Saturday, 28 July 2012 11:59

ኢትዮጵያና ኬንያ የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር ነገስታት የንግስናቸው ምስጢር ምንድን ነው?

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

ብራዚላውያን ከካቶሊክ የክርስትና እምነት ቀጥሎ የሚያመልኩበት ነገር አለ ከተባለ ያለጥርጥር የእግር ኳስ ጨዋታ ነው፡፡ ብራዚላውያን ለእግር ኳስ ጨዋታ ያላቸውን ስሜት “ይወዳሉ” ወይም “ያፈቅራሉ” በሚሉ ቃላቶች ብቻ መግለጽ ጨርሶ አይቻልም፡፡ ብራዚላውያን እግር ኳስን አያፈቅሩም፡፡ ያመልኩታል፡፡ እነሱ እግር ኳስን ይኖሩታል፣ ይኖሩበታልም፡፡

ብራዚላውያን እግር ኳስን ይኖሩታል፣ ይኖሩበታልም፡፡

ብራዚላውያን እግር ኳስን ማምለክ ብቻ ሳይሆን ከማንም በላይ አስንቀው መጫወትንም አሳምረው ያውቁበታል፡፡

እስካሁን ድረስ በተካሄዱት የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች ውስጥ አለማችን እንደ ብራዚል አምስት ጊዜ አሸንፎ የአለም ሻምፒዮን የሆነ ሌላ ሀገር የላትም፡፡ ብራዚላውያን እንደ ጨዋታው ሁሉ በአለማችን አቻ የለውም ለሚባለው የእግር ኳስ ቡድናቸውና ለሀገር ውስጥ ሊጋቸው ያላቸው ትኩረትና ድጋፍም ዲካ የለሽ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንም በእግር ኳስ ጨዋታ ፍቅር ያበዱ ተብለው ጐራ ከተለየላቸው ህዝቦች አንዱ ናቸው፡፡ ነገሩ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ጨዋታን ይወዳሉ፡፡ ይህ አገላለጽ ያንሳል ከተባለም “ያፈቅራሉ” ተብሎ ሊነገርላቸው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደብራዚላውያን እግር ኳስን አያመልኩትም፡፡ እንደ ብራዚላውያን በአለምአቀፍም ሆነ በአህጉራዊ ትልልቅ ውድድሮች በተደጋጋሚ አሸንፎ ሻምፒዮን የሆነ የእግር ኳስ ቡድንም የላቸውም፡፡

ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለውን ብሔራዊ ክብር የሚያጐናጽፏቸው ሯጮቻቸው ናቸው፡፡ አስደናቂዎቹ አትሌቶቻቸው በተለያዩ አለማቀፋዊና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ በማሸነፍ፣ የድል አድራጊነትን ልዩ ክብር ለረጅም አመታት አስለምደዋቸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በእግር ኳስ ፍቅር ያበዱ ናቸው ይባሉ እንጂ ጨርቃቸውን ያስጣላቸው የሀገራቸው የእግር ኳስ ሊግ ሳይሆን የአውሮፓ ሊጐች፣ በተለይም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ነው፡፡ ለሀገራቸው ውድድር ያላቸው ትኩረትና ድጋፍም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከሀገራቸው እግር ኳስ እድገት ይልቅ እረፍት ነስቶ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስጨንቃቸው የእንግሊዝ አርሴናል ክለብ ለበርካታ አመታት ከሻምፒዮንነት መራቁ ወይም ማንቸስተር ዩናይትድ ሃያልነቱን በከተማው ተቀናቃኝ ክለብ በማንቸስተር ሲቲ ይነጠቅ ይሆን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያኑ ይህ ታላቅ “ጭንቀት” ለረጅም አመታት የድል ጽዋ ሲያቃምሳቸው ከኖረውና የብሔራዊ ኩራታቸው ምንጭ ከሆነው የአትሌቲክስ ስፖርታቸውም በላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን የስፖርት የሚዲያ ባለሙያዎች የቅድሚያ ትኩረታቸው የአትሌቶቻቸው የማሸነፍ ዜና ወይም ጠቅላላ የአትሌቲክስ ጉዳይ ሳይሆን የቸልሲ ወይም የሊቨርፑል መሸነፍ አሊያም ነጥብ መጣል ነው፡፡

