Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 11:33

“አዲስ ዓመት”ና “ሚስቶ” ዕቅዶች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ነገረ ጽሑፌን በጥያቄ ልጀምር፡፡ ለመሆኑ የዘመን አዲስና አሮጌ አለው? ዘመን ሲታደስ ምን ይመስላል? እንደ እንቦሳ በየመስኩ ሲቦርቅ እናየዋለን? ከዚያም ወጣት ሆኖ ደረቱን ገልጦ ትከሻውን አሳብጦ “ማን ነክቶኝ“ ሲል እናስተውላለን? በሶስተኛ ደረጃስ ጐልማሳ ሆኖ እንደ ሰው ሲጨምት የምናስተውልበት ጥበብ አለን? አንድ ነገር ለማርጀት እነዚህን ደረጃዎች ማለፍ ያስፈልገው ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው “አረጀ” ሊባል የሚችል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው “አሮጌ ዓመት አልፎ አዲሱ ሲተካ…” ማለት ተገቢ የሚሆነው፡፡ ሌላም ጥያቄ ማከል ይቻላል፡፡ ዘመን ራሱ በአንዲት ነጠላ ዙር የሚያረጅ ከሆነ ሰው ምን ያህል ገልጃጃ ዕድሜ እየኖረ ነው? የዘመንን መታደስና ማርጀትስ በምን እናውቃለን?

ሰው በአዕምሮው የሚስላቸው፣ ስሎም የሚያምንባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱም የዘመን ኡደት ነው፡፡ የዘመን ኡደት ልክ እንደ መኪናችን ጐማ ሊታይ የሚችል ይመስለኛል፡፡ መኪናችን መቆሙን ወይም መንቀሳቀሱን የምናውቀው በሞተሩ ጐትጓችነት ጐማው መሽከርከር ሲጀምር ነው፡፡ ጐማው በፍጥነት እንዲሽከረከር ወይም ቀርፋፋ እንዲሆን የሚያደርጉት ሰውና ጥበቡ ናቸው፡፡

የዘመን ኡደትም አንዲሁ ነው፡፡ በዓለማችን የሚኖሩ ሰዎች የተለያየ ቀመር በማውጣት ዘመንን እንደ ጐማ ሲያሽከረክሩት ይታያሉ፡፡ በሃገራችን እንኳ የተለያየ የዘመን ቀመር አለ፡፡ ዘመኑን የምናሽከረክርበት የሃሳብ ጐማ መሆኑ ነው፡፡ “እንደ ጐርጐርዮሳዊው፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር” እያልን የቆጠራ ልዩነት የፈጠርነውም ሰው የዘመንን ጐማ በፍጥነት ወይም በተንቀራፈፈ መንገድ ስለሚያሽከረክረው ይመስለኛል፡፡ ፈረንጆች አካባቢ የተለየ ዘመን፣ እኛ አገር ደግሞ ሌላ፤ በውስጣችን እንደገና የተለያዩ ዘመናት ኖረው አይደለም፡፡ የልዩነቱ መነሻ የጐማው ፍጥነት የሚለካበት ሚዛን ነው፡፡ እርግጥ ነው ጐማ ያልቃል፤ ዘመን ግን ሰው ኖረም አልኖረም፣ ቆጠረውም አልቆጠረውም ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ያም ሆኖ አሮጌም ሆነ አዲስ የሚባል ነገር ሊኖረው አይችልም፡፡

ታላላቆቹ የሃይማኖት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ሰው ሁሉ የመጣው ከአንድ እናትና አባት ነው “አዳምና ሄዋን” ወይም “አደምና ሐዋ” ከሚባሉ፡፡ ይህ እውነት ቢሆን መልካችንም ሆነ የዘመን አቆጣጠራችን፣ ቋንቋና ባህላችን ቅጣንባሩ የጠፋ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡

አንዱ በጨረቃ፣ ሌላው በፀሐይ፣ ሌላው ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ጥምር ኡደት ዘመንን በመቁጠር ልዩነት ሊያሳይ አይችልም ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ዘመን አለ፡፡ ግን ዘመን ሲያረጅም ሆነ ሲታደስ የምናረጋግጥበት ምንም መንገድ የለም፡፡ እኛው ፈጠርነው እኛው እንመራበታለን፡፡ አንድ ዙር ሲሞላ ቀዳሚውን ዙር አሮጌ፤ ቀጣዩን ደግሞ አዲስ ብለን ስለምናምን እንጂ ዘመን አያረጅም፡፡ አርጅቶ ጡረታ የወጣ የዘመን አዛውንትም አናገኝም፡፡ በአንጻሩ የዘመን አዲስም የለም፡፡ ባይሆን ልክ እንደ ጐማ ወይም እንደ ፋብሪካ ማሽን ይሽከረከራል፡፡ እሱ ዙር በሞላ ቁጥር እኛ “አዲስ ዘመን መጣ” እያልን እብሽድንቅ እንላለን፡፡

