Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 11:41

ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ - ከዳተኛው መስፍን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ከትልቅ ወይም ከትንሸ መወለድ  ሞያ አይደለም…”

ኢትዮጵያ ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለጠጠር ሳይሰስቱ እየሰጡ አገራቸውን ለወራሪ አናስደፍርም ብለው በየጋራው በየሸንተረሩ ተሰማርተው፣ በኋላ ቀር መሣሪያ ጠላትን እየጣሉ የወደቁ ብዙ ጀግኖችን ያፈራች አገር ናት፡፡ ከስንዴ መካከል እንክርዳድ አይጠፋም እንደሚባለው ለገንዘብ ወይም ለርካሽ ቁሳዊ ጥቅም ሲሉ ለጠላት አድረው ያገራቸውን ምስጢር የሸጡ፣ ከጠላት ጐን ተሰልፈው አገራቸውን የወጉና ያደሙ በጣም ጥቂት ከዳተኞችን አብቅላለች፡፡

በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ ኢትዮጵያን በመክዳት ለጠላት አድረው ከጠላት ያልተናነሰ ጉዳት በገዛ አገራቸው ላይ ካደረሱ ከነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል ኃይለሥላሴ ጉግሳ ስሙ በቀዳሚት የሚጠቀስ ነው፡፡ ኃይለሥላሴ ጉግሳ የተወለደው በ1900 ዓ.ም ሲሆን የራስ ጉግሳ አርአያ ልጅ ነው፡፡ ይህ መስፍን ገና በ11 ዓመቱ በደጃዝማችነት ማዕረግ ሰሊዎ የተባለ የትግራይ አውራጃን በሞግዚት እንዲያስተዳድር የተሾመ ሲሆን የአፄ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ሴት ልጅ ከሆነችው ልዕልት ዘነበወርቅ ጋር በሰኔ ወር 1924 ዓ.ም ጋብቻ በመፈፀም ከንጉሳዊው ቤተሰብ አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡

ኃይለሥላሴ ጉግሳና ልዕልት ዘነበ ወርቅ የጫጉላ ጊዜያቸውን በአዲስ አበባ አሳልፈው ከቆዩ በኋላ ግዛታቸው ወዳለበት ወደ ትግራይ ተጓዙ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወጣቱ መስፍን የትግራይ ምሥራቃዊ ክፍል በሆኑት አጋሜ፣ አንደርታ፣ እንዳመሆኔ እና ዋጂራት ላይ ገዢ ሆኖ ተሾመ፡፡ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከግዛቱ እንደደረሰ በዚያን ጊዜ የሰባት ወር እርጉዝ የነበረችው ባለቤቱ ልዕልት ዘነበ ወርቅ ኃይለሥላሴ በጠና ታማ በህክምና ላይ እያለች ህይወቷ አለፈ፡፡

ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ሚስቱን መጠጥ እየቀማመሰ ይደበድባት ስለነበር የሞተችው ረግጧት ነው የሚል ወሬ አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ስለተሰማ፣ ከሚያስተዳድረው ግዛት አምስት አውራጃዎች ተነጥቆ አብዛኛውን የትግራይ ክፍል ያስተዳድር ለነበረው ለራስ ስዩም ተሰጠበት፡፡ እርሱም ለአንድ ዓመት ያህል ደጀ ጠኚ ሆኖ በአዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከአንድ ዓመት በኋላ የተነጠቀው ግዛት ተመልሶለት ወደ ትግራይ የገባ ቢሆንም ተጥሎበት የነበረው ቅጣት ከፍ ያለ ቅሬታ ሊያሳድርበት ችሏል፡፡ ዘመኑ ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረር የሚዘጋጁበት ጊዜ በመሆኑ የኢትዮጵያን ባለሥልጣኖች በገንዘብ በማባበል ለማስከዳት የሚሞክሩበት፤ ሰላዮቻቸውንና መሀንዲሶቻቸውን አስርገው በማስገባት ለመጪው ወረራ ጥርጊያውን የሚያቀኑበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ቅሬታ ያላቸው የመንግሥቱን ባለሥልጣናት ለማጥመድ እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩት ፋሺስቶች ኃይለሥላሴ ጉግሳን ትኩረታቸው ውስጥ አስገቡት፡፡ኃይለሥላሴ ጉግሳ ብዙ ጊዜ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ሲመላለስ የሚጓዘው በኤርትራ በኩል አድርጐ ሲሆን የኢትዮጵያ ወሰን ላይ የኢጣሊያ መኪና ተቀብሎ በአስመራ በኩል ምፅዋ ያደርሰዋል፡፡ ከዚያም በመርከብ ወደ ጅቡቲ፤ ከጂቡቲ ደግሞ በባቡር ሸዋ ይዘልቃል፡፡ ይህ በኤርትራ በኩል የሚደረግ ምልልስ ከኢጣሊያኖች ጋር በደንብ እንዲቀራረብ ረድቶታል፡፡ መቀራረቡም ይህ ሰው በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ያደረበትን ቅሬታ ጐረቤቶቹ ኢጣሊያኖች በመረዳታቸው፣ ይህንኑ ቅሬታውን ኮትኩቶ ለማሳደግ አመቺ ሁኔታን ፈጠረላቸው፡፡

ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከኢጣሊያኖች ጋር የምሥጢር ግንኙነት ማከናወን የጀመረው የፋሺስት ጦርነት ከመጀመሩ ቢያንስ ከአንድ አመት በፊት አስቀድሞ እንደነበር ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ ከነዚሁ ተከታታይ የምስጢር ግንኙነቶች አንዱ በሆነውና በግንቦት 19 ቀን 1926 ዓ.ም በተደረገው ግንኙነት፣ ይኸው ሰው ኢጣሊያኖች ወረራውን ከጀመሩ ከጐናቸው እንደሚቆምና ከመቀሌ እስከ ደሴ ያለውን መንገድ እንደሚያስከፍትላቸው ቃል መግባቱን ይፋ ከሆኑ የኢጣሊያ ሰነዶች ለማወቅ ተችሏል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ የነበረው ደቦኖ “በትግራይ በተሾሙት በራስ ስዩም እና በእርሱ (ኃይለሥላሴ ጉግሳ) መካከል ቅራኔ አለ፤ የስለላ ጓዶቻችንና አድዋ ያለው ቆንስላችን ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከእኛ ወገን እንዲሆን አድርገውታል… አስመራ መጥቶ የኛ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ሹመት እንድሰጠው ጠየቀኝ… ከኢትዮጵያ ጋር ግጭቱን እስክንጀምር ድረስ እሺ እያልኩ አቆየሁት፤ መጥበሻውን ከማዘጋጀታችን በፊት እንቁላሉን እንዳልሰብር ብዬ ነው” በማለት የማስከዳቱን ጅማሮ ዘግቧል፡፡

በመስከረም 1927 ዓ.ም መጪውን የኢጣሊያ ወረራ ለመመከት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አንዳንድ ዝግጅት ሲጀመር፣ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የድንበር መከላከያ መስመር አመራር ውስጥ በንጉሠ ነገሥቱ ማዕከላዊ ስፍራ ተሰጠው፡፡ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ግን በተለመደው የክህደት መስመሩ ተጠቅሞ፤ ይህንኑ አዲስ የወረራ መከላከያ እቅድ ኢጣሊያኖች ወዲያውኑ እንዲያውቁት በማድረጉ፣ መረጃው ኢጣሊያኖች በፍጥነት ወረራውን እንዲጀምሩ አበረታቷቸዋል፡፡

