Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 14:14

የሚውኒክ ኦሎምፒክና

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር

ዛሬ የኦሳማ ቢን ላደን መላ ታሪክ የሚተረከው ነበር እየተባለ ብቻ ነው፡፡ የእርሱ መገደል የአለም አቀፉ ፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ፊታውራሪ ለሆነችው አሜሪካና አጋሮቿ የተወሰነ እፎይታ ማስገኘቱ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው፡፡ ግን ደግሞ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ሌላም አንድ መሠረታዊና እውነት የሆነ ጉዳይም አለ፡፡ ኦሳማ ቢን ላደን ቢገደልም የመሠረተው አለም አቀፍ የሽብር ድርጅት አልቃኢዳ እንደሱ ጨርሶ አልሞተም፡፡ ይልቁንስ አደረጃጀቱን ለአፀፋ ጥቃት እንዳይጋለጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀያየር አባላቶቹንና የእንቅስቃሴ አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ ከአሜሪካ እስከ ካናዳ፣ ከአርጀንቲና እስከ ሰሎሞን ደሴቶች፣ ከስፔን እስከ ሶርያ፣ ከየመን እስከ ሳኡዲት አረብያ፣ ከአልጀሪያ እስከ ሊቢያ፣ ከኒጀር እስከ ቲምቡክቱ ማሊ፣ ከሞቃዲሾ ሶማሊያ እስከ ባሌ ኢትዮጵያ ድረስ በተለያየ ስያሜ የተዋቀረ የአልቃኢዳ የሽብርተኛ ክንፍና ህዋስ ያልተንሠራፋበት የአለማችን ሀገር አይገኝም፡፡ ይህ ጉዳይ የሚያረጋግጥልን ደግሞ አንድ እውነት ነው፡፡ የአለም አቀፍ ሽብር ስጋትና አደጋ አሁንም ድረስ በላያችን በማንዣበብ ላይ ያለ መሆኑን፡፡

አልቃኢዳም ሆነ ሌሎች አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች በሚሰነዝሩት የተለያዩ የሽብር ጥቃቶች ዋነኛ አላማቸው በተቻላቸው መጠን የጥቃታቸው ኢላማ የሆኑትን ሀገራት በእጅጉ ሊያሳምምና ሊጐዳ የሚችል መጠነ ሠፊ ቁሳዊና ሰብአዊ አደጋ ማድረስ ነው፡፡

እንዲህ ያለ ሰፊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር ደግሞ የኦሎምፒክ ውድድርና ሌሎች መሰል ትላልቅ አለማቀፋዊ ዝግጅቶች ከሁሉም የተሻሉና የተመረጡ ናቸው፡፡ ትልልቅ አለማቀፋዊ ዝግጅቶችን ለማስተናገድ ሃላፊነት የወሰዱ ሀገራት ትልቁ ጭንቀትም ይሄው አለምአቀፍ ሽብርና ሽብሩን ለመከላከል የሚደረገው ሠፊና እጅግ ውስብስብ ስራ ነው፡፡

ለአሜሪካ በማንኛውም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የፀጥታ ዘርፍ መቼም ቢሆን ለአፍታ እንኳ ከጐኗ ጠፍታ የማታውቅ የልብ ወዳጅና አጋር ሀገር ፈልጉ ብትባሉ፣ እስከ እድሜአችሁ ፍፃሜ ድረስ እንኳ ብትባዝኑ ከእንግሊዝ የበለጠ ሀገር በዚህ አለም ላይ ፈጽሞ ልታገኙ አትችሉም፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ነባራዊ ሁኔታ መሠረት፤ እንግሊዝን የአሜሪካ ወዳጅና ተባባሪ ሀገር ናት በሚል ብቻ ማለፉ አይቻልም፡፡ እንግሊዝ ለአሜሪካ ከወዳጅና አጋርም በላይ ናት፡፡

በዋይት ሀውስ ቤተመንግስት ውስጥ ጉንፋን ቢገባ፣ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ወይም የቅርብ ረዳቶቻቸው ቀድመው አፍንጫቸውን የሚያሹትና የሚያስነጥሱት ቢሮአቸው በለንደን የዶውኒንግ ቁጥር አስር ጐዳና ላይ የሚገኘው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ናቸው፡፡

አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች ቁጥር አንድ ሠይጣን ከሚሏት አሜሪካ ቀጥለው ዋነኛ ጠላት አድርገው በመቁጠር፣ እንግሊዝን የጥቃታቸው ዋና ኢላማ ያደረጉበት አንዱ ምክንያትም ይሄው ነው፡፡

ነገ ፍፃሜውን የሚያገኘውን ሠላሳ አንደኛውን የለንደን ኦሎምፒያድ ያዘጋጁት እንግሊዛውያን፤ እውነቱን እንዲህ ነው ብለው ገልጠው አይናገሩት ይሆናል እንጂ የለንደን ከተማ ኦሎምፒኩን እንድታዘጋጅ ከተመረጠችበት ቀን ጀምሮ ታላቅ ራስ ምታት የፈጠረባቸውና ከጠቅላላ ዝግጅቱ ይልቅ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባቸው የነበረው የአለም አቀፍ ሽብርና የፀጥታ አጠባበቅ ስራው ነበር፡፡ የእንግሊዝ የመከላከያ ሚኒስቴር በተለያዩ የመወዳደሪያ ቦታዎች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችና የባቡር ጣቢያዎች እንዲሁም በተለያዩ የተመረጡ አካባቢዎች ላይ ሚሳይል ለመትከል የተገደደውም ከዚህ የአለም አቀፍ ሽብርና ፀጥታ ጥበቃ ጭንቀቱ በመነሳት ነበር፡፡

