Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:17

የአካል ጉዳተኝነት ፈተናዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የልጅነት ውብ እድሜዋን ያሣለፈችው ከእድሜ እኩዮቿ ጋር እንደልቧ ተጫውታና ተሯሩጣ ነው፡፡

በተፈጥሮ የተቸራት ብሩህ አዕምሮዋ ከቅልጥፍናዋና ከፈጣን ተፈጥሮዋ ጋር ተዳምሮ በመንደራቸው እጅግ ተወዳጅ ልጅ አድርጓታል፡፡ በትምህርቷ ጐበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ የምትጠራው ራሔል፤ የጨዋታዎች ሁሉ አድማቂም እንደነበረች ይነገራል፡፡ እሷ ያለችበት ጨዋታ ሁሌም ሞቅ ያለ ነው፡፡ አብሮ አደግ ጓደኞቿ ከእሷ ጋር አብሮ ለመጫወትና እሷ ባለችበት ቡድን ውስጥ ለመግባት ሲሽቀዳደሙ ማየቱ በመንደሩ የተለመደ ጉዳይ ነበር፡፡ መንደራቸው ከአውራ ጐዳናው አጠገብ መሆኑ እነ ራሔልን እንደልብ ከመጫወት አላገዳቸውም፡፡ አባሮሽ፣ ሌባና ፖሊስ፣ ድብብቆሽ፣ ሰኞ ማክሰኞ፣ እግር ኳስ ሁሉም የጨዋታ አይነቶች እነሱ ሰፈር ይዘወተራሉ፡፡ ይህ እጅግ ደስታ የተሞላበት የልጅነት ጊዜዋ ግን አብሮአት ብዙ ለመዝለቅ አልቻለም፡፡ የአስራ አራት ዓመት ዕድሜ ሻማዋን ስታጠፋ ደስታዋም አብሮአት ጠፋ፡፡

በሰፈራቸው የተዘረጋው አዲሱ የቀለበት መንገድ ለመንደራቸው ውበትን ቢያጐናፅፍም ለነራሔልና ቤተሰቦቻቸው ግን ሥጋት ከመሆን አልዳነም፡፡ የሚያደናቅፈውና የማይጐረብጠው አስፋልት መንገድ የተመቻቸው አሽከርካሪዎች ሰፈራቸውን እንደ ልብ ይጋልቡበት ጀመር፡፡ እንደ ንፋስ እየፈጠኑ ከሚሄዱ መኪኖች ጋር እየተጋፉ መጫወቱ እንደቀድሞው ምቾት ባይሰጣቸውም መጫወታቸውን አልተውትም፡፡

በመንደራቸው ለልጆች መጫወቻ ተብሎ የተከለለ ሥፍራ አለመኖሩ አማራጭ ያሳጣቸው ታዳጊዎች መጫወቻቸውን ይዘው አስፋልት ላይ ወጡ፡፡ ጥቂት ቀናት በሠላም አለፉ፡፡ ይህም የወላጆችን ሥጋት ቀስ በቀስ እየቀነሰው ሄደ፡፡ ልጆችም በነፃነት ጨዋታቸውን ቀጠሉ፡፡ ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሔዱ፡፡ ከእነዚህ ቀናት አንዲቷ ግን የተረገመች ሆነች፡፡ ዕለተ ቅዳሜ ረፋድ ላይ ከወደ ጦር ኃይሎች መንገድ እየከነፈ የሚመጣው ፒክአፕ አስፋልት መሃል የገባባትን ኳስ ታቅፋ የምትመለስዋን ታዳጊ ገጫት፡፡

ራሔል በአደጋው ህይወቷን ባትነጠቅም ገና በደንብ ያልጠነከሩ ሁለት እግሮቿ የእሷ መሆናቸው ቀረ፡፡

ሮጣና ቦርቃ ያልጠገበችባቸው እግሮቿ ተቆርጠው ህይወቷ ተረፈ፡፡ ወላጆቿ አጋጣሚው በጣም  ቢያሣዝናቸውም ተስፋ ቆርጠው ተስፋ ሊያስቆርጧት ግን አልፈለጉም፡፡

ሰባተኛ ክፍል ላይ የቆመው ትምህርቷን በማስቀጠል ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚያደርሷት ቃል ገቡላት፡፡ አንድ አመቱ በህክምናና በማገገም አለፈ፡፡ እንደቀድሞው ከእኩያ ጓደኞቿ ጋር መጫወቱና መቦረቁ የቀረባት ታዳጊ፤ ከቤተሰቦቿ የተሰጣትን ተስፋ ይዛ መስከረምን ትናፍቅ ጀመር፡፡