አፄ ኃይለሥላሴ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተባለው መፅሐፋቸው፤ ስለዚህ ክዳት ተግባር ሲያወሱ “አባቱ ራስ ጉግሳና ራስ ስዩም በትግሬ ባላባትነት አየተቀናቀኑና እየተፎካከሩ ይኖሩ ነበርና አሁን አባቱ በሰፊው ይዘውት ከነበረው ግዛታቸው እርሱ ገና ልጅ ስለመሆኑ ሁለት ትንንሽ አውራጃዎች ወደ ራስ ስዩም ተጨምረውላቸው ነበርና ይህንን ምክንያት አድርጐ ጠቡን እያጐላው ሄደ” በማለት የኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ቅሬታ እንዴት እንደተጠነሰሰ አስታውሰዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ በዚሁ መፅሐፋቸው፤ ኢጣሊያኖች በራስ ስዩምና በኃይለ ሥላሴ ጉግሳ መካከል የነበረውን ቅራኔ ለወረራቸው ዓላማ ሊጠቀሙበት እንዳቀዱ መንግሥት መረጃ እንደነበረው አስታውሰው “ኢጣሊያኖች ከእርሱ ጋር መላላክ ጀምረው ኖሮ፤ አንዳንድ ሰዎች ይህንን ወሬ ቢነግሩን፤ አፄ ዮሐንስ የኢጣሊያኖች ተቃዋሚ ነበሩና ምንም ቢሆን የአፄ ዮሐንስ ዘር ነኝ የሚል ሰው ኢትዮጵያን ይከዳል ብለን ባለመጠርጠራችን የተወራበትን ወሬ በመናቅ ተውነው፡፡

እርሱም የታማበት ነገር እንዳይገለጥበት ‘ምናልባት ኢጣሊያኖች በጦር ኃይል የመጡብን እንደሆን በግዛቴ በአጋሜ ላይ ሆኜ እስከሞቴ የሚቻለኝን እሰራለሁ’ እያለ ይልክብን ነበር” ብለዋል፡፡

ኢጣሊያኖች በጣም የሚፈልጉትን የኢትዮጵያውያን የመከላከል ውጊያ እቅድ ምሥጢር ከኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ካገኙ በኋላ፣ እነርሱ መቀሌ እስኪገቡ ድረስ በተሾመበት ስፍራ ሆኖ የተለመደ ሥራውን እያከናወነ እንዲጠባበቅ አዘዙት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፋሺስቶች የፈለጉት ስለ ጦርነቱ የመከላከል እቅድና ውጊያ ከአዲስ አበባ የሚያገኘውን አዳዲስ መረጃ እየጠባ እንዲያመጣላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የጨለማ ሥራው በብርሃን እንዳይገለጥበት ስለፈራ ሳያማክራቸው በድንገት መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም ሌሊት ጥቂት ሰዎቹንና 28 መትረየሶች ይዞ ከኢጣሊያን ጦር ጋር ተቀላቀለ፡፡

ኢጣሊያኖች ለዚህ ሰው ውለታውን ለመመለስ በእቅዳቸው የነበረው የኢትዮጵያ ወረራ እስኪፈፀም ድረስ እንኳን አልቆዩም፡፡ ማርሻል ደቦኖ ይህንኑ ሲገልፅ፤ “ዱቼ (ሙሶሊኒ) በቴሌግራም ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳን የትግራይ ጠቅላይ ገዢ ብዬ አንድሾመው አሳወቀኝ፡፡ አሳቡ ጥሩ ነበር፤ እኔ እንዳጣራሁት ግን ሕዝብ የሚያቅፈው ትልቅ ሰው አይደለም፤ የተዋጊነት ባህሪም የለውም፡፡ የተከበረበት ምክንያት ባባቱ ትልቅነት ነው፡፡ ይሁንና በንጉሡ ቪክቶር ኢማኑኤል ሳልሳዊ ሥም የትግራይ ጠቅላይ ገዢ ብዬ ሾምኩት፡፡ ጀነራል ሳንቲሊ ስለዚህ ሰው ሲነግረኝ ግን ፈሪና የሚያፈገፍግ ነው” ብሎኛል ሲል ፅፏል፡፡

