Saturday, 14 July 2012 00:00

የጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን የመጨረሻ ሶስት ቀናት

Written by  አልአዛር
Rate this item
(1 Vote)

(ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)

ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን በግራ እጃቸው ደረታቸውን ደግፈው ይዘው፣ በቀኝ እጃቸው በያዙት ነጭ መሃረብ የግንባራቸውን ላብ እየጠረጉ፣ በቢሮአቸው ውስጥ በጣም ቀስ ባለ እርምጃ እየተንጐራደዱ ሳሉ ፀሐፊያቸው በሩን በቀስታ አንኳኩታ ከገባች በኋላ ጓድ ዝዳኖቭና ጓድ ለቭረንቲ ቤራ መምጣታቸውን ተናገረች፡፡ ልክ እሷ እንደወጣች ሁለቱ ጓዶች ገቡና እጅ እንደመንሳት ያለ አብዮታዊ ሠላምታቸውን አቅርበው ቆሙ፡፡ ጓድ ስታሊን እንዲቀመጡ በእጃቸው ምልክት ቢሰጧቸውም ልክ እንዳልገባቸው ሆነው እንደቆመ ቀሩ፡፡ ጓድ ስታሊን በቢሮአቸው ሲያስጠሯቸው መቸም ጊዜ ቢሆን ተቀምጠው አያውቁም፡፡ ትዕዛዝ የሚቀበሉት ሁሌም እንደቆሙ ነበር፡፡

ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን አንዲት አረፍተ ነገር ብቻ የተፃፈባት ብጣሽ ወረቀት ለጓድ ቤራ ሰጡት፡፡ ጓድ ቤራ በወረቀቷ ላይ በጓድ ስታሊን የእጅ ጽሑፍ የተፃፈውን ካነበበ በኋላ ለጓድ ዝዳኖቭ አቀበለው፡፡ ጓድ ዣዳኖቭ ወረቀቷን ካነበበ በኋላ ከጓድ ቤራ ጋር አይን ለአይን ተፋጠጡ፡፡ የጓድ ዝዳኖቭ እጅ በግልጽ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡

ጓድ ቤራ እንደተለመደው ተረጋግቶ እንደቆመ ነበር፡፡ ጓድ ዣዳኖቭ ወረቀቷን እንደገና ደግሞ አነበባት፡፡ “ጓድ ጀነራል አሊየክሲየቪችና ጓድ ጀነራል ዘጋኖቭ ባሉበት እንዲያዙና በአፋጣኝ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወስድባቸው” ይላል የወረቀቱ ቀጭን ትዕዛዝ፡፡

ሁለቱ ጓዶች እንደቆሙ ሲቀሩ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን “ጓዶች ችግር አለ” በማለት ጠየቋቸው፡፡ ሁለቱም በአንድ ድምጽ “ኒየት!” (የለም) በማለት መለሱ፡፡ “ታዲያ ከፊቴ ላይ ምን ይገትራችኋል” በሚል አይነት ጓድ ስታሊን በሁለት ጣቶቻቸው የውጡልኝ ምልክት ሲያሳዩዋቸው፣ ሲገቡ ያቀረቡት አይነት አብዮታዊ ሠላምታ ሰጥተው ወጡ፡፡

ሁለቱ ጓዶች ወደ የመኪኖቻቸው ከመግባታቸው በፊት ጓድ ቤራ የጓድ ዝዳኖቭን ክንድ ያዝ አደረገና “ምነው ጓድ ዝጋኖቭ … ምን ነክቶህ ነው በጓድ ስታሊን ፊት እንዲያ የተንቀጠቀጥከው? አብዮታዊ ወኔህ ከዳህ እንዴ?” አለው፡፡ ይህ የጓድ ቤራ ጥያቄ ቀላልና ጓዳዊ ጥያቄ አልነበረም፡፡ ጓድ ቤራ ልክ እንደ ሻርክ ነው፡፡ ደም ካየ፣ በምንም ተአምር አይምርም፡፡ ይህንን አመሉን ጓድ ዝዳኖቭም ሆነ ሌሎች ጓዶች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እናም አሁን ያቀረበለት ጥያቄ ደም የመፈለግ ጥያቄ እንደሆነ ጓድ ዝዳኖቭ ነቄ ብሏል፡፡ ስለዚህ ስሜቱንና ቀልቡን ሰብሰብ አድርጐ “ንየት!  ንየት! ጓድ ቤራ… የምን ወኔ መክዳት ነው! የጓድ ጀነራል አሊየክሲየቪችና የጓድ ጀነራል ዘጋኖቭ ታላቁን አብዮታችንን መክዳት በጣም እጅግ በጣም አናዶኝ ነው እንጂ!  እነዚህ ነባርና አንጋፋ የቀዩ ጦር ከፍተኛ መሪዎች ካልታመኑ ማን ሊታመን ነው ማለት ነው? እኮ ማንን ነው የምናምነው?” አለና የመኪናውን ጣራ በቡጢ ጠለዘው፡፡

