Sunday, 31 July 2011 13:55

አልማዝ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

ወደ አውሮፕላን ማረፍያው የደረሰው በጊዜ ነበር፡፡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በሙሉ አድርጓል፡፡ የደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 892 አውሮፕላን አዲስ አበባ የሚገባው ልክ ከጠዋቱ 4 ከ15 ደቂቃ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በዚያ አውሮፕላን አንዲት ህጻን ልጅ አቅፋ በምታመጣው አሻንጉሊት ውስጥ የተደበቀው ዕቃ ዕድሜ ልኩን ቁጭ ብሎ እንዲበላ የሚያደርገው ሀብት ዋጋ ያለው ነው፡፡ ሰማያዊ ህብር ያለው ሃምሳ ግራም የሚመዝን አልማዝ፡፡

ሰለሞን ቀላል ሰው አይደለም፡፡ ዕድሜው ወደ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ፣ አዳዲስና ውጤታማ የንግድ ሀሳቦችን በማመንጨት አብረውት በሚሰሩት ላይ አድናቆትን በመፍጠር የሚታወቅ ሲበዛ ጮሌ የሆነ እሳት የላሰ ደላላ ነው፡፡ ቀጠን ብሎ ረዘም ያለ፣ ወሬ የሚያነፈንፍ የሚመስል ሾካካ አፍንጫ ያለው፣ ፀጉሩ ወደ ኋላ ገባ ያለ ነው፡፡ አራት ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መናገር ይችላል፡፡ ጓደኞቹ በሙሉ የናጠጡ ሀብታሞች ናቸው፡፡ የግንኙነት መረቡ በጣም የሰፋ ሲሆን የቡና ነጋዴዎች፣ የጫት ቱጃሮች፣ የጅምላ ንግድ አከፋፋዮች፣ የሰራተኛና አሰሪ አገናኝ ወኪሎች ኪሱ ውስጥ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ በመገረም፣ በአድናቆትና በጥላቻ ነው የሚመለከቱት፡፡ ምክንያቱም እነሱ ሊያዩት ያልቻሉትን የቢዝነስ ሐሳብ በቀላሉ እያመነጨ ከመዳፋቸው ውስጥ ገንዘብ መንጭቆ ስለሚወስድ ነው፡፡ እንደውም አንዱ ጓደኛው ..ለምን የሐሳብ መሸጫ ቢሮ አትከፍትም.. እስኪለው ድረስ አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨት ተወዳዳሪ የለውም፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ ግን እንደሚመኘው ሃብታም መሆን አልቻለም፡፡ አብረውት የሚውሉት ቱጃር ጓደኞቹም ሲበሉ ከማብላት፣ ሲጠጡ ከማጠጣትና አልፎ አልፎ ለእጁ ከሚሰጡት ገንዘብ ያለፈ ነገር ሊያደርጉለት አልቻሉም፡፡ በድለላውም ቢሆን እንደሱ አነጋገር እስካሁን አሪፍ ዝግ ዘግቶ አያውቅም፡፡ ገንዘብ አጥቶ ባያውቅም ህይወቱን ከመሰረቱ የሚለውጥ ሀብት ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡  