አብዛኞቹ የለንደን ከተማ ነዋሪዎች ግን በኦሎምፒክ ውድድሩ ወቅት፣ የአለም አቀፉ ሽብርተኞች ኢላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢረዱም፣ በከተማው የተለያዩ ቦታዎች እንደ ጉድ በተተከሉት ሚሳይሎች ክፉኛ ተሸብረው ነበር፡፡ እናም “ዘውድ መድፋት እኮ የራስ ምታት በሽታን አያድንም” የሚለውን የኔዘርላንዳውያንን አባባል በመጥቀስ፣ የከተማቸውን ከንቲባና የኦሎምፒኩን አዘጋጆች፣ ሚሳይሎቹ ከተተከሉበት እንዲነቀሉላቸው ከፍ ያለ ስሞታ በማቅረብ አስቸገሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ቅልብጭ ያለች ቀጭን ትዕዛዝ ደግሞ “ይህ ታላቅ ድግሳችን ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንኳ ትልቅ አደጋ ይቅርና የትራፊክ አደጋም ቢሆን እንዲደርስ በጭራሽ አያስፈልግም፡፡ ከተማችን ለንደን የምትፎካከረው ከቻይናዋ ቤይጂንግ ከተማ  እንጂ ከጀርመኗ ሚውኒክ ጋር አይደለም፡፡ እኔም ብሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየርን መሆን አልፈልግም” የሚል ነበር፡፡

የስኮትላንድን፣ የዌልስንና የሰሜን አየርላንድ ግዛቶችን በማጣመር ታላቋ ብሪታንያ እየተባለች በግዙፍ ስም በምትጠራው በምድረ እንግሊዝ ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በላይ ስልጣን የጨበጠ ሌላ ማንም ሰው የለም፡፡ ማንም እንግሊዛዊ የእኒህን ሰው ህጋዊ ትዕዛዝ አልቀበልም ብሎ ማለፍ አይችልም፡፡

የፀጥታና የደህንነት ጥበቃን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ትዕዛዝ አንድ ብቻ ነው፡፡ በእንግሊዝ የደህንነትና የፀጥታ ጥበቃ ሠራተኞችና በኦሎምፒኩ አዘጋጆች ላይ የወደቀባቸውና ቸል ብለው ማለፍ የማይችሉት ትዕዛዝ ግን ሁለት ነበር፡፡ የመሪያቸው የዴቪድ ካሜሮንና የህዝባቸው፡፡ እናም ነገርየውን በደንብ ማሰብና ደንበኛ ውሳኔ መወሰን ነበረባቸው፡፡

በመጨረሻም የእንግሊዝ የመከላከያ ሚኒስቴር የተወሰኑትን ሚሳይሎች በማንሳት የህዝቡን ስሞታ መቀበሉን አረጋገጠ፡፡ በተለምዶ MI5 MI6 እየተባሉ የሚጠሩት የእንግሊዝ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የደህንነት ጥበቃ መስሪያ ቤቶች ግን ከተፎ አባሎቻቸውን ከነሙሉ ትጥቃቸው የሲቪል ልብስ አልብሰው፣ በተለያዩ ቦታዎችና በተመልካቹ መካከል በምስጢር በማሠማራት፣ ከተማቸው ለንደን እንደ ሚውኒክ እንዳትሆን አይናቸውን ሳይከድኑ፣ አዕምሮአቸውንና እጆቻቸውንም ለአፍታ ሳያዝሉ፣ ቀኑን ከሌቱ ሳይለዩ በፀጥታና ደህንነት ጥበቃ ስራቸው ላይ ተሠማሩ፡፡

የደህንነትና የፀጥታ ሠራተኞቹ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ የሩብ ፍፃሜ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች ከመካሄዳቸው ቀደም ብሎ የደረሳቸው መረጃ ግን ልባቸውን በድጋጤ ሊያቆመው ደርሶ ነበር፡፡ የዌምብሌይ ስታዲየም በር ቁልፍ ጠፋ! ሁሉንም በድንጋጤ ክው ያደረገ መጥፎ ዜና፡፡ የስታዲየሙ ቁልፎች እንዴት ሊጠፉ ቻሉ? ማን ወሰዳቸው? እንዴት ወሰዳቸው? ለምን ወሰዳቸው? የጥያቄ መአት ተግተለተለ፡፡

ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ የጨዋታዎቹ መካሄድና አለመካሄድ አልነበረም፡፡ የፀጥታ ጥበቃው ጉዳይ እንጂ፡፡

“ከተማችን ለንደን ሚውኒክን ልትሆን ይሆን?” ሁሉም በስጋት ተወጠረ፡፡ በዚህ ውጥረት ላይ ሁሉም ያሠላስል የነበረው “ትክክል በሆንክ ሰአት አንተንና ስራህን ማንም ዞር ብሎ አያስታውሳችሁም፡፡ በተሳሳትክ ጊዜ ግን ማንም ቢሆን አይረሳችሁም” የሚለውን የአይሪሾችን አባባል ነበር፡

በመጨረሻ ግን የስታዲየሙ ቁልፎች ጠፉ በተባለበት ሁኔታ ተገኙ ተባለ፡፡ ይኼኔ ለሁሉም እፎይታ ሆነ፡፡ የጀርመኗን ከተማ ሚውኒክን የመሆን የአደጋ ስጋትም የተገፈፈ መሰለ፡፡

አሁን ሁለት ጥያቄዎችን እንጠይቅ፡፡ ለመሆኑ በ1972 ዓ.ም በሚውኒክ ከተማ በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ምን የተፈጠረ ነገር ነበር? ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንስ ቢሆኑ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር መሆን አልፈልግም ያሉት ጐልዳ ሜየር ምን ቢያደርጉ ነው? የአለማችን የታሪክ መፃህፍት ጥቂት ገጾች ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ከዚህ የሚከተለውን መልሶ ይሰጡናል፡፡

አለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ መካከለኛው ምስራቅ ያለ ብጥብጥና ጦርነት ተለይቶት የማያውቅ አካባቢ በአለማችን ተፈልጐ መገኘቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ራቅ ያለውን የመጽሀፍ ቅዱሱን ታሪክ ብንተወው፣ እስራኤል እንደ አንድ ነፃና ሉአላዊ ሀገርነት ከቆመችበት ከ1948 ዓ.ም ወዲህ ያለውን የቅርብ ዘመን ብንወስድ እንኳ፣ ተደጋጋሚና ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የተካሄዱት በዚህ የአለማችን ክፍል ብቻ ነው፡፡

በዚህ አካባቢ ከሚኖሩት ሀገራት ውስጥም ከፍልስጤማውያን ጋር ባላት ጥልና ቁርሾ የተነሳ ጐረቤቶቿ አይንሽን ላፈር የሚሏትና ሁሌም ሊያጠፏት የሚዝቱባት ሀገር እስራኤል ብቻ ናት፡፡ በዚህ የተነሳ የእስራኤልና የእስራኤላውያን ኑሮ የቆቅ ኑሮ ነው፡፡ ለእስራኤላውያን በአንድ እጅ ዶማ፣ በሌላኛው ደግሞ ጠመንጃ መያዝ በምርጫ የሚደረግ ሳይሆን ሌላ አማራጭ የሌለው የህልውና ግዴታ ነው፡፡

ከ1948 ዓ.ም በፊት የእስራኤላውያን ታላቁ ህልም የራሳቸው የሆነች ሀገር መመስረት ነበር፡፡ ከ1948 ዓ.ም በኋላ ግን የቀን የሌሊት ምኞታቸው ሠላምና ሰላም ብቻ ነበር፡፡ የድፍን አለም ህዝብ፤ ሴት ልጅ የሀገር መሪ ሆና ለመጀመሪያ ጊዜ ያየው በ1969 ዓ.ም እስራኤላውያን በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በሌቪ ኤሽኮል ምትክ ወይዘሮ ጐልዳ ሜየርን ጠቅላይ ሚኒስትራቸው አድርገው ከመረጧቸው በኋላ ነበር፡፡ ያኔ በጐልዳ ሜየር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ምድረ እስራኤላዊ ወደር በሌለው ደስታና ተስፋ ተሞልተው ነበር፡፡ እንዲያ የሆኑት ደግሞ  ያለነገር አልነበረም፡፡

ወይዘሮዋ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በሠሩባቸው አስር አመታት ጊዜ ውስጥ ከማንኛውም የእስራኤል መሪና ዲፕሎማት በበለጠ ሁኔታ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው በርካታ ወዳጅ ሀገራትና ወዳጅ ህዝቦችን አስገኝተውላቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር እናት ብቻ አልነበሩም፡፡ በርካታ የልጅ ልጆቻቸውን በተለየ ፍቅርና እንክብካቤ ያሳደጉ አያትም ጭምር እንጂ፡፡ እናትና አያት የሆነች ሴት ደግሞ የቅድሚያ አጀንዳዋ ሰላም ነው፡፡

የጠመንጃውን ቃታ ከሚስቡት ሠዎች ውስጥም የመጨረሻዋ ናት ተብሎም ይገመታል፡፡ ስለዚህ መላው እስራኤላውያን አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር የናፈቁትን ሠላም ያስገኙልናል ብለው ተስፋቸውን ጥለውባቸው ነበር፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ አረቦች ሞልቶ የተረፈ የስነ ቃል ሀብት አላቸው፡፡ ከዚህ ድንቅ የስነ ቃል አባባል ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ “በአላህ ተማመን፡፡

ግመልህን ግን በደንብ እሰር” ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር ይህንን የአረቦች አባባል መረዳት ብቻ ሳይሆን በተግባር መተርጐምም ችለውበት ነበር፡፡

እናትነትና አያትነታቸው ሁልጊዜም ለሠላም ቅድሚያ እንዲሠጡ ቢያደርጋቸውም፣ ደመኛ ብዙ የሆነችውን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለመምራት የተሸከሙት ሀላፊነት ግን በእናትነትና በአያትነት ልባቸው ሁሌም የሚወጡት ሀላፊነት አልነበረም፡፡

እናም በአምላካቸውና በሰላም መተማመናቸውን ሳያጓድሉ ግመሎቻቸውን ግን በጋጣ ገልባጮች እንዳይነዱባቸው በሚገባ አስረዋቸው ነበር፡፡

