Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 12:44

የጓድ ዋና ፀሐፊ ጆሴፍ ስታሊን የመጨረሻ ሦስት ቀናት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በግብታዊነት የፈነዳ አብዮት ነበር ይባላል፡፡ ይህን በግብታዊነት የፈነዳ የተባለውን አብዮት በግንባር ቀደምትነት ለመምራት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እርስ በርስ መሻኮትና መተባበር ጀምረው ነበር፡፡ የወታደሩ ሃይል ግን ገና በጠዋቱ የመንግሥቱን ስልጣን ለመቆጣጠር ቻለ፡፡ ወታደሮቹ በማዕረግ ከፍ ያላሉ በእውቀትም ጨርሰው ያልገፉ ነበሩ ይባላል፡፡ ደርግ የመንግሥትን ስልጣን የያዘው ታሪክና ህዝብ የጣሉበትን ከፍተኛ ሃላፊነት ለመወጣትና ያን ግብታዊውን አብዮት በግንባር ቀደምትነት ለመምራት እንደሆነ ዘወትር ይናገር ነበር፡፡

ደርጉን የሚቃወሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የጦር ሃይሉ፣ የመንግሥትን ስልጣን በአቋራጭና በታጠቀው የጦር መሳሪያ ከህዝቡ ላይ ነጠቀ እንጂ ከህዝብ የተጣለበት አንዳችም ሃላፊነት የለም ይሉ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ከደርግ ጋር አይንና ናጫ ነበሩ፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት የነበራችሁ አለያም የሶሻሊስት አብዮት ታሪኮችንና እነዚህን አብዮቶች የመሩ አብዮታዊ ጓዶች የፃፏቸውን “ተራማጅ” ፅሁፎች ያነበባችሁ ወይም ደግሞ የሰማችሁ ሁሉ ጓድ ስታሊንንና ከላይ የተጠቀሰውን አብዮታዊ መፈክር በደንብ ታውቃላችሁ ማለት ነው፡፡

ጓድ ስታሊን፤ ከጓድ ሌኒን ሞት በሁዋላ ከ1922 እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ ለሰላሳ አንድ አመታት የሶቪየት ህብረት ኮሙኒስት ፓርቲንና ሶቪየት ህብረትን የመሩ አብዮታዊ ጓድ ናቸው፡፡ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን የተወለዱት በ1879 ዓ.ም ጐሪ በተባለች የጆርጂያ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ ጓድ ስታሊን የፓርቲው አባል ከመሆናቸው በፊት ይጠሩ የነበሩት ኢወስብ ድዡጋሸቪሊ በሚል ስም ነበር፡፡

ጓድ ዋና ፀሃፊ ስታሊን፤ የስልጣናቸው ነገር ሞታቸው ነው፡፡ በስልጣናቸው ከመጣ ለማንም ቢሆን ጨርሶ አይመለሱም፡፡ ከጓድ ሌኒን ሞት በሁዋላ የኮሙኒስት ፓርቲውን የዋና ፀሐፊነት ስልጣን እንደተቆጣጠሩ፣ ተፎካካሪና ተቀናቃኞቻቸው የነበሩትን ስመጥር የሶቪየት ህብረት ግንባር ቀደም ታጋይ አብዮተኞች እነ ሊዮን ትሮትስኪን፣ እነ ግሪጐሪ ዚኖቭየቭን፣ እነ ሌቭ ካሚኔቭን፣ እነ ኒኮላይ ቡካሪንንና እነ አሌክሲ ሪኮቭን ያለ አንዳች ርህራሄና ማመንታት በመግደል አስወግደዋቸዋል፡፡

ለጓድ ስታሊን ከሁሉም ተቀናቃኞችና ተፎካካሪዎቻቸው ውስጥ እንደ ሊዮን ትሮትስኪ በእጅጉ የሚፈሩት አልነበረም፡፡ ሊዮን ትሮትስኪ በብሩህ አዕምሮውና በላቀ የእውቀት ደረጃው ጓድ ስታሊንን በእጥፍ ድርቡ ያስከነዳቸው ነበር ይላሉ፤ የኮሙኒስት ፓርቲው ጓዶች፡፡ በዚህ የተነሳም ሊዮን ትሮትስኪን ስልጣኔን ይነጥቀኛል እያሉ አጥብቀው ይፈሩትና አምርረው ይጠሉት ነበር፡፡ በ1920 ታዲያ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን፤ ሊዮን ትሮትስኪን ከሶቭየት የኮሙኒስት ፓርቲ እንዲባረር አደረጉት፡፡ ከፓርቲው መባረሩ ብቻ በቂ አይደለም በሚልም ከአባት ሀገር ከታላቁ የሶቪየት ህብረት እንዲባረር አስደረጉት፡፡

በጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ከአባት ሀገር የተባረረው ሊዮን ትሮትስኪም በሜክሲኮ እስከ 1940 ዓ.ም ድረስ በስደት ኖረ፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ግን በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሰው ሀገር የሚኖር ቢሆንም የሊዮን ትሮትስኪ ነገር እንቅልፍ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ የፓርቲው ጓዶችማ ኧረ እንዲያውም “የቀን ቅዠት ሆኖ እያባነነና እያስበረገጋቸው አብዮታዊ ስራቸውን በአብዮታዊ ወኔና ተነሳሽነት ግለቱን እንደጠበቀ ማከናወን አቅቷቸዋል” እያሉ በሹክሹክታ ያወሩ ነበር፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ግን እንደ አንድ ታጋይ ግለሰብ፣ በአብዮታዊ ቁመናቸው ላይ የጥገኛ አስተሳሰብ እንዳይፈጥርባቸው መስጋታቸውን በኮሙኒስት ፓርቲው የፕሬዚዲየም ወይም የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ በራስ ተነሳሽነት ግለሂስ ካካሄዱ በኋላ፤ ለችግሩ ወቅቱንና አባት ሀገር የተያያዘውን እጅግ ፈጣንና ባለ ሁለት አሀዝ ተቀናቃኞችን የማስወገድ ግስጋሴ ከግምት ውስጥ ያስገባ ፈጣን ቅፅበታዊና የማያወላዳ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሆን የመፍትሄ እርምጃ እንደሚወስድ በከፍተኛ ወኔ አስታወቁ፡፡

የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን የስራ አፈፃፀም በእውነቱ በእጅጉ የሚያስገርም ነበር፡፡ በሊዮን ትሮትስኪ ላይ ለዚያውም በሰው ሀገር በስደተኝነት እያለ ስለሚወስዱት አብዮታዊ እርምጃ ለፓርቲው የፖሊት ቢሮ ባሳወቁ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በ1940 ዓ.ም፤ ወደር በሌለው ጭካኔ በመጥረቢያ አስፈልጠው አስገደሉት፡፡ በሞስኮ፤በሌኒንግራድና በቤሎ ሩሲያ ሚንስክ ከተሞች ውስጥ ይገኙ የነበሩ የየከተሞቹ የኮሙኒስት ፓርቲው መሰረታዊ ድርጅቶች ከፍተኛ ሃላፊዎችና መሪ ካድሬ ጓዶችም፤ ከትሮትስኪ ጋር በሚስጢር በመገናኘት የጠራ አብዮታዊ የትግል መስመር ባለመያዝና በትግል ወኔ መቀዛቀዝ ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠርጥረውና የቀረቡበት አብዮታዊ ፍርድ ቤትም በተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛነታቸውን በማረጋገጡ የዚያኑ እለት አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደረገ፡፡ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎችም ወደ ሳይቤሪያና ሌሎች የግዞት ሥፍራዎች ለከባድ የጉልበት ስራ ተጋዙ፡፡

በቀጣዩ የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ በትሮትስኪና በሌሎች የፓርቲው አባሎች ላይ ስለተወሰደው ፈጣን እርምጃ ጓድ ዋና ፀሐፊ ስታሊን ባቀረቡት ሪፖርት፤ “በተለይ በትሮትስኪ ላይ ቆራጥ አብዮታዊ ጓዶች የመንገድ ርቀትና የሰው ሀገር ባእድነት ሳይበግራቸው፤ ለአብዮታዊው የትግል መስመርና ለአባት ሀገር ባላቸው ዲካ የለሽ ፍቅር፤ በከፍተኛ ፅናትና አብዮታዊ ወኔ ፊት ለፊት ተጋፍጠው በማለፍና መኖሪያ ቤቱን ሰብረው በመግባት፣ የሰፊው ህዝብ ጠላት የሆነውን አድሃሪውን ትሮትስኪን ለሌሎች እሱን መሰል አድሃሪያንና ለእናንተም አብዮታዊና ቀስቃሽ የሆነ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል በሚል መልኩ ከታጠቁት የጦር መሳሪያ ይልቅ እዚያው ባገኙት መጥረቢያ ጨፍጭፈውና ፈልጠው ገድለውታል” ሲሉ መጥረቢያውን ስንት ጊዜ እንደሰነዘሩ በአሀዝ ጭምር በማስደገፍ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ በሪፖርታቸው ማጠቃለያ ላይ አንድ ዋና ቁም ነገር ተናግረው ነበር፡፡ በአድሀሪያን በራዦች፣ ከላሾችና ጐታቾች ላይ የሚወሰዱት እንዲህ አይነት ወሳኝ አብዮታዊ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ለሶቪየት ህብረት የጥበብና የእውቀት አለም፣ የኮሙኒስት ፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ ፀሃፊና ዋና የርዕዮተ አለም ሰው የሚባለውን ጓድ አንድሬ ዝዳኖቭን፤ ለጦር ሃይሉ ለፓርቲውና ለተቀረው ደግሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርና የአስፈሪው የደህንነት ሃይል መሪ የሆነውን ጓድ ቬራን ከነሙሉ ሃይልና ጉልበታቸው አሰማርቶ ለቀቃቸው፡፡

