Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:17

መስቀል እና ንግስት ሄሌና ወይም ዕሌኒ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቅድስት ሄሌና፣ ንግስት ሄሌና ወይም ንግስት ዕሌኒ ማን ናት?

መግቢያ

የመስቀል በዓል በሀገራችን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ መከበር ከጀመረ ከ1600 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ቃሉ ነጠላና ጥምር ሲሆን የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ ነጠላ ፍችውን ብንመለከት- የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ከሳቴ ብርሃን ተሰማ 1951 ዓ.ም ላይ  “የክርስቶስ መስቀል በሁለት ረዣዥም እንጨት እጅና እግሩ የተከነቸረበት ከራሱ እስከ እግሩ ወራጅ ግንድ ከቀኝ እጁ ወደ ግራ እጁ ከአግዳሚውም ግንድ በአራት ማዕዘን ተመሳቅሎ የሚታየው መስቀለኛ ዕንጨት” በማለት ሲፈታው፣ አማርኛ መዝገበ ቃላት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ 2001 ዓ.ም ደግሞ

1. “መስቀል- ቀጥ ባለ እንጨት አናት አካባቢ ሌላ አጠር ያለ እንጨት በማጋደምና ሁለቱን በማያያዝ የሚዘጋጅ በጥንት እስራኤላዊያንና ሮማውያን ጊዜ ወንጀለኞችን አሰቃይቶ ለመግደል ያገለግል የነበረ የሰው መስቀያ፤

2 “… ከብረት ከእንጨት …የሚዘጋጅ፣ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል፣ ምሳሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች ምልክት፣

3. የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ቦታ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ መስከረም 17 ቀን የሚከበር በዓል” በማለት ሶስት ትርጎሞች ይሰጠዋል፡፡ ቃሉ ከሌላ ቃል ጋር ተጣምሮ ሲመጣ ደግሞ ህማማተ-መስቀል “የክርስቶስ ልዩ ልዩ መከራው በጥፊ መመታቱ፣ መታሰሩ፣ መገረፉ፣ ግንድ መሸከሙ፣ ራቁቱን መሰቀሉ፣ አክሊለ ሶክ በራሱ ላይ መቀዳጀቱ ይኸንን የመሳሰለ ልዩ ልዩ መከራው …” ቀራንዮ መስቀል- “በቀራንዮ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዋነኛው የቀራንዮ መስቀል”፤ ዕርፈ መስቀል - “ማንካ፣ ቀሳውስት ለሚቆርቡ ምዕመናን ደሙን የሚያቀብሉበት ማንካ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚኖር …” በሚል በከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት ላይ የተፈቱ ሲሆን “የመስቀል ወፍ፣ የመስቀል አበባ” ወዘተ. የሚሉም አሉ፡፡

ለመግቢያ ያክል ይህን ካልን በቅድመ ክርስቶስ መስቀል ምን ትርጉም እንደነበረው በአጭሩ ተመልክተን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡

በቅድመ ክርስቶስ ዘመን የመስቀል ትዕምርትነት የቅጣት፣ የወንጀለኞች መቅጫና የመግደያ መሳሪያ ነበር፡፡ በግሪኮችና በሮማውያን ዘመን በሺ የሚቆጠሩ ወንጀለኞችና እስረኞች በመስቀል ላይ ተሰቅለው ተገድለዋል፡፡ ለምሳሌ ታላቁ አሌክሳንደር ከትሮይ ከተማ ውድቀት በኋላ ሁለት ሺ የሚሆኑ ትሮኒያውያንን በዚሁ መንገድ እንዲገደሉ እንዳደረገ ታሪክ ይመሰክራል፡፡

በሮማውያን ዘመንም ለብዙ ዘመናት በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ነበር፡፡ ቡድሃዎች ደግሞ ከዚህ በተለየ መልኩ መስቀልን እንደየህይወት ዛፍ እና የመንፈስ ምግብነት ያዩት ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም እንደ ጣኦት ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የምንመለከተው ግን ስለንግስት ሄሌና ታሪክ አብዝተን፣ በእሷ ምክንያት ስለሚነሱ ሰዎች ደግሞ በስሱ ይሆናል፡፡

 

ቅድስት/ንግስት ሄሌና/ዕሌኒ ማናት?