ጓድ ቤራ መልስ ከመስጠቱ በፊት ቀጠለና “ደህና ጓድ ቤራ አሁን አንድ አብዮታዊ ውለታ እንድትውልልኝ በጓዳዊ ስሜት እለምንሀለሁ፡፡ እነዚህን ከሀዲ አሳሞች የእኔ ፈጣን ተነቃናቂ መቺ ስኳዶች አይን ተከድኖ እስኪገለጥ ድረስ ከሚፈጅው ጊዜ በፈጠነ ሁኔታ የክህደታቸውን ዋጋ እንዲሰጣቸው ፍቀድልኝ” አለና ጓድ ቤራን ጠየቀው -ጓድ ዝጋኖቭ፡፡ ጓድ ቤራም ተጨማሪ ነገር ሳይናገር በእጁ “ወደፊት” የሚል ምልክት አሳየውና ሁሉም በየመኪኖቻቸው ገብተው ወደየገደላ ዘመቻቸው ከነፉ፡፡

ጓድ ዝዳኖቭ ከመኪናው ውስጥ እንደገባ ክራቫቱን እያላላ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ንግግሩ ጓድ ቤራን አሳምኖት ይሆን አይሁን እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ ላቡ በግንባሩና በአንገቱ መውረድ ጀመረ፡፡ ልቡ ግን የስታሊን ቀይ ብትር እንዲያርፋባቸው ስለተወሠነባቸው ሁለት ጀነራሎች በእጅጉ እየተጨነቀና እያዘነ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁለት ጀነራሎች ጋር ከወጣትነት ጊዜያቸው ጀምሮ በደንብ የሚተዋወቁና የምር ወዳጆች ነበሩ፡፡ በጓድ ስታሊን የተወሰነባቸውን አብዮታዊ ውሳኔ ሲያነብ በመደንገጡና በማዘኑ ያሳየው ስሜት በጓድ ቤራ የጥርጣሬ አይን ውስጥ ስላስገባው የራሱም ህይወት ከባድ አደጋ አንዣበበበት፡፡

ከዚህ ከባድ አደጋ ለማምለጥ ሲልም እነዚህን አብሮ አደግ ወዳጆቹንና የትግል ጓዶቹን በስታሊን ቀይ በትር ለመደምሰስ የቅድሚያ ሃላፊነት ለመውሰድ ተገደደ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአብዮቱና በጓድ ስታሊን በተለይ ደግሞ በሻርኩ በጓድ ቤራ ላይ የምሩን ተበሳጨባቸው፡፡

ጓድ ዝዳኖቭና ጓድ ቤራ ከቢሮአቸው እንደወጡ፣ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን ከጠረጴዛቸው መሳቢያ ውስጥ አንድ በቆዳ የተደጐሰ ወፈር ያለ የማስታወሻ ደብተር አወጡና የሰዎች ስም ከተፃፈበት ረጅም ዝርዝር ውስጥ የሁለት ሰዎችን ስም በያዙት እርሳስ በሁለት መስመሮች ሠርዘው አጠፉ፡፡

እነዚህ ሁለት ጀነራሎች በ1934 ዓ.ም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴና የፖሊት ቢሮው በጀነራልነት ማዕረግ ቀዩን ጦር እንዲመሩ ካደረጋቸው አብዮታዊ መኮንኖች ውስጥ የመጨረሻዎቹ አንጋፋ ጀነራሎች ነበሩ፡፡ ከጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን የማስታወሻ ደብተር ውስጥ ካለው የጀነራሎች የስም ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ሳይሰረዝ የሚገኙት ጀነራሎች የአንድ እጅ ጣት ቁጥር አይሞላም፡፡

ልክ እንደ ጀነራሎቹ ሁሉ በጓድ ስታሊን የማስታወሻ ደብተር ውስጥ ያልተሠረዘ የጥቂት ሰዎች ስም ዝርዝር የሚገኘው የሶቪየት ህብረት የኢንዱስትሪ መሪዎች ስም በተሰረዘበት ክፍል ላይ ብቻ ነው፡፡ በ1934 ዓ.ም ለፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የተመረጡ ጓዶች ስም የተዘረዘረበት ክፍል የሁሉም ስም ተሠርዟል፡፡ ይህ ማለት ተራና ግልጽ ነገር ነው፡፡ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን፤ እነዚህን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከተመረጡበት ከ1934 እስከ 1938 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ባለው የአራት አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በስታሊን ቀይ በትር ከፓርቲውም ከምድሪቱም ላይ አስወግደዋቸዋል፡፡

ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን የማስታወሻ ደብተራቸውን እያገላበጡ በአንድ ወረቀት ላይ የተለያዩ ሰዎችን ስም ቀስ እያሉ መፃፍ ጀመሩና ድንገት ፀሐፊያቸውን ጠርተው ተጠሪነቱ ለእርሳቸው ብቻ የሆነውንና በእርሳቸው ትዕዛዝ ብቻ የሚንቀሳቀሰውን የሚስጥር የደህንነት ጥበቃ ልዩ ሀይላቸውን አዛዥ ጓድ ኒኮላይ ያዞቭን ባስቸኳይ ወደ ቢሮአቸው እንዲመጣ እንድትጠራው አዘዟት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጓድ ስታሊን ለገደሏቸውና ላስገደሏቸው ሰዎች ሁሉ ተጠያቂነቱን በእሱ ላይ እያላከኩበትና ከእለታት ባንዱ ቀን የዛ ሁሉ ሀጢያት ማጠቢያ የመስዋዕት በግ እንደሚያደርጉት እርግጠኛ በመሆን የሚያደርገው ነገር ሁሉ ግራ ገብቶት በቁም ቅዠት እየተሰቃየ የሚገኘው ጓድ ኒኮላይ ያዞቭም፣ ጀርባውን ላብ እያሰመጠውና ጉልበቱን ብርክ ብርክ እያለው ሲከንፍ ከተፍ አለ፡፡

ጓድ ስታሊን ቢሮ ገብቶ የግንባሩን ላብ በኮቱ የቀኝ እጅ እጅጌ አሁንም አሁንም እየጠረገ ፊት ለፊታቸው እንደቆመ፣ ጓድ ስታሊን ቀስ ባለና ሸካራ በሆነ ድምጽ “ጓድ ቤራና ጓድ ዝዳኖቭ ትናንትና ባመጣኸው ዝርዝር መረጃ መሠረት እነዚያን የጦር ሀይሉ ፀረ አብዮተኞች አፋጣኝ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወስዱባቸው የፓርቲያችን ፖሊት ቢሮ የመከላከያ ኮሚቴ የወሰነውን ውሳኔ አስተላልፌላቸዋለሁ፡፡

“ያንተን ምርጥ ሠዎች በማሠማራት በደንብ ተከታተላቸውና እስከ ዛሬ እኩሉ ሌሊት ድረስ ውሳኔውን ማስፈፀም ካልቻሉ በተገኙበት ቦታ በቁጥጥር ስር በማዋል የማያዳግም አብዮታዊ እርምጃ ውሰድባቸው፡፡ እርምጃውን ከወሰድክ በሁዋላ ያለውን የፓርቲ ስራና የፈፀሙት የሀገር መክዳትና የፀረ አብዮተኝነት ወንጀል ዝርዝር ፀሀፊዬ ትሠጥሀለች፡፡ ለፓርቲው የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም የህዝብ አደረጃጀት ኮሚቴዎች ወስደህ ትሠጣቸዋለህ፡፡ ስራውን እነሱ ይሠሩታል፡፡ ጓድ ኒኮላይ፤ የነገርኩህ ሁሉ በደንብ ገብቶሀል?” አሉት፡፡ “አዎ ጓድ ዋና ፀሀፊ! አብዮታዊው አመራርዎት እንደ ሁሌው በጣም እጅግ በጣም ግልጽ ነው” አላቸው፡፡ ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ፤ የግንባሩን ላብ አሁንም በኮቱ እጅጌ እየጠረገ፡፡ “መልካም! እንግዲያው በፍጥነት ተንቀሳቀስ!” አሉና ጓድ ስታሊን አሠናበቱት፡፡ ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ፤ ወታደራዊ አይነት ሠላምታውን አቅርቦ ሊወጣ ሲል ጓድ ስታሊን ጠሩት፡፡ ወደ ጠረጴዛቸው ቀረብ ብሎ የሚሉትን ለመስማት ወይም የሚሠጡትን ትዕዛዝ ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ “ጓድ ኒኮላይ! አብዮቱም ሆነ እኔ ባንተ ላይ ባለን ጠንካራ እምነት የተነሳ የፓርቲያችን ፖሊት ቢሮ፤ ፓርቲውና አብዮቱን ከአድህሮት ሠርጐ ገብ ሀይሎች ለማድዳት እየወሰደ ባለው ጠንካራ አብዮታዊ እርምጃ መሠረት፣ በፓርቲው የፖሊት ቢሮ ውስጥ ተሰግስገው አብዮታችንን የሚቦረቡሩ እና የምዕራብ አድህሮት ሀይላትና የፂዮናውያን ተላላኪ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ ፀረ አብዮተኞች ስለተደረሠባቸው ለመላው የአለም የሶሻሊስት አብዮተኞች ሁሉ ትምህርት እንዲሠጥ በማሠብ የማያዳግምና አፋጣኝ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ወስኗል፡፡ ይህን ከፍተኛ አብዮታዊ ውሳኔ ለማስፈፀም ደግሞ አንተና የምትመራው ልዩ የሚስጥር የደህንነት ጥበቃ ሀይል ብቻ ከፓርቲያችን የፖሊት ቢሮ ተመርጣችኋል፡፡ ከነገ ጠዋት ጀምሮ እርምጃውን ማስፈፀም ትጀምራለች፡፡ ስራ ከመጀመርህ በፊት እኔ ቢሮ ትመጣለህ፡፡ የፀረ አብዮተኞቹ ስም ዝርዝር ይሠጥሀል፡፡ እስከዛው ድረስ ሠዎችህን አዘጋጅ፡፡” አሉት፡፡ ጓድ ኒኮላይ በመስማማት እራሱን ነቀነቀ፡፡ ልቡ ግን የስታሊን ቀይ በትር የነገ ሠለባዎች እነማን ይሆኑ የሚለውን እያውጠነጠነ ነበር፡፡

ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ፤ ይህንን ተጨማሪ ትዕዛዝ ተቀብሎ ከመውጣቱ በፊት ጓድ ስታሊን በድጋሚ ጠሩትና “እየው ጓድ ኒኮላይ! ታዲያ መዝረክረክና መንቀራፈፍ ብሎ ነገር የለም! ይገባሀል?” አሉት፡፡ ጓድ ኒኮላይ የጓድ ስታሊንን አይንና የፊት ገጽታቸውን ትኩር ብሎ ተመለከተው፡፡ አይናቸው ተጉረጥርጦ የፊት ገጽታቸውም ኮምጨጭ ብሏል፡፡ ይህን ገጽታቸውን መቸና ለምን እንደሚያሳዩ ጥንቅቅ አድርጐ ያውቀዋል፡፡ እናም እንዳዘዙት እንደሚፈጽም አረጋግጦላቸው ከቢሮአቸው ወጣ፡፡ ልክ እሱ እንደወጣ ፀሀፊያቸው ተሠናብታቸው ወጣች፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ሰአታቸውን ተመለከቱ፡፡ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት ሆኖአል፡፡ ከሠባት ደቂቃ በሁዋላ እርሳቸውም የቢሮአቸውን በር መለስ አድርገው፣ በየቢሮው ግራና ቀኝ በተጠንቀቅ የቆሙ ጠባቂዎቻቸው የሚሠጧቸውን ወታደራዊ ሰላምታ እየተቀበሉ ወደ ቤታቸው አመሩ፡፡ ምሳቸውን እንኳ እንዳልበሉ ያስታወሱት ረሀብ መሞርመር ሲጀምራቸው ነበር፡፡ እሱን ለማስታገስ ምግብ መቅመስ ግን ጨርሶ አላማራቸውም፡፡ ለዚህ የሚሆን ጊዜ አሁን የለም፡፡ ማርች 4 ቀን 1953 ዓ.ም ሊጠናቀቅ እየመሸ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ትልቅና ልዩ ረሀብ ሆዳቸውን ሳይሆን መላ የስሜት ህዋሳቶቻቸውን ወጥሮ ይዟቸዋል፡፡ ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ ነገ በጠዋቱ ሲመጣ እርምጃ መውሰድ በጊዜ እንዲጀምር የስም ዝርዝሩ ተዘጋጅቶ ማለቅ አለበት፡፡ ይህን ሲያስቡ ልዩ ረሀባቸው ጨመረ፡፡ እናም ይህን ልዩ ረሀብ ለማስታገስ ተጣደፉ፡፡ ከመኝታ ቤታቸው ውስጥ ባለው የጽህፈት ጠረጴዛቸው ላይ ቁጭ አሉና ከቢሮአቸው ይዘውት የመጡትን ልዩ የማስታወሻ ደብተራቸውን እያገላበጡ ጀምረውት የነበረውን የስም ዝርዝር እንደገና እንደ አዲስ መፃፍ ጀመሩ፡፡ አንደኛ ጓድ ማሊንኮቭ፡፡ ፃፉ፡፡ ምንም እንኳ የተጨበጠ ማስረጃ ልናገኝበት ባንችልም ያቺ የፂዮናውያን ሠርጐ ገብ ቅጥረኛ የሆነችው ይሁዲ ሚስቱ ፖሊና፤ በዶላሩም በምኑም ብላ ደልላው በቅልበሳ ሴራው ውስጥ መነካካቱ አይቀርም ይሆናል፡፡ ስለዚህ እሱ መፃፍ አለበት፡፡ ሁለተኛ ጓድ ሞሎቶቭ፡፡ ጓድ ስታሊን የስም ዝርዝሩን መፃፍ ቀጠሉ፡፡ የማስታወሻ ደብተራቸውን ገለጥ ገለጥ እያደረጉ ትንሽ ካዩ በሁዋላ እርሳሳቸውን አፋቸው ውስጥ ከተው አሰብ አደረጉና ራሳቸውን እየነቀነቁ “ኦው ያ ሞሮን… ሰካራም ካጋኖቪች አሉ፡፡ እናም ፃፉ፡፡ ሶስተኛ ጓድ ካጋኖቪች አራተኛ ጓድ … ድንገት በግራ ደረታቸው ላይ የውጋት ስሜት ተሠማቸው፡፡ በቀኝ እጃቸው የሚወጋቸውን ደረታቸውን እያሻሹ ለመፃፍ ሞከሩ፡፡ ጓድ … የደረታቸው ውጋት ባሠባቸው፡፡ መፃፍ አልቻሉም፤ እርሳሱ ከእጃቸው ወደቀ፡፡ ይህን ጊዜ ሰው እንዲመጣላቸው የመጥሪያ ደወሉን ለመደወል እንደምንም ከተቀመጡበት ለመነሳት ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡ ቀጥሎ ልባቸው ከደረታቸው ውስጥ ፈንድቶ የፈረሰ ያህል እጅግ ሀይለኛ የህመም ስሜት ተሠማቸውና ወለሉ ላይ ክልትምትም ብለው ወድቀው ተዘረሩ፡፡ ያ ሀይለኛ የህመም ስሜት እንደገና ደረታቸውን መታቸው፡፡ ግማሽ ሠውነታቸውና ፊታቸው ጭብጥ ኩምትር አለ፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ለስንት ሰአት ያያል እንደሚቆዩ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በመኝታ ቤታቸው ውስጥ ማንም ሠው አልነበረም፡፡ እናም ሊረዳቸው ወይም እርዳት እንዲያገኙ የሞከረ ሠውም አልነበረም፡፡