የጓድ አንድሬ ዝዳኖቭና የጓድ ቬራ ገዳይ ስኳዶች፤ የግድያና የሽብር ዘመቻቸውን ሲያካሂዱ አዘውትረው የሚያሰሙት አንድ መሪ መፈክር ነበር፡፡ “እንደ ትሮትስኪ ያሉ ከላሽና በራዥ አድሃሪ የአብዮቱ ጠላቶችን በስታሊን ቀይ በትር እንደመስሳቸዋለን! የስታሊን ቀይ በትር የፀረ አብዮተኞች ምስ ነው!” እያሉ ይፎክሩ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለት እጅግ ጨካኝና አስፈሪ ጓዶች ያደራጇቸው ገዳይ ስኳዶቻቸው፣ ከከፍተኛው የፓርቲ፣ የመንግሥትና የጦር ሃይሉ ባለስልጣኖች አንስቶ እስከ ተራው ህዝብ ድረስ የአብዮቱ ሳይሆን የጓድ ስታሊን ተቃዋሚ ናቸው ወይም ደግሞ ገና ለገና ሊቃወሙ ይችላሉ ወይም ሊቃወሙ ያስባሉ ያሏቸውን ሁሉ በነጠላና በጅምላ እየለቀሙ በከፍተኛ ጭካኔ የስቃይ ሰለባ በማድረግና በመግደል አስከሬናቸውን በየከተሞቹ አውራ ጐዳናዎች ላይ ይጥሉ ነበር፡፡

እንግዲህ ደርግም ተቃዋሚዎቹንና ተፎካካሪዎቹን ሁሉ ያለርህራሄና ፍርድ ለመፍጀት እንዲመቸው “ለትሮትስካይቶች ውርውር የስታሊን ቀይ በትር” የሚለውን የስታሊን የሽብር ዘዴ በመኮረጅ ነው ተግባራዊ ያደረገው፡፡ ያው እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ትሮትስካይት የሚባል አብዮተኛ ታጋይ አልነበራትም፡፡ ወታደራዊ ደርግ ትሮትስካይት የሚል ስም የሰጠው በዋናነት ለኢህአፓና ለአባላቶቹ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ደርግ በኢህአፓና በአባላቶቹ ላይ የተጠቀሠውን መፈክር እያሠማ ከፍተኛ የሆነ ሽብር (ቀይ ሽብር ይለዋል) በመክፈት አንድ ሙሉ ትውልድ ወደር በሌለው ጭካኔ ለመፍጀት ቻለ፡፡ ደርግ አሪፍ ኮራጅ መሆኑን ያስመሠከረው መፈክር በማውጣት ብቻ ሳይሆን በአፈፃፀሙም ጭምር ነበር፡፡

ወታደራዊው ደርግ በስተሁዋላ ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ የተባለ አብዮታዊ የኮሙኒስት ፓርቲ አቋቁሞ ነበር፡፡ የዚህን ፓርቲ አደረጃጀትና አመራርም ለመኮረጅ የተሞከረው ከሶቪየት ህብረት የኮሙኒስት ፓርቲ ነው፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር የነበሩት ጓድ መንግስቱ ሀይለማርያም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲም ዋና ፀሀፊ ነበሩ፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ መንግስቱ ሀይለማርያም፤ ከጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ጋር በሁለት ነገሮች ብቻ ይመሳሠላሉ፡፡ ሁለቱም የየፓርቲያቸው ዋና ፀሀፊ መሆናቸውና ተቃዋሚና ተፎካካሪያቸውን ሁሉ ከፍ ባለ ሽብርና ግድያ ፈጅተው መጨረሳቸው ነው፡፡ የሚለያዩበት አንድ ትልቅ ጉዳይ ደግሞ ጓድ ዋና ፀሀፊ መንግስቱ ሀይለማርያም አንድ ሙሉ ትውልድን ፈጅተውና ሀገራቸውን በሁሉም መስክ ወደ ጥልቅ መቀመቅ ከተው፤ ከፍጅት በተረፉ ተቃዋሚዎቻቸው ከስልጣናቸው ተባረው ወደ ሌላ ሀገር ሲሰደዱ፤ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ግን ተቃዋሚና ተፎካካሪዎቻቸውን ሁሉ በገፍና በጅምላ ገድለው ቢጨርሱም አባት ሀገር ሶቪየት ህብረትን ከተራ የገበሬ ሀገር ወደ ኢንዱስትሪና የኑክሊየር ባለቤት ታላቅ ሀገርነት መቀየር ችለዋል፡፡