1972 ዓ.ም የኦሎምፒክ ውድድር አመት መሆኑን እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ እስራኤላውያንም ተገንዝበውት ነበር፡፡ አመቱ ሲጋመስም ውድድሩን ለማዘጋጀት የተመረጠችው የጀርመኗ ሚውኒክ ከተማ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ነበረች፡፡ መቸም ማንም እንደሚያውቀው ሁሉ የኦሎምፒክ የስፖርት ውድድሮች ሰላማዊ የውድድር መድረኮች ናቸው፡፡ በዚህ የሚውኒክ ኦሎምፒክ ላይ እስራኤሎች ጦርነት ያንገሸገሻቸውና ሰላም የናፈቃቸው ህዝቦች መሆናቸውን ለመላው የአለም ህዝብ ለማሳየት በእጅጉ ጓጉተው ነበር፡፡ ይህን ጉጉታቸውን የኦሎምፒኩ ዋነኛ እቅድና ግብ አድርገውትም ነበር፡፡ ሌላው እቅዳቸው ከሌሎች የውድድሩ ተካፋይ ሀገሮች እቅድ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በኦሎምፒኩ ውድድር ሜዳሊያ በማግኘት የሀገራቸው ስምና ክብር እንዲልቅ ማድረግ! በቃ ይሄው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየርም ከባለስልጣኖቻቸው ጋር በመሆን ቅልብጭ ያለ የምሳ ግብዣ በቤተመንግስታቸው አሰናድተው ሲያበቁ፣ ተወዳዳሪ ስፖርተኞቹን ለግብዣ ጠሩዋቸው፡፡ የምሳ ግብዣው ከተጠናቀቀ በኋላም የተወዳዳሪ ስፖርተኛ ልጆቻቸውን ግንባር እየሳሙ፣ ያችን አንድዬ እቅዳቸውን ማሳካት እንዳይረሱ ካስገነዘቧቸው በሁዋላ “የአምላካችን በረከትና ጥበቃ አይለያችሁ! አንገትና ደረታችሁን ለወርቅ ሜዳሊያ ያድርገው! በድል ተመለሱ፡፡” በማለት መርቀው እስከ ቤተመንግስታቸው በር ድረስ ወጥተው ሸኟቸው፡፡ ስለ እስራኤልና እስራኤላውያን ጉዳይ አንስቶ የሚያወራ ሰው ሊያደርገው ቢፈልግ እንኳ ቸል ብሎ ሊያልፈው የማይችለው ነገር አለ ከተባለ፣ ስለ ፍልስጤምና ፍልስጤማውያን ጉዳይ አለማውራት ብቻ ነው፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ነገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንደሚባለው አይነት ነው፡፡ ከዚህ በላይ የተገለፀውም የሳንቲሙ አንድ ገጽታ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ የእስራኤል በሳንቲሙ ሌላኛው ወገን ያለው የፍልስጤማውያን ታሪክ ደግሞ ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡

ስለ ሚውኒክ ኦሎምፒክ ጉዳይ ከተነሳ ፍልስጤማውያንም ብጥርጥር አድርገው ያውቁ ነበር፡፡

በዚህ ኦሎምፒክ አማካኝነትም እየተቀበሉት ያለውን ግፍና መከራ፣ አገር አልባነታቸውንና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ እያደረጉት ያለውን በከባድ መስዋዕትነት የተሞላ ትግል መላው አለም እንዲያውቅላቸው ለማድረግ ክፉኛ ቋምጠው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አላማቸውን የሚያሳካና ከተቻለም በውድድሩ በማሸነፍ ባንዲራቸውን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ የሚችሉ፣ እንደ እስራኤሎችም ሆነ እንደ ሌሎች ተካፋይ ሀገራት “አላህ ይርዳችሁ በድል ተመለሱ፡፡” ብለው መርቀው የሚልኳቸው ስፖርተኞች ግን አልነበሯቸውም፡፡

ይህን ክብር የነፈጋቸው ደግሞ የተወዳዳሪ ስፖርተኞች አለመኖር ሳይሆን ነፃና ሉአላዊ ሆኖ የቆመ የራሳቸው ሀገር የሌላቸው በመሆኑ ነበር፡፡ መሬታችንና ነፃነታችንን ነጥቃ ለዚህ ብሔራዊ ውርደት ዳርጋናለች ያሏት ደግሞ አንዷን ጐናቸውን እስራኤልን ነው፡፡

ፍልስጤማውያን ይህ ሁኔታ በነበራቸው ላይ ሌላ ቅሬታን ስለፈጠረባቸው በእርግጥም ሆድ ብሷቸው ነበር፡፡ ይህንን ቅሬታቸውንና ጠቅላላ ሀገር አልባነታቸውን እያሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተከፍተው ይቆዝሙ በነበረበት ወቅት፣ ፒኤልኦ እየተባለ ባጭሩ በሚጠራው የፍልስጤም አርነት ድርጅት፣ በመቺ ቡድንነት የተቋቋመው “ብላክ ሴፕተምበር ወይም “ጥቁር መስከረም” የተባለው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን መሪዎች ራማላ ከተማ በሚገኝ አንድ ሠዋራ ቤት ውስጥ ባለ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡

የዚህ ቡድን መሪዎች የተቀመጡበት አስቸኳይ ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ ደግሞ “ፍልስጤማውያን የልኡካን ቡድን አባላትን ወደ ሚውኒክ ኦሎምፒክ መላክ” የሚል ነበር፡፡ ማህሙድ ሀምሻሪ የተባለው የቡድኑ መስራችና ግንባር ቀደም መሪ “ፂዎናዊቷ ሀገር ይሁዲዎቿን ታሪክ ይሠሩልኛል ብላ ወደ ኦሎምፒኩ መንደር ልካቸዋለች፡፡ እኛም የራሳችንን ልጆች ወደዚያው መላክ አለብን፡፡ እነሱም ፂዎናዊቷ ጠላታችን እስከ እድሜ ልኳ ድረስ ልትዘነጋው የማትችለውን አስደናቂ ታሪክ ይሠሩላታል፡፡ ይህን ቅዱስ ታሪክ ለመስራትም ጀግኖች ታጋዮቻችን በጉጉት እየተጠባበቁት ይገኛል፡፡” በማለት አስረዳ፡፡ ሁሉም ተስማሙ፡፡ አሊ ሀሰን ሳላሜህና ዋኢል ዝዌይተር የተባሉት ሌሎች መሪዎችም ተጨማሪ አስተያየቶችን በማቅረብ መወያየታቸውን ቀጠሉ፡፡

አራት ሰአት ከሃያ ስምንት ደቂቃ የፈጀውን አስቸኳይ ስብሰባቸውን ጨርሰውና ሶላት ሰግደው ሲነሱ፣ አንድ ከፍተኛና ምስጢራዊ ውሳኔ ወስነውና ውሳኔአቸውን የሚያስፈጽሙበት ዝርዝር የድርጊት መርሀ ግብር ነድፈው ነበር፡፡