ወላጆቿ በቀጣዩ አመት ት/ቤት እንደሚያስገቧት ቃል ገብተውላታልና፡፡ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ሠራተኛ የሆኑት ወላጅ አባቷ፤ ለልጃቸው የሚሆን ት/ቤት ፍለጋ የጀመሩት ገና ክረምቱ ሣይገባደድ ነበር፡፡

በአካባቢያቸው የሚገኙ ት/ቤቶችን በሙሉ ዞረው ጠየቁ አልሆነላቸውም፡፡ በዊልቸር ድጋፍ የምትንቀሳቀሰው ታዳጊ ልጃቸው ከሰፈራቸው ራቅ ወዳለ ት/ቤት ሄዳ መማሯ አስቸጋሪ እንደሚሆንባት ቢገባቸውም አማራጭ አልነበራቸውምና ፍለጋቸውን አራዘሙት፡፡ መሠረት ዕድገት፣ ብርሃን በር እድገት በህብረት፣ እውቀት ወገኔ፣ ሰላም በር … ሁሉም አልተሳካም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ት/ቤቶቹ እንደ ራሔል ያሉ አካል ጉዳተኞችን ለማስተናገድ በሚችሉበት ሁኔታ አለመሰራታቸው ነው፡፡ የት/ቤቶቹ መወጣጫ ደረጃዎች፣ አካል ጉዳተኞች ሊጠቀሙበት የሚችሉበት መፀዳጃ ቤት አለመኖር የት/ቤቶቹ ዋንኛ ችግር ነው፡፡ ተማሪ በመመዝገብ ላይ ያሉ ሠራተኞች ገና የታዳጊዋ አካል ጉዳት ሲነገራቸው ሊመዘግቧት እንደማይችሉ ይነግሯቸዋል፡፡ አባት በተሰጣቸው ምላሽ እያዘኑ ሌላ ት/ቤት ፍለጋ ይወጣሉ፡፡

ከእኚህ አባት ጋር የተገናኘነው በዚሁ የትምህርት ቤት ፍለጋቸው አጋጣሚ ነበር፡፡ ለሣምንታት በዘለቀው ፍለጋ የተሣካ ነገር ባለማግኘታቸው ተስፋ ወደመቁረጡ ተጠግተዋል፡፡ በታላቅ ጉጉትና ተስፋ መስከረምን ለምትጠብቀው ታዳጊ ልጃቸው ምን ምላሽ እንደሚሰጧት ግራ ገብቷቸዋል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች ከፍለው ለማስተማር አቅም ባያጡም እንደ እሳቸው ልጅ አይነት አካል ጉዳተኞችን ተቀብሎ የሚያስተምር ት/ቤት አለመኖሩ ተስፋቸውን አጨልሞታል፡፡

ትምህርት ቤቶችን የመሰሉ መሠረታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሁሉንም ዜጋ በእኩል መንገድ ሊያስተናግዱ በሚችሉበት መንገድ ለምን እንደማይገነቡ አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ከዚህ ቀደም እምብዛም አሣስቧቸው አለማወቁ ደግሞ በእጅጉ አስገርሟቸዋል፡፡ ለካስ ሁሉም ሰው ሲነካና በራሱ ሲደርስ ነው ጉዳቱን የሚያውቀው ይላሉ፡፡ ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ስል ተዘዋውሬ የተመለከትኳቸው ት/ቤቶች በሙሉ አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የተሰሩ አይደሉም፡፡ በአብዛኛው ት/ቤቶች ተሠርተው ያየኋቸው አዳዲስ ህንፃዎች እንኳን ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ አመቺ በሆነ መልኩ የተሠሩ አይደሉም፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ማግኘቱ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መካኒሣ አካባቢ በሚገኝ አንድ ት/ቤት በአንድ በጐ አድራጊ ድርጅት የተሰራው የአካል ጉዳተኞች መፀዳጃ ቤት እንደ ማሣያ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ይህ ችግር በትምህርት ቤቶች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ጉዳይ አለመሆኑን ያጫወተችኝ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆነችውና በቅርቡ ሴት ልጅ በሰላም መገላገሏን የነገረችኝ ወ/ሮ ሠናይት ታከለ ነች፡፡ በደረሰባት ድንገተኛ የመውደቅ አደጋ እግሮቿ ለጉዳት የተዳረጉት ወ/ሮ ሠናይት የዊልቸር ተጠቃሚ ከሆነች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከወራት በፊት እርጉዝ መሆኗን በማወቋ የእርግዝና ክትትል ለማድረግ በአካባቢዋ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ሄደች፡፡ በእርሷና እርግዝናን በሚከታተሉት የጤና ባለሙያዎች መካከል ያለው ርቀት ከሃያ ሜትሮች የማይዘል ቢሆንም ለእሷ የኪሎ ሜትሮች ያህል ሩቅ ነበሩ፡፡ እንዴት ነው የምትደርሰው? ከምርመራ ክፍሉ ትይዩ በዊልቸሯ ላይ እንደተቀመጠች ለምርመራ የሚወጡና የሚገቡ ሴቶችን እያየች በእድሏ ስታዝን ቆይታ ወጣች፡፡ ማነሽ? ከየት ነሽ? ለምን ወጣሽ? ብሎ የጠየቃት አልነበረም፡፡ እርግዝናዋ ሰባተኛ ወሩን እስኪያስቆጥር ድረስ የህክምና ባለሙያን የማየት ዕድልም አላገኘችም፡፡ “ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት እኮ ጤናማውም አካል ጉዳተኛውም እኩል ሊገለገልባቸው የሚገቡ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ እንዴት እነዚህ ቦታዎች አካል ጉዳተኛው ሊጠቀምባቸው በሚችልበት መልኩ አይዘጋጁም የወ/ሮ ሠናይት ጥያቄ ነው፡፡ መውለጃው እየተቃረበ ሲሄድ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ሆስፒታሎች ሁሉ መዞሯን ትናገራለች፡፡ ግን በአንዳቸውም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ ስፍራ አላየሁም ትላለች፡፡