በአውሮፓ አሁን ወቅቱ የበጋው ጊዜ ሊገባ እያኮበኮበ ነው፡፡ ሁሉም የአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጐችም የአመቱን ውድድራቸውን አጠናቀው፣ ለቀጣዩ የውድድር ወቅት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያኑም ሆኑ ጠቅላላ የስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎቻቸው ቀልባቸውንና ልባቸውን የሚስብና በየቀኑ ለተደጋጋሚ ጊዜ የሚያቀርቡት የአውሮፓ እግር ኳስ ሊግ ወሬ እንደልባቸው ማግኘት አይችሉም፡፡

የአውሮፓውያኑን የእግር ኳስ ሊግ በተለይ ደግሞ የእንግሊዝን ፕሪምየር ሊግ በሳተላይት ቴሌቪዥን በመከታተል፣ ስለ እግር ኳስ ጨዋታ አሠለጣጠንና የተጨዋቾች አሠላለፍ ዘዴ፣ እንደማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርግሰን የመሳሰሉትን አንጋፋና ውጤታማ አሠልጣኞችን በመተቸትና ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ ምክር በመለገስ ረገድ የየትኛውም ሀገር ዜጋ ቢሆን ኢትዮጵያውያኑን በተለይም የስፖርት የሚዲያ ባለሙያዎችን መወዳደር አይችልም፡፡

በኢትዮጵያ ከስሩ ሰዎች ሠባቱ የአውሮፓ የእግር ኳስ ሊግ የተዋጣላቸው ተንታኞች ናቸው ቢባል አነሱ ካልሆነ በቀር አጋነናችሁት ብሎ የሚቀየም አይኖርም፡፡

አሁን የአውሮፓን ብቻ ሳይሆን የመላውን አለም የስፖርት ትኩረት የተቆጣጠረው የለንደን ኦሎምፒክ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ውድድሮችን በማዘጋጀት የእንግሊዟ ለንደን ከተማ “ሀትሪክ (ሶስቴ) የሠራችበት የ2012 ዓ.ም 31ኛው የለንደን ኦሎምፒክ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ለጊዜውም ቢሆን የስፖርት ትኩረታቸውን ወደዚህ ኦሎምፒክና የአትሌቲክስ ቡድናቸው ማስመዝገብ በሚችለው ውጤት ላይ ለማድረግ ተገደዋል፡፡

የኢትዮጵያን ድንበር የደቡብ ወሰን ተሻግሮ ቁልቁል ሲኬድ ጐረቤቷ ኬንያ ትገኛለች፡፡ ኬንያውያን እንደ ጐረቤቶቻቸው ኢትዮጵያውያን በእግር ኳስ ፍቅር ያበዱ ናቸው ብሎ ማንም አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፡፡ እግር ኳስን በተመለከተ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኬንያውያንም በአለም አቀፍ ውድድሮች ተካፍሎ ሻምፒዮን የሆነ የእግር ኳስ ቡድን ኖሮዋት እንደማያውቅ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተለያዩ አለማቀፋዊና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ተደጋጋሚ ድሎችን በመጐናፀፍ የብሔራዊ ኩራት ምንጮቻቸው ዝነኛ አትሌቶቻቸው ናቸው፡፡ በዚህ በአትሌቲክስ ስፖርት ከኢትዮጵያውያን በተቃራኒው የሚያቆማቸው አንድ ጉዳይ ለመላው ኬንያውያንም ሆነ ለስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎቻቸው የአትሌቶቻቸው የድል ዜናም ሆነ ሌላው አትሌቲክስ ነክ የሆነው ነገር ከሁሉም የላቀ የትኩረት አጀንዳቸው መሆኑ ነው፡፡

