Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 01 September 2012 10:39

የሀዘን መግለጫና አጠቃላይ ሀገራዊ ምልከታ ከሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ሊቀመንበር)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ መለስ ዜናዊ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ የትጥቅ ትግሉን በመቀላቀል በሂደቱም ውስጥ ትልቅ ግለሰባዊና ድርጅታዊ አቅም መፍጠር የቻሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ነበሩ፡፡ በግሌ እንደ አብዛኛው  ዜጋ ዜና እረፍታቸው እጅግ ያሳዘነኝ ክስትት ነበር፡፡  ዜና ህልፈታቸው በተለይ ለቤተሰቦቻቸው መሪርና አሳዛኝ፣ ለመሪ ድርጅታቸው  ከማሳዘንም በላይ እጅግ አሳሳቢ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚህ አኳያ ህልፈተ ህይወታቸውን  ተከትሎ  በቤተሰቦቻቸውና  በወዳጆቻቸው  ዘንድ ለተከሰተው ሃዘን መጽናናትን፣ ለሳቸው መንፈሳዊ ምህረትንና ድህነትን እመኛለሁ፡፡

በፓርቲያችን(ኢዴፓ) ውስጥ በጋራ የምናራምደውና በግሌ አጥብቄ የማምንበት የሊብራል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  የሚከተሉት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም  እጅግ የተራራቁና የማይዛመዱ ቢሆንም አቶ መለስ እንደ ሁነኛ ዜጋ (Senior Citizen) በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የአስተሳሰብ  ንቅናቄን (Movement) የፈጠሩ፣  ከእምነታቸው የመነጨ አዳዲስ ራዕዮችን ይዘው የተነሱና  ይህንኑ አቋማቸውንም በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና አስደግፈው የሚከራከሩ  ጠቅላይ ሚኒስቴር ነበሩ፡፡ ከዚህ አኳያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በተለይ  ዜና እረፍታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ንቅናቄ ዙርያ ከግል ፍልስፍናቸው ከመነጨም ሆነ በፓርቲያቸው ላይ  ከነበራቸው ተጽእኖና  አስተዋጽኦ አኳያ የራሳቸው የሆነ አንድ አይነት ክፍተት ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ  ዜናዊ ዜና እረፍትን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ በኢህአዴግ በኩል የሚሰጡት መግለጫዎች፣ ሁሉ ነገር እንደነበረና እንዳለ እንደሚቀጥሉ  የሚገልፁ ናቸው፡፡  የኢህአዴግ ፍላጎት ይህ ቢሆንም እውነታው ጋር ለመድረስ ግን ብዙ የቤት ስራ እንደሚጠይቃቸው አምናለሁ፡፡ ለዚህም በቂ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ የስልጣን ሽግግሩም ቢሆን ቅድሚያ ሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በተላበሰ መልኩ፣ ከብሄርና ከጎሳ ግጭት እጅግ ልቆ በመገኘት፣ ከስልጣንና ከፓርቲ የውስጥ ሽኩቻ በጸዳ መልኩ በተለይም የሁሉንም ኢትዮጵያውያን  የጋራ ጥቅምና የሃራችንን ሉአላዊነት ባማከለና ባረጋገጠ መንገድ መፈጸም ይኖርበታል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡

በእኔ እምነት ለኢትየጵያ ሕዝብ ድንገተኛ የሆነ የስልጣን ሽግግር አዲስ አይደለም፡፡ የአጼ ሚኒሊክ፣ የአጼ የሃይለስላሴም ሆነ የደርግ ስርዓት ከሞላ ጎደል ያልተጠበቁና ድንገተኝ የስልጣን ሽግግር ውጤቶች ናቸው፡፡ እስካሁን አለመረጋጋትና ትርምስ መገለጫችን ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬም ሌላ ቀን እንደመሆኑ መጠን፣ ከስጋትም ሆነ ከስግብግብነት በመነጨ የግለኝነት ዝንባሌ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊከሰት የሚችለው የአቅርቦት መመናመን፣ የግብይት ስርዓት መዛባት፣ የኢንቨስትመት መዳከም፣ የግል ሃብትን በተለያየ መንገድ የማሸሽ ዝንባሌ ከመጀመሩና ማጣፊያው ከማጠሩ በፊት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ስጋት የማይነገረውን የሃገርን ደህንነትና ሉአላዊነት  የማስጠበቅና ጥቃትን ለመከላከል የሚስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግን ሳይጨምር ነው፡፡

በመጨረሻም ላስተላልፍ የምፈልገው መልዕክት አለኝ፡፡ እያንዳንዱ ታሪካዊ ዳራ የራሱ ወሳኝ ክስትት (Turning Point) አለው፡፡ ይህ ወሳኝ ክስትት ጥሎ የሚያልፈው አሳዘኝ ወይም  አስደሳች ገጽታ እንደተጨባጭ ሁኔታው የሚለያይ ቢሆንም  ከሂደቱ መማርና የሃገርን ልዕልና በማስጠበቅ  የሕዝብን ሕልውና በተሻለ ደረጃ ማስቀጠል የማንኛውም መንግስት ዓይነተኛ ሚና መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የመንግስት ሕጋዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ በሁላችንም ዘንድ  ማለትም ገዢውም ሆነ በስደትም ሆነ በሃገር ውስጥ የምንገኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መደማመጥ፣ እውቅና መስጠት፣ ይቅር ለመባባል መዘጋጀት፣ ያለፈውን በመርሳትና ወደፊት ለማሰብ ታጥቆ መነሳት የሚጠይቀን ጊዜ ላይ እንገኛለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምንም ያህል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ወይም የፍልስፍናና የአሰራር ክፍተት ቢኖረንም የሃገራችንንና የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ጥቅም  ግንባር ቀደም አላማችን ካደረግን፣ የርዕዮተ ዓለምና የፍልስፍና እንዲሁም የአሰራር  ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በመተባበር፣ ጠንካራ ሃገርና ሕዝብ ለመፍጠር ዛሬም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ጊዜው ሳይረፍድ እንጠቀምበት፡፡ ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንመለስ።

 

 

Read 1397 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:42

Latest from