ልጇን የተገላገለችው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ቢሆንም ሁኔታው ለእሷ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በምጥ ላይ ምጥ ሆነብኝ በማለት፡፡ “አካል ጉዳተኝነት ሴትነት ሲጨመርበት ፈተናው እጅግ ከባድ ነው” የምትለው ወ/ሮ ሰናይት፤ “ከአስረኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳቋርጥ ያስገደደኝ አካል ጉዳተኝነቴ በሴትነት ተፈጥሮአዊ ሂደቴ ውስጥም ትልቅ ጋሬጣ ሆኖብኛል ስትል ትናገራለች፡፡ “የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው አደጋው የደረሰብኝ፡፡ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ትምህርቴን ለመማር ተመልሼ ገባሁ፡፡ ግን ፈተናውን ተቋቁሜ ትምህርቴን መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ዕድሜዬ ገና የጉርምስና መግቢያ ላይ ስለነበር የወር አበባ ማየት ጀመርኩ፡፡ በትምህርት ቤታችን ውስጥ የሚገኘው የመፀዳጃ ቤት ተማሪው በሙሉ እኩል የሚጠቀምበት ከመሆኑም በላይ ለእንደኔ አይነቱ አካል ጉዳተኛ አመቺ አልነበረም፡፡ እናም በየወሩ ለአራትና አምስት ቀናት  ያህል ትምህርት ቤት መቅረት ግዴታዬ ነበር፡፡ ወደ ት/ቤት ስሔድ ሽንቴ እንዳያስቸግረኝ ውሃ ሳልጠጣ እውል ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ በጣም ለምቸገርበት የኩላሊት ህመም ዳርጐኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከአንድ አመት በላይ መቀጠል ባለመቻሌ የምወደውን ትምህርቴን አስረኛ ክፍል ላይ አቋርጬ ወጣሁ፡፡ በአካባቢዬ በሚገኝ አንድ የሙያ ማሰልጠኛ ውስጥ ገብቼ በስፌትና በጥልፍ ሥራ ሰልጥኜ ወጣሁ፡፡ ዛሬ ራሴን የማስተዳድርበትን ሙያም ያገኘሁት ከዚሁ ማሰልጠኛ ነው፡፡ በህይወቴ ውስጥ ያለፉት ፈተናዎች ግን እጅግ ከባድ ናቸው፤ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህንን የአካል ጉዳተኝነት ፈተናዎች ለማቃለል ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው፡፡ ለሁሉም ዜጋ የሚደረገው ነገር ሁሉ አካል ጉዳተኛውንም ያማከለና እሱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አካል ጉዳተኛውም እኮ ሌላ አገር፣ ሌላ መንግስትና ሌላ ወገን የለውም፡፡”

የሰናይት መልዕክት ጠንከር ያለ ነው፡፡ በተለይ በተለይ እንደ ትምህርት፣ ህክምና እና ትራንስፖርትን የመሳሰሉ መሰረታዊ ጉዳዮች አካል ጉዳተኛውም እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸቱ ግድ ሊል ይገባል፡፡ እንደ ታዳጊ ራሔልና እንደ ወ/ሮ ሰናይት ሁሉ መማር እየፈለጉ ያልቻሉትን በርካታ አካል ጉዳተኛ ወገኖች መማር ይችሉ ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ከመንግስትም ሆነ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በቀላል ወጪና ጊዜ ሁሉም መሠረታዊ ተቋማት አካል ጉዳተኛውንም ያማከሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላልና በእርግጥም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

 

 

 

 

Read 1672 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:23