አሁን ግን ይሄ ሁሉ ሊቀየር ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖር የነበረው ሚስተር ኮፊ የተባለው በእናቱ ጋናዊ፣ በአባቱ ደቡብ አፍሪካዊ የሆነው ጊዜ ያነሳው ቱጃር ህይወቱን ሊቀይርለት ነው፡፡ ሚስተር ኮፊ ከወላጅ አባቱ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ያለው የአልማዝ መሸጫ ሱቅ የወረሰ የናጠጠ ቱጃር ነው፡፡ ከሁለት አመታት በፊት ግን አዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ውስጥ ተራ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ነበር፡፡ የተዋወቁትም ሚስተር ኮፊ የሚኖርበትን ቤት ደልሎ ያገኘው ሰለሞን ስለሆነ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የቅርብ ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ በርካታ ምሽቶችን አብረው ሲጠጡ አሳልፈዋል፡፡ ግዙፉና ውስጥ ረጅሙ ሚስተር ኮፊ ከሚወዷቸው ነገሮች ዘወትር ከአፉ የማይለየው ፒፓውን፣ በርበሬ የበዛበት የዶሮ ወጥና ትላልቅ ጡቶች ያላት የሐበሻ ሴት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ሰለሞን ታድያ መዓዛ የተባለችውንና በአካባቢው በጡቷ ትልቅነት ምክንያት ..ሱቅ በደረቴ.. በመባል የምትታወቀውን የአክስቱን ልጅ ያስተዋወቀው የዛሬ አመት ገደማ ነበር፡፡ ሚስተር ኮፊ ከመአዛ ጋር በፍቅር ከነፈ፡፡ በመጨረሻም አገባት፡፡ ለዚህ ውለታውም ሰለሞን በሚስተር ኮፊ አይን እንደ ወንድም የሚታይ የልብ ጓደኛ ሆነ፡፡  የዛሬ ሶስት ወር የሚስተር ኮፊ ቱጃር አባት በጠና ታመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጠራ በሁለት እጁ የሰለሞንን ትከሻ ይዞ በፍም እንደማይረሳው ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ይኸው እንዳለውም አልረሳውም፡፡ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያለው አልማዝ ልኮለታል፡፡
መታወቂያውን አሳይቶ ወደ ተርሚናሉ ገባ፡፡ የአውሮፕላን ማረፍያው ተርሚናል በሰው ብዛት ተጨናንቋል፡፡ አንዱን የመስተንግዶ ሰራተኛ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 892 ፣ አዲስ አበባ ደርሶ እንደሆነ ሲጠይቀው፣ ከገባ አምስት ደቂቃ እንደአለፈው ነገረው፡፡ የለበሰው አመድማ ካፖርት እስኪውለበለብ ድረስ እየሮጠ ወደ መንገደኞች መግቢያ በር አመራ፡፡ እንደደረሰም የተሰለፉ ሰዎች የጉዞ ሰነዶቻቸውን ለባለስልጣኖች እያሳዩ ነበር፡፡ ልጅቷንም ከሩቁ ለያት፡፡ አንዲት ፀጉረ ረጅም፣ የሙሽራ ቀሚስ የለበሰች፣ አሻንጉሊት የያዘች የስምንት አመት ከሐበሻ እናትዋ ጋር የተሰለፈች ሀበሻ ሴት ልጅ፡፡ ሰለሞን እፎይ አለ፡፡ እስዋ በያዘችው አሻንጉሊት ውስጥ ሃምሳ ግራም የሚመዝን ሰማያዊ ህብር ያለው እጅግ በጣም ውድ የሆነ አልማዝ አለ፡፡  
በራሱ የብልጠት ሐሳብ እየተገረመ ልጅቷን በደንብ ተመለከተ፡፡ እናትዋንም በጥንቃቄ አያት፡፡ ነገረኛ ብጤ ትመስላለች፡፡ በሰከንድ አርባ ቃላት የምትናገር አይነት፡፡ አሁን በሷዋ ቤት ልጅዋ ከአንድ ደቡብ አፍሪካዊ የተሰጣት የአሻንጉሊት ስጦታ ተራ የመጫወቻ አሻንጉሊት ብቻ መስሏት ይሆናል፡፡ ይህቺን ብልጠት የፈጠረው ሰለሞን ነበር፡፡