ከስድስት ቀን በኋላ ምስራቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኝ አንድ የምስጢር መሰብሰቢያ ቦታ ሲገናኙ ውይይታቸውን ለመጨረስ የፈጀባቸው ጊዜ አስራ ሠባት ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ያለፉትን ስድስት ቀንና ሌሊቶች ያሳለፉት በከፍተኛ ዝግጅት ተወጥረው ነበር፡፡ እናም ይሄኛው ስብሰባ የወሰኑትን ውሳኔ ለማስፈፀም ባደረጉት የስራ ክፍልል መሠረት፣ እያንዳንዳቸው ያከናወኑትን ስራ መረጃ ለመለዋወጥ ብቻ ነበር፡፡

ዋኢል ዝዌይተር ወደ ሚውኒክ ኦሎምፒክ በመጓዝ “ታሪክ” እንዲሠሩ የፍልስጤም “ልዩ የኦሎምፒክ ልኡካን” ቡድን አባላት መመረጣቸውንና አስፈላጊው የጉዞ ማስረጃ ሁሉ መዘጋጀቱን አስረዳ፤ መርሃባ ተባለ፡፡ ማህሙድ ሀምሻሪ ደግሞ የተመረጡት የቡድኑ አባላት የጉዞው አላማ በግልጽ ተነግሯቸው እንዳመኑበትና ግዳጁንም ማን፣ ምን፣ የትና እንዴት አድርጐ በማከናወን ማስፈፀም እንደሚችል የተዘጋጀውን ዝርዝር ፕላን በሚገባ በማጥናት ሲለማመዱ መቆየታቸውን አስረዳ፡፡ እሱም መርሃባ ተባለ፤ በመጨረሻ የተናገረው ሁሌም ፊቱ የማይፈታውና በፊዚክስ እውቀቱ የት ይደርሳል የተባለው ሁሴን በሽር ነበር፡፡ ከደረቱ ሊደርስ ትንሽ የቀረውን ደማቅ ጥቁር ሪዙን ወደ ታች እየጐተተ እንዲህ አለ፤ “ጀግኖቹ ግዳጁን እንዲፈጽሙበት ቀደም ብለን ከመረጥነው መሳሪያ በአይነቱም ሆነ በጥራቱ እጅግ የላቀ የጦር መሳሪያዎችን በእጅ ማስገባት ችያለሁ፡፡ እነዚህን መሳሪያዎችም ወደ ሚውኒክ በምስጢር የሚያጓጉዝልኝ ሰው በአቡ ኒዳል ታጋዮች አማካኝነት አግኝቼ ወደዛው ተጓጉዘዋል፡፡ ሚውኒክ ያለው ያ የተባረከ የአላህ ሰውም በሰላም መድረሳቸውን አረጋግጦልኛል፡፡ እንሻ አላህ! ሁላችንም ታሪክ እንሠራለን፤ ይሁዲ ጠላቶቻችንን አይቀጡ ቅጣት የምንቀጣበት ጊዜ ደርሷል!”

ሁሴን በሽር ይህን ንግግር ተናግሮ እንደጨረሰ መርሃባ አላሉትም፡፡ ሁሌም በአድናቆትና በደስታ እያቀፉ ግንባሩን ሳሙት እንጂ፡፡ ከዚህ በኋላ ያደረጉት ነገር ቢኖር የመጨረሻውን ግዳጅ ለማስፈፀም የሀላፊነት ድርሻ መከፋፈል ነበር፡፡ ዋኢል ዝዌይተርና ሁሴን በሽር በጀርመን ሚውኒክ የዘመቻው ዋነኛ መሪዎች ለመሆን ሃላፊነቱን ወሰዱ፡፡ ማህሙድ ሀምሻሪ ደግሞ በድጋፍ ሰጭነት ተመደበ፡፡  ቀሪውና የመጨረሻው ስራ ለስምሪት ወደ ጀርመን ሚውኒክ ከተማ መነቃነቅ ብቻ ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ይህን የመጨረሻ ፈቃድ መስጠት የሚችለው ደግሞ አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ ሊቀመንበር አቡ አላ፡፡ ይህን መቺ ቡድን ቀድሞውኑ ሀ ብሎ ያቋቋመው የፍልስጤም አርነት ድርጅት ሊቀመንበር ያሲር አራፋት ነበር፡፡

ሞሀመድ ሀምሳሪ ወደ ቱኒዝ ሄዶ አቡ አላን በምስጢር በማግኘት እቅዱን ከነአፈፃፀሙ እንዲያስረዳና የመጨረሻውን ፈቃድ አግኝቶ እንዲመጣ በተወሰነው መሠረት፣ ይህንኑ ፈጽሞ ተመለሰ፡፡ የ“ጥቁር መስከረም” አባላትና መሪዎች የሆኑት የፍልስጤማውያን የሚውኒክ ኦሎምፒክ “ልዩ የልኡካን ቡድንም” ወደ ጀርመን ሚውኒክ ከተማ መረሹ፡፡

መላው የኦሎምፒኩ ተካፋይ ሀገራት ከውድድሩ መጀመር ሁለት ቀናት በፊት፣ የፀጥታና የደህንነት ጥበቃን በተመለከተ የውድድሩ አዘጋጆች የሠጡትን ማረጋገጫ በሙሉ ልባቸው አምነው ተቀብለውት ነበር፡፡ እስራኤልም ከዚህ የተለየች አልነበረችም፡፡ የልጆቿን ደህንነት ጉዳይ በጀርመን የፀጥታ ሀይሎች ላይ ጥላ እፎይ ብላ አርፋ ነበር፡፡ ውድድሩም ተጀምሮ በመልካም ሁኔታ መካሄዱን ቀጠለ፡፡