የሁለተኛው የአለም ጦርነት ለአባት ሀገርና ለጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን እጅግ ፈታኝ ጊዜ ነበር፡፡  በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐችን ህይወት በልቶ ኢኮኖሚውንም አንኮታኩቶት አልፏል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነትና በጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን የብረት ክንድ አመራር አባት ሀገር ሶቪየት ህብረት ከጦርነቱ ፍፃሜ በሁዋላ መልሶ ለማንሠራራት ችሏል፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ከጦርነቱ በሁዋላ የምስራቅ አውሮፓንና አንዳንድ የእስያ ሀገራትን በአባት ሀገር ተጽዕኖ ስር ለማስገባት ባሳዩት እጅግ ብልጥነት የተሞላውና ቆራጥ አመራር፤ ናዚ ጀርመንን ለመደምሠስ በተደረገው ፈታኝ ትግል ወቅት ወዳጅና ተባባሪ የነበሩ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የመሳሠሉ ሀገራት ወዳጅነትና ተባባሪነታቸውን በመተው፤ የምዕራቡን አለም የአድህሮት ሀይሎች በመምራት በአባት ሀገርና በመሪው በጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ላይ ቀዝቃዛ ጦርነትን አወጁ፡፡ አባት ሀገርና ጓድ ዋና ፀሀፊ ግን ለዚህ የአድህሮት ሀይሎች ቀዝቃዛ ጦርነት ጨርሶ ሊበገሩ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በመካከለኛው ምስራቅ፤ በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ የአባት ሀገርንና የሶሻሊስት አብዮቱን ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ቻሉ፡፡

በእርግጥ የሁለተኛው የአለም ጦርነትና በሁዋላ የቀጠለው ቀዝቃዛው ጦርነት ምንም አይነት ጉዳት አላስከተለም ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም እጅግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ በማቃወስ፤ አብዮቱንና አባት ሀገርን ያለ ቆራጡ መሪ ለማስቀረት ሞክሯል፡፡

ገና በሀያ አንድ አመት አፍላ የወጣትነት እድሜያቸው በህቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የጆርጂያ አብዮታዊ ድርጅቶችን በተራ ታጋይነት በተቀላቀሉበት ጊዜ “የትግሉ ነው ህይወቴ” የሚለውን አብዮታዊ መዝሙር እየዘመሩ ታግለው ሲያታግሉ የኖሩት ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ግን ለገጠማቸው የጤና ቀውስ እንኳን እጃቸውን ፊታቸውን ሊሠጡት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡

1953 አ.ም ግን ገደ ቢስ አመት ነበር፡፡ ይህ አመት ለአብዮቱና ለአባት ሀገር በእርግጥም መጥፎና ውቃቢ ቢስ አመት ነበር፡፡ የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ጤንነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ በግልጽ ታየ፡፡ ይህን የጓድ ዋና ፀሀፊ ጤንነት በእጅጉ መዛባት የተገነዘቡ የኮሙኒስት ፓርቲው አንዳንድ አባላት፤የምዕራቡን የአድህሮት ሀይሎች በተለይ ደግሞ የአሜሪካንና የእንግሊዝን ኢምፔሪያሊዝም ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሚያደርጉ በይፋ ገልፀው ነበር፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንም ቢሆን ጤናቸው በከፍተኛ ሁኔታ መዛባቱንና ከእንግዲህም የሚቀራቸው ጊዜ እጅጉን ውስን መሆኑን በመረዳታቸው በሚቀራቸው ጊዜ የተለመደውን ብልህ፤ አርቆ አስተዋይና ቆራጥ አብዮታዊ አመራር መስጠት እንደሚገባቸው ተገንዝበውት ነበር፡፡ እናም ረዘም ያለ አብዮታዊ ጊዜያቸውን በመውሰድና ከራሳቸው ጋር በአብዮታዊ ጥሞና በመምከር፤ በቅድሚያ የሚወሠዱ እርምጃዎችን ዝርዝር በአምስት ገጽ ጽፈው ማዘጋጀት ቻሉ፡፡ በቅድሚያ የተወሰደው አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት አብዮታዊ እርምጃ፤ የፖለቲካ ጭቆናውን ከመቸውም ጊዜ በላይ ማጥበቅ ነበር፡፡ ይህንን አብዮተዊ እርምጃ በዋናነት እንዲያስፈጽምም በዚህ ጉዳይ የተካበተ ልምድ ያለው ጓድ አንድሬ ዝዳኖቭ፤ ከጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተሠጠው፡፡ እርሱም የተሠጠውን ግዳጅ በተለመደ ትጋቱና ጭካኔው የአፈፃፀም ብቃቱን አስመሠከረ፡፡

