴ ሞት የሚፈራ ሰው እስካሁን አላየሁም፡፡ ሲጋራውን እርግፍ አድርጐ ተወው፡፡ መጠጡን ግን ማቆም አልቻለም፡፡ ከልክ ያለፈ እንቅስቃሴ ላለማድረግ ይጠነቀቅ ነበር፡፡
..አንድ ቀን ጠዋት ስልክ ይደወልለታል፡፡ አንድ ጓደኛው እቤቱ ውስጥ በተፈጠረ የእሳት ቃጠሎ ተለብልቦ ለመሞት እያጣጣረ እንደሆነ ነገሩት፡፡ በፍጥነት ወደተባለው ሆስፒታል ሄደ፡፡ ጓደኛው በፋሻ ተሸፍኖ አልጋ ላይ ተኝቷል፡፡ ምንም አልተረፈም፡፡ ፊቱ የሌላ ፍጡር መስሏል፡፡ አጐቴ ጓደኛው በደቂቃዎች ዕድሜ ውስጥ እንደሚሞት አወቀ፡፡ ቀስ ብሎ ጆሮውን አስጠጋ፡፡ አየሁት አለው ጓደኛው ትንፋሹ ከፍ ዝቅ እያለ፡፡ አጐቴ ጓደኛው የሚቃዥ መሰለው፡፡ እና ሊያረጋጋው ሞከረ፡፡ ..አይዞህ ሀኪሞቹ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ትድናለህ፡፡.. አለው፡፡
..ጓደኛው ግን የተስፋ መቁረጥ ፈገግታ ፈገግ አለ፡፡ ..አልድንም፡፡ ምክንያቱም አይቼዋለሁ.. አለው፡፡
..ማንን ነው ያየኸው?.. ሲል ከሦስታችን መሃል አንደኛው ጓደኛችን ጠየቀ፡፡ ይስሐቅ አንድ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ ሦስታችንም ዓይን ዓይኑን እያየን ነበር፡፡ የጫቱ መንፈስ ይሁን የሚያወራው ወሬ አላውቅም ግን ፍርሃት ብጤ ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ሰአቴን ተመለከትኩ፤ ዘጠኝ ሰዓት ከሩብ ይላል፡፡    
ይስሐቅ ሲጋራውን አንዴ ማግ አድርጐ ሳበና ወሬውን ቀጠለ፡፡ ..አጐቴም የጠየቀው ይህንን ነበር፡፡ ..ማንን ነው ያየኸው.. ሲል ጠየቀው፡፡
ጓደኛው ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ..መስኮቱ ጋ ተደግፌ ሲጋራ ላጤስ ክብሪት ልለኩስ ስል የመስኮቱ መስተዋት ላይ አየሁት፡፡ የራሴው መልክ ነበር፡፡ እኔ እንዳልሆንኩኝ ግን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ጥላው ክብሪቱ ላይ አርፎ ነበር፡፡ ክብሪቱን ለኮስኩ፡፡ ግን. . . ሻይ ልጥድ የከፈትኩትን ጋዝ ረስቼው ነበር፡፡ ድንገት ፈነዳ፡፡.. አለና በረጅሙ አቃሰተ፡፡ ከዚያ በተለበለበ እጁ የአጐቴን ኮት ጨምድዶ ይዞ ወደሱ አስጠጋውና ..ጥላው. . . ጥላው ያረፈበት.. ብሎ ሳይጨርስ ዓይኑ ፈጦ፣ አፉ እንደተከፈተ ደርቆ ቀረ፡፡.. አለ ይስሐቅ ሲጋራውን መተርኮሻው ላይ ደፍጥጦ ሲያበቃ፡፡
..ሞተ?.. አልኩኝ ይስሐቅን አፍጥጬ እያየሁ፡፡
..አዎ ሞተ፡፡..
..ያየው ግን ምን ነበር?..
..እራሱን ነው ያየው፡፡ ግን የገረጣውንና ሬሳ የመሰለ ራሱን ሳይሆን ሌላ ነገር..
..እያልከኝ ያለኸው ሞትን አየው ነው?.. አልኩና ሳቅ አልኩኝ፡፡ እሱ ግን አልሳቀም፡፡ ድርቅና ፍጥጥ ብሎ ተመለከተኝ፡፡ ወዲያው ፈገግታዬ ጠፋና በመላው ውስጤ ፍርሃት ነገሰ፡፡ ሁለቱ ጓደኞቻችንም ዓይናቸውን አፍጥጠው ይስሐቅን ይመለከታሉ፡፡
ይስሐቅ ቀጠለ፡፡ ..አጐቴ ጓደኛው በቀላሉ የሚረበሽና ዘባራቂ ሰው እንዳልሆነ አሳምሮ ያውቃል፡፡ እንዲያውም በጣም የተረጋጋና በምንም ዓይነት አፈ ታሪክና የማይጨበጡ ወሬዎች የማያምን ሰው እንደሆነም ያውቃል፡፡ ከመሞቱ በፊት አጓጉል ቀልድ ሊቀልድ እንደማይቃጣም ግልጽ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የአጐቴ ጓደኛ ቀብር ከተፈመ በኋላ ነገሩ እየተረሳ መጣ፡፡ ነገሩ አልፎ ረጅም ጊዜ ቢቆይም አጐቴ ግን አንድ ነገር አልረሳም፡፡ ጓደኛው ከመሞቱ በፊት ያለውን፡፡ ጥላው፡፡..