በመግቢያው ላይ ስለመስቀል ፍች ትንሽ ማለቴ ለዚህኛው ርዕሴ ማካሄጃ እንዲሆነኝ በማሰብ ነው፡፡ ንግስት ሄሌና/ዕሌኒ በኋላ ቅድስት ሄሌና በላቲንኛ ደግሞ ፍላቪያ ኢዮሊያ ሄሌና አውጉስታ በመባል የምትጠራ ሲሆን የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ናት፡፡ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የትውልድ ቦታዋን የተመለከተው አፈታሪክ “እንግሊዝ፣ ሄሌኖፖሊስ ቢታንያ ሆኖ የዘር ግንዷ ከኤዥያ ይመዘዛል” የሚል ነው፡፡

“ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ነው” የሚሉም አሉ፡፡ የትውልድ ዘመኗንም እንዲሁ በተጠጋጋ ግምት ከ246 -250 ዓ.ም መካከል ባለው አስምረው ህልፈተ ህይወቷ በ330 ዓ. ም በአሁኑ ጊዜ ስታንቡል በምትባለው በቱርክ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ቅድስናዋ በሮማ ካቶሊክ፣ በምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ በኦሬንታል ኦርቶዶክስ፣ በአንጀሊካ እና ሉተራን ቤተ ክርስቲያኖች ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ዘመን የተወለደችው ንግስት ሄሌና፣ የሮማ ጄኔራል የነበረውንና በኋላ ንጉስ የሆነውን  ክሎረንስን አግብታ፣ በ274 ዓ.ም ቆስጠንጢኖስ የተባለ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡

በ292 ዓ.ም ግን ከባሏ ጋር ተፋታ (ንጉሱ ለዘሯ ሲል ቴዎዶራን በማግባቱ) ለብዙ አመታት ከነበራት ክብር ዝቅ ብላ ኖረች፡፡

በ306 ዓ.ም ግን ንጉስ ክሎረንስ ሲሞት፣ ሰራዊቱ በአባቱ ምትክ ቆስጠንጢኖስን ተክቶ አነገሰው፡፡ ይህ ሁኔታም ንግስት ሄሌናን ወደቀድሞ ክብሯ እና ማዕረጓ እንድትመለስ አደረጋት፡፡

በሀገራችንም በመካከለኛው ዘመን በዚህ ስም የምትጠራ ኢትዮጵያዊት ንግስት እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል፡፡ በታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናትና በኢትዮጵያዊቷ ንግስት እሌኒ መካከል ያለው የዘመን ልዩነት ግን እጅግ የተራራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊቷ በ16ኛው ክ.ዘ፣ ቅድስት ሄሌና ደግሞ በ3ኛው ክ.ዘ መጨረሻና በ4ኛው ክ.ዘ መጀመሪያ ላይ የኖሩ ናቸውና፡፡ ጉዳዩ ከተነሳ አይቀር ስለኢትዮጵያዊቷ ንግስት ዕሌኒ ትንሽ ብል መልካም ይመስለኛል፡፡

በሚያዚያ 1522 ዓ.ም (እንደነቤኪንግሃም) የሞተችው ንግስት ዕሌኒ (ሄንዝ የተባለ ጸሃፊ 1520 ይላል)  የሃድያ ንጉስ የነበረው የንጉስ መሃመድ ልጅ ስትሆን በኋላ ክርስትናን ተቀብላ ከአጼ ልብነ ድንግል ጋር ተጋብታ የኖረች ጠንካራ ሴት ነበረች፡፡ በህይወት ዘመኗ በመንግስት አስተዳደር ላይ ተጨባጭ ሚና የነበራት፣ ለብዙ ነገስታትም አማካሪ ሆና ያገለገለች (ቢያንስ ለዘርዓ ያዕቆብ፣ ከሌላ ሚስት ለተወለደው የእንጀራ ልጇ በዕደ ማርያምና ለአጼ ናኦድ) ታላቅ ፖለቲከኛ ነበረች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተወለደችበትን በትክክል ባታስቀምጥም ሞቷ በ1522 ዓ.ም ነው ከሚሉት ጋር ትስማማለች፡፡ ቤተክርስቲያኗ ለንግስት ዕሌኒ ዕውቅና የምትሰጣት  በመልካም ክርስቲያንነቷና ሃይማኖተኛነቷ ብቻ ሳይሆን በተለይ በሥላሶች ላይና በቅድስት ማርያም ንጽህና ላይ በጻፈቻቸው መጻህፍት ትልቅ ዋጋ ከመስጠት አኳያም ነው፡፡ ይሄ እግረመንገድ የተነሳ ስለሆነ ወደዋናው ነጥብ ልመለስ!

