Saturday, 23 June 2012 07:09

የሙስና ሪከርድ የሰበረችው ደቡብ ሱዳን

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ አዲስ ቀን ነው፡፡ አዲስ ቀን እንደመሆኑም የተለየና አዲስ ታሪክ ይዞልን ብቅ ብሏል፡፡ ለዘመናት እነ ናይጀሪያ፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሊቢያ፣ አንጐላና መሠሎቿ በአሸናፊነት ሲፈራረቁበት የነበረው የአፍሪካ ሙስናና የሀገር ሀብት ዝርፊያ የሻምፒዮንስ ሊግ አዲሱን ሻምፒዮን ሀገር አግኝቷል፡- ደቡብ ሱዳንን፡፡ ደቡብ ሱዳን የዚህ ሊግ አዲሱ ሻምፒዮን ሆና  ብቅ ብላለች፡፡ያለፉት አምስትና ስድስት አመታት በአፍሪካ የድህረ ነፃነት የታሪክ ዘመን የተለዩ አመታት ናቸው፡፡ እነዚህ አመታት በሁሉም መመዘኛዎች ከሁለም የተሻሉ ነበሩ፡፡

እነዚህ አመታት የእድገትና የብልጽግና ብርሀን በአፍሪካ መብራት የጀመረበት፤ ስለ አፍሪካ እድገትና ብሩህ ተስፋ በድፍን አለሙ መለፈፍ የተጀመረበት ጊዜያት ናቸው፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡበት፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የበፊት የድህነትና የረሀብ ታሪካቸው ጨርሶ ያልነበረ ያህል በአለም ግንባር ቀደም የሆነ እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችለውበታል፡፡ ይህ ባለፉት ጥቂት አመታት ተስፋ የለሽ አህጉር ተብላ ትጠራ በነበረችው አፍሪካ የተፈፀመ አኩሪ ጀብዱ ነው፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የአለማችን ህዝቦች በጦርነትና በአስከፊ የረሀብ እልቂት ያውቋት የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዲት ሊትር ነዳጅ ዘይት ሳታመርት፣ የእርሻ መሬቷን በትራክተር ሳይሆን በአካፋና በዶማ በመቆፈር፣ ላለፉት ሠባትና ስምንት አመታት ባስመዘገበችው እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ገድል፣ አማልእክት ከሠማይ የወረዱ ያህል በእጅጉ ተደምመዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታት በመቶ አመት ሳይሆን በሺህ አመትም እንኳ ሊሆን ይችላል ተብሎ በማይገመትበት ሁኔታ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ባለሙያዎች ለስራ ፍለጋ ወደ አፍሪካ ተሠደዋል፡፡

ይህ ሁሉ ገድል ግን የታሪኩ አብዛኛው ክፍል እንጂ ሙሉው ስዕል ከቶውንም አይደለም፡፡ የፈተናው ውጤት የሚያመለክተው አፍሪካ በሙስና መውደቋን ነው፡፡

የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከጥቂት ወራት በፊት በሚመሩት መንግስት ውስጥ ስለተንሠራፋው ከፍተኛ ሙስና ከአንድ ሠው በስተቀር የኢህአዴግ አባል አጋርና ደጋፊ በሆኑ ሠዎች ለተሞላውና በተለምዶ ፓርላማ እያልን ለምንጠራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሠጥተው ነበር፡፡ ያ የፓርላማ ስብሠባ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሙስናን በተመለከተ የቀረበላቸውን ጥያቄዎች በተለመደ ዘዴአቸው ሳያድበሠብሱና በሌላ ሳያላክኩ፣ ኮርማውን በቀንዱ ይዘው እውነቱን በግልጽ የተናገሩበት ስብሠባ ተደርጐ መቆጠር ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚያ የፓርላማ ንግግራቸው በንግዱ ማህበረሠብና በመንግስታቸው ውስጥ ያሉት ሙሠኞች ወይም በእርሳቸው አገላለጽ የግልና የመንግስት ሌቦች በሙስናና በዝርፊያ ክህሎታቸውና የአፈፃፀም ብቃታቸው መራቀቅ የተነሳ መንግስታቸው እነሱን ለመቋቋም አቅም እንዳጣ፣ የመንግስታቸው የተለያዩ ፖሊሲዎችና አፈፃፀማቸው ጠቅለል ባለ አነጋገር የመንግስታቸው አሠራር ለሙስናውና አይን ላወጣው ዝርፊያ መነሻና ለመባባሱም አሪፍ መደላድል እንደሆነ እቅጩን ተናግረዋል፡፡

ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የግሉና የመንግስት ሌቦች አሊያም መንግስታቸው በትግሉ ተሸንፈው እስኪወድቁ ድረስ ከፀረ ሙስናው የፍልሚያ ጐራ ግንባራቸውን በማጠፍ እንደማይሸሹ የተናገሩት ንግግር ግን የመሪዎች የተለመደ ራስን ከሃፍረት መከለያ ነገር ስለሆነ ፋይዳው ለታሪክ መዝገብ ብቻ ነው፡፡ ይህን የምለው ቢያንስ በሁለት ቀላል ምክያቶች ነው፡፡

አንደኛ ይህን መሰሉ ንግግር እጅግ የተለመደና ከሞላ ጐደል ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች በምርጫ ቅስቀሳም ሆነ በአዘቦቱ ጊዜ ለህዝባቸው በተደጋጋሚ ቃል የሚገቡት የንሸጣ ወይም በአራዳ ልጆች ቋንቋ የምርቃና ጊዜ ንግግር በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ደግሞ ከንግግር ባለፈ እጅግ አብዛኛውን ጊዜ በተግባር ተተርጉሞ የማይታይ በመሆኑ ነው፡፡ ይህን እውነታ ተጨባጭ አብነት በመጥቀስ እናቅርበው ብንል የኢኳቶሪያል ጊኒ የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩትን ፕሬዚዳንት ቴወይሮ ኦቢያንግ ንጉዌማን በቀላሉ መጥቀስ እንችላለን፡፡ የሆኖ ሆኖ የጠቅላይ የሚኒስትር መለስን እውነተኛውን ንግግር እንደመላው አፍሪካ የሙስናና የሀገር ሀብት ዝርፊያ ትግል እውነተኛ ገጽታ አድርጐ መቁጠር ይቻላል፡፡ በተለያየ መሪና በተለያየ ሁኔታ ቢገለጽም ከንግግሩ መሀል የሚገኘው እውነት አንድ ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኢህአዴግ መራሽ መንግስት ሁሉ አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታትም ከባዶ ቃላቸው በቀር በሙስናው ትግል ፈተና ወድቀዋል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከእስከ በማይባል ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት የታደሉ መሆናቸው ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ጋቦን ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ አንጐላ፣ ናይጀሪያ ሴራሊዮንና ኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን የመሳሠሉ የአፍሪካ ሀገራት ተፈጥሮ ባደላቸው ሀብት ብቻ እንኳን ለራሳቸው ለድፍን አለሙ መትረፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከጠቅላላው ህዝባቸው ቀላል የማይባለው ክፍል በድህነት እየማቀቀ የስቃይ ህይወት ይገፋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የእነዚህ ሀገራት መሪዎች፣ ታላላቅ ፖለቲከኞችና የጦር ሀይል ባለስልጣኖችና ቤተሠቦቻቸው ያካበቱትን ከፍተኛ ሀብትና የሚመሩትን ቅንጡ ህይወት አገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ስለሆነ መዘርዘሩ ሊያሠለች ይችላል፡፡

የኢኮኖሚ እድገትን በተመለከተ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ባለፉት ጥቂት አመታት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አዲስ የእድገት ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የተንሠራፋውን ሙስናንና የሀገር ሀብት ዝርፊያን በመከላከሉ ረገድ ግን አፍሪካን ድል አልቀናትም፡፡ ይልቁንስ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ጭንቅላታችንን ይዘን ጉድ እያልን የጮህንበት የሙስናና የዝርፊያ ታሪክ ዛሬ ጊዜ ያለፈበትና ያረጀ ታሪክ መስሎ ቀርቧል፡፡