ለብራዚላውያንና አርጀንቲናውያን የእግር ኳስ ጨዋታ ”ዋነኛው ፊታውራሪ እኔ ነኝ!” የሚል የፉክክር ምንጭ ነው፡፡

አሜሪካንና ጃማይካን በጥብቅ የሚያፎካክራቸው ነገር አለ ከተባለም የአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር ነው፡፡ የአለም ፈጣኑ ሰው የሚል የክብር መጠሪያ በማግኘት ለበርካታ አመታት የአሜሪካና የጃማይካ አትሌቶች የአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድርን እየተፈራረቁ ነግሰውበታል፡፡

ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጥታ እንደ ሉአላዊት አገር ከቆመችበት ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ለክፉ የሚሰጥ ነፋስ ሳይነፍስባት፣ ከኢትዮጵያ ጋር በመልካም ጉርብትናና ወዳጅነት እየኖረች ያለች ሀገር ናት፡፡ በመካከላቸው ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ሠላማዊ ጉርብትናቸው ዋነኛ መሠረቱ ወንድማማችነትና የጋራ ትብብር ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ለበላይነት የሚደረግ ከፍተኛ ፉክክር አለ ከተባለ የዚህን ፉክክር ምንጭ የምናገኘው ከጦር ሀይል ጉልበታቸው ጨርሶ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ከሠላማዊው የስፖርት መድረክ ብቻ ነው፡፡ የሁለቱን ሀገራት ብቸኛ የሃያልነት ፉክክር የምናገኘው በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር ነው፡፡ የአለምን የአጭር ርቀት የሩጫ ውድድር አሜሪካና ጃማይካ እንደነገሱበት ሁሉ፣ ካለፉት ሠላሳና አርባ አመታት ወዲህ የረጅም ርቀት የሩጫ ወድድርን እንደ ኢትዮጵያና ኬንያ በበላይነት መቆጣጠር የቻለ አንድም ሀገር በአለማችን ጨርሶ አልታየም፡፡

ለረጅም ዘመናት በአለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የረጅም ርቀት ውድድሮች የአሸናፊነት የግምት ርዕስ የሚሆነው ከኢትዮጵያና ከኬንያ ማን ያሸንፋል የሚለው ብቻ ነው፡፡ የሌላው ሀገር በተለይ ደግሞ የአውሮፓና የአሜሪካ ተወዳዳሪዎች ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜግነታቸውን ቀይረው ለአውሮፓና ለአሜሪካ ከሚወዳደሩት እንደ ሞ ፋራህ አይነት ካልሆኑ በቀር፣ ለዚህ የአሸናፊነት ግምት የመታጨት እድላቸው በእጅጉ ያነሰና ሲያጋጥምም እንደ ብርቅ የሚታይ ነው፡፡

በዚህ የተነሳም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የአሸናፊነትና የበላይነት የፉክክር ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ በኬንያውያን ላይ መጠኑ ልቆ ይታያል እንጂ ሁለቱም ሀገራት አንዳቸው በአንዳቸው መሸነፉን በጣም ይጠሉታል፡፡ እንዲህ ያለውን ከፍተኛ የፉክክር ስሜት በሁለቱ ሀገራት ላይ መመልከት የምንችለው በከፍተኛ አለምአቀፋዊ ውድድሮች ላይ ነው፡፡ እነሆ አሁን ሃያ ስድስተኛው የለንደን ኦሎምፒክ እየተካሄደ የሚገኝበት ጊዜ ነው፡፡ እናም ይህ ኦሎምፒክ ተጠናቆ ማንኛቸው በበላይነት እንደሚያሸንፉ እስኪታወቅ ድረስ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኬንያ አስደሳቹንና ሠላማዊውን የበላይነት የፉክክር መንፈስ እንደገና ይዞላቸው መጥቷል፡፡