..የዚያ የራስህን መልክ ይዞ በሚያንፀባርቅ ነገር ላይ የሚታይህ ሞት ይሁን መልአከ ሞት ጥላ ያረፈበት ነገር የመሞቻህ መንስኤ መሆኑን፡፡ አጐቴ ይህንን አልረሳም፡፡..
..የራስህን መልክ ነው የምታየው.. ሲል አንዱ ጓደኛችን ጠየቀ፡፡
..አዎን ግን አንተ አይደለህም፡፡ ምክንያቱም ያ አንተን የሚመስል ነገር የሞት መንፈስ ያረፈበት ነው፡፡.. አለ ይስሐቅ አንድ ሲጋራ አውጥቶ እየለኮሰ፡፡
ሲጋራውን ማግ አድርጐ ሲስብ ትንሽ ሰከንድ ወሰደ፡፡ በበኩሌ የዚህን ታሪክ መጨረሻ ለማወቅ ብጓጓም ከመጠን በላይ ፈርቻለሁ፡፡ በአራታችን መሃከል ያረፈውም ድባብ ይህ ነበር፡፡ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰአት ከሃያ ላይ እንደዚህ ዓይነት ወሬ ሲወራ ሰምቼ አላውቅም፡፡
..አጐቴ ለረጅም ጊዜ በጥንቃቄ ራሱን እየጠበቀ ሲኖር ቆየ፡፡ እንደነገርኳችሁ እንደሱ ሞትን የሚፈራ ሰው አልተፈጠረም፡፡ አንድ ቀን ምሽት የመኪናው ፍሬን ሸራ ተበላሽቶበት ሊያስጠግን ወደ ጋራጅ ይሄድና ሜካኒኩን አጥቶት ይመለሳል፡፡ መኪናውን ወደ ተከራየው አፓርታማ መኪና ማቆሚያ ስር ያቆምና ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ በእጁ ከሱፐር ማርኬት የገዛው ሦስት ኪሎ ሙዝ ይዞ ነበር፡፡ ገላውን ለመታጠብ ሻወሩን ሲከፍተው ውሃ አልነበረም፡፡ በስጨት ብሎ ለመጠባበቂያ ውሃ ይዞ ከተቀመጠው በርሜል ውሃ ድስት ላይ ሞላና ጋዙ ላይ ጣደው፡፡ አንድ ሙዝ ልጦ በላና ልጣጩን የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ላይ እንደ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ወረወረ፡፡ ነገር ግን ኢላማውን ስቶ ልጣጩ መሬት ላይ አረፈ፡፡ አዲስ የገዛው ሸሚዝ እንዳማረበትና እንዳላመረበት ለማየት ግድግዳው ላይ ወደተሰቀለው መስተዋት ጠጋ ብሎ ተመለከተ፡፡ ከሰውነቱ ጋር ልክክ ብሏል፡፡ አንዱ የሸሚዙ ቁልፍ ግን የተለየ ህብር እንዳለው በመስተዋቱ ውስጥ ተመለከተና ጐንበስ ብሎ ሸሚዙን አየው፡፡ ልክ ነው፡፡ ምንም የተለየ ህብር የለም፡፡ እንደገና ቀና ብሎ መስተዋቱን ተመለከተ፡፡ አሁን አየው፡፡.. አለ ይስሐቅ ሲጋራውን መተርኮሻው ላይ እየደፈጠጠ፡፡
..ሞትን?.. አልኩኝ ድምን የሹክሹክታ ያህል ቀንሼ፡፡ ሁላችንም ፀጥ እረጭ ብለናል፡፡ ይስሐቅ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና ..አዎን ሞትን.. አለኝ፡፡
ከዙርባው ላይ አንድ ዘለላ የጫት እንጨት መዘዘና መቀንጠስ ጀመረ፡፡
..አጐቴ ለረጅም ጊዜ ሲጠነቀቅ ኖሯል፡፡ እራሱንም ሲጠብቅ ግን አሁን መስተዋቱ ላይ ያየው የራሱ ምስል ያበጠና ላብ በላብ የሆነ ፊት ያለው ሲሆን ፊቱ ላይ የፌዝ ፈገግታ ይታይበታል፡፡ አጐቴ በድንጋጤ በርግጐ ወደ ኋላ አፈገፈገና ለመሮጥ ሞከረ፡፡ የዛ መስተዋቱ ላይ ያረፈው ምስል ጥላ የት እንዳረፈ በዓይኑ እየፈለገ በመደናበር ሮጠ፡፡ እግሩ ለመሮጥ አየር ላይ በተነሳበት ቅጽበት ጥላው ያረፈው የሙዙ ልጣጭ ላይ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ እግሩ የሙዙ ልጣጭ ላይ ከማረፍ ውጭ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ጥንቁቁና ሞትን የሚፈራው አጐቴ እንደምንም ብሎ ሚዛኑን ጠበቀና ተፈናጥሮ የሙዝ ልጣጩን ዘለለው፡፡ የሙዙን ልጣጭ ቢረግጠው ኖሮ ተንሸራቶ በጀርባው ይወድቅና አናቱን ከብረት የተሠራው የውሃ መያዣው በርሜል ይመታው ነበር፡፡ የጋዙን ምድጃ ተደግፎ መሬት ላይ ሲቀመጥ ምድጃውን በሃይል ነቅንቆት ነበር፡፡.. አለ ይስሐቅ የቀነጠሰውን ጫት አፉ ውስጥ እየከተተ፡፡