ዛሬ አዲስ ቀን ነው፡፡ አዲስ ቀን እንደመሆኑም የተለየና አዲስ ታሪክ ይዞልን ብቅ ብሏል፡፡ ለዘመናት እነ ናይጀሪያ፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሊቢያ፣ አንጐላና መሠሎቿ በአሸናፊነት ሲፈራረቁበት የነበረው የአፍሪካ ሙስናና የሀገር ሀብት ዝርፊያ የሻምፒዮንስ ሊግ አዲሱን ሻምፒዮን ሀገር አግኝቷል፡- ደቡብ ሱዳንን፡፡ ደቡብ ሱዳን የዚህ ሊግ አዲሱ ሻምፒዮን ሆና  ብቅ ብላለች፡፡ የደቡብ ሱዳንን አዲስ የሙስና ታሪክ የሠማ ሠው መደንገጥ ባይችል እንኳ ማዘኑ አሊያም አጃኢብ መሰኘቱ የማይቀር ነው፡፡ደቡብ ሱዳን፤ ከሱዳን መንግስት ጋር ከሠላሳ አመት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ተዋግታለች፡፡ ይህ ጦርነት በአፍሪካ ከተካሄዱት ረጅም ጦርነቶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡ በዚህ ረጅምና እጅግ አታካች ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ደቡብ ሱዳናውያን ደግሞ እጅግ አስከፊ ለሆነ የስደት ኑሮ ለዘመናት ተዳርገው ኖረዋል፡፡ ጦርነቱ ግን ዛሬ አብቅቷል፡፡ ባለፈው ሀምሌ ወር በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ደቡብ ሱዳናውያን ከሱዳን መንግስት ተገንጥለው፣ የራሳቸውን ነፃና ሉአላዊ መንግስት መስርተዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ነፃና ሉአላዊ መንግስት መቋቋም ከሞላ ጐደል ለሁሉም ደቡብ ሱዳናውያን የአመታት ህልማቸው ፍቺና ለብዙዎቹም የረጅም አመታት መራራ የትጥቅ ትግል ውጤት ነው፡፡

ደቡብ ሱዳናውያን ኒውዮርክ አሜሪካ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጽህፈት ቤት የሀገራቸው አዲሱ ባንዲራ ተሠቅሎ ሲውለበለብ እያዩ እንዲህ ነው ብለው በቃላት ለመግለጽ ባልቻሉት ከፍተኛ ልዩ ስሜት ተውጠው እንባቸውን ያፈሠሱትም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩና ያስተማሩ ኤርትራውያን የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ምሁራን ሀገራቸው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ በነፃ መንግስትነት በተቋቋመች ማግስት፣ በአምስትና አስር አመት ጊዜ ውስጥ ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋታለን ብለው በዋናነት ምስኪኑን ፕሬዚዳንታቸውን ከዚያም መላውን ህዝባቸውን ማሳመን ችለው ነበር፡፡

ደቡብ ሱዳናውያንም ነፃ በወጡበት ቀን በማግስቱ ሳይሆን በዚያው በቀኑ አዲሷ ነፃ ሀገራቸው፣ የአፍሪካ ቀንድ ዱባይ እንደምትሆንና የእነሱም የወደፊት ህይወት ብሩህና በእድገትና በብልጽግና የተሞላ እንደሚሆን በእርግጠኛነት ተናግረው ነበር፡፡