አልማዙን እንደሚልክለት፣ ነገር ግን እንዴት እንደሚልክለት ግራ የገባው ሚስተር ኮፊ ሲያማክረው የፈጠረው ሃሳብ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ህፃናትን ማንም ውድ ዕቃ አስርጐ በማስገባት ሊጠረጥራቸው አይችልም፡፡ ሌላው ደግሞ የህፃናት የመጫወቻ አሻንጉሊቶች፣ ልክ እንደ ነጭ እርግብ የንፁህነትና የየዋህነት ምልክት ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ አሻንጉሊቱ በስጦታ ለራሷ ተሰጣት እንጂ ለሰለሞን አድርሺ ተብሎ አልተሰጣትም፡፡ እሱ ነው በራሱ መንገድና ዘዴ አሻንጉሊቱን እጁ ውስጥ ማስገባት የሚጠበቅበት፡፡ ይህ ደግሞ እሱን ከማንኛውም በፖሊስ የመጠርጠርና የመያዝ አደጋ የሚከላከል ዘዴ ነው፡፡ መቼም ይሄን ያህል ውድ ዋጋ ያለው የከበረ ድንጋይ ወደ ሐገር ውስጥ ሲገባ ያለው ጣጣ ብዙ ነው፡፡ በህጋዊ መንገድ መግባት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጥያቄ ጭራሽ ባይነሳ እንኳን አድርስ ተብሎ የሚላከው ሰው በምን ይታመናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማን አይኑ እያየ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያለው ዕቃ አሳልፎ ይሰጣል? ስለዚህ አልማዙን አድራሹ እራሱ ሲያውቅ ወደ አዲስ አበባ እንዲያደርስ ማድረግና ምንም በማይጠረጠር ሁኔታ እጅ ውስጥ ማስገባት አማራጭ የሌለው ዘዴ ነበር፡፡ ቢነቃም ማን ማንን ያገኛል? አዲስ አበባ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ለዚህ ነበር ሰለሞን አልማዙን አንድ አሻንጉሊት ውስጥ ደብቆ ለአንድ ህፃን የመስጠት ሃሳብ ያመጣው፡፡ ከዚያ አሻንጉሊቱን በጣም የወደደው መስሎ በብዙ ገንዘብ ይገዛዋል፡፡ ወይም በሌላ የተሻለ አሻንጉሊት ይቀይረዋል፡፡ መቼም ማንም ቢሆን ይሄን ሃሳብ የሚቃወም የለም ግን እንደው የተረገመ ጠማማ ሰው እንኳን አጋጥሞት በሁለቱ መንገድ እምቢ ቢል በሐይል ነጥቆ ወይም ሰርቆ ይፈረጥጣል፡፡ ማንም ሰው አሻንጉሊት ተሰረቅኩኝ ብሎ እንደጅል ከኋላው አይሮጥም፡፡ ወይም ለፖሊስ አያመለክትም፡፡
ከመንገደኞች መግቢያ ፊት ለፊት ካለ የእንግዶች መቀመጫ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ አንዲት ወፍራም ድብዬ ሴትዮ አጠገቡ አለች፡፡ ከጥጥ የተሠራ ወፍራም ቡናማ የድብ አሻንጉሊት ይዛለች፡፡ ከመንገደኞቹ አንድ ሰው እንደምትጠብቅ ጠርጥሯል፡፡ ይህች ሴት የያዘችውን አሻንጉሊት ቢያገኝ፣ ያለ ምንም ጥርጥር ከዚያች የሱን አልማዝ ያለበትን አሻንጉሊት ከያዘች ልጅ ጋር ሊቀያየር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ዱብዬ ሴትዮ የያዘችው አሻንጉሊት በጣም ውድና የሚስብ፣ ህፃናት የሚወዱት አይነት ሲሆን አልማዙ ያለበት አሻንጉሊት ግን በዋጋውም ረከስ ያለ፣ ብዙ ዓይን የማይስብ ተራ አሻንጉሊት ስለሆነ ነው፡፡ወሬ ለመፍጠር ሞከረ፡፡ ሴትዮዋ ተግባቢ ተጫዋችና ቅን ሴት ናት፡፡ ምን እያደረገች እንደሆነ ሲጠይቃት፣ ልጇን እየጠበቀች እንደሆነ ነገረችው፡፡ ከዚያ ድርቅ ብሎ አሻንጉሊቱን ትሸጥለት እንደሆነ ጠየቃት፡፡ ሴትዮዋ በመገረም አየችው፡፡