ዘመኑ ዙር በሞላ ቁጥር ብዙ “ሚስቶ” ዕቅዶችን እናቅዳለን፡፡ “ሚስቶ” መሰረቱ ምን እንደሆነ ባይገባኝም ቀዩም፣ አልጫውም፣ ወዘተርፈውም የተቀላቀሉበት ማለት እንደሆነ በየምግብ ቤቱ እናስተውላለን፡፡

ዘመን ኡደቱን ባጠናቀቀ ቁጥር የሚታየው የዕቅድ አይነትም ልክ እንደ “ሚስቶው” ነው፡፡ አንዳንዱ ለዘመናት ተጣብቆበት ከኖረው የሲጋራ፣ ወይም የመጠጥ፣ ወይም የጫት፣ ወይም የዝሙት ሱስ ለመላቀቅ ለራሱና ለቤተሰቡ ደጋግሞ ቃል ይገባል፡፡ ወይም ያቅዳል፡፡ ሌላው ጠንክሮ ለመስራትና ገቢውን ለማሳደግ ያቅዳል፡፡ ሌላው የኔ ቢጤው ላጤ ደግሞ ሚስት ለማግባት ሴቷም ባል ለማግባት ዕቅድ ይነድፋሉ፡፡ ሌላውም በትምህርት የሚበረታበትን ዕቅድ ይነድፋል፡፡ ከዚህ ለየት ያለ ዕቅድ የሚያወጣውም ብዙ ነው፤ ወደ አሜሪካ፣ ወይም አውሮፓ፣ ወይም ደቡብ አፍሪካ፣ ይህ ካልሆነም አረብ አገር ለመሰደድ ቁርጥ ያለ ዕቅድ ያወጣል፡፡

ይህ በየግል የሚታቀድ ሲሆን በመንግሥት ደረጃ የሚታቀደውም ብዙ ነው፡፡ መንግሥት ሲያቅድ የዕቅዱ ማስፈፀሚያ የሚሆን የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የማቴሪያል ሃብት እንደሚያስፈልገውም በዕቅዱ ላይ ያመለክታል፡፡ በተቻለ መጠን እነዚህና ሌሎች ሁኔታዎች መሟላታቸውንም ያረጋግጣል፤ ከዚያ ነው ወደ ተግባር የሚገባው፡፡

በግለሰብ ደረጃ የሚታቀዱት አብዛኞቹ ግን ምኞት እንጂ እቅድ አይደሉም፡፡ ያ ባይሆን  ከኖረበት ሱስ ለመላቀቅ የግድ አዲስ ዓመት መጠበቅ ያለበት አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱም አዲሱ ዓመት የተለመደ ኡደቱን ይቀጥላል እንጂ አዲስ ነገር ሊያመጣ አይችልም፡፡

ከሱስ ለመላቀቅ የሚያስፈልገው የዘመን እሽክርክሪት ሳይሆን ከልብ መወሰን መቻል ነው፡፡ እንኳን ከጠንቀኛ ሱስ ለመላቀቅ ሰውን ያህል ታላቅ ፍጡር ለመግደል ቁርጥ አርጐ ያቅድ የለም?

የተለያየ ሱስ የተጠናወተው ጓደኛ አለኝ፡፡ ዘመን በተቆጠረ ቁጥር ለጓደኞቹም ሆነ ለቤተሰቦቹ ቃል በመግባት የሚቀድመው የለም፡፡ ግን ተግባር ላይ የለበትም፡፡

ሁልጊዜ የሚገርመኝ ቃሉን ላለመጠበቅ ወይም ለዕቅዱ አለመሳካት የሚሰጠው ምክንያት ነው፡፡

“አላጨስም፤ አልቅምም፣ አልጠጣም…ወዘተ ብለህ በምትወደው ልጅህ ስም፣ በፈጣሪ ስም ምለህ ቃል ገብተህ አልነበረም? ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ?” ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ “ሚስቴ አበሳጨችኝ” ወይም “አንድ የማይረባ አለቃ አለኝ በነገር እየጐነተለ አላስኖረኝ አለ፡፡ ወይም “አንድ ነዝናዛ ጐረቤት አለችኝ፡፡

ስወጣ ስገባ በነገር አለንጋ ትገርፈኛለች” አለዚያም “የተረገመች ቤት አከራይ አለችኝ ከመሬት ተነስታ ኪራይ ትጨምርብኛለች…” ይለናል፡፡ ሰበቡ ማለቂያ የለውም፡፡