ማርት 5 ቀን 1953 ዓ.ም ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ፤ በታዘዘው መሠረት ሠማይና ምድሩ እንደተላቀቀ ገና በጠዋቱ በጓድ ስታሊን ቢሮ በመገኘት የሚሠጡትን የስም ዝርዝር እየተጠባበቀ ነበር፡፡ ጓድ ስታሊን ግን ገና ወደቢሮአቸው እንኳ አልገቡም፡፡ ነገሩ አላምርሽ ያላት ፀሀፊያቸው አንዳንዴ እንደምታደርገው ወደ ቤታቸው ስልክ ደወለች፡፡ ስልካቸው ይጠራል፡፡ ግን የሚመልስ ሰው የለም፡፡ በተደጋጋሚ ሞከረች፡፡ ስልኩ ይጠራል፡፡ የሚመልስ ሠው ግን የለም፡፡ ልቧ ፍርሀት ሲገባው ለግል ጥበቃ ሀላፊያቸው ደውላ ነገሩን አሳወቀችው፡፡ የመኝታ ክፍላቸውን ሲጠብቅ ያደረው የልዩ ጥበቃ አባል ወታደር የመኝታ ቤት በራቸውን መጀመሪያ በቀስታ ቀጥሎ በሀይል አንኳኳ፡፡ የሚከፍትለት ወይም አንዳች አይነት መልስ ማግኘት አልቻለም፡፡ ደግሞ ደጋግም አንኳኳ … አንኳኳ… መልስ ማግኘት አልቻለም፡፡

ይሄኔ በጓድ ስታሊን የመኖሪያ ቤት ሽብር ተፈጠረ፡፡ ተጨማሪ ሽብር የሆነው ደግሞ የጓድ ስታሊንን የመኝታ ቤት ከፍቶ ለመግባት የሚደፍር ሠው መታጣቱ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የመኝታ ቤቱ በር ተከፈተ፡፡ እናም ለድፍን ሠላሳ አንድ አመታት አንድ መቶ ስልሳ ሚሊዮን የሆነውን የሶቪየት ህብረትን ህዝብ ወደር በሌለው ጠንካራ የብረት ክንድ ሰጥ ለጥ አድርገውና አንቀጥቅጠው የገዙት ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን በከፍተኛ የልብ በሽታ ተመተው ወለል ላይ ተዘርረው ሞተው ተገኙ፡፡ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን፤ በሞቱበት የመጨረሻዋ ሶስተኛ ቀን አጠገባቸው የተገኘ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ አሊያም የትግል ጓድ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የአርባ ቀን እድላቸው ስለሆነ አልነበረም፡፡ ሁሉንም ገድለው ስለጨረሷቸው እንጂ፡፡

