Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:42

“ስለመለስ ሳስብ ከውስጤ የማይጠፋው ፈገግታው ነው” አረጋሽ አዳነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመለስን የመሞት ዜና የሠማሁት በሬዲዮ ነው፡፡ ዜናው ደስ የማይልና እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ መሞቱን ስሰማ ከቁጥጥር ውጭ ሆኜ ነበር፡፡ ቢታመምም ተሽሎት ይመለሳል የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ በአንድ ጊዜ ሁኔታዎች እንዲህ መለዋወጣቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ከእኔ ጋር በትግሉ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ማለት ይቻላል አብረን ነበርን፡፡ ብዙ የመከራ ወቅቶችን አብረን አሳልፈናል፡፡ መለስ ትልቅ የስራ መንፈስ ያለው ብቻ ሳይሆን ጨዋታ እና ቀልድ አዋቂም ነበር፡፡ ያንን ጊዜ እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ አርፌ አንዳንድ ነገሮችን እሠራለሁ ባለበት ሰአት እንዲህ መሆኑ ቅስም የሚሠብር ነው፡፡

ህወሓት ውስጥ ክፍፍል በተፈጠረበት ወቅት የተለየ ሃሳብ ስለነበረኝ በሌላ መልኩ  መታገል ይቻላል ብዬ አምኜበት ነው ከህወሓት የወጣሁት፡፡ ይህንን ሳደርግ ደግሞ ምንም አይነት የግል ጥላቻ ኖሮ ሳይሆን በልዩነት መታገል ይቻላል ብዬ ነው፡፡ ባለፈው አገራዊ ምርጫም በአንድ የምርጫ ጣቢያ እሱ ኢህአዴግ/ህወሓትን ወክሎ፤ እኔ በተቃዋሚ በኩል ሆኜ ብወዳደር ህዝቡ ኢህአዴግን ከፈለገውና ከመረጠው ይቀጥላል፤ ካልሆነ አማራጭ ያገኛል ብዬ ነው፡፡ እንጂ የግል ችግር ኖሮብኝ አይደለም፡፡

መለስን በአካል ያየሁት በ1993 በክፍፍሉ ወቅት ነው፤ ከዛ በኋላ በተለያዩ ሚዲያዎች እንጂ በአካል አላየሁትም፡፡

ይህ ጉዳይ በጣም ያሳዝናነኛል፡፡ የደርግ አውሮፕላኖች ከላይ በቦምብ ሲደበድቡን አብረን የመከራ ጊዜ ያሳለፍን ሰዎች እንዲህ መለያየት አልነበረብንም፡፡

ለህዝቡ እና ለቤተሰቡ መጽናናትን ይስጥ፤ ኢህአዴግም አብሮ የመስራት እድል እንዲፈጠር እንዲያደርግ እጠይቃለሁ፡፡ ለመለስ ሞትን መመኘት በባህልም ሆነ በሞራል አይን ሲታይ አግባብ አይደለም፡፡

ስለ መለስ ሳስብ ዘላለሜን ከውስጤ የማይጠፋ ፈገግታው ነው፡፡ ሜዳ ላይ እያለን በዛ ሁሉ ውጥረት መሀል የሳቅ እና የቀልድ ምንጭ ነበር፡፡

 

 

Read 2896 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:47