ከቀናቶች መካከል ለመልካም ስራ የተቀቡ እንዳሉ ሁሉ፣ ከመካከላቸው ተለይተው ለክፉ ስራ የተመረጡ ቀናቶችም አሉ፡፡ የሁሉም ተካፋይ ሀገራት ስፖርተኞች አገር ሠላም ብለው አሸንፈው ሜዳሊያ ለመሸለም ሰላማዊውን ፉክክር እየተፎካከሩ ባለበት ወቅት ግን ከቀናቶች ሁሉ ተለይቶ በተረገመ አንድ ክፉ ቀን፣ ማንም ይሆናል ወይም ይከሰታል ብሎ ያልገመተውና ያልጠረጠረው አስከፊ አደጋ ተከሠተ፡፡ ከእስራኤሎች ይልቅ የፍልስጤሙ “ልዩ የኦሎምፒክ የልኡካን ቡድን” እድል ቀናው፡፡ ይሄው የፍልስጤም ታጣቂ የ“ጥቁር መስከረም” መቺ ሀይል “እንኳን ሠው ወፍ ዝር አይልም” እያለ ሲፎክር የነበረውን የጀርመንን የደህንነትና ፀጥታ ጥበቃ ሀይል በማጃጃል፣ የአትሌቶቹን የመኖሪያ ካምፕ ሰብረው በመግባት አስራ አንድ የእስራኤል ስፖርተኞችን በጥይት ደብድበው ገደሉ፡፡ ማህሙድ ሀምሻሪ እንዳለውም፤ እንደ መጠሪያ ስማቸው ጥቁር የሆነ “ታሪክ” ሰሩ፡፡ የእስራኤል ስፖርተኞች እንዳቀዱት ሰላም ፈላጊዎች መሆናቸውን ለአለም ሀዝብ አሳይተው ሳይጨርሱና ያሰቡትን የኦሎምፒክ ሜዳሊያ አንዷንም እንኳ ሳያገኙ የጠላቶቻቸው የጥይት ራት ሆኑ፡፡

የስፖርተኞቻቸው በባላንጣዎቻቸው በፍልስጤም ታጣቂዎች በግፍ የመጨፍጨፋቸው ዜና ለእስራኤላውያን የብራ መብረቅ ነበር፡፡ ህፃን አዋቂ ሳይባል ሁሉም እስራኤላዊ እሪ ብሎ በሀዘን ልብሱን እየቀደደ ደረቱን ደቃ፡፡ ፊቱንም ነጩ! ሁላቸውም ወደ ሚውኒክ ኦሎምፒክ በድል ተመለሱ ብለው መርቀው ከሸኟቸው ስፖርተኛ ልጆቻቸው በጉጉት ይጠብቁት የነበረው የድላቸውን እንጂ በጠላቶቻቸው ጥይት የመጨፍጨፋቸውን ዜና ጨርሶ አልነበረም፡፡ እናም በሀዘን አንጀታቸው በእጥፍ ተቆርጦ ጧ ፍጥርቅ ብለው አምርረው በማልቀስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ጐልዳ ሜየርን “አንቺ ሴትዮ ለግመሎቻችን ጋጣ ሁነኛ ጠባቂ አላቆምሽለትም ነበርን?” ብለው አቤት አሉ፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው አስደንጋጩ ዜና በቅድሚያ የተነገራቸው ለጐልዳ ሜየር ስለነበር፣ የእርሳቸውም የወላድ አንጀት በሀዘን እርር ኩምትር ብሎ ነበር፡፡ በአይሁድ ሃይማኖታዊ የስነ ምግባር ደንብ መሠረት ቢኩር ሾላይም፤ ማለትም የታመሙትን መጠየቅና ያዘኑትን ማጽናናት የተለመደ ነውና የሟች ስፖርተኞችን ወላጆች በየቤታቸው እየዞሩ ኤልያህ (እግዚአብሔር) ያጥናችሁ እያሉ ለቅሶ ሲደርሱ፣ የወላድ አንጀታቸው አላስችል ብሏቸው ከሀዘንተኞቹ ጋር አብረው ተንሰቅስቀው አልቀሰዋል፡፡ በሀይማኖታቸው ደንብም የሽቫውን ጊዜ (የሰባት ቀናት የሀዘን ጊዜ) አብረዋቸው ተቀምጠዋል፡፡

የሽቫው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር ከል ለብሰው ገዳዮቹን እየተራገሙ ብቻ ቁጭ አላሉም፡፡ ይልቁንም ከእናትየዋና አያትየዋ ጐልዳ ሜየርነት ወደ አስቴርነት ተቀየሩ እንጂ፡፡ አስቴር በይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ በታናካህ፣ በስሟ አንድ አንጓ መጽሐፍ የተሰየመላትና ዜና መዋዕሏ የተተረከላት፤ በቅዱሱ መጽሐፍ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ የነበረውን ሀገር ሁሉ ይገዛ እንደነበር የተነገረላት የንጉስ አርጤክስስ ሚስት የሆነች ንግስት ናት፡፡ አስቴር ንግስት ብቻ አልነበረችም፡፡ አይሁዳውያን ወገኖቿን በታላቅ ጥበብ ከእልቂት የታደገችና ደመኛ ጠላታቸውንም የእጁን ስራ እንዲያገኝ ያደረገች የጀግኖች ጀግና ይሁዲ መሪ ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር በዚያን ወቅት ይጠበቅባቸው የነበረው በእርግጥም አስቴርን አይነት መሪ መሆን ነበር፡፡እናም ህዝባቸውን ከአደጋና ከእልቂት መጠበቅና ፊት ለፊት የተገዳደራቸውን ጠላታቸውንም በመጣበት መንገድ መመለስ፡፡ ልክ በሰይፍ የመጣ በሰይፍ ይወድቃል እንደሚባለው፡፡