እናም በአዲሱ ዓመት ሊቀር የተወሰነበት፣ በሚወደው ልጁና በእግዚአብሔር ስም ምህላ የያዘበት ጉዳይ መስከረም አጋማሽ ሳይደርስ ከንቱ ይሆናል፡፡

በዚህም ዙሩ ይቀጥላል፡፡ ዘመኑ እሽክርክሪቱን ይያያዛል፤ ሱሱም እነደነበረ ይነጉዳል፡፡ ለዘመናት የማይቀጥለው የባለ ሱሱ ዕድሜና ጤና ነው፡፡ አንድ ቀን፣ አንድ ቦታ ላይ ድንገት እንደ ሻማ ብርሃን ድርግም ማለቱ አይቀርማ፡፡

ለማግባት የሚያዘው ዕቅድም ሌላው “ሚስቶ” ህልም ነው፡፡ ዕቅዱ ተጋቢዎች ተገናኝተው ልብ ለልብ ተግባብተው፤ የጋብቻ ስነስርዓት የሚከናወንበትን ዕለትና ወር ለመወሰን ከሆነ መልካም ነው፡፡

ግን “ዘንድሮ ትዳር እመሰርታለሁ” ብሎ ማቀድ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ትዳር የጨበጣ ውጊያ አይደለማ፡፡ ስለፈለግነው ብቻ የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ተፈላላጊዎች በሆነ መግነጢሳዊ ሃይል መሳሳብ መቻል አለባቸው፡፡ ተሳስበውም መገናኘትና መግባባት፣ ከዚያም ለትዳር ብቃትና ምሉዕነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ምሉዕነቱ የሚረጋገጠውም አካላዊ፣ ስነልቡናዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አዕምሮአዊ ሁኔታዎች ሲሟሉ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ ትዳር ለመያዝ ማቀድ ሳይሆን ሁለቱ ተፋቃሪዎች በአንድ ላይ ለመኖር መወሰናቸውን ይፋ ለማድረግ የሚችሉበትን ቀን መወሰን አያስቸግርም፡፡

ዕቅዱ መያዝ የለበትም ይህንኑ ለማወጅ እንጂ ሚስት ወይም ባል ለመፈለግ አይደለም፡፡ ያ ማቀድ ሳይሆን መሻት ነው፡፡

ወደ አሜሪካ፣ ወደ አውሮፓ፣ ወይም ወደ ደቡብ አፍሪካና ከጠፋም ወደ አረብ አገሮች ለመሰደድ የሚያዘው ዕቅድም በመሰረቱ ጤናማ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ስደት በዕቅድ የሚተገበር አይደለም፡፡ ስደት በሀገር ላይ መኖር የማያስችል የፖለቲካ፣ የጦርነት፣ ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ወዘተ ሲያጋጥም እንጂ ከመሬት ብድግ ብሎ የሚከወን ቀላል ተግባር አይደለም፡፡

“አያ በሬ በሬ አያ በሬ ሆይ፣

ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዲል ያገሬ አርሶ አደር፤ ስደት መዘዙ እጅግ ብዙ ነው፡፡

በፊልም የምናየው አማላዩ ነገር ሁሉ በዕውኑ ዓለም ፈጽሞ የሚገኝ አይደለም፡፡ የባህል፣ የቋንቋ፣ የዕምነትና የአስተሳሰብ፤ ሌላው ቀርቶ የአካባቢ ሁኔታዎች ጣጣ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ወዳሰብነው አገር ሳንደርስ መንገድ ላይ የመቅረት አጋጣሚዎችም ብዙ ናቸው፡፡

ውጭ ሄደን ልንሰራ የምናቅደው ስራኮ በአብዛኛው ተወላጆቹ ነጮች ሊሰሩት የሚፀየፉትን ነው፡፡ እዚያ ደግሞ የወግም፣ የመዝናኛም ጊዜ የለም፡፡ ከሁሉም በላይ የጊዜ ዋጋ ይበልጣል፡፡ ከዚህ ባካና ጊዜ ጋር አብሮ መክነፍ ካልተቻለ ውጤቱ ችጋርና ደዌ ይሆናል፡፡ እኛ ደግሞ ፈርዶብን፤ ስንሄድ ተጀንነን፣ ስንበላ ተቆንነን፣ ስንሰራማ በእጅጉ ተንቀርፍፈን ነው፡፡

ባዕድ ሃገር ሄደን (ተሰደን)፣ ተዋርደንና ተንገላትተን የምንሰራውን ሩቡን እንኳ አገራችን ላይ ብንሰራ ያለምንም ጥርጥር ያልፍልናል፡፡