ንግስት ዕሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ ካነሳሷት ምክንያቶች አንዱ-

ወደዚህ ርዕስ ከመግባታችን በፊት ስለታላቁ ቆስጠንጢኖስ አንድ የታሪክ ሁነት መግለጽ የግድ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለመስቀሉ መገኘት ትልቅ ፋይዳ አለውና! ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እንደነገሰ ከሶስት አቅጣጫ ከሶስት የተለያዩ ወገኖች ጋር ጦርነቶች ሊያደርግ ተነሳ፡፡ ውጊያውን ከማድረጉ በፊት ግን ስለማሸነፉ ልቡን ጥርጣሬ ወረረው፡፡ እንዲህ የልቡ ጥርጣሬ ከፍ ባለበት በሙሉ የቀትር ሰአት ግን አንድ በብርሃን የተሞላ መስቀል ከሰማይ ወደ ንጉሱ ቀረበ፡፡ በዚህ በከዋክብት ብርሃን በተሞላ መስቀል ላይም “በዚህ ምልክት ተዋጋ” የሚል ጽሁፍ ተመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሱ ፈጥኖ በሰማይ ላይ የተመለከተውን መስቀል የሚመስልና የሚያክል እንዲሰራ በማዘዝ ከሰራዊቱ ቀድሞ እንዲመራ አደረገ፡፡ በመስቀሉ ኃይልም በቁጥር ከሱ ሰራዊት የሚበልጥ ጦር የነበራቸውን ጠላቶቹን አሸነፈ፡፡ በሌላ በኩል ንጉሱ በስጋ ደዌ በሽታ ይሰቃይ ስለነበር ወደአቡነ ሲልቨስተር (Bishop Sylvester) ቀርቦ ሲያማክራቸው፣ በክርስቲያን ወግ መሰረት አጥምቀውት ተፈወሰ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው በ325 ዓ.ም በቤተክርስቲያን ላይ የተነሳውን ክርክር ተመልክቶ ከአለም ዙሪያ 318 ሊቃነ ጳጳሳትን በመጥራት “ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ ፍጡር ነው፤ ሁለት ባህርይ እንጅ አንድ አይደሉም” ብሎ የተነሳውን አርዮስን በኒቂያ ጉባኤ ላይ አስወግዞ ከቤተክርስቲያን እንዲለይ ያደረገውና ስርአትንና ኃይማኖትን የሚመለከቱ ሃያ ያህል ቀኖናዎች እንዲሰሩ ያደረገ ነው፡፡

እንግዲህ ንግስት ሄሌና ምንም እንኳ ቀደም ሲል ከፍ ያለ ክርስቲያናዊ መንፈስ የነበራት ቢሆንም በነዚህ ሁኔታዎች ነው በልጇ ላይ  አምላኳ ያደረገውን ከፍ ያለ ክብርና በረከት ያደነቀችው፡፡ በዚህም በክርስትና ዕምነት የተመሰጠችው ንግስት ሄሌና ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት ተጓዘች፡፡ በዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ በማውጣት (በጎልጎታ) ዕውነተኛውን መስቀል በሰራው ተአምራት፣ ሁለቱ ወንጀለኞች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች በመለየት (ታሪኩን በየአመቱ የምንሰማው ነው) የክርስትና ምልክት የሆነውን መስቀል ለአለም ክርስቲያኖች ያበረከተቸው፡፡ በዚህም ሳታበቃ መስቀሉን ባገኘችበት ጎልጎታና በሌሎቹ የተቀደሱ ቦታዎች ላይ ቤተጣኦቶችን አፈራርሳ ቤተክርስቲያን ለማሳነጽ የበቃች፤ በዚህም የቅድስና ክብር የተሰጣት ናት፡፡ ለዚህ ስራዋም  በተከታዮቿ ዘንድ የውዳሴ መዝሙር ለእሷና ለልጇ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ተደርሶላቸዋል፡፡ አጭሩን የምስጋና ግጥም እንደሚከተለው ተርጉሜዋለሁ!

“ቆስጠንጢኖስ ንጉስ ሄሌና እናቲቱ፤

የኢየሱስን መስቀል ሞት የሞተበቱ፤

የአማኞች መሳሪያ የጠላት ሰቀቀን፤

በፈጣሪ ፈቃድ ይኼው አገኙልን፤

በፍቅር ተገልጦ ጦሩን የሰበቀ፤

በጠላት ሜዳ ላይ ፍርሃት የለቀቀ፡፡”

የሚል ድንቅ ውዳሴ!

በመሰረቱ በንግስት/ቅድስት ሄሌና ታሪክ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ በትውልድ ቀኗ፣ በኅልፈቷ፣ በወላጆቿ፣ በትውልድ ቦታዋ ወዘተ. ላይ ከፍ ያሉ ክርክሮች አሉ፡፡

አብዝቶ ለማንበብ ለሚፈልግ ግን ይሄ መነሻ ይሆናል እላለሁ፡፡

 

 

Read 6091 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:30