እናም በሀገራቸው ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና እንዲህ አሉ “እጣ ፈንታ አመፀኛን ትወዳለች፡፡ በሰላማዊው የኦሎምፒክ አደባባይ ስፖርተኛ ልጆቻችንን በግፍ የገደሉት አመፀኞች የአመፃ እጣ ፈንታቸውን በቅርቡ ያገኟታል፡፡ እናንት ነፍስ ገዳይ አመፀኞች ሁላችሁም በሚገባ አድምጡኝ፡፡ እኛ አይሁዳዊ ነን፡፡ ህጋችንም አይን በአይን ጥርስም በጥርስ ነው፡፡ እንደ ቀደሙት ማካቢያን ተዋጊ ወገኖቻችን ሁሉ የዛሬዎቹ እስራኤላዊ ጐበዛዝቶች ነፃነታቸውንና ህልውናቸውን ለማስከበርና ለማስጠበቅ ሲሉ በገባችሁበት ጉድጓድ ገብተው በመዶሻቸው አናታችሁን በመቀጥቀጥ የአመፃና የግፍ እጃችሁን ዋጋ ይሰጧችኋል!”

ጐልዳ ሜየር ለወትሮው ፈገግታ የማይለየው የነበረውን ረጅምና ሰፊ ፊታቸውን ክፉኛ አኮሳትረው ይህን ዛቻቸውን ለወዳጅም ለጠላትም አሰሙ፡፡ ለወዳጃቸው ብድሩን ሊያስከፍሉለት ለጠላታቸው ደግሞ የእጁን ሊሰጡት፡፡ ቀጠሉናም ከካቢኔ አባሎቻቸው፣ ከጦር ሀይል ጀነራሎቻቸውና ከደህንነት ሃላፊዎቻቸው ጋር ከተመካከሩ በሁዋላ አትሌቶቹን የገደለውን የፍልስጤም የ”ጥቁር መስከረም” ታጣቂ ቡድንን የመደምሰስ ተልእኮ የተሰጠው አንድ ልዩ የኮማንዶ ቡድን “የእስራኤል ረጂም ክንድ” በሚል መጠሪያ በስለላ ድርጅቷ በሞሳድ እንዲቋቋም አደረጉ፡፡ ይህ ልዩ የኮማንዶ ቡድን የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈፀም ከመሰማራቱ በፊት፣ በቢሯቸው አስጠርተው እንዲህ የሚል አጭርና የማያወላውል መመሪያ ሰጡ፡፡ “ልጆቻችን በግፍና በጭካኔ እንዲገደሉ አስቀድመው እቅዱን ከነደፉት፣ ካስፈፀሙትና በግድያውም ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከተሳተፉት ነፍሰ ገዳይ የ“ጥቁር መስከረም” ቡድን አባላት ውስጥ  አንዱን እንኳ ብትምሩትና ከእጃችሁ ቢያመልጥ ልብ አድርጉ! ከእናንተ ራስ ላይ አልወርድም!”

ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር፤ ይህን ትእዛዛቸውን ከሰጡ በኋላ የሆነው ነገር ሁሉ ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የሚነገር ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል የደህንነትና የስለላ ድርጅት  ሞሳድ በአለም ላይ ዝነኛ የስለላ ድርጅት የሆነው ያለ ነገር እንዳልሆነ በተግባር አሳየ፡፡ ለዚህ ተልእኮ ለይቶ ያቋቋመው “የእስራኤል ረጅም ክንድ” የተባለው ልዩ የኮማንዶ ቡድን ነፍሰ ገዳዮቹ የፍልስጤም የ“ጥቁር መስከረም” ታጣቂ ቡድን መሪዎችና አባላት አሉ በተባሉበት የአለማችን ሀገራት ሁሉ በመሰማራት ለማመን በሚያስቸግር ፍጥነት፣ ዘዴና ብቃት አንድ በአንድ ልቅም አድርጐ በመግደል የዜጐቹን ደም በተራው ተበቀለ፡፡ እንደ ቀደመው የአይሁድ ህግ አይን በአይን፡፡ ጥርስም በጥርስ፡፡

በግድያው ከሁሴን በሽር ጋር ሆኖ የመራው ዋኢል ዝዌይተር፤ ከግድያው በኋላ ወደ ጣሊያን በሻገር ሮም ከተማ ውስጥ አይነ ግቡ ባልሆነ አንድ አፓርትመንት ውስጥ ተከራይቶ መኖር ጀምሮ ነበር፡፡ አንድ ቀን በእለት ስራው ሲባዝን ውሎ ወደ መኖሪያ አፓርትመንቱ ለመግባት ሊፍት ውስጥ ብቻውን ገባ፡፡

የገባበት ሊፍት ሦስተኛው ፎቅ ላይ ደርሶ ሲቆም ሁለት ሰዎች ገቡ፡፡ ዋኢል ዝዌይተር ነገሬ ብሎ በደንብም አላያቸውም ነበር፡፡ ሁለቱ ሰዎች ግን ድንገት በአረብኛ “ማንም ከእስራኤል ረጅም ክንድ ማምለጥ አይችልም!” በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፡፡ ይህን ጊዜ ዋኢል ዝዌይተር ደንግጦ ሁለቱን ሰዎች በደንብ ለማየት ሞከረ፡፡ ነገር ግን አልቻለም፡፡ ሁለቱ ሰዎች በፍጥነትና ተራ በተራ የተኮሱበት ሁለት የ.22 ካሊበር ሽጉጥ ጥይቶች ግንባሩን ሁለት ቦታ ላይ በስተው ጣሉት፡፡

