Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:54

ሀበሻ፣ ለማይጨበጥ ዓመሉ ያንባ… የመሪ ሀዘን፣ ከኑሮ ውድነቱ መሪር ሀዘን ጋር ሲቆራኝ የምር ያስለቅሳል…

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አቶ መለስ ለዓላማቸው ኖረዋል፤ ኢትዮጵያ ለራሷ ታልቅስ!

ፈር መያዣ- በአሁኑ ጊዜ በጋራ ሀገራችን ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ መሪር እውነቶቻችንን እየጠቆሙ መወያየት “መርዶ ነጋሪ” የሚያስብል አይመስለኝም፤ ለነገሩ ሀገር ከመሪዋ ሀዘን የበለጠ ሰዋዊ ጉዳዮች እንደሌሉ አስረግጣ እንባ እያራጨች ባለችበት በዚህ ሰዓት፣ ምንም ሀሳብ “መርዶ” የመሆን ወይም የመምሠል አቅም ይኖረዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ፣ የተወሰኑ የምር ችግሮችና ችጋሮችን እየጠቀስን፣ ለቅድመ ጥንቃቄና ለንቃት መፍጠሪያ እንዲሆኑ አድርገን ብንወያይባቸው፣ ለሁላችንም የሚበጁ ይመስለኛል፡፡

ሀገራችንን እግር ከወርች እያሠሩ ካሉ መሪር ችግሮቻችንና ችጋሮቻችን መካከል ልንቆጣጠረው ያልቻልነው የኑሮ ውድነት፣ ቀዳሚውና ፈታኙ ነው፡፡ ለፖለቲካዊና ለማህበራዊ ልማቶቻችን ትልቅ ደንቃራ እየሆነ ያለው ቅጥ ያጣ ብሔርተኝነት (ጐጠኝነት) እና ሙስና ደግሞ በሁለተኛና በተወራራሽ የሚነሱ ችግሮቻችን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የሀይማኖትና የእምነት ግጭቶች በሦስተኛ ደረጃ የሚነሱ ይመስለኛል፡፡ እነዚህን ፈታኝ ሀገራዊ አደጋዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ እና/ወይም በማባበስ፣ ልማታዊ ሥራዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ልማታዊ አስተሳሰቦቻችንን እያቀጫጩና እየቀጩ ያሉ፣ ምክንያታዊ የኑሮ ፍልስፍና የነጠፈባቸው ህዝባዊ ወይም ሀገራዊ የማይጨበጡ ፀባዮች አሉን፤ የምር ልናለቅስባቸው የሚገቡ፡፡ የተወሰኑ አንኳር ጉዳዮችን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግሮች ጋር በትይዩ ብናጤናቸው መልካም ይመስለኛል፡፡

መሪ ያጣ ህዝብ ወይስ ህዝብ ያጣ መሪ - እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ባለፈው ክፍለ ዘመን በሀገራችን ታሪክ፣ አቶ መለስ ቀብራቸውን በወጉ ያደረጉ የመጀመሪያው የሀገር መሪ ይመስሉኛል፡፡ የታሪክ ሰነዶቻችን እንደሚነግሩን ከሆነ አብዛኞቹ የሀገራችን መሪዎች እንኳን ቀብራቸው፣ አሟሟታቸው ቅጥ አልነበረውም፣ እንደ ኑሮ ፍልስፍናችን፣ ህልፈታችንም ቅኔ ነው፡፡ መሪዎቹ በህይወት እያሉም፣ ከሞቱ በኋላም ከህዝብ ጋር የተዋወቁ አይመስልም፤ ሆድና ጀርባ ስለመሆናቸው ነው ሲነገር የምንሰማው፤ ተጽፎም ያነበብነው፡፡

ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ያሉትን ሦስት መንግሥታት ከህዝብ ጋር የነበራቸውን መስተጋብር መመርመር ይቻላል፡፡ የንጉሡም ሆነ የደርግ ዘመን ብዙ ህዝባዊ ቁጣዎች፣ ብዙ ሀገራዊ ኩርፊያዎችን አስተናግደዋል፡፡ ተጠንፍፎ ከሚዘከረው ታሪካቸው ውስጥ ለዛሬው ትውልድ እየተላለፈ ያለው አብዛኛው፣ ጥግ የያዘና ጥፋት ያዘለ ታሪክ ነው ማለት ይቻላል፤ ይህ የሀገራዊ መነጽሩ እይታ ነው፡፡ የተወሰኑ ልሂቃን የሚነግሩን፣ መረጃ እያጣቀሱ የሚያስረዱን ጉዳዮች ደግሞ ሌላ ፅንፍ ላይ ቆመው ይገኛሉ፡፡ መሪዎቹም ሆኑ ሥርዓቶቻቸውም ካለፉ በኋላ፣ በተለይ የፖለቲካው ቅኔ ሲፍታታ፣ ብዙ ሰምና ወርቅ ገድሎቻችን ይዘከራሉ፡፡

ብዙ ውዳሴና ሙገሳ የሚያቀርቡ፣ ብዙ ሀዘኔታና ይቅርታ የሚያደርሱ ብዙ ዜጐች ያጋጥማሉ፡፡ የኋላ ኋላ ከፖለቲካው ቅኔ ውስጥ በአብዛኛው መሳ ለመሳ፣ በተወሰነ መልኩ ደግሞ በለጥ ብሎ፣ የህዝቡ ውስጠ ወይራዎች (ወርቆች) ይሰማሉ፡፡ በሁለቱ ሥርዓቶች ብቻ የታዩት ህዝባዊ ጐርፎች፣ ሀገራዊ ግለቶች በቀኝም በግራም የህዝብ ማዕበል ፈጥረዋል፤ የጅምላ ወሬዎችና ውሳኔዎች፣ ጭፍን ጥላቻዎችና ስሜታዊ ጉዳዮች የበለጠ ጐልተዋል፡፡ ሥርአቶቹ፣ የህዝቡን አላዋቂነትና ስንፍና ሲተቹ፣ ህዝቡ ደግሞ የሥርዓአቶቹን ፈላጭ ቆራጭነት ሲያሙ ይሰማል፡፡ ዛሬም ግን፣ በሥርዓቶቹ ውስጥ ያለፉ አስተዳዳሪዎችም ሆኑ ተዳዳሪዎች፣ ለትውልድ አስተማሪ የሆነ ፖለቲካዊ የህይወት ልምዶችን ሀገራዊ ቅርፅ አሲዘው በሀቅ ሲያካፍሉ አይታዩም፡፡ የዛሬው ትውልድም ከጥላቻና ከሃሜት የዘለለ ገቢራዋ ህይወት ሳይቀስም፣ ከአሁኑ የመንግሥት ሥርዓት ጋር መጓዝ ጀምሯል፡፡

አሁን ባለው የመንግሥት ሥርዓት ጠቅላይ ማኒስትር መለስ፣ ለድርጅቶቹም (ለህውሐት እና ኢህአዴግ) ሆነ ለመንግሥትና ህዝብ ብዙ ነገር እንደሰሩ እየተመሰከረላቸው ነው፡፡ በለጋ የወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ያመኑበትን የፖለቲካ አቅጣጫ አመላክተው፣ በሞቀ ቤት ሳይሆን በተቃጠለ ጫካ በጥይት አረር ተፈትነው ዓላማቸውን አሳክተው፣ እስከመጨረሻ “አንድ ግራም ጉልበት” እስኪቀራቸው እየሰሩ ያለፉ መሆናቸው “ታላቅ መሪ” ቢያሰኛቸው አይበዛባቸውም፡፡