የኤርትራውያን በአምስትና አስር አመት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ሲንጋፖር የመሆን እቅድ እቅድ ሳይሆን መያዣ መጨበጫ የሌለው የቀን ቅዠት ነበር፡፡ ለምን የሚለው ጥያቄ ግልጽ ስለሆነ ማብራራት አያስፈልግም፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የአፍሪካ ቀንድ ዱባይ መሆን እንደሚችሉና መጭው ህይወታቸውም የእድገትና የብልጽግና እንደሚሆን በእውናቸው ቢያስቡም ሆነ በህልማቸው ቢያልሙ እውነት አላቸው፡፡ አዲሲቱ ሀገራቸው ምንም እንኳ የምርትና ሽያጩ ነገር የተወሳሠበ ቢሆንም የከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ሀብት ባለቤት ናት፡፡ እናም ከዚህ የተፈጥሮ ፀጋ የሚያገኙትን ከፍተኛ ገቢ በልባምነት ከተጠቀሙበት እንደ ዱባይ ለመሆን ርቀቱ የትከሻቸውን ስፋት ያህል ቅርብ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የአዲሲቱ ሀገራቸው አዲስ መሪዎች ልብ መነሁለል መጀመሩንና ያ ብሩህ ተስፋና ህልማቸው በብርሀን ፍጥነት መጨለምና መጥፋት መጀመሩን ለመረዳት የወሰደባቸው ጊዜ አስራ አንድ ወራት ብቻ ነበር፡፡ ይህ ጊዜ በጣም ፈጣንና አጭር ጊዜ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የሀገራቸውን ነፃነት አንደኛ አመት እንኳ ገና አላከበሩም፡፡ የሀገራቸውና የእነሱ የወደፊት ብሩህ ተስፋ መቀበሪያ ከሆነው የአስከሬን ሳጥን ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡት እንግዲህ በዚህ አንድ አመት እንኳ ባልደፈነ እጅግ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ልክ የዛሬ ወር የደቡብ ሱዳን የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን፣ ከአንድ የቅርብ ባልደረባው ጋር በመሆን ድንገት ወደ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ ጐራ ብሎ ፕሬዚዳንቱን ባስቸኳይ ማነጋገር እንደሚፈልግ ለረዳቶቻቸው አስታወቀ፡ቀጠሮ ስላልነበረውና ፕሬዚዳንቱም አጣዳፊ ጉዳይ ስለያዙ ሊያነጋግሩት እንደማይችሉ ቢነግሩትም ሠውየው በእሳቸው ቀጥተኛ ትዕዛዝ ያከናወነውን ከፍተኛ የሀገር ጉዳይ ይዞ እንደመጣና አሁኑኑ ካላነጋገሩት ከቢሮአቸው እንደማይወጣ ፈርጠም ብሎ ተናገረ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ረዳቶች ይህን ሠውየ በሚገባ ያውቁታል፡፡ የከፍተኛ ትምህርቱን በእንግሊዝና በጀርመን የተማረ፤ የደቡብ ሱዳንን የነፃነት ትግል በውጭ ሀገራት ያስተባብሩ ከነበሩት ታጋዮች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በከፍተኛ የአይን ቁራኛ እየጠበቁት ይህንኑ ለፕሬዚዳንቱ አሳወቁ፡፡ ሰውየውና ባልደረባው ተፈቅዶላቸው ወደ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ እንደገቡ፣ በትዕዛዛቸው መሠረት መስሪያ ቤታቸው ያካሄደውን የኦዲት ምርመራ ሪፖርት አቀረቡላቸው፡ ፕሬዚዳንቱም የቀረበላቸውን ሪፖርት ለጥቂት ደቂቂዎች በአትኩሮት ከተመለከቱ በሁዋላ አንደኛው ገጽ ላይ አይናቸው እንደተተከለ ቀረ፡፡ ከዚያም ጠረጴዛቸውን በቀኝ እጃቸው መዳፍ እየደበደቡ አንድ ቃል እየደጋገሙ ጮክ ብለው መናገር ጀመሩ፤ “ይህ የማይታመን ነገር ነው! ይህ የማይታመን ነገር ነው!”

የኦዲት ምርመራ መስሪያ ቤቱ ያመጣላቸው ሪፖርት፤ ሀገሪቱ ነፃ ከወጣችበት ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ ባሉት አስራ አንድ ወራቶች ብቻ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ወደ ብሔራዊ ካዝናው ገቢ ከተደረገው ገንዘብ ውስጥ አራት ቢሊዮን ዶላሩ (70 ቢሊዮን ብር) እምጥ ይግባ ስምጥ  እንዳልታወቀ ይገልፃል፡፡

የደቡብ ሱዳን የነፃነት ትግል ቁጥር ሁለት መሪና የአዲሲቱ ደቡብ ሱዳን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፤ የኦዲት ምርመራ ሪፖርቱ መልካም ዜና ይዞላቸው እንደማይመጣ ቀድሞውኑም ቢሆን በደንብ ያውቁታል፡፡ የድርጅታቸውንና የቤታቸውን የውስጥ ገመና ስፋትና ጥልቀቱን እንደ እሳቸው በቅርበት የሚያውቅ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የሙስናውና የሀገር ሀብት ዝርፊያው ይህን ያህል ይከፋል ብለው ግን ጨርሶ አልጠበቁም አልገመቱምም ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፤ ሠባ አምስት ለሚሆኑ የቀድሞና አዳዲስ ባለስልጣኖቻቸው የሪፖርቱን ጉድ በመግለጽ እያንዳንዳቸው ከመንግስት ካዝና በተለያየ ምክንያትና ዘዴ የወሰዱትን ከፍተኛ ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲመልሱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈው ላኩ፡፡