ከመጀመሪያ ሚስታቸው ከካቶ ሞት በኋላ ያገቧት ናዴዥዳ ለረጅም አመታት ያደረሱባትን ጥቃትና እንግልት መቋቋም ባለመቻሏ ራሷን በመግደል ከመከራ ለመገላገል በቃች፡፡ ያዕቆብ የተባለው የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው የጓድ ስታሊንን ቅጣት ይቀበል የነበረው ገና በለጋነቱ ነበር፡፡ የጓድ ስታሊን አባት ስታሊንን በወጣትነታቸው አንድ እጃቸው እስኪያጥር ድረስ ይደበድባቸው እንደነበረው ሁሉ እሳቸውም ልጃቸውን ያዕቆብን ክፉኛ ይደበድቡት ነበር፡፡

ይሄው ልጃቸው ያዕቆብ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ በወታደርነት ዘምቶ ሲዋጋ በጀርመኖች መማረኩ ሲነገራቸው፣ ጓድ ስታሊን ያዕቆብ የተባለ ልጅ የለኝም ብለው ክደውታል፡፡ ምርኮኛው ያዕቆብ ዛሬም ድረስ አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ በምርኮ እንዳለ ህይወቱ አልፎአል፡፡ ይህን የሰሙት ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን ግን ወዲያውኑ የተማረኩ የሶቪየት ህብረት ወታደሮችና ቤተሰቦቻቸው እንደ ከሀዲ እንዲቆጠሩ አብዮታዊ መመሪያ ሰጡ፡፡ በዚህ መመሪያ መሠረትም የልጃቸው የያዕቆብ ሚስት እንድትታሰርና የስታሊን ቀይ ዱላ እንዲያርፍባት ተደረገ፡፡ ብቸኛ የልጅ ልጃቸውም በአያቷ መመሪያ መሠረት ወላጅ አልባ ለመሆን በቃች፡፡

ጓድ ስታሊን በ1947 ዓ.ም የብጂነየቭ፣ በ1948 ዓ.ም ደግሞ አናሳቭየቭና የተባሉ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን በአብዮታዊ እርምጃ ከአብዮቱና ከቤተሰባቸው ካምፕ ውስጥ እንዲወገዱ አድርገዋል፡፡ ተወዳጅ የነበረችው ሴት ልጃቸው ስቬትላና በድንገት የገባችበት ጠፋ፡፡ ለምን እንዴትና የት ጠፋች ብሎ የፈለገም ሆነ ለመጠየቅ የደፈረ አንድም ሰው አልተገኘም፡፡ በቀጣዩ አመት በ1949 ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር ተፈፀመ፡፡

ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን ጠርተው በጆሮአቸው የሆነ ነገር ሹክ ብለው የላኳቸው ሁለት የኬጂቢ የደህንነት ወታደሮች፤ የአጐታቸው ልጅ የሆነችውን የኪራን የመኝታ ቤት በር በጠዋት አንኳኩ፡፡ ኪራ ወደ ቤቷ ዳግመኛ የተመለሠችው ለአራት አመታት ከእስር ቤት እስር ቤት እየተፈራረቀባት ከፍተኛ ስቃይ ከተቀበለች በኋላ ነበር - በ1952 ዓ.ም፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ለቅርብ ቤተሠቦቻቸው ያልመለሱትን ቀይ ዱላቸውን ለቅርብ ወዳጆቻቸውና ጓዶቻቸው ይቆጥቡታል ተብሎ ጨርሶ አይጠበቅም ነበር፡፡

ባለቤታቸው ናዴዥዳ ራሷን ከገደለች በሁዋላ የጓድ ስታሊን የቅርብ ወዳጆች የነበሩት ሁለት ሠዎች፡- ልጃቸው ስቬትላናና የፓርቲው የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው ጓድ ኪሮቭ ነበሩ፡፡ በተለይ ከጓድ ኪሮቭ ጋር የነበራቸው ቅርበትና ወዳጅነት ልዩ ነበር፡፡