ከዓላማቸውና ከርዕያቸው ጋር ልዩነት ያለው ጤነኛ ዜጋ፣ ህዝባዊ ማዕበል በሚንጠው፣ ለማንም ግራ በሚያጋባ የፖለቲካ ቅኔ ካልተጠመቀ፣ በሀበሻ የምቀኝነት ልማድና ጭፍን ጥላቻ ካልታጠረ በቀር፣ የአቶ መለስን የዓላማ ፅናትና ትጉህ ሠራተኛነት ሊክድ አይችልም፡፡ የሰውዬውን ታሪክ ሰሪነት ሊናገር ይገባል፤ ይህን ለመመስከር ደግሞ፣ እስትንፋሳቸው እስኪቋረጥ መጠበቅ አያስፈልግም ነበር፡፡

ከህውሃት እና/ወይም ከኢህአዴግ የተገነጠሉ አንዳንድ ታጋዮችም ሆኑ ሌሎች ተቃዋሚዎች፣ ዛሬ ስለ አቶ መለስ ብቃትና ጠንካራ ሠራተኝነት ማንም ሳይጠይቃቸው ጭምር ከመቀባጠር፣ በህይወት እያሉ ቢመሰክሩላቸው የስሜት ማዕበል ካንሳፈፋቸው ተራ ዜጐች በተለዩ ነበር፡፡

ከጭፍን ስሜታዊ የፖለቲካ ጐርፋቸው ወጥተው የአቶ መለስን ጠንካራና ደካማ ጐን በሀቅ መስክረው ቢሆን፣ ትርፉ ለሀገር ነበር፡፡ እነዚህ አንዳንድ አልኩ ባይ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የአንድን መሪ ጥንካሬ ለመመስከር ህልፈተ ህይወቱን መጠበቅ ለምን አስፈለጋቸው? ከማዕበሉስ በምን ይለያሉ!? በርግጥ ብዙዎቹ፣ በቅኔያዊ የፖለቲካ ጨዋታቸው ከፍነውም ቢሆን፣  ሚዛናዊ የሆነ አስተያየት ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡

ቀደም ሲል በወፍ በረር በሦስቱ ሥርዓቶች የረበበው ሀገረሰባዊው የመሪና የተመሪ ግንኙነታችን ጥልቅ ጥናት የሚሻው እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ ከፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን በፊት ማህበራዊ የአስተሳሰብና የአሰራር ልማዳችን ሊመረመርና ሀገራዊ የለውጥ አቅጣጫ ሊነደፍለት የሚገባ ይመስላል፡፡ የነቁ የፖለቲካ መሪዎች ካሉ፣ የህዝቡን ማህበራዊ የኑሮ ዘልማድና አስተሳሰብ ማቃናት ይቻላል ሊባል ይችላል፡፡ ልክ ነው የነቁ ጥቂት ፖለቲከኞች ሀገራዊ ለውጥ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል፡፡

በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ከዥጉርጉር ባህልና ቋንቋችን የሚቀዳው ዥጉርጉር ማንነታችን፣ ያልሰከነና ያልጠራ የተዥጐረጐረ ህዝባዊ ባህሪ ያጋባብን ይመስላል፡፡ የፖለቲካ መሪዎቻችንም ከዚህ ማህበረ ባህላዊ የኑሮ ስርአት አብራክ ውስጥ የተፈጠሩ ስለሆኑ ከተጠያቂያዊ የአስተሳሰብና የአሰራር ልማድ ይልቅ፣ የህዝባዊ ማዕበል ስሜት የሚንጣቸው ቅርብ አሳቢ ፖለቲከኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡

ፖለቲከኞቻችን ከህይወት ልምዳቸው እና ከንባብ ገጠመኛቸው ባገኙት የበሠለ የፖለቲካ ርእዮተዓለም እየተገሩ ጥሩ የሀገር መሪ ለመሆን ቢጥሩ እንኳ፣ በጣት ከሚቆጠሩት ስልጡን ፖለቲከኞች (መሪዎች) ይልቅ፣ በቅኔ የኑሮ ዘልማድ የገነገነ፣ መያዢያ መጨበጫ በሌለው ግንፍል ስሜት የሚናጠው ዜጋ በመጠንም በአይነትም ስለሚበልጥ፣ የሚፈለገው ሀገራዊ ለውጥ በቀላሉ ሊመጣ እንደማይችል ቢያንስ ልንጠረጥር ይገባልና በተለይ ለአመነበት ጉዳይ ቶሎ የማይፈላ ወይም ቶሎ የማይቀዘቅዝ ህዝብ በአሉባልታና በወሬ ብቻ ቶሎ ለብ ስለሚል፣ ለመንግስትም ለሀገርም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ስለዚህ፣ መሪ ርዕይ አንግቦ ለለውጥ መትጋቱ ብቻ የትም አያደርስም፤ ርዕዩን መርምሮ ለተግባራዊነቱ ቀናኢ የሆነ ስልጡን ትውልድ (ህዝብ) ካልተፈጠረ፡፡

በተለይ ከሰሞኑ ሀገራዊ ሀዘናችን ጀርባ እየተሰማኝ ያለው ነገር፣ ከመንግስታዊ፣ ከፖለቲካዊ ለውጦች በፊት ማህበረሰባዊ ለውጦች ግድ የሚሉን መሰለኝ፡፡

ህዝብ፣ በስሜት ከሚናጥባቸው ከየሥርዓተ መንግስቱ (የንጉሡን የደርግንም ልብ ይሏል) ህዝባዊ ማዕበሎች ጀርባ፣ የህብረተሰቡ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ኋላቀርና ፍዝ መሆኑ ጐላ የሚል እየመሰለኝ ነው፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ “መሪ ያጣ ህዝብ ወይስ ህዝብ ያጣ መሪ” የሚሉት ፅንፍ ላይ የሚቆሙ ሃሳቦችን ማንሳትም የሚቻል መስሎኛል፡

በሁለቱ ፅንፎች መካከል ብዙ ክፍልፋይ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያስቡ መሪዎች እና/ወይም ህዝቦች ካልተፈጠሩ፣ የዘልማድ አስተሳሰባችንም ሆነ እኛ እራሳችን ቅኔ እንደሆንን መቀጠላችን የሚቀር አይመስልም፡፡መሪ ህዝቡን ግራ ሳያጋባ፣ ህዝብም ለመሪው ግራ ሳይሆን… ግልፅና ቀናኢ መስተጋብር ለመፍጠር ካልተሞከረ፤ መሪን፣ በቁሙ እያብጠለጠሉ፣ መልካም ተግባሩን በአሉባልታና በጭፍን ጥላቻ እያመከኑ፣ ህይወቱ ሲያልፍ ከንቱ ውዳሴ ማዥጐድጐዱ አዲስ ቅኔያዊ የፖለቲካ ባህላችን እንዳይሆን ያሰጋል፡፡አቶ መለስ፣ አላማቸውን ዳር ለማድረስ የተፋለሙ ጥንቁቅ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ለመመስከር፣ ወደ መቃብር መውረዳቸውን መጠበቅ አይገባም፤ ዓላማቸውን ሳይመረምር የሚያደንቃቸውም የሚጠላቸውም የማዕበል ተንሣፋፊ ሁሉ ለራሱም ለሀገርም አይጠቅምም፤ አቶ መለስ ለዓላማቸው ኖረዋል፤ እኛ በስሜት በሚናጠው ግራ አጋቢ ባህሪያችን እናልቅስ፤ በተለይ በስግብግብና ተጠራጣሪ የንግድ ሥርአታችን ጭምር እያሻቀበ ላለው የኑሮ ውድነት፣ ከምር እናልቅስ! አንድ ኩንታል ጤፍ 2ሺ ብር ለማለት ቅንጣት ያልተሳቀቁ ስግብግብ ነጋዴዎች በእነዚህ የሀዘን ቀናት አጋጥመውኛል፡፡

 

 

Read 5675 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:05