የትም ሄድን የት ሊያልፍልን የሚችለው ጠንክረን ከሰራን ብቻ ነው፡፡ ካልሰራን አሜሪካ፣ አውሮፓም ሆነ ደቡብ አፍሪካ አይደለም ገነት ብንገባም ተአምራዊ ለውጥ ልናገኝ አንችልም፡፡ “ወጥተህ፣ ወርደህ፣ ወዝህን አንጠፍጥፈህ ብላ” ነዋ የሚለው መጽሐፉ፡፡ ስለሆነም የስደት ዕቅዳችንን እንደገና ልናጤነው ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሞቱበት ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የሚገባው ቃልና የሚያዘው ዕቅድም እጅግ ብዙ ነው፡፡

በመሠረቱ “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ እናሳካለን” ብሎ መማል መገዘቱ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ ራዕያቸው የፓርቲያቸው፣ የፓርቲው ራዕይ ደግሞ የአባላቱና የህዝቡ መሆን አለበት፡፡

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ቀጣይነት ያለው ልማት በአገራችን ማየት የሚቻለው፡፡ አለዚያ እንደ ሱሰኞች ሚስቶ ዕቅድ ዘመን ዙሩን ሲያገባድድ እየጠበቁ ብዙ ማውራት፣ መማልና መገዘት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉት የሚናገር ፓርቲ የሰውየውን ዕቅድ ራዕይ ለመተግበር አይሳነውም፡፡

ግን ከላይ እስከታች ያሉ አባላቱ በዘርና በሃይማኖት ከመሳሳብ፣ ከመቅቡጥ (ሙስና) የፀዱና የዓላማ ሰዎች መሆን ሲችሉ ነው በእርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ በገቢር መግለጥ የሚቻለው፡፡

የለውጥ (ትራንስፎርሜሽን) እና የዕድገት ዕቅዱ ከተጀመረ በዘመን ዑደት ሲሰላ ሶስተኛ ዓመቱን ያዘ፡፡ ምን ያህሉ እንደተከናወነ፣ ምን ያህሉ እንደቀረ፣ ያጋጠመ ችግር ካለም እሱ፣ ወዘተ ለህዝብ ይፋ መደረግ አለበት፡፡

ለምሳሌ በዕቅድ ዘመኑ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ (ሃዲድ) ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ግን እስካሁን ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡

አንዳንዴ ብቻ የባቡር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ በሃሳብ አሟሙቀውን በኮምፒተር ሰሌዳ (ስክሪን) ላይ የሚምዘገዘግ ዘመናዊ ባቡር ያስጐበኙናል እንጂ በተጨባጭ ምን እንደ ተሰራ አያሳዩንም፡፡ የዕቅድ ዘመኑ ደግሞ እየነጐደ ነው፡፡ በቀረው የሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንኳን አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የአዲስ አበባ ከተማን የቀላል ባቡር ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ይህን የምለው ጨለምተኛ ሆኜ ወይም ደግሞ የታሰበው ልማት ዕውን እንዳይሆን የመመኘት መጥፎ አባዜ ተጠናውቶኝ አይደለም፡፡ “አካሄዱን አይተው ስንቁን ይቀሙታል” እንዲሉ ለሁለት የዘመን ዙሮች ከታየው እንቅስቃሴ በመነሳት የሰነዘርሁት ሃሳብ ነው፡፡

በሌላው ዘርፍም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

እንደኔ ግን የማይተገብሩትን ከማቀድና ህዝቡን ህልም በሚመስል ተስፋ ከማስፈንደቅ ገንዘብን፣ ዕውቀትን፣ የማቴሪያልና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ማቀድ ሳይንሳዊ ዘዴ ነው፡፡ ተገቢም ነው፡፡

“አፍ የሚጐርሰውን እጅ ይመጥነዋል”ና! አለዚያ “በዚህ ዓመት ከሱሴ እላቀቃለሁ” ብሎ እንደሚምልና እንደሚገዘት፤ ምሎ ተገዝቶም መስከረም አጋማሽ ላይ ቃሉን እንደሚበላ ብኩን ዜጋ መሆናችን ነው፡፡

በአጠቃላይ ዘመን ዙሩን በሞላ ቁጥር “ይህን አከናውናለሁ፣ ይህን አሳካለሁ፣ ወዘተ” ብሎ ማሰብ ማሰላሰሉ ባይከፋም ቁምነገሩ በሃሳብ ፀንቶ ዓለምንም ማውገርገር መከወን ስንችል በእርግጥም ዕቅዳችን ሊሳካ ይችላል፡፡

አለዚያ ቀይም አልጫም ያልሆነ ሚስቶ ዕቅድ አውጥተን የትም መድረስ አንችልም ባይ ነኝ - ሚስቶ የሚሆነው ደግሞ ዕቅድና አለመስራት ሲቀላቀሉ ነው፡፡ ስለሆነም መስራት ወይም መሆን የምንፈልገውን ነገር ነገ ሳይሆን ዛሬ! አሁን እንጀምር!

 

 

 

 

Read 2760 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 11:46