በ1934 ዓ.ም የተካሄደው አስራ ሠባተኛው የኮሙኒስት ፓርቲው ኮንግረስ ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ድንገት እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ በዋናነት የመሩት የሠፈራና ሌሎች የግብርና ፕሮግራሞች በህዝቡ ላይ በተለይ ደግሞ በአርሶ አደሩ ላይ በፈጠሩት መጠነ ሠፊ እልቂትና ከፍተኛ ችግር የተነሳ፣ የተወሰኑ ጉባኤተኞች ጓድ ስታሊን ከስልጣናቸው ወርደው በምትካቸው የቅርብ ወዳጃቸው ጓድ ኪሮቭ የፓርቲው ዋና ፀሀፊ እንዲሆኑ ጥያቄአቸውን በግልጽ አቀረቡ፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንም በጉባኤተኞቹ የቀረበውን ይህን ጥያቄ አጠገባቸው ተቀምጦ ከሳቸው ጋር ጉባኤውን ሲመራ የነበረውን የጓድ ኪሮቭን ትከሻ በአድናቆት አይነት መታ መታ እያደረጉና በዝነኛው የ”ጆርጂያውያን” ማራኪ ፈገግታ አጅበው አስተናገዱት፡፡ ልባቸው ግን የጓድ ኪሮቭን ነገር “ይቺ ባቄላ ካደረች…!” የሚለውን አባባል በከፍተኛ ፍጥነትና ትኩረት እያውጠነጠነ ነበር፡፡ የፓርቲው ኮንግረስ ከተጠናቀቀ አራት ወራት በሁዋላ ዲሴምበር 1 ቀን 1934 ዓ.ም ሌኒንግራድ በሚገኘው የጓድ ኪሮቭ ቢሮ ኮሪደር ላይ ኒኮላየቭ የተባለ ፀጉረ ልውጥ፤ ማካሮቭ ሽጉጡን ጫማው ውስጥ በካልሲው ደብቆ፣ እንደ ስልጡን ዘብ በቀስታ እርምጃ ሲንጐራደድ ታየ፡፡ መደበኛዎቹ የጓድ ኪሮቭ ጠባቂዎች የአለቃቸውን ቢሮ ለቀው መኪናውን እየጠበቁ እንዲቆዩ በጊዜ ተነግሯቸው፣ ወደ መኪና ማቆሚያው ቦታ ሄደዋል፡፡

ከጠዋቱ አምስት ሰአት ሊሆን ስምንት ደቂቃ እንደቀረው፣ ሁለት የሽጉጥ ተኩስ ድምጽ ተሠማ፡፡ ጓድ ኪሮቭ ተቀምጦበት ከነበረው የቢሮ ወንበሩ በጀርባው ለጠጥ ብሎ አንገቱ የግራ ትከሻውን ተደግፏል፡፡ ልክ በሁለቱ አይኖቹ ትክክል ግንባሩ ላይ በተበሱት ቀዳዳዎች ደሙ ያለ ማቋረጥ ይፈሳል፡፡

ተኩሱ ከተሠማ አስራ ሁለት ደቂቃ በሁዋላ ጓድ ኪሮቭ የአሜሪካ ኤምፔሪያሊዝምና የጺዮናውያን ቅጥረኛ በሆነው ኒኮላየቭ መገደሉን ስልክ ተደውሎ ለጓድ ስታሊን ተነገራቸው፡፡ ጓድ ስታሊንም የደቂቃ እድሜ እንኳ ሳያጠፉ የራሳቸውን መርማሪዎች፣ ዳኞችና ገዳይ ስካዶችን አስከትለው ከሞስኮ ወደ ሌኒንግራድ ተፈተለኩ፡፡ ነፍስ ገዳዩ ኒኮላየቭ የጓድ ስታሊን መምጣት ሲነገረው እፎይ ብሎና ወዲያውኑ እንደሚለቀቅ እርግጠኛ በመሆን በቁጥጥር ስር አውለው ይጠብቁት የነበሩትን የኬጂቢ ወታደሮች እየተሳደበና እያስፈራራ ነበር፡፡ ጨርሶ መውጪያ በሌለው ጉድጓድ ውስጥ መግባቱና የእሱ ነገር ያከተመለት ጉዳይ መሆኑን የተረዳው ጓድ ስታሊን ለብቻው ወስደው ጓድ ኪሮቭን እንዲገድል ያዘዙትና ሁሉን ነገር ያቀነባበሩለት የፓርቲው የፖሊት ቢሮ አባላት የሆኑት ጓድ ካሚኒየቭና ጓድ ዚኖቪየቭ መሆናቸውን እንዲያጋልጥ ፊቱን በቃሪያ ጥፊ እየወለወሉ ሲያዙት ነበር፡፡

ጓድ ስታሊን ያዘዙትን ለማድረግ ከመስማማቱ በፊት ቀደም ብሎ የጓድ ስታሊን ልዩ ትዕዛዝ ነው ብሎ ጓድ ኒኮላይ ያዞቭ የሰጠውን መመሪያና ቃል የተገባለትን የማዕረግ እድገት በጭንቀት እየለፈለፈ ሊያስታውሳቸው ሲሞክር፤ ትንሽ ፈንጠር ብለው ቆመው የነበሩትን የኬጂቢ ወታደሮች ጠርተው፤ ከጓድ ኒኮላይ ያዞቭ ቢሮ ውሰዱትና ሁለት ሰአት አቆይታችሁ አምጡት ብለው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከሁለት ሰአት ቆይታ በሁዋላ ሲመጣ ኒኮላየቭ ሰው ሳይሆን የሠው ቲማቲም ሆኖ ነበር፡፡

ቀትር ላይ የቀረበው የቴሌቪዥን ዜና ደግሞ ኒኮላየቭ፤ ጓድ ኪሮቭን የአሜሪካው ሲአይኤና የጺዮናዊት እስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ቅጥረኞችና የፓርቲው የፖሊት ቢሮ አባላት በሆኑት በጓድ ካማኒየቭና በጓድ ዚኖቪየቭ ትዕዛዝ እንደገደለ ያደረገውን ኑዛዜ አቀረበ፡፡