..እና አመለጠ?.. አለ አንዱ ጓደኛችን፡፡
..ለጊዜው አመለጠ፡፡ ግን አምልጦ አላመለጠም፡፡ ቀና ብሎ ሲመለከት የጋዙ ምድጃ ላይ ያስቀመጠው ውሃ የጠጣበት የብረት ኩባያ ላይ ምስሉን እንደገና አየው፡፡ አሁን ግን የፌዝ ፈገግታ ፊቱ ላይ አይታይም ቁጣ እንጂ፡፡ ጥላው ያረፈው ድስቱ ላይ ነበር፡፡ አጐቴ መሬቱ ላይ ተንከባለለና ቦታውን ለቀቀ፡፡ ቅድም ምድጃውን ተደግፎ ሲቀመጥ የነቀነቀው ድስት ሚዛኑን ስቶ ለመውደቅ በቋፍ ላይ ነበር፡፡ ልክ አጐቴ ቦታውን እንደለቀቀ ድስቱ ወድቆ አጐቴ የነበረበት ቦታ ላይ ተገለበጠ፡፡ ሲንተከተክ የነበረው ውሃ ተገልብጦ አጐቴ የነበረበት ቦታ ላይ ተደፋ፡፡ ነገሩ አላማረውም፡፡ ያን ቤት ለቆ መውጣት እንዳለበት ወሰነ፡፡ እየሮጠ በሩን ከፍቶ ወጣ፡፡ መጥፋት አለበት፡፡ የትም ይሁን የትም መራቅ፡፡ ደረጃውን ወርዶ ያቆመውን መኪና አስነስቶ በከባድ ፍጥነት እየነዳ ተፈተለከ፡፡ ትንሽ ርቀት እንደተጓዘ አሁንም አየው፡፡ የመኪናው ስፖኪዮ ላይ፡፡ ጥላው ፍሬኑ ላይ አርፏል፡፡ አጐቴ አሁን ነው የባነነው፡፡ ለካ የመኪናው ፍሬን አይሠራም፡፡ ደጋግሞ ቢረግጠውም የመኪናው ፍጥነት አልቀነስም አለ፡፡ የመኪናውን ማርሽ በፍጥነት ቀያየረና መኪናውን ከመንገዱ ጠርዝ ጋር እያላተመና ጐማውን ከጠርዙ ጋር እያስታከከ መኪናውን አበረደና ዘሎ ከመኪናው ወረደ፡፡ መኪናው ሄዶ ከአንድ ዛፍ ጋር ተጋጨ፡፡ ቁና ቁና እየተነፈሰ መኪናው ወደተጋጨበት ዛፍ አመራ፡፡ በድንጋጤና በድካም ሰውነቱ ዝሎ ተዝለፍልፏል፡፡ ዛፉ ስር ተቀመጠና አረፍ አለ፡፡ ያቺን ከአሉሚንየም የተሠራች የውስኪ መያዣ አውጥቶ ውስኪውን ከተጐነጨ በኋላ ደርቆ ቀረ፡፡ ምክንያቱም ያን ያበጠ ፊት ያለውና ላብ በላብ የሆነውን የራሱን ሞት ያንዣበበት ፊት ቆርቆሮው ላይ ተንባርቆ ታየው፡፡ ጥላው ደረቱ ላይ አርፎ ነበር፡፡.. አለና ሁላችንንም ትኩር ብሎ አየን፡፡ ..ደረቱ ላይ.. አልኩኝ፡፡
..አዎ ደረቱ ላይ፡፡ ጥዋት በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ያጐቴን ሬሳ አገኙት፡፡ የመረመረውም ዶክተር የሞተው በልብ ድካም ነው አለ፡፡.. አለና ሦስታችንንም እየተመለከተ ..ክርክራችሁ ሰው ሞትን ማምለጥ ይችላል ወይስ አይችልም ነበር?.. አለና ጠየቀ፡፡
..አዎ.. አልኩት
..እኔ ምን አውቃለሁ፡፡ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡.. አለና አንድ ዘለላ ጫት መዘዘ፡፡ እኔም አንድ ዘለላ ጫት መዘዝኩኝ፡፡ የሆነ ጥላ እዚያ አካባቢ እንዳላረፈ እርግጠኛ ለመሆን የጐሪጥ እያየሁ ሰአቴን ተመለከትኩኝ፡፡ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ይላል፡፡

 

Read 4481 times Last modified on Thursday, 15 September 2011 07:16