ወደ ፈረንሳይ ያመለጠው ማህሙድ ሀምሻሪ፤ የፓሪስ ከተማ በሚገባ ውጣውና ደብቃው ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን የቧንቧ ጠጋኝ መሳሪያዎች የያዘና ሰፊ ቀይ የስራ ቱታ የለበሰ ልጅ እግር ቴክኒሻን በጥገና ሰበብ ማህሙድ ሀምሻሪ አርፎበት የነበረውን የሆቴል ክፍል በር ከፍቶ ገባና የስልኩን መነጋገሪያ ፈቶ፣ ትንሽዬ ቦምብ ከትቶ አጠመዳትና በመጣበት አኳኋን ተመልሶ በመውጣት በሆቴሉ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ወዳቆማት መኪና ገብቶ ከአካባቢው ተሰወረ፡፡ መሸትሸት ማለት ሲጀምር ከሆቴሉ በር ፊት ለፊት ካለ ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ቡና እየጠጣ ሲጋራ ሲያጨስ የነበረ ሰው ለቴክኒሻኑ ስልክ ደወለለትና “መፍቻዎችህን ውሰዳቸው እንጂ?” አለው፡፡ ልክ በዚህ ጊዜ ደግሞ ማህሙድ ሀምሻሪ ውስጡ አፕል፣ ሁለት ፓኮ ሲጋራና አንድ ጠርሙስ ግራንትስ የተሰኘ ውስኪ የያዘ ቦርሳውን አንጠልጥሎ ወደ ሆቴል ክፍሉ በመግባት ላይ ነበር፡፡ ከአራት ደቂቃ በኋላ፣ ቴክኒሻኑ ስልኩን አንስቶ የሆነ ቁጥር ደወለ፡፡ ማሀሙድ ሀምሻሪ ፈጠን ብሎ እየጠራ የነበረውን የሆቴል ክፍሉን ስልክ ሲያነሳውና ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ሲሰማ አንድ ሆነ፡፡

ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆፕሮስ ኒኮሲያ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የሁሴን በሽርን መኖሪያ ቤት የጥገና ሰራተኛ በመምሰል ከፍተው ከገቡ በኋላ ወደ መኝታ ቤቱ በመዝለቅ አንድ ትንሽዬ ቦንብ ከትራሱ ስር አጥምደው ሹልክ አሉ፡፡ እነሱ ይህን በሚያደርጉበት ወቅት ደሞ ሌላ አንድ ሰው ፓሪስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ አፓርትማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ በቆመች አንዲት መኪና ላይ ለይቶ ለማየት የሚያስቸግር ቦንብ ማንም ሰው ሳያየው አጥምዶ ጨርሶ ነበር፡፡

ከቀን ሽቀላው ደክሞት የመጣው ሁሴን በሽር፤ ጫማውን እንኳ ሳያወልቅ ዘፍ ያለበትን አልጋ ትራሱን ለማስተካከል ወደ አንገቱ ስር ሳብ አደረገው፡፡ ወዲያውኑ የፈነዳው ቦምብ የሁሴን በሽርን ሰውነት እንደ አንድ ነገር በታትኖ፣ በቤቱ ጣራና ግድግዳ ላይ ረጨው፡፡

ፓሪስ በሚገኘው አፓርትማ ጋራጅ ውስጥ መኪናውን አቁሞ ከሴት ጓደኛው ጋር ሲጫወት ያመሸው ሞሀመድ ቦውዲያ እስከ መኪናው ድረስ የሸኘችውን ጓደኛውን ከንፈሯን ስሞ ከተሰናበታት በኋላ እያፏጨ ወዳቆማት መኪና አመራ፡፡ በሩን ከፍቶ ገብቶ የአደጋ መከላከያ ቀበቶውን ካሰረ በኋላ፣ የመኪናውን ቁልፍ አስነሳ፡፡ ቡም! ከደቂቃዎች በኋላ የፍንዳታው ቦታ የተገኙት ፖሊሶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች ክፉኛ ከተጨረማመተችው መኪና ውስጥ ያገኙት የሞሀመድ ቦውዲያን የግራ እግር ቁራጭ ብቻ ነበር፡፡

የእስራኤል ረጅም ክንድ የተሰኘው ይህ የሞሳድ ልዩ የኮማንዶ ቡድን የወሰዳቸውን እነዚህን የግድያ እርምጃዎች ተከትሎ ፍልስጤማውያንና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖቻቸው፣ መላው የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት፣ ሶቪየት ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ጭፍራዎቿ ወዘተ እስራኤልን በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየርን “ደም የጠማት! ነፍሰ በላ፡፡ ነገረኛ ጠብ አጫሪ!” በማለት በውግዘትና በእርግማን ቢረባረቡባቸውም የጐልዳ ሜየር መልስ ግን ከአረቦች የስነቃል አባባል አንዱን መርጦ መጥቀስ ብቻ ነበረ “አንድ ሺ እርግማን ያረጀ ሸሚዝ መቅደድ እንኳ አይችልም!”

የእስራኤል የኮማንዶ ቡድን ግን ስራው ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም ነበር፡፡ የ “ጥቁር መስከረም” ቀንደኛ መሪ የሆነው አሊ ሀሰን ሰላሜህ ገና አልተገኘም ነበር፡፡ ከአምስት አመት ያላሰለሰ ክትትልና ፍለጋ በኋላ ግን ቤይሩት ሊባኖስ ውስጥ አገኙትና እንደሌሎቹ ጓደኞቹ ሁሉ በምስጢር ባጠመዱበት ቦንብ በማጋየት ወግ ላለው ቀብር እንኳ እንዳይበቃ አደረጉት፡፡

የአሊ ሀሰን ሰላሜህን ግድያ ተከትሎም በእስራኤል ላይ የውግዘት ናዳ ወርዶባቸው ነበር፡፡ በዚህኛውም ጊዜ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐልዳ ሜየር የሰጡት መልስ ልክ እንዳለፈው ከራሳቸው ከአረቦች አባባል ተስማሚ ነው ያሉትን አንዱን መርጦ መጥቀስ ብቻ ነበር፡፡ “ቆርጣችሁ መጣል ያቃታችሁን የባላንጣችሁን ክንድማ ሳሙት እንጂ!”

 

 

Read 3233 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 14:19