Print this page
Saturday, 22 September 2012 11:05

የማየት ፍሬ

Written by  በእውቀቱ ሥዩም
Rate this item
(2 votes)

በለንደን የሚኖሩ አበሾች በሥራ ሰዓት ሽንጣቸውን ገትረው ይዝናናሉ፡፡ በእረፍት ሠዓት ደሞ ሌላ ነገር ገትረው ይዝናናሉ፡፡ ከዋና ዋና መዝናኛዎች አንዱ ጫት ነው፡፡ እነ ገለምሶ የቪዛ ደጅ ጥናት ሳያጉላላቸው ቀድመውኝ ባሕር ተሻግረው አገኘኋቸው፡፡ ዝነኛው ማሙዬ ጫት ቤት ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተደባልቀው ተቀምጠው ቅጠሉን ከወሬው ጋር ያደቁታል፡፡ በአንድነት መኖር ያልቻሉት ወንድሞቻችን ባንድነት መቃም አላስቸገራቸውም፡፡የለንደን ጉብኝት ትረካዬን በዚህ መጣጥፍ ብደመድመው ይሻላል፡፡ “አንድ ወር ቆይቶ አመት ሊያወራ ነው?” የሚል ሐሜት ሽው ሲል ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ ምን ይገርማል፤ ሳሙኤል ጆንሰን የተባለው የእንግሊዝ ደራሲ ኢትዮጵያን ሳያይ ስለኢትዮጵያ ከመቶ ገፆች በላይ ድርሠት ፅፎ የለ፡፡ ፈረንጅ ያበሻን ረጅም ስም መጥራት ይከብደዋል፡፡ ሳሙኤል ጆንሰን “ራስ ስዕለ ክርስቶስ” እላለሁ ብሎ የድርሠቱን ዋና ገፀባሕርይ “ራሴላስ ብሎ ጠራው፡፡

በፈረንጅ በኩል የመጣውን ሁሉ እንደ ትልቅና እንደ ቅዱስ የሚቆጥሩ አንዳንድ ያገራችን ወላጆች ልጆቻቸውን “ራሴላስ” ብለው ይጠራሉ፡፡ ተማሪ እያለን አጠገባችን ከተቀመጠ ተማሪ ፈተና ስንቀዳ ስርዝ ድርዙን አብረን እንደምንቀዳው ማለት ነው፡፡

ለንደን ኑሮ እሣት ነው፡፡ አውሮፕላን ከወረድሁ ጊዜ ጀምሮ በየርምጃው ኪሴን ሲቀልለኝ ይሰማኝ ነበር፡፡ የሆቴሌ ኮምፒውተር የሃያ ደቂቃ ኢንተርኔት አገልግሎት ለመሥጠት አንድ ባውንድ እንዳጎርሠው ጠየቀኝ፡፡ በየርምጃው ክፈል ነው! ክፈል ነው! ክፈል ነው፡፡ የእንግሊዝ የሾላ ዛፍ በግንዱ ቀዳዳ ሳንቲም ካልተጨመረለት ፍሬውን አይጥልም፡፡ ካጋነንሁ ላይቀር ይሄን ልጨምር፡፡ መላው ለንደን በብላሽ መስጠት የማያውቅ አንድ ትልቅ Pay Zone ነው፡፡

የኑሮውን እሣትነት አንስቼ ሳማርር የሰማ አንድ የለንደን ኗሪ አበሻ እንዲህ አለኝ “ይገርምሃል፡፡ በለንደን አንድ ፓኬት ኮንደም አራት ፓውንድ ነው፡፡ በዚህ ዋጋ አዲስ አበባ ካዛንቺስ ሴት መግዛት ይቻላል”

ለንደን በገባሁ ጥቂት ቀናት በኋላ የጥንቱ አለቃዬ አብይ ተክለማርያም ከሚማርበት ኦክስፎርድ በባቡር እየሠገረ መጣና “ምን እንዳስጐበኝህ ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ ብሪትሽ ሚውዝየም ውሰደኝ እንድለው ጠብቆ ይሆናል፡፡ ምሣ ሠዓት ስለነበር በቅርብ የሚገኝ የአበሻ ሬስቶራንት እንዲያስጎበኘኝ ለመንሁት፡፡ በዳበሣ በር የሚከፍት “ኦይስተር” የተባለ ትኬት ገዛልኝና ሜትሮ ባቡር ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ እንግሊዞች ባቡር ይተኩሣሉ እንጂ ባቡር ይነዳሉ አልልም፡፡ ተተኩሠን እንደ እርሣሥ ቀጣዩ ፌርማታ ላይ ወደቅን፡፡ ጉች ጉች ካለ ጡት ቀጥሎ ብዙ የተዘፈነለት ባቡራችን ትዝ አለኝና ፈገግ አልሁ፡፡

