Monday, 10 September 2012 14:14

ትችላለች

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

አረንጓዴ፣ ብጫ ቀይ የሴቶች ግጥም ነች!

የጀግና ዋጋ መወደድ ነው ወይ ጀግንነትን የሚፈጥረው?... አልኩኝ ለራሴ፡፡ ወርቅን ብርቅ የሚያደርገው በቀላሉ የማይገኝ መሆኑ ነው?...ሁሉም ሰው በውስጡ የጀግንነት መንፈስ አለው፡፡ መንፈሱን ወደ ተግባር የሚለውጠው ግን ወርቅ የሆነው ብቻ ነው፡፡ ጀግናና ወርቅ አንድ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የጀግና ዋጋ መወደድ፤ ጀግንነትን ያበረታታል እንጂ አይፈጥርም፡፡ ጀግንነትን የሚፈጥረው ሰውነት ነው፡፡ …ጀግንነትን ለመረዳት፤ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ የበለጠውን ለመለየት የውድድሩን ህግ ማወቅ አያስፈልግም፡፡

አበበ ቢቂላ፤ በልጅነቱ ፀሀይን በሩጫ ተሽቀዳድሞ ስትጠልቅ የምትገባበትን ለማየት መመኘቱ … የውድድሩ ህግ ነው፡፡ ውድድሩ የሚገባው ለሰው ብቻ፤ ግጥምነቱም፣ ውበቱም ለሰውኛ ብቻ የሚገለፅ ነው፡፡ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ከምድር ስፋት አንፃር ሲታይ የውቅያኖስ አንድ እንባ ጠብታ ነች፡፡ በመቶ ሜትር ሩጫ ውድድር…መቶ ቢሊዮኑ ጋላክሲዎችን የማቋረጥ አቅም በሰው ልጅ መንፈስ ውስጥ ፈጥሮ እንዲንጠራራ ማነሳሳቱ ነው ግጥምነቱ፡፡

እንጂማ፤ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የሮጠው ጀግናም … ወደ ኬኒያ መሄድ ቢፈልግ፤ ያው የህዝብ ትራንስፖርት መሳፈሩ አይቀርም፡፡ ግን፤ አርባ ሁለቱን ኪሎ ሜትር ቲኬን  ጥርሷን አስነክሳ ያስሮጠቻት መንፈስ ናት … የህዝብ ትራንስፖርት የሆነውን መኪናም ሆነ አውሮፕላን የመስራት ጽናት ስትጐላ የምትፈጥረው፡፡ ጀግንነቱ በአጭሩ ይህ ነው፡፡  በዋና ወንዝ የማቋረጥ ጽናት የሌለው የሰው መንፈስ፣ ውቅያኖስ የማያቋርጥ መርከብ አይሰራም፡፡ ወርቅን ቆፍሮ ማውጣት የማይችል መንፈስ፤ የወርቅን ዋጋ ሊያከብር አይችልም፡፡

ሁሉም እርስ በእርስ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት፤ ለማንቂያ በፃፍኩት መጣጥፍ ላይ “ሴቶች ግጥም አይችሉም” የሚል ድምዳሜ አቅርቤ ነበር፡፡ በለንደኑ ኦሎምፒክ የታዘብኩት ነገር… ድምዳሜዬ ትክክል አለመሆኑን አረጋገጠልኝ፡፡ ሴቶች ግጥም ባይችሉ… ግጥሚያ ላይ ተወዳድረው ወርቅ ባላመጡ ነበር፡፡ ሴቶች ግጥም ባይችሉ እንኳን፣ ረጅም ድርሰት ግን ይችላሉ፤ ማለት ነው፡፡ የእግር ድርሰቱን በእጅ ከሚፃፈው ነጥለን ማየት ጐጠኝነት ነው፡፡ ሁሉም እርስ በእርስ የተሳሰሩ ናቸው፡፡

ዘንድሮ ግጥም የሴቶች ነው፡፡ የረጅም እና የአጭር ግጥም የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የአስር ሺ፣ አምስት ሺ፣ የማራቶን፡፡ …ግጥም የሰው ልጅ ህያው መንፈስ ነው፡፡ ሴቶች “ወይዘሮ” ብቻ ሳይሆን “አቶ” ዎችም ናቸው፡፡ …በጥንቱ ስርዓት ድርብ ጭቆና የነበረባቸው ሴቶች፣ አሁን ድርብ ድል ተጐናጽፈዋል፡፡

