Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 10:12

የበሽር አላሳድ መንግስት ተቃውሞ አይሎበታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ምዕራባውያን የሶሪያን ኤምባሲዎች ዘጉ

ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ የተቀሰቀሰው የሶሪያ ህዝባዊ አመፅ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፤ የመንግስታቱ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት፤ እስከ አሁን 9ሺ ገደማ ንፁሃን ዜጐች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የሶሪያ መንግስት ሲወስደው በቆየው ወታደራዊ እርምጃዎች የምዕራባውያን አቋም ፈራ ተባ ማለት ይታይበት የነበረ ቢሆንም ከአንድ ሳምንት በፊት ሆላ በተባለች መንደር የተፈፀመው ግድያ ቁጣን መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን ለእርምጃም አነሳስቷቸዋል፡፡  የግድያውን ሪፖርት ተከትሎ ምዕራባውያኑ ባለፈው ማክሰኞ በየአገሮቻቸው የሚገኙ የሶሪያ ኤምባሲዎችን እንደዘጉ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ኤምባሲዎችን ከዘጉት መካከል አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ካናዳ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤አውስትራሊያ፤ ስፔን እና ኔዘርላንድ ይገኙበታል፡፡

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በአሜሪካ የሚገኘው የሶሪያ መንግስት ተወካይ አገሪቱን በሰባ ሁለት ሰአታት ውስጥ ለቆ እንዲወጣ መመሪያ ተሰጥቶታል፡፡ ለጭፍጨፋውም የሶሪያን መንግስት ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የሪፐብሊካ ፓርቲን ፕሬዚደንታዊ እጩ  ሚት ሮሚ፤ አሰቃቂ የመንግስት ግድያዎችን ለማስቆም ወታደራዊ እርምጃዎችን የመውሰጃው ሰዓት አሁን ነው ብለዋል፡፡ የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚ/ር፤ በህዝቦቹ ላይ የመሳሪያ ናዳ የሚያዘንብ መንግስት ጠበቅ ያለ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎች ይወሰድበታል ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም ገልፀዋል፡፡ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጫናውን የደገፈው የእንግሊዝ መንግስት፤ የሶሪያን ኤምባሲ የዘጉት አገሮች የበሽር አላሳድ መንግስት ላይ ጠበቅ ያለ ማእቀብ እንዲጣል ግፊት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

አርባ ዘጠኝ ህፃናትና ሰላሳ አራት ሴቶች የሚገኙበት፣ በአጠቃላይ የአንድ መቶ ስምንት ሰዎችን ህይወት ያሳጣውን ግድያ ማን እንደፈፀመ እስካሁን በትክክል ያልተረጋገጠ ቢሆንም የአካባቢው ሰዎች በሶሪያ መንግስት የተደራጀና “ሻዕቢያ” በመባል የሚታወቀው የሚሊሺያ ቡድን ድርጊቱን እንደፈፀመ ይናገራሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ሩፔርት ኮልቪል እንደሚሉት፤ ድርጊቱ በመንግስት ወታደሮች ይፈፀም በመንግስት በሚደገፉ ሚሊሻዎች ለማወቅ ጉዳዩ መጣራት አለበት፤ ስለዚህ የድርጅቱ መርማሪዎች ይህን ለማጣራት ሁሉም ነገር ክፍት እንዲሆንላቸው ለሶሪያ መንግስት ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

በግድያው እጁ እንደሌለበት የገለፀው የሶርያ መንግስት፤ የተቃውሞ ሰልፈኞችን ለመበተን በስፍራው የነበረውን የመንግስት ሀይል ለማጥቃት የሞከረ አሸባሪ ቡድን ግድያውን እንደፈፀመ ተናግሯል፡፡

ከሶሪያ መንግስት ወታደሮች እና የፀጥታ ሰራተኞች ጋር የሚተባበሩ  ተቃዋሚዎች አሉ በሚባሉባቸው ቦታዎች የሀይል እርምጃ የሚወስዱ ሚሊሺያዎች ህዝባዊ አመፁ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ እንደተደራጁ ቢነገርም ከበሽር አላሳድ መንግስት ስለነሱ ምንም አይነት መረጃ ተሰጥቶ እንደማያውቅ የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡

በኮፊ አናን የሚመራው የመንግስታቱ ልዩ መልእክተኛ እስካሁን በሶሪያ ትርጉም ያለው ሥራ እንዳልሰራ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የሶሪያ ብሄራዊ ካውንስል መሪ ቡርሀን ጋህሊዮን የሶሪያን ጉዳይ ለኮፊ አናን መተው ማለት ሁኔታዎችን ማባባስና ንፁሀን እንዲገደሉ መፍቀድ ነው ብለዋል፡፡ “ከሰሞኑ ጭፍጨፋ በኋላ አናን ምንም አይነት የሞራል ብቃት የላቸውም” ሲሉም ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ የሶሪያ አብዮታዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሁሴን ሰይድ በበኩላቸው፤ የአሳድ መንግስት ግድያ ሲፈፅም ኮፊ አናን ከለላ እየሰጡ ነው ይላሉ፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ  ተንታኝ ማሪና አትዋይ፤ የኮፊ አናን ዕቅድ አስፈላጊ ቢሆንም ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ሲሉ፤ የሶሪያ የፖለቲካ ተንታኝ ሮበርት ዳኒን በበኩላቸው፤ “ኮፊ አናን እየሰሩ ያሉት የዲፕሎማሲ ስራ ነው፡፡ ጉዳዩ የሚፈልገው ደግሞ ካሮት ወይም ዱላ የሚለውን አማራጭ ነው” ይላሉ፡፡

ኮፊ አናን ከግድያው በኋላ ከበሽር አላሳድ ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩ የጠቆሙ መረጃዎች፤  ፕሬዚደንቱ ለአስራአምስት ወራት የቀጠለውን ደም መፋሰስ እንዲያስቆሙ መጠየቃቸውን አመልክተዋል፡፡ “አሁን ጫፍ ላይ ደርሰናል፤ የሶሪያ ህዝብ እጣ ፈንታ ደም መፋሰስና መከፋፈል እንዲሆን አይፈልግም” ሲሉ ኮፊ አናን ለአላሳድ ተናግረዋል፡፡

ከሌሎች የዓለም መንግስታት ተለይተው የበሽር አላሳድን መንግስት ሲደግፉ የቆዩት ቻይናና ራሺያ ግድያውን ተከትሎ የተለያያ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ የበሽር አላሳድን መንግስት በቀጥታ ያላወገዘችው ቻይና፤ የተኩስ አቁም ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች፡፡ በተቃዋሚዎቹ መሀል አሸባሪዎች ቢኖሩም የአሳድ መንግስትም  የዜጎቹን ደህንነት የማስጠበቅ ሃፊነት አለበት ያለችው ራሺያ በበኩሏ፤ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ አላሳድ የራሺያን ድጋፍ ሊያጣ እንደሚችሉ አስጠንቅቃለች፡፡

 

 

 

Read 3338 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:11