ባቡራቸው ተንቀሳቃሽ ቤተመጻሕፍት ይመስላል፡፡ ምድረ ፈረንጅ በየጋዜጣው ላይ ተደፍቷል፡፡ ውጭ አገር ቆይተው የመጡ ሰዎች በየጋዜጣው “ፈረንጆች በጣም አንባቢ ናቸው፡፡

ባቡር ውስጥ የማያነብ ሰው ካለ ጥቁር መሆን አለበት” በማለት የሚያወሩትን እሰማ ነበር፡፡ ያገሬ ባላገር ሲተርት “ወሬ ቢነግሩህ፣ ሐሳብ ጨምርበት” ይላል፡ እስቲ በዚህ ወሬ ላይ ትንሽ ሐሳብ እንጨምርበት፡፡ እውነት ነው ፈረንጆች ያነብባሉ፡፡ ንባባቸው በጎጎል Dead Souls ድርሠት ውሰጥ የሚገኘው ፔትሮሻ የተባለ ገፀ ባሕርይ እንደሚደርገው አይነት ፍዝ ንባብ ይመስላል፡፡

ከማወቅ ፍላጐት ሳይሆን ከብርቱ ብቸኝነት የመነጨ ነው፡፡ ጥግ ላይ ቆሞ ከማፍዋጨት የላቀ ትርጉም የለውም፡፡ ባገራቸው ልማድ መሠረት ከማያውቁት ሰው ጋር ለማውራት አይደፍሩም፡፡ ስለዚህ ከሚያውቁት ጋዜጣ ጋር ለማውራት ይገደዳሉ፡፡ በግዕዝ “ንባብ” የሚለው ቃል “መነጋገር” የሚል ትርጉም አለው፡፡ መፅሐፍ አነበበ ማለት ከመፅሐፉ ጋር ተነጋገረ ማለት ኖሯል፡፡ ጥቁሩ ስደተኛ አብዛኛውን ጊዜ ብቻውን አይወጣም፡፡ ወይ ዘመድ ወይ አገር አላማጅ ጓደኛ አጠገቡ ይኖራል፡፡ እናም ከወረቀት ጋር ሳይሆን ከሕያው ወንድሙ ጋር ይነጋገራል፡፡

ስለዚህ ፈረንጅ ተሣፋሪዎችን ባንባቢነታቸው ማድነቅ ጥቁር ተሣፋሪዎችን ባለማንበባቸው መናቅ ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀን ወደ ማንችስተር በሚወስደው ባቡር ውስጥ የማያነብ ተሣፋሪ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ባነብ ኖሮ በመስኮት በኩል ያየኋቸው ብዙ ድንቅ ትዕይንቶች ያመልጡኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሐብታም አፀድ የመሰለ መካነ መቃብር አየሁ፡፡ እጅግ ብሩህ ንፁህ በሆነ አረንጓዴ መስክ ላይ ነጫጭ ሰሌዳዎች እንደ ፈንድሻ ተበትነዋል፡፡ እንዲህ ያማረ መቃብር ቢኖረን ኖሮ ሙታንን ደረት እየመታን ሳይሆን ከበሮ እየመታን እንሸኛቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ጫፍ ላይ በሚገኝ አንድ ደብር ጓሮ ለቀብር ተገኘሁ፡፡ በየመቃብሩ መሀል ላይ የተነሰነሰውን አይነምድር ላለመርገጥ እንደ ፈንጅ አምካኝ በጥንቃቄ መራመድ ነበረብኝ፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ያለኝ አማራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሬ እንግሊዝ ውስጥ መሞት ነው፡፡

***

አንዳንዴ “አገሬ” የተባለውን የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም አነብ አነብና

“አገሬ ቆላ ነው ደጋ ወይና ደጋ

እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ”

የሚሉት መስመሮች ላይ ሲደርስ ግራ እጋባለሁ፡፡

በተለይ የመጨረሻው መስመር ተራ ይሆንብኛል፡፡

“እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ” የሚለው ሐሳብ ምን የሚገርም ነገር ኖሮት የገብሬን ልብ ማረከ እላለሁ፡፡

ለንደን ሰንበትበት ስል ግን ተራ የነበረው የገብሬ ግጥም ሳይሆን የእኔ ችኩል ግምገማ መሆኑ ገባኝ፡፡ ገብሬ እኒያን ስንኞች የደረሳቸው ጀርመን ኮሎኝ ውስጥ ነው፡፡ ሲነጋም በሚጨልምበት ወቅት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡

