Print this page
Saturday, 01 September 2012 11:10

በ5 ዓመት ሚሊየነር የሆነ የአንጅባራ ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ረዘም ቀጠን ያለ ለግላጋ ወጣት ነው፡፡ ሸሚዝና ጂንስ ለብሶ ሲታይ ወጣቱን ሚሊየነር ነው ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ታሪኩን ሲሰሙ ግን እውነት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀ ሥራ ፍለጋ አልተንከራተተም - ዘጠኝ ሺህ (9000) ብር ተበድሮ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ከፍቶ ሥራ ጀመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሚሊዮን ብሮች እያንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት በ10 ሚሊዮን ብር የዱቄት ፋብሪካ ለመክፈት የሕንፃው ግንባታ መጀመሩን ተናግሯል - ዳዊት ባንትይሁን፡፡ ዳዊትን ያገኘነው በቅርቡ ከሐምሌ 23-27 ቀን 2004 በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች 7ኛው ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ተሞክሮውን ለጉባኤተኞቹ ባቀረበበት ወቅት ነበር፡፡

የዳዊት ተሞክሮ አርአያነት ለሌሎች ወጣቶችም ትምህርት ይሆናል ብለን ስላሰብን ከወጣቱ ጋር ያደረግነውን ውይይት በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

መቼና የት ተወለድክ? ዕድገትና ትምህርትስ?

ከኮሶ በር አጠገብ ባለችና ከታ በተባለች መንደር በ1979 ዓ.ም ተወለድኩ፡፡ የሕፃንነት ጊዜዬን ያሳለፍኩትና ትምህርት የጀመርኩት እዚያው ከታ ነው፡፡ የታዳጊነትና የወጣትነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማርኩት በአማራ ክልል በአዊ ዞን በእንጅባራ ከተማ ነው፡፡ አሁንም አድራሻዬ እንጅባራ ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄአለሁ፡፡

እንደተመረቅህ የት ተመደብክ?

እኔ የትም መ/ቤት አልተመደብኩም፣ አልሠራሁም፡፡ እንደተመረቅሁ የግል ሥራ ነው የጀመርኩት፡፡

መነሻ ካፒታሉን ከየት አገኘህ? ከዚያስ በፊት የሥራ ልምዱ ነበረህ?

አዎ! ቤተሰቦቼ ነጋዴ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ብረት እያመጡ ይነግዳሉ፡፡ እየተማርኩ በትርፍ ጊዜዬ አግዛቸው ስለነበር እዚያ እየሸጥኩ ነው የሥራ ልምድ ያዳበርኩት፡፡ እንደተመረቅሁ ጊዜ አላባከንኩም፡፡ ወዲያውኑ ከወላጆቼና ከዘመዶቼ ጋር ተመካክረን ዘጠኝ ሺህ ብር አበደሩኝ፡፡ በዚህ ገንዘብ ምን ልሥራ? በዚህ አካባቢ ምንድነው የሚፈለገው? በምን ዘርፍ ብሰማራ ነው ትርፋማ ሆኜ ብድሬን የምመልሰውና የምቀጥለው በማለት ጥናቶች አደረኩና ካፒታሌ በሚችለው መጠን በቤትና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ዘርፍ ለመሰማራት ወሰንኩ፡፡ ከዚያም ቤት ተከራይቼ ሥራ ጀመርኩ፡፡

የአናጢነት ሙያ ነበረህ?

የለኝም፡፡ በአንድ የሙያ ዘርፍ ለመሰማራት ሙያው ቢኖርህ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን  የግድ የዚያ ዘርፍ ባለሙያ መሆን አይጠበቅብህም፡፡ ዘርፉ የሚያዋጣ ይሁን እንጂ ባለሙያ ቀጥረህ ማሰራት ትችላለህ፡፡ እኔም ያደረኩት እንደዚያ ነው፡፡

የመጀመሪያ ምርታችሁ ምን ነበር?