የኮሙኒስት ፓርቲውና የመንግስት የሚዲያ አውታሮች በሙሉ ፓርቲው በጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን መሪነት ያከናወናቸውን ስኬቶችና ጓድ ዋና ፀሀፊ የአብዮቱና የኮሙኒስት ፓርቲው ማዕከል መሆናቸውን ያለ መታከት እንዲዘግቡና ህዝቡን እንዲያስገነዝቡ ተደረገ፡፡

በአባት ሀገር ውስጥ የሚገኙ ሳይንቲስቶችና ሌሎች ምሁራን፤የኪነጥበብ ሰዎች ወዘተ-- በሚያከናውኑት የሳይንስ የድራማ፤ የታሪክ፤ የስነጽሁፍ፤ የስነ ጥበብና የሙዚቃ ስራዎች ሁሉ የኮሙኒስት ፓርቲውንና የመሪውን የጓድ ዋና ፀሀፊን ሚና ከሁሉም ነገር በላይ አጉልተው እንዲያሳዩ ተደረገ፡፡

ከጓድ አንድሬ ዝዳኖቭ በመቀጠል ተጠርቶ በጓድ ዋና ፀሀፊ ቀጭን ትዕዛዝ የተሠጠው ለጓድ ቤራ ነበር፡፡ የፖለቲካ ጭቆናውን ከመቸውም ጊዜ በላይ ማጥበቅ የሚለው የጓድ ዋና ፀሀፊ አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት አብዮታዊ ትዕዛዝ፤ ለጓድ ቤራ ሌላ ተጨማሪ ማብራሪያ የማያስፈልገው አጭር፤ ግልጽና ቀላል ትዕዛዝ ነበር፡፡ በከፍተኛና እጅግ በሚያረካ የአፈፃፀም ብቃት ግዳጁን ተወጥቶ የጓድ ዋና ፀሀፊን አንጀት እንደሚያርሠው፤ “ጨርሶ ሀሳብ አይግባዎ ጓድ ዋና ፀሀፊ! ይህ ጥርሴን የነቀልኩበት ስራዬ ነው፡፡ እርስዎስ እኮ አሳምረው ያውቁታል፡፡ በዚያ ላይ ከየትም አንስተው ለመሪው ፓርቲያችን የፕሬዚዲየም (የፖሊስ ቢሮ ወይም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ) አባልነት ያበቁኝ ውለታስ ቢሆን እንዲህ በቀላል ተከፍሎ ያልቃልን?” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል፡፡

የብርሀን በሚባል ፍጥነትም የነገ አናርኪስት፤ የወደፊት ትሮትስካይት በራዥና ከላሽ የሚል የወንጀል ስያሜ በመስጠት በሺ የሚቆጠሩ የፓርቲ፤የመንግስትና የጦር ሀይል አባሎችን፤ ወጣትና አዛውንት ዜጐችን ገደለና የቀሩትን በእስር ቤቶችና የግዞች ጣቢያዎች አጎራቸው፡፡ የኮሙኒስት ፓርቲው ባለስልጣናት የፖሊት ቢሮ አባሎችም ሳይቀሩ በጓድ ቤራ የሽብር እርምጃ በከፍተኛ ፍርሀት ራዱ፡፡ እነዚህ የፖሊት ቢሮ አባላትና ከፍተኛ የጦር ሀይሉ መኮንኖች በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ ወድቀውና እንደ ህፃናት ልጆች በከፍተኛ ሁኔታ ተሸብረው መጠጊያና ከለላ ፍለጋ በእርሳቸው ዙሪያ አለመጠን ሲሽከረከሩ ያስተዋሉት ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ በጓድ አንድሬ ዝዳኖቭና በጓድ ቤራ የግዳጅ አፈፃፀም በእጅጉ መርካታቸውን ከገለፁላቸው በሁዋላም ይህ አመርቂ የስራ አፈፃፀም ግለቱን እንደጠበቀ እንዲቀጥል አዘዙ፡፡