..የልጄ የልደት በአሉ ዛሬ ነው፡፡ ልክ የዚህ ዓይነት አሻንጉሊት መርጦ ገዝቼለት ነበር፡፡ በታክሲ ስመጣ ታክሲ ውስጥ ረሳሁትና ጠፋ፡፡ ልጄ ምን ያህል ልቡ እንደሚሰበር ይታይሽ.. አለ እየተቅለሰለሰ፡፡
ሴትዮዋ በሀዘኔታ ከንፈሯን መጠጠች፡፡ ..ግን. . ... ብላ ንግግርዋን ስትጀምር ..ስምንት መቶ ብር እከፍላለሁ፡፡.. አለ፡፡ የብሩ መጠን አጓጉቷትም ይሁን በሌላ አይኖችዋ ፈጠጡ፡፡ ሰለሞን አሻንጉሊቱን ለመስጠት እያወላወለች መሆኑን ተረዳ፡፡ እግረ መንገዱን አልማዙ ያለበትን አሻንጉሊት የያዘችውን ህፃን አሻግሮ ተመለከተ፡፡ ከእናቷ ጋር ተሰልፋለች፡፡ እናቷ የጉዞ ሰነዶቿን ለማሳየት ተራዋ እንደደረሰ አስተዋለ፡፡ ..እሺ ምን አሰብሽ?.. አላት ሴትዮዋን፡፡
..ግን ችግሩ ምን መሰለህ. . ... ብላ ሳትጨርስ ..ይገርምሻል ልጄን የማሳድገው ያለ እናት ነው፡፡ እናቱ የዛሬ ዓመት በመኪና አደጋ ህይወትዋ አልፏል.. አለና ፊቱን በሀዘን አኮማተረ፡፡
አሁን ሴትዮዋ አልቻለችም፡፡ ተሸነፈች፡፡ በሀዘን ከንፈርዋን መጠጠችና አሻንጉሊቱን ሰጠችው፡፡ እያመሰገነ ስምንት መቶ ብር አውጥቶ ሲሰጣት ሁለት መቶ ብር ብቻ ይበቃኛል ብላ ቀሪውን መለሰችለት፡፡ ወደ መንገደኞች ፊቱን ሲያዞር እናትና ልጅ ተያይዘው የጉምሩክ ሠራተኞችን አልፈው በበሩ ሲወጡ ተመለከተ፡፡ ሴትዮዋን ተሰናብቶ ተነሳና ቀስ ብሎ ተከተላቸው፡፡ እናትየዋ ሻንጣዋን እየጐተተች ባንድ እጇ ልጇን ይዛለች፡፡ ልጅቷ ደግሞ አሻንጉሊቷን አቅፋ አብራት ትራመዳለች፡፡ ከእናትየዋ አጠገብ ደርሶ እየተራመደ ..ላግዝሽ?.. አላት፡፡
በለስ ቀናው፡፡ ልጅቷ ሰለሞን የያዘውን ትልቅ የሚያምር የድብ አሻንጉሊት ስታይ በጉጉት እየተናጠች የእናቷን እጅ እየነቀነቀች ..ካልገዛሽልኝ.. ብላ መወትወት ጀመረች፡፡ ሰለሞን እናቷን ለማገዝ ሻንጣዋን ይጐትታል፡፡ ሴትዮዋ ልጇን ከተቆጣች በኋላ ሰለሞንን በእፍረት እያየች ..ልጆች ሁሉም ነገር የሚሸጥ ይመስላቸዋል.. አለች፡፡ ልጅቷ ግን ማልቀስ ጀመረች፡፡
..ግድ የለም፡፡ በጣም ስለወደደችው ልሰጣት እችላለሁ፡፡ ለልጄ የልደት በዓል የገዛሁት ስጦታ ነበር፡፡ አሁን ግን እሷ የያዘችውን አሻንጉሊት ልሰጠው እችላለሁ . . . ከቀየረችልኝ.. አለ ለልጅቷ ያዘነ መስሎ፡፡
..እውነት?.. አለች ሴትዮዋ፡፡ ..በእውነት በጣም ጥሩ ሰው ነህ፡፡..
..በይ አንቺ አምጪ . . . እሱን አመሰግናለሁ በይ.. አለች እናትየዋ፤ ከሰለሞን የተቀበለችውን የድብ አሻንጉሊት ለልጅቷ እየሰጠችና ትንሹን አሻንጉሊት ከልጅዋ XytqblC””ሰለሞን የሚሆነውን ማመን አልቻለም፡፡ የሚፈልገውን አሻንጉሊት እጁ አስገባ፡፡ ..መልካም ጊዜ.. አለችውና ተለየችው፡፡ መታገስ አልቻለም፡፡ በፍጥነት ወደ መዳጃ ቤት አመራና ገብቶ በሩን ቆለፈው፡፡ አሁን ሥራው አክትሟል፡፡ እሱም በፍጥነት ተሰውሯል፡፡ አዲስ አበባ እንደሆነ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ማን ማንን ፈልጐ ያገኛል!