አሁን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ሀገራቸው ሁለተኛ ጠላት ከፊታቸው ላይ ተደቅኖባቸዋል፡፡ ጊዜ፡፡ ጊዜ ጨርሶ የለም፡ ደቡብ ሱዳን ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆነውን ብሔራዊ አመታዊ ገቢዋን የምታገኘው ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንኩ በተቀማጭ ሂሳብነት ይገኛል ብለው ይገምቱት የነበረው አራት ቢሊዮን ዶላር በማይታመን ፍጥነትና ሁኔታ በባለስልጣኖቻቸው ተመዝብሯል፡፡ አዲስ ገቢ እንዳያገኙ ደግሞ የነዳጅ ዘይት የማምረትና የመሸጥ ተግባሩ ከሱዳን ጋር በቅርቡ በገባችው ወታደራዊ ግጭትና የከረረ የፖለቲካ ሽኩቻ የተነሳ ተስተጓጉሏል፡፡ ስለዚህ አገሪቱ ግድግዳዉን ልትገጨው በፈጣን እርምጃ እየተንደረደረች ነው፡፡ ለፕሬዚዳንቱም ሆነ ለሀገሪቱ ጨርሶ ጊዜ የለም፡፡ የፕሬዚዳንቱን ደብዳቤ ተከትሎ የደቡብ ሱዳን ፓርላማ፣ እነዚያ ሠባ አምስት የቀድሞም ሆነ አዲስ ባለስልጣኖች ፍርድ ቤት ወንጀለኝነታቸውንም ሆነ ንጽህናቸውን እስኪያረጋግጥ ድረስ ከፓርላማ አባልነታቸው አግዶ እንደሚያቆያቸው በይፋ አስታውቋል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት፣ ከሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ ቢሮና ከፓርላማው የወጡ ወሬዎች እንዳረጋገጡት፤ የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ከተላከበት ካለፈው ወር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከእነዚሁ ባለስልጣናትና የፓርላማ አባላት ወደ ብሔራዊ ባንኩ ካዝና ተመላሽ መሆን የቻለው ከተዘረፈው አራት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ስልሳ ሚሊወን ዶላሩ ወይም አንድ ቢሊዮን አምሳ ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን በአስራ አንድ ወራት ብቻ የተፈፀመው ከፍተኛ የሀገር ሀብት ዝርፊያ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ሲገለጽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ከአለም አቀፉ የነዳጅ አምራችና ሻጭ ሀገሮች ድርጅት (ኦፔክ) የተገኘ መረጃ፤ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ጋር ሉአላዊ የነዳጅ ዘይት አምራችና ሻጭ ሀገር ከሆነች ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ ወደ አምስት ነጥብ ሠባት ቢሊዮር ዶላር ወይም ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ሠባት ቢሊዮን ብር (በ17.50 ተባዝቶ) ገቢ እንዳገኘች ይገልፃል፡፡

ቀደም ብሎ እንደተገለፀውም ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በባለስልጣኖች ብቻ የተዘረፈው አራት ቢሊዮን ዶላር ወይም ሠባ ቢሊዮን ብር የሚሆነው ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች በየቀኑ አስራ ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ ሀያ አንድ ሺ ሁለት መቶ አስራ ሁለት ዶላር ወይም ሁለት መቶ አስራ ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ ሀያ አንድ ሺ ሁለት መቶ አስር ብር ከብሔራዊ ካዝናው ተግተው ሲዘርፉ ነበር፡፡

በፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ የተነሳ ተመላሽ የሆነው ስልሳ ሚሊዮን ዶላር ወይም አንድ ቢሊዮን አምሳ ሚሊዮን ብርም መሸፈን የሚችለው በአምስት ቀናት ብቻ የተዘረፈውን ገንዘብ ነው፡፡ በሶስት መቶ ሀያ አምስት ቀናት የተዘረፈው ከፍተኛ ሀብት ገና ይቀራል፡፡

ይህንን የሀገራቸውን እጅግ አስከፊና መጠነ ሰፊ የዝርፊያ ጉድ የሠሙት ደቡብ ሱናዳውያን በመጀመሪያ አምነው መቀበል ተስኗቸው የናይጀሪያ ወይም የአንጐላ አሊያም የሌላ ሀገር ጉድ ነው ብለው ተከራክረው ነበር፡፡ በሀገራቸው መሪዎች ለዚያውም በዘጠኝ ወራት ብቻ የተፈፀመ የራሳቸው ቤት ጉድ መሆኑን የገዛ ፕሬዚዳንታቸውና ፓርላማቸው እቅጩን ተናግረው ሲያረጋግጡላቸው ግን ልባቸው እስኪቆም ድረስ በድንጋጤ ክው ብለው ነበር፡፡