አልጋ ነበር - ሲንግል አልጋ፡፡ ትዝ ይለኛል ለማስለመድ ብዬ ያለ ትርፍ በ280 ብር ነበር የሸጥኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ጥረቴን ያዩ አንዳንድ የሚያውቁኝ ሰዎች “ሥራው ቢበላሽም አንተ እንድታድግ እንፈልጋለን” በማለት ትዕዛዝ እየሰጡ ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ በዚህ ዓይነት ጀምሬ ብድሬን ከፍዬ በመንቀሳቀስ ነው አሁን ያለሁበት ደረጃ የደረስኩት፡፡

አሁን በድርጅትህ ምን ምን ቁሶች ይመረታሉ?

በአሁኑ ሰዓት በርካታ ቁሶች እናመርታለን፡፡ ሶፋ፣ አልጋ፣ ብፌ፣ ቁም ሳጥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ … በአጠቃላይ አንድ የቢሮና የቤት ዕቃ አምራች ድርጅት የሚያመርታቸውን ቁሶች እናመርታለን፡፡

አሁን ካፒታልህ ምን ያህል ደርሷል?

ሥራ የጀመርኩት በ1999 ዓ.ም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 3.9 ሚሊዮን ብር አለኝ፡፡ በፖል ሪየስና በአስመጪዎች በኩል 2.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ባለ 10 ጐማ ገልባጭ መኪናና አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ አዝዣለሁ፡፡ እነዚህ መኪኖች በቅርቡ በሁለትና ሦስት ወር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ከታሰበ ካፒታሌ 6.5 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ አራት የድርጅት ቤቶችና ትላልቅ መጋዘኖች ሠርቼ እየተከራዩ ነው፡፡

ችግሮች አጋጥመውህ ነበር? እንዴት ተወጣሃቸው?

ወጣት ሆነህና ልምድ ሳይኖርህ የራስህን ሥራ ስትጀምር መቼም መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ እንደማይሆንልህ ግልጽ ነው፡፡ እኔም የካፒታል እጥረት፣ የገበያ ትስስር፣ የመስሪያ ቦታ ችግር፣ … ነበሩብኝ፡፡

አንድ ነገር ስትሠራ እምነት የሚጣልብህ ሰው መሆን ይኖርብሃል፡፡ ደንበኞቼ ለእኔና ለሥራዬ ከበሬታ አላቸው። ስለዚህ የቅድምያ ክፍያ ስጠይቃቸው ያለመጠራጠር ይሰጡኛል፡፡ የገንዘብ ችግሩን በዚህ መንገድ ተወጣሁት። ሌላው አስቸጋሪና ፈታኝ የነበረው የመሥሪያ ቦታ ነበር። የክልሉ መንግሥት ማበረታቻ ብሎ በሰጠኝ 400

ካ.ሜ ቦታ ላይ ማምረቻ ሠርቼ ይህን ችግር ተወጥቼዋለሁ፡፡ የገበያው ችግርም ስለለመደ አሁን ተቀርፏል፤ ጥሩ ገበያ አለን፡፡

የስኬትህ ምሥጢር ምንድነው?

ጠንክሮ መሥራትና ሱሰኛ ያለመሆኔ ነው፡፡ እኔ ምንም ሱስ የለብኝም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥነ-ምግባር ያደኩ፣ ታማኝና ቃሌን አክባሪ ስለሆንኩ የሰዎች መወደድና ፍቅር ስላለኝ ይመስለኛል፡፡

ከድህነት ለመላቀቅና ኑሮን ለማሸነፍ የምታደርገው ትግልና መፍጨርጨር እውቅና ተሰጥቶት ያውቃል?