…በኮሚቴ የወንዶችን የግጥም መንፈስ ለማኮላሸት የተሰራ ስራ ብቻ እንዳይኖር እሰጋለሁ፡፡ እንደዛ አይነት ነገር ተደርጐ ከሆነ ያሳዝናል፡፡ “አባባ ኢትዮጵያም“ አንገቱን ቀና አድርጐ ያስኮረፈው ነገር ካለ፤ መናገር አለበት፡፡ በወንድ ድምጽ፡፡ ወይንስ አንዱ ፆታ ግጥም እንዲችል ሌላው አለመቻል አለበት፡፡ ወንዶች በማራቶን መግጠም እንዲችሉ ምናልባት ዩጋንዳ ሄደው የእግር አጣጣል ቋንቋ መማር ይኖርባቸዋል -  የራሳቸው የእግር ፊደል “ሀ” “ሁ” ከጠፋቸው፡፡ በወንድ ድምጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግጠም…ጉሮሮን የሚያፍኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

“አበበ እንጂ መች ሞተ” ይላል አባባ ፀጋዬ፡፡ አበቦቹ ማበብ እየናፈቁ አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡

ወርቅ ለማግኘት መፈለግ አለበት፡፡ ፈላጊ ያልሆነ መንፈስ ውስጥ ወርቅን ፈልጐ ማግኘት አይቻልም፡፡ ጀግኖች መኖር አለባቸው፡፡ መፈለግ አለባቸው፡፡ ወርቁን ጨብጦ የተመለሰ ጀግና የተመለሰው ወደ ሀገሩ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወደ አለም ህዝብም ነው፡፡

የምድር እና የጁፒተር ፕላኔት ምርጥ አትሌቶች ቢወዳደሩ ጥሩነሽ የምትወክለው ፕላኔቷን ነው፡፡ ያኔ፤ የድሉ ትርጉም፤ ከወርቅም በላይ ይሆናል፡፡ የሰው አሸናፊነትን እና ተሸናፊነት ወርቅ ማጣት እና ማግኘት ይመስለዋል እንጂ አይወክለውም፡፡ ጀግንነት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የጀግና መጥፋት የሰው መጥፋት ነው፡፡

የወርቅን ዋጋ ማወቅ የወርቅን ፍለጋ ያፋፍመዋል፡፡ አንድ ወርቅ አግኚ፤ ወርቁን ሲያገኝ አብሮ የአገኛኘት መንገዱንም ተምሯል፤ አስተምሯል፡፡ አንድ ሁለትን መውለድ አለበት፤ ነበረበት፡፡ ሁለት አራትን፡፡ ሁለት በልምድ እና በጊዜ ሲባዛ ብዙ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ግጥም መቻል ሰው መሆን ማለት ነው፡፡ አለመቻል ደግሞ ተገላቢጦሹን፡፡ በእጅ የሚገጠም ግጥም እየተበላሸ ከመጣ…በእግር የሚገጠመው ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡…በእግር የሚገጠመው ወርቅ ከሆነ (የሴቶቹ)…በእጅ የሚገጠም ነሐስ ሊሆን አይችልም፡፡ ነሐስ ከነበረም ወርቅ ይሆናል በቅርቡ፡፡

ስለዚህ ተሳስቻለሁ…ግለ ሂሴን (ምላሴን) ራሴ ለራሴ ውጫለሁ፡፡

ሴቶች ግጥም ይችላሉ፡፡ …የወንዶች የኩራት ሀውልት ማቀርቀሩ…ከሴቶች ቀና ማለት ጋር የተገናኘ ከሆነ…እንዳቀረቀረ ሊቀር ነው፡፡…አባባ ኢትዮጵያ፤ በእማማ ጀርባ ላይ እንደታዘለ ማወቁ ሊያሳፍረው አይገባም፡፡ እማማ እኮ አረብ ሀገር ሄዳ የምትሰራው አባባ ራሱን መቻል እና እሷን ማስተዳደር ባለመቻሉ ነው፡፡

እና ስሚ አንቺ (አቶ) እማማ ኢትዮጵያ…ሴቶች ግጥም ይችላሉ፡፡ የአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ …እንደ እንግሊዛዊያኑ ባንዲራ (Union Jack) ተጨማሪ ስም አልነበራትም፡፡ እንደ ታላቋ ብሪታኒያ ኢትዮጵያ የሚለው ስምም የማንነት ገላጭ ተቀጥያም የሰጣት እስካሁን የለም፡፡

ኦሎምፒኩን ከተመለከትኩ በኋላ ስሟ ተከሰተልኝ፡፡ አረንጔዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ…የሴቶች ግጥም ነች፡፡

 

 

Read 1904 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:28