መዳጃ ቤት ውስጥ ሆኖ ያቺን ከፕላስቲክ የተሠራች ምስኪን አሻንጉሊት እንደ ዶሮ ለመገነጣጠል ደቂቃ አልፈጀበትም፡፡ ያገኘው ግን ሃምሳ ግራም የሚመዝን የከበረ ድንጋይ ሳይሆን ኤቨርሬዲ የሚል ጽሑፍ ያለበት ባትሪ ድንጋይ ነው፡፡ ቀዝቃዛ ላብ በጀርባው እየፈሰሰ እንደገና ያንን አሻንጉሊት ብትንትኑ እስኪወጣ ድረስ ፈተሸው፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሽንት ቤቱ እየሮጠ ወጣና መጀመሪያ እነሱን ወዳገኘበት ቦታ ሮጠ፡፡ ዱብዬዋ ሴትዮ ቆማ ወደ መንገደኞች መግቢያ ስትመለከት አገኛት፡፡ ቁና ቁና ይተነፍሳል፡፡ በዓይኖቹ እናትና ልጅን እየፈለገ እንደሆነ ወፍራዋ ሴትዮ እንዳታውቅበት ፈገግ አለ፡፡ ..አሁንም እዚህ ነሽ?.. አለ መሮጡን እንዳታውቅበት ለመረጋጋት እየሞከረ፡፡
..ምን ላድርግ ልጄን እየጠበቅኩኝ ነዋ፡፡ ፓስፖርትም ላይ ስህተት አለ ብለው እኔን አሰልፈው እሷን አቆይተዋት ነበር፡፡ አሁን መጣች፡፡.. አለች ሴትዮዋ ፈገግ ብላ ወደ መንገደኞች መግቢያ በር እያየች፡፡ ሰለሞን ዞር ብሎ ሲያይ የስምንት ዓመት ልጅ የምትሆን ወደ ሴትዮዋ ስትመጣ ተመለከተ፡፡
..አንቺም ከዚያው ነው የመጣሽው?.. ድም ተደናቀፈ፡፡
..ሁለችንም ከደቡብ አፍሪካ ነው የመጣነው . . . ከጆሃንስበርግ..
..ታዲያ የሸጥሽልኝ አሻንጉሊት. . ... ብሎ ሳይጨርስ ..ሽሽ. . . እንዳትሰማ፡፡ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ነው ዛሬ ጠዋት ከዚያ ስንነሳ በስጦታ የሰጣት፡፡ ሐበሻ ሚስት አለችው፡፡ በጣም ነው ሀበሻ የሚወደው.. አለችና ወደሷ ሮጣ የመጣችውን ልጇን አቀፈቻት፡፡ ሰለሞን ዛሬ ጠዋት ሚስተር ኮፊ በስልክ ያለውን አስታወሰ፡፡ ..አልማዙን ከእናትዋ ጋር የምትመጣ በግምት የስምንት ዓመት ህፃን የምትሆን የያዘችው አሻንጉሊት ውስጥ ልኬዋለሁ፡፡..
አልማዙ የነበረበትን ትልቁንና ውዱን አሻንጉሊት በማይረባውና ባዶ በነበረው አሻንጉሊት ቀይሮታል፡፡ እንደ ዕብድ እየሮጠ አሻንጉሊቱን የቀየራቸውን እናትና ልጅ ለማግኘት ተቅበዘበዘ፡፡ በየጥጋጥጉ በመውጫ መግቢያው፤ ውስጥም፤ ውጭም የትም አልቀረውም፡፡
ምን ዋጋ አለው፡፡ አዲስ አበባ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ማን ማንን ያገኛል!

 

Read 3826 times Last modified on Sunday, 31 July 2011 14:00