የ1953 ዓ.ም የጃንዋሪ ወር የመጨረሻ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ በልዩ ሀኪሞቻቸው አማካኝነት ጠቅላላ የጤንነት ምርመራ አደረጉ፡፡ ሀኪሞቹም በጤንነታቸው ዙሪያ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም ለክፉ የሚሠጡ እንዳልሆኑ ነገሯቸው፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ግን ሀኪሞቹን አላመኗቸውም፡፡ ረጅም ጊዜ እንደሌላቸውና ከጊዜ ጋር አብዮታዊ እሽቅድምድም መግጠም እንዳለባቸው ወስነዋል፡፡

የጓድ ዝዳኖቭና የጓድ ቤራ የሽብር ዘመቻም ልክ እንደታዘዙት አብዮታዊ የአፈፃፀም ግለቱን ጠብቆ እንደቀጠለ ነበር፡፡ የፓርቲው የመንግስትና የቀዩ ጦር ከፍተኛ ባለስልጣናትም ከሽብሩና ከፍጅቱ ለማምለጥ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንን ዙሪያቸውን መክበባቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንም በዙሪያቸው የከበቡዋቸውን ባለስልጣኖች መልካም ወይም የተሻለ የጤንነት ሁኔታ ከእርሳቸው ደካማ ጤንነት ጋር እያወዳደሩ “ነገና ከነገ ወዲያ እንዲያ እድሜዬን ሙሉ የታገልኩበትንና የለፋሁበትን አብዮቱንና የመሪነት ስልጣኔን ትቼላቸው የምሄደው ለእነዚህ ትናንሽ ሠዎች እኮ ነው!” በማለት በከፍተኛ ሁኔታ መቆጨትና ማዘን ጀመሩ፡፡ ይህ የሀዘንና የቁጭት ስሜት በፈጠረባቸው ተጽዕኖ አማካኝነትም ዙሪያውን በከበቧቸው ከፍተኛ ባለስልጣኖች መካከል እንደሆኑ ድንገት ሻማ ወይም ባለ ከፍተኛ ሀይል የኤሌክትሪክ አምፑል መሆን አሠኛቸው፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ብዙውን ጊዜ ምኞት ተመኝተው አያውቁም፡፡ ማድረግ ወይም መሆን የሚፈልጉትን ያደርጉታል እንጂ፡፡ እናም ሻማ ወይም የኤሌክትሪክ አምፑል መሆን አሠኛቸው - የእርሳቸውን መጠጊያና ከለላ ፈልገው ዙሪያቸውን የከበቡዋቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ልክ እንደ እሳት ራት በሻማው አሊያም በኤሌክትሪኩ አምፑል እየተቃጠሉና ጠሽ እያሉ አንድ ባንድ ሲወድቁ ለማየት፡፡

ይህ ድንገተኛ ፍላጐታቸው በእጅጉ አስደሠታቸው፡፡ ወዲያውኑም ቀደም ብለው በሁለት ገጽ ጽፈው አዘጋጅተውት የነበረውን በአስቸኳይ የሚወሰዱ አብዮታዊ እርምጃዎች ዝርዝር አጣጥፈው የጠረጴዛቸው መሳቢያ ኪስ ውስጥ ከተቱና አጀንዳቸውን ገልጠው አዲሱን ይህን ውሳኔአቸውን “እጅግ በጣም አስቸኳይ!” የሚል ርዕስ በመስጠት ፃፉት፡፡

ያን እለት ምሽት ይህን እጅግ አድርጐ ያስደሠታቸውን አዲስ እቅድ እንዴት እንደሚያስፈጽሙት ሲያወጡና ሲያወርዱ አደሩና አንድ ዘዴ መጣላቸው፡፡ በዘዴኝነታቸው እየተደሠቱ አንዳች ጊዜ ሳያጠፉ በማግስቱ ለእቅዳቸው ተግባራዊነት በአብዮታዊ ስሜት ተንቀሳቀሱ፡፡