አዎ! ብዙ ጊዜ የክልሉ መንግሥት፣ ሴክተር መ/ቤቶችና የከተማ አስተዳደሮች ባዘጋጇቸው መድረኮች እየተጋበዝኩ ልምድና ተሞክሮዬን ለወጣቱ አካፍያለሁ፡፡ ራሴንና አገሬን ለመለወጥ በማደርገው ጥረት ብዙ ሽልማቶችና የምስክር ወረቀቶች አግኝቻለሁ፡፡ ከ26 ያህል ሽልማቶች አምስቱ ዋንጫ ናቸው፡፡

ሥራዬና ጥረቴ እውቅና ካገኘሁባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ከሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር እየሠራ ያለው ዶክመንተሪ ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በእኔ የሥራ አጀማመርና ጥረት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ 1፡30 (አንድ ሰዓት ተኩል) ያህል ርዝመት አለው፡፡ ይህ ፊልም የኅብረተሰቡን አመለካከት በመቀየር ወጣቱን ወደ ሥራ ሊያስገባ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡

የወደፊት ዕቅድህ ምንድነው?

የወደፊት ዕቅዴ በ10 ሚሊዮን ብር የዱቄት ፋብሪካ ማቋቋም ነው፡፡ የሕንፃው ግንባታ ተጀምሯል፡፡ በ2005 መጨረሻ ምርት ለመጀመር አቅደናል፡፡ የዱቄት ፋብሪካ እስካሁን በአካባቢው የለም፡፡ ጥሬ ዕቃውም በአካባቢው ስለሚመረት ችግር አይኖርም፡፡

ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ከዱቄት በተጨማሪ ከተረፈ-ምርቱ የከብቶች መኖም ያመርታል፡፡ ዳቦ፣ ብስኩት፣ ኩኪስ፣ ኬኮች፣ … ለማቅረብም ዕቅድ አለን፡፡

ሌላው ዕቅዴ፣ ከምንም ተነስቼ እዚህ የደረስኩት ማኅበረሰቡ እየረዳኝ ስለሆነ ብድራቸውን መክፈል አለብኝ፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በማኅበራዊ ዘርፍ በመሳተፍ የዜግነት ድርሻዬን ለመወጣት ጧሪ ያጡ አረጋውያንና ወላጅ-አልባ ሕፃናት የሚረዱበትና ከችግር አረንቋ የሚወጡበትን አንድ ወፍጮ ቤት ለማቋቋም አቅጃለሁ፡፡

ፋብሪካው ትልቅ በመሆኑ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ100-150 ለሚደርሱ ዜጐች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ግምት አለን፡፡ አሁን በፈርኒቸር ቤቱ 28 ሠራተኞች አሉ፡፡

ሰው ጠንክሮና ሐሳቡን ዓላማው ላይ ብቻ አድርጐ ከሠራ ተለውጦ ራሱንም ሆነ አገሩን መጥቀም ይችላል ያለው ዳዊት፣ ወጣቱ ከአደንዛዥ ዕፆችና ከሱስ ርቆ የመንግሥትንም ሆነ የሌሎችን እጅ ሳይጠብቅ የፈጠራ ባለቤት መሆን ይችላል ብሏል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ስትሰማ ምን ተሰማህ?

ኢትዮጵያን ለማሳደግና ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የነበራቸውን ሕልም እውን ለማድረግ ብዙ ዕቅዶችና ውጥኖች ቀርፀዋል፡፡ ከዕቅዶቻቸው ስኬቶች አንዱ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአገሪቱ የታየው ዕድገት ተጠቃሽ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብም በዕድገት ጎዳና ለማራመድ በድፍረት ከጀመሯቸው ዕቅዶች ዋነኛው የአባይ ግድብ ነው፡፡ ሲታገሉለት የቆዩትን የዚህን ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ፍሬውን ሳያዩና ሳይረኩ በመሞታቸው ጥልቅ ኅዘን ነው የተሰማኝ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሩህሩህነት፣ ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅርና ከድህነት ማጥ ለማውጣት ያደርጉት የነበረው ጥረት ከፍተኛ ነበር፡፡ እኚህን ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ዕድገት ታላቅ ራዕይ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በአጭር የተቀጩትን ጀግና መሪ ማጣት ለመላው ሕዝባችን ከባድ ኅዘንና ዱብ ዕዳ ቢሆንም፣ ጅምር ዕቅዶቻቸውን ከግብ በማድረስ እንዘክራቸዋለን፡፡

 

 

Read 4123 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:23