ግማሽ ሠአት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ጓድ ካማኒየቭና ጓድ ዚኖቪየቭ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደረገ፡፡ በማግስቱም ገዳዩ ኒኮላየቭ ብቻ ሳይሆን ሚስቱ፣ ወንድሙና የወንድሙ ሚስት ሳይቀር በስታሊን ቀይ ዱላ ተመቱ፡፡

ከጥቂት ወራቶች በሁዋላም “የአብዮቱ ኮከቦች” ይባሉ የነበሩት ጓድ ካማኒየቭና ጓድ ዚኖቪየቭ ከሲአይኤና ከሞሳድ ጋር በመተባበር ጓድ ኪሮቭ እንዲገደል እንዳደረጉ “የእምነት ቃላቸውን” ሠጡ ተብለው በቴሌቪዥን ቀረቡና በስታሊን ቀይ ዱላ ተደብድበው እንዲገደሉ ተወሰነባቸው፡፡ ጓድ ካማኒየቭና ጓድ ዚኖቪየቭ የጓድ ስታሊን ታማኝ ደጋፊና ወዳጆች ነበሩ፡፡

የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን የልብ ወዳጆች ነገር ከተነሳ መወሳቱ የማይቀረው የፓርቲው የፖሊት አባል የነበረው የጓድ ቡካሪን ነገር ነው፡፡ ጓድ ቡካሪን የስታሊን የቅርብ ወዳጅና አጋር የነበረ፣ ጓድ ስታሊን “የአብዮቱ ምርጥ ልጅ” እያሉ ዘወትር ያሞካሹትና ያደንቁት የነበረ ጓድ ነው፡፡ ድንገት ግን የጓድ ስታሊን ቁጣ ሠለባ ሆነና የፈጠራ ክስ ተዘጋጅቶለት ለፍርድ ቀረበ፡፡

ሌሎቹ የፖሊት ቢሮ አባሎች ከሱ በፊት የተጐነጩት የሞት ጽዋ ለሱም እንደማይቀርለት የተረዳው ጓድ ቡካሪን፤ ለጓድ ስታሊን ደብዳቤ በመፃፍ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው - “ጓድ ዋና ፀሀፊ፡- መቸም ሁሉን ነገር አንተ በሚገባ ታውቃለህ፡፡ በአብዮቱና በአብዮቱ አላማዎች ዛሬም ድረስ እምነቴ ጠንካራ ነው፡፡ ለፓርቲውና ለአመራሩም ቢሆን ያለኝ ታማኝነት ጨርሶ የማያወላውል ነው፡፡ የሞት ፍርድ የሚፈረድብኝ ከሆነ በጥይት ተደብድቤ ከምገደል በእስር ቤት ክፍሌ ውስጥ መርዝ ጠጥቼ እንድሞት እንድትፈቅድልኝ በቀደመው የትግል አብዮታዊ ወዳጅነታችንና በአብዮቱ ስም እማፀንሀለሁ፡፡” የሚል፡፡ ጓድ ስታሊን ግን የቡካሪን ጥያቄ ነገሬም ሳይሉት ቀሩ፡፡ ጓድ ቡካሪን የሞት ፍርድ ተፈረደበትና በጥይት ተደብድቦ ተገደለ፡፡

የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንን ሞትና አሟሟታቸውን በተመለከተ የመጨረሻ ጥያቄ የሚሆነው የሀኪም እርዳታን የተመለከተው ነው፡፡ “ምነው ጓድ ስታሊን የሀኪም እርዳታ ሳያገኙ ቀሩሳ?” መልሱ ቀላል ነው፡፡ የዶክተሮች ሴራ በሚል ምርጥ ሀኪሞችን ሁሉ ፈጅተውና እስር ቤት አጉረው የትኛው ሀኪም መጥቶ ያክማቸው?

የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን የመጨረሻዋ ቀን ማርች 5 ቀን 1953 ዓ.ም ያለፈው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንን በማስመልከት ብዙ ሠዎች ብዙ ነገር ተናግረዋል፡፡ ከሁሉ የበለጠውን አሪፍ ንግግር የተናገረችው ግን እናቱ ናት፡፡ ከመሞቷ በፊት ያደረገውን ድርጊት ሁሉ ለመታዘብ የበቃችው እናቱ፤ በመጨረሻ የተናገረችው እንዲህ ብላ ነበር፡- “ልጄ ሆይ፤ ቄስ ሆነህ በሆኖ ኖሮ ላንተም ለሌሎቹም መልካም በሆነ ነበር፡፡”

 

 

Read 3511 times Last modified on Friday, 13 July 2012 16:56