ጃንዋሪ 30 ቀን 1953 ዓ.ም የሶቪየት ህብረት ብሔራዊ ቴሌቪዥንና መላው የፓርቲና የመንግስት ሚዲያዎች በአባት ሀገር ደህንነትና በታላቁ የጥቅምት አብዮት ላይ የተቃጣ ከፍተኛ የአድህሮት ሀይሎች ሴራ መጋለጡንና በሀቀኛ አብዮታዊ ጓዶች ትግል መክሸፉን ይፋ አደረጉ፡፡ ይህም ሴራ “የዶክተሮች ሴራ” እየተባለ እስከዛሬ ድረስ ይጠራል፡፡ ከኮሙኒስት ፓርቲው የፖሊት ቢሮ የወጣው መግለጫ፤ አብዛኞቹ ይሁዲ የሆኑ የህክምና  ዶክተሮች ከፂዮናዊት እስራኤል፤ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ የስለላ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዋና ፀሀፊውን ጨምሮ የፓርቲውን ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተለየና በረቀቀ የህክምና ዘዴ ለመግደል ሲያሴሩ እንደተገኙና አንዳንድ የፓርቲ፤ የመንግስትና የቀዩ ጦር ከፍተኛ ባለስልጣናት አብዮቱ ፤ታሪክና ህዝብ የጣለባቸውን ከፍተኛ አደራ ወደ ጐን በመተው ፤ ከእነዚህ ከሀዲ ዶክተሮች ጋር አብረው ሲያሴሩና ዙሪያ መለሰ የሆነ ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ እንደተያዙ ጨምሮ አስረዳ፡፡ ከሳምንት በሁዋላም እነዚሁ ዘጠኝ የህክምና ዶክተሮች፤ በቴሌቪዥን ቀርበው ጓድ ዝዳኖቭንና ጓድ ቤራን ጨምሮ የፓርቲውን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመግደል ማሴራቸውንና ለዚህም ሴራቸው ከእስራኤል፤ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ የስለላ ድርጅቶች ትዕዛዝ እንደተቀበሉ አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣኖችም ለሴራቸው ተፈፃሚነት ሙሉ ትብብር እንዳደረጉላቸው የእምነት ቃላቸውን ሠጡ፡፡

ቀጥሎ የተደረገው ነገር ወይም የተወሰደው እርምጃ ለጓድ ቤራና ለጓድ ዝዳኖቭ ብቻ የተተወ አልነበረም፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ሁሉንም የደህንነትና የስለላ ምስጢራዊ ሀይሎችን ተጠሪነት በቀጥታ ወደ እሳቸው አዙረው ዘመቻውን በዋናነት መምራት ጀመሩ፡፡ በሌላ አነጋገር  ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ቀደም ብሎ መሆን አሠኝቷቸው እንደነበረው ሻማ ወይም ባለ ሀይለኛ ብርሀን የኤሌክትሪክ አምፑል ሆኑ ማለት ነው፡፡

ሁሉም የስለላ የደህንነት ሀይሎች ከዚህ የዶክተሮች ሴራ ጋር ተባብረዋል የተባሉ የፓርቲ፤ የመንግስትና የቀዩ ጦር ከፍተኛ ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የስታሊን ቀይ ዱላቸውን ይዘው በሙሉ ሀይላቸው በመላው አባት ሀገር ላይ ዘመቱ፡፡

ከዚያ በሁዋላማ ምኑ ቅጡ! ጊዜው ከባድ የጭንቀትና የጥበት ጊዜ ሆነ፡፡ በርካታ የፓርቲ የመንግስትና የቀዩ ጦር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ እንደ እሳት ራት በሻማውና በአምፑሉ ተቃጥለው ጦሽ እያሉ በጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን እግር ስር መውደቅ ጀመሩ፡፡ የተቀሩት ባለስልጣኖችም የተመዘዘው የስታሊን ቀይ ዱላ ካሁን አሁን ያርፍብን ይሆን በሚል በቃላት በማይገለጥ ስጋትና ጉልበትንና ልብን በሚያርድ ታላቅ ፍርሀት ውስጥ ተውጠው በመንቀጥቀጥ ላይ ነበሩ፡፡

በተለይ ከይሁዲዎች ጋር የጋብቻም ሆነ ሌላ ግንኙነት ያላቸው ባለስልጣናት ስጋትና ጭንቀት አያድርስ ነበር፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ለረጅም ጊዜ የፓርቲው የፖሊት ቢሮ አባልና የአባት ሀገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ በፍፁም ታማኘነት ያገለገለውን የጓድ ሞሎቶቭን ይሁዲ ሚስት እንኳ አልማሯትም፡፡ ከሴራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላት በሚል ከታሠረች በሁዋላ፤ ከፍተኛ ኢሠብአዊ ስቃይ እንድትቀበል ተደርጋለች፡፡ ጓድ ሞሎቶቭም ነገ እኔም አይቀርልኝም በሚል ተስፋ ቆርጦ ነሁልሎ ነበር፡፡

የማሠር የማሠቃየቱና የመግደሉ እርምጃ፤ ጊዜ የለኝም በሚለው የጓድ ዋና ፀሀፊ ውትወታ ለድፍን አንድ ወር አብዮታዊ ግለቱን እንደጠበቀ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡

ወዲያውኑም ህዝቡ ሁሉ በነቂስ ወጥቶ ለተከታታይ ቀናት አብዮታዊ ሠላማዊ ሠልፍ እንዲያካሂድና የፓርቲውና የአብዮቱ ማዕከል የሆኑት ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ አብዮቱንና አባት ሀገርን ከምዕራቡ የአድህሮት ሀይል ሴራ ለመታደግ የወሰዱትን ቆራጥና አብዮታዊ እርምጃ እንደሚደግፉና በፓርቲውና በመንግስት መዋቅር ስር ተሠግስገው የቀሩትን አድሀሪያንና ቡችሎቻቸውን መንጥሮ በማውጣት፤ በስታሊን ቀይ ዱላ እንዲደመሰስላቸው እንዲጠይቅ ተደረገ፡፡