ከደረሠባቸው ከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን በመጠኑም ቢሆንም በማገገም ፕሬዚዳንቱን ሳልቫ ኪርንና የፓርላማውን አፈ ጉባኤ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቁ ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ብቻ ነበር፡፡

ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ማብራሪያ የተጠየቁት የፓርላማው አፈ ጉባኤ ምን ብለው እንደተናገሩ አላውቅም፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ግን፤ “ከሀገሪቱ ካዝና ገንዘብ የዘረፉ ባለስልጣኖች ሁሉ ለረጅም ዘመናት የተዋጉበትን የትግል አላማ የካዱ ናቸው”  ብለዋል፡፡ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከዚህ የተለየ ንግግር መጠበቅ በእርግጥም የዋህነት ነው፡፡ ይህ የተለመደና የሚጠበቅ የፕሬዚዳንቶች ንግግር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ንግግር ለቁጥር የሚያታክቱ የአፍሪካ መሪዎች ላለፉት ከስልሳ አመታት ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይና ትክክለኛ ምላሽ የሚያስፈልገው የህዝብ ጥያቄ ግን ሌላ ነው፡፡

ከተመዘበረው አራት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ፕሬዚዳንቱ ሳልቫ ኪር ምን ያህሉ ደረሳቸው? ወይም ደግሞ በሆነ ተአምር በደመወዛቸው ብቻ የሚተዳደሩ ምስኪን ፕሬዚዳንት ናቸው እንበል፡፡ ይህ ሁሉ የሀገር ሀብት በብርሀን ፍጥነት ሲዘረፍ እንደ ፕሬዚዳንትነት ለዚያውም የትጥቅ ትግል ያካሄደ ድርጅት መሪ ሆነው የማንን ጐፈሬ ያበጥሩ ነበር?

በትጥቅ ትግል ነፃ የወጡና የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያቋቁሙትን መንግስት ባለስልጣናት የሚመለምሉት ከድል አድራጊው ድርጅታቸው አባላት ውስጥ መሆኑን መናገር በተለይ ለኢትዮጵያዊያን ለቀባሪው እንደ ማርዳት ያህል ነው፡፡ ከቱኒዚያ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ከሴኔጋል እስከ ኤርትራ በአራቱም ማዕዘናት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተለያየ ጊዜ ይህን ድርጊት ፈጽመውታል፡ ፕሬዚዳንት ሳልባ ኪርም ከነፃነት በሁዋላ የመሠረቱትን መንግስት እርሳቸው ከሚመሩት የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄና ጦር ግንባር ቀደም ታጋዮችና የጦር መሪዎች ውስጥ መርጠው በመመልመል አዋቅረዋል፡፡

ረጅም የትጥቅ ትግል በማካሄድ ሀገራቸውን ከውጭ አገዛዝ ነፃ ያወጡ ወይም የነበረውን አገዛዝ በማስወገድ የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠሩ ድርጅቶች የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ግንባር ቀደም ካድሬዎች የያዙትን ስልጣን ላካሄዱት የነፃነት ትግልና ለከፈሉት መስዋዕትነት እንደ ካሳ ክፍያቸው አድርገው ሲቆጥሩት የሀገሪቱን ብሔራዊ ሀብትም ላስገኙት ነፃነት የውለታ ምንቸው በማድረግ እንዳሻቸው ሲዘማነኑ በታጋይነታቸው የተነሳም እራሳቸውን ከህግ በላይና ህግን ለሌሎች ብቻ አውጪ አድርገው ሲቆጥሩ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከትናንት እስከ ዛሬ ስንታዘብ የኖርነው ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖችም ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ የሀገሪቱን ነፃነት ከሠላሳ አመታት በላይ ብረት አንስተን ታግለን በደማችን በአጥንታችንና በህይወታችን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለን አስገኝተናል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ በመሆን ደግሞ ያስገኘነውን ነፃነት ፍሬውን በማጣጣም ላይ እንገኛለን በማለት ጆሮውን ለሠጣቸው ሁሉ መናገር የጀመሩት አዲሱ ነፃነታቸውና ሉአላዊነታቸው የተፃፈበት ቀለም ቀና በወጉ ሳይደርቅ  ነበር፡፡