የሚያሳጣ ምናልባትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ችሎታውን ውድድሮችን በማሸነፍ ማስመስከር ለሚችል ወጣትና ተስፈኛ አትሌት፣ በኢትዮጵያና በኬንያ የስምንት መቶና የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር፣ የሶስት ሺ ሜትር መሠናክል፣ የአምስት ሺ የአስር ሺ ሜትርና የማራቶን ሯጮች ቡድን ውስጥ አባል ለመሆን ከመቻል ይልቅ በግሉ ተወዳድሮ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን የበለጠ እድል ሊኖረው ይችላል፡፡

ኬንያዊው ፓትሪክ ማካው፤ ባለፈው መስከረም ላይ የተደረገውን የማራቶን ውድድር ያሸነፈው በኢትዮጵያዊው ዘመን አይሽሬ ታላቅ ሯጭ ሀይሌ ገብረስላሴ ተይዞ የቆየውን የማራቶን ሪከርድ በመስበርና ሁለት ሰአት ከሶስት ደቂቃ ከሠላሳ ስምንት ሰኮንድ አዲስ ሰአት በማስመዝገብ ነው፡፡ ፓትሪክ ማካው ያስመዘገበው ይህ የማራቶን ድል ለኬንያውያን ቶርታ ኬክ ከእነ ክሬሙና ስትሮው ቤሪው አይነት ነበር፡፡ ተራ ሳይሆን ድርብርብ ድል ነበር፡፡ ውድድሩን ማሸነፍ አዲስ የማራቶን ሪከርድ ማስመዝገብ፡፡ ያሸነፉትና ሪከርዱንም የሠበሩበት የዋነኛ ተፎካካሪያቸውን የኢትዮጵያ አትሌቶች በማሸነፍ፡፡

ይህን ድርብርብ ድል ያስጠገባቸው የአለም ቁጥር አንድ የማራቶን ሯጫቸው ፓትሪክ ማካው ግን በለንደን ኦሎምፒክ የሚወዳደረው የኬንያ የማራቶን ቡድን አባል መሆን አልቻለም፡፡ ይህ የሆነው የኬንያ የአትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኞች በጥላቻ አሊያም በሙስና ወይም በሆነ በሌላ ምክንያት የማራቶን ቡድኑ አባል እንዳይሆን ስላደረጉት አይደለም፡፡ የቡድኑ አባል ሆኖ እንዳይመረጥ ሰበብ ሊሆን የሚችል የጤና እክል ገጥሞት ስለተጐዳም ጨርሶ አይደለም፡፡ “እንዴ! ፓትሪክ ማካው እኮ የአለምን የማራቶን ሩጫ ሪከርድ በመስበር መቆጣጠር የቻለ ቁጥር አንድ ሯጭ ነው፡፡ ይህን እንኳን የሀገሩ ልጆች ኬንያውያን ይቅርና መላው አለም ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ የወቅቱ እውነታ ግን ከዚህ ሀገራዊም ሆነ አለማቀፋዊ እውነታና ዝና በእጅጉ የተለየ ነው፡፡

ማንም ከኬንያ የኦሎምፒክ የማራቶን ሩጫ ቡድን አባላት ውስጥ የአለማችንን ቁጥር አንድ የማራቶን ሯጭ የፓትሪክ ማካውን ስም ማግኘት አይችልም፡፡ ምናልባት ለመናገር ወይም ፈታ ብሎ ጉዳዩን ለማስረዳትና ሌሎችን ለማሳመን አስቸጋሪ ነው ካልተባለ በቀር ፓትሪክ ማካውን ከቡድኑ ውስጥ ማግኘት ያልተቻለበት ምክንያት አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ የማራቶን ቡድኑ አባላት መሆን የሚችሉትን ምርጥ ሯጮች ለመምረጥ የተደረገውን ውድድር ፓትሪክ ማካው ማሸነፍ አቃተው፡፡