ማሪዮ አፔሎ የተባለ የጦርነቱ ዘመን ዘጋቢ ስለ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ሲጠቅስ፤ “መቀሌን ለመያዝ በጥቅምት ወር ስንጓዝ የቪሞዛናን ጦር ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ እየመራ መቀሌ ገባን… የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ፤ የንጉሱ አማች፣ የእኛ ወዳጅ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ፤ የሠራዊታችን ጥሩንባ ነፊዎች የኢጣሊያን የጥንት ወታደሮች እያነሳሱ ሲዘፍኑ በመካከላቸው ሆኖ አብሮ እየፈነደቀ፣ የመካከለኛው ዘመን ሥራ በሚታይበት ቤተ መንግሥት የኢጣሊያን ሠንደቅ ዓላማ ሰቀለ” ብሏል፡፡

ፋሺስቶች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳን በ1928 ዓ.ም እና በ1930 ዓ.ም ኢጣሊያን ካስጐበኙት በኋላ የራስነት ማዕረግ በመስጠት ውለታቸውን መልሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት እሥራኤላዊው ሀጋይ ኤርሊክ፤ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ኢትዮጵያን ክዶ ለወራሪዎቹ በፍፁም ልቡ ማደሩን በመጠቆም፤ ኢጣሊያኖች ግን በእርሱ ላይ እስከ መጨረሻው እምነት እንዳልነበራቸው ይገልፃሉ፡፡ ኢጣሊያኖች ጥቅምት 5 ቀን 1928 ዓ.ም ጠቅላይ ገዢ አድርገው በመላው ትግራይ ላይ ቢሾሙትም፤ በአምስቱ ዓመት የወረራ ዘመን ግን በምቾት ከሚኖርበት ከአዲስ አበባ ከተማ እንዲወጣ አላደረጉትም ሲሉ ሀጋይ ኤርሊክ ያክላሉ፡

የእንግሊዝ ጦር እና የኢትዮጵያ አርበኞች ፀረ ፋሺስት ዘመቻቸውን እያፋፋሙ በየአቅጣጫው በድል መገስገስ ሲጀምሩ፤ ዜናው ለኢትዮጵያውያን የድል ብስራት፣ ለኢጣሊያ ፋሺስቶች እና ባንዶቻቸው ደግሞ የመርዶ አዋጅ ይዞ መጣ፡፡

እናቱን የከዳ ለሞግዚቱ አይጠቅምም እንደሚባለው፤ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የኢጣሊያኖች ጀንበር ማዘቅዘቋን ሲመለከት ደግሞ በተለመደው የክህደት ጠባዩ ፋሺስቶችን ክዶ ራሱን የእንግሊዞች ባለሟል ለማድረግ ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በዚህም ጊዜ ከእንግሊዞች ጋር በመሆን አምባላጌ ላይ በተደረገው ፀረ ፋሺስት ዘመቻ ተካፍሎ ኢጣሊያኖችን ወግቷል፡፡ ፋሺስቶች ከተባረሩ ወዲያም መኖሪያውን በእንግሊዝ ሞግዚትነት ትተዳደር በነበረችው በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ውስጥ አድርጐ ተቀመጠ፡፡ወረራው ከተጀመረ ልክ ከአምስት አመታት በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ ድል ሆኖ አፄ ኃይለሥላሴና የኢትዮጵያ አርበኞች ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ በድል ተመለሱ፡፡ ዘመኑ ፋሺስቶች የተባረሩበት እንደመሆኑ ሰላዮች፣ ወላዋዮችና ከዳተኞች ደግሞ በተራቸው የሚቀጡበትን ጊዜ ይዞ መጣ፡፡ በመሆኑም አፄ ኃይለሥላሴ ሐምሌ 23 ቀን 1933 ዓ.ም ከዳተኛው ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ለፍርድ ይቀርብ ዘንድ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥ የእንግሊዝ መንግሥትን በኦፊሴል ጠየቁ፡፡እንግሊዞች ኃይለሥላሴ ጉግሳን በመጀመሪያ ወደ ዩጋንዳ፣ በመቀጠል ደግሞ ወደ ሲሼልስ ወስደው በመሸሸግ አሳልፎ ላለመስጠት ዳተኝነትን አሳዩ፡፡ አራት ዓመታት ከፈጀ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በኋላ፣ የእንግሊዝ መንግሥት ከዳተኛውን ለኢትዮጵያ አሳልፎ ለመስጠት ስለተስማማ፣ ጳጉሜ 2 ቀን 1938 ዓ.ም ኃይለ ሥላሴ ጉግሳን የያዘው አውሮፕላን አዲስ አበባ ገባ፡፡ እንግዳውን ከአየር ማረፊያ የተቀበሉት የፀጥታ ሰራተኞች ወደ ወህኒ እንዲወርድ አደረጉ፡፡

ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ በእሥር ላይ ሆኖ አንዳንድ ዝግጅቶች ሲከናወኑ ከቆዩ በኋላ የካቲት 14 ቀን 1939 ዓ.ም ፍርድ ቤት ከጠበቃው ጋር ቀርቦ፣ ከዚህ በታች በተዘረዘረው ቅደም ተከተል መሰረት ክስ ቀረበበት፡፡

የንጉሠ ነገሥቱን ግዛት አንዱን ክፍል ወይም መላውን አሳልፎ መስጠት

ከጠላት ጋር መላላክና ጠላትን መርዳት

የጦር አለቆች የታዘዙትን የዘመቻ ሥራ እንዳይፈፅሙ ማሰናከል

በመንግሥት ላይ መሸፈት

በገዛ አገር ላይ መዝመት

ራስ አበበ ዳምጠው በፕሬዚደንትነት በተሾሙለት በዚህ ፍርድ ቤት፤ ስድስት ኢትዮጵያውያንና ሁለት እንግሊዛውያን ጉዳዩን በዳኝነት ተመልክተዋል፡፡ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል ከበየነ በኋላ፤ ሐምሌ 23 ቀን 1939 ዓ.ም በኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ላይ ፍርድ ሰጠ፡፡በዚሁ ፍርድ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘባቸው ወንጀሎች ከባድና ያልተለመደ ባህል ያላቸው በመሆናቸው አገሪቱን የማይገመት ጉዳት ላይ መጣሉን በውሳኔው ላይ ተጠቅሶ፤ “ፍርድ ቤቱ ሕግ የሚያዘውን ከባድ ቅጣት በተከሳሹ ላይ እንዲፈርድ አስገዳጅ ስሜት ስለገጠመው በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ደንብ በ42ኛው ቁጥር መሠረት፣ ተከሳሹ ላደረገው ዋና ጥፋት ብቻ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል” ብሏል፡፡የፍርዱን አፈፃፀም በተመለከተም “ተከሳሹ ወደመጣበት ወህኒ ቤት ተመልሶ፤ ከዚያም ወደ ፍርድ መፈፀሚያ ቦታ ተወስዶ እስኪሞት ድረስ በአንገቱ ይሰቀል፤ ነፍሱን እግዚአብሔር ይማር፤ የሞት ፍርድ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ሳያፀኑት አይፈፀምም” በማለት የዘረዘረ ሲሆን ውሳኔውም በዳኞች ሙሉ ድምፅ ተደግፏል፡፡ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የሞት ቅጣት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እሥራት ተለውጦለት ከሐምሌ 2 ቀን 1940 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞው ኢሉባቦር ክፍለ ሀገር በጐሬ ከተማ ወህኒ ቤት ለቀለብ በወር ሁለት መቶ ብር እየተቆረጠለት ለ26 አመታት ከታሰረ በኋላ፣ በግንቦት ወር 1966 ዓ.ም ወደ አምቦ ከተማ ተዘዋውሮ በ1967 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ታውቋል፡፡በመጨረሻም ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሥ የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ልጅ መሆኑ መጠቀስ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት አፄ ኃይለ ሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ መወለድ ሞያ አይደለም፤ ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሞያ ነው” እንዳሉት፤ ይህ ሰው ራሱን ለትልቅ ነገር መውለድ (ማድረስ) ስለተሳነው የክህደትና የውርደት ሥራ ሞያና መታወቂያው ሆኖ ስሙን ሲያጅበው ይኖራል፡፡

 

 

 

 

Read 4905 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 11:48