በርካታ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖችና ቤተሠቦቻቸው ጁባ ከተማ በሚገኘው የመኖሪያ ቤቶቻቸው ደጃፍ ላይ አንድ አይሉ ሁለት ሶስት የቅንጦት ዘመናዊ ሀመርና ፓርሽ መኪኖች ማቆም የቻሉበት በየተዘዋወሩበት ሀገር ሁሉ የታላላቅ ሆቴሎችን ሙሉ ግቢ አዘግተው ለቀናት፣ መዝናናት የቻሉበት ካልሲና ሙታንታ ለመግዛት ብቻ ድባይና ይህን የውሀ መንገድ ማድረግ የቻሉበት ሚስጥርም ሌላ ሳይሆን ይሄው ነው፡፡ በአስራ አንድ ወራቶች ብቻ አራት ቢሊወን ዶላር የሚያህል የሀገር ሀብት ሊዘረፍ የሚችለው ሁሉም የመንግስቱ ባለስልጣናት የሀገሪቱን ብሔራዊ ባንክ እንደየግል ቦርሳቸው ገንዘቡንም ለታገሉበት ውለታ ክፍያ አድርገው በመቁጠር መከፋፈል ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች ያደረጉትም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአባት ቤት ላይ የተደረገ ከፍተኛ ወረራ ነው፡፡

የትጥቅ ትግል በማካሄድ የመንግስት ስልጣን የተቆናጠጡ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ባገኙት አጋጣሚና ሠበብ እየፈለጉም ለህዝባቸው ሳያስገነዝቡት የማያልፉት አንድ ዋና ጉዳይ ለአመታት ነፍጥ አንግበው የወጣትነት ሙሉ ዘመናቸውን በረሀ ለበረሀ እየተንከራተቱ የተዋጉትና የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉት ለራሳቸው ሳይሆን ሠፊውን ህዝብ ነፃ ለማውጣትና ሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር መሆኑን ነው፡፡ ሠፊው ህዝብ ግን ይህን ንግግራቸውን እያዳመጠ ጭንቀላቱን በአወንታ እያወዛወዘ ልክ ነው ይላቸዋል እንጂ አምኖአቸው አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ንግግራቸው ውሸት ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ  ነፃ ወጡ የተባሉ ህዝቦች ዛሬም ድረስ ነፃ አውጥተናችሁአል እያሉ ነጋ ጠባ ከሚነግሯቸው መሪዎቻቸው ጋር የነፃነትና የመብት መከበር ትግል እያካሄዱ ስለሚገኙ ነው፡፡ እኛ ታግለን ነፃ አውጥተንሀል  እየተባለ የሚነገረው ህዝብ በተግባር የሚያየው የእሱን ነፃ መውጣት ሳይሆን የነፃ አውጭዎችን ነፃ መውጣት ነው፡፡ ህዝቡ በተግባር ሲያየው የኖረው የእሱን መብት መከበር ሳይሆን የነፃ አውጪዎቹን መብት መከበር ብቻ ሳይሆን ከህግም በላይ መሆንን ነው፡፡ ነፃ አውጪዎቹን ያለማመኑ ምንጭም ባዕድ አምልኮ ወይም የክፍ ዘር ድግምት ሳይሆን በተግባር የሚታየው ይሄው ድርጊት ነው፡፡ ይህ ማስረጃ ይቅረብበት ተብሎ ሙግት የማይገጠምበት ግልጽ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በአርባ አራቱ ታቦት እየማሉና እየተገዘቱ ቢነግሩን በጭራሽ የማናምናቸው አንድ ሌላ ተጨማሪ ጉዳይ ይህ ሁሉ የሀገራቸው ሀብት ህዝባቸውን ታግለው ነፃ አወጡ በሚባሉ ባለስልጣኖቻቸው ሲዘረፍ አላየሁም አልሠማሁም የአባቴ ቤት ሲወረርም እኔ አብሬ አልወረርኩም ቢሉን ነው፡፡ ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ግን መጥኔውን ይስጠው፡፡

 

 

Read 3438 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 07:18