የለም! ማሸነፍ አቃተው የሚለው ቃል የነገሩን ሙሉ ስዕል አይገልፀውም፡፡

በዚያ ውድድር ፓትሪክ ማካው ያቃተው ማሸነፍ አይደለም፡፡ ስድስተኛ ሆኖ ነው የጨረሰው፡፡ የአለማችን ቁጥር አንድ ማራቶነኛ፤ አዲስና ወጣት የማራቶን ሯጭ የሀገሩን ልጆች ጨርሶ መቋቋም ሳይችል ቀረ፡፡ በዚህም በኬንያም ሆነ በአለም አዲስ ታሪክ ዳግመኛ ለማስመዝገብ በቃ፡፡ ፓትሪስ ማካው የአለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ሆኖ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ ያልቻለ፣ የመጀመሪያው አሳዛኝ የማራቶን ሯጭ ሆነ፡፡

አልጋ ወራሹ ሯጭ እያሉ በአድናቆትና በፍቅር ስለሚያሞኻሹት ቀነኒሳ በቀለ ለኢትዮጵያውያን መናገር አንድም ለቀባሪው እንደማርዳት አሊያም ስለሀገራቸው ድንቅ አትሌት ባይተዋርና እንግዳ እንደሆኑ አድርጐ እንደመቁጠር ተደርጐ ሊወስድ ይችላል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ከአራት አመት በፊት በቤጂይንግ ቻይና በተካሄደው ኦሎምፒክ፣ በአምስትና በአስር ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር መላ አለምን አጀብ ባስባለ ድንቅ ብቃት በማሸነፍ፣ ሀገሩን የሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንድትሆን ለማድረግ ችሏል፡፡ በቀነኒሳ ድርብ ድል የተነሳም በዓለም ታላቅ የውድድር አደባባይ ላይ ብሔራዊ መዝሙራቸው እየተዘመረ፣ ከሁሉም ነገር በላይ ፍቅርና ክብር የሚሰጡት ብሔራዊ ባንዲራቸው ከፍ ብሎ ሲሰቀል የተመለከቱት ኢትዮጵያውያን፤ ወደር በሌለው ብሔራዊ የኩራት ስሜት ተውጠው የደስታና የድል አድራጊነት ሲቃ የሚፈጥረውን እንባ አንብተዋል፡፡

የዝነኛውን አትሌት የቀነኒሳ በቀለን አለማቀፋዊ ገድል ማንም ቢሆን በቀላል ማስታወሻ ዘርዝሮ ለማስረዳት ይቸገራል፡፡

ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ “አልጋ ወራሹ” እያሉ የሚጠሩት ከቶውኑ ያለነገር አይደለም፡፡ በኦሎምፒክ የሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ድርብ ድል ባለቤት በሆነበት የአምስት ሺና የአስር ሺ ሜትር ሩጫ ግን ዘውዱን ከመጀመሪያው ንጉስ ከሀይሌ ገብረስላሴ ተቀብሎ ከደፋና ከነገሠ ቆይቷል፡፡ የእነኝህ ርቀቶች የአለም ሪከርድ ባለቤትነት የተያዘውም በእርሱ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያና በኬንያ የመካከለኛና የረጅም ርቀት ሩጫ የብሔራዊ ቡድን ውስጥ በአባልነት ለመካተት ያለውን ከፍተኛ ትግልና ፉክክር ለማሳየት ቀነኒሳ በቀለ ሌላ ተጨማሪ አብነት መሆን ይችላል፡፡ የሁለቱም ርቀቶች ንጉስና የአለም ሪከርድ ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ፤ በኦሎምፒክ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል መሆን የቻለው በአስር ሺ ሜትር ቡድን ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በአምስት ሺ ሜትር ቡድኑ ውስጥ ለቀነኒሳ በቀለ የሚሆን ቦታ የለም፡፡ የሱን ቦታ ከእሱ የበለጠ ብቃት ያለው አትሌት ይዞታል፡፡