በእኛ አገር ንጋትና ብርሃን ሌሊትና ጨለማ የማይነጣጠሉበት ውል አላቸው፡፡ አውሮፓ ስንገባ ይህ ውል ይፈርሣል፡፡ ባገራችን እንደ ተራ ነገር የቆጠርነው የንጋት ብርሃን በሰው አገር ተቀምጠን ስናስበው እንደ ሉል የከበረ ሆኖ ይታየናል፡፡ “እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ” የሚለው የገብረክርስቶስ መስመር ትልቅ ትርጉም ይዞ ብቅ የሚለው ይኸኔ ነው፡፡

በለንደን የሚኖሩ አበሾች በሥራ ሰዓት ሽንጣቸውን ገትረው ይዝናናሉ፡፡ በእረፍት ሠዓት ደሞ ሌላ ነገር ገትረው ይዝናናሉ፡፡ ከዋና ዋና መዝናኛዎች አንዱ ጫት ነው፡፡ እነ ገለምሶ የቪዛ ደጅ ጥናት ሳያጉላላቸው ቀድመውኝ ባሕር ተሻግረው አገኘኋቸው፡፡ ዝነኛው ማሙዬ ጫት ቤት ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተደባልቀው ተቀምጠው ቅጠሉን ከወሬው ጋር ያደቁታል፡፡ በአንድነት መኖር ያልቻሉት ወንድሞቻችን ባንድነት መቃም አላስቸገራቸውም፡፡ ይህንን ስመለከት፡-

“ድንበር ቢለያችሁ

ሱስ አገናኛችሁ”

በማለት በልቤ አንጎራጐርሁ፡፡ በአወዛጋቢው የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይም በተመድ ድጋፍ ጫት ቤት እንዲከፈት ተመኘሁ፡፡ ከባሩድ ጭስ ወደ ሺሻ ጭስ መሸጋገር በራሱ Progress ነው፡፡

በለንደን ያገኘኋቸውን አበሾች ውለታ በሌላ ጊዜ እፅፋለሁ፡፡ አለዚያም ለባለውለታዎቹ የምስጋና ደብዳቤ እፅፋለሁ፡፡

ብዙዎቹ በጣም ቅኖችና ብሩሆች ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ ታዲያ እንደ ርግብ ብሩህ የሆኑ ያሉትን ያህል እንደ አይነርግብ የጨለሙም ይኖራሉ፡፡ ዛሬ ባዲስ አበባ፣ መደባደብን በውቤ በረሃ ጊዜ የቀረ አራዳነት አድርገን በምንቆጥርበት ሰአት፣ የተፈነከተ ሰው ስናይ “ከማን ጋር ተጋጨህ” ሳይሆን “ከምን ጋር ተጋጨህ” በምንልበት ሰአት፣ በለንደን፣ ምግብ ቤቶችን በአምባጓሮ የሚቀወጡ ጉልቤዎች ሞልተዋል፡፡ የአገሩ ሕግ የጦር መሣሪያ መታጠቅን አይፈቅድም፡፡ ጉልቤው ስደተኛ ግን የቢራ ጠርሙሱን ወደ ጦር መሳሪያ ለመቀየር አልተቸገረም፡፡

ጥቂት የአበሻ ሬስቶራንት ባለቤቶች ጠቡን ከማስቀረት የጦር መሣሪያውን ማስቀረት ይቀልላል ብለው የብርጭቆ ጠርሙሶችን በላስቲክ መጠጫዎች ተኩዋቸው፡፡

ይሄ ለውጥ ብዙ ሰላማዊ ጠጭዎችን አላስደሰተም፡፡ “ውስኪ በፖፖ እየቀረበልኝ እንዴት እንድዝናና ትጠብቃለህ?” አለኝ አንዱ የተማረረ፡፡

አንድ ቀን ከማራቶን ምግብ ቤት ፊትለፊት በሚገኝ ጐዳና ላይ አበሾቹ ለሁለት ተቧድነው፣ ሲከታከቱ የሚያሳይ የሞባይል ቪዲዮ ተመለከትሁ፡፡ አንዱ ሌላውን በከዘራ ሲያባርረው ያየሁ ስለመሰለኝ “ከዘራውን ከየት አገኘው?” ብዬ ባለ ቪዲዮውን ጠየኩት፡፡

“እንጃባቱ! ከብሪቲሽ ሚውዝየም ሰርቆት ይሆናል!” የሚል መልስ ቀረበልኝ፡፡

 

 

Read 4216 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 11:16