የፓርቲው የፖሊት ቢሮም፤ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ተከታታይ ሠላማዊ ሠልፍ በማካሄድ የጠየቀውን አብዮታዊ ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት የመጀመሪያው ዙር አድሀሪያን ሴረኞችን የመደምሰስ ዘመቻ በድል መጠናቀቁንና ሁለተኛውና ወሳኙ ዘመቻ መጀመሩን

ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንም፤ ሻማ ወይም አምፑል ሆነው ዙሪያቸውን ከበዋቸው ከነበሩት ከፍተኛ ባለስልጣኖች ውስጥ የተወሰኑትን ልክ እንደ እሳት እራት ጠሽ አድርገው እያቃጠሉ እግራቸው ስር መጣሉ በእውነቱ በጣም ተመችቷቸውና በእጅጉም አስደስቷቸው ነበር፡፡ እናም እንደገና ደግሞ አሠኛቸው፡፡ ጊዜው እየሮጠ ነው፡፡ የጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን የጤንነት ሁኔታም ጨርሶ አላወላዳ ማለት ጀምሯል፡፡ ማርች አንድና ሁለት ቀን 1953 ዓ.ም አሟቸው ቢሮም ሳይገቡ ወደ ደጅም ሳይወጡ ቤታቸው ውስጥ ተኝተው አሳለፉት፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ወሳኙ ጊዜ በጣም እንደቀረበ ተሰምቷቸዋል፡፡ እናም ጊዜ የለም፡፡ ማርች ሶስት ቀን ትንሽ ሻል አላቸውና የፓርቲውን የፖሊት ቢሮ አስቸኳይ ስብሠባ ጠሩ፡፡ ሁሉም የፖሊት ቢሮ አባላት ከስብሠባው መጀመር አንድና ግማሽ ሰአት ቀደም ብለው ተገኝተዋል፡፡ ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊንም በቢሮአቸው መስኮት ላይ ቆመው በሽንጣሙ የፖሊት ቢሮ አባላት ዋዝ ሌሞዚን በሾፌር የመጡትን ባለስልጣኖች ሲያዩ ስሜታቸው ክፉኛ ተጐዳባቸው፡፡ እኔ እየሞትኩ ነው በማለት አሰቡ፡፡ እጅግ ተከፉ፡፡

ስብሠባው እንደተጀመረ የወትሮውን ሞገሱንና ጉልበቱን ባጣ ድምጽ፤ የሴራው ተባባሪዎችን መንጥሮ የመደምደሠሱ የመጀመሪያ ዙር እርምጃ በጓድ ዝዳኖቭና በጓድ ቤራ አብዮታዊ ጥረት መሳካቱን ካስረዱ በሁዋላ፤ በተደረገው ምርመራ በዚህ አደገኛ ሴራ እጃቸውን ያስገቡ በርካታ የፖሊት ቢሮ አባላት ስም ዝርዝር መገኘቱንና በእነሱም ላይ ፈጣንና የማያዳግም አብዮታዊ እርምጃ በእሳቸው ቀጥተኛ ትዕዛዝ፤ የጓድ ዝዳኖቭና የጓድ ቤራ የደህንነት ሀይሎች እንደሚወስዱ አስታወቁ፡፡ ጓድ ዝዳኖቭና ጓድ ቤራ ብቻ በከፍተኛ የኩራትና ጌታውን የማስደሰት ስሜት ፈገግ ብለው ራሳቸውን በመስማማት አይነት ከፍ ዝቅ እያደረጉ ሲያወዛውዙ ሌሎች በድንጋጤ ክው ብለው ደርቀው ነበር፡፡

ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን ይህን ከተናገሩ በሁዋላ፤ የእለቱ ስብሠባ መፈፀሙን እንኳ ሳያሳውቁ ከተቀመጡበት ወንበር ሠውነታቸውን እየጐተቱ ተነሱና በቀስታ እርምጃ የስብሠባውን አዳራሽ ለቀው ወጡ፡፡

ማርች 4 ቀን 1953. ዓ.ም ጓድ ዋና ፀሀፊ ስታሊን፤ ጓድ ዝዳኖቭና ጓድ ቤራን በቢሮአቸው አስጠርተው እንዲህ አሏቸው፡፡

(ሳምንት ቀሪውና የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል፡፡)

 

 

Read 3594 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:48