በአምስት ሺና በአስር ሺ ሜትር ታላላቅ አለምአቀፍ ውድድሮች መላ አለምን በከፍተኛ ሁኔታ ባስደነቀ ተአምራዊ ብቃት በተደጋጋሚ ጊዜ በማሸነፍ፣ የሀገሯ ስምና ዝና በአለም አደባባይ እንዲልቅ ማድረግ የቻለችውን ድንቋን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን፤ ኢትዮጵያውያን የሀገሯ ልጆች “ጥሩዬ” በሚል አጭር የፍቅር የቁልምጫ ስም ይጠሯታል፡፡ ጥሩነሽ ግን ከጥሩም በላይ ናት፡፡ ጥሩነሽ እጅግ ድንቅና አይበገሬ “World class” አትሌት ናት፡፡ እንደ ቀነኒሳ በቀለ ሁሉ በቤጂይንግ ኦሎምፒክ ልዕልት በሆነችበት በአምስት ሺና በአስር ሺ ሜትር ሩጫ በማሸነፍ የሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ድርብ ድል ባለቤት መሆን ችላለች፡፡

ይህ የኦሎምፒክ ድርብ ድሏ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ድል ነው፡፡ በአንድ ኦሎምፒክ በሁለት የረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር ላይ በማሸነፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻለች አፍሪካዊት አትሌት፤ የሀገሬ ባለቅኔ “ነገር የገባት ሰጐን” ብሎ ቅኔ የተቀኘላት “ጥሩዬ” ብቻ ናት፡፡

እንዲህ የለ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ባለቤትና የአምስት ሺህና የአስር ሺ ሜትር ሩጫ ውድድር ንግስት የሆነችውን ድንቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን፤ በኦሎምፒክ ተሳታፊ ከሆነው የሀገሯ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከአስር ሺ ሜትር የተወዳዳሪዎች ቡድን ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ በሚወዳደሩባቸው ርቀቶች የአለም ቁጥር አንድ የሆኑት እነ ማካው፣ ቀነኒሳና ጥሩነሽ በሚጠበቅባቸው ሁሉ መወዳደር አለመቻላቸው፣ በኢትዮጵያና በኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ አባል ሆኖ ለመመረጥ ያለው ፉክክር ምን ያህል ፈታኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ አሁን ትልቁን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ ይህን የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር እነዚህ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ብቻ በበላይነት መቆጣጠር የቻሉበት ምስጢር ምንድነው?ይህን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያ ያላቸው የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ የኢትዮጵያውያንና የኬንያውያን የተፈጥሮ ዘረመል፣ ለስኬታቸው ዋና መሠረት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ባለሙያዎች ደግሞ የአትሌቶቹን አሯሯጥና ያደጉበትን ሁኔታ በማጥናት፣ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶችን በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር የአለም ቁንጮ ያደረጋቸው የኑሮ ሁኔታዎችና ሌሎች ማህበራዊ ምክንያቶች ናቸው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ሀይሌ ገብረስላሴ አንድ እጁን ወደ ደረቱ አስጠግቶ የሚሮጠውን አሯሯጡንና ከብቶችን ለማገድም ሆነ ውሃ ለመቅዳት ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ወጣቶች በየእለቱ በሩጫ የሚያሳልፉትን ጊዜና የሚሸፍኑትን ረጅም ርቀት ለዚህ ምክንያታቸው እንደ አብነት አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡

ምስጢሩን ለማወቅ የሚደረገው ጥረትና ምርምር ግን አላቆመም፡፡ የኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን በረጅም ርቀት ሩጫ እያሸነፉ አለምንና ተማራማሪዎችን ማስደመማቸውም እንዲሁ፡፡ ለንደንም ተረኛ የንግስና ከተማቸው ለመሆን እነሆ አማልክት እድሉን ሰጥተዋታል፡፡

 

 

Read 4541 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 12:01